Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የበደል ድርድር –የቅጥፈት ውድድር። (ከሥርጉተ ሥላሴ)

$
0
0

09.01.2014 /ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ/

Andargachew 1እንደ ሰው አለመሆንን ፍንትው አድርጎ ባሳዬው የሰሞናቱ የበደል ድርድር አብዛኛው የጭድ ክምር ሆኖ ነው እኔ በግሌ ያገኘሁት። በሌላ በኩል ግን ይህንን እጅግ የወረደ የቴሌቪዥን ቅንብር አይቶ ወያኔ መላእክ ሌላው ዓለም ጭራቅ ብሎ ብይን የሚሰጥ ሰው ይገኛል ብሎ መገመት እራሱ እውርነት ነው። ቀድሞ ነገር ለሰብዕዊ መብት ክብር ህጋዊነትን ለማብሰር የሃሳብ ነፃነት፤ የመደራጀት ነፃነት፤ የዕምነት ነፃነት፤ የመሰብሰብ ነፃነት፤ የመምረጥና የመመረጥ ነፃነት ዕውን መሆን አላባቸው – በጥቂቱ። ይህን ስለአደረጉ አስሮ – ደብድቦ – አፍኖና አሰቃይቶ „ሰብዕዊ መብታቸው ተጥበቆ ተዝናንተው ያልተጠዬቁትን ሳይቀር ተናገሩ¡“ ማለት እጭነት ነው። ለመሆኑ የወንድማቸውን ሁኔታ በአካል ተገኝተው ለማዬት ከሀገረ አሜሪካ ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ የሄዱትን እህታቸውንስ ስለምን በ24 ሰዓት ባዕታቸውን ዬእትብት መንደራቸውን ለቀው እንዲወጡ አደረገ ወያኔ? ይህም የወያኔ የነፃነት ገነት ተብሎ ሊወደስ ይሆን¡?
አዎን! የነፃነት አረበኞቻችን ሃሳባቸውን በመግለጻቸው ለምን ታሰሩ? የሚለውን ጥያቄም መመለስ ያስፈልጋል። ሃሳብን መግለጽ እኮ ወንጀል አይደለም። የማይገሰስ ሰማያዊ መብት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። በአንጻሩ ነፃነቱን የተነጠቀ ሰው በማናቸውም ሁኔታ ተደራጅቶ ለነፃነቱ የሚያደርገው ትግልም ቢሆን ህጋዊ ነው። ህገወጥ የሚሆነው ነፃነቱን የቀማው አካል ወንበዴው ወያኔ ሰብዕዊ መብትን እረግጦ፤ የሰው ልጅን ሰብዕዊ መብት ለማስከበር በተጉት ላይ የሚያካሂደው የህሊና ዘረፋ፤ ህሊናን አስገድዶ ድፈረት ነው- ወንጀሉ። አስገድዶ ህሊናን በመዳፈር በታሪክ ወያኔ የመጀመሪያውን ረድፍን ይይዛል።
ወያኔ በቀል ነው መርኹ። በቀል ደግሞ ምህረት የለሽ ነው። ምህረት የለሽ መሆን ደግሞ ከሰው ደረጃ አውርዶ አውሬነትን ያውጃል። ይህ ደግሞ የሚጨበጥ የሃቅ እንክብል ነው። በእያንዳንዷ ቀን፤ በእያንዳንዷ ሰዓት፤ በእዬአንዳንዷ ደቂቃ የዜጎቻችን ደም በህገወጡ ጎጣዊ ድርጅት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በወያኔ ይፈሳል። በወገኖቻችን ላይ ኢ- ፍትሃዊ ተግባር ይፈጸማል። እያንዳንዷ የወያኔ የመኖር ስንቅ ቋሳን ሰንቆ አሪወሳዊ ተግባርን መፈጸም ነው። ይህ ደግሞ በሚታዩ ብቻ ሳይሆን ብዙ በማይታዩ የሰው ልጅ ሊደርስባቸው በማይችሉ ማናቸውም ስለታማ ጦር ጥቃት ይፈጸማል። ወገኖቻችን – ይቀቀላሉ። መፈተኛና መሞከሪያም ይሆናሉ – በገደል ውስጥ እያሉ ተቅብረው አንድ ሜትር በአንድ ሜትር በሆነ ዛኒጋባ ይሰቃያሉ። ወንድ ከሆነ ወያኔ ስለምን ያሉበትን ቦታ ሆነ የተሰወሩበትን ሁኔታ አደባባይ አያውለውም?!
ቀድሞ ነገር እስር ቤት ሆኖ ለዛውም በወያኔ እጅ ተወድቆ „ምቾት ላይ ናቸው¡“ ብሎ ማወጁ የወያኔን የማስተዋል ደረጃ ምን ያህል ቁልቁል እንደሆነ ያሳያል። ለምን? ሰው ሃሳቡን በመግለጹ፤ የተሻለ ሥርዓት እንዲኖር በማለሙ እኮ ለምን ይታሠራል? ለዚህ መልስ አለው ሽፍታው ወያኔ?! ከታሠሩ በኋላ እንኳን ባልተቋረጥ እገዳ ከቤተሰብ – ከጠያቂ ጋር እንዳይገናኙ፤ ስንቅ እንዳይገባላቸው ለምን ያደርጋል?! መልስ አለው ሽፍታው ወያኔ? ለነገሩ ወያኔ በሰብ ተፈጥሮ ማለትም እንደ ሰው በራሱ ተፈጥሮ የሸፈተ አሜኬላ እኮ ነው። እራሱን አያምንም ሌላውንም አያምንም። እራሱን ሆኖ መኖር አይችልም። ስለምን ሰብዕነትን የዘለለ እሾኽ በመሆኑ።
እንሆ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሁለት የግንቦት 7ትን ጥንካሬ ላነሳ ፈልግሁ። የታዘብኩትን – በእኔ ዕይታ። የጹሑፌ ሐዲድ ነውና። የመጀመሪያው የግንቦት 7 ከፍተኛ አመራር አካላት የነገን መተንበይ ባልችልም እስከ አሁን ባለው ሁኔታ የመደማመጥ አቅማቸው አንቱ ነው። የሃሳብ ልዩነት በፓርቲ ህይወት ውስጥ እንደሚኖር ግድ ይላል። ነገር ግን ይህን የሀሳብ ልዩነት በበለጸገ የዴሚክራሲ መደማመጥ መምራት መቻል ሥልጡንነት ነው። ከፍተኛ አመራር አካላቱ ሲካሰሱ ወይንም የፈነገጡ ሃሳቦችን አደባባይ አውለው ማስተባበያ ድርጅቱ ሲሰጥባቸው አይታይም። ስለዚህ ግንቦት ጊዜውን በአግባቡ ማስተዳደር የቻለ፤ በጋራ አመራርና በግል ኃላፊነት መመራቱን ዕውነታው ይመሰክራል። ሁለተኛው ብርቱው የብቃት ሚስጢር ደግሞ ግንቦት ህጋዊ በሆነ የህዝብ መድረክ፣ የመገናኛ አውታር ወይንም ማህበራዊ ድህረ ገጽ አቻ የነፃነት ትግል ፓርቲዎችን ሲተች፤ ሲያቃልል፤ ሲያብጠለጥል ተደምጦ አያውቅም። ይህም የጥንካሬው ሌላው የተግባር ህንፃው ነው።
ይህ ደግሞ ለገዢው የጎጥ ድርጅት አይመችም – ፈጽሞ። ከጠጠር ላይ የመተኛት ያህል ይጎረብጠዋል፤ ከረመጥ ላይ የመጋደም ያህል ያርመጠምጠዋል – ከሹል ድንጋይ ላይ የመቆም ያህል ያቆነጠንጠዋል። ስለዚህ የተሰበረ የፍላጎት ድልዱዩን ለመጠገን ሌላ መንገድ ፈለገ። …. ግንቦት ካለተፈጥሮው፤ ከላአደገበት ተመክሮው ከሌሎች ፓርቲዎች ወይንም ድርጅቶች ጋር ማዋጋት ፈለገ። ይህ … ይቀጥላልም። በህልሙ የሚነስተው ነበላባላዊ የነፃነት አርበኛ መጠሪያ ሥም ከህዝብ ፍቅር ለማግለል ብዙ አሳቶች ነገም ይጫራሉ …. ነገር ግን እኛ ሆን የጉዳዩ ባለቤት የነፃነት ትግሉ አባዎራዎች በበሰለ ተምክሮና – ማስተዋል፤ በቀና እና ቀጥ ባለ ህዝባዊ ፍላጎት ትግሉን ሊመሩና ሊያስተዳደሩ ይገባቸዋል። የጠላት ሴራ ጉቶዎች ሆኑ ጉንጉኖች ጅማሯቸው … ይከታተላል። መሆን ያለበት መፈለግና ማሳካት የመቻልን አቅም ይለካልና … ከጫካ ዶክተሪን በልጠው መገኘት ይኖርባቸዋል – እያንዳንዱ የነፃነት ትግሉና መሪው። ። ህዝቡንም ድንቆችን ከነክብራቸው ሊጠበቅቻውና መንፈሱን ሳይሳሳ ሊለግሳቸው ይገባል። የሚቻልን – ለማስቻል ነገን በብቃት ማዬት ይጠይቃል።
ለዚህም ነው በጣም በተከደነ ሁኔታ ሥጋት ያለበት የወያኔ አመራር ኢትዮጵውያንን ቀንዲል ሥም በማስጠራት በዛ ላይ መጥፎ ምስል እንዲኖር ለማድረግ የተጋው። ግን ጥረቱ የበከተ – የበሰበሰና የዛገጠ አተላ ነው የሆነው። ከእሱ በላይ ህዝብ አካሎቹን የነፃነት ትግሉን ተስፋዎች ሆኑ መሪዎችን ልጆቹን ያውቃል – አሳምሮ። ነፍስ አስቶ – ሌላ ሰብዕና ፈጥሮ፤ በመርዝ አደንዝዞ – ይቀዳል። የተናገራችሁት ይህ ነበር ይባላሉ – እስረኞቻችን። በዝብርቅ ፊልም ቅንብር እሱ እንደሚያመቸው ያው በጫካ ተመክሮ ተለብዶ – ተለስኖ – በስሚንቶ ታሽጎ እንዳዬነው ይቀርባል። …. ፍላጎትን ጠንቅቆ የሚያውቀው የአስተዋዩ የኢትዮጵያ ህዝብ አብራክና ማህጸን ክፋይ ወገን ግን ይህን የቅጥፈት ድርድር በሚገባ በልቶ ያውቀዋል። ይልቁንም በምን የብቃት ልክ እዬተመራ መሆኑንም ይመዝንበታል። እንዲህ ማጣፊያ ሲያጥር – ወያኔ ግርድ ያበጥር። ሌላው ደግሞ በጣም ወያኔ ተንጠራራ – እኛ የምናስከፍለው የቋሳ ዋጋ ዝቅ ያለ ነው ይቀረናል —- ዓይነት …. ለሰው ልጆች የስቃይ መጠን ውድድር አሰኘው። – በዴሞክራሲ ትርጎሜና የተግባር ክንውን ከአደጉት ሀገሮች ጋር እራሱን አለካካ። ሽልማትም አሻው —- መካሬ የለሽ፤ ግራጫ የመከነበት ፍልስ ድርጅት – ነገ የሸሸው።
አዎን! የሚገርመው – ወያኔ በእጁ የገባውን ጀግና መንፈስ በጣም ከቀደመው በላይ በሰፋ ሁኔታ ይፈራዋል። በመንፈሱ ብቻ ይርበደበዳል። ያለውን እንኳን በተሰተካከለ ሁኔታ ለማቅረብ አቅም የለሽ እዲሆን ያደረገውም ይሄው ነው። በራሱ ፍርድ ቤት እንኳን ለማቅረብ ድፍረት ከድቶታል። ኮሽታው ሁሉ በድንጋጤ ያደናብረዋል። ስለምን የእኔ የሚለው ከጎኑ የቆመ አንድ ብጣቂ ሃቅ የለምና። በራሱ ድርጊት እፈረቱ በቀለሰለት ጎጆ ተደብቆ ይዳክራል።
ጎጠኛው ወያኔ ሃቅን እንደ ፈራ ኑሮ ከሃቅ ጋር ሳይገናኝ፤ ከሃቅ ጋር ሳይመክር እልፈቱን ያውጃል። ወያኔ ሲከስም ዘር አልባ ሆኖ ነው። ስለምን? የሰብዕነት ፍርፋሬ ተጠግቶት ስለማያውቅ። እውነት ስለ ራቀው። ህዝባዊ ፍቅር ስለ ፈለሰበት – ከባህር የወጣ አሳ ነው። የወያኔ መኖሪያው ዙ ቢሆን መልካም በሆነ ነበር። እንደ እንሰሳ ኑሮ – እንደ እንሰሳ ማለፍ። አዬንለት አዲስ የተባለለትን ቪዲዮ – አንድ የሚጨበጥ ነገር በሌለው ፍሬ ፈርስኪ የፋንድያ ክምር – ዜሮን ደመረ። እኔ እንኳን አዲስ ነው ለማለት በጣም ነው የተቸገርኩት። ምክንያቱም በተከበሩ አቶ አንዳርጋቸው እጣት ላይ የነበረው ቁስለት ሆነ የጥፍራቸው ደሙ የተመጠጠው ግርጠት አሁንም እንደ አለ ነው። የሰውነት ላሂያቸውን በሚመለከት የፊልም ቅርበትና ርቀት ቀረጻ ካልሆነ በስተቀር እንደ ወቅቱ ተፈሪነት ሁኔታ ያን ጊዜ የተቀረጸውን ቆራርጠው ክፍል አንድ – ሁለት – ሦስት እያሉ ይቀጥላሉ ባይም ነኝ። በሌላ በኩል የዋሁም ደህና ነው የተሻለ ገጽ አለው እንዲል መንፈስ ለማዛል የተጠቀሙበት ነውም ባይ ነኝ። ምክንያቱም በጣም ነው የኖረውን ቁጫን ሁሉ በእሳቸው ላይ የተወጡት። ማንፌስቶውን ጽፎ ወያኔ ድርጅቱን ሲመሰርት የተሰማው ያህል ቁርሾ ነው በሂደቱ ማዬት የተቻለው። ስለዚህም የተከበሩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አገግመው ለመወጣት እንዲህ ቀላል አይሆንም ባይ ነኝ። ለዚህም ነው እሳቸውን በሚመለከት ቀዳዳዎች ሁሉ የተወታተፉት። ወያኔ ለፈጸመው ድርብርብ – ዘመን ይቅር ለማይለው ወንጀል አቅርቦ በአካል ለማሳዬት አቅም ያንሰዋል። ነፍስ ያለቀጠሮ ስለማትወጣ እንጂ የክርስቶስን መከራና ስቃይ እንደተቀበሉ መረዳት አያቅትም።
ወሳኝ
ከሰሞናቱ የቪዲዮ ይፋ መረጃ አንድ ዋሳኝ ጉዳይን ዘለግ ባለ ሁኔታ ማዬት ያለብን ይመስለኛል። ከወያኔ ኢንባሲዎች ውጪ የወያኔ ደጋፊ አከርካሪዎች ዘማች እጅ ምን ያህል ለብቅላ ሆነ ለጉርጉራ የመደመጥ አቅም እንዳላቸው እኔ በግሌ ማዬት ችያለሁ። በሌላ በኩል „የታላቋ ትግራይ ህልመኞችንም“ መስመር ተመልክቸበታለሁ። ወያኔ ከቅርቡ ያለውን ጉዳይ እንኳን ከተፈጸመ በኋላ ነው ማዬትና ማስተዋል የሚችለው። እንኳንስ የውጩን የማገናዘብ አቅም ሊኖረው ቀርቶ። ባናኝና ዕብን ነውና። ቀላሉ ምሳሌ የ97 ምርጫ ወያኔ በእጁ ያለውና የሌለውን የተረዳው መቼ ስለመሆኑ ጭብጥ ማስረጃ ነው። ከዚህ በኋላ ነቅቶ ስንት ነገሮችን እንደ ከለሰ ይታወቃል። ስለዚህ በዚህ ስሌት ሲኬድ የአሁኑ ቪዲዮ መንፈስ መነሻው የት እንደሆነ ለማገናዘብ ይቻላል ባይ ነኝ። እርግጥ የጠጠረና ረቂቅ ነው … እንዲህ በበሩ ዘው ተብሎ ተገብቶ የሴራውን ውስጥ ማዬት አይቻልም እንጂ ፍሬ ነገሩ ውጪ ያለው የወያኔ የድጋፍ መስመር የዳንኪራው ሁሉ ማሳረጊያ ሆኖ ነው – እኔ በግሌ ያገኘሁት። ውዶቼ የኔዎቹ ፈትሽቱት – ከልብ ሆናችሁ። ሌላ መልዕክት ያሰተላልፍላችኋል።
መቋጫ
የሆኖ ሆኖ ምንግዜም በጠላት እጅ የወደቀ ወገን ታሪካችን ነው። ምንጊዜም በጠላት እጅ የወደቀ ወገናችን አርበኛችን ነው። ምንጊዜም በጠላት እጅ ጥቃት የተፈጸመበት ህዝብ ሰንደቃችን ነው። ምንጊዜም በጠላት እጄ የተጎሳቆለ ተቋም ዓርማችን ነው። ምንጊዜም በጠላት እጅ የወደቀ መንፈስ ዝክራችን ነው። ምንጊዜም በጠላት እጅ ስቃይ የተፈጸመ ገላ ደማችን ነው። ምንጊዜም በጠላት እጅ የጥቃት ሰለባ የሆነ አካል መርሃችን ነው። ሲጠቃለል ታሪክም ዘመንም የነፃነት ትግሉን መጸሐፍ ይጽፋሉ። መጸሐፎቻችን ውስጦቻችን ናቸው። ታማኞቻችን ማተቦቻችን ናቸው – የወልዮሽ ብሄራዊ ሃይማኖታችንም።
ትናንትም ዛሬም ነገም የተከበሩ አቶ አንደርጋቸው ጽጌ መንፈሳቸው የነፃነት ደወል ነው። የከፈሉት መስዋዕትነት – የሚቀበሉት ስቃይ፤ ያዩት ፈተና የበለጠ እንድናከብራቸው – እንድንወዳቸው – አንድናደንቃቸው ያደርገናል። ሥማቸውን ስናሰብው በደማችን ሃዲድ ያበራል። ተግባራቸውን ስናሰላው በእዝነ ልቦናችን ያፈልቃል – ለምንግዜም። ግርማቸው – አንደበታቸው – ድርሳናችን ነው። የተግባር ሰውነታቸው የትም ይሁኑ የትም መንገዳችን ነው።
አንድ አስተዋይና ሳቂተኛ ንፋስ ይመጣል – አውሬን ለማሰናበት።
ሁሉን ለሰጠ ጀግና ክብራችን የሰንድቕዓላማችን ያክል ነው!
ጀግኖቻችን መርሆቻችንና መንገዶቻችን ናቸው።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles