የካቲት ፳፫ ቀን ፪ሺህ፯ ዓም
ተፃፈ ከኣባ ሚካኤል።
ቸሩ መድኃኔ ዓለም ይመስገንና እርሱ በመጀመሪያ የሰውን ዘር ከዘለዓለማዊ ሞት ሊታደግ ሲመጣ ዓለሙ በሙሉ እርሱን ደስ የማያሰኝ የጌታ ጠላት ነበር። ጌታ መድኃኔ ዓለም ግን ለሰው ልጅ ያለው ፍቅር እርሱን ከዙፋኑ ስለሳበው ዕውነተኛ የፍቅር መሥዋትን ይህቺውም ሕይወቱን ኣሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ ወድዶናል፥ በደሙም ነፃ ኣውጥቶናል። ሕግ ሁሉ በፍቅር ስለሚፈጸም ጌታ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ ካለን በኋላ ጌታችን ያለው፦ እኔንስ ብትወዱ ትዕዛዜን ጠብቁ ነው፥ በዕውን ትዕዛዙን ጠብቃችኋል?
ዛሬ በኢትዮጵያ ሃገራችሁ ውስጥ ፖለቲካው ባመጣባችሁ በደል ምክንያት በተከበራችሁበት ሃገራችሁ ላይ ለመኖር ስላልቻላችሁ በዐራቱም ማዕዘናት ተሰድዳችሁ ባላችሁበት ክፍለ ዓለማቶች ሁሉ ኃይማኖታችሁን ጠብቃችሁ ቤተ ክርስቲያኖችንና መስጊዶችን ከፍታችሁ እየተገለገላችሁ ትገኛላችሁ። ይህንንም በማድረጋችሁ እራሳችሁን ታድጋችኋል፤ ይህም ለጊዜው መልካም ነው፥ ምንም ቢሆን እንደ ዕራስ ሃገር ኣይሆንምና።
ባላችሁበት ሥፍራ ሁናችሁ ደግሞ የሃገራችሁን ውሎና ኣዳር በትጋት ትከታተላላችሁ። ሁላችሁም “በዚያች ሃገር” ላይ ሳይሆን በኢትዮጵያ ሃገራችሁ ላይ ሠላም ወርዶና እርቅ ተደርጎ መቻቻልን የተዋሃደ ሕዝባዊና ፍህታዊ የሆነ መንግሥት ፈጥራችሁ እንዲሁም የመከላከያ ኃይሏ ለሕዝቧ እንዲያገለግል እንጂ ሥልጣን ላይ የሚወጣውን ጥቅም ኣስከባሪ እንዳይሆን ቀርጻችሁ ወደ ሃገራችሁ ተመልሳችሁ ተከብራችሁና ኣክብራችሁ መኖርን ትሻላችሁ።
በውድ ሃገራችን ላይ እንጂ በባዕድ ሃገር ላይ ኣንኖርም ያሉና በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩትን የእህቶቻችሁንና የወንድሞቻችሁን ሕይወት ስናይ ደግሞ ነፃነታችውን ለማግኘትና እናንተም በየሃገሩ ተበትናችሁ የምትገኙትን ወደ ሃገራችሁ እንድትመለሱ በሚያደርጉት ትግል ላይ እናንተ የፈራችሁትንና ከሃገር ያሳደዳችሁን ህዋሓት፦ እነርሱ በጠራራ ፀሐይ እየተጋፈጡት ድብደባ፣ እስራት፣ መሸማቀቅ፣ ረሃብ ወዘተ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛውን የፍቅርን ዋጋ ሞትን እየሞቱላችሁ ይገኛሉ።
የሚገርመኝ ቢኖር ክርስቲያኖች ወይም ሙስሊም ሆናችሁ ሳለ ጠላትህ ቢራብ ኣብላው፣ ቢጠማም ኣጠጣው፣ ቢራዝ ኣልብስው /ሮሜ ፲፪ ቁ ፳/ የሚለው የኣምላክ ቃል በየጊዜው እየተሰበከላችሁ ጠላቶቻችሁ ሳይሆኑ የገዛ ወንድሞቻችሁ እንኳን ቢራቡም፣ ቢጠሙም፣ ቢራቆቱም፣ በግፍ ቢገደሉም ወዘተ ፓትርያርኩም፣ ጳጳሱም፣ ቄሱም፣ ፓስተሩም፣ ሼሁም፣ ኢማሙም እንዲሁም ምዕመኑ ዝም። እግዚዖታን እንኳን ነፈጋችሗችው። በሃገር ቤቱስ ላሉት ውስጡን ለቄስ ነው፥ ህዋሓት ናት የሓይማኖቱን ሥራ የምትሠራው። ከሃገራችሁ ዕርቃችሁ በነፃነት የምትኖሩ ክርስቲያኖች እስቲ ቆም በሉ። በእውን የሞተላችሁን ክርስቶስን ትወዱታላችሁ? ትዕዛዙንስ ትፈጽማላችሁ? ኣምላካችሁ ክርስቶስ ለሞተላት ክብርት ቤተ ክርስቲያን ፍቅር ኣላችሁ? ወይስ ከኢትዮጵያ ጠላት ጋር ኣብሮ የወገኑ ሞት ለእርሱ ሕይወት እንደ ሆነለት ሆድኣደር ሆናችሁ? ሙስሊሞችስ?
ህዋሓት ዛሬ ሳይሆን ከ፳፬ ዓመት በፊት ጀምራ የኦርቶዶክስ ክርስቲያንና የእስልምናን ዕምነት ለማጥፋት በሚገባ የቤት ሥራዋን ሠርታ ዛሬ በተግባር እየተረጎመችው ነው። ንዋየ ቅዱሳኖችን ኣውጥታ ሽጣለች፣ ቤተ ክርስቲያንን ኣቃጥላለች፣ መነኮሳትን ከገዳም ድረስ በመሄድ ደብድባለች፣ በቅርቡም ኢትዮጵያ ካለው ሲኖዶስ ይልቅ ለኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሃገር ቤት ግልጋሎት የሚሰጠውን ማኅበረ ቅዱስንን ልትመታ ቃጥቷታል፥ ምንም እንኳን ማኅበረ ቅዱሳን ከሃገር ቤት ውጪ የተከፈቱትን ኣብያተ ክርስቲያናት ህዋሓት በሚቆጣጠረው በሃገር ቤቱ ሲናዶስ ሥር እንዲተዳድሩ በማድረግ ከፍ ያለ ሚና ቢጫወትም ለህዋሓት ማኅበረ ቅዱሳን ከኣብዮታዊ ዲሞክራሲው ኣይበልጥበትምና ከ፪ሺህ፯ ምርጫ በውኋላ ተመልሳ የቃጣችውን በተግባር ልታውል ትችላለች ብዬ እገምታለሁ፤ እስልምና ኃይማኖትን የሚመሩትን ትመርጣለች፤ ፕሮቴስታንቶቹን ደግሞ ኣንድ ቀን መንካቷ ኣይቀርም።
እስቲ እዩ፥ በኣካባቢያችሁ ስለ ኢትዮጵያ የሚያስቡትንና ኢትዮጵያን ነፃ በማድረግ ኃይማኖት እና ፖለቲካ ተከባብረው በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲኖሩ ደማቸውን ከሚያፈሱት ጋር ኣጋር በመሆን ጊዜያቸውንና ገንዘባችውን ለትግሉ መሳካት የሚሰጡትን፣ ስለ ወገናቸው ግድ የሚላቸው፣ ስለ ኃይማኖታችውም ስለ ሃገራቸው ፖለቲካም ቢናገሩ ዕውነተኞችና ታሪክ ሠሪዎችን፣ ህዋሓት እስካለች ሃገሬን ባላይስ መጀመሪያ ነፃነቴን ያሉትን። በኣንፃሩ ደግሞ እናንተ ዛሬ ገንዘብ ኣግኝታችሁ ቤት በሃገር ቤት ስትሠሩና ንብረት ስትመሠርቱ ወደ ሃገር ቤት የምትልኩት የውጪ ምንዛሪ የህዋሓትን የጭቆና ሥርዓት እንደሚረዳ እያወቃችሁ ስለራሳችሁ ብቻ ትጨነቃላችሁ። ገንዘባችሁ ባለበት ምናችሁ ኣብሮ ይኖራል ኣለ? ህዋሓት እንዲህ እያረገች ነው የምትቆጣጠራችሁ።
ከሃገራችን ተከትሏችሁ የመጣው የፖለቲካ ችግር ደግሞ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናችሁን በሦስት ቦታ ከፍሏታል። ኣሁን ባላችሁበት ሃገር የኣቡነ ማቲያስ ሥም የሚጠራባቸውን ቤተ ክርስቲያኖችን ብትመለክቱ፥ ወይ በበላይነት ወይም በኃላፊነት ላይ ያሉት ካህናቶችና ግለሰቦች የህዋሓት ደጋፊዎች ናችው። በመሆናቸውም፥ ምዕመኑን በተቻላቸው መጠን ኢትዮጵያን ከህዋሓት እንዳያላቅቅና ወደ ተቃዋሚ የትግሉ ጎራ እንዳይሄድ ኣድርገውታል። ኣይ ሃገራችን መልካም ኣስተዳደር ኣላት ትግሉ ኣያስፈልግም የምትሉ ካላችሁ ግን ለምን በሃገራችሁ እንደማትኖሩ ይገርመኛል፥ ሌላ ተልዕኮ ከሌላችሁ በስተቀር።
በምን ሰሌት እያሰላችሁ ነው ህዋሓት ከምትመራው ሲኖዶስ ጋር ተሰልፋችሁ ቤተ ከርሰቲያኒቷን እያጠፋችኋት ያላችሁት። ባለፈው ሣምንት ውስጥ ከእንጦጦ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዕድሜ ጠገብ ወርቆች ወዘተ ለኣባይ ግድብ መዋጮ ተወሰዱ የሚል ዜና ሰማሁ ግን ኣቡነ ማቲያስ ከጽህፈት ቤታቸው ስለዚህ ጉዳይ ያወጡት መግለጫ የለም። እናንተ የእርሳቸውን ሥም በማንሳት የምትተባበሩትስ ምን ኣላችሁ? ምንም። ቤተ ክርስቲያኗስ ኣትጠፋም፥ ኣንዴ በክርስቶስ ደም ላይ ተመሥርታለችና፥ ውዮ ግን ለእናንተ የኣምልኮ መልክን ብቻ ለያዛችሁ፥ ለወገናችሁ ስቃይ ሳይሆን ስለራሳችሁ ብቻ ለምትጨነቁ።
በውጭ ሃገር ሲኖዶስ መቋቋሙን ባንደግፈውም የኣቡነ መርቆርዮስን ፓትርያርክነት የሚክዱት ህዋሓት የሰለበቻችው የዋሆች ካልሆኑ በስተቀር ኣሁንም ቢሆን ሕጋዊው ፓትርያርክ እንደሆኑ ሌሎቻችን እንረዳዋለን። ይህንንም የውጪውን “ሲኖዶስ” ደግሞ ጠጋ ብሎ ላየው ሰው፥ የጎንደር ሃገር ስብክት እንጂ የኢትዮጵያ ሲኖዶስ ለመባል የሚችል ስብስብ ኣይደለም፤ እንዲሁም ለወደፊቱ ፓትርያርክ ለመተካት እንኳን ሥልጣን የለውም። እዛ ጊዜ ላይ ቢደረስ፥ የገለልተኛው ቁጥር ከሌሎቹ እንደሚበልጥ እገምታልሁ።
ለዚህ ሁሉ ችግር መንስኤ የሆነችውን ህዋሓትን በማስወገድ ነፃነታችሁን ማወጅ ኣማራጭ የሌለው መንገድ ነው። ኣቋማችሁን ኣስተካክላችሁ ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ ስብሰባ ስትጠሩ በስበሰባው ላይ ተገኙና ስለ ኃይማኖታችሁና ስለ ሃገራችሁ ያገባናል በሉ። በፀሎትና በሃሳብ እንዲሁም በገንዘባችሁ ወገኖቻችሁን ታደጉ። ካህናቶቻችሁ በሃገር ቤት የሚደረገውን ግፍ ኃይማኖትን በጠበቀ መልኩ እንዲያወግዙ ግዴታ ኣለባቸውና ይህንን እንዲያደርጉ ጫና መፍጠር ኣለባችሁ። ካህናቶቹ ይህንን ባያደርጉ ግን፥ ስለ ኢትዮጵያ ህዝብ ግድ ከሚላቸው ካህናቶች ከሚያገለግሉበት በመሄድ የሕብረት ጸሎት በማድረግና በተግባር ደግሞ ሰለ ኢትዮጵያ ነፃነት ከሚታገሉት ጎን በመቆም ዕውነተኛ ፍቅርን በማሳይት ትዕዛዝ ማክብራችሁን ኣረጋግጡ።
ተፃፈ ከኣባ ሚካኤል።
The post ወንድሙን የሚጠላ ነፍሰ ገዳይ ነው! – ከኣባ ሚካኤል appeared first on Zehabesha Amharic.