የተከበራችሁ አባቶች ፥ እናቶች፥ ወንድሞች፥ እህቶችና ልጆች ! ዛሬ በዚህ የተሰባሰብነው ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን የዛሬ 119 ዓመት እንደዛሬው በነገድ ወይምብ ብሔር እንዲሁም በሃይማኖት ሳይከፋፈሉ ፥ ለአንድ ብቸኛ ዓላማ በአንድነት ተሰልፈው ባህላቸውን ፤ ሃይማኖታቸውን፤ ታሪካቸውን፤ ሰብአዊና ብሔራዊ ነፃነታቸውን፤ ባጠቃላይ ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን አጥፍቶ የቅኝ ተገዥ ባርያ አድርጎ ለመግዛት ከአህጉረ አውሮፓ ተንቀሳቅሶ፥ ባህረ ኢያሪኮንና ቀይ ባሕርን ተሻግሮ፥ የእናት አገራችንን ክብረ ወሰን ጥሶ የገባውን የጣልያን ወራሪ የጠላት ጦር አይቀጡ ቅጣት ቀጥተው ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ጥቁር ሕዝቦች በአውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች ላይ ድል ተቀዳጅተው በዓለም ታሪክ ውስጥ ታላቅ ምዕራፍ ያስመዘገቡትን ታሪካዊ ዕለት እኛ የልጅ ልጆቻቸው በኩራት ለማስታወስ ነው ። ይህ ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ደማቸውን ቀለም አጥንታቸውን ብዕር አድርገው ያስመዘገቡት ታላቁ የታሪክ መዝገብ የተመዘገበበት ዕለት፥ እሑድ ዕለተ ሰንበት ፥ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ነበር።
ለመሆኑ የጦርነቱ መንስኤ ምን ነበር ?
አውሮፓንን ያጥለቀለቀው የ19ኛው ምእት ዓመት ዘመናዊ የእንዱስትሪ ለወጥ ወይም እንዳስትርያል ሪቮሉሺን ለእንዳስትሪያቸው ጥሬ ዕቃ፥ ማለት እንደማዕድን የመሳሰሉትን ሀብተ ከርሠ ምድሮች እንዲፈልጉ አውሮፓውያኑን አስገደዳቸው። ስለዚህ ዘመናዊ እንዳስትሪ ባስገኘላቸው ዘመናዊ የጦር መሳርያ አውሮፓዊ ያልሆነ ዘር የማይኖርባቸውን የአፍሪካንና የ እስያን ፤ ቀደም ብለውም የሰሜንና የደቡብ አሜሪካን ነባር ሕዝቦች እየጨፈጨፉ በቁጥጥራቸው ስር አደረጉ።የፈለጉትን ጥሬ እቃም በነፃ ማጋዝ ፤ ያመረቱትን ሸቀጥም በቅኝ በሚገዟቸው አገር ሕዝቦች ላይ በማጋረፍ ካፒታሊዝምን ገነቡ። በቅኝ የሚገዟቸውን ሕዝቦች ነባር ኃይማኖታቸውን፣ ቋንቋዋቸውንና ታሪካቸውን ለወጡት። የስነ መንግሥት፥ የምጣኔ ሀብት፥ የማኅበራዊ ኑሮ ነፃነታቸውንና ሰብአዊ ክብራቸውን ገፈፉት። ስነ ልቦናቸውን በመቀየር በራሳቸው እንደሰው የመተማመን ባህርያቸውን እንዲያጡ በማድረግ የበታችነት ስሜት እንዲያድርባቸው አደረጉ። ባጠቃልይ በቃላት ለመግለጽ የሚያስቸግር ኢሰብአዊ ድርጊት የሚፈጽሙበት ዘመን ነበር። ይህን በመሰለው የዓለም ተጨባጭ ሁኔታ ፥ አውሮፓዊ ያልሆነ ሕዝብ ፥ በተለይም ጥቁር አፍሪካዊ ሕዝብ ሁኖ ለአውሮፓውያን ነጮች አልገዛም ፣ ክብረወሰኔንና ሰብአዊ ክብሬን አላስደፍርም ብሎ ለውጊያ መሰለፍ የማይሞከር እርምጃ ነበር። ዘመኑ ነጮች ነጭ ያልሆነውን ሕዝብ ነፃነት መግፈፍ ከላይ ከአዶናይ (ከአምላክ) የተሠጣቸው ሥልጣን አድርገው ይቆጥሩት ነበር።ለዚህ አላማቸውም ‘የሞራል የበላይነት አለን ‘ ይሉ የነበሩት ምስዮኖቻቸው በክርስትና ስም “የቄሣርን ለቄሣር ፥ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር አድርግ ” የተባለውን መለኮታዊ ትእዛዝ ጥሰው የቄሣራውያን መሳርያ ሁነው ከክርስትና እምነት ጋር የተቃረነ የግፍ ተልእኮ ይፈጽሙና ያስፈጽሙ ነበር። በክርስትና ስም የተፈጸመውን ባርባራ ኪንግሶልበር የተባሉ አሜሪካዊት “ ዘ ፖይዝን ውድ ባይብል” በተባለው ታሪካዊ ልብ ወለድ መጽሐፋቸው በሰፊው ገልጸውታል። ፖፕ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛም ይህን በሚመለከት የዛሬ 18 ዓመት አካባቢ በዘመኑ በክርስትና ስም ግፍ ለተፈጸመባቸው ሕዝቦች ይቅርታ ጠይቀውበታል።
አውሮፓውያን በዚህ መልክ በተለይም በአፍሪካ ሕዝቦች ላይ ይህን ግፍ ሲፈጽሙበት በነበረበት ዘመን አገራችን ኢትዮጵያ ለዚህ አይነት የነጮች ግፍ ሰለባ ባትሆንም በራሷ ልጆች በመሳፍንት አገዛዝ ተከፋፍላና በእርስ በርስ ጦርነት ተዳክማ ነበር። በዚህም ምክንያት ማዕከላዊ መንግሥቷ መኖሩና አለመኖሩ ለውጭ ኃይሎች አጠራታሪ ነበር። በዚህ ሁኔታ እንግሊዞች በ1797 ዓ.ም. ምጽዋ ላይ ሰፈሩ። ነገር ግን አካባቢው ያኔ በራስ ሚካኤል ስዑልና ማዕከላዊ መንግሥቱን ወክለው በነበሩት በጎንደር ነገሥታት ቁጥጥር ሥር እንደነብር በሚገባ የሚያረጋግጡ የታሪክ መረጃዎች ኣሉን። ይህ በዚህ እንዳለ ፥ በ1846 ዓ.ም ጀምረው ቆላማውን የባህረ ነጋሺ አካባቢ ግብጾች ሰፍረውበት ነበር። ከዚያም አንድ የግል ንብረት የነበረ የኢጣልያ የባህር ጭነት ማጓጓዥያ ኩባንያ አሰብን ከአካባቢው መስፍን (ሡልጣን) በ1874 ዓ.ም ገዛው። በመቀጠልም ከ3 ዓመት በኋላ በእንግሊዞች አበረታችነት በ1877 ዓ.ም የኢጣልያ ሠራዊት ምጽዋ ላይ ሠፈረ። በዚህም ወቅት ግብጽም በበኩሏ በዚህ አካባቢና በሃረር በኩል ክብረ ወሰናችን ደፍራብን ነበር።
ይህን በመሰለ ሁኔታ አገራችን ኢትዮጵያ ከአድዋ ጦርነት በፊት ለ20 ዓመታት ያለ እረፍት ከውጭ ጠላቶች ጋር ክብረ ወሰኗንና ብሔራዊ ነፃነቷን ለመጠበቅ ስትታገል መቆየቷ ይታወሳል። ለዚህ ታላቅ ብሔራዊ ነፃነትና ማንነት ጥበቃ ጀግኖች መሪዎቿም መስዋዕት ሁነዋል። ከተሰውት መሪዎች መካከል ሁለቱን እንጥቀስ። ዘመነ መሳፍንትን አጥፍተው ዘመናዊትና አሐዳዊት ኢትዮጵያን የመሠረቱት ጀግናው አፄ ቴዎድሮስ በጀኔራል ናፔር የተመራውን የእንግሊዝ ጦር በለስ ቀንቷቸው ድል ባያደርጉትም መቅደላ ላይ በ1860 ዓ.እ ‘’እምተቀንዮ በነገደ ያፊት ፥ ይሄሰኒ መዊት” ብለው ራሳቸውን ሰውተዋል። አዎ ‘የአቢሲንያው አምበሳ በአሮፓ ድመት ተዋርጀ እጅ ሰጥቸ ከምገዛስ የማይቀረውን ሞት ብመርጥ ይሻለኛል’ ብለው ፥ በፈረንጆች አቆጣጠር April 13, 1868 (በእኛ በ1860 ዓ.ም)፣ ሊረዳቸው የሚገባው የወገን ኃይልም ለጠላት አሳልፎ ስለሠጣቸው፣ የራሳቸውን ሺጉጥ ጥይት ጠጥተው፥ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ከ13 ዓመት የውስጥ ውጣ ውረድ በኋላ ይህን በሚመስል አሳዛኝ ሁኔታ ተሰውተዋል።
ከአፄ ቴዎድሮስ አሳዛኝ እረፍት በኋል ለሁለት ዓመት ያህል ንጉሥ ተክለ ጊዮርጊስ በሚል የዘውድ ስም የነገሡት ዋግሹም ጎበዜን ድል አድርገው የነገሡት አፄ ዮሐንስ 4ኛ እና የጦር መሪያቸው የነብሩት ጀግናው ራስ አሉላ አባ ነጋ የመሩት የኢትዮጵያ ጦር ፥ በ1867 ዓ.እ ጉንደት ላይ እና በ1868 ዓ.እ ጉራ ላይ የግብጽን ጦር ፣ በ1879 ዓ.እ ዶጋሌ ላይ የኢጣልያንን ጦር ተዋግቶ ድል ተቃዳጅቶ ነበር። ከዚያም በመቀጠል አፄ ዮሐንስ ጎንደርን ወሮ የነበረውን የድርቡሽ/ሱዳን ጦር ለመዋጋት የሰሜኑን ግንባር ትተው ወደ ጎንደር ተመለሱ። ጎንደርን ነፃ ካወጡ በኋላ መተማ ከሀገራቸው ድንበር ላይ መጋቢት 1 ቀን 1881 ዓ.ም ፥ በፈረንጆች March 10, 1889 ለሀገራቸው ተሰውተዋል።
ስለዚህ እነዚህ ያለምንም ፋታ ከውጭ ወራሪ ኃይል ጋር ለ20 ዓመታት የተደረጉ ጦርነቶች ይህን ዛሬ የምናስበውን የአድዋን ድል በአፄ ምንይልክ ለተመራው ኅብረ-ብሔራዊ ጦር ትልቅ ልምድና ወታደራዊ ተመክሮ ሠጥተውት ነበር። በአንፃሩ ደግሞ ለ20 ዓመታት የተደረገው የማጥቃትና የመከላከል ጦርነት ብዙ ብሔራዊ የሀብት ምንጭ አስጨርሶ ነበር። የዘመነ መሳፍንት ስሜትም በአንድ አንድ አካባቢ ጨርሶ አልጠፋም ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ከፍተኛ ድርቅ ሀገሪቷን ጎድቷት ስለነበር ከአድዋ ድል በኋላ ጣልያንን ከኤርትራም ጭምር ጨርሶ ለማስወጣት የነበረውን ወታደራዊ እቅድ እንዲደናቀፍ አድርጎታል። ስለዚህ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ችግሮች ተባብረው የኢትዮጵያን ሕዝብ አጎሳቁለውት ስለነበር ነበራዊ ሁኔታው ለኢጣልያ ወራሪ ጦር ምቹ ሁኒታን የፈጠረ መስሎ ይታይ ነበር። ሆኖም ግን ይህን የተፈጥሮና ሰው ሠራሺ ችግር አፄ ምንይልክ በጣም አዋቂና አስተዋይ መሪ ስለነበሩ ሁሉንም በብልሀትና በትግስት ይዘውት ነበር። ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ብጡል ኃይለ ማርያምም ‘’መልካም ሚስት ለባልዋ ዘውድ ናት” እንደተባሉት ፥ እውነትም ዘውዳቸው ስለነበሩ የሚሠጧቸውን ምክር ሁሉ ንጉሠ ነገሥቱ በጥሞና ያዳምጡ ነበር። እቴጌ ጣይቱ በሀገራችን ሥርዓተ ትምህት መሠረት ከውዳሴ ማርያም ጥሬ ንባብም አልፈው ዜማውን ፤ እንዲሁም ጾመ ድጓና ቁም ጽፈት ጭምር ደበረ ታቦር ኢየሱስ እየተማሩ ያደጉ ሴት ነበሩ። ከዚህም ሌላ የስሜኑ መስፍን የደጃዝማች ዉቤ ኃይለ ማርያም ወንድም የደጃዝማች ብጡል ኃይለ ማርያም ልጅ ስለነበሩ የቤገምድርንና ስሜንን ፥ ከዚያም አልፈው ጠቅላላ የሰሜን ኢትዮጵያን ሕዝብ ስነልቦና በሚገባ ጠንቅቀው ያውቁ ስለነበር አፄ ምንይልክ “እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዮጵያ “ የሚል ማኅተመ ስም ሠጥተዋቸው ነበር። እቴጌ ጣይቱ ጎንደሬ ብቻም ሳይሆኑ ከወሎ ኦረሞወችና ሺሬ ከትግራይዮችም ተወላጅ ስለነብሩ ፥ ያኔ የጣልያን ጠቅላይ ምንስቴር የነበረው ፍራንሲስኮና መረብ ምላሺን “ኤርትራ” በሚል ስም በጣልያን ፓርላማ አሰይሞ ፥ ከአፄ ዮሐንስ ዘመነ ዕረፍት ጀምሮ ሲገዛ የነበረው ጀኔራል ባርትየሪ ውስጥ ውስቱን የሰሜን ኢትዮጵያን መሳፍንቶች በምንይልክ ላይ እንዲያምፁ ሲያደርጉት የነበረውን ማባበል እቴጌቱ በነበራቸው የሥጋ ዝምድና ትስስር አክሽፈውታል። ማለት የሰሜን ኢትዮጵያ መሳፍንቶች የጠላትን የማባበልና የመከፋፈል ሴራ ሳይቀበሉት ቀርተዋል።
ጣልያን ኢትዮጵያን ጠቅልሎ የመግዛት ዓላማው የማይሳከለት መሆኑን ከተረዳ በኋላ የኤርትራ ግዛቱ ብቻ በኢትዮጵያ በኩል እውቅና እንዲያገኝለት ወሰነ። አፄ ምንይልክም ዙርያውን በአውሮፓ ቅኝ ገዥ ኃይሎች ተከበው ስለነብሩ ሁሉን ከማጣት ብለው፥ ከነበረው ተጨባጭ ሁኔታ ተነስተን ስናየው ሃሳቡን መቀበል ግድ እንደሆነባቸው መገመት አያዳግትም። ስለዚህ በሁኔታው አስገዳጅነት ሚያዝያ 25 ቀን 1881 ዓ.ም ኢጣልያ የኤርትራ ቅኝ ገዥ መሆኗን የሚያረጋግጥ 19 አንቀጽ ያለው ስምምነት ወሎ ውስጥ ልዩ ስሙ ውጫሌ ከተባለ ቀበሌ ላይ ተደረገ። በተለይ አንቀጽ 17 በጣልያንኛ የተጻፈው ከዐማርኛው ጋር የተቃረነና አሻሚ ትርጉም ይዞ ነበር ለአውሮፓ መንግሥታትና ሕዝቦች የተበተነው። ኢትዮጵያ የኢጣልያ ጥገኛ (protectorate)እንደሆነችና ከውጭ መንግሥታት ጋር የሚኖራት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት በኢጣልያ በኩል ካልሆነ እንደ ነፃ ሀገር በራሷ ብቻ ማድረግ እንደማትችል ተደርጎ ነው ለአውሮፓ መንግሥታት የተበተነው ።
ይህ ውል የተጭበረበረ እንደነበር በኢትዮጵያ በኩል ሊታወቅ የቻለውም አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ የተባሉ ኢትዮጵያዊ የቋንቋ ሊቅ በጣልያንኛ የተጻፈውን እንዲመረምሩት ተሠጥቷቸው ስለነብር ፣ አለቃ ይህን ነገር በሚገባ ለንጉሡ አደገኛነቱን አስረዷቸው። ይህን እንደተረዱ አፄ ምንይልክ ወደቤተ መንግሥታቸው እየተመላለሰ ፤ ‘’ጌታየና ግርማዊ’’ እያለ በለሰለሰ አንደበቱ በውዳሴ ከንቱ ሲደልላቸው የነበረውን ስኞር ኮንቲ አንቶሊኒ የተባለውን፥ ማለት ጣልያንን ወክሎ ውሉን የፈረመውን ዲፕሎማት አስጠርተው ፥ አንቀጽ 17 የተጭበረበረና ከዐማርኛው ቅጅ/ኮፒ በፍፁም የማይገናኝ መሆኑን እንደደረሱበት ነገሩት። እሱ ግን በተለመደው ለስላሳ አንደብቱ ‘’ይህን ያለወት ሰው በመንግሥትዎ ላይ ቅን አስተሳሰብ የሌለውና በጠላትነት ሊነሳብዎ ያሰበ ሰው መሆን አለበት አንጅ ነገሩ ምንም የተጭበረበረ ትርጉም የለውም” ብሎ ለጊዜው አሳመናቸው። ንጉሡም በአለቃ ላይ ተበሳጭተው አለቃን እንዲታሰሩ አደረጓቸው። ‘እውነትና ብርሃን እያደር ይጠራል ‘ ነውና ፥ ሳይውል ሳያድር ሙሴ ማሪ ዴሎሜኩል የተባለ ፈረንሳዊ ዲፕሎማት በጅቡቲ በኩል ወደ አንኮበር መጥቶ ልክ አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ የተናገሩትን ነገር ሳይጨምርና ሳይቀንስ በማስረዳት አገራቸው ኢትዮጵያ የጣልያን ጥገኛ አገር እንደሆነች የአንቀጽ 17ቱ ውል እንደሚያስረዳ በአውሮፓ መንግሥታት ዘንድ ግንዛቤ እንደተጨበጠ ነገራቸው። ንጉሡም አለቃን ይቅርታ ጠይቀው ፈቷቸው።
አፄ ምንይልክ ይህን ከተረዱ በኋላ ለአውሮፓ መንግሥታት ማስተባበያቸውን ላኩ። ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ማስተባበያ ያኔ ሦስተኛውን ዓለም በአብዛኛው በቅኝ ስትገዛ የነበረችው ታላቋ ብርታንያ አልቀበለውም አለች። አፄ ምንይልክም እናንተ ባትቀበሉት ‘ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔርና ልጆቿ ትዘረጋለች’ ብለው በአምላካቸውና በሕዝባቸው ተማምነው አሻፈረኝ አሉ። አንቀጽ 17ን ብቻም ሳይሆን ጠቅላላ የውጫሌን ውል ኢትዮጵያ ማፍረሷን ወይም መሰረዟን ንጉሠ ነገሥቱ ጥር 4 ቀን 1885 ዓ.ም. ለዓለም አሳወቁ። ፈረንሣይና ሩሲያ የኢትዮጵያን ተቃውሞ በመቀበል የኢጣልያንን የኢትዮጵያ የበላይ ጠባቂነት እንደማይቀበሉት ተስማሙ። በተለይ የሩሲያው ንጉሥ ወይም ዛር ኒኮላስ ወታደራዊ እርዳታ ለማድረግ ወሰኑ። የጦር መሣርያም በመላክ ውሳንያቸውን በድርጊት ፈጸሙ።
በዚህ ምክንያት ከሁለት ዓመት ውዝግብ በኋላ የጣልያን ወራሪ ጦር መረብን ተሻግሮ ደብረ ሃይላ ላይ አደጋ ጥሎ አካባቢውን እንዲጠብቁ ተሹመው የነበሩትን የትግራይ ባላባቶች፣ ፊታውራሪ ንጉሤን፥ ቀኛዝማች ኃይለ ማርያምን፥ ቀኛዝማች አንድአርጋቸውንና ባላምባራስ በየነን ወግቶ በመስከረም 29 ቀን 1888 ወረራ መጀመሩን አፄ ምንይልክ ሰሙ። ከዚህ በኋላ አፄ ምንይልክ ጥቅምት 2 ቀን 1888 ዓ.ም የሚከተለውን የጦርነት አዋጅ አውጀው ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜን ጦር ግምባር ከእቴጌ ጣይቱ ጋር ኅብረ ብሔር ሠራዊታቸውን መርተው ለመንቀሳቀስ ተዘጋጁ። የጦርነቱ አዋጅ በዛን ጊዜው ዐማርኛ ይህን ይመስል ነበር።
ቃለ አዋጅ !
“እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ፣ አገሬን ጠብቆ አኖረኝ። እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ። እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለኔ ሞት ኣላዝንም። ደግሞም እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም። እንግዲህም ያሳፍረኛል ብየ አልጠራጠርም።
አሁንም አገር የሚያጠፋ፥ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል። እኔም ያገሬን ከብት ማለቅ የሰውንም መድከም አይቸ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር።
አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም። ያገሬ ሰው ! ካሁን ቀደም የበደልኩህ አይመስለኝም። በድየህም ከሆነ ለሀገርህ ስትል ይቅር በለኝ። አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም። ስለዚህ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለሚስትህ፥ ለሃይማኖትህ፥ ለሀገርህና ለታሪክህ ስትል በጸሎትህ እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጠላኝ አለህ ፣ አልተውህም ! ማርያምን ! ለዚህ አማላጅ የለኝም ! “ የሚል ነበር የአዋጁ ቃል ።
አዋጁን አውጀው ወደ ሰሜን ጦር ግምባር ከመሄዳቸው በፊት የተቀረውንም የሀገሪቱን ክፍል ዙሪያውን አውሮፓውያን ከበውት ስለነበር ወሰን ጠባቂ ጦር መመደብ ነበረባቸው። በዚህ መሠረት የጅማው ሹም ጅማ አባ ጅፋር ፥ የሊቃው ሹም ደጃዝማች ገ/እግዚአብሔርና ደጃዝማች ጆቴ፥ የወላይታው ሹም ንጉሥ ጦና ካዎና ሌሎች፥ የምዕራቡንና ደቡቡን ድንበር እንዲጠብቁ። በምሥራቅና በሰሜን ምሥራቅ ደግሞ ከአፋር አርበኞች ጋር ተባብረው በአሰብ በኩል ጠላት እንዳይመጣ እንዲጠብቁ ራስ ወልደ ጊዮርጊስ፥ ደጃዝማች ተሰማ ናደውና የወሂን አዛዥ ወልደ ጻድቃን 15,000 ጦር ይዘው እንዲሰለፉ ሁኖ ነበር።የመናገሻ ከተማዋንና አካባቢውንም ራስ ዳርጌ ሣህለ ሥላሴ፥ ራስ ልዑል ሰገድና ደጃዝማች ኃይለ ማርያም 8000 ጦር ይዘው እንዲጠብቁ ተመድበው ነበር።
ይህን ካጠናቀቁ በኋላ የሰሜኑ ዘመቻ ቀጠለ። የመጀመሪያውን የጠላት ጦር አምባ ላጌ ላይ በፊታውራሪ ገበየሁና ፊታውራሪ ተክሌ የተመራው የግንባር አብሪ ጦር በሻለቃ ቶዘሊን ይመራ የነበረውን የጠላት ጦር ኅዳር 28 ቀን 1888 ዓ.ም ደምስሰው ጠላት ሲጠቀምባቸው የነበሩትን መድፎችና ሌላ መሳርያ ከነብዙ ጥይቱ ማርከው፥ የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ ከአምባይቱ ላይ ሰቅለው እያውለበለቡ ቆዩ። (የአምባላጌ ከፍታ 11,279 ፊት ነው።) ቀጥለውም ግፋ ወደፊት በማለት ታህሣስ 29 የክርስቶስ የሥጋዌ ልደት መታሰቢያ ቀን መቀሌ ደርሰው መሺጎ ከነበረው ከጠላት ጦር ጋር ፍልሚያ ጀመሩ። ነገር ግን ምሺጉን ሰብሮ መግባት ከወገን በኩል ከፍተኛ መስዋዕትነት የሚጠይቅ መሆኑ ስለተረጋገጠ ፥ እቴጌ ጣይቱ ሲመሯቸው ከነበሩት መካከል 300 አርበኞችን ጠላት ባልጠበቀው መንገድ ልከው ፥ ጠላት ሲጠቀምበት የነበረውን የውሀ ምንጭ ኣስደፈኑት። ከ15 ቀን ቆይታ በኋላ የጠላትን ጦር በተለመደው ኢትዮጵያዊ ሰብአዊ ርህራሄ ምሺጉን ለቆ እንዲሸሺ ምህረት አደረጉለት። የዚህ ታሪክ ምንጭ አንዱ ከሆኑት ከአቶ ዮሐንስ መሸሻ ጽሑፍ ላይ የመቀሌውን ድል አስመልክቶ የገጠሙት ግጥም እንዲህ ይላል።
መቀሌ እንዳ ኢየሱስ ጦር ያሰፈረው ፥
አንድ ሺህ አንድ መቶው እውሀ እንዲጠማው፥
ምንጩን አዘግታ ጣይቱ አቃጥላው፥
ማጆር ጋሊያኖ ጉሮሮው ደርቆበት እንባ ሲወርደው፥
መኮነን አማልዶት እምየ ምንይልክ በምህረት ላከው ።
የኢትዮጵያ ጦር በዚህ ሁኔታ ጠላትን ከመቀሌ ካስለቀቀ በኋላ በቀጥታ ጠላት ሠፍሮበት ወደነበረው ሕዳጋ ሐሙስና አዲግራት መሄዱን ትቶ በምዕራብ በኩል ወደ አድዋ ሄደ። ምክንያቱም ሕዳጋ ሐሙስና አዲግራት ላይ የጠላትን ምሺግ በቀላሉ መስበር እንደማይቻል የወገን ጦር መረጃ ነበረው። የጠላት ጦርም የወገን ጦር ወደ አዲግራትና ሕዳጋ ሐሙስ እንደማይመጣ ከተረዳ በኋላ ፥ ወደ ምዕራብ ተንቀሳቅሶ ከአድዋ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ከምትገኘው ሳውርያ ላይ ምሺግ ቆፍሮ 20,170 የታጠቀ ጦር ይዞ የኢትዮጵያ ጦር ጥቃቱን እንዲጀምር ይጠባበቅ ነበር። ነገር ግን ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ወታደራዊ እቅድ እንጅ በጠላት ፕላን መሄድን ስላልፈለጉ ጥቃቱ ከጠላት በኩል የሚጀመርበትን ዘዴ ማቀነባበር ጀመሩ። ማን እንደሚጀምር ሲጠባብቁ ግን በሁሉም በኩል ስንቅ እያለቀ ነው። የባሰው ግን በጣላት በኩል ነበር። በዚህም ምክንያት ጠላት ጥቃቱን እንዲጀምር ሁኒታዎቹ እያስገደዱት መጡና የአድዋው ትያትር /ትርኢት እንደሚከተለው ሆነ።
የካቲት 20 ቀን 1888 ወደማታ አካባቢ የግፈኛውን የጣልያ ወራሪ ጦር ሲመሩ የነበሩት 5ቱ ጀኔራሎች እንትጮ ተራራ ላይ ድንኳናቸው ወስጥ ተሰብስበው የጥፋት ተልዕኳቸውን ማሳካት የሚችል ወታደራዊ ፕላናቸውን መቀየስ ጀመሩ። የጀኔራሎቹም ስም የሚከተለው ነበር። የኤርትራ ገዥ የነበረው ጀኔራል አረስቲ ባራትየሪና አራቱ የብርጌድ ኣዝዦች ፥ ጀኔራል አልበርቶን፥ ጀኔራል አርሞንዲ፥ ጀኔራል ዳቦርሚዳ፥ እና ጀኔራል ኢለና ነበሩ። በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ጣልያናዊና ጥቁር እራስ አስካሪ በዚያ ዘመን ደረጃ እጅግ ዘመናዊ ሥልጠና በተሠጣቸው የበታች የጦር መኮንንኖች ስር ተሰልፎ ትእዛዝ ከበላይ አዛዦቹ በመጠባበቅ በተጠንቀቅ ላይ ነበር። ያን የመሰለ ሠራዊት በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ለውጊያ ሲሰለፍ በታሪክ የመጀመሪያው እንደነበር ብዙ የታሪክ ጠበብቶች ይስማማሉ።
20 ኪሎ ሜትር ራቅ ብሎ አድዋ ላይ ደግሞ ፣ ቀደም ብሎ ጣልያኖችን በድንበር ሲከላከላቸው የነበረው የራስ መንገሻ ዮሐንስ ጦር ብቻ ሳይሆን ባጠቃላይ ከላይ ተደጋግሞ እንደተገለጠው የመላው ኢትዮጵያ ኅብረ ብሔር ጦር በታላቁ ንጉሠ ነግሥት ምንይልክ ኃይለ መለኮትና በጀግናዋ እቴጌ ጣይቱ ብጡል ኃይለ ማርያም የበላይ አዛዥነት፣ በእግዚአብሔር የበላይ ጠባቂነትና በርሱም ፍፁም ታማኝነት፣ ሠራዊቱ ከዚህ እንደሚከተለው በሀገር ወዳድ አዛዦች ስር እየጣለ ለመውደቅ በቆራጥነት ተሰለፈ።
በሰሜን በኩል የትግራይ ጦር በራስ መንገሻ ዮሐንስ አዛዥነት፣ በስተደቡብ በሽሎዳ ተራራ በኩል ያኔ የማህል ሰፋሪ እየተባለ የሚታወቀውን ሠራዊት በመምራት ፊታውራሪ ገበየሁ፣ የሐረርን ጦር በመምራት የአፄ ኃይለ ሥላሴ አባት ራስ መኮነን ወ/ሚካኤል፣ የታች ወሎን ጦር በመምራት ንጉሥ ሚካኤል አሊ ፣ ዋግሹም ጓንጉል ፥ ደጃዝማች ኃይሉና (የራስ ካሣ አባት) ጃንጥራር አስፋው (የእቴጌ መነን አባት)የዋግን ፥ የላስታንና የአምባሰልን ጦር በመምራት በአድዋ ከተማ ደቡብ በኩል ፣ ራስ መንገሻ አትከም የኤፍራታን ፣ ራስ ወሌ ብጡል (የቴጌ ጣይቱ ወንድም) የቤገምድርንና ስሜንን ጦር በመምራት ፣ ደጃዝማች ባሻህና ሊቀ መኳስ አባተ የሽዋን ጦር በመምራት ፣ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የጎጃምን ጦር በመምራት ፣ ደጃዝማች ባልቻ አባ ነብሶ ጀግናውን የኦሮሞና የጉራጌን ፈረሰኛ ጦር በማሰለፍ ‘’ኢትዮጵያ ወይም ሞት !” እያሉ ለእናት አገራቸው ነፃነት እየጣሉ ለመውደቅ ተሰለፉ።
የግብጹ ተወላጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፥ ታቦተ ጽዮንን በማስያዝ ፣ የአኩስሙ ንቡረ ዕድና የደብረ ሊባኖሱ እጬጌ አፍሮ አይገባውን መስቀል ተሸክመው፣ከአኩስም ቆይታቸው አድዋ ላይ ለውጊያ ወደተሰለፈው ብሔራዊ ጦር ሲጓዙ በተመለከታቸው ጊዜ ሠራዊቱ “የሙሴ ጽላት/ የአማላክ እናት መጣችልን” በማለት የበለጠ መንፈሳዊ ሞራልና ኢትዮጵያዊ ወኔ ተሰማው። በአምላኩ ኃይል ግፈኛውን ወራሪ የጣልያን ሠራዊት እንደሚያቸንፍ ያለምንም ጥርጥር እምነቱን በማረጋገጥ ‘ግፋ ወደፊት ማለት ጀመረ። ሊቀ ጳጳሱም “ ልጆቸ ሆይ ! በዛሬዋ ዕለት ፥ የካቲት 23 ፥ 1888፥ እግዚአብሔር አምላክ ከእኛ ከደካማዎቹ ጎን ተሰልፎ በግፈኛ ወራሪዎች ላይ እውነተኛ ፍርዱን የምናይበት ቀን ይሆናል። የቅዱሳን አባቶቻችሁ ፥ የነቅዱስ ያሬድ፥ የነቅዱስ ላሊበላ፥ የነቅዱስ ተክለ ሃይማኖት፥ የነአባ ኤዎስጣቴዎስ ከፋሌ ባህር፥ የነአባ ፊልጶስ ዘደብረ ቢዘን፥ የነአባ ሳሙኤል ዘዋልድባ አምላክ ከእናንተ ከግፉአኑ ጋር ነው ! ሂዱ ወደፊት! ኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖታችሁን፥ መካነ ቅዱሳንና ሀገረ እግዚአብሔር የሆነችውን ቅድስት ኢትዮጵያንና ንጉሣችሁን ተከላከሉ ! ኃጢአታችሁ ይሰረይላችሁ።” በማለት ጸሎተ ንስሐ ለንጉሡና ለሠራዊቱ ሠጡ። ካህናቱም ከዚህ ድርጊት ጋር የሚዛመደውን፥ ንጉሠ እስራኤል ዳዊት ከ1,000 ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት የተነበየውን ትንቢት በዚህ ታሪካዊ አካባቢ የተወለደው ኢትዮጵያዊው ቅዱስ ያሬድ በ520 ዓ.ም አካባቢ በደረሰው የዜማ ስልት
- ወወሀብኮሙ ትእምርተ ለእለ ይፈርሁከ ፥ ከመ ያምስጡ እምገጸ ቀስት፥ ወይድኀኑ ፍቁራኒከ።
- ጸርሁ ጻዳቃን ወእግዚአብሔር ሰምዖሙ ፥ ወእምኩሉ ምንዳቤሆሙ ያድኅኖሙ፥ ቅሩብ እግዚአብሔር ለየዋሃነ ልብ ።
- ይገንዩ ቅድሜሁ ኢትዮጵያ ፥ ወጸላእቱሂ ሀመደ ይቀምሁ።
- አንተ ቀጥቀጥኮ አርስቲሁ ለከይሲ ፥ ወወሐብኮሙ ሲሳዮሙ ለሕዝበ ኢትዮጵያ።
- ኢትዮጵያ ታበጽህ እደዊሃ ሃበ እግዚአብሔር ፥ ነገሥተ ምድር ሰብህዎ ለአምላክነ ፥ ወዘምሩ ለስሙ እያሉ ይጸልዩ ነበር።
የእስልምና እምነት ተከታይ የነበሩ ኢትዮጵያውያንም ከክርስትና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ተሰልፈው እኩል መስዋእትነት ከፍለዋል። እንደ ካህናቱም ሁሉ መንፈሳውያን ሸኽወቹም ድዋ በመያዝ ወይም በመጸለይ አገራቸው ኢትዮጵያን ባህር አቋርጦ ከመጣው ግፈኛ ጠላት ከተቃጣባት ጥፋት እንዲታደጋት አምላካቸው አላህን በመማጸን ላይ ነበሩ። ክርስቲያኑም ሆነ ሞስሊሙ የክተት አዋጁ ከታወጀበት ከጥቅምት 2 ቀን 1888 ዓ.ም ጀምሮ ቀንና ሌሊት የጋራ አምላኩን ከመማጸን አላቋረጠም ነበር።
የጦርነቱ ዝግጅት ሰው ሰራሺ በሆነው ዘዴም ፥ ማለት በመረጃ አሰባሰብም በኩል የተጫወተው ወሳኝ ሚና ነበረው። ታሪኩ እንደዚህ ነበር። አውአሎም ሐረጎት የተባለ የአካባቢው ተወላጅ ወጣት ለኢጣልያ መንግሥት በመረጃ አቅራቢነት እንዲያገለግል ተቀጥሮ ይሠራ ነበር። ታድያ አውአሎም ምንም ቢሆን አፉ እንጅ ልቡ ወደወገኖቹ ያደላ ነበርና ፣ ጠላት በእናት አገሩና በወገኖቹ ላይ ሊፈጽመው ለተዘጋጀው ጥፋት ተባባሪ መሆንን አልመረጠም። ይህም ኢትዮጵያዊ ንቃተ ህሊናው ከጠላት የተማረውን የመረጃ አሰባሰብ ዘዴ አገሩንና ወገኑን እንዲጠቅምበት አስገደደው። ይህን የተቀደሰ ዓላማ ለጓደኛው ለብላታ ገ/እግዚአብሔር ያለምንም ፍርሀት ገለጸለት። ሁለቱ ጓደኞች ይህን ሲያሰላስሉ በነበረበት ወቅት ውዝግቡ በሰላም እንዲፈታ ድርድር ቀጥሎ ነበር። የነዚህ ሁለት ኢትዮጵያውያን አለቃ የነበረው ጣልያናዊው የመረጃ መኮንን ስለድርድሩ “ ኃያሉ የጣልያን መንግሥት ሠራዊት ይህን የኢትዮጵያን የዝንብ መንጋ ባንድ ቀን አራግፎ ግዛቷን መቆጣጠር ያቅተዋል ተብሎ ነው ድርድር እየተባለ ጊዜያችን የምናጠፋው ?” እያለ ሲደነፋ ለሀገራቸው ሕዝብ ያለውን ንቀት ሲገልጽ፥ አውአሎም እየሰማ ውስጡ ይቃጠላል። ከዚያ ብላታ ገ/እግዚአብሔር አውአሎምን ከራስ መንገሻ ዮሐንስ ጋር የሚተዋወቅበትን መንገድ ይፈልግና ከራስ ጋር አገናኘው። ራስ መንገሻም የአውአሎምን ታማኝነት ካረጋገጡ በኋላ የሚከተለውን ዘዴ ይቀይሳሉ።
ዘዴውም ይህ ነበር። የካቲት 21 ቀን ማርያም ስለሆነች አብዛኛው መሳፍንት ከሚመራው ጦር ጋር ቤተ ክርስቲያን ለመሳለምና ለመጸለይ ወደ አኩስም ጽዮን እንደሚሄድ፣ የንግሥቲቱ ወንድም ራስ ወሌም ስለሞቱ ንጉሡና ንግሥቲቱ በኀዘን ላይ እንደሆኑ፣ አንዳንድ መሳፍንቶችም የሚመሩትን ጦር ይዘው ጣልያንን ድል ማድረግ እንደማይቻል ተስፋ ቆርጠው እየከዱ ወደየመጡበት እየተመለሱ እንደሆነ ፣ የተቀረው ሠራዊትም ስንቅ ጨርሶ ምግብ ፍለጋ ተከዜን ተሻግሮ ጠለምትና ወልቃይት ድረስ እንደሄደና ንጉሡና ንግሥቲቱ ከጥቂት የክብር ዘበኞቻቸው ጋር ድንኳናቸው ውስጥ ስለሚገኙ፥ ስንቅ ፍለጋ ወደ ጠለምትና ወልቃይት የሄደውና፥ ወደ ኣኩስም ጽዮን የሄደው ሠራዊት ከመመለሱ በፊት እሑድ የካቲት 23 ቀን አደጋ ቢጣል በቀላሉ ድል አድርጎ ንጉሡንና ንግሥቲቱን መማረክ እንድሚቻል አድርጎ፥ አዘናጊና የተሳሳተ መረጃ አውአሎም ለጀኔራል ባራትየሪ እንዲሠጠው ይሆናል። እቴጌ ጣይቱ እጅግ በጣም አርቆ አሳቢና ጥበበኛ ስለነበሩ ፥ የጠበቀ እምነት እግዚአብሔርም ስለነበራቸው፥ ከአውአሎም ጋር የተቀየሰውን ዘዴ በቃል ኪዳን ለማጠንከር አውአሎምን እንደልጃቸው እጁን ጨብጠው እየሳቡ ወደ ድንኳናቸው ይዘውት ገቡ። “ ይህን የማቀርብልህን ምግብ እንደ ክርስቶስ ሥጋ ወደሙ ቆጥረህ እናት አገርህንና ወገንህን ላትከዳ በመሃላ ቃል ገብተህ ይህን ያቀርበኩልህን ምግብ ተመገብልኝ “ አሉት። እርሱም “ አገሬንና ወገኔን ለጠላት አሳልፌ ብሠጥ ፥ ሰማይና ምድርን የፈጠር አምላክ ይፍረድብኝ” በማለት ይህን ጠንከር ያለ የተለመደውን አስተማማኝ ኢትዮጵያዊ ቃል ኪዳን ከገባ በኋላ ምግቡን ተመግቦ ፥ ኢትዮጵያ በድል አድራጊነት የተወጣችበትን ወሳኝ ብሔራዊ ግዳጁን ለመወጣት ወደጠላት ጦር ሠፈር ጉዞውን ቀጠለ።
ከጠላት ካምፕ እንደ ደረሰ ከላይ የተዘረዘረውን የተሳሳተ፥ ግን ለጠላት እጅግ አስደሳች የሚመስለውን መረጃ ለጀኔራል ባራትየሪ አቀረበ። ባራትየሪም በቀረበለት መረጃ ረክቶና ተደስቶ ከምሺጉ ወጥቶ ምንይልክን ለመማረክና አገሪቱንም በቅኝ ለመግዛት እየተዝናና መጣ። የተናቀው የኢትዮጵያ ጀግና ሠራዊት ግን ቀደም እንደተገለጸው በየምሺጉ ሁኖ ማህል እስከሚገባ ድረስ አድፍጦ ጠበቀው። ከዚያማ ያን ነጭ የሮማ ስንዴ በጋለ ጥቁር ምጣድ ይቆላው ጀመር !! (እልልልልል!!)። በዚሁ ዕለት ፥ እሑድ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. ወደ 11 ሰዓት አካባቢ እንደ አንድ አገር ሕዝብ በአንድ አመራር ሥር የተሰለፈው የኢትዮጵያ ጀግና ሕዝብ፥ በአምላኩ በእግዚአብሔር ረዳትነት ፥ በጀግና መሪዎቹ አርቆ አሳቢነትና አገር ወዳድነት ጠላቱን ደምስሶ ብሔራዊና ሰብአዊ ማንነቱን ጠብቆ አስጠበቀ። በዚህም ታሪካዊ ድል ከጠላት እብሪተኛ ጀኔራሎች መካከል ጀኔራል አርሞንዲና ጀኔራል ዳቦርሚዳ ሲገደሉ ፣ ጀኔራል ኢለና ወደኤርትራ እንደአጋጣሚ ከተወሰነ ጦር ጋር አመለጠ። 262 የኢጣልያን ተወላጅ መኮንኖችና 4,000 ተራ ወታደሮች ሲገደሉ ፥ 954 የደረሱበት ሳይታወቅ ቀርቷል (Missing in action)። 470 ነጭና 958 ጥቁር ራስ ባንዳዎች ቆስለዋል። ጀኔራል አልቨርቶን ጨምሮ 1,900 ነጭና ከ1,000 በላይ ወደውም ሆነ ተገደው ከጠላት ጋር ተሰልፈው ወገኖቻቸውን የወጉ የመረብ ምላሺ አበሾች ተማርከዋል። 56 መድፎችና 11,000 በዘመኑ የነበሩት ቀላልና ከባድ መሳሪያዎች ሊገመት ካልተቻለ ጥይት ጋር ተማርኳል። ክ100,000 በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሠራዊት ይዟቸው የተሰለፈው 40 መድፎችና 80,000 የሚሆኑ ቀላል የጦር መሣሪያዎች እንደነበሩ ሪቻርድ ፓንክረስትና ሌሎች የታሪክ ጸሓፊዎች ዘግበዋል። ከወገን በኩልም ለሀገራቸው ክብርና ነፃነት መስዋዕት የሆኑት ጥቂቶች አልነበሩም። ከ5,000 በላይ ተሰውተዋል። 8,000 ቆስለዋል። ከተሰውት ውስጥ የአፄ ምንይልክ የአከስት ልጅ፥ የወ/ሮ አያህሉሽ ሣኅለ ሥላሴ ልጅ ደጃዝማች ባሻህና ፊታውራሪ ገበየሁ ይገኙበታል።
ይህን በመሰለ ሁኔታ ለመጀመሪያ ጊዜ አውሮፓዊ የሆነ የነጭ ኃይል በጥቁር አፍሪካዊ ኃይል በመደምሰሱ ድሉ የኢትዮጵያውያን ብቻም ሳይሆን በዚያ ዘመን ተንቆና ተዋርዶ በቅኝ ግዛትና በባርነት ቀምበር ሥር ሲማቅቅ ለነበረው የመላው ጥቁር ዘር ሁሉ ነበር ተደርጎ የታየው። አዎ በአፍሪካ ፥ በካረብያንና በሰሜን አሜሪካ በዘረኛ ነጮች መንግሥትና ሕዝብ ሰብአዊነታቸው ተርሰቶ የነበሩት ጥቁሮች የደስታ ጭላንጭል የሰሙበት ዕለት ነበር። ከዚህም ዕለት ጀመሮ ነበር እነዚህ ህዝቦች ለነፃነታቸው ቆርጠው ለመታገል የበለጠ የተበራቱት። ወርሐ የካቲትንም ልዩ ትኩረት ሠጥተው ‘’Black History Month/ ታሪካዊ የጥቁሮች ወር “ እያሉ እስከዛሬ ድረስ በየዓመቱ እንዲያስቡት ካደረጋቸው አንደኛው ምክንያት ይህ የአድዋ ድል ነው።
እንግዲህ ከተለያዩ የታሪክ ምንጮች የቀዳዋቸው ፥ አባቶቻችንና እናቶቻችን የሠሩት እውነተኛው ትውልድ አኩሪ ታሪክ ከረጅሙ በአጭሩ ይህን ይመስላል። ጥያቄው ግን ዛሬስ ያች የታሪክና የብሔረሰቦች ቤተ መዘክር የሆነችው አገራችን ኢትዮጵያ የ 1888ቱ አይነት ጠንካራ የውጭ ወራሪ ክብረ ወሰኗን ጥሶ ቢገባ ለድል የሚያበቃት አስተዋይ መሪ አላት ወይ ? የጋራ ማንነቱ መገለጫ ከሆነው ከኢትዮጵያዊነቱ ይልቅ ለየግል ማንነቱ፥ ማለት ለዐምሐራነቱ፥ ለኦሮሞነቱ፥ ለትግሬነቱ፥ ለጉራጌነቱ፥ ለአፋርነቱ፥ ለወላይታነቱ፥ ለአገውነቱ ወዘተርፈ..ቅድሚያ እንዲሠጥ ተደርጎ እየተተካ ያለው አዲሱ ትውልድ ፣ ነገ ከነገ ወዲያ አንድነቱን ጠብቆ፥ የሚመጣበትን የውጭ ጥቃት ሊመክት ይችላል ማለት እንዴት ይቻላል? ይህ የአሁኑ ትውልድ ለብሔር ማንነቱ ነው እንጅ ቅድመ ሁኔታ መሥጠት እንደማይችል እየተነገረው ያለው ኢትዮጵያዊነቱን እኮ በሕገ መንግሥቱ ኣንቀጽ 39 ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው እስከፈለገው ድረስ ነው። ማለት የብሔር ማንነት ግዴታ ሲሆን ኢትዮጵያዊ ማንነት ግን በአማራጭ ደረጃ ነው ትውልዱ እንዲቀበለው ተደርጎ እየተተካ ያለው። ለዚህ እኮ ነው ብሔራዊ ማንነት ከብሔር ማንነት ይቅደም የሚል አጀንዳ ያላቸው በግልም ሆነ በድርጅት ደረጃ እንዲዳከሙ ሁነው በግል ማንነት ላይ ያተኮረ አጀንዳ ያላቸው እየተጠናከሩ የመጡት።
ታድያ የዛሬ 119 ዓመት ‘’ አባት ያበጀው ለልጅ ይበጀው ‘’ ብለው ከአራቱም ማዕዘናት በአንድ ኢትዮጵያዊ ማንነት፥ በአንድ ሠንደቅ ዓላማ አርማ፥ በአንድ መንግሥታዊ አመራር ሥር፥ አንድ አገር አንድ ሕዝብ ብለው ተሰልፈው ደማቸውን ቀለም አጥንታቸውን ብዕር አድርገው ያስመዘገቡትን አኩሪ ታሪክ ጠብቀን ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ አይጠበቅብንም? ለጥያቄው መልሱ አወንታዊ ነው መሆን ያለበት። አዎ እኛም ዛሬ ለነገው ትውልድ የሚያኮራና የነገው ትውልድ ዛሬ እኛ አባቶቻን የሠሩትን አኩሪ ታሪክ እያሰብነው እንዳለነው ሁሉ ነገም እኛን እንድንታወስ የሚያደርግ ጥሩ ታሪክ እየሠራን እንለፍ። ይህ ነው የሰውን ልጅ ከእንስሳት ልዩ የሚያደርገው። እናም እንሰባሰብ እንጅ አንበታተን። አንድነት ኃይል መሆኑን ይህ አድዋ ላይ ከ 119 ዓመት በፊት የተሠራው ታሪክ ዘለዓለማዊ የሆነ ታላቅና ቋሚ ምሥክር ነውና በእኩልነት ላይ የተገነባ አንድነት እንገንባ እያልኩ ዝግጅቴን ከዚህ ላይ አጠናቃለሁ። በጥሞና ስላዳመጣችሁኝ አመሰግናለሁ፤ እግዚአብሔር ይሥጥልኝ።
ከበደ አገኘሁ ቦጋለ፣ የካቲት 23 ቀን 2007 ።
መወድስ ቅኔ ዘአለቃ ዘወልዴ ዘአንኮበር ለአፄ ምንይልክ የተሠጠ።
ትውልድ የኀልፍ ወሰነ አበው ወትውልድ ይተርፍ እምነ አቡሁ በግብር ፤
ምሳሌ ዝኒ ላዕሌከ ሣህለ ማርያም (ምንይልክ)ደብር፤
ሐሰውከሂ ኢትበለኒ እሙነ ዜናሁ ለሰሎሞን በኩር፤
ጠይቅ ወተዘከር ፥ እመ ነባቢሁ ተቀብረ አምጣነ ንባቡ ኢይትቀበር፤
በይነ ጽድቅሂ ወበይነ ርትዕ ወበይነ የዋሃት መንክር ፤
እስከነ ትግሬ ይመርሐከ ስብሐተ የማንከ ፍዳ ጸር፤
አርቲዐከሂ ፍኖተ ማዕከለ ወሎ ሀገር ፤
ተሠራሕ ለኮንኖ ወንገሥ በጎንደር።
The post የ 119ኛው ዝክረ አድዋ ፤ 1888 – ከበደ አገኘሁ ቦጋለ appeared first on Zehabesha Amharic.