የኤርምያስ ለገሠን ‹ግልጽ ደብዳቤ› አነበብኩት፡፡ አንብቤው በሁለት ምክንያት ሳልጽፍለት ዘገየሁ፡፡ በአንድ በኩል ስለ ኤርምያስ ከነበረኝ የዋሕ ግምት የተነሣ ኤርምያስን ያህል ሰው ይህን ያህል አይሳሳትምና በቀጣዮቹ ቀናት በስሜ የወጣ ጽሑፍ ነው እንጂ የጻፍኩት እኔ አይደለሁም ይል ይሆናል ብዬ በመገመት፡፡ ጽሑፉ እንደወጣ ብዙ ሰዎች አሁን እኔ የምነግርህን ሲገልጡት ነበርና ትሰማቸዋለህ ብዬ አስቤ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሐዲስ ዓለማየሁ የባሕል ማዕከል ባዘጋጀው ዐውደ ጥናት ላይ ልካፈል ወደ ደብረ ማርቆስ ተጉዤ ስነበር፡፡
ከደብረ ማርቆስ ተመልሼ ገጸ ድሮቹን ሳሥሥ ግን ኤርምያስ ከነ ስህተቱ ጸንቶ አገኘሁት፡፡ ገሥግሦ የመጣን ደኅና አድርገህ ጫነው ነውና ለዚህ ሰው መንገር ያለብኝ ነገር አለ ብዬ አሰብኩ፡፡
ይህን ‹ግልጽ ደብዳቤ› ኤርምያስ አይጽፈውም ያልኩት እንዲህ ጊዜና ሁኔታን የማያገናዝብ ሰው ነው ብዬ ስላልገመትኩት ነው፡፡ አንድን ጽሑፍ ለመጻፍ ሲል ብቻ የሚጽፍ ሰው አድርጌ ስላልገመትኩትም ነው፡፡ ያንን መጽሐፉን በዕውቀትና በመረጃ ስለመሰለኝ ‹ቅዳሴው አልቆብህ ቀረርቶ ትሞላበታለህ› ብዬ ስላላመንኩ ነው፡፡
ኤርምያስ ሆይ፤
ይሄ አሁን አንተ አይተህ የደነገጥክለት ጽሑፍ አንተ ባዳመጥከው ጊዜ (በ2007 ዓም) የቀረበ ጥናት አይደለም፡፡ ምናልባት ‹ምንትስ የሰማ ለት ያብዳል› ሆኖብህ ካልሆነ በቀር፡፡ ጽሑፉ የቀረበው ነሐሴ 25 ቀን 1999 ዓም አሜሪካ፣ ዴንቨር ኮሎራዶ ከተማ ተደርጎ በነበረው ሰባተኛው የአሜሪካ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባኤ ነው፡፡ የተለቀቀው ደግሞ ከአንድ ወይም ከሁለት ቀን በኋላ www.tewahedo.org በተሰኘ ገጸ ድር ነው፡፡
በዚያ ጥናት ውስጥ ‹አክራሪነት› የተፈረጀው ከእምነት አንጻር ነው፡፡ አክራሪ እስላም ስልም ‹‹በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ሆን ብሎ የጥፋት ዓላማ በመያዝ፣ የሕዝቡን አብሮ ተገናዝቦ የመኖር ሥርዓት በማፍረስ፣ አንዳንዴም የሌሎችን ዓላማ በማንገብና የቤት ሥራ በመውሰድ የተሠማራውንና እስልምናን ሽፋን የሚያደርገውን የጥፋት ኃይል ነው›››፡፡ ክርስቲያኖች ሁሉ ቅዱሳን ናቸው እንደማልለው ሁሉ ሙስሊሞች ሁሉ አክራሪዎች ናቸው ብዬ አላውቅም፡፡ አልልምም፡፡ ምክያቱም፣ ስላልሆነ፡፡
እስከ 2002 ዓ.ም ያለው ወቅት ማለት ደግሞ አንተ ራስህ በመጽሐፍህ እንደነካካኸው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ሕልውና ለማየት በማይፈልጉ ‹አክራሪ ሙስሊሞች› ቦታዋን የመንጠቅ፣ ካህናቷን የማረድ፣ ገዳማቷን የማቃጠል፣ ቅዱሳት መጻሕፍቷን የመዝረፍና ወደ ባዕድ ሀገር የማሻገር እኩይ ተግባር ይከናወን የነበረበት፣ እንዲያውም ሁኔታው ራሱ ጫፍ የደረሰበት ጊዜ ነበር፡፡
አንተ ዛሬ ስትወጣ በሌሎች ብቻ አመካኘኸው እንጂ በአዲስ አበባ አየር ጤና ኪዳነ ምሕረት የጥምቀት ቦታ ክርክር ጊዜ የመንግሥትን ሥልጣን ይጠቀሙ ከነበሩት ሰዎች አንዱ ነበርክ፡፡ በወቅቱ እኔ የማኅበረ ቅዱሳን ሚዲያዎች ኃላፊ ነበርኩ፡፡ ጉዳዩን ከእግር እስከ ራሱ ዐውቀው፣ እከታተለውም ነበር፡፡ መረጃዎቹንም ከየአቅጣጫው እናገኝ ነበር፡፡ አጠናቅረንም በጋዜጣ እናወጣ ነበር፡፡ በዚያም ምክንያት አያሌ ጫናዎችን ካደረሱብን ሰዎች አንዱ አንተ ነበርክ፡፡ ቢሮህ አስጠርተህን ቤተ ክርስቲያኒቱንና የፈረደበትን አማራ ምን ብለህ እንደተሳደብክ የምናውቀው አንተ እና እኛ ነን፡፡
ከአሰቦት መነኮሳት የ1984 ዓም መታረድ በኋላ በሚዲያ ዋና ክፍል እኔና ጓደኞቼ ከሠራናቸው ሥራዎች መካከል አንዱ አክራሪ ሙስሊሞች በቤተ ክርስቲያኒቱ ከጥንት እስከ ዛሬ ያደረሱትን፣ ሊያደርሱትም ያሰቡትን መረጃ ማሰባሰብ ነው፡፡ አንዳንዶቹን በቦታው ተገኝተን፣ ሌሎቹን ከቦታው በሚመጡ መረጃዎች፣ የቀሩትንም ከተለያዩ የመረጃ ምጮች አሰባስበናቸው ነበር፡፡ ከሚመለከታቸው የውጭ ዩኒቨርሲቲዎችና የመረጃ ምንጮችም በውድ ዋጋ የገዛናቸው ነበሩ፡፡
በነገራችን ላይ ያ ጽሑፍ በፕሮጀክተር ታግዞ ቀርቦ ስለነበር የመረጃ ምንጮቹን የሚያሳየው የጎንዮሽ ማስተዋሻን ማንበብ አላስፈለገም፡፡ ለዚህ ነው ምንጩን የድምጹ መልእክት ላይ ያላገኘኸው፡፡ የድምጹን መልእክት የለቀቅኩትም እኔ አልነበርኩም፡፡ የኦርቶዶክስን ትምህርቶች በመረጃ መረብ በመልቀቅ የሚታወቀው www.tewahedo.org የተሰኘ ገጸ ድር ነው፡፡ ዛሬም በዚሁ ገጸ ድር ላይ ስላለ ማየት ትችላለህ፡፡ ወይም አዘጋጁን በገጸ ድሩ ላይ ባሠፈረው የመመየሊያ አድራሻው(email)ብትጠይቀው የሚነግርህ ይመስለኛል፡፡
አንተን ወደ ባሰው ስሕተት የወሰደህ የተሟላ መረጃ ሳታገኝና ለማግኘትም ሳትፈልግ ወደ ድምዳሜ መንደርደርህ ነው፡፡ የመጀመሪያው፣ እኔ ጥናቱን በ1999 ዓም ዴንቨር ኮሎራዶ፣ በ2000 ዓም አዲስ አበባ ደብረ ገሊላ ዐማኑኤል ቤተ ክርስቲያንና በዮርዳኖስ ሆቴል (ማኅበሩ ስለ ሚሊኒየም ባዘጋጀው ጉባኤ) ካቀረብኩት በኋላ ነው ‹ሽመልስ ከማል ሠራው› ያልከው ጥናት ለመንግሥት የቀረበው፡፡ ያ ጥናት ለመንግሥት አካላት ሳይለዋወጥ መቅረቡን በወፍ በረር እናውቅ ነበር፡፡ ስለዚህም የተከተለ ከቀደመ ይወስዳል እንጂ የቀደመ ከተከተለ አይወስድምና ‹ቃላት ሳይቀየሩ የቀረበው› እኔ ያቀረብኩት ጽሑፍ እንጂ በእናንተ ስብሰባ ላይ የቀረበው ጽሑፍ ወደ እኔ መጥቶ ሊሆን አይችልም፡፡ አንተ ራስህ በመጽሐፍህ ውስጥ አድንቀህ የጠቀስከው የአቡነ ሳሙኤል መጽሐፍኮ ይህንን ዋቤ አድርጎ የተጻፈ ነበር፡፡ እርሳቸውም ‹ከሽመልስ ከማል ወስደው› ነው ልትል ነው?
ሁለተኛው ስሕተትህ ቤተ ክርስቲያኒቱንና የቤተ ክርስቲያኒቱን ልጆች የምታይበት ዓይንህ ዛሬም አለመስተካከሉን የሚያሳየው ስሕተት ነው፡፡ ይህቺ ቤተ ክርስቲያን የሚቆረቆሩ ብቻ ሳይሆኑ መሥዋዕት ሆነውም ታሪክ የሚሠሩ ልጆች አሏት፡፡ እነዚያ ልጆች ናቸው አይገቡ ገብተው እነዚያን መረጃዎች የሰበሰቧቸው፡፡ አንዳንዶቹን መረጃዎች ለማግኘት እንደ ሠለስቱ ደቂቅ በእሳት ውስጥ ማለፍን ይጠይቅ ነበር፡፡ አንተና ሌሎቻችሁም የደነገጣችሁት ‹‹ሰው በቅንዐተ እምነት ተነሣስቶ እንዲህ አይሠራም፣ ሌላ ከጀርባው አንድ ነገር አለ›› ብላችሁ ስለምታምኑ ነው፡፡
በበሻሻ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ጅማ ውስጥ በጥቅምት 1998 ዓም አክራሪ ሙስሊሞች በየዋሐን ምእመናንና ካህናት ላይ የፈጸሙትን ግድያ ሕዝቡ ሲሰማኮ አንተና ሌሎቻችሁም ጣታችሁን እኛ ላይ ጠቁማችሁ ስንት ቀን እሥር ቤት አመላልሳችሁናል፡፡ አንተ ራስህ በመጽሐፍህ የገለጥከው ራስህ ቆመህ ያስፈረስከውን ቤተ ክርስቲያን በተመለከተ በድፍረት መጀመሪያ የዘገብነው በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ላይ ነበር፡፡ ያኔ ምን እንዳላችሁን ታውቃለህ፡፡
ሦስተኛው ስሕተትህ ‹የዶክተር ሺፈራው ጥናት ለምን በአንተ ጥናት ውስጥ አልቀረበም?› የሚለው ነው፡፡ ለምን ይቀርባል? እኔኮ የራሴን ጥናት ሠርቼ በራሴ መድረክ ላይ ነው ያቀረብኩት፡፡ 1999 ዓም ከ2001 ዓም በኋላ የሚመጣ ነው ካላልከኝ በስተቀር፤ በኋላ የተደረገ ጥናት እንዴት ተደርጎ ነው በፊት በተሠራ ጥናት ውስጥ የሚካተተው?
የዛሬ 8 ዓመት ጥናቱ ሲሠራ ያገኘናቸውንና ያመንባቸውን መረጃዎች ተጠቅመናል፡፡ ያ ማለት ግን ሁሉን ዐውቀን ነበር ማለት አይደለም፡፡ አንተ ጉዳዩን ሲያባብሱ ነበሩ ያልካቸው ባለ ሥልጣናት አክራሪነትን ሲመሩትና ሲያቀጣጥሉት ነበር ካልክ መረጃውን በበቂ ሁኔታ አንተ በቦታው የነበርከው ንገረን፡፡ ከዚያ ውጭ መከላከያ ሠራዊት ያደረገውን ጥረት ግን በአካል በመገኘት ጭምር ዐውቀዋለሁና ልዋሽ አልችልም፡፡ የተወሰኑ የመንግሥት አካላት የወሰዱትን በጎ ርምጃም ልዋሸው አልችልም፡፡ እውነት ነበርና፡፡
እጅግ ያስገረመኝ ደግሞ ‹በጥናታዊ ጽሑፍህ አሁን ያለውን የሙስሊሞች ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለምን አላነሣህም?› ብለህ የጠየቅከው ጥያቄ ነው፡፡ ለመሆኑ ይኼ እንቅስቃሴ ጥናቱ በቀረበበት በ1999 ዓም ተነሥቶ ነበር? ወይስ ለምን ወደፊት ይመጣል ብለህ ትንቢት ለምን አልተናገርክም ማለትህ ነው? ስሜ ነው እንጂ እኔኮ ነቢይ አይደለሁም፡፡ እንዲያ ከሆነ ደግሞ አንተም ስምህ የነቢይ ነውና በኋላ በኢሕአዴግ ውስጥ ደረሰ የምትለውን ችግር ቀድመህ ዐውቀህ ለምን ከአባልነት አልታቀብክም? የሚል ጥያቄውን ስትመልስ እመልስልሃለሁ፡፡
ስለ ‹ስደተኛው ሲኖዶስ› አቋሜን በተደጋጋሚ ገልጫለሁ፡፡ የፖለቲካውን ገጽታ አንተ ንገረን፡፡ በክርስትናው ግን መንጋውን ጥሎ የሚሄድን እረኛ ጻድቅ የሚያሰኝ ነገር ስላላገኘሁ ነው፡፡ ‹የቅዱስ ሲኖዶስ መንበሩ አዲስ አበባ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ነው› የሚለው የቅዱስ ሲኖዶስ ደንብ የወጣውኮ አሁን በስደት ያሉት አንጋፋዎቹ አባቶች አዲስ አበባ እያሉ በ1972 ዓም ነው፡፡ ያንን የማክበር ግዴታ የሁሉም ነው፡፡ ‹አባት አንጂ መንበር አይሰደድም› የሚለው ደግሞ ዛሬም ነገም አቋሜ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች እንኳን ተሰድደው ፓርቲ አቋቋሙ እንጂ መንግሥት አላቋቋሙም፡፡ በምን ቀኖናዊ መብት ነው ተሰድዶ መንበር ማቋቋም የሚቻለው? ከመንበሩ ውጭ ሆኖ ሀገረ ስብከቱን ያስተዳደረ አንድ ሲኖዶስ እስኪ በታሪክ ይጠቀስልኝ? እኔ አንተን ጥቀስ ብዬ አላስቸግርህም፡፡
‹መንግሥት በቅዱስ ሲኖዶስ ጫና ማድረጉና ጣልቃ መግባቱ› ተቀባይነት የሌለውና የምእመናንን ገድል የሚጠይቅ መሆኑ ባይካድም አሁን ያሉትን አበው ብቻ የሚመለከት ወቀሳ ግን አይደለም፡፡ ለቤተ ክርስቲያናችን አንዱ የዘመኑ ተግዳሮት ብሔራዊ ሲኖዶስ ከተቋቋመ ጀምሮ ከመንግሥት ተጽዕኖ ነጻ የሆነ ሲኖዶስ አለመኖሩ ነው፡፡ ያ ማለት ግን ለእምነታቸው የሚሞቱ፣ ለእውነት የሚሟገቱ አበው በቅዱስ ሲኖዶስ ውስጥ የሉም ማለት አይደለም፡፡ አንተ ራስህ ይህንን በመጽሐፍህ ስለጠቀስከው ለቀባሪ አላረዳም፡፡
እዚህ ላይ ግን በግልጽ ልነግርህ የምችለው የመንግሥት ባለ ሥልጣናት በተወሰኑ አባቶች ላይ ተጽዕኖ ሊያደርሱ ይችሉ ይሆናል እንጂ አንተ እንዳልከው ቅዱስ ሲኖዶሱን እስከ ማሽርከር የሚደርስ ዐቅም ፈጽሞ የላቸውም፡፡ቢኖራቸው ኖሮ አንተ ራስህ ተገኝተህ የታዘብከውን የአባቶች ጥንካሬ ማየት አትችልም ነበር፡፡ በ2006 ዓም በሰበካ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ የተገኙትን የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ተወካዮች በመረጃና ማስረጃ ሲወጥሩ፣ እምነታቸውን ሲመሰክሩና ያለ ፍርሃት ሲናገሩ እኔ ራሴ አባቶቼን በዓይኔ አይቻቸዋለሁ፡፡ ይህን ያደረጉት አሜሪካ ሆነው አይደለም፡፡ በቢላዋው ሥር ሆነው እንጂ፡፡
‹ለምን አሁን ቀረበ?› ብለህ የጠየቅከኝ በ2000 ዓም ቢሆን ኖሮ አብራራልህ ነበር፡፡ ጥናቱ የቀረበው በ1999 ዓም፣ አንተ ጥያቄውን ያነሣኸው ደግሞ በ2007 በመሆኑ ‹ይለፈኝ› እልሃለሁ እንደ ጋይንት ሰው፡፡
በመጨረሻ ኤርምያስ ሆይ
‹ብለነው ብለነው የተውነው ነገር
ባሏ ትናንት ሰምቶ ታንቆ ሊሞት ነበር›
የተባለው ደርሶብህ፤ ማጣሪያና ማብራሪያ ሳታገኝ ወርደህ በመጻፍህ፤ ገረመኝም አሳዘነኝም፡፡ የገረመኝ ‹አንተን የሚያህል› ብዬ የማስብህ ሰው ሁለቴ እንኳን ሳይለካ ለመቁረጥ በመቸኮሉ፤ ያሳዘነኝ ደግሞ ‹ኤርምያስ ሌላውንም ነገር የሚነግረን እንዲህ አመክንዮአዊ ሐሰት ይዞ ነው ማለት ነው› እንድል ስላደረገኝ ነው፡፡ አመክንዮአዊ ሐሰት ማለት በአቀራረቡ ተጠየቃዊ የሆነ፣ ነገር ግን በስሕተት መረጃዎች የተሞላ ማለት ነው፡፡
በመጨረሻ ዳዊት ለሳዖል የዘመረውን መዝሙር ልጋብዝህ
‹ኃያላን እንዴት ወደቁ›
The post ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ለአቶ ኤርሚያስ ለገሰ የሰጠው ምላሽ: ኤርምያስ ኤርምያስ ሆይ! appeared first on Zehabesha Amharic.