Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የ“ምርጫ” ወግ እና የውይይት ማስታወቂያ –ተክለሚካኤል አበበ

$
0
0

ስለሂደት፤ ስለትእግስት፤

  • Election2007የዚህ ጽሁፍ ዓላማ፤ የአንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ መሪዎች፤ አሁድ ድሴምበር 28 ቀን ከሰአት በኋላ 2pm ላይ፤ በውጭ ለምንገኝ ኢትዮጵያውያን ያዘጋጁትን የስልክ ውይይት ማስተዋወቅ ነው። ይሁን እንጂ ማስታወቂያውን እርቃኑን ባሰፍረው፤ አይማርክም በሚል፤ አንዳንድ ተያያዥ ነገሮችን ላለብሰው ፈቀድኩ። መለመላውን ከሚቀርብ የስልክ ጉባኤ ማስታወቂያ ይልቅ፤ ትንሽ ውዝግብ የለበሰ ማስታወቂያ ቀልብ ይስባል፡፡
  • አንደኛው ልብስ፡ ሂደት የሚሉት ነገር ነው፡፡ ስለምርጫና ሰላማዊ ትግል ሳስብ አሁን አሁን የሚታየኝ ነገር፤ ሂደት የሚለው ሀሳብ ነው፡፡ ውዝግብ አንድ፤ ለኔ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ሰላማዊ ትግል የድሮውን የልደቱ አያሌውን መንገድ ተከትሎ ቢሆን ኖር፤ እስካሁን አሸንፈን ነበር፡፡ የዛሬ አስራ አምስት አመት አካባቢ፤ የኢዴፓ መሪዎች ይመስለኛል ሲናገሩ ያደመጥኩት፡፡ በየምርጫው አስር አስራአምስት፤ ሰላሳ አርባ ወንበሮች ብንይዝ፤ በሂደት፤ ባራት ባምስት ምርጫዎች አሸንፈን የመንግስት ስልጣን እንይዛለን የሚል ስሌትና ስልት ነበር፡፡ ያኔ በአንድ ምርጫ አሸንፈን ስልጣን እንይዛለን የሚል ቅዠት አልነበረም፡፡ አሁን አሁን ሳስበው ያንን መንገድ ተከትለን ቢሆን ኖሮ በ2012ቱ ምርጫ ስልጣን ልንይዝ እንችል ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ፤ እነብርሀኑ የልደቱን ትተው፤ የሀይሉ ሻውልን መንገድ ተከተሉ፤ አይወድቁ አወዳደቅ ወደቅን፡፡
  • በሂደትና በትእግስት ማመን አለብን፡፡ በተለይ እድሜያችን ሲገፋና ሽንፈት ሲደጋገምብን፤ የበለጠ በሂደትና በትእግስት ማመን አለብን፡፡ ይሄንን ትእግስትና ሂደት የሚል ቃል ለምን አነሳሁ? ምርጫ ምርጫ የሚሉ ሀይሎች የእምነታቸው መግፊያ ሀይል ሂደት የሚለው ቃል ይመስለኛልና ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች አሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትሀዊና ነጻ ምርጫ ለማድረግ እንደማይሞከርና፤ ኢህአዴግ በምርጫ ስልጣን እንደማይለቅ ለማሳየት የኤርምያስ ለገሰን ኤክስፐርቲዝ ሁሉ ሲጠቅሱ ተስተውለዋል፡፡ አሁን በማርያም፤ አንድነት መጪው ምርጫ ነጻ ምርጫ እንደማይሆን ያጣዋል? ጥያቄው፤ እንዲህ ያለ ፍትህ የጎደለው ምርጫ ውስጥ መሳተፍ ፋይዳው ምንድርነው? አንድነትንም ይሁን ሌሎች ፓርቲዎችን፤ የዚህ ሀሰተኛ ምርጫ ተባባሪ፤ የስርአቱም አዳማቂ አያደርጋቸውም ወይ፤ የሚለው ይመስለኛል፡፡
  • ጥያቄውን በማያዳግም መልኩ መመለስ ይከብዳል፡፡ አንዳንድ ነገሮች ጭራሹኑ መልስም ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ወይም ጊዜ ይመልሳቸዋል፡፡ እኔ እንደተረዳሁት ግን፤ አንድነትም ይሁን ሌሎች ያገርቤት ድርጅቶች፤ ምርጫውን እንደአንድ የትግል ግንባር የወሰዱት ይመስለኛል፡፡ እንደአንድ የትግል ግንባርም፤ አስቀድመን እጅ ከምንሰጥ፤ ትንሽ እንፋለምበት አይነት ነገር፡፡ አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ቀላሉን መንገድ ይመርጣሉ፡፡ ምርጫ እንሳተፍም ብሎ አኩርፎ መውጣት ቀላሉ መንገድ ነው፡፡ አንድነት ግን ያንን ቀላሉን እጅ አጣጥፎ የሚቀመጡበትን መንገድ አልመረጠም፡፡ በራሳቸው በኢህአዲጎች ሜዳ ትንሽ እንሞግታቸው ያለ ይመስለኛል፡፡ አንድነቶች ወደምርጫ የሚገቡት የምርጫውን ምርጫ አለመሆን ለማሳየት ይመስለኛል፡፡ ትግል ደግሞ ሂደት ነው፡፡ ተከታታይ ነው፡፡ አምና አይተነዋል ተብሎ ቁጭ አይባልም፡፡
  • የለም ምርጫው የተበላ እቁብ ነው፤ በዚህ ሂደት ውስጥ ገብተን አናጃኩምም ብለው የሚከራከሩትም ቢሆን መከራከሪያቸው ስሜት ይሰጣል፡፡ ችግር የሚፈጥረው፤ ሁሉም የራሱን መከራከሪያ እንደብቸኛው የተቀደሰ ሀሳብ፤ አንዱ አንዱን እንደእንቅፋት ቆጥሮ ጠለፋ የተጀመረ እንደሆነ ነው፡፡ በአንድነት በኩል እንደድርጅት ምርጫው ውስጥ መሳተፍ የለባችሁም የሚለውን ክርክር የሚመለከቱት በበጎ ነው፡፡ መሪዎቹ፤ በተቻለ መጠን ወደምርጫ የሚገቡበትን ምክንያት ለማስረዳት ይተጋሉ፡፡ በቅርበት እንደተረዳሁት፤ ይሄ በዚህ እሁድ ድሴምበር 28 ከሰዓት የተዘጋጀው የስልክ ውይይትም የዚሁ ሂደት አካል ነው፡፡
  • አንዳንድ በውች የሚኖሩ የአንድነት ደጋፊዎች ግን ምርጫ መግባትን እንደብልሀት የሚጠይቁትን ሁሉ የአንድነት ጠላት፤ የግንቦት ሰባት ወኪሎች አድርጎ የመፈረጅ አዝማሚያ ያሳያሉ፡፡ ለምሳሌ፤ ወዳጄ መሳይ መኮንን በዚህ ሳምንት፤ ምክንቶቹን ዘርዝሮ፤ ምርጫ መሳተፍ ሞኝነት ነው ብሎ ስለተሟገተ፤ አንዳንዶች የመሳይን አቋም የኢሳት አቋም፤ ኢሳትን ደግሞ የአንድነት ጠላት አድርገው ለመፈረጅ ሲጣደፉ አስተውያለሁ፡፡ ይሄ ስህተት ነው፡፡
  • አንደኛ፤ ያለፈው ልምድ፤ የአሁኑም የመንግስት አቋም እንደሚያሳየን ከሆነ፤ ምርጫው ፍትሀዊ እንደማይሆን ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ፤ ምርጫ መግባት ያዋጣል ብሎ የማሳመን ሸክም ያለው ምርጫ እንግባ የሚለው ወገን ላይ ነው፡፡ ሁለተኛ፤ በዚህ መገናኛ ብዙሀን ሁሉ በታፈኑበት ሰዓት ለአንድነት ደጋፊዎች ከኢሳት ጸብ መግጠም ብልህነት አይደለም፡፡ ከሚዲያ ጸብ ገጥሞ ያሸነፈ ማግኘትም ይከብዳል፡፡ የቀድሞ የቶሮንቶ ከንቲባ፤ ሮብ ፎርድ እና ወንድሙ ከሚዲያ ጸብ ገጠሙ፡፡ በመጨረሻም ከሚዲያ የገጠሙት ጸብ ለሽንፈታቸው ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ስለዚህ አንዳንድ የአንድነት ደጋፊዎች አንድነትን ከኢሳት ባያላትሙት መልካም ነው፡፡
  • ኢሳት የአንድነትን የምርጫ ማስታወቂያ ያለምንም ጥያቄ አንጠልጥሎ እንዲሄድ መጠበቅም ደካማነት ነው፡፡ በርግጥም ምርጫ መግባት የሚለው ሀሳብ በደንብ መፈተሽ፤ መተንተን፤ በክርክርም መዳበር አለበት፡፡ ያለቀለት መልካም ሀሳብ አድርገው የሚያስቡ የአንድነት ደጋፊዎች ካሉ ተሳስተዋል፡፡ የምርጫ መግባትን ትክክለኛነት የሚጠይቁትን ሁሉ የአንድነት ተቃዋሚዎች፤ የግንቦት ሰባት ደጋፊዎች አድርጎ ማየት ሰንካላ አተያይ ነው፡፡ አንዳንድ ደጋፊዎች ጠንቀኞች ናቸው፡፡ ከትርፋቸው ኪሳራቸው ይበዛል፡፡ ስለዚህ አንድነትና አመራሩ ከጠንቀኛ ደጋፊዎች መጠንቀቅ አለባቸው፡፡
  • ከልምድ እንዳየነው፤ አንድነትም ይሁን ሌሎች አገርቤት ያሉ ድርጅቶች በርትተው ስራቸውን ከሰሩ፤ ኢሳት ይዘግባል፡፡ የኢሳት ጉልበት አገርቤት ነው፡፡ የኢሳት ቅመም፤ አገርቤት የሚካሄድና የሚከሰት ክስተት ነው፡፡ የአንድነቶች ሃላፊነት ያንን ክስተት መፍጠር ነው፡፡ ለኢሳት ፍጆታ ሳይሆን ለራሳቸው አላማ መፈጸም፡፡ ለምሳሌ፤ አሁን በዚህ ሰዓት፤ አንድነቶች እንደሚሉትም ለምርጫው ዝግጁ ከሆኑ፤ ቢያንስ በዋና ዋና ከተሞቻቸው በእጩነት ያሰለፏቸውን ሰዎች ምስል፤ የትምህርት ደረጃ፤ ልምድ፤ ራእይ፤ በስብሰባ፤ በሰለልፍ፤ በኢሳትም ይሁን በሌላ ሚዲያ እያቀረቡ ትግሉንና ፕሮፓጋንዳውን ማጡዋጡዋፍ እንጂ፤ ከሚዲያ ጋር ጸብ መግጠም የለባቸውም፡፡ አንድነት የምርጫ አጀንዳውን ሁሉ ዛሬ ካላሳወቀ፤ ምን ይዞ ምርጫ ውስጥ እንደሚገባ አልገባንም፡፡ የጸረ ሽብር ህጉን እንቃወማለን የሚለው መፈክር የምርጫ አጀንዳ አይሆንም፡፡ የሆነ ሆኖ፤ የምርጫውም ይሁን የትግሉ ስልት ውይይት ይቀጥላል፡፡ እስከዚያው ግን፤ ሰዎች ባመኑበት እንዲጓዙ ነጻነታቸውን እንቀበል፡፡
  • በዚህ ዙር፤ የኔ አሰላለፍ ከአንድነት ሆኗል፡፡ ምክንያት፤ አንደኛ የዛሬ አምስት አመት፤ አረጋሽ አዳነ አድዋ ላይ እንድትሰለፍና ሟቹን አቶ መለስን እንድትፋለም ከጓደኞቼ ጋር ሆነን ትንሽ ገንዘብ ልከንላት ነበር፡፡ በምርጫው ባናሸንፍም፤ አቶ መለስ በህወት ተሸነፉና አድዋን በአካል ለቀቁልን፡፡ መንፈሳቸውና ውርሳቸው ግን አራትኪሎን አልለቀቀልንም፡፡ እስካሁን ባለውም ሁኔታ፤ በንጽጽር አንድነት ተጠናክሮ የሚወጣና የሳቸውን ውርስ ሊያጸዳ የሚችል ተፎካካሪ ድርጅት ይመስላል፡፡
  • በርግጥ የአንድነት አመራር ከሰማያዊ ሰዎች ጋር የሚያደርገውን እንካሰላንቲያ ማቆም አለበት፡፡ ይሄ ጠቅላላ ጉባኤን በሳምንት ዝግጅት ማካሄድን እንደስኬት የሚቆጥሩትን ነገርም መተው አለባቸው፡፡ ጠቅላላ ጉባኤን ያህል ነገር አስቀድሞ ታልሞ መካሄድ ሲገባው፤ ድንገት መደረጉ፤ ስልጣን ቢይዙም እንዲህ በድንገተኛ ስበሰባ ነው እንዴ የሚመሩን የሚለውን ጥያቄ ይፈጥራል፡፡ አንድነት፤ ከኢህአዴግ የተሸለ እንጂ፤ እንደኢህአዴግ መሆን የለበትም፡፡ የ250 ሚሊዮን ብር መንገድ ባስመረቀ ባመቱ፤ ለባቡር ስራ የሚያፈርሱ አይነት መንግስት አንፈልግም፡፡ የሆነ ሆኖ ግን፤ ሰማያዊንና ሌሎች እህት ድርጅቶችን አስተባብሮ መጓዝ ከቻለ፤ አንድነት በመጪዎቹ ወራት ጠንካራ ሆኖ የማይወጣበትና፤ በዚህኛው ዙር ባይሆን፤ በ2012ቱ ምርጫ አሸናፊ የማይሆንበት ምክንት የለም፡፡
  • ይሄ ጭላንጭል ተስፋም ስላለ አንድነትን እንደግፋለን፡፡ እንጂ የግንቦት ሰባትንና የአርበኞች ግንባርን ውህደት ስንጠብቅ አናረጅም፡፡ ከላይ ከመግቢያዬ እንደገለጽኩት፤ የአንድነት ሊቀመንበርና ካቢኔው፤ ከአንድነት የሰሜን አሜሪካ ድጋፍ ሰጪ ማህበር ጋር በመተባበር፤ በፓርቲው እንቅስቃሴዎች ዙሪያ የስልክ ጉባኤ አዘጋጅቷል፡፡ ውይይቱ የሚካሄደው፤ እሁድ ዲሴምበር 28, 2ዐ14 በ 2:00 PM Eastern ሲሆን፤ እርስዎም ተገኝተው የአንድነትን መልእክት እንዲያደምጡ ተጋብዘዋል፡፡ የመገናኛ/ውይይት መስመሩ 1 857 216 6700 ሲሆን Access code 478975፡፡ እንዲሁም፤ 712 775 7085 Access code 767490 ነው፡፡

ተክለሚካኤል አበበ፤ ቶሮንቶ፤ ካናዳ፤ ትህሳስ፤ 2007 (2014)


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>