Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ህልም እንደ ፈቺዉ ነዉ  –ሰመረ አለሙ   

$
0
0

ሰመረ አለሙ

tplfአንዳንዴ አያድርስ ነዉ ነገር በየት በኩል እንደሚያፈተልክ አይታወቅም:: ኢትዮጵያ የምትወጋበትንም ሆነ የምትወጋበትን የጦር መሳሪያ ህወአት እየገዛ ለኤርትራ የሚያቀብለዉ ደባ ያልጣመዉ አንድ ወዳጂ በቅርቡ ወደ ኤርትራ በተወሰደዉ አንጀት አርስ ሄሊኮፕተር MI 35 ምክንያት ሲበሳጭ እኔም ያማደርገዉ ባጣ ብስጭት ጥቅም የለዉም መላ መፈለግ ነዉ ብዬ ብመክረዉም የዜግነት ግዴታህ እስከዚህ ድረስ ነዉ በማለት በንቀት ተመልክቶኝ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ይዞ ተሰወረ።  ይህ መሳሪያን የሚያከበር  ትንታግ የሆነ የቀድሞ የአየር ወለድ ባልደረባ የእሱ መንገድ ከኔዉ  የተለየ ሁኖ ዉስጥ ዉስጡን ሲሰራ ቆይቶ በሀገር ፍቅር ሰሜት ልባቸዉ የነደደ ከዘር እና ሀይማኖት በላይ ዘራቸዉና እምነታቸዉ ኢትዮጵያዊ የሆነ በደግነት፤በጀግንነት፤በቆራጥነት መስፈርት ጣራዉን የነኩ በቅርብ የሚያዉቃቸዉን የ50 አለቃ ስንሻዉ በላይነህንየ10 አለቃ ጣፋ ኢዶሳን፤ ቆራሄ ላይ በተደረገዉ ጦርነት ቦታዉን ሳይለቅ ለኢትዮጵያ ሀገሩ ሰማእት ስለሆነዉ ስለ ደጃዝማች አፈወርቅ አባቱ ዘወትር ሲተርኩለትና በኢትዮጵያዊነት መንፈስ እያነጹ ያሳደጉት የሀረሩ መምህር አብዱረህማን ኡስማን፤ በትምህርት ደረጃዉ እና በሀገር መዉደድ ስሜቱ የሚነገረለት ዘለቀ ማንደፍሮ፤ ከትግራይ የፈለቁ ጉዶች ኢትዮጵያ ላይ እንዲህ ያለ በደል ሲያደርሱ ቁጭቱን ለመወጣት ቀን ሲጠብቅ የነበረዉ የራስ አሉላ የልጅ ልጂ ነዉ ተብሎ የሚነገርለት ገ/መድህን ወ/ኢትዮጵያን ያካተተ በአካል ጥንካሬዉ፤ በወገን አፍቃሪነቱ ፤በሩቅ እይታዉ የታመነበት በኮማንዶ ቡድን መሪዉ በጌታቸዉ አበጋዝ አማካይነት በስዉር ምልመላ እና ስልጠና በማድረግ 150 አባላቱን በጥንቃቄ በ3 ቦታ በመክፈል በተለያየ ጊዜ ወደ ትግራይ ልኮ ሁኔታዉን ሲያዳምጥ ቆየ።

ይህ  የኮማንዶ ቡድን አረብኛ፤ትግርኛ፤አማርኛ፤አፋርኛ፤ኦሮምኛ  አቀላጥፎ መናገር በመቻሉ በቆየበት ቦታ ሁሉ ባይተዋርነት ሳይሰማዉ ጸጉረ ልዉጥ መሆኑ ሳይታወቅ ስራዉን በሚገባ አጠናቀቀ። በሳምንቱ በሶስተኛዉ ቀን ቀደም ሲል በወጣዉ ንድፍ መሰረት አካባቢዉን ካጠና በሗላ በሌሊት ትግራይ ዉስጥ ጠላትን ሳይሆን ወገንን ለማጥፋት የተከማቸዉን የመሳሪያ ዲፖ ጠባቂዎችን በማገት ለተልእኮዉ የሚረዳዉን ምርጥ ምርጥ መሳሪያ በመያዝ ሌሊቱን ተሰዉሮ በትግራይ እና በኤርትራ ክፍለ ሀገር ያለዉን አዋሳኝ ድምበር በመያዝ ሌሊት ሌሊት ብቻ በመጓዝ ቀን ቀን በፈረቃ በማረፍ ከትግራይ ጋር የተፋጠጠዉን የኤርትራን ጦር ወደ ጎን በመተዉ በአዲግራት በኩል ወደ ኤርትራ አመራ።   በአዲግራት መጠነኛ ዝግጂት ከተደረገ በሗላ በወጣዉ እቅድ መሰረት በመርሳ ፋጡማ እና አዲ ቀይ መሀል ለመሀል በመሰንጠቅ ቡድኑ ቀይ ባሕር ደረሰ።  ይህ መንገድ ሊመረጥበት የቻለዉገ/መድህን ወ/ኢትዮጵያ በዚህ አካባቢ የአሉላ አባ ነጋ ርዝርዦች በብዛት ከመገኘታቸዉም በላይ አጋሜ በኤርትራና በአዲሶቹ የህወአት ገዢዎች እንደ አደጋ ከመታየቱም በላይ አፍቃሪ ኢትዮጵያዊነቱም ከግምት በመግባት ነበር። ቡድኑ ከቀይ ባህር በሞተር ጀልባ እስከ ምጽዋ በመብረር በደረቅ መሬት አካባቢ በተገኘዉ ተሺከርካሪ በመጠቀም ሌሊቱን አስመራ ከተማ ገባ።

ትግራይ ዉስጥ የመሳሪያዉ ዲፖ መዘረፉ ከጆሮ ጆሮ ተላልፎ ህዘቡ ዘንድ በመድረሱ ይህ ነገር በወገን መደረጉን የጠረጠሩ አፍቃሪ ኢትዮጵያዉያን ደስታቸዉን ሲገልጹ የጊዜዉ ተጠቃሚዎችና ጥቅሜ ሊነካ ይችላል ብሎም አደጋ ሊፈጠር ይችላል  ብለዉ የሰጉ የህወአት አባሎች ስጋትና ብስጭት ተጨማምሮባቸዉ ለጭንቀታቸዉ ማሳረፊያ ይረዳናል በሚል አብዝተዉ አረቄና አቅል መግዣ ኪኒን ቢወስዱም በየጊዜዉ የሚሰማዉ ወሬ ሰላም ሊሰጣቸዉ ባለመቻሉ የደም ግፊታቸዉ አለአግባብ ጨምሮ ለመኮብለል፤ ንብረት ለመሸጥ፤ ለማሸጋገር ጊዜ ባለማግኘታቸዉ የሚያደርጉት መላ ጠፍቷቸዉ ብቻቸዉን ማዉራትና መቃዠት ይዘዉ ነበር።

ቀደም ሲል እንደ ተገለጸዉ ወደ ተልእኮዉ ሲመጣ በተለይ የ 50 አለቃ ስንሻዉ በላይነህ እና የ10 አለቃ ጣፋ ኢዶሳ አስመራ ለ10 አመት ከመቆየታቸዉም በላይ በዛ ቤተሰብ አበጂተዉ ቋንቋዉንም ባህሉንም በመጋራታቸዉ የአስመራን መግቢያ መዉጫዉን በሚገባ ከማወቃቸዉም በላይ ትግርኛን አቀላጥፈዉ ስለሚናገሩ ለተልእኮዉ መሳካት የጠረጠረ አባል አልነበረም። ከላይ በተጠቀሰዉ አይነት ይህ ለ3 የተከፈለዉ የኮማንዶ ቡድን በዉድቅት ተስቦ የመጀመሪያዉ ቡድን አስመራ ወደ ታገቱት የጦር መኮንኖች ሲገሰግስ ሁለተኛዉ ቡድን ሽፋን እና ከለላ ሲሰጥ 3ኛዉ ቡድን ታጋቾቹ እስኪመጡ የጦር አዉሮፕላኖቹ ያረፉበትን ቦታ በርቀት በንቃት ይጠብቅ ነበር። የኢትዮጵያ የአየር ሐይል አብራርዎችን እና ወያኔ በሀገር ዉስጥ የሚያደርሰዉን ጥፋት የጠሉና በኤርትራ በኩል ኢትዮጵያን ነጻ እናወጣለን ብለዉ አረመኔዉ ኢሳይያስ አፈወርቅ እጂ የወደቁ ኢትዮጵያዉያንን የማስለቀቁ ተቀዳሚ ተግባር ለመጀመሪያዉ ቡድን ተሰጥቶ ጉዞዉ በአስቸኳይ ወደ እስር ቤት ሆነ።

በአስመራ የአጋቾቹ ዘበኞች ለጭንቀት እንዲረዳቸዉና ረሀባቸዉን እንዲያሰታግስላቸዉ ቪኖ አብዝተዉ በመጠጣታቸዉ ይህ የኮማንዶ ቡድን ከቅዠታቸዉ ቀስቅሶ መሳሪያቸዉን በመረከብ ቁልፋቸዉን ከወሰደ በሗላ ኢትዮጵያኑን እስረኞች “አትደናገጡ የወገን ጦር ነዉ አገራችሁ ትፈልጋችሗለች” የሚል ወገናዊ ማረጋገጫ ቃል ሰጥቶ ከአካባቢዉ በተገኘዉ መጓጓዣ በመጠቀም ወደ ሚጠብቃቸዉ እና መለስ ዜናዊ ወደ ሰጣቸዉ አዉሮፕላኖች ገሰገሰ። እዚህ ላይ ሰብአዊነትን የተላበሰዉ የቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር እና ይህ የኮማንዶ ዩኒት በሰዉና በእንሰሳ ምንም ጉዳት እንዳይደርስ ተቀዳሚ ተግባሩ አድርጎ እነዚህ ለእንጀራ ብለዉ ስርአቱን ያገለገሉ ዘበኞችን የእነሱ ያለመኖር ቤተሰቦቻቸዉ ላይ የሚያደርሰዉን ጉዳት በመረዳት ምንም አደጋ ሳያደርስ አይዟችሁ እናንተንም ነጻ እናወጣለን ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር ብሎ ያደረገዉ ስንብት እነዛ ጠባቂዎች ላይ የፈጠረዉ ወገናዊነትና የስልጣኔ ተምሳሌነት ይህ ነዉ ብሎ መገመት አይቻልም ነበር። እንደዉም በሗላ ኤርትራ ዉስጥ ለተነሳዉ ኢትዮጵያዊነትን ፍለጋ በግምባር ቀደምትነት “ኢትዮጵያ ወይም ሞት” ብለዉ ትልቅ መፈከር ይዘዉ ከህዝቡ ፊት ለፊት ሰልፈኛዉን ይመሩ እንደነበር ከፎቶግራፍ የተገኘዉ መረጃ ላይ ተመልክቷል።

ወያኔ ለኤርትራ ያሳለፈዉን የኢትዮጵያ የአየር ንብረቶች በአረመኔዉ ኢሳይያስ አፈወርቅ የታሰሩት ጀግኖች ተለቀዉ ዳግም አብራሪዎቹ እና ተዋጊዎቹ አዉሮፕላኖች ሲገናኙ የነበረዉ መንፈስ እናቷን በናፈቀች ጥጃ ይመሰል ካልሆነ ሌላ ተቀራራቢ ነገር ሊገኝለት አይችልም ነበር። የታጋቹ ብዛት ይሄ ነዉ ሊባል ባለመቻሉ ኤርትራ በዉሰት ይሁን በምጽዋት የተገኘ አንድ አዉሮፕላን ለዚሁ ተግባር እንዲዉል ተመድቦ  የታገቱት ወገኖች በሙሉ ወደ ሀገራቸዉ ባስቸኳይ ጉዞ እንዲያደርጉ ተደረገ።  የኢትዮጵያ ጀግኖች ጢያራቸዉን አሙቀዉ አዲዮስ አስመራ ብለዉ በተራ በተራ እየተነሱ ወደ ታላቋ ኢትዮጵያ አየር ክልል ከመድረሳቸዉ በፊት ሁኔታዉ በታሰበዉ መልኩ መካሄዱን ሲቆጣጠር የነበረዉ MI 35 ቡድን እስክንገናኝ ብሎ በኢሳይያስ አፈወርቅ ለታገተዉ ለኤርትራ ህዝብ መልካም ምኞቱን በመግለጽ እንደ ሌሎቹ ሁሉ ኢትዮጵያ አየር ለመድረስ ይጣደፍ ጀመር።  እነዚህ ከጠላት የተማረኩ የኢትዮጵያ ንብረቶች ወደ ሀገራቸዉ ሲገቡ የኢትዮጵያ ክልል እነሱን ለመቀበል ቀድሞ አስቦበት የተዘጋጀ ይመስል ዝናብም ፤ንፋስም፤ ደመናም ከሀገሩ ጠፍተዉ ጥርት ያለ ሰማይ በመሆኑ አብራሪዎቹ አቅጣጫ ማሳያዉ ላይ ብዙም ትኩረት ሳይሰጡ  ያለ ችግር በትግራይ አልፈዉ ወልቃይት ጠገዴን ታክከዉ አፋርን ኢትዮጵያዊነቱን አድንቀዉ ደብረ ዘይት የአየር ክልል ከማረፋቸዉ በፊት የናፍቆት ያህል ነዉ መሰል የደብረ ዘይትን ሰማይ አንድ አራቴ ከዞሩ በሗላ ተራ በተራ  አረፉ። “ደብረ ዘይት አለ አንዱ መኮንን የወጣትነት ትዝታችን ለሀገራችን ለመሞት ቃል የገባንላት ምድር” በማለት የደብረ ዘይት አየር እንደ ናፈቀዉ ነገር ሁሉ   ሳምባዉ መያዝ ከሚችለዉ በላይ ወደ ዉስጥ አስገባዉ።

ታድያ ወስጥ ዉስጡን በጣም ጥብቅ በሆነ ምስጢር ወጣቱ ከቀደሙት ምክር እየጠየቀ አገር ምድሩ ወያኔ ላይ አምጾ ኑሮ ደብረ ዘይት እነሱ ለማረፍ በማኮብኮብ ላይ እያሉ በሀገር ፍቅር ልባቸዉ የነደደ የአየር ሀይሉ አባላት ላለፉት 23 አመታት ቁም ስቅል ሲያሳዩት የነበሩትን ዘረኞች፤ እነዚህ ወገን ከወገን ተናቁሮ እንዲኖር በየጊዜዉ ደባ የሚፈጽሙትን፤ እነዚህ ሰዉ በማሰር፤ በመግረፍ፤በመግደል ልባቸዉ የማይነካ የዲያብሎስ መልእክተኞችን፤ የአገዛዙ ተወካዮችን ሰብሰብ አድርጎ በጥብቅ የተጠበቀ ባዶ ክፍል በጥሩ ቁልፍ በመከረቸም በሩ ላይ ታሺጓል ፍርዳቸዉን ከኢትዮጵያ ህዝብ ያገኛሉ የሚል ወረቀት አትሞ ባስቸኳይ የኢሜል፤ የቴክስት፤ የስልክ ምልልስ ለህዝባችን ተሰራጭቶ እነዚህ በባእድ ሀይል የተጫኑብን ኢትዮጵያዊ መንፈስ ልባቸዉ ዉስጥ የላደረ ባንዳ መሪዎችን ሀገር ለቀዉ እንዳይወጡ በባህር፤በየብስ፤በአየር ዜጋ በተጠንቀቅ እንዲጠብቅ መልእክት ተላለፈ።

በአዲስ አበባ የህዝብ ቁጣ ተቀስቅሶ ከየአቅጣጫዉ ወደ ቤተመንግስት የሚጓዘዉን የሚያስቆም ሀይል በመጥፋቱ የመከላለከያ ሰራዊት፤የፖሊሰ ሀይል፤ ፌደራል ፖሊስን ጨምሮ እኛ ከህዝብ ጋር ነን እኛ ለእንጀራችን ብለን ነዉ እያሉ የጭንቅ ቀን ተማጥኖ ሲያቀርቡ  በሀይማኖት፤በብሄር፤በተለያየ የመከፋፈያ ዘዴ ኢትዮጵያን ቁም ስቅል ሲያሳዩ የነበሩት አማራ ሳይሆኑ አማራ ኦሮሞ ሳይሆኑ ኦሮሞ የሆኑትም ከያሉበት እየተለቀሙ ኢትዮጵያዊ አስተዳደር እስኪመሰረት የሀገር ሺማግሌ እና የተከበሩ ምሁራን አቅጣጫ እስኪየመላክቱን በጥብቅ እንዲቆዩ ለአካባቢዉ ሚልሺያ ከአደራ ጋር ተሰጡ።  ኢትዮጵያ በዘር ስትከፋፈል፤ኢትዮጵያዉያን እንደ ዉሻ በየቦታዉ ሲደፉ ወገናዊነቱ ለዘሩ ብቻ የሆነ የፓርላማ ወንጀለኛ በሙሉ እንደ ደብረ ዘይቱ ወንጀለኞች ሁሉ በተዘጋጀላቸዉ ማረፊያ ተወስደዉ በሩ ላይ እንደ እናንተ ሳይሆን ሚዛን ባለዉ ፍርድ ፍርዳችሁ ይታያል የሚል ማህተም ታትሞ ለተበቂያቸዉ ተሰጡ።

ይኸዉ የኮማንዶ ቡድን ሀይልን ጨምሮ በኢትዮጵያዊነት ምግባር የተመሰገኑ ከዘር አመለካከት የጸዱ የጦሩን ሀላፊዎች ይዞ ወደ ጎንደር ሲያቀና መለስ ዜናዊ ያላግባብ የቸረዉ የጎንደር መሬታችን ላይ የሰፈሩት የዉጭ  ሀይሎች ሁኔታዉ ስላላማራቸዉ አካበቢዉን ጥለዉ  በመፈርጠጣቸዉ  የጎንደር ህዝብ ከዚህ ህዝባዊ ጦር ጋር በመሆን ችካሉን ተዎድሮስ/ዮሐንስ/ምንሊክ፤ሐይለስላሴ ባቆዩለት ድምበር ላይ ቸከለ። በዚህ  ትልቅ ፌሺታ ተካፋይ ለመሆን  በበሺታ ምክንያት አልጋ ላይ የቀሩ ጎንደሮች ዛሬን ብቻ ድምበሩ ላይ አድርሱን ስንሞት አትቅበሩን ብለዉ በማስቸገራቸዉ በወሳንሳ ወደዛዉ ተወስደዉ በአሉን በአይናቸዉ እንዲያዩ ወጣቶች ልዩ ትብብር በማድረጋቸዉ በአሉ ልዩ መልክ ያዘ። ብቻ የዛን ቀን በደስታ ብዛት ህዝቡ አብዝቶ በመተኮሱ የዱር አራዊት ለብዙ ጊዜ ሰላም አጥተዉ መክረማቸዉ  በጣም ተምረናል የሚሉ ከፈረንጂ አገር የተመለሱ የጎንደር ተወላጆችን ትንሺ እንዳሳሰበ በጉርጉምታ መልክ ተሰምቶ ነበር። ለነገሩ ልክ ነዉ አራዊቱስ አገራቸዉ አይደል?

የጎንደር መሬት ወደ ኢትዮጵያ ተካሎ ጎንደር በኢትዮጵያ ባንድራ ስታቆጠቁጥ በጋምቤላ ለሱዳን እና ለህወአት ደጋፊዎች አለአግባብ የተሰጠዉ መሬት ያበሳጨዉ ህዝብ በመንግስት ሀላፊዎች ላይ ያልታሰበና ያልተጠበቀ እርምጃ በመዉሰዱ ኦባንግ ሜቶ ዘንድ ባስቸኳይ መልእክት ተላልፎ እሱም ጓዜን ንብረቴን ሳይል በተከታዩ ቀን አዲሰ አበባ በማረፍ ሌሊቱን ተጉዞ ጋምቤላ ገብቶ ከህዘቡ ጋር ተገናኝቶ በመሀከላቸዉ ወያኔ የፈጠረዉን ጠላትነት (አንዋክ፤ ኑዌር፤አማራ) አርግቦ የጋምቤላ ህዝብም እንዲሁ አላግባብ የተወሰደበትን መሬት በቁጥጥሩ ስር በማድረግ ወያኔ የሰጠዉን ከፋፋይ ባንድራ በማቃጠል ደማቅ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ባንድራችንን ከድምበር እንጨት ባልተናነሰ መልኩ በሰፊዉ ዘርግቶ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር እያለ ህዝቡም ኦባንግ ሜቶን ወደ ላይ እየወረወረ ሲቀልብ ኢትዮጵያ ዳግም ኢትዮጵያ ለመሆን መዘጋጀቷን አመላካች ነገር ሆነ።

በትግራይም የእነ አሉላ አባነጋ የመንፈስና የስጋ ዝርያዎች ባንዳ ሲነግስ ጊዜና ቅዝምዝምን ዝቅ ብሎ ማሳለፍ ነዉ እንዲሉ አድፍጠዉ ጠብቀዉ ይህ ሁኔታ ሲፈጠር የአጋሜ ህዝብና አፍቃሪ ኢትዮጵያ የትግራይ ተወላጆች ሰልፋቸዉን ከኢትዮጵያ ህዝበ ጋር አስተካከሉ።  ኢትዮጵያዊነታቸዉን በሚወዱ ጥቂት የትግራይ ወጣቶች የተቀሰቀሰዉ አመጽ አደዋ የቀረዉ የምንሊክ ጦር ባለዉለታቸዉ መሆኑን ያስታወሱ ታላላቅ ሰዎችና ወጣቶች በወያኔ መሪዎቻቸዉ ላይ ተቃዉሞ በማሰማታቸዉ ከተቃዉሞም አልፎ ወደ እርምጃ በመሸጋገራቸዉ ይህ ነገር በዚህ ከቀጠለ ከፍተኛ የሰዉ እልቂት ሊፈጠር ይችላል በሚል ስጋት ኮሚቴዉ ወደ ክቡር አቶ ገ/መድህን አርአያ በአስቸኳይ የቴሌግራም መልእክት አስተላለፈ። አቶ ገ/መድህን ከአዉስትሬሊያ ተጉዘዉ ጉዳዩን ከማለዘባቸዉ በፊት የአሉላ አባ ነጋ የመንፈስ ልጆች በትግሬነት ስም ከኢትዮጵያዊነት ያቆራረጡዋቸዉን የህወአት ተወካዮች በደም ፍላት ዋና ዋና የሚባሉትን ተኩሰዉ በመጣላቸዉና የነሱን ንብረት በእሳት በማጋየታቸዉ የአቶ ገ/መድህን ባስቸኳይ ወደዚህ ቦታ መገኘት ከምንም በላይ አማራጭ የሌለዉ መፍትሄ ሁኖ ተገኘ።

ለአቶ ገ/መድህን አርአያ የተላከዉ መልእክት ብዙ ገጽ የያዘ ሳይሆን  ኢትዮጵያ ትፈልግሀለች የሚል ብቻ ነበር። ይህንን ያነበቡት አቶ ገ/መድህን ነገሩ ስለገባቸዉ አጠገባቸዉ ካለዉ ወዳጃቸዉ ገንዘብ ጠይቀዉ ከቤታቸዉ በአል ብቻ ሲሆን የሚለብሱትን ጃኖ አንጠልጥለዉ ወደ አዉሮፕላን ማረፊያ ባስቸኳይ በመሄድ ለሸኛቸዉ ወዳጃቸዉ ከቀረሁም ከመጣሁም አደራ ብርቱ ሰነድ እቤት ትቻለሁና  በህይወት ካልተመለስኩም ለፕሮፌሰር ሐ/ማርያም ላሬቦ በጥንቃቄ ይድረስልኝ በማለት ከሜልቦርን አዉስትሬሊያ በትራንዚት አድርገዉ ወደናፈቋት የትዉልድ መንደራቸዉ እና አገራቸዉ ጉዞ ጀመሩ። አቶ ገ/መድህን ለፕሮፌሰር ሐይለ ማርያም  ላሬቦ እንዲደርስላቸዉ የፈለጉት ሰነድ ምን መሆኑ ባይታወቅም ሐይሌ ላሬቦ ለሚጽፉት ለወያኔ ታሪክ ይረዳቸዋል በሚል ሳይሆን እንዳልቀረ ይገመታል። አቶ ገ/መድህን በጥያቄያቸዉ መሰረት አሉላ አባ ነጋ አየር ሜዳ ጃኖዋቸዉን ለብሰዉ በክብር ሲወርዱ  ለዚህ ላደረሳቸዉ አምላክ እግራቸዉ መሬቱን እንደነካ ተንበርከከዉ ምስጋና አቀረቡ።  ለክብራቸዉ በተደረገዉ ትልቅ ሰልፍ በየቦታዉ ከሚዉለበለዉ ከእዉነተኛዉ የኢትዮጵያ ባንድራ ጎን የተሰለፈዉ ወጣት ጋር ትእይንቱ ሲታይ የትግራይን ነጻ መዉጣት አመላካች  ሆነ።  አቶ ገ/መድህን ወደ መቀሌ በማምራት በዛ ከሀገር ሺማግሌዎች ጋር መከሩ። አቶ ገ/መድህን እንደዛ ሲያላግጡባቸዉ ሊገድሏቸዉ ሲያሳድዷቸዉ የነበሩ የቀድሞ ፋሺስት ባለስልጣኖች ካሁኑ ፍርድ ጠባቂዎች ጋር አይን ለአይን ሲተያዩ አምላካቸዉን በድጋሚ አመሰገኑ ትግራይም ያ ሁሉ ነዉጥ ያ ሁሉ ሺብር አቶ ገ/መድህን አርአያ በሙሴ ብትር እንደነኩት ሁሉ ጸጥ አለ።

በሰሜን ያለዉ ሁኔታ ይህን ሲመሰል ኦሮምያ ክልል በቋንቋ፤በሀይማኖት በተፈበረከ ጠላትነት ህዝቡን ሲያፋጁት የነበሩ ከአረብ ጋር ባላቸዉ ንክኪ የነጁዋር መሀመድ ደቀ መዝሙሮች እየተለቀሙ ኢትዮጵያዊ ስልጠና ሲሰጣቸዉ በደል የደረሰባቸዉ ዜጎች ስለደረሰባቸዉ በደል ሳይዉል ሳያድር ፍርድን ይጠይቁ ገቡ። አገርህ አይደለም እየተባሉ መንገድ የተጣሉት ፤ቤተሰባቸዉ የተበተኑት ይህ ቀን ዳግም ይመጣል ብለዉ ባለመጠርጠርጠራቸዉ ሁሉም እንደየ እምነቱ አምላኩን አመሰገነ። እዚህ ላይ የ10 አለቃ ኢዶሳ ኦሮሞን የኦሮሞ ብቻ የደረገዉ ማነዉ? አማራን የአማራ ብቻ ያደረገዉ ማነዉ? ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ ከሰፈሩ ወጥቶ በማንኛዉም የኢትዮጵያ ግዛት አርሶ፤ነግዶ፤ሰርቶ እንዲኖር አዲሱ እምነታችን ያዛል። ልጆቻችን በዉጭ ሀገር ስልጣን ይዘዉ ሲሰሩ ለ1000 አመታት ሲጋባ ሲወልድ በሀገሩ የኖረን ህዝብ ለመለያየት ካለመቻሉም በላይ የዚህ ሀሳብ አራማጆች ከሚናገሩት በላይ ከእምነታቸዉ ጀርባ ያለዉ ተንኮል ሊመረመር ይገባል ብሎ በሳል አስተያየት በተለያዩ በኦሮሞ አካባቢዎች በመስጠቱ እናዉቃለን የሚሉትን ምሁራንም ጭምር አስገርሞም አስደስቶም ነበር።

እዚህ ላይ ኢትዮጵያ ካላት በላይ የሰጠቸቻቸዉ በተለያዩ የአለም መድረክ እንድትወክላቸዉ የሾመቻቸዉ ወደ ዉጭ ልካ ያስተማረቻቸዉ ታላቅ ስራም የሰጠቸቻቸዉ የዘር ድርጂት የፓርላማ አባሎች የበሉበትን ወጭት ሰባሪ ሁነዉ በመለሰ ዜናዊ ፓርላማ ኢትዮጵያ የምትጠፋበትን ፕሮግራም ሲያጸድቁ የነበሩ ዘረኞች ለክብራቸዉ ሳይሆን ለሆዳቸዉ ያደሩትን የ10 አለቃ ኢዶሳ ቀና ብሎ እነሱን በማየት በግሰጼ ሲመለከታቸዉ  የመንፈስ ድህነታቸዉ በጉልህ ይታይ ነበር። የ10 አለቃ ኢዶሳ እዚህ ላይ ሳያቆም እነሱን በንጽጽር ከአብዲሳ አጋ፤ከጄነራል ጃገማ ኬሎ፤ከይልማ ዴሬሳ፤ከነገበየሁ ባልቻ ጋር በማነጻጸር  ኢትዮጵያዊ ትምህርት ሰጥቷቸዉ ላደረሱት በደል የተቋቋመዉ ኮሚቴ እንደሚመረምረዉ  ማስታወሻ ሰጥቶ ወደ ቀጣይ ፕሮግራሙ ተዘዋዉሯል።

ኮሚቴዉ በአስቸኳይ የኢትዮጵያን ግዛቶች ማዳረስ ቢገባዉም ወደ ደቡብ በአፋጣኝ ለመሄድ አልቻለም። የደቡብ ህዝብ ቀደም ብሎ የመለሰ ዘራዊ ተንኮል ስለገባዉ አማርኛ የጋራ መግባቢያችን ነዉ ቋንቋን በግድ ተማሩ ብሎ ማስተማር የማይሆን ነዉ በቋንቋችን በትእዛዝ ሳይሆን በፍቃዳችን እንናገራለን ከሌሎች ኢትዮጵያዉያን ወንድሞቻችን እንደ መሸጋገሪያ ድልድይ አማርኛን እንጠቀማለን በማለታቸዉ በመለስ ዜናዊና በአሁኑ ሐይለማርያም ትእዛዝ በሄሊኮፕተር መትረየስ ቢታጨዱም ኢትዮጵያዊነታቸዉን የሚያስተዉ ነገር ስላልተገኘ  ከኮሚተዉ ጋር በስልክ ብቻ እየተገናኙ አካባቢያቸዉን ይቆጣጠሩ ነበር። ሆኖም የዚህ ከፋፍለህ ግዛ ተሳታፊዎች እና ሆድ አደሮች እዚህ ንጹህ እንቅስቃሴ ላይ መርዛቸዉን እንዳይረጩ አንኳር አንኳሮቹ እየተለቀሙ ፍርዳቸዉን እንዲጠብቁ ተወሰነ። ኮሚቴዉ ጊዚያዊ ፋታ ሲየገኝ ወያኔ ወልቀይት እና ጠገዴ፡ በአማራዉ ክልል እና አማራዉ በሰፈረባቸዉ ቦታዎች ባደረገዉ አስዳደሪያዊ በደሎችና ወንጀሎች በተለይም የዘር ማጽጃ እርምጃዎች ፤በአፋር፤እና በተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛቶችም ጭምር የተፈጸመዉን ወንጀል እና በደል በአግባቡ መርምሮ ለብሄራዊ ፍርድ ቤት ለማቅረብ ቃል ከመግባቱም በላይ በተመሳሳይ ሁኔታ አፋር እና ሱማሌም በህወአት በተፈጸመባቸዉ ወገኖች  የዚህ ስርአት አራማጆች ለፍርድ እንደሚያቀርብ ቃል ሰጥቶ የሚቀጥለዉ አጀንዳዉ ለምሁራኑ ጥሪ በማድረግ ከዘር፤ከሀይማኖት፤ኢትዮጵያዊ ካልሆነ አስተሳሰብ የጸዳ አመራር እንዲቋቋም ለምሁራኑ ቡድን አሳስቦ በገለልተኝነት ነገሩን መመልከት ያዘ።

 

እንግዲህ እንዲህ ያለ ህዝባዊ አመጽ በጥሩ መሪ ካልተደገፈ ከበጎ ጉኑ ክፉዉ ያመዝናል የሚል ድምጽ እየጎለበተ ስለመጣ በአዉሮፓ፤ አሜሪካ፤ካናዳ፤አዉስትሬሊያ የሚኖሩ ወገኖች ዘወትር የህዝባቸዉ ችግር ችግራቸዉ የሆነ ምንም እንኳን እነሱ የተደላደለ ኑሮ ቢኖሩም የህዝባቸዉን ፍዳ ማየት ከህዘቡ ባላነሰ ሁኔታ የሚሰማቸዉ  ኢትዮጵዉያን ምሁራን በዚህ ችግር ጊዜ ከህዝባቸዉ ጋር እንዲቆሙ መጥተዉም አመላካች የሆነ ነገር እንዲጠቁሙ ሀገር ዉስጥ ካለዉ ሀገር ወዳድ ምሁር  ጋር በመመሳጠር ለኢትዮጵያ የሚበጂ ነገር እንዲፈልጉ ጥሪ ተላለፈ። ከአሜሪካ ከአዉሮፓ እንዲሁም ከተለያዩ የአለም ክፍል የሚጎርፈዉ ምሁር ሲታይ ኢትዮጵያዊ ምን ያህል አገሩን እንደሚወድ ጉልህ ማስረጃ ሆነ። ከነዚህም ከሩቁ ከተስተዋሉት መሀል ኢንጂነር ዘዉገ አስፋዉ፤ዶ/ር አክሎግ ቢራራ፤ ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ፤ዶ/ር አሰፋ ነጋሺ፤ ዶር ፍቃዱ በቀለ፤ ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ፤ፕሮፌሰር ክንዴ አየለ፤ዶር ነገደ ጎበዜ፤ ዶ/ር ኦላና ፤ፖል ትዋት፤ ፡አምባሳደር ዘዉዴ ረታ፤የስዊድኑ አባ ጃፈር እና ከብዛታቸዉ የተነሳ ስማቸዉን ማስታወስ ያልተቻለዉ ፕሮፌሰር ጌታቸዉ ሐይሌን አስቀድመዉ ቦሌ አየር ማረፊያ ሲደርሱ እንኳን ለአገራችሁ አበቃችሁ በማለት ድፍን የአዲስ አበባ ህዝብ ታይቶ ተሰምቶ በማይታወቅ አቀባበል ደስታዉን ገለጸ። ይህን አሳዛኝ እና የደስታ ግንኙነት ለህዝቡ በምሁራኑ ስም መልእክት እንዲያስታልፉ እድሉ ለሊቀ ሊቃዉንት ፕሮፌሰር ጌታቸዉ ሐይሌ ተሰጥቶ በምሁራኑ ስም ንግግራቸዉን ከመጀመራቸዉ በፊት ይህንን ሰሜት ማስታመም ስላልቻልኩ ስሜቴንም መቆጣጠር ስለተሳነኝ ከታላቅ አክብሮት ጋር የማስተላልፈዉ መልእክት ለሌላ ቀን ይሁንልኝ ኢትዮጵያን አምላክ ይጠበቅ፤ ያለፈዉ አይነት ስርአት አይመለስብን በማለት እንደ ልመናም እንደ ቁጭትም ብስጭትም በተቀላለቀለበት ስሜት አንገታቸዉን ዝቅ ሲያደርጉ ፕሮፌሰር ጥላሁን ይልማ ለሀገሩ ሊያበረክት ይችል የነበረዉ ታስቦት ኣቀረቀረ በሀገር ወዳድነቷ የዘመኑ ጣይቱ የተባለቸዉ ዶ/ር አበባ ፈቃደ በምሁራኑ ስም ድርሻዋን ለመወጣት ቃል ሰጠች። እነዚህ  አንጋፋ ምሁራን በተለያየ ጊዜ በተለያየ ሀላፊነት የሰሩ ስራቸዉን ወያኔ በርካሺ ፕሮፓጋንዳ ያሳደፈባቸዉ ዜጎችን ጨምሮ ከምን ጊዜም ባላነሰ በዚህ በአዲሱ ግምባታ እንደሚሳተፉ ቃል ሲሰጡ በዚህ ሁኔታ ሊካፈሉ ያልቻሉ ባሉበት አገር የበለጠ ግልጋሎት ለኢትዮጵያ አገራቸዉ ሊሰጡ የሚችሉ የአሜሪካ የጠፈር አግልግሎት ሊቃዉንት  በቪዲዮ በተለቀቀ መልእክት ለምሁራኑ ቡድን መልካም ምኞታቸዉን አሰተላልፈዉ ለታሪክ ማስታወሻነቱ በቪዲዮ ተይዞ እንዲቆይ ጠይቀዋል።

በመሀል ሀገር እንዲህ ያለ ጊዜ የማይሰጥ ሁኔታ ሲፈጠር ለካ ኤርትራ ክፍለ ሀገር ዉስጥ ዉስጡን ሲብላላ የቆየዉ ኢትዮጵያዊነት ስሜት ገንፍሎ ኢሳይያስ አፈወርቅን ለጉብኝት እንደወጣ ሲያስቀረዉ እዛ የሚኖሩት የእሱ አፋኝ ገዥዎች እና ተባባሪዎች  እየተለቀሙ ወደ እስር ቤት ሲገቡ አንዳንድ ኢሰብአዊ ጉዳት የደረሰባቸዉ ኤርትራዉያን በገነፈለ ሰሜት የራሳቸዉን እርምጃ እንደወሰዱ ተነገሯል። በዛ በኩል ያለዉ መሀል ኢትዮጵያ ካለዉ የተለየ ቢሆንም እነሱ ግን ኢትዮጵያ ወይም ሞት በማለታቸዉ ያለፈዉ ስህተት እንዳይደገም በማለት ጉዳያችሁ ላይ ይመከርበታል ተብለዉ ቢነገሩም  አሻፈረኝ በማለታቸዉ አገር ምድሩ በአረንጓዴ ብጫ እና ቀይ ባንድራ በመጥለቅለቁ የኤርትራን ህዝብ ጥያቄ ለማሟላት አዲስ የተቋቋመዉ ኮሚቴ ከኤርትራ ጋር ንክኪ ያላቸዉንና በኤርትራዉያን የተከበሩ ምርጥ ኢትዮጵያዉያንን  አቶ ጌታቸዉ ረዳን ጨምሮ ወደዛ እንዲጓዙ ትእዛዝ ተላልፎ ኮሚቴዉ ሁኔታዉን መከታተል ጀመረ። አቶ ጌታቸዉ ረዳ አስቦበት ይሆን ባጋጣሚ አይታወቅም በጥበብ ያቆጠቆጠ ኢትዮጵያዊ እጀጠባብ ጥለቱ የኢትዮጵያ ባንድራ የሆነ ለብሶ አስመራ ካረፈዉ አዉሮፕላን ዘሎ ከመሰላሉ ሲወርድ በአየር ማረፊያዉ የተሰበሰበዉ ኢትዮጵያዊነት የጠማዉ የኤርትራ ወጣት ልቅሶም ደስታም ተደማምሮበት የሚያደርገዉ ሲጠፋዉ ኮሚቴዉ መልእክት ለማስተላለፍ ቋንቋ ሲመርጥ አንድ የሀገሬዉ ሰዉ ቀረብ ብሎ ጌቶቼ ሀሳብ አይገባችሁ ሰዉ ኢሳይያስ እና ስርአቱን በመጥላት እንደ ተማከረ ሁሉ ተቃዉሞዉን ለመግለጽ  ከአማርኛ በስተቀር ምንም አይናገርም የሚሰማዉ ዘፈን ሁሉ የማህሙድ አህመድ ፤የጥላሁን ገሰሰን ፤የአስቴር  አወቀን ሲሆን ወጣቱ ደግሞ ቴዲ አፍሮን እንደ ማምለክ ይከጂለዋል ብሎ ማረጋገጫ በመስጠቱ  ግማሹ ተወካይ በአማርኛ ሲናገር ቀሪዉ ለምናልባት በማለት በትግርኛ፤ጣልያንኛ/አረብኛ ኢትዮጵያዊነትን ለኤርትራ ህዝብ በድጋሚ መስክሯል።

እንግዲህ በአንድ ትንሽ አጋጣሚ የተጀመረዉ ነገር  ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምእራብ ህዝብ ዉስጥ የነበረ ሰሜትን ቀስቅሶ በጥቂት ጊዜ ዉስጥ ኢትዮጵያዊነት ቦታዉን ሲይዝ ይህ የተገኘዉ ድል ከህዝብ እንዳያመልጥ እነዚህ ቱባ ቱባ ምሁራን የሀገር ዉስጥ ምሁራንን ጨምሮ በማሳሰባቸዉ ከዚህ በታች የተመለከተዉ ፕሮግራም ባስቸኳይ ተግባራዊ እዲሆን በእዝ ሰንሰለቱ ትእዛዝ ተላለፈ። የሚያሰራ ስርአት አጡ አንጂ ላለም የሚበቁ ምሁር ባሉባት ኢትዮጵያ በዉስኪ እና በጫት ሰክረዉ ሲመሩ የነበሩ ወሮበሉች ያበላሹትን የማስተካከል ስራ በነዚህ ምሁራን ላይ ወደቀ። በፍርድ፤በቴክኒክ ፤አስተዳደር፤በምጣኔ ሀብት ስራ ላይ አንቱ የተባሉ በትምህርት፤በስራ፤በኢትዮጵያዊነት ስነስርአት የታነጹ ዜጎችን ቦታ ቦታ በማስያዝ ስራዉ ይቀላጠፍ ገባ የኮሚቴዉ ተቀዳሚ ተግባራት።

  1. ወገንን ከወገን በሀይማኖት፤በዘር፤በክልል የሚያናቁሩ ፍልስፍናዎች እና ድንጋጌዎች ከዛሬ ጀምሮ ዉድቅ መሆናቸዉን ማስረገጥ
  2. ኢትዮጵያዊ ከሰሜን ኤርትራ እስከ ባሌ ከጎጃም እስከ ሀረር አፋር ድረስ አገሩ በመሆኑ በየትኛዉም ቦታ ተዘዋዉሮ ነግዶ ፤አርሶ፤ ሰርቶ መኖር እንዲችል
  3. ሀገር ላይ አደጋ በደረሰ ጊዜ ዜጋ ብሄራዊ  ግዴታዉን እንዲወጣ ሲጠያቅ አገሩ ክልሉ ብቻ ባለመሆኑ በየትኛዉም አካባቢ ተገኝቶ ብሄራዊ ግዴታዉን በደም እና አጥንት መክፈል ግዴታዉ መሆኑን ማሳወቅ፤፡
  4. ለወደፊቱ እንዲህ ያለ ጸረ ኢትዮጵያ የማፊያ ድርጅት እንዳይፈጠር ይህን እንዲያስታዉስ ብሄራዊ ሀዉልት ሰርቶ ይህን ክፉ ዘመን ለተተኪዉ ትዉልድ ተነግሮ ከዚህ አደጋ እራሱን እንዲጠበቅ ማድረግ
  5. የኢትዮጵያ ልጆች ከዚህ በፊት እንደተደረገዉ ሁሉ በአከባቢያቸዉ ብቻ ሳይሆን በየትኛዉም አካባቢ ተገኝተዉ እዉቀት እና ለምድ ብቻ መለኪያ ሁኖ ማስተዳደር እንዲችሉ ማድረግ።ኢትዮጵያዊዉ የወለጋ ተወላጂ ደጃዝማች ክፍሌ ዳዲ ጎንደርን ቀደም ሲል እንዳስተዳደሩ ሁሉ
  6. በነዚህ 20 አመታት የኢትዮጵያ ንብረት ገዥም ነጋዴም ሁኖ በቆየዉ በህወአት አባሎችና ድርጅቶች የተያዙና የተዘረፉ ንብረቶች ሁሉ በተደራጀ ኦዲተር ተመርምረዉ ንብረቱ ብቻ ሳይሆን ከየት እንዳመጡትና ባልከፈሉትም ታክስ በሀላፊነት እንዲጠየቁ ሲሆን ተነስ ተብሎ ፍርድ ለተጓደለበት ለቀድሞ ባለ መሬት እና ንብረትም ተመጣጣኝ ካሳ እንዲሰጥ
  7. በዶ/ር አክሎግ ቢራራ የሚመራ የኢኮኖሚስት ቡድን የሀገር አዋቂዎችን ጨምሮ ኢትዮጵያን ባፋጣኝ ወደ መሀከለኛ ገቢ የምትሸጋገርበትን የተግባር ፕሮግራም ባስቸኳይ መንደፍ እቅዱ ተግባር ላይ መዋሉን የሙያ አጋሮቻቸዉ አንዲቆጣጠሩ ማድረግ
  8. ህዝብን እና አገርን ከጠላት ለመከላከል እንዲያስችል በዘር፤በሀይማኖት፤በሰፈር ልጅነት ያልተማከለ ኢትዮጵያዊ ጦር ባስቸኳይ ማቋቋም። የኢትዮጵያ የመከላከያ መሳሪያዎችም ኢትዮጵያ አደጋ ቢደርስባት የቀለጠፈ አገግሎት ሊሰጡ በሚችሉበት ቦታዎች እንዲቀመጡ ማድረግ ሁኖ
  9. ይህንን ህዝባዊ ተልእኮ ኮሚቴዉ ግዳጁን እንዳይወጣ በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ ደንቃራ የሚጥሉት ሀሉ በተቋቋመዉ ፍርድ ቤት ቀርበዉ ተመጣጣኝ ፍርዳቸዉን እንዲያገኙ ማድረግ ተቀዳሚ ስራዉ አድረጓል።

*  ቁጥር 6 የተመለከተዉን ዘረፋ ንብረት ማሸሺ በዶ/ር ሼክሰፒር ፈይሳ እና በ ፕሮፌሰር አልማርያም የሚቋቋመዉ ግብረ ሀይል ቀደም ሲል ዶ/ር ሼክሰፒር ፈይሳ እንዳደረገዉ ሁሉ የህግ እዉቀቱን ተጠቅሞ ማስረጃ በማሰባሰብ በወያኔ አባሎች የተሰረቀዉ፤የኮበለለዉ የኢትዮጵያ ሀብት ወደ ሀገሩ የሚመለስበትን መንገድ በአፋጣኝ ተግባረዊ እንዲሆን ማድረግ።

*  አሁን ከነጻ አጥኝዎች በተሰጠዉ አሀዝ 16 ቢሊዮን ዶላር የኢትዮጵያ ሀብት በነዚህ ማፊያ ድርጅቶች አማካይነት ከሀገር በመኮብለሉ ለባለቤቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ ባስቸኳይ የሚመለስበት መንገድ እንዲፈለግና  እያንዳንዱ ዜጋም በዉጭም በሀገርም የሚኖር ለዚህ ምርመራ አስተዋጽኦዉን እንዲሰጥ ማድረግ።

*  በዚህ አጋጣሚ ከሀገር ዉጭ ሆነ ሀገር ዉስጥ የሚኖር ዜጋ በተለያየ መልክ በወያኔዎችና ረዳቶቻቸዉ ቁጥጥር ስር ያለዉን ሃብት የኮበለለበትን ሀገር፤ የንብረቱን አይነት፤ ግምቱን የሚያሳይ ዝርዝር ሼክስፒር ፈይሳ በሰጠዉ የመገናኛ መስመር አማካይነት ለግብረ ሀይሉ እንዲያሳዉቁ እንዲደረግ።

ይህ ጊዜያዉ የምሁራን እና የሀገር ወዳድ ኮሚቴ ለሀገራቸዉ ትልቅ ግልጋሎት ሰጥተዉ ለዚህ ጊዜ ሳይበቁ ላረፉት እንደ ጥላሁን ገሰሰ፤ሎሬት ጸጋዬ፤አፈወርቅ ተክሌ፤ኢንጂነር ቅጣዉ እጂጉ፤ሐይሉ ገ/ዮሀንስ (ጎመራዉ)  ለመሳሰሉት ዜጎች አንድ መታሰቢያ እንዲያቆም ተደርጎ ኢትዮጵያን በዘር በሀይማኖት በጎሳ የከፋፈለዉ ስርአት ከቅሪቱ ጋር ተወግዶ ህዝቡ ያለፈዉን ታሪክ ብቻ በማድረግ ወደፊት በፍቅር እንዲኖር የመገናኛ መስመሮች ኢትዮጵያዊነትን ብቻ እንዲያጎሉ አድርጎ ይቅር ለእግዚሀርን ጨምሮ ወደ ፊት በሰላም መኖር።

በዚህ ህዝባዊ ማእበል ቦታ እንደሌለዉ የተረዳዉ ጁዋር መሀመድ ከእንግዲህ ምን ቀረኝ ብሎ ወደ የመን ለሌላ ስልጠና ሲያቀና ተስፋዬ ገ/አብ የሚያናግረዉ ጠፍቶ ልቡን እንደ መንሳት ብሎት ቅቤ ሰጡኝ እያለ ከራሱ ጋር ሲያወራ የተመለከቱት ኢትዮጵያዉያን  በሀዘን መልክ ይሁን ወይም ክፉን በደግ በሚለዉ መርህ ተባብረዉ ትኩስ የፈለቀ ጠበል እንደወሰዱት ተነግሯል። ነገር መልክ መያዙ ኢትዮጵያዊነት ማበቡን የተረዱ የህዋአትን መሰረት የጣሉ አረጋዊ በረሄ፤ብስራት አማረ፤ሰየ አብረሀ የመሳሰሉት የቀድሞ ህወአቶች እንግዲህ ምን ቀረን ሰዉም ይጣላናል በማለት አስከሬናችንን ወደ ኢትዮጵያ አትላኩ ብለዉ በመናዘዛቸዉ ፈቃዳቸዉን ለመፈጸም ቤተ ሰብ በመጠባበቅ ላይ ነዉነዉ።

ለዚህ ሁሉ ታሪካዊ ተልእኮ ምክንያት ለሆኑት ጀግኖች ለክብራቸዉ በተደረገዉ ግብዣ ላይ  ምኞታቸዉ ሲጠየቅ የ 50 አለቃ ስንሻዉ በላይነህ እና የ10 አለቃ ጣፋ ኢዶሳ ቤተሰቦቻቸዉ በእድሜ ስለገፉ እነሱን በእርሻ እየረዳን ለመኖር ወደ መንደራችንን ወደ ቢቸና እና አርሲ እንመለሳለን ብለዉ ቃል ሲሰጡ መምህር አብዱረህማን እና ማንደፍሮ ዘለቀ ትንሽ ገንዘብ ፈልገዉ በትምህርታቸዉ ለመግፋት ምኞታቸዉ መሆኑን ሲገልጹ የተቀሩት ደግሞ ለጊዜዉ ባያስቡበትም እንኳን ሀገር ነጻ ወጣ እንጂ መተዳደሪያችንን ወደፊት እናስብበታለን ብለዉ ለተሰበዉ ህዝብ ሲገልጹ በዚህ ልቡ የተነካዉ ኢትዮጵያዊ ነጋዴ ይሄማ ሊሆን አይችልም ገና ሀዉልት እናቆምላችሗለን፤ ከዚህ የአረመኔ ስርአት፤ ከዚህ ነጋዴም አስተዳዳሪም፤ ዘራፊም ሰርአት የገላገላችሁን በማለት በአጭር ጊዜ ዉስጥ በቼክ እና በጥሬ ገንዘብ ለአባይ ግድብ በግዳጂ ከተዋጣዉ በላይ ለነዚህ ጀግኖች አዋጥተዉ በመስጠታቸዉ እነዚህ 150 ጀግኖች ቀሪዉን ዘመናቸዉን ስለኑሮዋቸዉ እንዳያስቡ ሁነዉ እንደ ሀሳባቸዉ ለመኖር የሚያስችላቸዉ ገንዘብ በመሰብሰቡ እነሱም ተሰብሳቢዉን አመስግነዉ በክብር ተሰናብተዉ ሲለያዩ በማስታወሻነት በግል የተበረከተላቸዉ ብቻዉን እራሱን የቻለ መጓጓዣ አስፈልጎት ነበር።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር።      እንግዲህ ለክፉም ለደጉም በዚህ ድረሱኝ semere.alemu@yahoo.com

The post ህልም እንደ ፈቺዉ ነዉ  – ሰመረ አለሙ    appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>