Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የውስጥ እንደራሴ –እንደ ህዝብ … –ሥርጉተ ሥላሴ

$
0
0

ሥርጉተ ሥላሴ 25.02.2015 /ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ/

676

የትውልድ ፍካቱ ሲታይ በምህረቱ – ህይወቱ።

እስትንፋስ ቅምረቱ፤ ሲሳይ ሃብትነቱ – ነብያቱ።

ዕሴት ነፍስነቱ፤ ሊቀ ሊቃውንቱ – ህዝብነቱ።

አብነት መክሊቱ – ብሩክ ቀናነቱ፤ ብላቴ – ወተቱ።

ነበር ለናቱ ድር ማገር – ቀንና ህብስቱ።

ከውስጡ ዕውነቱ። ዓናቱ –  በአንቱ።

ጥበብ ቤቷን ሳርታ – ማዱንም ሰጥታ፣

እልል ብላ ኩላ – ማጫ አማትታ፣

አፍሪካን አቅልማ – ቅኔውን አጉልታ፤

ዘሃውን – በድጓ፤ ንባቡን – በዕድማታ

ዜማውን – በዜማ፤ ጣዕሙነን – አሰርፃ – አቅንታ

ትርጉም – በሥም ሠርታ

ተክሊል – አቀዳጅታ

ከሁሉ አቃ – – አልቃ – አልቃ — በሜሮን ቀብታ!

ቃን – ሰጠችን፤ መርቃ – አድምቃ!

የኔታን ሸለመች – ሸማ አጎናጽፋ!

ምን አለ በሥጋ – ሞት ባይኖር – ሞት ባይኖር

በመኖር – በመኖር።       12.02.2015 / ቪንተርቱር/

ሳያሾልክ – ጊዜውን፤ ሳያስተጓጉል – ጸጋውን፤ ሥጦታን አብርቶ የመራ እንደ አንድ ዜጋ ወይንም ቀንጣ ፍጥረት ሳይሆን እንደ አንድ የሰከነ፣ ልበ ሙሉ ጨዋ ህዝብ ሊታይ የሚገባው የአህጉራችን ቀንድ ነበር ብላቴ ጌታ ሎሬዬት ጸጋዬ ገበረመድህን። የቅኔው ዐፄ መንፈሱ ቀናይ ነበር ለአፈሩና – ለባዕቱ። የሥነ ጥበቡ አባወራ ህሊናው ብሩህ ነበር ለሰንደቅዓላማው ለአረንጓዴ ቢጫ ቀዩ። ለተውኔት ዕድገት ዓምዱ ነበረ – ርስቱ፤ ብሄራዊ ነፃነቱ ክብረ ዘውዱ ነበር – ጉልቱ። ለቋንቋ ሥልጣኔ አንጎል ነበር ጌታዬ – የኔታ።

በጥምረት ብቃቶቹ ለአፍሪካ ጠሐይነቱ፤ ለዓለም ሙቀት ነበር የሥነ ጥበብ እጬጌው ብላቴ ጌታ ሎሬዬት ጸጋዬ ገ/መድህን። የብላቴ ጌታ ዬትንፋሾቹ ዘር ቆሞስ ነበሩ። ዘሮቹ ደግሞ የኢትዮጵያዊነት ማህተመ – ህሊና። ጠብታው ተስፋ ነበር – የማግሥት ገቨር። ተስፋውም ሀገሩ ኢትዮጵያ በነፃነት ጸንታ – ደምቃ  – በቅታ – ልቃ መታዬት ነበር የባተለበት – የውስጠ – ህትምቱ። ከቅንጣቷ ነገር እስከ ግዙፉ የሀገሩ ጠረን ድረስ ለብላቴው ትርጉማቸው፣ ንባባቸው፤ ሚስጢራቸው የድህንት ቁርባኖች ነበሩ – አልፋና ኦሜጋ። የማይገሰሱ – የማይደፈሩ – የሚያበሩ የማይሰበሩ መንፈሰ ዕሴቶች። ቀንዲል።

ባለቅኔው – ገጣሚው – ጸሐፊው፣ ሐያሲው፤ መምህሩ፤ የሰብዕዊ መብት ተሟጋቹ ብላቴ  የሚያውቀው ኢትዮጵያዊነቱንና ሰው መሆኑን ብቻ ነበር። ብላቴ የሚያወቀው የጥቁር አፈር የእማማ አፍሪካ ጥሪኝ ንጥር ውጤት መሆኑን ብቻ ነበር። ብላቴ  በኢዮጵያዊነቱ ሳያፍር፣ አንገቱን ሳይደፋ ቀና ብሎ ነበር የኖረው፤ የሐገር ሃበትነትነቱን ለአደባባይ ያበቃውም በዚህ ማህሌት ውስጥ ነበር፤ የታሪክ ማማ ነበር ለእማማ። ሥነ – ጥበብን በሁለንታናዊ ሁለመናነት ብድግ አድርጎ ያሳደገ – በትረ፤ ኢትዮጵያዊነትን ልቡ ያደረገ ህብረ ሙሴ! ኑሮው ከውስጡ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ጠረን የተቃኘ፤ ፀዳሉ ፍሉቅ – ፍሬውም ዘለቅ ነበር የአብነት ትምህርት ቤትነቱ። ዬማንነቱ ጽናጽለ ድምጸ – ደም ግባቱ ሆነ ብሄራዊ ግርማ ሞገሱ ሚዛን የማይወጣለት ዘለግ ያለ ዕድሜ ጠገብ ነበር ጎልቶ የሚታይ፣ ሁለመናው መጠነ ሰፊ፣ ባለ ብዙ ዘርፍ ትውፊተ ውርስ ነው። በብላቴ መንፈስ ውስጥ የልዩነት ጸላዬ ሰናይ ሊቀርብ አይችልም ነበር። ስለምን? የብላቴ መስቀል ኢትዮጵያ ነበረችና። ጋኔሉን ሁሉ የሚያባርርበት – የሚከካበት ጽናቱ፣ ኃይሉ፣ መድህኑ ኢትዮጵያዊነተ – መስቀሉ ነበር የሁለመናው መናገሻ – መዲናው፤ መተንፈሻ ቧንቧውም። የብላቴ ዕምነተ – ሃይማኖት ኢትዮጵያዊነት ነበርና። የብላቴ ቀለመ ጥልፉ ኢትዮጵያዊነት ብቻ። የብላቴ ባህል መሪ ኢትዮጵያዊነት ብቻ። የብላቴ ወግ ኢትዮጵያዊነት ብቻ። የብላቴ ዘር ግንድ ኢትዮጵያዊነት ብቻ። ትውፊቱም – እሱ። ምግባሩም ትውፊት፤ እሱ – በእሱ እንቁላሌ በእንቁላሌ የተሠራ የልዕልት ኢትዮጵያ የማህጸኗ ርትሃዊ ጠሐይ ብቻ ሳይሆን የማንንት – የእኛነት የብርሃን ሃዲድ መሃንዲስ ነበር።

ጋሼ ጸጋዬ እንደ አባትነቱ – አባት። እንደ መሪነቱ ቆፍጣና – መሪ። እንደ ሥጦታው የሥነ ጥበብን ህግጋትን ያከበረ – የተገበረ፤ ለህግጋቱ የተገዛ፤ ለሰው ልጆች እኩልነትና ነፃነት ታግሎ ያስተማረ – ዕውነት፤ በሰውነቱ እንደ ሰው የኖረ ብቻ ሳይሆን ሰው መሆንን ሆኖ በቁሙ የሰበከ፤ ሲያልፍም መንፈሱን በመምህርነት – በሐዋርያነት ተክሎ አፅድቆ በሥጋ የካቲት 25.2006 እ.አ.አ ልክ ዛሬን ቀን የተለዬ ታላቅ አህጉራችን ነው። ክፍለ ዘመናችን ነው።

እያንዳንዷ እርምጃው፤ የስንኞቹ ጉዞ የአኃቲነት ተዘውታሪነት ( the unit of frequency) ንድፋቸው ሆነ ንቃሳታቸ አይራገጡ – አይፈነጩ – አያዘግሙ – አይቆራርጡ – አይታበዩ – አያፈርሱ – አይጫድሩ – አይቦጫጭሩ – አያዘግሙ፤ አይለግሙ – አይድኹ፤ አይዋጉ፤ ብጥብጥ አይፈጥሩ፣ አያሯሩጡ – አያደፍጡ – አይቆጡ – አያዳሉ፤ አያሳክኩ – ትናጋ አያስደርቁ፤ ትንፋሽ ነስተው – አይነዶለደሎ፤ በዘፈቀደ አይራማዱ፤ ጠብ ጠማኝ ብለው አንባጎሮ አያስነሱ፤ አያንዘላልጡም ነበር፤ ከማዕዳችን ውስጥ እንጂ በዝንፈት ውጪውን ሳያውቁ የሰበሉ ነበሩ። ፍሬዎቹ አይጎረብጡ – አይፈልጡ – አይቆርጡ፤ – አይቀዱ – አይቦጫጭቁ፤ አያስሩ – አይቀፈድዱ፤ አያስሉም ወይንም አይሰለቹም። ይልቁንም በቅኑ ለግላጋ ጽዑም ለዛ ሰተት ብለው በትህትና ከውስጥ ለውስጥ አጋብተው ከነጩ ደም እንደ ነጩ፣ ከቀዩ ደም እንደ ቀዩ፣ ከፕላዝማው ደግሞ እንደ ፕላዝማ አብረው እንደ ተፈጠሩ ቀዶ ጥገና ሳያስፈልጋቸው ልክክ ብለው በማያዳግም ሁኔታ የራስ አካል መሆን የሚችሉ ማህተሞች ናቸው። የመንፈሱ ጭማቂዎች – ፈውስ መድህኖችና ለማዳ ሲሆኑ ለጥበቡ እራሱ የፊደል ገበታዎች ናቸው – ለዚህም ነው ጸጋዬ ቤት የሚባለው። እርግጥ ረቂቅና ጥልቅ ከመሆናቸውም በላይ አጥኑኝ የሚሉ ናቸው። በግርድፍ ወይንም በድምስስ መሄድ አይቻልባቸውም ወይንም አይጋልብባቸውም። ፍልስፍና ብቻ ሳይሆኑ ሥራዎቹ የምርምር ተግባር የመሆንን አቅም ያላቸው፤ ለወደፊቱ ትውልድ እንደ አንድ ሥርዓተ ትምህርት ተቀርፆላቸው ዜጎች የሚመረቁባቸው አቅም ናቸው። ለዚህ በህይወት እስካለን ድረስ ለቋንቋ እድገትና ብልጽግና ተስፋ ያለን፤ ለቋንቋችን ቀናይ ሰዎች ተግተን እንሠረበታለን። ለነገሩ የአማርኛ ቋንቋ ዕለተ ተንሥኤ እኮ ዘወትራዊ ሁኗል። ፋሽስትን ድል አድርጎ እራሱን ነፃ ያወጣ ቋንቋ ቢኖር አማርኛ ቋንቋ ነው። እኛን ቀደምን አንባሳደራችን – የፊደል ገበታችን። ካቴናውን ሁሉ አመድ አድርጎ በጣጥሶ እንሆ ጉብ አለ ከአናት። ጉልላት ሆነ ተናፋቂው!

የጌታ ብላቴ የመንፈስ ጭማቂዎች ልዩ፣ ከልዩ የፈለቁ በመሆናቸው ሥጋን በስተው ነዳለ ወይንም ቀዳዳ አይፈጥሩም። ወይንም አሽገው አይለጉሙም። ነፃነት የሸለሙ የፍትህ ሚዛኖች ናቸው። ምህረትን የሚያውጁ ፍትኃተ – አንባ ናቸው። ራሳቸው ነፃ የወጡ እንዲሁም ሌላውንም ከአርነት የሚታደጉ ትጉኽ አርበኞችም። ስለምን? መነሻቸው ከላቀውና ዓለምን ከፈጠረው ፈተናን አሸንፎ ከተፈጠረው ሚስጢር የተቀዱ ማንነትን የነገሡ ናቸውና። ተፈጥሯዊ ናቸው። ማስዋቢያ ደባልነት አይሻቸውም። ሲፈጠሩ ተኩለው ነው። ስክነታቸው የተንጠባጠቡ ወይንም የሚፈራገጡ ወይንም ጥገና የሚያስፈልጋቸው ጋድም ልስኖች አይደሉም። ተቀብተው የተፈጠሩ ቅብዕ – ቅዱሶች እንጂ። አንዱ እርእሥ እራሱ ብቻውን ሲሰላ ዓዋጅ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ሥነ ጹሑፍ ህገ = መንግሥት ሆኖ እናገኘዋለን።

የዬኔታው የፊደላት ምት ፍሰት፣ እንዲሁም ሐረጋማ ወጥነት ሆነ የቃላቱና የፍቺው ሂደት ትንፋሽና መንፈስ የገነት ብር አንባር ነው። በቃላቶች ደም ውስጥ ያሉ ሴሎች ሁሉ ንቁና ትጉኃንም መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ዝቅ ብለው ለማገልግል የወሰኑና የሆኑም ናቸው። የፍላጎቶቹ አቅጣጫ ሁሉ የሀገርን መኖርን፤ የነፃነትን ተፈጥሮ፤ የዜግንትን ፍሬ ነገር፤ የአብሮነትን ቃናዊ ጣዕም፤ የቀለምን ቀለማማነት ጌጣማ ትርፍ በጥንቃቄና በማስተዋል፤ እንዲሁም በአርምሞና በተደሞ የተረጎሙ ቋሚ የዝባድ ሐውልቶቻችን ናቸው። በጋሼ ጸጋዬ ቤት በሰው ልጆች ተፈጥሮ ውስጥ ደንበር፤ ወሰን፤ ክልል፤ አልተከተረም። በፍጹም። ሰው እንደ ሰው ቁሞ የሚሄደው 24 አካላቱ ተሽንሽኖ ሳይሆን እንደ ተፈጥሯቸው በሰመረ አኃቲነት መኖር ሲችሉ ስለመሆናቸው ሊቀ ሊቃውንቱ ሆኖበት – ኖሮበታል። ህይወቱ እራሱ ብቁ ሰባኪ ነበር ማለት እችላለሁ። ሥራዎቹ ማህደራቸው „ሰው መሆንን“ ብቻ ያወድሳሉ – ያነግሣሉ። ያቀስሳሉ – ይዳኛሉ። በዬኔታ ብላቴ ዕዝነ ህሊና ውስጥ „ሰው“ በባህል፤ በጎሳ፤ በኑሮ ደረጃ፤ በኃይማኖት አልተሸነሸነም። ለጋሼ ጸጋዬ እንደ ቃሉ „ሰው ማለት ፈጣሪ በአምሳሉ ባርኮና ቀድሶ፤ እንደ እራሱ አድርጎ እንዲያመሰግነው የፈጠረው የተፈጥሮ የላቀው ቅዱስ ፍጡር ነው“ ብሎ ነበር የሚያምነው።

ስለዚህ ጋሼ ጸጋዬ ዕምነቱና ፍላጎቱ፤ ስሜቱና ራዕዩ፤ አስትምህሮቱና አቅጣጫው፤ ዶግማውና ቅኖናው፤ ህልሙና ግብዕቱ መነሻቸው ሆነ መድረሻቸው „እንደ ሰው ተፈጥሮ እንደ ሰው ዬመኖርን ህግጋት የደነገጉ፤ በተመክሮ የበሰሉ ለዬዘመኑ ብሩህ ቋሚ ህገ – አምዶች ናቸው። ተቋማት። የዬኔታ ጌታ ብላቴ ወርቆች ከጓሮ ቀጭጨው የቀሩ ሳይሆኑ ይልቁንም  ዓለምን ያስደመሙ በድምቀትም ቦግ ብለው ያበሩ ጨረራማ ዘመናዊ ሞገዶች ናቸው። ሥራዎቹ በራሳቸው የተማመኑ፤ የትውልድን ኃላፊንት በብቃት የተወጡ ዕጹቦች ናቸው። „የወንድ ልጅ ዕንባውን … „_ እርእሱን ብቻ ቁጭ አድርጋችሁ እዩት። ተፈጥሮን በፆታ የመረመረ፣ አዳምን ያመሳጠረ፣ የተረጎመ የዘለቀ ተግባር ነው። የሊቁ የሊወናርዱ ዳቬንቺን የአዳምና የመንፈስ ጉዞ በፈጣሪ ርቁቅ ዶግማ ያሳዬውን ሥዕል አባታችን አናገረው ሚስጢሩን። ሳይንስ – ፍለስፍና – የተፈጥሮ ሚስጢር የተገለጠለት – ኑሮን በአግባቡ ለማድመጥ የጠራ ጆሮ ያለው አድርጎ መፍጠሩን እርእሱ ብቻውን ይነግራችኋል። ከዚህ በተጨማሪ … የሊቀ ሊቃውንቱ ብላቴ ሎሬዬት ጸጋዬ ገ/መድህን ተግባራት ንዝረቱ ይሰበስባል ወደ ቤት እዩ፤ በውስጡም ኑሩ ይላል። ይጣራል፣ ውበታችሁን መርምሩና አጊጡበት፤ አላችሁ ተዝቆ የማያልቅ፤ ያልደረሳችሁበትም ከከርሰ ምድር በላይና በታች በደምና በሥጋችሁ ቅንብርና ቅምረት ዕንቁ አለና ገስግሱ ወደ ውስጥነታችሁ በጋራ ይላል፤ አታባክኑ ጸጋችሁንም በማለት አብዝተው ይመክራሉ። ውበታችሁን አቆሽሻችሁ መልከ ጥፉ አትሁኑ ይላሉ – ትንቢትም ይናገራሉ። አዎና! –  ያናግራሉ በርትሁ አንደበት ….. ልሳን አላቸውና።

…. ጋሼ ፀጋዬ የጸደቀው ሲፈጠር ነው። ስለምን „ሰውን“ መተርጎም ስለ ቻለ። አባቴ – ህገ ወንጌልን አልተላለፈም፤ ወይንም ቁራዕንን ወይንም ባህላዊ የዕምነት ሌሎች አንባዎችን። ስለዚህ እራሱ ጋሼ ፀጋዬ ህግ ነበር ማለት ይቻላል። የመኖርን ህግጋት ሠርቶልናል – በጋራ ቤታችን በኢትዮጵያ። ለዛውም እያባበለ – እያቆላመጠ –  እያስማማ – እንደ ነፋሻማ ጅረት አስክኖ እዬመራ። ሰውነት እዬደባበሱ እያከሙ በውስጥ ለውስጥ በሚጓዙት ቅኔዎቹ፤ በስንኝ – ጧፎቹ፤ በጥበብ ሐረጋማ ሥነ – ህሊናው፤ ትብስ ትብሺ ተባብለን፣ ቤት ያፈራውን በፍቅር ተካፍለን፣ ክብራችን ጠብቀን፣ በእኩልነት በአፈራችን እንኖር ዘንድ ሐዋርያነት። ተመክሮው ለብሄራዊ ነፃነታችን አደራ በይ ሳንሆን ዘብ እንቆም ዘንድ እንጂ ለጎጥ ጨረታ ቀርበን ሰብዕናችን ቀረመት እንዲውል አልነበረም ያስተማረን። የአፍሪካ አቅም እንሆን ዘንድ፤ የአለም ጉልበት እንሆን ዘንድ ነበር ዝቅ ብሎ የመከረን። የሥነ ጥበብን ሥነ – ተፈጥሮ ብርንዶ በአፋ አፋችን ሲያጎርሰን – ኢትዮጵያዊነት ዜግነታችነን ውጠን ኃይል እንሆን ዘንድ ብቻ ነው እንጂ …. መጠጊያ ጥርኝ  አፈር በባዕታችን ተነፍገን አፈር ለማኝ ወይንም በክትና በዘወትር ልጅነት ሰብዕናችን ተድጦ በግርድና በባርነት እንኖር ዘንድ አላሰተማረንም። ለህትምት የበቃውን „እሳት ወይ አባባ መድብሉን“ በማስተዋል እንደ ጸሎት መጸሐፋችን ማለት እንደ ውዳሴ ማርያም ወይንም እንደ ድርሳነ ሚኬኤል ብንመላለስበት የዬኔታ ጌታ ብላቴን ሎሬት ጸጋዬን ገ/መድህን ተፈጥሮ ሚስጢር የፍጽምናን ተፈጥሮ ማዬት እንችላለን። ሚስጢሩን ስናገኘው ዘመን ባመጣው የጥፋት ውሃ መረከብ ገብትን በመጠመድ ጊዜም አናጠፋም። በጎጥ ሱሰኝነት በሽታም ሆነ ጉንፋን አንጠቃም። ዘርም ከሥሩ አፍልሰን የእርግማን ምርተኛ ሆነ ሞርተኞች አንሆንም። ይልቁንም ወደ አትራፊ የወል ጉዳያችን በመረዳዳት – እናተኩራለን። አቅምም – አናባክንም። ልዕልት ኢትዮጵያን አብርተን በጸጋዎቿ እናሳድጋታለን። ፍቅርን – እናውቃለን። ፍቅር ማወቅ ብቻ ነው ዬአዋቂነት መለኪያው – ዬዕድሜም እንዲሁ። ፍቅር መኖርን ብቻ ሳይሆን ዘመንን ሆነ ወቅትን እንደ ባህሬው ያኖራል። ፍቅር ለሀገር ልዑላዊነት ኤዶሙ ነው።

እንደ እኔ መጠመድ ከሌላ ሥራ ይሠራል – መኖርም ይኖራል። ተጽዕኖን በግል የሚጫኑ ወይንም በሌላው የሚጥሉ ቢታቀቡ የነፃነት ፊደል በመንፈስ ተቆጠረ ማለት ነው። ነገር ግን እንደሚታዬው ከሆነ በብዙ ሁኔታ ሰው እራሱን አስሮታል። ገድቦታል። ሌላውንም ለማሰርም ይንደፋደፋል። ስለምን? ከሰው ምክንያታዊ ተፈጥሮ ዝንፍ ስለሚል። አልፎ ተርፎም ዬእያንዳንዱ የሰው ልጆች እንቅስቃሴ እዬጎረጎረ ሰላምንና ነፃነትን ይነስታል። ይህ ድርጊት ተነሳቹን ወይንም ተጠቂውን ብቻ ሳይሆን የነሳቹን ወይንም የአጥቂውን ኩርማ መንፈስም ያውካል። ስለምን? እኩይ ተግባር መንፈሱ እራሱ እውክና ተራጋጭ ነውና። ስለሆነም በግራ ቀኙ በኩል ዬነፃነት ጥርኝ ለማኝ ይሆናል ማለት ነው። ውቅያኖሶች ሲቀዝፉ በነፃነት ነው። ነፋስም ሲዳንስ እንዲሁ። ወፎችም በባንዳቸው ሲዘምሩ በመሰሉ። ብርሃን ሲጨፍርም – በነፃነት። ሰውም እንዲህ እንዲሆን ነበር የተፈጠረው፤ ቢያንስ በእጁ ባለው ነገር ላይ እንዲወስን – አንዲሆነውም። በሌላውም ላይ እራፊ ግፊያ እንዳያደርግም። ግን የሚታዬው በተቃራኒው ነው። መቅዘፊውን መንፈስ በመስበር በጠባቡ ጉሮኖ ውስጥ ገብቶ አዬር ማጣት፣ ማሳጣትም – በፈቃድ። ስለምን? – አላውቅም። ሰው ወዶ እንዴት ያለተገደበውን ነፃነት እራሱ ግድብ ይሠራለታል? በሌላው ላይስ ለምን? አንድ ጥብቆ ክፍል ከስድስት ወይንም ከሰባት ቢከፈል መግቢያ ሊኖረው ይችላል ይሆናል። ማኖር ግን አይችልም። ቢያንስ የጋሼ ጸጋዬ አድናቂዎች፤ አክባሪዎች፤ ወዳጆች፤ ፈለጉን የተከተሉ፤ ሥሙን የሚያነሱ፣ አብነቱን ለመከተል የቆረጡ፤ የሚዘምሩለት ሆነ የሚያዜሙለት በእሱ መንፈስ – እሱ ባለፈበት ህይወት ውስጥ እራሳቸውን መለካት ያለባቸው ይመስለኛል። እኔንም ጨምሮ። ትክክል በልኩ ወይንስ ዝቅ …. ?

ክወና። የቅኔውን ልዑል የኔታ ብላቴ ጌታ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህንን በሥጋ መለዬቱን ስናስበው – ውስጣችን የሚሰማነን የከሰለ ሃዘን የሚክስልን መፍቻው አንድ ነው። ብቸኛው ፈውስ እሱ በቀዬሰው የፓን አፍሪካዊነት – ኢትዮጵያዊነት መንፈስ ለመኖር ቆርጦ መወስን ስንችል ብቻ ነው። እሱ በኖረበት እርግጠኛ ማንነት ውስጥ መኖር ስንችል ነው። ከህይወቱ ሆነ ከምግባሩ ለመማር ልቧችንና ህሊናችን ስንከፍት ነው። በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ብሩህ ሰንደቅ ዓላማችን ሥር ስንሰባሰብ። በመንፈሰም በአካልም።

ስለሆነም የአባትን አቋምን መቀበሉ ሳይሆን ፍሬ ነገሩ በውስጡ አለሁ የለሁም? ብሎ መፈታተን ያስፈልግ ይመስለኛል። የኔ ክብር፣ የእኔ ሃይማኖት አባትዓለም ነፍስህን አርያም ገነት ያኑርልን አምላካችን። አሜን! በተረፈ የፊታችን ሃሙስ በ26.02.2015 እ.ኤ.አ የመንፈሱ ውደሳ – በሥሙ በተሰዬመው የማስታወሻ ድምጸ ራዲዮ Radio Tsegaye  or www.lora.ch.tsegaye or www.tsegaye.ethio.info Aktuell Radio Sendung ላይ ልዩ ዝግጅት ይኖራል – በሁለት ጉዳይ። በምንና ምን? አዬር ላይ ከ15 – 16 ሰዓት ስንገናኝ ወይንም አርኬቡ ላይ በማግሥቱ ጊዜው ከኖረዎት ገብተው ሲያደምጡት ያገኙታል። አክብሮቱንም – ፍቅሩንም – ስስቱም – ናፍቆቱንም ሁሉንም በዘንካታ ትህትና ሰጥቼ ልሰናበት ወደድኩኝ። ነገ ሌላ ቀን ነውና በቀጣዩ በአዲስ ጉዳይ እስክንገናኝ ድረስ መኖሩ ከተገኘ ማለቴ ነው የእኔ ክብሮችና ማዕረጎቼ ደህና ሰንብቱልኝ። እግዚአብሄር ይስጥልኝ ዘሃበሻ ማህበራዊ ድህረ ገፅ – እጅግ አመሰግናለሁ።

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/13104

http://ethio.info/tsegaye/February2009/TESFA-ELEGY-FOR-TSEGAYE-GEBRE-MEDHINE.pdf

ጋሼ ጸጋዬ ለእኔ እንደ ህዝብ ሊታይ የሚገባው የወስጥም እንደራሴ! ስለምን? የመንፈሱ ሥነ – ፍላጎት ማህጸን ህዋስ ህዝብ ነውና! ሴሉ ደግሞ ዜግነተ – ኢትዮጵያዊነት! ክብር!

ለእኔስ ሰው መሆኔ ብቻ ይበቃኛል።

እግዚአብሄር ይስጥልኝ

The post የውስጥ እንደራሴ – እንደ ህዝብ … – ሥርጉተ ሥላሴ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>