Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

አቶ አሰፋ ጫቦን ለቀቅ… ከሺመልስ አበበ

$
0
0
አቶ አሰፋ ጫቦ

አቶ አሰፋ ጫቦ

አቶ አሰፋ ጫቦ በኢሳት ቴሌቪዥን፣ በአዉራምባ ታይምስ ድህረ ገጽና በፊንፊኔ የድህረ ገጽ ሬድዮ ያደረጉትን ቃለ መጠይቆች ተመልክቻለሁ፤ አድምጫለሁ። እንዲሁም በኢትዮሚዲያ ድህረ ገጽ ላይ በብእር ስሙ መላኩ ይስማዉ የሚባል ግለሰብ የጻፈዉን ዉርጅብኝ አንብቤ በጣም ከልቤ አዘንኩ። በፍኖት ሬድዮም ስለ አቶ አሰፋ የተለፈፈዉን ተራ ትችትና ዘለፋም ሰምቼ በጣም አዘንኩ። አቶ አሰፋ የተናገሩትን በመረጃም ሆነ በሙግት መልክ በሰለጠነ መንገድ አንድ በአንድ መሻር ሲቻል ከደረጃ ዝቅ ባለ መንገድ ተራ ትችት ዉስጥ መግባቱ ከግምት ያስገባል እንጂ ሌላ እዉቀት የሚጨምር አይደለም። ለመሆኑ መቼ ነዉ የሰለጠነ ዉይይት የሚደረገዉ?

ይህ አይነቱ ስም የመጥራትና አወቅሁሽ ናቁሽ ትችት በቀድሞዉ ቀዝቃዛ ጦርነት ጊዜ ሲካሄድ የነበረ ባህርይ በአሁኑ ወቅት እተካሄደ ማየቱ ምን ያህል ሗላቀር የፖለቲካ ባህርይ እንደሆነ መረዳት አያዳግትም። በደርግ ጊዜ የነበረን የፖለቲካ ቆርሾ በአሁኑ ሰአት እንዳለ መድገም ደግሞ መለወጥ አለመቻልን የሚያመለክት ይመስለኛል። በአቶ አሰፋ ላይ የተካሄደዉ አግባብ የሌለዉ ትችት ይህንን መልስ እንድሰጥ አስገድዶኛል።

እኔ አቶ አሰፋ ጫቦን አዉቃቸዋለሁ። በመጀመሪያ ያወቅሗቸዉ የጋርዱላ አዉራጃ አስተዳዳሪ ሆነዉ ጊዶሌ ከተማ ሲመጡ ነዉ።
በየካቲት ስድሳ ስድስት አመተ ምህረት ንቅናቄ አርባ ምንጭ መጥተዉ ከሼቻ (የላይኛዉ ከተማ) ወደ ሲቀላ (የታችኛዉ ከተማ) ይነዱ በነበሩት ጉርድ ላንድሮቨር ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ሆኜ ወስደዉናል። በፈገግታ ላንድሮቨሩን አቁመዉ ግቡ ብለዉን ስለለዉጡ እያወሩንና እኛም ደግሞ በአንክሮ እያዳመጥን እንደነበር አስታዉሳለሁ። ደርግ ስልጣን ላይ ወጥቶ እድገት በህብረትን አዉጆ እኔም ደግሞ ከአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወደ ከምባ ወረዳ ከአዲስ አበባ ከመጡ ዘማቾች ጋር ዘመትኩ። ታናሽ ወንድማቸዉ የሆነዉ እሸቱ ጫቦም እንዲሁ ዘምቶ ነበር።

ዘመቻዉን ጥዬ ስመለስ አቶ አሰፋ የህዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዚያዊ ጽህፈት ቤት ዋና ጸሀፊ ሆነዉ እንደተሾሙ አርባ ምንጭ ከተማ ሰማሁ። ይህ መስሪያ ቤት ካድሬዎችን ቀጥሮ በየቦታዉ እየላከ ቅስቀሳ የሚያስደርግ መስሪያ ቤት እንደሆነም በወቅቱ ተረዳሁ። በወቅቱ በነበረኝ ንቃተ ህሊናና ከጓደኖቸም ካገኘሁት ምክር ከአቶ አሰፋ መራቁ የተሻለ ነዉ የሚል እምነት አሳድሮብኝ ነበር።እ. ኢ. አ. በ1969 ዓ. ም. ትምህርት ጀመርን። በኢሕአፓ እና በመኢሶን መካከል ይካረር ነበረዉ የፖለቲካ ትግል በአርባ ምንጭ ከተማና በነበርኩትም ትምህርት ቤትም ይብላላ ነበር።

እ. ኢ. አ. በ1969 ዓ. ም. በአንድ ወቅት የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መማሪያ ክፍሎች ዴስኮች ላይ ለእያንዳንዱ ተማሪ ተብሎ በእጅ የተጻፉ የኢሕአፓ ወረቀቶች ተበትነዉ ነበር። ክፍል ስገባ ወረቀቱን አነበብኩ። ወረቀቱ የተሞላዉ በኢህአፓ መፈክሮች ነዉ። እያንዳንዱም ተማሪ አንብቦት ዝም ብሏል። ትምህርትም ተጀምሮ ሳለ የአርባ ምንጭ ወረዳ ፖሊስ ጣቢአ አዛዥ የነበረ ሻምበል ተስፋዬ የሚባል ከጠቋሚ ተማሪዎች ጋር በመሆን በየክፍሉ እየዞረ ማን ነዉ ወረቀት የበተነዉ እያለ ይጮህ ነበር።እኔ የነበርኩበት ክፍልም መጥቶ ጮኸብን። ብዙ ተማሪዎች ክፍል ለቅቀዉ ሲወጡ እኛም ወጣን። ብዙ ጠቋሚ ተማሪዎች በቦክስ ተመቱ። ቁጥሩ አንድ መቶ የሚሆን ማስ የሚባል (ፈረንሳይ የተሰራ አስር ጥይት ጎራሽ) ግማሽ አዉቶማቲክ ጠብመንጃ የታጠቀ የፈጥኖ ደራሽ ሀይል ትምህርት ቤቱን ከበበ። በዚህን ጊዜ ነበር አቶ አሰፋ ጫቦ ወደ ትምህርት ቤታችን የመጡት።

አቶ አሰፋ በጉርድ ላንድሮቨር ሲመጡ ተማሪዎች አሰገቧቸዉ ብለዉ ሲጮሁ ዋና መግቢያዉን በር ይጠብቁ የነበሩት ተማሪዎች አስገቧቸዉ። ከዚያም ሰንደቅ አላማ የሚከበርበት ቦታ መኪናዉን አቁመዉ ከመኪና ሲወጡ ተማሪዎች ከበቧቸዉ። ከዚያም ተማሪዎች ጪኸታቸዉን ማሰማት ጀመሩ። አቶ አሰፋ የላንድሮቨሩ ሞተር ኮፈን ላይ ቆመዉ ሳለ የድምጽ ማጉያ ተሰጥቶአቸዉ ከተማሪዎች ጥያቄ መቀበል ጀመሩ። ከዚያም መልስ መስጠት ጀመሩ። ተማሪዎች በጥሞና አዳመጧቸዉ። እርሳቸዉም “…ይህቺ የዴሞ ቅስቀሳ ነች። ትምህርታችሁን ብትከታተሉ ይበልጥ ትጠቀማላችሁ…” ብለዉ ተናገሩ። ሌሎች መልሶችም ባያረኩን እንኳ እሳቸዉ ምልስ ሊሰጡ እንደማይችሉ ተማሪዎች የተረዱትም ይመስለኛል። በቦክስ የተመቱና የደሙ ተማሪዎች በአምቡላንስ ወደ ሆሲፒታል ተላኩ። ጥቃቱን የፈጸሙ ተማሪዎች ከተጠያቂነት እንደማይድኑ አቶ አሰፋ ማሳሰቢያ ሰጡ። ይህ እየሆነ ሳለ የመቶ አለቃ ጳዉሎስ ቦጋለ መጥቶ አቶ አሰፋ እንዲናገር እድል ሲሰጠዉ ድምጽ ማጉያዉን ተቀበሎ መደንፋት ጀመረ። “…የአድሀሪያን ልጆች የሬሳ ሳጥን በሚያክል አገልግል ፍትፍትና ጭኮ እየተላከላቸዉ ተንደላቅቀዉ እየተማሩ የጭቁን ልጆች እንዳይማሩ ለማድረግ የተጠነሰሰ ሴራ ነዉ…” እያለ ደነፋ። ብዙ ዛቻዎችንም ዛተ። ከዚያም አቶ አሰፋ ከመቶ አለቃ ጳዉሎስ ጋር ለጥቂት ደቂቃዎች ተነጋገረ። የመቶ አለቃ ጳዉሎስ እየተቆጨ ሲናገር እንደነበር ታዘብኩ። ኮሎኔል ተስፋዬ የሚባል የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉን መርቶ የመጣዉ ወደነርሱ ጠጋ ብሎ የነገሩትን ሰምቶ ሄደ። ከዚያም አቶ አሰፋ ለዚያኑ ቀን ትምህርት እንደሌለና ወደ ቤታችን እንድንሄድ ነገሩን። እኛም ወደ ቤት ስንሄድ የታዘብኩት ነገር ቢኖር የመቶ አለቃ ጳዉሎስ ቦጋለ ከአቶ አሰፋ ጋር ሲጨቃጨቅ እንደነበር ነዉ። በወቅቱ ከጓደኞቼ ጋር ስንነጋገር የደረስንበት መደምደሚያ ቢኖር የመቶ አለቃ ጳዉሎስ እርምጃ ለመዉሰድ ፈልጎ በአቶ አሰፋ እምቢተኝነትና ተጽእኖ ደም ላይፈስ እንዳልቻለ ነዉ። በወቅቱ ቁጥሩ አንድ መቶ የሚሆነዉ የፈጥኖ ደራሽ ሀይል የግድያ ትእዛዝ ቢሰጠዉ ኖሮ ምን ያህል ተማሪ እንደሚሞት መገመት አያዳግትም.። በተማሪዎችም ዘንድ አቶ አሰፋ ክብር ሊያገኙም ችለዋል ይህችን ዉለታ ለተማሪዎች ስለዋሉ።

ከአቶ አሰፋ ጋር በርእዮተ አለም አመለካከት ብለያይም አንኳ በእርሳቸዉ ብርታት ከሞት ልድን ችያለሁ። በወቅቱ ከከበቡን ፈጥኖ ደራሾች ቢያንስ ወደ አስር የሚሆኑትን አዉቃቸዋለሁ። ተማሪዎች የነበሩ ናቸዉ። በሌላ ወቅት አግኝቼ ስጠይቃቸዉ በአቶ አሰፋ እምቢተኝነት የመቶ አለቃ ጳዉሎስ ቦጋለ ትእዛዝ ለመስጠት እንዳልፈለገ አዛዣቸዉ የነበረዉ ኮሎኔል ተስፋዬ እንደነገራቸዉ አጫወቱኝ። ትእዛዝ ቢሰጣቸዉ ኖሮ እኔንም ሊገድሉ እንደሚችሉ ነገሩኝ። እኔም የህችን የአቶ አሰፋን ዉለታ ሁል ጊዜ እንዳስታዉስ አደረገኝ። አቶ አሰፋን ወድጄ አላዉቅም። ግን ይህ ዉለታቸዉ እንዳከብራቸዉ አድሮጎኛል።

ብዙ ሰዎችን አስገድለዋል የሚል ክስና ስሞታ በተደረጉት ትችቶች ዉስጥ ተካትተዋል። አርባ ምንጭ ዉስጥ የተደረጉት ግርፊያዎች ናቸዉ የኢሕአፓን አባላትና ደጋፊዎች ለማጋለጥ ተብሎ። ፋሺስቱ አሊ ሙሳ በገዛ እጁ የገደላቸዉ አተ ተፈሪ (የእኔ ዘመድ የሆነችዉ አየለች ማመጫ ባለቤት)፣ ክፈተዉ (የአጎቴ ባለቤት ወንድም)፣ እና ኑሩ (አቶ አሰፋ ሲታሰሩ በእርሳቸዉ ምትክ የተመደበዉ) ሲሆኑ አርባ ምንጭ ዉስጥ ምንም የፖለቲካ ግድያ አልተካሄደም። አንድም የኢሕአፓ አባል አልተገደለም። ግርፋት ግን ተካሂዷል። በጎፋ አዉራጃ ዋና ከተማ ሳዉላ ከተማ የመቶ አለቃ ጳዉሎስ ቦጋለ ፊዉዳሎች ናቸዉ ብሎ የረሸናቸዉ ጥቂት ግለሰቦች ናቸዉ። የገለብና ሀመር ባኮ አዉራጃ ዋና ከተማ ዉስጥ አንድ የጊዶሌ ተወላጅ የሆነ ካድሬ አንድ ነጋዴ ገድሏል። እ. ኢ. አ. በነሐሴ ወር 1976 ዓ. ም. (August 1984 G. C.) ለትምህርት ኢትዮጵያን ለቅቄ እስከምወጣ ድረስ እዚያዉ ጋሞ ጎፋ የኖርኩ ስለሆነ ሁኔታዎችን ጠንቅቄ አዉቃለሁ። በአቶ አሰፋ ላይ የተደረገዉ አሳዛኝ ትችት ከእዉነት የራቀ መሆኑ በጣም አሳዘነኝ። ጸሀፊዎቹና ተቺዎቹ ከተባራሪ ወሬ የቀሰሙትን ነገር እንደ እዉነታ አድርገዉ ማቅረባቸዉ ዋጋ ቢስነቱን ከማጋለጥ በስተቀር የሚያመጣዉ ነገር ያለ አይመስለኝም። አቶ አሰፋ ቢጠየቁም እንኳ በኢሕአፓነት ተጠርጥረዉና ታስረዉ ለተገረፉት እንጂ በአስገዳይነት አይደለም። ብዙ ተማሪዎች በኢሕአፓነት ተጠርጥረዉ በተለያዩ ቦታዎች ታስረዉና ተገርፈዉ ወደ ሰላማዊ ኑሮና ትምህርት እንዲመለሱ ተደርጓል። ግድያ እንዳይካሄድ ካድሬዎች እንኳ አቶ አሰፋን ያሙ የነበረ ለመሆኑ ሲነገር ሰምቻለሁ። አቶ አሰፋ ኢሕአፓዎች እንዳይገደሉ አድርገዋል። ጋሞ ጎፋ ዉስጥ ባጠቃላይ እስራትና ግርፊያ ተካሄደ እንጂ የፖለቲካ ግድያ አልተካሄደም። ይህ ደግሞ በአዲሰ አበባና ሌሎች ከተሞች አንዳንድ የቀበሌ ሊቀመናብርት በቀይ ሽብር ወቅት ወጣቶች እንዳይገደሉባቸዉ ያስሯቸዉና ይገርፏቸዉ ከነበረዉ በምንም ተአምር አይለይም።

ኢሕአፓዎች ያደረጉትስ የከተማ ቃፊር የግድያ ዘመቻ እና በመካከላቸዉ በነበረዉ የፖለቲካ መከፋፈል እርስ በእርስ የተጋደሉት፤ እንዲሁም ወጣቱን ያስጨረሱት ተረሳና የአቶ አሰፋ ድርጊት ጎልቶ ታይቶ ነዉ ወይ እንዲህ አይነቱ ትችት የተደረገዉ? ትችት በትክክል መረጃ ተይዞ ሲቀርብ ያምራል። ያለበለዚያ ቂም መወጣጫ ወይም ለፖለቲካ ፍጆታ ይዉላል። ደርግም፣ ኢሕአፓም፣ መኢሶንም፣ ወያኔም ሆን ማንም ድርጅትም ሆነ ግለሰብ ከተጠያቂነት አይድንም።

ኢትዮጵያ ለሁላችንም እኩል እናት አገር ነች። ማንም ከማንም አይበልጥም። የበደሏት፣ የገደሏትና የሞቱላትም እንዲሁ አሉ። እያንዳንዱ ትዉልድ የራሱ የሆነ ባህርይ እንዳለዉ ሁሉ ለቀጣዩ ትዉልድ የሚያስተላልፈዉ ትምህርት ገንቢ ሀሳብና ራእይ ያለዉ ቢሆን ይመረጣል። ካልሆነም ደግሞ የታሪክ ተወቃሽ ሆኖ ይቀራል። አገር በቂም በቀል የሚመራ መሆን የለበትም። ታሪክም ቢሆን የሚጻፈዉ በቂም በቀል አይደለም። ወቀሳ፣ ትችትና ሂስ ገንቢ የሚሆኑት አግባብ ባለዉ ሁኔታ ሲፈጸሙ ነዉ። ታሪክም እንዳይወቅሰን ደግሞ ብናስብበት የበለጠ ጠቃሚነት አለዉ ብዬ አምናለሁ።

ሺመልስ አበበ
shimelisabebe@gmail.com

The post አቶ አሰፋ ጫቦን ለቀቅ… ከሺመልስ አበበ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>