Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የማለዳ ወግ …የተዘጋውን የአረብ ሀገራት የኮንትራት ሰራተኛ አቅርቦትን ለመክፈት የወጣው ረቂቅ ! (ነቢዩ ሲራክ)

$
0
0
* ስለ ሰራተኞች መብት ጥበቃ መነሳቱ አልተዘገበም
* በተወያይ ኤጀንሲዎች በኩል ግን ረቂቁ ውዝግብ አስነስቷል
* ከዚህ ቀደም ያለ በኮንትራት ለተበተኑትስ ዜጎችስ ምን ታስቧል ?Nebiyu Sirak አዲሱን መረጃ ያገኘሁት ሃገር ቤት ከሚታተመው ከአድማስ ጋዜጣ ላይ ነው ፣ እንዲህ ይላል ” ወደ አረብ አገራት የሚሄዱ ሰራተኞች ላይ የሚደርሰውን ችግርና እንግልት ለማስቀረት በሚል ከአንድ ዓመት በላይ ተቋርጦ የቆየውን አሰራር ለማስጀመርና ለመቆጣጠር የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ውዝግብ አስነሳ፡፡ ”  … ወረድ ብለን ዝርዝር መረጃውን ስንቃኝ በዋናነት መታየት ያለበት አንኳሩ የሰራተኞች ይዞታና የመብት ጥበቃ ጉዳይ በዘገባው ላይ አልተካተተም። ይህም ይሁን ብለን ዝርዝሩን ስንቃኝ ከዚህ ቀደም በነጻ ያገኙትን ቪዛ በደላላ በየገጠር ከተሞች ሰብስበው እህቶቻችንን ከመላካቸው አስቀድሞ ፈቃድ ሲያወጡ ለመንግስት ያቀረቡት የገንዘብ መያዣ በደል ደርሶባቸው ለሚመለሱ ዜጎች ካሳ ሲከፈል አላየንም አልሰማንም ። ከሁሉም የሚያመው ሰራተኞች ሲላኩ ለሚደርስባቸው አደጋ  ኢንሹራን ሳይቀር ገንዘብ አስከፍለው የላኳቸው ቢሆንም በተበደሉበት በደል ተፈጽሞባቸው ሃገር ቤት ሲገቡ በከፈሉት ኢንሹራን ተጠቃሚ አይደረጉም። የሰራተኞችን መብት አሟልተው ስራ ለማሰማራት እንግዲህ ውል ገብተው በወሰዱት ፈቃድ ልክ ውል ሲያፈርሱ ህግ አስፈጻሚ አካላት በኩል በዝምታ የታለፉት የእኛ ስራና ሰራተኛ አገናኝ ደላላ “ኤጀንሲዎች ”  በአዲሱ ረቂቅ ያነሱት ተቃውሞ ” ቅድመ ሁኔታዎች አያሰሩንም” የሚል መሆኑን እያመመኝ አነበብኩት!  እንቀጥል …በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ሰራተኞችን የሚልኩ ኤጀንሲዎች ያሰሙት ቅሬታ የስራ ፈቃዱን ለማግኘት ” ከአንድ ሚሊዮን እስከ አምስት ሚሊዮን ብር ካፒታል ሊኖረው ይገባል ” መባሉና “ለሰራተኛው መብትና ደህንነት ዋስትና ማስከበሪያ የሚውል 100 ሺህ ዶላር ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ በዝግ ሂሳብ የማስቀመጥ ግዴታ አለበት ” መባሉ ነው ። ጋዜጣው ኤጀንሲዎች ለስራ ወደ ውጭ አገር የላኳቸውን ሰራተኞች በሚሔዱባቸው ሃገራት ላሉ ኢንባሲና ቆንስል መስሪያ ቤቶች በ15 ቀናት እንደሚያስታውቁ ይጠቁማል ።

የኤጀንሲዎች የአዞ እንባ …

ኤጀንሲዎች  ይህ መሰሉ ረቂቅ ህግ እንደማያሰራቸው እንዲያውም “በውጭ ሃገር ስራ ለማሰማራት የሚፈልጉትን ዜጎች እድል ያጠባል ፣ ህገ ወጥነትን የሚያባብስ ነው ” ሲሉ ህመሙን የመከረኞቹ ህመም በማድረግ የአዞ እንባ የማንባት አይነት ቅሬታ መሰማታቸውን በአድማስ ጋዜጣ ዘገባ ተጠቅሷል ። እንደ ጋዜጣው ዘገባ ኤጀንሲዎች ረቂቁን ህግ በወይይቱ የተቃወሙበትና ያልደገፉበት ዋንኛ ምክንያታቸው የተደነገገውን ቅድመ ሁኔታ ለማሟላት እንደሚከብድ መሆኑንም ጋዜጣው ያስረዳል ።

ዳግም እንዳናነባ …!

ከወራት በፊት ጀምሮ “ወደ አረብ ሃገራት የተዘጋው የኮንትራት ቪዛ ይከፈታል !” የሚል መረጃ በሰፊው በመሰራጨት ላይ እንዳለ በሹክሹክታ ከሰማን ወዲህ ረቂቁ ለውይይት መቅረቡን ይህው ሰማን ። ከዚሁ ጋር ባያያዝኩት የ EBC TV ዘገባ እንደ ምትመለከቱት የዜና ዘገባ ከወራት በፊት የተባበሩት ኢምሬትን የጎበኙት ፕሬዘደንት ዶር ሙላትና የኢምሬት አምባሳድር አቶ አብድልቃድር የተዘጋውን የአረብ መንገድ መቸ እንደሚከፈት ተጠይቀው ሲመልሱ  ህግ ሆነ መመሪያ እየወጣ መሆኑን ጠቁመው ነበር ። ከዚህ ጋር በማያያዝ በሰጡት መግለጫም ከአሁን ቀደም  ከአረብ ሃገራት ጋር ያልነበረው የሁለትዮሽ ስምምነት በቀጣይ መከወን እንዳለበት ገልጸውም ነበር ። ይህ መግለጫ በተነገረ ማግስት በቪዛው ንግድ ተሰማርተው ከገጠር እስከ ከተማ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ እህቶቻችን ለሳውዲ ” ገበያ”  ያቀረቡት ባለ ኤጀንሲ ደላሎች ጅዳና ሪያድ መምጣት መጀመራቸው መረጃ ቢጤ አቅርቤም ነበር  ።  አሁን በውስጥ አዋቂዎች የሰማነው ፣ የተባለው ሁሉ  እውን እየሆነ ፣ እውነቱ እየጠራ የሄደ ይመስላል  !

ከዚህ ቀደም በሁለት ሃገራት መካከል ስምምነትና በቂ ዝግጅት ሳይደረግ በሳውዲ ብቻ ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጥ ዜጋ  የህግ ሽፋን ህጋዊ ፈቃድ ባላቸው ኤጀንሲዎች በየገጠር ከተሞች ተግዘው በተለያዩ ከተሞች ተበትነዋል። ዛሬ በኮንትራት የመጡት ” ያሉበትን ይዞታ እንዲህ ነው” ብሎ መረጃ መስጠት ቀርቶ ፣ የትና በምን ሁኔታ እንደሚገኙ የሚያውቁ ኤጀንሲዎችም ሆነየ የመንግስት ተወካዮች የሉንም የምለው በእርግጠኝነት ነው ።  በተደጋጋሚ ከሚደርሱኝ መረጃዎች መረዳት እንደ ቻልኩት በአሁኑ ሰዓት መግቢያ መውጫው ጠፍቶባቸው ፣ በደልን እያስተናገዱ የሚንገላቱት በርካታ እህቶች በየቤቱ እንዳሉ አውቃለሁ።  በዚህ መሰሉ የተወሳሰበ ችግር ዜጎች እየተሰቃዩ ፣  መብታቸው የሚያስጠበቅ ስራ እየተሰራ በሌለበት ሁኔታ ሌላ እንባ ልናነባ የተቃረብን ይመስላል !  የኮንትራት ሰራተኞችን አበሳ ብዙ ነው፣  የሚሰራው ታስቦና ተጠንቶ ስላልሆነ ፣ መብታችን የሚያስጠበቅልን ስለጠፋ ተዋርደናል ። አሁን ድረስ በዚህ ዙሪያ ያገባናል ብለን  ስንጽፍና ስንናገረው እንደ ተቃዋሚ እየታየንም ቢሆን ግፍ ሰቆቃና ስቃዩን ሊያሰለች በሚችል ስፋትና ጥልቀት ጽፈነዋል ፣ ተናግረናል!  ሰሚ ግን የለም !

በህግ መመሪያ የተቀመጠው የመንግስት ዲፕላማቶች ቀዳሚ ስራ ባሉበት ሃገር የሚገኙ ህጋዊም ሆኑ ህገ ወጥ ዜጎችን ሰብአዊ መብት ረገጣ እንዳይደርስባቸው መከላከል ቢሆንም ይህ እተሰራበት አይደለም።  የህገ ወጦችን ቀርቶ በኮንትራት ሰራተኛና አሰሪ ስምምነት የመጡ ዜጎችን  መብት ማስከበር አልቻሉም ! የቪዛ ውል ማስፈጸሚያ ገንዘብ እየሰበሰቡ ባጸደቁት የኮንትራት የስራ ውል ላይ የተጻፉት ስምምነቶች የዜጎች  ይዞታ የመከታተልና የማስፈጸም ሃላፊነትን ሲወጡ አላየንም !እውነቱ ይህ በመሆኑ ሰብዕናችን መርከስ ይዟል ፣  ግፍ እየተፈጸብን ነው ። በዚህ ሁኔታ ረቂቁ ጸድቆና በተግባር ውሎ ዳግም እንዳናነባ ያሰጋል  !
ግልድ መሆን ያለበት ነባራዊው እውነታ …የረቂቁ ጉዳይ በእንዲህ እንዳለ ከኢትዮጵያ መንግስት አስቀድሞ ከኢትዮጵየ የኮንትራት ሰራተኞች እንዳይመጡ ያገደው የሳውዲ መንግስት እገዳውን እስካሁን አላነሳም። በዚህ ላይ መንግስት ከአረብ ሃገራት በኩል እግዱ ተነስቶ ሰራተኞች እንዲያቀርብ ጥያቄ እየቀረበለት መሆኑን ደጋግመን ሰምተናል ። ከአረቦች በኩል ግን የምንሰማው ለየቅል ነው !ወደ ረቂቁ ስንመለስ ፣  ብዙዎቻችን የሚያሳስበን በማህበራዊና ሰራተኛ ሚኒስትር ለኤጀንሲዊች ውይይት የቀረበው ረቂቅ ህግ በሰራተኞች ይዞታና መብት ጥበቃ ዙሪያ የተነሳ ጉዳይ አለመኖሩም ነው ። በአድማስ ጋዜጣ ጋዜጣ ዘገባ በማህበራዊና ሰራተኛ ሚኒስትር በቀረበው ረቂቅ ኤጀንሲዎች መወያየታቸውን ሲያስረዳ ፍቃድ ለመውሰድ የተጣለባቸውን ከፍተኛ ገንዘብ የማስያዝ ፣ ሰለሰራተኞች እድሜ የትምህርት ደረጃ ገደብ እና ሰራተኞችን በሚሄዱበት ሃገር ኢንባሲና ቆንሰል መ/ቤት በ 15 ቀን ውስጥ ከማስመዝገብ ቅድመ ሁኔታ ያለፈ አለመወያየታቸውን የቀረበው ዘገባ ያስረዳል ።

በረቂቁ ላይ ሰራተኞች ቢያንስ እስከ ስምንተኛ ክፍል በላይ የሆኑት ብቻ እንደሚያካትት ከመጠቆሙ ባለፈ ሰራተኞች ማግኘት ስላለባቸው በቂ ስልጠናና ተዛማጅ ቅድመ ዝግጅት በቀረበው ረቂቅ ቀርቦ ለውይይት አለመደረጉ ያሳስባል።  ከዚህ ቀደም ድህነትና የኑሮ ውድነቱን ተከትሎ በልጆቻቸው ህይወታቸውን ለመለወጥ የቋመጡ ወላጆች በደላሎች ቀቢጸ ተስፋ ተታልለውና የተሳሳተ የእድሜና የትምህርት መረጃና  የመጓጓዣ ሰነድ አቅርበው ከሃገር እንዳይወጡ የተሰራውን ስራ የሚከላከል ዘዴ በረቂቁ አልቀረበም።  አለም አቀፍ የሰራተኛ ህግንና ሰብአዊ መብት ማስከበሪያ ድንጋጌዎችን ባገናዘበ መልኩ ሰራተኞች ስለሚከፈላቸው ክፍያ ፣ ስለጤና ፣ ስለ እረፍት ሰአታቸው እና ስለመሳሰሉት መሰረታዊ የኮንትራት ሰራተኞች አንገብጋቢ ጥያቄዎች  ውይይት ሳይደረግበት ስለኤጀንሲዎች ፈቃድ ማግኘት ቅድመ ሁኔታ ውይይት መቅረቡ ያሳስባል። በረቂቁ ውይይት ከመደረጉ አስቀድሞ ኤጀንሲዎች  ከዚህ በፊት ስላቨጋገሯቸው ዜጎች ነባራዊ ይዞታና ሁኔታ ፣ አድራሻና ያሉበትን ሁኔታ በዝርዝር መረጃ አላቀረቡም። በላኳቸው ሰራተኞች ላይ ለተፈመውና እየተፈጸመ ላለው በደል ተጠያቂው ሳይታወቅ ስለመጭው ፈቃድ አወጣጥ ከኤጀንሲዎች ጋር በረቂቁ ዙሪያና መስፈርት ዙሪያ  መወያየቱ ጠቃሚ አይመስለኝም።

የኮንትራት ሰራተኞች ጉዳይ ሲነሳ በየአረብ ሃገራት ያሉትን ኢንባሲና ቆንስል መስሪያ ቤቶች ለዜጎች በሚሰጡት ያልተሟላ ግልጋሎትና ያልሰመረ የመብት ማስጠበቅ ይጠቀሳል። ይህ ለምን ሆነ ሲባሉ የሰራተኛና በበጀት እጥረት እንዳለባቸው አዘውትረው ይናገራሉ። በዚህ  መንገድ አሁን ድረስ ስለሚንከላወሱት የኢንባሲና የቆንስል መ/ቤቶች ረቂቁ ምን ይላል ? የሚለው እንዳለ ሆኖ በሃገር ቤት ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ዝግጅት ፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት በረቂቁ ውይይት አልተነሳም።

…እልፍ አእላፍ የኮንትራት ሰራተኞች አሁን ያሉበት ይዞታ በውል ሳይመረመርና ሳይታወቅ እየተንገዋለለ ባለበት ሁኔታ  የተዘጋውን ለመክፈት ሂደት ግልጥልጥ አለማለት  ያስፈራል። ከዚህ በፊት በኮንትራት የገቡት ጉዳይ ገለል አድርጎ ስለ አዲሱ ህግና መመሪያ እንነጋገር መባል ችግሩን ያገዝፈዋል እንጅ አይቀርፈውም ። ይፋ መውጣት የጀመረው ረቂቁ ህግና በዚህ ጫፍ ያለው  ዝግጅት የተዳከመ አለያም የለም የሚባል አይነት መሆኑ አሁንም የዜጎችን አበሳ በቅርብ ለምንመለከተ ውን  ዜጎች ያሳስበናል። መፍትሄው በአረብ ሃገራት ያሉትን ዜጎች ጨምሮ  የሁሉም ባለድርሻ አካላት በረቂቁ ህግ ተሳትፎ ሊያደርጉበት ይገባል። በፈለገው መንገድም ይሁን በረቂቁ ህግና መመሪያ ዙሪያ ግልጽና ጥልቅ ውይይት ካልተደረገ አሁንም ዳግም እንደምናነባ ልብ  ያለው ልብ ይበል  !

ጄሮ ያለው ይስማ  !

ቸር ያሰማል  !

ነቢዩ ሲራክ
ህዳር 24 ቀን 2007 ዓም

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>