ከአንድ ሰአት በላይ የፈጀውን ጥናታዊ ጵሁፍህን ሰማሁት። ሰምቼ ስጨርስ ደነገጥኩ። ከራሴም ጋር ለሰአታት ሙግት ገጠምኩ ። ኢህአዴግን ለቅቄ የወጣሁት ልቤ የፈቀደውን በነጳነት ለመናገር ነውና የማውቀውን እና የሚሰማኝን መናገር እንዳለብኝ ተሰማኝ ። ርግጥ በሐይማኖት ጉዳዬች ላይ መናገር ከባድ እንደሆነና ዋጋ እንደሚያስከፍል ጠንቅቄ አውቃለሁ ። በሌላ በኩል የሚያውቁትን አለመግለጵም የፀፀት ዋጋ አለው። በመሆኑም ባለመናገሬ ከሚሰማኝ ሙግት መናገሩን ስለመረጥኩ የሚከተለውን አጭር አስተያየት ለመስጠት ተገደድኩ።
1• ያቀረብከውን መረጃዎች እንዴት እንዳሰባሰብካቸው የተገለፀ ነገር የለም። በተለይም በድህረና ቅድመ ምርጫ 97 ባሉት ሶስት አመታት( ከኃላም ከፊትም) ያቀረብካቸውን መረጃዎች ምንጭ ማወቅ እፈልጋለሁ ። ይህን ጥያቄ የማነሳበት መሰረታዊ ምክንያቶች ስላሉኝ ነው።
1•1• በኢትዮጵያ አቆጣጠር 2001 አ• ም• ኢሕአዴግ ለሕዝቡ ይዞለት የመጣው እቅድ ” በአክራሪነት ” ስም ሀይማኖቶችን ማዳከም ነበር። ይህንንም ለማቀጣጠል እንዲረዳው በኢህአዴግ ቢሮ፣ በኮሙዩኒኬሽን ጵ/ ቤት፣ ፌደራል ጉዳዬች እና ፌደራል ፓሊስ መረጃ እንዲሰባሰቡ ተደረገ። የእስልምና ጉዳዬች ላይ ዝርዝር ጥናቱን እንዲሰራ የቤትስራ የተሰጠው ሽመልስ ከማል ነበር። ዛሬ አንተ ካቀረብክልን ውስጥ ግማሹ የቃላት ለውጥ እንኳን ሳይደረግለት በሽመልስ ከማል ጥናታዊ ፅሁፍ የቀረበ ነበር። በወቅቱ እጅግ ከመደንገጤ የተነሳ ሽመልስ እንዴት እንዲህ አይነት ጥናት እንደሰራ ለማወቅ ከጀርባው መጓዝ ነበረብኝ ። መጓዜ ያልጠበኩትን ውጤት አመጣ። ሽመልስ በእስልምና ላይ ከፍተኛ ጥላቻ የያዘው በቤተሰቡ ውስጥ በተፈጠረው ምስቅልቅል እድገት መሆኑን ተገነዘብኩ። አባቱ በአንድ ወቅት የመስኪድ አስተዳደር ነበሩ። በኃላ የሳውዲ ጉዞ አድርገው ሲመለሱ አስተዳደሩን በመነጠቃቸው ከሀይማኖቱ በተቃራኒ ተሰለፋ ። ” ከመካ መዲና ደርሶ መልስ” የሚል መጵሀፍ አሳትመው ክርስትና ተነሱ። ስማቸውም ወደ ሀይለየሱስ ተቀየረ። ባስታወቀው እርምጃ ቤታቸው ተመሰቃቀለ።ወንድማማች እና እህታማቾች የሚጠሩበት የአባት ስም እስከ መለያየት ደረሰ። ባጭሩ የሽመልስ ፀረ -እስላም የመሆን ምንጩ ይሄ ነው። በመሆኑም በሽመልስ ሲቀርቡ የነበሩ ዳታዎችና ትንታኔዎች እንደወረዱ ከአንተ ሲቀርቡ ስሰማ የመረጃ ምንጭህን ተጠራጠርኩ። በተለይ ቴኳንዶ ፣አክሱም፣ መያዶች …ወዘተ ብለህ የገለጵከው የካርቦን ግልባጭ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
1•2• ሌላኛው ዳታ የሰበሰበው የፌደራል ጉዳዬች ሚኒስተር የነበረው ዶክተር ሽፈራው ከፓሊስ ጋር በመሆን ነበር። ዶክተሩ ያጠናቀረው መረጃ ተመሳሳይ ሲሆን በማጠቃለያው ” የኦርቶዶክስ አክራሪነት አለ” የሚል ነበር። የአክራሪነቱ አስኳል ማህበረ ቅዱሳን እንደሆነ አፅንኦት ሰጥቶበት ነበር። ይህ የዶክተሩ መረጃ በአንተ ጥናታዊ ፅሁፍ ላይ አልቀረበም ።
( ግምቴን አስቀምጬ ለማለፍ ይህን የዶክተር ሽፈራው ዳታና ትንታኔ ለሌላ የእስልምና መምህር እንዲደርሰው ይደረግና እንደአንተ እንዲያቀርብ ይደረጋል ። ርዕሱንም ” የኦርቶዶክስ አክራሪነት ” ብሎ እንዲጠራው ይደረጋል ።)
2• የመረጃዎቹ ምንጭ እንደተጠበቀ ሆኖ ኩነቶቹ ሲፈጠሩ ሀገሪቷ የነበረችበትን ፓለቲካዊ ሁኔታ ከግምት አላስገባህም። ለምሳሌ ከምርጫ 97 በኃላ በኦሮሚያ የተከሰቱት የሐይማኖት ግጭቶች የተጠነሰሱት በአቶ መለስና ደህንነት ጵ/ ቤት ሲሆን ዋነኛ አሰፈጳሚዎቹ እነ አባዱላና የኦህዴድ ካድሬዎች ነበሩ። ” ቅንጅት የክርስቲያን ጠበቃ ነው” የሚለው መልእክት የተቀረፀው አንተ በጥናታዊ ጵሁፍህ ላይ ” ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል” የሚለው መርሆ አቀንቃኝ የሆነው አቶ በረከት ነው። በየጉራንጉሩ መልእክቱን ያሰራጩት ደግሞ ” እኔ ከሞትኩ… ” በሚለው ብሂል እነ አባዱላና ጁነዲን ናቸው። በተለይ በድሬደዋ የጠነሰሱት ሴራ ባይከሽፍ ኖሮ ዘግናኝ እልቂት ይከሰት ነበር። በመሆኑም ከምርጫ 97 በኃላ የተከሰቱት ግጭቶች ( በተለይ በኦሮሚያ) ጠንሳሾቹ አሁን እየመሩን ያሉት ፓለቲከኞች ሲሆኑ መንስኤውም ፓለቲካው የፈጠረው ነበር። አንተ ግን በየትኛው ቦታ ላይ የፓለቲከኞቹን ሚና ማንሳት አልፈለክም ። ይልቁንስ መንግስት አበረደው፣ መከላከያ አረገበው ማለትን መርጠሀል። ጥናትህን ሰፋ ብታደርገው ኢትየጵያ ውስጥ አክራሪነት በዋነኛነት እየሰፋ የሄደው በፓለቲካው መበላሸት ምክንያት የተፈጠረ መሆኑን ትደርስበት ነበር። አሁንማ በድጋሚ ለማየት ጊዜው አልረፈደም።
3• በጥናታዊ ጵሁፍህ ላይ በአሁን ሰአት ያለውን የኢትየጵያ ሙስሊሞች ” ኢትዬጲያዊነት የተላበሰ፣ ሰላማዊና ፍትሐዊ ጥያቄ” ማንሳት አልፈለክም ። እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የተቃወሙት የመንግስት ጣልቃ ገብነት ነው።ኢህአዴግ ከሀይማኖቱ ላይ እጁን እንዲያነሳ ነው በሰላማዊ መንገድ እየጠየቁ ያሉት። አመራራችን በእኛ ይመረጡ፣ ተቋማችንን ራሳችን እናስተዳድር የሚል ነው። ለዚህ ደግሞ እኔ በየትኛውም ቦታና ሰአት ምስክር መሆን እችላለሁ። ታዲያ አክራሪን፣ አክራሪ ካልሆነው ለይቶ የማስረዳት አላማ ካነገብክ ለምን ፍትሐዊ የሆነውን ይህን ጥያቄ ሳታነሳ ቀረህ? እንደ ገዥዎቻችን ” የሙስሊሙ ጥያቄ አክራሪነት የወለደው ነው” የምትለን ከሆነም ወደ መድረክ አውጣውና እንነጋገርበት ።
4• አጀንዳህ ስለ ” ሙስሊም አክራሪነት ” ሆኖ ወደ ማጠቃለያህ ላይ በውጭ ሀገር ያለውን ሲኖዶስ ወደ መዝለፍ ለምን ተሸጋገርክ። ከአንደበትህ የወጣው ቃል ” የሐሰት ሲኖዶስ ተቋቁሞ መንጋ የማይጠብቅ ጳጳሳት ይሾማል ” የሚል ነው። ይህ ንግግር በራሱ አንድነት የሚያመጣ ነው? ውጭ ያለው ሲኖዶስ የሐሰት ነው / አይደለም ከሚለው ትርክት በፊት ይህ እንዲፈጠር ያደረገው ምክንያት ምንድነው የሚለውን ብታነሳ የተሻለ መልስ ታገኝ እንደነበር እገምታለሁ። ሐገር ቤት ያለውን ሲኖዶስ ማን ከጀርባ ሆኖ እንደሚያሽከረክረው ካላወክ በኢትዮጵያ ምህዳር ላይ መኖርህን እንድጠራጠር ያደርገኛል።
4• ሌላኛው ” ለምን አሁን?፣ ምን አዲስ ነገር አለ?” የሚል ጥያቄ እንዳነሳ አድርጐኛል ። የሙስሊሞች ሰላማዊ ትግል በተጠናከረበት፣ መንግስት በጅምላ ማሰር በጀመረበት ፣ ማህበረ ቅዱሳን ላይ በተዛተበት ወቅት ለምን የሚከፋፍል አጀንዳ ይዞ ብቅ ማለት ተፈለገ? የማን አጀንዳ ነው እየተራመደ ያለው የሚለውን ማየት ተገቢ ይሆናል
Ermias Legess / የ መለስ ትሩፋቶች/
The post የመለስ ትሩፋቶች ደራሲ ኤርሚያስ ለገሰ ለዲያቆን ዳንኤል ክብረት የጻፈው ግልጽ ደብዳቤ appeared first on Zehabesha Amharic.