Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ህወሃቶች በደደቢት ለአርቲስቶቹ የነገሯቸው እና ያልነገሯቸው ታሪኮች ሁሉ የሚያሳዩት አሁንም ህወሓት ስለመንደሩ እንጂ ለኢትዮጵያ አለመቆሙን ነው

$
0
0

Agazi+Victim-1
ፎቶ -በ1997 ዓም በአዲስ አበባ በአጋዚ ጦር የተገደሉ ኢትዮጵያውያን

መንደርደርያ

ኢትዮጵያ በታሪክ የእርስ በርስ ጦርነትን እንደ ትልቅ ታሪክ የምትዘክር ሀገር ሆና አታውቅም።እንደዚያ ቢሆን ኖሮማ ዘመነ መሳፍንት የብዙ የእርስ በርስ ጦርነቶች ባለ ታሪክ ነበር።ሆኖም ግን የወቅቱ የሀገራችን መሪ ግዜያዊ ድል ሲያገኝ የእኔን ማሸነፍ የኢትዮጵያ ታሪክ አድርጉልኝ ሲል አልተሰማም።ጉዳዩ የእርስ በርስ ጦርነት ነዋ! በተቃራኒው ግን ኢትዮጵያ ለነፃነቷ እና ለአንድነቷ የሞቱላትን ከህወሓት በፊት የነበሩት የኢትዮጵያ መሪዎች ትልቅ ቦታ ሰጥተውት ኖረዋል።እነኝህ መሪዎች ከጣልያን ጋር የነበረውን ትንቅንቅ ዘከሩ እንጂ ለስልጣን የተደረጉ ውግያዎችን የኢትዮጵያ ትልቁ ታሪክ ነው ብለው አልተሟገቱም።ህወሓት ግን ያለፉትን ለኢትዮጵያ የሞቱትን እየነቀፈ እና እየወቀሰ ሲመቸው ደግሞ ለማደብዘዝ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ እየከፈተ ኢትዮጵያ የተፈጠረችው ደደቢት ላይ ነው መሰል ንግግር ሊያሰማን ይዳዳዋል።
ፖለቲከኞችን ማሳመን ያልቻለው ህወሓት ለአርቲስቶች ምን ነገራቸው?

ሰሞኑን አርቲስቶችን አሳፍሮ ደደቢት ላይ የከረመው የወያኔ አመራር ቡድን 150 ሚልዮን ብር ወጪ(ለፀጥታ ጥበቃ፣ትራንስፖርት፣ለሁሉም አርቲስቶች የቀን አበል፣የምሽት እራት እና ዳንስ ወዘተ) መውጣቱን የውስጥ አዋቂ ዘገባዎች ዘግበዋል።አርቲስቶቹም ድራማ ሲሰሩ ከርመዋል።ሰው ለሰው ድራማ በዋና አክተሩ ተወክሏል፣የህወሓት የዛሬ የአዲስ አበባ እና መቀሌ ህንፃ ባለቤቶች ሲደንሱ ታይተዋል።ለአርቲስቶቹ በእርስ በርስ ጦርነት ወቅት እንዴት ድልድይ እንደፈረሰ፣የቱ ጋር ትግራይን ለመገንጠል እንደተዶለተ፣የቱ ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ለሻብያ የምፅዋ ጦርነት የትግራይ ልጆች እንዲላኩ እንደተወሰነ፣የቱ ጋር ስለ ብሔር ብሔር በሚል ሽፋን የኢትዮጵያ ጉድ የሆኑትን ጉድ የብሔር ድርጅቶች ለመፈልፈል ህወሓት እንደዶለተች ተነገረ።

ለአርቲስቶቹ ከተናገሩት ውስጥ አቶ ስዩም መስፍን፣አቦይ ስብሐት እና ሳሞራ የኑስ እንዴት ኢህአፓን እና ኢድዮን እንዴት ከትግራይ እንዳስወጡ ተተረከ።አቦይ ስብሃትም በመሃል የሚያስቆማቸውን ሳል እየሳሉ ሲቀጥሉ እንዲህ አሉ ”የቀድሞዎቹ ተቃዋሚዎች ሁሉም የተሰገሰጉት የቀደመውን ስርዓት ለመመለስ የሚፈልጉ ነበሩ” ካሉ በኃላ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር የብሔር ችግር ነው ካሉ በኃላ የብሔር ችግርን ”የማይታረቅ ቅራኔ” ሲሉ ስደመጡ ተሰብሳቢውን አስደንግጧል።

ቀጥሎ ከተናገሩት ውስጥ አቶ በረከት ነበሩ።አቶ በረከት አቦይን የወረፉበት ንግግር አቦይን ”ድራማቲክ” አቀራረብ ያለው ሲሉ ተደምጠዋል። አቶ በረከት የገለጡበት መንገድ እንዲህ ይነበባል -”የአቦይ ስብሐት አይነት ድራማቲክ አቀራረቦች ስንሰማ ልንዋጥ እንችላለን።በታሪክም ልንጠፋ እንችላለን” በማለት ነበር።የሁሉም ንግግሮች ያጠነጠኑት ትግራይ በሌላው ኢትዮጵያ ላይ የበላይ እንደሆነ ማብራራት ነበር።ደደቢት ላይ ህወሓት ባይመሰረት ኖሮ ኢትዮጵያ ትጠፋ እንደነበር ለመግለፅ መድከም ሌላው ለማስተላለፍ የታሰበው መልዕክት ነበር።

ህወሓት የፖለቲካ ማሳመኛው ፍልስፍናው ሁሉ ተሟጦ የቀረው የደርግ ዘመንን ደጋግሞ ማንሳት ብቻ ሆኗል።አሁን ኢህአዴግን ፖሊሲህ ዘመን ያለፈበት በቂም፣በዘር እና በበቀል የታሸ ነው የሚለው ደግሞ ኢህአዲግ አዲስ አበባ ሲገባ ገና በእግራቸው መቆም ያልቻሉ ሕፃናት የነበሩ ወይንም ገና ያልተወለዱ ናቸው።ህወሓት የኢትዮጵያን ሕዝብ ዲሞክራሲ የነጠቀ፣በጠራራ ፀሐይ ድምፄ ተሰረቀ ያሉ ወጣቶችን በጥይት የቆላ፣ብሔር ከብሄር በማጋጨት ከእራሱ የወጡ አባሎቹ የመሰከሩበት፣አባላቱ በሙስና በሰበሰቡት ገንዘብ መሃል አዲስ አበባ እና መቀሌ ላይ ባለ ሰባት ፎቅ ሲገነቡ እፍረት የማይሰማቸው አባላት ያሉት ወንጀለኛ ድርጅት መሆኑን የሚሞግቱት አሁንም ወያኔ አራት ኪሎ ቤተ መንግስትን ሲቆጣጠር በእናታቸው እቅፍ ሆነው ጡት የሚጠቡቱ ናቸው። በመሆኑም ተከራክሮ የማያሳምነውን ትውልድ ሸሽቶ ስለፖለቲካ ቢናገሩ እናንተን አይመለከትም ለማለት የሚቀሉትን አርቲስቶችን መማፀኑ ካለተከራካሪ የእኔን ብቻ ስሙኝ ስልት መሆኑ ነው።

ህወሓት ለአርቲስቶች ያልነገራቸው

የህወሓት መሪዎች አርቲስቶቹን ፈረንጆቹ ”ዱላ እና ካሮት” በሚሉት አስተያየት እያዩ እና አንዳንዴ ፈገግ መልሰው ኮስተር እያሉ በማሳቀቅ የተረኩት ሁሉ ዛሬ ላለችው ኢትዮጵያ እና ዓለማቀፋዊ ሁኔታ ፋይዳው ምንድነው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። የስብሰባው ዋና ዓላማ ህወሓት የተንጠለጠለበት የጎሳ ፖለቲካ እንዳይበጠስ በመስጋት የጎሳውን ታላቅነት የሰበከ መስሎ ብዙዎች አይናቸውን ተክለውባቸዋል ባለው አርቲስቶች በኩል ህዝብን ማስፈራራት፣ተስፋ ማስቆረጥ እና ”መጪውም ገዢዎችህ እኛ ነን።” የሚል መልእክት ለሕዝቡ ማስተላለፍ ነው።”መጪው ምርጫንም ክደደቢት አንፃር ተመልከቱ እና እንዴት ነው በካርድ ስልጣን እንድለቅ የምታስቡት?” የሚልም ቃና አለበት።

እዚህ ላይ ግን አምባገነኖች የራሳቸውን ታሪክ እራሳቸው ከሚተርኩት በዘለለ ነፃ የታሪክ ምሁራን የራሳቸውን ምርምር አድርገው ታሪክ እንዲፅፉ አይፈልጉም እና ተራክዎችም ሆነ ሰሚዎች እራሳቸው እንደሆኑ የመቃብር ጉዞ ይጀምራሉ።እዚህ ላይ ህወሃቶች ለአርቲስቶቹ ያልነገሯቸውን ማንሳት ተገቢ ነው።
አቦይ ስብሐት፣አቶ ስዩም እና አቶ በረከት ቢቢሲ ስላረጋገጠው ህወሓት ለትግራይ ሕዝብ በ 1977 ዓም እረሃብ የመጣውን የዕርዳታ እህል ሱዳን እየተወሰደ ይሸጥ እንደነበር እና የጦር መሳርያ ይገዛበት እንደነበር አልነገሩትም።
በደርግ ዘመን በአሶሳ የአማራ ተወላጅ ናችሁ ተብለው በአንድ ቤት ተከተው በእሳት ስለተቃተሉት ምንም አላሉም።
ኤርትራ ከኢትዮጵያ ትለይ ብለው እስከ ምፅዋ እና ከረን ድረስ የትግራይ ተወላጆች ደም እንዲገብሩ መላካቸውን አላነሱትም።
ህወሓት እስካሁን ድረስ በአሜሪካ የሽብር መዝገብ ላይ እንደሰፈረ መሆኑን ትንፍሽ አላሉም።
በህወሓት የተሳሳተ ፖሊሲ ሳብያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሴት እህቶቻችንን ለአረብ ሀገር መከራ መዳረጋቸውን ያነሳ የለም።
በህወሓት ውሳኔ በሺህ የሚቆጠሩ ሕፃናት ለጉድፈቻነት መዳረጋቸው እና በለውጡ ህወሓት ብዙ ሚልዮን ዶላር ማትረፉን ትንፍሽ ያለ የለም።
ህወሓት ከተሞች በጎዳና ተዳዳሪዎች፣ወጣቶች ለጫት እና ለሽሻ፣የዩንቨርስቲ ምሩቃን የኮብል ስቶን ሥራ ሰራተኛ እንዲሆኑ የተደረጉት በዘመነ ህወሓት መሆኑን ለመናገር የደፈረ የለም።
በከተሞች የሚኖሩ ብዙ ሺዎች የገዛ ቤታቸው በግሬደር ሲፈርስ እና የጎዳና ተዳዳሪ የሆኑት በህወሓት ዘመን መሆኑን ህወሀቶች አላነሱትም።
ገበሬው ለዘመናት ከኖረበት ቦታ በጎሳ እና በቋንቋ እየለዩ ለዘመናት ከኖረበት ቦታ የተፈናቀለው በዘመነ ህወሓት መሆኑን ያወሳ የለም።
አስራሶስት የህወሓት አመራሮች በስዊድን ዓለም አቀፍ የጦር ፍርድ ቤት በዓለም አቀፍ ወንጀለኛነት ከተከሰሱ ገና ቀናት እየተቆጠሩ መሆናቸውን ሊያስታውሱ አልፈለጉም።
ከሁሉም የሚገርመው ህወሃቶች ከአርትስቶቹም ሆነ ከትግራይ ሕዝብ የደበቁት ትልቅ ጉዳይም አለ።የሀውዜን እልቂትን ጉዳይ።ይህንን እልቂት አቦይ ስብሐት አዲስ የማስቀየሻ ያሉትን ሃሳብ ይዘው ቀርበዋል።”በጉዳዩ ላይ የእስራኤል እጅ አለበት” ነበር አቦይ ያሉት።መቸው ህወሃቶች ከገደሉ ወይም ከተኮሱ አልያም ከተናገሩ በኃላ ነው ማሰብ የሚጀምሩት።ለእዚህም ነው ነገሩን ከመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ጋር በማያይዝ ከአረብ ሃገራት ያተረፉ የመሰላቸውን የተናገሩት። ከህወሓት የለቀቁት የቀድሞ ከፍተኛ ባለስልጣናቱ ግን በሃውዜን እልቂት ላይ የህወሓት ቁልፍ ባለስልጣናት እጅ ሆን ተብሎ የተቀናበረ መሆኑን ያብራራል።አቶ ገብረ መድህን አርአያ፣አቶ ግደይ እና አቶ አብርሃም ያየህ በተለያየ ጊዜ በጉዳዩ ላይ ማብራርያ ሰጥተዋል።ከእዚህ በታች የአቶ ገብረ መድህን የቀድሞው የህወሓት መስራች እና የፋይናንስ ኃላፊ በሃውዜን እልቂት ህወሓት አቀናባሪ እንደነበር እና ምክንያቱንም ጭምር እንዲህ ያብራራሉ።

”“ወይ፡ ሀውዜንም የወያኔ ድራማ ነው።” በዚያን ጊዜ ሕወሀት በምትሰራው ስራ ምክንያት እጅግ በጣም ተጠልታ ነበር። ሰው አጣች። ምልምል ጠፋ። እናስ? ተንኮል አሰቡ። የዚያን ግዜ የትግራይ አስተዳዳሪ ለገሰ አስፋው ነው። ከዚያ ወያኔ ሀውዜን አንድ ክ/ጦር እያስገባች እያስወጣች ወያኔ ሀውዜን ስብሰባ ልታደርግ ነው የሚል ወሬ ለደርግ ደህንነት እንዲደርሰው አደረገች። ሀይሉ ሳንቲም (ሳነቲም ቅጽል ስሙ ነው) የሚባል የወያኔ የጦር ደህንነት፡ የወያኔ ጦር ሀውዜን ሊሰበሰብ ነው የሚለውን መረጃ ለለገሰ አደረሰ። እውነት እንዲመስልም፡ በገበያው ቀን የተወሰኑ ታጋዮች ባካባቢው ውር ውር ሲሉ እንዲታዩ ተደረገ። የሀውዜን ገበያ መቼም እጅግ የታወቀ ነበርና ከብዙ ቦታ ብዙ ሰዎች ለንግድ ይመጣሉ። በእለቱ ስድስተ የደርግ ሚጎች እየተመላለሱ በመስቀልያ ቅርጽ፡ ገበአውን ደበደቡት። ይሄ ሁሉ ሲደረግ ቪዲዮ ይነሳ ነበር። ነገሩ ለረጅም ግዜ የተቀነባበረ መሆኑ የሚታወቅባቸው ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው። ወደ አስራ ሁለት ፎቶ አንሺዎች ሱዳን ውስጥ ሄደው እንዲሰለጥኑ ተደርጓል። ገብሬ የዚያን ግዜ ቪዲዮ ካሜራ አያውቅም ነበር። እነ ተክለወይን አስፍሀ፡ እነ ሱራፌል ምህረተአብ፤ እነ እያሱ በርሄ ካሜራ ቀራጭነት ሱዳን ውስጥ ተምረው መጡ። ያ ሁሉ ድብደባ ሲደረግ ተራራ ላይ ቆመው እያንዳንዱን ሚግ ከሁሉም አቅያጫ ቪዲዮ ያነሱ ነበር። ይቀርጹ ነበር። በነጋታው ይሁን ማታውኑ ያ ሁሉ ፊልም ሱዳን ውስጥ በቲቪ ታየ። ገበያ ላይ የሞተው ሰው እንሰሳ፡ ህዝብ፡ ሽማግሌ ሕጻናት በቲቪ በደንብ ተቀርጿል።

የምንስ ለቅሶ መልሶ መልሶ

ባጠቃላይ ህወሓት በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ምንም አይነት አሻራ የለውም የሚል የለም።ሆኖም ግን መታሰብ ያለበት ጉዳይ ዛሬ ላይ በሞቱት አጥንት ላይ ተቀምጠው በሙስና በስብሰው፣ዲሞክራሲን በእግራቸው እረግጠው እና በርካታ ግድያ ፈፅመው የሞቱትን እያነሱ መመፃደቅ አሁንም በሞቱት ላይ መሳለቅም አያጣውም።ለሕወሃቶች የምመክራቸው ሴኮቱሬ ከደደቢት ያስተላልፍ የነበረውን ፕሮፓጋንዳ ዛሬ ላይ ደግመው ማንበብ ቢችሉ የሚል ነው።”ትግላችን የኢትዮጵያ ሕዝብ ካለምንም ገደብ የመፃፍ፣የመናገር እና ሃሳብን በነፃት የመግለፅ ነፃነትን ለማረጋገጥ ነው።ትግላችን ህዝቦች ካለ አንዳች ፍርሃት ሰላማዊ ሰልፍ የሚያደርጉበትን በፈለጉት የሀገሪቱ ቦታዎች የመኖር መብታቸው እንዲረጋገጥ ነው” ይል ነበር። ለእዚህ ነዋ ”ህገ መንግስቱ ይከበር” ያሉትን ንፁሃን ወጣቶች እስር ቤት የምታማምቁት? ለእዚህ ነዋ ! ”ነፃነት ለፍትሃዊ ምርጫ” ብለው የተሰለፉትን የሰማያዊ ፓርቲ እና የዘጠኙን ፓርቲዎች ጥሪ በድብደባ መባረራቸው እና መታሰራቸውን ምን እንበለው። በደደቢት ህወሃቶች ለአርቲስቶቹ የነገሯቸው እና ያልነገሯቸው ታሪኮች ሁሉ የሚያሳዩት አሁንም ህወሓት ስለመንደሩ እንጂ ለኢትዮጵያ አለመቆሙን ነው።

ጉዳያችን ታህሳስ 23/2007 ዓም (ጃንዋሪ 1/2015)


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>