ከሥርጉተ ሥላሴ 08.02.2015 /ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ/
„የሰው ልጅ መንገድን ያዘጋጃል፤ እግዚአብሄር ግን አካሄዱን ያቃናለታል ምሳሌ 16 ቁጥር 9“
ደጉ ቀን። ዕንባ ዓለምዓቀፍ ዕውቅና አገኘ። ኑሮን ሳያውቁት ሞት የተፈረዳባቸው ጽንሶች መንፈስ አንደበትን – ከፈተ። ዕንቡጥ ተቀጥፎ ኢትዮጵያን ገነባን አለማን የተባለው የሀሰት ታሪክ ፉኛ እንሆ – ተነፈሰ። የሰው ልጅ ሥጋና ደም ቃጠሎ ጭስ እንሆ ሃቅን – አፈለቀ። እኛ በወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ ተቃዋሚነት የተሰለፍን በትክክል የቆምንበት ሃሳብ ሆነ መንገድ አመክንዮ በእርግጥም የነጠረ የእውነት መሰረት እንዳለው ምስክር ሆነ። ምዕራፍ!
ድል በማንኛው ቅርጽ ወይንም ፎርም ሊከሰት ይችላል። ውጤትም – እንዲሁ። ጥረትና ሰብሉም በመሰሉ መንገድ። የነፃነት ትግሉ ወደ ኋላ ለማጓተት ወያኔ ባሴረበት ዘመነ – መጠራቅቅ፤ እንሆ ጨለማን ማሟሟት የሚችል አቅምን ፈጣሪ አምላክ እራሱ አመቻችቶና አሳምሮ አደራጀ። ብርሃንም ሊመጣ ጓጓ! ናፈቅነው በጨለማ አጥር የታጠረብን – ልጆቹ። እነዛ ንጹኃን ቀን ከሌት ተግተው በፆም – በፀሎት – በሰጊድ – በድዋ- በሰላድ -የተጉት ህይወት መስታውቱን ፏ አድርጎ ተስፋችን አጠራው።
ትምክህት – ገደል ነው። ትእቢትም – ውርጭ። እነኝህ ለነፃነት ትግሉ ጠቃሚዎች አይደሉም። ለዕንባም ቅርብ የሥጋና የደም ዘመድ ሊሆኑም አይችሉም። የተከፋና የጨነቀው አፈር ለብሶ አፈር ተንፍሶ ንግግሩ ሆነ ውይይቱ ከተስፋው ጋር እራሱን ዝቅ በማድረግ ሲሆን ዘንበል ብሎ የመዳህኒትዓለም ጆሮ ያዳምጣል። ክህሎቱ ሲደመጥ የያዙትን ይዞ ተጨማሪ ለማግኘት እራስን ገርቶ በትክክለኛው ጎዳና ቀጥ ብሎ መጓዝ መሆኑን የትርፉ ጸጋና መድህን ስለመሆኑም ያገናዝባል። ቅኔውም በቅኔው ጉባኤ በቅኝት – ይሰክናል።
አቅምን ፈጣሪ፣ አቅምን ባራኪ፣ አቅምን ሸላሚ ፈጣሪ ነው። አቅምን ፈጥሮ ለአቅምን ጥበቃ ያደረገ አምላክ የተመሰገነ ይሁን። አሜን! እንሆ የታላቋ አሜሪካ ሞጋች አቅምን ሰማይ ሰጠን። ስለምን? የዕንባ ጥሪት ጉልበቱ ከኃያላኗ አሜሪካ በመብለጡ። እርግጥ ነው እንደ ስደተኝነታችን ሁሉንም ሳያማሩ አለስልሶ መያዝ እንደሚገባን የአቶ ዮፍታሄ ተከታታይ ጹሑፎች መንፈሳችን ገርቶታል። ስለሆነም ክርር ያለ ባይሆንም ረዳት እንድናገኝ አምላካችን ስላደረገ ግን ማመስገን ይገባናል። ከላይ ሊንኩን በለጠፍኩላችሁ አውሮፓዊ የዕንባ አጋርነት አቋም መግለጫ ውጤት ምን ተገኘ? ምን አተረፍን? ምንስ ይቀረናል? በጥቂቱ …..
- ይህ ዶከመንተሪ ሁለገብና ፋክትን የጨበጠ ቪዲዮ በተለይ አውሮፓ ላይ ክልትምትም ለሚሉ ወገኖች ታላቅ እናታዊ ትንፋሽ ነው። የሀገሬ ልጆች – የጹሑፌ ታዳሚዎች፤ ስደት ለሁሉ ስደተኛ እኩል አይሳካም። በፍጹም። አውሮፓ ላይ ለስደት የማይኮነው የለም። ሃይማኖት ይቀዬራል፤ ሥም ይለወጣል። ዜግነት ይቀዬራል፤ መረጃ ይቀጣላል፤ ዕድሜ ይለወጣል፤ ወላጅ ይገደላል። ከማይፈልጉትን ሰው ጋር ጋብቻ ይፈጸማል። የፖለቲካ ውሳኔ ይቀዬራል። ፈተናው ብዙ ነውና። ስለምን? ኬዝ ሲሰጥ የሚወጥሩ ነገሮች መጠነ ሰፊ በመሆናቸው። ከሁሉም በላይ አውሮፓ ላይ የሚሰደድ ዜጋ አብዛኞችን የአውሮፓ ሀገሮች ይረግጣል። ስለዚህ የሚሰጣቸው መረጃዎቹ ተመሳሳይ እንዳይሆኑ መለወጥ ግድ ነው። መረጃዎች ሲለወጡ በጣም መልካም የሆኑ የግለሰቡ ታሪኮች ሁሉ ነው አብረው ቀብር የሚበዬንባቸው። ሌላ ሰብዕና በቀላሉ ማምጣት ባይቻልም ተጽዕኖ የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች አሉ። ዕድሜ አሳንሰው ለሚሰጡ ለምሳሌ ቢታመሙ መዳህኒቱ ከዕድሚያቸው ጋር ተመጥኖ ነው የሚሰጣቸው። ስለዚህ ተግባራዊነቱ የዚያን ያህል ነው። የአውሮፓ ስደተኛ ኢትዮጵያዊ ኑሮ በካንፕ ውስጥ ነው። ይህ ማለት እንሰሳ ጋር የመኖር ያህል ከባድ ነው – የበረት ኑሮ። እስከ 15 ዓመት ካለ መኖሪያ ፈቃድ የመኖር አጋጣሚ አለ። „ውጣ / ውጪ/“ የተለመደ የመርዶ ዜና ነው። የታሰረ ህይወት ነው። ከሁሉ በላይ ከባዱ ዜግነታቸውን ቀይረው ለሚሰጡ ወገኖች ፈተናውን ለመግለጽ አቅም የለኝም። መኖር በእግር ብረት ልበለውን? ስለዚህ አሁን አድማጭ ማግኘት ይቻላል። የኢትዮጵያው የፋሽስት አስተዳደር ስለ ተጋለጠ ስደቱ ዕውቅና አገኘ ማለት ነው። አውሮፓዊውን ውሳኔያዊ ንድፍ ስታዳምጡት ቀላል ሊመስል ይችል ይሆናል። ያለፈው ዘመን ውሃ ያዘለ ተራራ የመሸከም ያህል ስለ ነበር ለእኔ በቁም የመጽደቅ ያህል ነው የሚሰማኝ።
- ሳይታክቱ መጣር ውጤት እንዳለው ሐዋርያ ሁኖ አስተምሯል። በመረጃ የተደገፈው ቪዲዮ፤ የቀጣይ ጥረትን ጠቃሚነትም አስተምሯል። መሥራት ፍሬን ያፈራል – ጥረትም ተስፋን ይፈጥራል።
- አብዛኞች የሚፈሩት ደፍረው ለመናገር የማይችሉትን ቁልጭ ያለ የነጠረ ሃቅ በሙሉ ቪዲዮው ላይ ተደጋግሞ ታዳምጣላችሁ“ የትግሬ መንግሥት“ አዲስ የድል ምዕራፍ ነው – ለሥርጉተ። የእኛ ነው ተብሎ በሚዘጋጅ ሰላማዊ ሰልፍ ሳይቀር „ኢህአድግ“ እዬተባለ ነው። ለምን ሲባል አውሮፓ የሚያውቀው በዚህ የህብረ ፓርቲ መጣሪያ ነው የሚል ሞጋች ሃሳቦች ነበሩ። የትግራይ ወያኔ ሃርነት ወያኔ ለማለት አቅሙ የተሟጠጠ ነበር ማለት ይቻላል። በጹሁፍ ሆነ በዘገባ የሚደመጠው እንዲሁ ነበር። ከዚህ በኋላ አሁንስ እኛም እናባብልው ይሆን የለበጣውን ሥያሜ? ሌላው በኽረ ጉዳይ ካርታውን ለይቶ አንድ ነጣለ ጎሳና ክልል በማለት በተደጋጋሚ ነበር የጥቃቱን ስፋትና ሃቅን እንደ ጸሐይ ፍንትው አድርጎ የገለጠው። ስለዚህ ለቀጣዩ የትግል መስመር ወጥ አቅጣጫ ዘገባው ተልሟል። እኛማ ትብስብሶች ነን። ወያኔ በሚለው ላይ እንኳን የጋራ አቋም ያልነበረን። ኢህአድግ እያልን አይደል እምናሽሞነሙነው — ወይንም በቅንፍ። ድፈርት አነሰን።
- የነፃነት ትግሉ ልሳን የሆነው ኢሳትም የዳበረ ዕውቅና አግኝቷል። ይህም ቀለማማ ማማዊ ስኬት ነው።
- የትጥቅ ትግሉ አስፈላጊነት ምንጩን በሚገባ በማብራራት የነፃነት ፍለጋው ጉዞ ተገዶ ወደ ትጥቅ ትግሉ መግባቱንም እውቅና ሰጥቶታል፤ ይህም ማለት የመተንፈሻ ቧንቧ ማስገኛ እንደሚያስፈልግ ታምኖበታል ማለት ነው።
- „በቃህ ወያኔ!“ ጉልበታም አውሮፓዊ መርህ ሆነ።
- እኛ ጀግና እነሱ „አሸባሪ“ የሚሏቸውን አርበኞቻችን የደመቀ ዕወቅና ከአክብሮት ጋር አግኝተዋል። ለእኛ ዕድሜ የመጀመሪያው ገድላማ የሰማዕታቱ መጸሐፍ ነው ማለት እችላለሁ እኔ – በግሌ።
- የነፃነት ትግሉ በሚያካሂደው ማናቸውም እንቅስቃሴ ጥግ አግኝቷል፤ አድማጭ አግኝቷል። ኢትዮጵያው ወስጥ ያሉ ማናቸውም የውጭ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፤ የሃይማኖት ተቋማት ሆኑ ኢንባሲዎች የቆሙበትን እንዲያስተውሉ ዓይናቸውን ከፍቶላቸዋል። ኢትዮጵያን ወያኔ ሃርነት ትግራይ በቁማቸው እያፈረሰው በመሆኑ መጪው ጊዜ ወያኔ አስከ ቀጠለ ድረሰ እዬተናደ እነሱም አብረው እዬሰመጡ ስለመሆኑ በአፅንሀኖት ገልፆል። በተፃራሪ አልፎ አልፎ ከሃቅ ያፈነገጡ መረጃወችን ፍሰት በሚመለከት የቪኦኤ ሆነ የዶቼ ቬሌ የዜና አውታሮችና እና ሃቅ ተፋጠው እውነቱን በጠራና በነጠረ መንገድ ቪዲዮው በመረጃ በተደገፈ፤ እንዲሁም በፎቶ ግራፍ በተጠናቀረ ከእነሱ በላቀ ሁኔታ እውነትን አፍልቆታል። በተጨማሪም የኢትዮጵውያን የተጋድሎ ታሪክ ተከታትለው ባሉበት ቦታ ሀገር እንኳን አለመዘገባቸው የታሪክ ግድፈት መሆኑን በረቀቀ ሁኔታ መንገድ መርቷል። ለሰው ልጅ ከሰብዕዊ መብት መከበር በላይ ምንም ነገር የለምና። አብሶ ለጋዜጠኛ። ጋዜጠኛ ሀገሩ እውነት ነው። ሃይማኖቱም የሰው ልጅ መብት መከበር።
- እጅግ የተገፉና፤ የተረገጡ ዒላማ የሆኑ ብሄረሰቦችን ሆነ ክልሎችን በጉልህ አውጥቷቸዋል። ዬአውሬውን ተባባሪዎችንም እንዲሁ ለይቶ ተለጣፊነታቸውን አሳይቷል፤ ይህ በራሱ የቀጣፊውን የወያኔ ሃርነት ትግራይን ማንፌስቶ ስቅለት ላይ ያወለ፤ የ40 ዓመቱን ደባ ያጋለጠ፤ የወደፊት ተስፋውንም አመድ ያደረገ አዲስና ልዩ የማግሥት ዬትንሳኤ ብሩኽ ምዕራፍ ነው ማለት ይቻላል። ወያኔን ለተከተሉ መንገዱ ገደል ስለመሆኑ ነግሯቸዋል። ወፍ እንዳላወጣቸው።
- ኢትዮጵውያን በተሰደድንበት ሀገር ሁሉ ባለቤት የሌለን ምንዱባን እንደሆንም ከልብ፤ ከውስጥ እናታዊ በሆነ ሁኔታ አምክንዮውን በመላ ዓለም ለሚገኙ የሰብዐዊ መብት ተሟጋች ፍጡራን፤ ድርጅቶች ሁሉ መንፈሳቸውን አሳምሮ ገርቷል። አስተምሯል። መስኖ በመሆንም ድርቅ የመታውን አካባቢ ሁሉ አልምቷል፤ እንዲሆም ስለ ሃቅ አደባባይ ላይ መክሯል። ስለዚህ በውስጡ ጠረኑ የሶልዳርቲ ዓለምዓቀፍ ጥሪም አቅርቧል። የኢትዮጵውያን ትግል ሰው የመሆን የነፃነት ትግልና ነውና ሊታገዝ ሊረዳ ይገባል ብሏል ጥንቅሩ። ለወያኔ ሃርነት ትግራይ ዘረኛ መንግሥት የሚደረገው ማናቸውም እንክብካቤ እገዛ፤ ድጋፍና ብድር መቆም አለበትም ብሏል። ለሰባዊ መብት ረገጣ ጭቆና ዘረኝነት የምትለግሱትን ማናቸውንም ትብብራችሁን አቁሙ በማለት ረጂዎችን ዲታ ሀገሮችንም በሚገባ ገስፆልም። ለም መሬት ቀረምት ላይ ያሉትንም አላተረፋቸውም። ሚስጢር ተገለጠ። የማይገለጥና ተከድኖ የሚቀር ምንም ነገር የለምና። ዕንቁ።
- የትግሉን ውስብስብነት እርዝማኔ ምክንያታዊ ትንታና በሚመለከት ደግሞ ሌላ አምክንዮን ፈጥሯል። ነገ ኢትዮጵያ ሊገጥማት የሚችለውን ፈታኝ ወቅት በማብሰል፤ መፍትሄውን ቁልጭ አድርጎ በማያወላዳ መልኩ የሥርነቀል ለወጥን አስፈላጊነት ብቻ ሳይሆን፤ የአንድነት ጉዞ ስለመሆኑ አመሳጥሯል። ፍላጎትና ራዕይ በአኃቲ በመስመር እንዲህ በዓለምዐቀፍ ደረጃ በቅኔ የገጠሙበት ሰሞናት ቢኖሩ ይህ ታላቅ ቀን የምሥራቹን ይዞ ብቅ ያለበት ወቅት ነው።
- እኛ ብቻችን የማንወጣቸው ብዙ ነገሮች አሉን። ለዛሬ ብቻም አይደለም። ለወደፊትም የውጭ ኃይሎች ድጋፍ፤ እርዳታና ግንኙነት ተፈጥሯዊ ነው። ስለዚህ ለነገም ከነፃነት በኋላ ለሚኖረን ተደማጭነት ከማናቸው ሀገር ህዝቦችና አህጉርና ዓለምዓቀፍ ድርጅቶች ጋር አዲስ ሃዲድ – ተከፍቶልናል። አሁን ብቻችን አይደለንም። ነገም ብቻችን – አንሆንም። ኢትዮጵውያን በዬተሰደዱበት ሀገር በማፍያው የወያኔ አፋኝ ቡድን እዬታነቁ ለአራዊት የሚሰጡበት መቅኖ አፍሶታል ያ ገድለኛ ጽኑ የእኛ የሆነ፤ ውስጣችን በቅዱስ መንፈሱ የዳሰሰ፤ ዕንባችን ከልቡ የተጋራና ያበሰ የብራስልሱ የሃቅ – ማህደር። የታሪክ ሰንድቃችን ነው። ልባችን – የፈወሰ። መኖራችን – ያደሰ። ዳግም ትንሳኤ፤ ለቀጣዩ ትግል ጽኑ – አንባ፤ መጠለያ እንሆ ሆነ። ልዩ የአቅም ኃይልና ጉልበት ሆነ። ጥሩ እንድናልም ተስፋን እንድንጠብቅ አደላደለን። አጠበቀን! ክፈተቱን ሁሉ ደፈነ! ተመስከን አምላኬ!
- የዛሬ ዓመት ረዳት አውሮፕላን አብራሪ ጀግና አበራ ሀይለመድህን በወሰደው የዝምታ „የአሻም“ እርምጃ የኢትዮጵያ አዬር መንገድ ክብር ተነካ ብለው ላኮረፉ ወገኖች፤ ከትግሉ እራሳቸውን ላገለሉ ዜጎች ምክንያቱን እንዲያድምጡበት በሩን ቧ አድርጎ ከፍቶላቸዋል። „ለከፋው ማጭድ አታውሰው“ ስለመሆኑ፤ ህሊና መንፈሳቸው ከእኛ ጋር ለሆኑት ቅን ወገኖች። ወያኔ ተነካ ብለው ላጎሩትም ቢሆን እስኪበቃቸው አስታጥቋቸዋል። ህቅ እያላቸው ሃቅን እንዲውጡ …. አስገድዷቸዋል።
- እጅግ በጣም ብዙ ሰው ምን ሊገኝበት፤ ምን ሊያተርፍ፤ ወያኔን በፀሎት ብቻ፤ ወያኔ ፈጽሞ ሊናቃነቅ የማይችል ነው በማለት ዕንባን ሳያጋሩ አድብተው ለተቀመጡትም ቢሆን፤ ስለራሳችሁ ጉዳይ እኛ አግብቶናል። ስለምን እናንተ ጉዳያችሁን ቸል አላችሁ የትስ ነው ያላችሁት ክብራችሁ ሲቃጠል? በማለት አፋጧቸዋል። ስለዚህ ነገ … መቅናቱን ያዬ ቅናት አዎንታዊ ያድርበትና …. ዛሬም ቀን ነው። ትናንት ያለደርኩትን ጨምሬ በእጥፍ ካሳ ለመክፈል ዛሬውኑ ብሎ ከራስ ጋር ቃል ኪዳን እንዲያሰር ኮረኮንቹን፣ ወጣ ገቡን መንገድ ድልድል አድርጎ ጥሪ አቅርቦላቸዋል። የዕንባ ቀለበት ውል የምጥ ጥሪ ከአውሮፓ ኮሚሽን – ለኢትዮጵውያን። ከድንቅ በለይ የፈለቀ እፁብ ድንቅ። በቀለም ሆነ በዝርያ ከማይገናኙን። ግን ሰው በመሆን ብቻ ከሚያምኑት – ንፁኃን። ከድንቅ በላይ ግርማና ሞገስ ያለው – ገድል። ወሸኔ!
- ተስፋ /// ተስፋ የእኔ ወዳጄ ነው ፍቅረኛዬ። ተስፋ ሥሙን እራሱ በጣም ነው የምወደው። የመጀመሪያው መጸሐፌ „ተስፋ“ ነው። በድህረ ገፄ ሆነ በራዲዮ ፕሮግራሜ መግቢያ ተዘውትሮ ከተስፋ ጋር ንግግር፣ ቃለ ምልልስ አለ። ተስፋ ሲኖር መኖር አለ። መኖር ሲኖር ህይወት አለ። ህይወት ሲኖር ፍቅር አለ። ፍቅር ሲኖር ትውልድ አለ። ትውልድ ሲኖር ሀገር አፈር መሬት ባዕት – አለ። አፈር ሲኖር ሰንድቅዓለማ አለ። ሰንደቅ ዓለማ ሲኖር ማንነት አለ። ማንነት ሲኖር ራዕይ አለ። ራዕይ ሲኖር ማቀድ አለ። ማቀድ ሲኖር ነገ አለ። ስለዚህ ሁሉ በጨለመብን ዘመን አብሶ ሀገር ቤት ላሉ ወገኖቻችን አንድ መልካም ዜና ብዙ ዋጋ አለው። እነሱማ መተንፈሻ አጥተው ታፍነዋል። እና አንጋፈውና ሃብታሙ እንዲሁም ሥልጡኑ የአውሮፓ ህብረት የወል ቅዱስ ድምጽ መዳህኒት የተስፋ – ወጌሻ የተሰበረ ተስፋ፤ አራሽ ለነገ ተስፋ። አገላለጹ እኮ እኛም ከእናንተ ጋር ነን ነው። ለእኛ የሚበልጥብን የሰብዕዊ መብት መከበር እንጂ የለበጣ የወያኔ ሃርነት ትግራይ አጃቢ ቅጥፈታዊ ዘገባ አይደለም ነው። ተመስገን!
- እስከ ዛሬ ዕንባን በመጋራት ከእኛ ጋር ሳይታክቱ በጠራ መንገድ ዬቆሙት ዓለምዓቀፍ የሰብዕዊ መብት ተሟጋቾችን ሆነ የሲቢክስ ድርጅቶችን ማናቸውም ዘገባው አድንቋል። ሪፖርቱንም – ተጠቅሞበታል። እንዲህ ዕውቅና መስጠቱ ከጎናችን የቆሙ የስብዕዊ መብት አስከባሪ ዓለምአቀፍ ድርጅቶ የበለጠ ከእኛ ጋር በመቆም እንዲሰሩ የፋፋ ተነሳሽነት ፈጥሯል፤ በተዘዋዋሪም አምስግኗቸዋል። ተግባራቸውንም አድንቆላቸዋል። በሌላ በኩል ዝምታን የመረጡ፤ ችል ያሉትንም ዓለምአቀፍ ድርጅቶች ሆኑ የሲቢክስ ድርጅቶች በሚመለከትም ቢሆን በውስጣቸው የውድድር መንፈስ ፈጥሮ እንቅስቃሴ እንዲጀምሩ አነሳስቷል። ማለፊያ!
- ለእኛ ህ! ለእኛማ ጥሩ የመተንፈሻ ንጹህ አዬር አስገኝቶልናል። ለታታሪ ወገኖቻችንም ቢሆን መስዋዕትንት ፈቅደው ማገዶ ለሆኑት ዕውቅና በሚገባ ሰጥቷል። በርቱ! ቀጥሉ! ብራቮ ብሏቸዋል። ለልዝ እንጨቶች ደግሞ ተንቃሳቀሱ ሲል መልዕክቱን ልኳል። የድምጹ ቶን አራሱ ተቆርቋሪነቱ ከቆሰለ መንፈስ የወጣ ስለመሆኑ ሲመረመር የፈጣሪን ድንቅ ተግባር ያሳያል። ተደግሞ – ተድግሞ ቢደመጥ የማይጠግብ የሱባኤ ድርሳን ነው። ጸሎተ – ነፃነት! ያልተወለዱን እንዲህ ተንገበገቡልን። ተመስገን ፈጣሪዬ!
- የውጪ ትግል ምን ሲያደርግ? ምንስ ሲፈይድ? ሁሉንም ወያኔ ተቆጣጥሮታል ለሚሉት ደግሞ በትህትና አስተምሯል። ይልቅ የነፃነት ትግሉን ተቀላቀሉ በማለት ሐዋርያዊ መልእክቱን ልኳል። አብሶ የጀርባ ቅማሎችን አይሆኑ አድርጎ ነው ያራጋፋቸው – ሪፓርቱ። በነፃነት ሥም ንግድ ይቁም! ሲል ነው አቋሙን ቁልጭ አድርጎ ያሳዬው። ዋው!
- በግልም ሆነ በድርጅት ኢትዮጵያውያን አውሬውን የትግራይ ነፃ አውጪው ድርጅትን በሚመለከት የሚሰጡት መረጃ፤ ዬሚላኩት ፊልም፤ የሚሰበሰቡ ፊርማዎች፤ የተካሄዱ ሰላማዊ ሰልፎች የሚላኩ የኢትዮጵውያን ጠንካራ ማህበራዊ ድህረ ገጽ ዘገባዎች አትኩሮታዊ ሊንኮች ሁሉ አቅምን በመገንባት እረገድ አስተዋፆአቸውን ከፍ አድርጓ – አብልጽጓቸዋል። ተግባራቸውንም ብድግ አድርጎ ባለማዕረግ አድርጎታል። ተጠናክረው፣ በፈካ ተስፋና በደረጀ የራስ መተማመን ስሜት እንዲቀጠሉም በፅኑ አበረታቷል። እኔን ሲገባኝ ቅንጣት ጥረት አልባካነም። የፈሰሰ መረጃ የለም። ሁሉም ዕውነትን በማብራት ጨላማን ለሟሟሟት ጠቃሚ ህዋስ ሁነዋል።
- በጎሳ ዬመደራጀት ፍላጎትን ሆነ መፍትሄ አምንጭነቱንም ተስፋ አምክኖታል – ሪፖርቱ። በብዙ ህብረ ብሄር ብሄረሰብ ለአበበች – ለተዋህደች፤ በቀለማም ባህል ለተንቆጠቆጠች – ለሰከነች፤ በተላያዩ የዕምነት ዓዕማድ ህብረ ዝማሬ ላይ ለምትገኘው ኢትዮጵያ የቀደምቱን አብሮነቱን ሚዛናዊነት ዘመን በምልሰት ቃኝቶና አድንቆ፤ ሰው ሰራሹን ወያኔዊ ስንኩል መንፈስ አድቅቆታል። ኢትዮጵያ ብቻ ከዓለም ተነጥላ በጎሳ የምትመራ መሆኗ፤ ያለሰለጠነ ጉዞ መሆኑንም አስምሮበታል፤ በዚህ ትንተና አውሮፓዊው ውሳኔዊ ንድፍ የነገውን ውብ ነገን አኃታዊ አቅጣጫ በፍጹም ሁኔታ ብራ* አድርጎ ግንብቶታል ወይንም አንፆታል – አንጽቶታልም።
የኔዎቹ ወገኖቼ – የነፃነት ትግል የጫጉላ ሽርሽር አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ጊዜና ትእግስትን፤ ጽናትና ብርታትን፤ ሳይንጠባጠቡ በተከታታይነት መንፈስን ሰብስብ አድርጎ ቆርጦ መቀጠልን የሚጠይቅ ነው። እንሆ ጊዜ ለተግባር ሰጥቶ እሱ አንድዬ በፈቀደ ጊዜና ወቅት ይህን መሰል ወርቅ ዕውቅና ከእጃችን ሰተት ብሎ ገብቷል። እኔ አንዳንድ አጫጭር ኮርሶችን ስወስድ እምመርጠው እርእስ „ሰብዕዊ መብት ረገጣ በኢትዮጵያ“ የሚል ነው። እንዲያውም ኮርሰኞቼ ስሜን ትተው „ሰብዕዊ መብት“ ይሉኛል። ነገር ግን መምህሮቼ የሚሟገቱኝ ተጨባጭ አህጉራዊ ዕውቅና ያመጣ ነገር አቅርቢ ይሉኝ ነበር። በሴኔቱም ዓመታዊ ሪፖርት ብዙም አይረኩም ነበር፤ የእኛን ሆም ፔጆች ሊንክ ስሰጣቸውም ከልብ አያዩትም ነበር። የሦስተኛ ወገንን ወላዊ ጉልበታም ምስክርነት ነበር የሚሹት። አሁን ተመስገን ነው። በእዬአድራሻቸው ይላክላቸዋል። ሃቅ ሲያፈራ – ድል ይጎመራ።
ክወና — አውሮፓ አቀፉን ውሳኔያዊ ንድፍ ትርፉን በጥቂቱ ነው ያነሳሁት። እስከ ዛሬ ኑረው አሁን ለምን የሚሉ ቅኖች ይኖራሉ? ትግል ማለት ምን ማለት እንደ ሆነ ስለማያውቁ ሊሆን ይቻላል። ውጤትም ትግልም ስኬትም የሂደት ቅምረት ናቸው። ሁሉ ነገር መብሰል አለበት። ለመብሰል ጊዜ ይሻል። ደግሞ በውስጡ ለማይኖር ለሌላ አካል ዕምነቱን አምጦ ዕውቅናን ለመውለድ ሰፊ መጠነ ሰፊ ጊዜ ይጠይቅ ነበር። እንደ ገናም እኛን መስለው ስርንቅ መረጃ ሲሰጡ የነበሩ የዶሮ ቅማሎችንም* መዘንጋት የለብንም። ተስክስከዋል እኮ። ከሁሉ በላይ ግን የመዳህኒት ፈቃድ „ጊዜ ገቢረ ለእግዚአበሄር“ ይላል መጸሐፉ። ይጠብቃል። አሁን እኔ እንደማስበው ውሃ ስኳርን ወይንም ጨውን ያሟሟል። እሳት ደግሞ ወርቅን ያቀልጣል። ሁለንትና – ሁለቀፍ የሆነው ዘገባ ጨለማውን ዬወያኔን ዘመን አሟሙቷታል ባይ ነኝ። ኩሽሽ ብሏል አሁን የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ። ከጨለማ መሟሟት በኋላ ስለሚኖረው ነገር ደግሞ የቅድሚያ እስቤ በተረጋጋና በሰከነ ሁኔታ ጥናቱ – ፍልስፍናው ተደራጅቶ በተከታታይ እንዲቀጥልም ጠቁሟል ባይ ነኝ። ለእኔ ሰንድቅዓላማዬ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ በዓለም ከፍ ብሎ በወርሃ የካቲት 2015 ተውሎብልቦልኛል። ደስ ብሎኛል። ፈክቻለሁ። ፍልቅልቅ ብያለሁ። ጥንካሬ፣ ጉልበትና አቅም አግኜቻለሁ። በልበ ሙሉነት ተራምጃለሁ። ከሃፍረተኞች ጋር ባለመተባበሬ ደግሞ አምላኬ ስለረዳኝና ስላገዘኝ ስለሆነ ዝቅ ብዬ ተንበርክኬ አምስግኝበታለሁ። እግዚአብሄር ይስጥልን የአውሮፓ ኮሚሽን = ኑሩልን።
ይህ መስመራዊ አኃታዊ መንፈስ የፈጠረውን ዘመን ታላቅነት በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል። ሳያሾልኩ። ማግኘት አይደለም ትልቁ ቁም ነገር ያገኙትን በአግባቡ መጠቀም እንጂ። የማያስፈልገው ነገር ትጥቅን ማላላት እንዲሁም መመካት ነው። ከበፊቱ በተሻለ በምህረት ጎዳና እራስን መርምሮ፤ ፈትሾ የራስን ግድፈትም አርቆ ራህብን ለመፈወስ እያንዳንዱ በግል ሁሉም በጋራ ትውልዳዊ ድርሻውን ለመወጣት ከተጋ ነገ የኢትዮጵያ ይሆናል። ሳቂተኛ ፍቅልቅ ያለ ጠረነ – ጥሪኝ ለእኛ ይመጣል። ለቀኑ ቀን ይሰጣል። ቀኑን ቀን ይባርክለታል። ትርፉም ተሰፋን ያለመልማል። የኔዎቹ ለነበረን ወሸኔ ጊዜ ፍቅሬን ሸልሜ ልሰናበት – ወደድኩ። ደህና ሰንብቱልኝ ቸር ወሬ ያሰማን። አምካችን። አሜን!
መፍቻ 1. የዶሮ ቅማል – የዶሮ ቅማል በዓይን አይታይም። እጅግ አነሳዎች ስለሆኑ። ቀለምም የላቸውም። ምንአልባት በማይክሮስኮፕ ሊታዩ ይችሉ ይሆናል። ነገር ግን ወረራ ሲያካሂዱ ነፍስን አስተው ሲያንገበግቡ ግን ከፈላ ውሃ የመግባት ያህል ነው። አይታዩም እንዳይለቀሙ። መፍትሄው ዲዲቲ ብቻ ነው። እኔ ጫካ በነበርኩበት ጊዜ ገጥሞኝ ነበር። ዲዲቲ ነበር ጸበል የሆነኝ። ዱር ቤቴ ያሉ ወገኖቼ ሽልማቴም ጀግናዬም ያልኩት የማይታዩ ፈተናዎችን ጥልቀት ስላዬሁ ነበር። እና የእኛ ባለንጣዎችም መስለውና ተመስሳለው አንዳንዶቹ ለነፃነት ትግሉ መቆርቆሩንም መሳተፉንም ልቀው ያደርጋሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ከዬትኛውም ተሳትፎ የሉም፤ ንክኪ አይሹም። በስለላ ከሚያገኙት የውርዴት ውርጃ ጋር ነው የሚኖሩት፤ እኛም ሳናውቃቸው ግን እዬገደሉን አብረን በሀገር ልጅነት ፍቅር እንኖራለን። ከነዚህ የሚሰጠው የተሳሰተ መረጃ አቅማችን የበላው አሳማው ጉዳይም ነበር ለማለት ነው ቃሉን የተጠቀምኩት።
- ብራ — ዝንብ ሲነሃረር ውሎ አድሮ ወይንም ሰንብቶ፤ ጭፍግግ ያለው ቀን፤ የከፋቸው ሰዓታት፤ ጉሙሙ የንፈሱም መከፋትን አክሎ ስንብት ማድረጋቸውን ልዕልት ፀሐይ በጠራ ሰማይ ላይ ሆና ሙቀቷን ሳትሳሳ እዬሳቀች ስትለግስ ብራ ሆነ ይባላል።
አርበኞቻችን መርሆቻችን ናቸው!
The post ጨለማ ሲሟሟ … ብርኃንም – ይጓጓ! – ከሥርጉተ ሥላሴ appeared first on Zehabesha Amharic.