Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ምክር እስከመቃብር  – (ከኣልፎ ሂያጁ ማስታወሻ የተቀነጨበ) –በእውቀቱ ሥዩም

$
0
0

እንደምነሽ ሸገር
እንደምነሽ ሸገር

Bewketu Seyoum – Hagere Mariam (Maryland) USA [Must Listen)
የቤት ኣከራየ የጋሽ ጣሰው ኣገር እየመጣሁ ነው፡፡ ወደ ኣዲስ ኣበባ እየመጣሁ ነው፡፡እናቶች ኣባቶች ልጆች ኦርጅናሎች ሰልቫጆች! እኔ ሳልመጣ ውጊያውን እንዳትጀምሩት ኣደራ፡፡ ኣጭርና ጣፋጭ ይሁን እንጂ በማንኛውም ትግል ላይ ለመሳተፍ ዝገጁ ነኝ፡፡የጥይት መከላከያ ቆብ ሹራብና ሱሪ እንዲሁም ፈንጅ የማይበትነው ጫማ ከተሰጠኝ ኣንድ ሻለቃ እመራለሁ፡፡ኣነሰ ከተባለ ኣንዲት ኮረብታ እቆጣጠራለሁ፡፡ በጦር ምህንድስና ላይ እሳተፋለሁ፡፡ ባሩድ ኣገነፋለሁ፡፡ የታንክ ጎማ እነፋለሁ፡፡በሰላሙ ቀን ለሞባይል፤ በቀውጢው ቀን ለሽጉጥ ማስቀመጫ የሚሆን ሰገባ እሰፋለሁ፡፡
ይሄም ኣላዋጣ ካለ የኤፍሬም ይሳቅን ቡድን የሚፎካከር ኣስታራቂ ቡድን ኣቋቁሜ” ኣንተም ተው ኣንተም ተው፤ ያስታረቅሁበትን ኪሴ ውስጥ ክተተው” የሚል ኣገልግሎት እሰጣለሁ፡፡ቃሌ ነው፡፡የተናገርኩት ከሚጠፋ በቅርቡ የገዛሁት ጋላክሲ ሙባይል ይጥፋ(በዝች ንግግር ውስጥ የተደበቀ ጉራ እንዳለ እናንተ ሳትሉኝ ኣውቀዋለሁ)
ገና ለገና ካሜሪካ ሊመጣነው በማለት ማጅራቴን ለመመታት እያሟሟቃችሁ ያላችሁ ዱርየዎች እንዲሁም ከዱላ የተረፈች ማጅራቴን በማሸት ትርፍ ለማጋበስ የተሰናዳችሁ ወጌሻዎች ተስፋ ቁረጡ ፡፡ ቤሳቢስትን የለኝም፡፡(ማጅራት መምታት ሲነሳ ፋሲል ደመወዝ ትዝ ኣለኝ፡፡እንኳን እግዜር ማረህ ልለው ብደውል ከዲሲ በርሮ ኣትላንታ እንደገባ ነገረኝ፡፡ለኮንሰርት ይሁን ለስልታዊ ማፈግፈግ ኣልነገረኝም፡፡ ወይ ኣበሳ!እኛ ኢትዮጵያውያንኮ ምስኪን ነን ፤ ኣገር በቀል- ዱላ ሸሽተን ስንሄድ የውጭ ኣገር ዱላ ይጠብቀናል፡፡
ኣሜሪካ ሁለት ወር ስቆይ ያተረፍኩት ነገር ቢኖር ግብዣና ምክር ነው፡፡ዲታው ቢራ ጋብዞ ወደ ኣገርቤት ይዣት የምመለስ ቦርጭ ያወጣልኛል፡፡ቺስታው ቦርጬ እንዴት እንደምቀንስ ይመክረኛል፡፡ኣሜሪካ ፍሪሽ የሆነ ሰው ኑሮው ምክር እስከመቃብር ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ወደ ኣሜሪካ ገንዘብ የተላከለት የመጀመርያው ሰው ሳልሆን እቀራለሁ?
ለምሳሌ ጺም ለመቆረጥ ኣስር ዶላር መከስከስ ነበረብኝ፡፡ ፈርዶብኝ ኣሜሪካ ስገባ ጺሜ ያለወትሮው ቶሎቶሎ ማደግ ጀመረ፡፡ኣዲኣበባ እያለሁ ጺም ኣልነበረኝም፡፡እንዲያውም” ይሄ ልጅ ጺሚ የሚባል ነገር የለውም ስልብ ነው እንዴ?” የሚል ኣሜት በመንደራችን ይናፈስ ነበር፡፡ስልብ ኣለመሆኔን ለማሳየት ኣንድ ሁለት ቀን መንገድ ዳር ሸንቻለሁ፡፡

እንደልማዴ ከቀናኝ የሚጋብዘኝ ከፈረደብኝ የሚመክረኝ ኣላጣም በማለት Fenton መንገድ ላይ ወደሚገኝ ያበሻ ምግብ ቤት ጎራ ኣልኩ፡፡ ኣንዱ መድረክ ላይ የሱዳን ዘፈን ይዘፍናል፡፡ከተስተናጋጆች ውስጥ ኣንድም የሚያዳምጠው የለም፡፡ሁሉም ሙባይሉ ላይ ኣቀርቅሯል፡፡የታደለው ከፍቅረኛው በቫይበር የተላከለትን የክንፈር ምስል እያየ በደስታ ይዋኛል ፡፡ያልታደለው”የትምርት ቤት ክፍያ እየደረሰብኝ ስለሆነ ቶሎ ላክልኝ እንጅ”የሚል ካገር ቤት የተላከ መልክት እያነበበ ተክዟል፡፡ ሌላው ግድግዳው ላይ በተንጠለጠለው ቲቪ ላይ የሚተላለፈውን ያሜሪካ እግርኳስ እየተመለከተ ምድር ጠቦታል፡፡ ያሜሪካ እግርኳስ ቢሏችሁ እንደ ዋናው እግርኳስ እንዳይ መስላችሁ፡፡ ኣንዱ ጠብደል ጥቁር ሙልሙል ኳስ ይዞ ይሮጣል፡፡ሌላው ኣሳድዶ ይደርስበትና ዘርጥጦ ይጥለዋል፡፡ ለኔ ይህ ጨዋታ ሳይሆን ህጋዊ እውቅና ያለው ኣምባጓሮ ነው፡፡በዚህ መሃል ዘፋኙ “ከ እኔ ጋ ናችሁ?” እያለ ኣስሬ ቢጣራም ማንም ተጉዳይ ኣልጣፈውም፡፡ ልምምድ ላይ ያለ ይመስል ለራሱ ዘፍኖ ወረደ ፡፡ስላሳዘነኝ ባንኮኒውን እንደመቋሚያ ተደግፌ በጥሞና ኣዳመጥሁት፡፡ድምጹ ከዛፍ ላይ ኣምፖል ያረግፋል፡፡ቢሆንም ዘፈኑን ኣለቅጥ ያስረዝመዋል፡፡የሱን የሱዳን ዘፈን ታግሶ መጨረስ ሱዳንን በእግር እንደማቋረጥ ነው፡፡

ጥግ ላይ ክበበው ገዳ ተቀምጧል፡፡ ወንበር ስቤ ኣጠገቡ ተሰየምሁ፡፡ ራት ይጋብዘኛል ብየ ስጠብቅ ከራት ጋር የተያያዘ ገጠመኝ ጋበዘኝ፡፡
ክበበው ገዳ ጎረምሳ እያለ የለቅሶ ቤት እራት ኣያመልጠው ነበር፡፡ እንድያውም እንዲያባላኝ እያለ ቃሪያ በኪሱ ይዞ መዞር ጀምሮ ነበር፡፡ ኣንድ ለቅሶ ላይ ታድያ እራት ሲቀርብ ክበበው ከቤቱ ይዞት የመጣውን ቃርያ ከኪሱ ኣውጥቶ ኮርሸም ሲያደርግ የተመለከተ የሰፈር ልጅ ወደ ኣስተናጋጆች እያጨበጨበ “እዚህ ጋ ቃርያ ኣልደረሰኝም” ብሎ ጮከ፡፡

ኣለፍ ብሎ፤ የጃንሆይ ኣምባሳደር ዘውዴ ረታና ያሬድ ጥበቡ ቁጭ ብለዋል፡፡ያሬድ ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ ሲሆን ዘውዴ የተንቀጠቀጠው ተራራ ነው፡፡ኣሁን ዲማሚቱና ተራራውም ባንድ ጠረጴዛ ዙርያ ተቀምው ሳያቸው ገረመኝ፡፡

ከማጅራቴ ኣካባቢ “ልትጽፍ ነው የመጣህ ኣይደል”የሚል ሹክሽክታ ሰማሁ፡፡ወይንሸት ናት፡፡ ባለፈው ኣመት ከባህል ቡድናችን ጋር ስትመጣ ኮከብ ድምጻዊ ነበረች፡፡ኣሁን እዚሁ ቀርታ ኮከብ ኣስተናጋጅ ሆናለች፡፡ኣፍንጫዋ ላይ የወርቅ ቡግር የመሰለ ሎቲ ለጥፋለች፡፡እዚህ ኣገር ሴቶች ሎቲ የሚያንጠለጥሉት ጆሮኣቸው ላይ ሳይሆን ኣፍንጫቸው ላይ ነው፡፡ ስለወይንሸት በሌላ ምእራፍ እተርካለሁ፡፡

በሩ ኣጠገብ ተኬን ኣየሁት፡፡ ተኬ በደርግ ዘመን ካይሮ ላይ ከጠፋው የብሄራዊ ቡድናችን ገንዘብ- ያዥ ነበር፡፡ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር ባደረገችው በግጥምያ ዋዜማ ላይ በረኛውን ጨምሮ ብዙ ተጫዋቾች ስለኮበለሉ እሱ የበረኛውን ቦታ ተክቶ ተሰልፏል፡፡ ከተቃራኒ ቡድን የተለጋች ኳስ ወደእሱ ኣቅጣጫ ስትመጣ በገንዘብ ቆጠራው ለምዶበት ጣቱን በምላሱ እያጣቀሰ ሲርበደበድ ፤ ኣስራ ሰባት ጎል ገበቶበታል፡፡ (ምንጭ፡ የይድነቃቸው ተሰማ ሪፖርት)ተኬ ጉዳዩ ሲነሳበት ያማርራል፤“ይሄ ውለታ ቢስ ህዝብ የገባብኝን ኣስራ ሰባት ጎል እንጂ ያዳንሁትን ሰባት መቶ ጎል ኣላሰበልኝም” ይላል፡፡ካገሩ ወጥቶ መቅረት ኣሳብ ፈጽሞ ኣልነበረውም፡፡ይሁን እንጅ ይህን ሽንፈት ይዞ ጓድ መንግስቱ ፊት መቆም የሚያመጣውን ነገር ኣስቦ በዛው” ነካው“፡፡

ኣሁን በሩ ኣጠገብ ቁጭ ብሎ ”ብሉ ሙን“ ቢራ ይጠጣል፡፡ የቢራ ጠርሙሱን በጥርሱ ከፍቶ ቆርኪውን ጠረጴዛ ልይ ተፋው፡፡ቢራ መክፈቻ ቢቀርብለትም ተጠቅሞበት ኣያውቅም፡፡እግዜር መንጋጋን የፈጠረው ሲርብህ ኣጥንት እንድትቆረጥምበት ሲጠማህ የቢራ ጠርሙስ እንድትከፍትበት ነው ይላል፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>