ነቢዩ ሲራክ
ታሪካችን በጦርነት ተከቦ ዘመን በዘመን ሲተካ ፣ የቀደመው ይሁን ቢባል እንኳ በዘመነችው አለም መካከል ያለች ቀሪ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ የሃገሬ እናቶች እንባ የሚጠርገው አጥቷል። ከዘመነ ጃንሆይ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ እስከ ደርግ ፣ ከዚያም አሁን እስካለንበት የኢህአዴግ አገዛዝ ለሀገር ሰላም ፣ ለዲሞክራሲና ፍትህ የዜግነት ድርሻቸውን የሚወጡ ፣ የተጉና ” ስለ ሃገሬና ህዝቤ ያገባኛል ” ያሉ ልጆችን በአብራካቸው ያፈሩ እናቶች መከረኛ እናቶች ናቸው። ልጆቻቸው ፍትህን ናፋቂ ፣ መብታቸውን ጠይቂ ናቸውና ” እንደ ጋሪ ፈረስ ጋሪ አንነዳም ” ያሉ ኩሩ ዜጎችን አፍርተዋልና ህግና መመሪያ እየወጣ ፣ የወጣው ህግና መመሪያ እየተጣሰ ቤታውን አጨልሞታል ። ትናንት የነበረው ዛሬም የቀጠለው ደረቅ አሳዛኝ እውነት ይህ ነው !
አዎ የእናት አብራክ ጀግና ማፍራቱ አላቆመምና የጀግና አርበኛ እናቶች እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም የእኛ እንደ ከፋቸው ፣ ሰርክ እንደተሸበሩና ሰላማቸውን አጥተው ኑሮን ለመግፋት ተገደዋል። የእሳተ ነበልባል ለወጥ አራጅ እናቶች ናቸውና ይገፋሉ ፣ በገዛ ሃገራቸውና በቀያቸው ፣ በስጋትና በሽብር ተከበው ኑሮን በመከራ ፣ በደል እየተፈጸመባቸው ለመሆኑ ብዙ ማሳያዎችን ከቀደመው እስከ ቀረበው ፣ ከቀረበው እስከምንገፋው የለው የእኛ ሀገር የፖለቲካ ምህዳር የፈጠረው አሳዛኝ የተገፊ እናቶች ታሪክ ዋቢ ነው … !
ትንታጉ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ …
ተመስገን ደሳለኝ ደርግ በወደቀ ማግስት “ክፉው ዘመን አለፈ ፣ መጨራረስ መገዳደል እልባት አገኘ ” ተብሎ ተስፋ በተጣለበት ፣ “ዲሞክራሲ ሰፈነ !” ተብሎ አዋጅ ነጋሪት በተጎሰመ ፣ በተነገረበት ” የዲሞክታሲያዊ እኩልነት ህገ መንግስት ” የጸደቀ ሰሞን የአንደኛ ደረጃ አስኳላ ትምህርቱን ያላጠናቀቀ ገና በአስራዎቹ የእድሜ ክልል የነበረ ወጣት ነው ። ባለፉት 23 አመታት ግን ተግቶ ትምህርቱ የተከታተለው ብትቱ ታዳጊ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ዘልቆ እውቀትን በመገብየት በተገቢ መንገድ አጠናቀቀ ።
ጎልማሳው ተሜ ….የሃገር ፍቅሩን ከቀሰመበት የትምህት ረድፍ አልፎ ተርፎ ፣ ከጎረቤት ፣ ከከባቢው ወርሷም አደገ … እናም ከጥቂት አመታት በፊት ነፍሱ ሲፈቅድ በተሰጠው የመጻፍና ማንበብ መብት ማዕቀፍ ብዕር ጨበጠ .. ተመስገን አውነትን ይዞ ፣ ዲሞክራሲን መከታ አድርጎ ያልተመቸውን የፖለቲካ አካሔድ ተቃዋሚ ፣ ገዠ ፖርቲ ሳያይና ግራ ቀኝ ሳይለይ ይሞግት ገባ ። የተዋጣለት ጋዜጠኛና የፖለቲካ ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትንታኝ ጸሃፊ ለመሆን ከበቁት የዘመናችን ትንታግ ሰላማዊ ትግል አርበኞች መካከል አንዱ ለመሆን ለተመስገን ጊዜ አልፈጀበትም ! እናም ስራውን ተግቶ ቀጠለ …
ጋዜጠኛ ተመስገን የመጻፍ የመናገር መብቱን ተጠቅሞ ፣ በሰላማዊ በሆነ መንገድ ለሃገሩ ይሆናል ያለውን ሰላማዊ የትግል ስልት በማመላከት ፣ ወጣቱ ፍርሃትን አስወግዶ ለሰላማዊ ትግል እንዲተካ መስበክ ያዘ ፣ መሰናክል ጋሬጣው ከማንሳት ይልቅ … ጋዜጠኛ ተመስገን ብዙ ታገለ ፣ አታገለ … ማለቱ ብቻ ይቀላል !
የቆየው ውርስ ተከትሎናልና ፣ ጥላቻውን አድገንበታልና የዚያ ወጣት ትንታግ የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ መንገድ በዘባተሎው ፖለቲካ ተሰናከለ ! … ባለ ራዕዩን ብዕረኛ ፓለቲካው ጠልፎ ጣለው ! ተሜ ግን የዋዛ አይደለም ” … ለእኔ ሳይሆን ለታገልኩለት አላማ ጸንታችሁ ታገሉ ! ” እያለ የወህኒውን ህይዎት በጸጋ ተቀብሎት ኑሮን መግፋት ይዟል ! …
ተገፊዋ የተመስገን እናት …
… የተሜ እናት ግን እያነቡ ነው … ብዙ ማለት አልችልም ፣ የተገፊዋን እናት ደብዳቤ ደርሷል ፣ አዝኛለሁ ! የምንሰማቸው ከሆነ …ተገፊዋ እናት በአብራካቸው ክፋይ በልጃቸው በጋዜጠኛ ተመስገን ላይ ወህኒ ቤት ውስጥ ህግ እየተጣሰ የሚፈጸምበት መበት ገፈፋ ሰላም ነስቷቸው ” የሰው ያለህ ፣ የህግ ያለህ! ” ብለውናል ። የእኒህ እናት ጩኽትና ሮሮ የሀገሬ ለውጥ አራማጅ ጀግና ልጆችን የወለዱ እናቶች ሁሉ ጥሪ ለመሆኑ ላፍታ አልጠራጠርም ። ምንም እንኳን ይህ አሁን ድረስ የቆየና የቀጠለው የሀገሬ እናቶች መከራ አንዱ ክፍል ቢሆንም ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላለፉት 30 ቀናት ከማንም ጋር እንዳይገናኝ መደረጉና የእናቱ አቤቲታ ጉዳዩን ጀሮ ገብ መልስ የሚያሻው ቀዳሚ ጉዳይ አድርጎታል ።
ዛሬ ጋዜጠኛ ተመስገን ጥፋት ምንድን ነው? ፍርዱስ ፍትሃዊና ተመጣጣኝ ነውን ብለን አንጠይቅም ፣ አንሞግትም ! ዛሬ የምንሞግት የምንጠይቀው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በእስር መብቱ አይጣስ ፣ ህገ መንግስቱ ይከበር እያልን ነው ። ተመሰወገን ከሚወዱ ከሚናፍቁት አቅመ ደካማ እናቱ ፣ ከቤተሰብ ከቅርብ ዘመዶቹ ፣ ከሐይማኖት ፣ ከሐኪምና ከህግ አማካሪ ጋር የመገናኘት ህገ መንግስታዊ መብቱን እንዲያከብርለት እንደ ዜጋ ድምጻችን የማሰማት ቢያንስ የሞራል ግዴታ አለብን ! ግፍ ሲበዛ ጥሩ አይሆንም ፣ ጆሮ ያለው ይስማ !
ፍትህ እንሻለን !
ነቢዩ ሲራክ
የካቲት 3 ቀን 2007 ዓም
===================================
የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እናት ደብዳቤ
===========================
ቀን 02/06/2007 ዓ.ም
ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን
አዲስ አበባ
ጉዳዩ፡- የልጄ ተመስገን ደሳለኝን ጉብኝት ይመለከታል
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከአብራኬ የወጣ ሁለተኛ ልጄ ነው፡፡ ገና ከህፃንነቱ ጀምሮ ለሰው አሣቢ፣ ሀገር ወዳድና ታታሪ ስለመሆኑ ከእኔ በላይ የሚያውቁት ይመሰክራሉ፡፡ ልጄ ተመስገን ለወገኔ አሰብኩ ባለ በእስር ቤት ያለጎብኚ እየተሰቃየብኝ ይገኛል፡፡ መቼም፣ የእናት ሆድ አያስችልምና እባካችሁ ልጄን ታደጉት፡፡ እባካችሁ ቢያንስ ካለበት እየሄድኩ የልጄን አይን እንዳይ እንዲፈቀድልኝ ተባበሩኝ፡፡
የልጄን ድምጽ ከሠማሁ ይኸዉ አንድ ወር ሞላኝ፡፡ ታናሽ ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ ለወንድሙ ብሎ የቋጠረዉን ምሣ ይዞ ዝዋይ ማረሚያ ቤት ቢሄድም በማረሚያ ቤቱ ጠባቂዎች ተደብድቦ የያዘውን ምግብ እንኳ ሣያደርስ ሜዳ ላይ ተደፍቶ ተመልሷል፡፡ መቼም እናንተም ልጆች ይኖራችኋል፤ ደግሞም የልጅን ነገር ታውቁታላችሁ፡፡ እኔ አሁን በእርጅና ዕድሜዬ ላይ እገኛለሁ፡፡ ከአሁን በኋላ ብቆይም ለትንሽ ጊዜያት ነው፡፡ በዚህች ጊዜ ውስጥ ልጄን እየተመላለስኩ እየጠየኩ፣ ድምፁን እያሰማሁ፣ አይዞህ እያልኩ ብኖር ለእኔ መታደል ነበር፡፡ እባካችሁ እርዱኝ የልጄ ድምጽ ናፈቀኝ፡፡ እሱን መጎብኘት የተከለከለበት ምክንያት ምን እንደሆነ እንኳን እስካሁን አላወቅሁም፡፡ ከወንድሙ ድብደባ በኋላም ጥር 10 ወደ ጠዋት አካባቢ የሄዱት ጓደኞቹ እና ወንድሞቹ ሳያዩት ተመልሰዋል፡፡
ተምዬ ስታመም የሚያስታምመኝ፣ “አይዞሽ እማዬ” የሚለኝ ረዳቴ ነው፡፡ ሌላ ዘመድ የለኝም፡፡ የምተዳደረውም ልጆቼ ለፍተውና ደክመው በሚያመጧት ትንሽ ብር ነው፡፡ ዛሬ ግን ይኸዉ ልጆቼም ወንድማቸውን ለማየት እየተንከራተቱ ነው፡፡
በእናታችሁ ይዣችኋለሁ፤ ከቻላችሁ ልጄ እንዲፈታልኝ እና እኔም ያለችኝን ቀሪ የእድሜ ዘመን አይን አይኑን እያየሁ እንድኖር እንድታደርጉልኝ፤ ይህን ማድረግ ከአቅም በላይ ከሆነ ደግሞ ካለበት ድረስ እየተመላለስኩ እኔና ሌሎች ልጆቼ እንዲሁም ወገኖቹ እንዲጠይቁት ቢደረግልኝ ስል በአክብሮት እጠይቃችኋለሁ፡፡ ልጄን አውቀዋለሁ፡፡ አንድ ነገር ሲገጥመዉ ሆድ ይብሰዋል፡፡ ቢያንስ እንኳን ቤተሰቦቹን ሲያይ ስለሚፅናና ይኸዉ እንዲፈቀድልኝ እማፀናለሁ፡፡ እኔ ምንም አቅም የሌለኝ አሮጊት ነኝ፡፡ ሁሉንም ለናንተ ሠጥቻችኋለሁ፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር እንደምታስተካክሉልኝ እና እንደገና የልጄን ፊት እንዳይ እንደምታደርጉኝ ሙሉ ተስፋ አለኝ፡፡
እንግዲህ የየካዉ ቅዱስ ሚካኤል ይከተላችሁ፡፡ መቼም የእናትን ሆድ ታውቁታላችሁ፤ የልጅ ነገር አያስችልም፡፡ ሆድም ቶሎ ይሸበራል፡፡ ስለዚህ እባካችሁ እኔንም ልጆቼንም እርዱን እንላለን፡፡
ከሰላምታ ጋር
ወ/ሮ ፋናዬ እርዳቸው
ግልባጭ
– ለጠ/ሚኒስተር ፅ/ቤት
– የህግና፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ – ለአፈ-ጉባኤ ፅ/ቤት – የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) – ለእምባ ጠባቂ – ለአሜሪካ ኢምባሲ – ለእንግሊዝ ኢምባሲ
===================================
#Ethiopia_allow_to_visit_and_Medical_Care_for_Temesgen_Desalegn
The post የማለዳ ወግ …የተገፊዋ እናት ደብዳቤ …! * ያልተመቻቸው የእኛ እናቶችን እንባ .. appeared first on Zehabesha Amharic.