በቅርቡ በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ አካባቢ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ በአገራችን ውስጥ ስላለው ችግር መፍትሔ ለማምጣት ይጠቅማል በሚል በጠራው ውይይት ላይ ኢትዮጵያውያን ከአውሮጳ፣ ከአሜሪካና ከካናዳ ተጠራርተው በመምጣት በዓይነቱ ለየት ያለ ውይይት አድርገዋል፡፡ “ሰላም፣ ፍትሕ፣ ዕርቅና መከባበር የሰፈነበት ማኅበረሰብ ለመመሥረት” አንዳችን ስለሌላችን በመናገር ሳይሆን እርስበርስ ስለችግራችን መወያየት አለብን በሚል መሪ ሃሳብ ኢትዮጵያውያኑ ግልጽና በቅንነት ላይ የተመሰረተ ውይይት አካሂደዋል፡፡ “ከዘረኝነት ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ” የመስጠት አስፈላጊነትም በስፋት ውይይት የተደረገበት ጉዳይ ነበር፡፡
በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው ኤምባሲ የስብሰባው አካል እንዲሆን ለአምባሳደር ግርማ ብሩየንቅናቄው ዋና ዳይሬክተር ኦባንግ ሜቶ የላኩ ቢሆንም ከኤምባሲው በኩል የተሰጠ ምላሽም ሆነ በውክልና በስብሰባው ላይ የተገኘ አለመኖሩ በጋዜጣዊው መግለጫ ተወስቷል፡፡ የመግለጫው ሙሉ ቃል ከዚህ በታች ቀርቧል፡