መግቢያ፤
ኢትዮጵያንና አርሚኒያን ከሚያመሳስሏቸው ጉዳዮች አንደኛው የአንድ ዓይነት የኦርቶዶክስ ሃይማኖት የእምነት መሠረት (ዶግማ) ተከታዮች ያሉባቸው ሐገሮች መሆናቸው ነው። በዚህ ጽሑፍ የማተኩርበት ተመሳሳይነት ግን ሁለቱም ሐገሮች በከባድ የጦር ወንጀሎች ተጠቅተው እያንዳንዳቸው ቢያንስ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ የተጨፈጨፈባቸው መሆኑ ነው። ሌላም እጅግ አስጸያፊ ግፍ የተፈጸመባቸው ሐገሮች ናቸው። በተጨማሪም፤ ሁለቱን ሐገሮች ያቀራረባቸው ሌላው ጉዳይ በኦቶማን ዘመነ መንግሥት፤ ከቱርኮች ግፍ በመሸሽ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት መልካም ፈቃድ ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱት 40 አርመኖች ኑሯቸውን በሐገራችን መቀጠላቸው ነው። እነዚህ አርመኖችና ተወላጆቻቸው በኢትዮጵያ ተመቻችተው የኖሩና ብዙዎቹም አማርኛውን ያቀላጥፉ እንደ ነበር የታወቀ ነው። በዚህ አጋጣሚ፤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካኝነት ዱባይ በምሠራበት ጊዜ እዚያ ይኖር የነበረውን፤ ወዳጄን፤አቶ የርቫንትን እያስታወስኩ፤ አርመኖች ያቋቋሟትን ሻርጃ (Sharjah) የምትገኝ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያውያን ምእመናን በማጋራታቸው፤ ውለታቸውን አልረሳውም።
በአርመኖችና በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸሙት እልቂቶችና የጦር ወንጀሎች፤
በአርመኖች ላይ የተፈጸመው የጦር ወንጀል እ.አ.አ በ1915-23 በኦቶማን (Ottoman) (በኋላ ቱርክ) ዘመነ መንግሥት መገባደጃ ጊዜ ነበር። እንደሚታወቀው፤ በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመው እልቂት እ.አ.አ በ1935-41 በኢጣልያ ፋሺሽቶችና በቫቲካን ያልተቆጠበ ድጋፍ የተከናወነ ነበር። ከላይ እንደ ተገለጸው፤ ሁለቱም ሐገሮች ቢያንስ አንድ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ ተጨፍጭፎባቸዋል። በተጨማሪም እጅግ ብዙ አርመኖች ከሐገራቸው እንዲሰደዱ ተገድደው ለከባድ ችግር ተጋልጠዋል። በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመው ግፍ በብዙ የኢጣልያ አውሮፕላኖች በተነሰነሰው የመርዝ ጋዝ እንዲሁም በሌሎች ልዩ ልዩ መሣሪያዎች የተጨፈጨፈው ሕዝብ፤ (በሶስት ቀኖች አዲስ አበባ የተገደሉት 30 000 ኢትዮጵያውያን ጭምር) ብቻ ሳይሆን የወደሙትን 2 000 ቤተ ክርስቲያኖች፤ 525 000 ቤቶችና 14 ሚሊዮን ያህል እንስሶች ያካትታል። በተጨማሪም እጅግ ብዙ ዝርፊያ የተከናወነ መሆኑ የታወቀ ነው።
የአርመኖች ትግል ለፍትሕ፤
በአርመኖች በኩል፤ ከ100 ዓመት በፊት በቱርኮች ለተፈጸመባቸው ወንጀል ተገቢውን ፍትሕ ለማስገኘት ያላሰለሰ ትግላቸውን እየቀጠሉ ነው። መሠረታዊ ዓላማቸውም ያ ከባድ ጥቃት የዘር ማጥፋት ወንጀል (genocide) መሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅላቸው ለማድረግ ነው። በዚህ በፈረንጆች የዘመን አቆጣጠር በ2015 የእልቂቱ መቶኛ ዓመት የሚደፍን በመሆኑ በሰፊው ለመዘከር እቅድ አላቸው። በዚህ ተግባር ከተሰማሩት ውስጥ፤ የአርመን መንግሥት እንዲሁም በአሜሪካ የሚገኙ፤ (ሀ) የአርመን ብሔራዊ ኮሚቲ በአሜሪካ (Armenian National Committee of America) (www.anca.org) እና (ለ) የአሜሪካ አርመናዊ ሸንጎ (Armenian Assembly of America) (www.aaainc.org) ይገኙበታል።
ሰሞኑን በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መማከሪያ (Foreign Affairs Council) በተሰኘው ድርጅት አማካኝነት ታትሞ በወጣው ፎሪን አፌርስ (Foreign Affairs) መጽሔት (January/February 2015)፤ ቶማስ ደ ዋል (Thomas de Waal) የተባለ ዘጋቢ፤(“The G-Word; The Armenian Massacre and the Politics of Genocide”) (ትርጉም፤ የጂ-ቃል፤ ስለ አርመኖች እልቂትና የዘር ማጥፋት ፖለቲካ) በሚል አርእስት የሚከተሉትን ቁም-ነገሮች አቅርቧል፤
(ሀ) እ.አ.አ. በ1918 የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቲዮዶር ሩዝቬልት (Theodore Roosevelt) በአርመኖች ላይ ስለ ተፈጸመው ስደትና እልቂት አሜሪካ በኦቶማን መንግሥት ላይ ጦርነት ማወጅ አለባት በማለት ሐሳባቸውን በደብዳቤ ገልጸው ነበር።
(ለ) የአርመኖች የፍትሕ ትግል በአሜሪካ መንግሥት መርሆ ላይ ከፍተኛ አጽንኦት አስክትሏል። እ.አ.አ. በ1951 የአሜሪካ መንግሥት ጠበቆች ቱርኮች በአርመኖች ላይ የፈጸሙት እልቂት እንደ የሰው ዘር ማጥፋት ወንጀል (genocide) እንዲታይ ሔግ (The Hague) ለሚገኘው ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት (International Criminal Court) አመልክተው ነበር። ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት የዘር ማጥፋት ወንጀል ስምምነት (United Nations Genocide Convention) የታወጀው እ.አ.አ. በ1948 ከአርመኖች እልቂት በኋላ በመሆኑ እስካሁን ጉዳዩን ለፍርድ የማቅረቡ ሒደት አልተሳካም።
(ሐ) እ.አ.አ. በ1975 የአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት (House of Representatives) መሪ፤ ቲፕ ኦኒል (Tip O’Neill) እ.አ.አ. ሚያዚያ 24ን (April 24) የሰውን ልጅ የርስ በርስ ኢሰብአዊነት ብሔራዊ የመዘከሪያ ቀን (National Day of Remembrance of Man’s Inhumanity to Man” ተብሎ እንዲሰየምና በዘር ማጥፋት ወንጀል የተጠቁትን በሙሉ፤ በተለይም እ.አ.አ. በ1915 ለተሰዉት አርመኖች መታሰቢያ እንዲሰየም ሥልጣኑን ለአሜሪካ ፕሬዚዳንት የሰጠበት የውሳኔ መግለጫ አውጥቶ ነበር። ነገር ግን በሌላው የአሜሪካ ምክር ቤት፤ በሴኔት (Senate) የአርመኖችን እልቂት እንደ የዘር ማጥፋት ወንጀል የመቁጠር ጉዳይ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።
(መ) ፕሬዚዳንት ሬጋንም (President Reagan) በመጀመሪያ በ እ.አ.አ. በ 1981 ለአርመኖች የዘር እልቂት (genocide) እውቅና በመስጠት ገለጻ አድርገው ነበር። ነገር ግን እ.አ.አ. በ1982 ሁለት አርመናዊ ወጣቶች በሎዛንጀለስ ከተማ የቱርክ ቆንስል መሪ የነበረውን ከማል አሪካንን (Kemal Arikan) በመግደላቸው የፕሬዚዳንት ሬጋን አቋም ተለወጠ።
(ረ) የቱርክ መንግሥት ለአሜሪካ ጠንካራ ድጋፍ ከሚያበረክቱት መንግሥቶች አንዱ በመሆኑ በተለይም የሰሜን አትላንቲክ ሐገሮች ድርጅት (NATO) አባል በመሆኑ በአርመኖች ላይ ስለ ተፈጸመው የኦቶማኖች የጦር ወንጀል አሜሪካ ያላት አቋም ተለዋዋጭ ሆነ።
(ሠ) የአሜሪካና የቱርክ መንግሥቶች ባላቸው የጥቅም ቅድሚያ ለአርመኖች የሚገባውን ፍትሕ ለጊዜው ያመከኑት ቢመስልም የአርመን ታጋይ ድርጅቶች የመቶ ዓመት ጥረታቸውን አጠንክረው እየቀጠሉ ነው። ለዚህም በምርጫ መብታቸው እየተጠቀሙ በአሜሪካ የኮንግሬስ አባሎችና በሐገሩ ፕሬዚዳንት ላይ የማያቋርጥ አጽንኦት እንዲከሰት ለማድረግ እየጣሩ ነው። የዚህም ጥረት ውጤት አንደኛው ምሳሌ፤ እ.አ.አ. በሚያዚያ 24 ቀን 2010፤ ፕሬዚዳንት ኦባማ (President Obama) የሚከተለውን ገለጻ ማድረጋቸው በቶማስ ደ ዋል ጽሑፍ ተዘግቧል፤
“1.5 million Armenians were massacred or marched to their death in the final days of the
Ottoman Empire……..The Meds Yeghern (“Great Catastrophe”) is a devastating chapter in the
History of the Armenian people, and we must keep its memory alive in honor of those who
were murdered and so that we do not repeat the grave mistakes of the past.”
(ትርጉም፤ በኦቶማን መንግሥት የመጨረሻዎቹ ቀናት 1.5 ሚሊዮን አርመኖች ተጨፍጭፈዋል ወይም ለሞት
ወደሚዳርጋቸው እንዲጓዙ ተደርገዋል። ታላቁ ሰቆቃ (መቅሠፍት) በአርመኖች ታሪክ እጅግ አሰቃቂ ምእራፍ
ነበር። ያለፈውን ስሕተት እንዳንደግመው ለተገደሉት ሰዎች ክብር የዚያን ዘመን ትዝታ ሕያው አድርገን
ልናስታውሰው ይገባናል።)
ከዚህ በላይ ከተዘረዘረው መገንዘብ የሚቻለው፤ ምንም እንኳ አርመኖች የሚፈልጉት፤ ማለትም በቱርኮች የተፈጸመባቸው ጭፍጨፋ እንደ የዘር እልቂት ወንጀል (genocide) የማሳወቅ ዓላማ እስካሁን ባይሳካላቸውም ጥረታቸው በከፍተኛ ደረጃ እየቀጠለ የአሜሪካ መሪዎች ጭምር ተስፋ አላስቆረጧቸውም። “የአርመን ብሔራዊ ኮሚቲ በአሜሪካ” ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ዲሬክተር የሆነችውን ወ/ሮ ኤሊዛቤት ሹልድጂያንን (Elizabeth Schouldjian) ሰሞኑን በስልክ አነጋግሬያት አርመኖችና የአርመን መንግሥት ትግላቸውን የሚቀጥሉ መሆኑንና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚያከናውኑት እንቅስቃሴ ከአውሮፓ የሰብአዊ መብት ፍርድ ቤት ጋር ጭምር ጉዳዩን እንደሚገፉበት ገልጻልኛለች።
የኢትዮጵያስ ትግል?
ኢትዮጵያ ለተፈጸመባት እጅግ አሰቃቂ ግፍ ተገቢውን ፍትሕ አላገኘችም። ካሣ ተብሎ ለቆቃ ግድብ መሥሪያ የዋለው $25 ሚሊዮን እና ወደ ሐገሩ የተመለሰው የአክሱም ሐውልት በምንም መስፈርት ብቁ ነው ሊባል አይችልም። ኢጣልያ ለሊቢያ $5 ቢሊዮን፤ ለዩጎዝላቪያ $125 ሚሊዮን፤ ለግሪክ ሐገር $105 ሚሊዮን፤ ለሶቪየት ዩኒየን $100 ሚሊዮን፤ ወዘተ ከተስማማችው ጋር ሲመዛዘንና በተለይም በኢትዮጵያ ላይ ከፈጸመችው ክፍተኛ የጦር ወንጀል ጋር ሲነፃፀር በግልፅ የሚታየው የተዛባ ፍትሕ የሚያስቆጭ ነው። “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው፤ ኢጣልያ የፈጸመችው ወንጀል አልበቃ ብሏት፤ በቅርቡ፤ የቫቲካን ተወካይ በተገኙበት፤ አፊሌ በምትባል የኢጣልያ ከተማ፤ “የኢትዮጵያ ጨፍጫፊ” በመባል ለሚታወቀው፤ ለሮዶልፎ ግራዚያኒ አንድ መታሰቢያና መናፈሻ ተመርቆለታል። እንደ ኬንያና ኢንዶኒዚያ ያሉ ሐገሮች ከቀድሞ አጥቂዎቻቸው ከእንግሊዝና ከኔዘርላንድስ ተገቢውን ይቅርታ ተጠይቀው ካሣ ጭምር ሲከፈላቸው ኢትዮጵያ የተሟላ ፍትሕ ሊነፈጋት አይገባም። ስለዚህ፤ ዓለም አቀፍ ሕብረት ለፍትሕ – የኢትዮጵያ ጉዳይ (Global Alliance for Justice – The Ethiopian Cause) የተሰኘው ድርጅት ከዚህ በታች ለተዘረዘሩት ዓላማዎች እየታገለ ይገኛል፤
(ሀ) የኢጣልያ መንግሥት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተገቢውን ካሣ እንዲከፍል፤
(ለ) ቫቲካን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ፤
(ሐ) የኢጣልያ መንግሥትና ቫቲካን የተዘረፉትን ንብረቶች ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲመልሱ፤
(መ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፋሺሽት ኢጣልያ በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመችውን የጦር ወንጀል
እንዲመዘግብ፤ እና
(ሠ) በቅርቡ ለፋሺሽቱ “የኢትዮጵያ ጨፍጫፊ” ለሮዶልፎ ግራዚያኒ ኢጣልያ ውስጥ በአፊሌ ከተማ፤ የተሠራው
መታሰቢያ እንዲወገድ።
አቤቱታውንም ለሚመለክታቸው ሁሉ፤ ለኢጣልያ መንግሥትና ለቫቲካን፤ ለአውሮፓ ምክር ቤት፤ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት፤ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ ለፕሬዚዳንት ኦባማና ለሌሎች አንዳንድ የዓለም መንግሥታት መሪዎች፤ እንዲሁም በፍትሕ ለሚያምኑ ሰዎች በሙሉ አቅርቧል። በዚህ አጋጣሚ በየዓመቱ የካቲት 12ን ለመዘከር በ30 ከተሞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሐገር ፍትሕና ክብር ለሚንቀሳቀሱ ሁሉ ልባዊ ምሥጋና ይድረሳቸው። የኢትዮጵያ አርበኞች ማሕበርም የሚያከናውነው ጥረት ሊጠቀስ ይገባል።
በተጨማሪም፤ በድርጅቱ ድረ-ገጽ (www.globalallianceforethiopia.org) የሚገኝ፤ ቫቲካን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ እየተፈረመ ያለ ዓለም አቀፍ አቤቱታ ይገኛል። እስካሁን ክ4200 ሰዎች በላይ ፈርመውታል። ይህንን ጽሑፍ የሚመለከቱ ሁሉ አቤቱታውን እንዲፈርሙት ተጋብዘዋል።
4
ለውድ ሐገራችን ለኢትዮጵያ ስለሚያስፈልገው ፍትሕና ክብር እስካሁን የተከናወነው ጥረት የሚያበረታታ ቢሆንም በውጤት ደረጃ አመርቂ ደረጃ አልደረሰም። በተለይም አርመኖች ለክብራቸውና ለሐገራቸው ፍትሕ ከሚያከናውኑት ትግል ጋር ሲነፃፀር በኛ በኩል ጥረታቻችንን ማጎልበት እንደሚገባን ግልጽ ነው። ስለዚህ ለሐገርና ለፍትሕ የሚቆጭ ሁሉ በትግሉ እንዲሳተፍና እንዲደግፍ ያስፈልጋል። የአገር ወዳዶች የተባበረ ጥረት የትግሉን ውጤት የተሳካና የተፋጠነ ለማድረግ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
ቸሩ የኢትዮጵያ አምላክ ለሐገራችን የሚገባው ክብርና ፍትሕ እንዲገኝ የጀመርነውን ጥረት፤ በሁሉም አገር ወዳድ ተሳትፎ፤ አጠናክረን እንድንቀጥል ብርታቱን ይስጠን። አሜን!