Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የዲያቆን ዳንኤል ስሜታዊ ትንተናና መሬት ላይ ያለው እዉነታ ! ክፍል 2 –ከአብዱላህ

$
0
0
daniel-kibret-300x207

ዲያቆን ዳንኤል

ዲያቆን ዳንኤል በዚህ በታሪክ ላይ ባተኮረው ንግግራቸው ያስተላለፉት መልእክት ኢትዮጵያዊያን ሙስልሞችን  የእስልምና ሃይማኖትን የተቀበሉ አገር በቀል ህዝቦች ሳይሆኑ ከውጭ በመምጣት ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ተብላ ትጠራ የነበረችን ሃገር ድንበር ደፍረው እንደ ሰፈሩ የባእድ ህዝቦች አድርገው ነው ።  በመሆኑም እነዝህ ህዝቦች ዘመሰረቷቸውን ሱልጣነቶችን ድንበር መውረርን ተቀምቶ የነበረን ድንበር እንደ ማስመለስ ካልሆነም አገር እንደ ማቅናት በማድረግ ሃሳባቸውን አስቀምጠዋል።   በሱልጣነቶቹ ስር ያሉትን ህዝቦች መጨፍጨፍን ጠላትን እንደ መግደል ፣ የሱልጣኔቶቹ ራሳቸዉን ለመከላከልም ሆነ እንደ ዘመኑ መንግስታት ግዛት ለማስፋት ከዉጭ ሃሎች እርዳታ መጠየቅን ከታሪካዊ ጠላት ጋር በማበር አገር የማድማት ሴራ የሚል ፍቺ ሰጥተዋል።  በሌላ በኩል ግን የዛረዉን የሰሜኑን የአገራችንን ክፍል ይገዙ የነበሩ የክርስትና እምነት ተከታይ ነገስታቶቻችን ለተመሳሳይ ዓላማ  ከዉጭ ሃሎች እርዳታ ሲጠይቁ ድርጊታቸውን አገርን ከታሪካዊ ጠላት ለማዳን የተወሰደ እርምጃ እያሉ ሲያወድሱ ህሊናቸውን አልኮሰኮሳቸዉም ።                         ያቆን ዳንኤል በንግግራቸው ትኩረት ያደረጉት የዛጉየን ስረዎ- መንግስት በ 1270 በሃይል ገርስሶ እራሱን ሰለሞናዊ ብሎ  በመሰየም መንግስት የሆነው ሃይል ላይ ነበር ።  ይህ እራሱን ሰለሞናዊ ብሎ የጠራው የመንግስት ሃይል በዛሬው  የሃገራችን ሰሜናዊ ክልል ብቻ ተወስኖ የነበረውን ግዛቱን የመስፋፋት ህልም የነበረው ነበር።   የዛጉይ ስረዎ- መንግስት ግዛቱን ዝርያው በሰፈረበት ስፍራ ላይ ብቻ ከልሎ ከዚያ ርቆ ለመውጣት ምንም ፍላጎት ያላሳየ  ግዛትን የማስፋፋት እቅድ ያልነበረው ሃይማኖቱንም በሌሎች ላይ የመጫን ፍላጎት ያላደረበት በመሆኑ ከድንበሩ አጎራባች ከነበሩ ሙስሊም ሱልጣኔቶች በጋራ ተከባብሮ በሰላም ይኖር የነበረ ስርዓት እንደነበር ታሪክ ያወሳል።  በወቅቱ የነበሩት ሱልጣኔቶች በዝያን ዘመን እስልምናን በተቀበሉ በዛሬው መካከለኛ  ፣ ምስራቅ እና ደቡብዊ የአገራችን ክፍሎች ይኖሩ የነበሩ ሃገር በቀል ህዝቦች የተመሰረቷቸው ነበሩ።  እነዚህ ሱልጣኔቶች የራሳቸው ስልጣኔ ፣ የአስተዳደር ስርአት ፣ ገንዘብ ወዘተ የነበራቸው እና በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል እንደ ነበሩት ነገስታቶቻትን ነጻ እና ራሳቸዉን የቻሉ ግዛቶች ነበሩ ።  ነገር ግን ዲያቆን ዳንኤል ሃገራችን ኢትዮጵያ ከዚያ ዘመን በፊት የሃገር ምስረታ  nation building ሂደት አጠናቃ የነበረች እና ልክ የዛሬውን ድንበር ይዞታ እና ቅርፅ የነበራት በማስመሰል  ሱልጣነኔቶቹን ከባእድ አገር በመጡ ወራሪ ህዝቦች የተመሰረቱ አድርገው ለማቅረብ ሞክረዋል ።

ከዚህ ጋር በተያያዘ መልኩ ከአረብ አገሮች  ወደ ሃገራችን ገብተው የነበሩ ጥቂት የእስልምና ሃይማኖት አባቶችን  እስልምናን ሳይሆን አረባዊነትን ለማስፋፋት ጥረት ያደርጉ እንደነበር ገልፀዋል።  ነገርግን  ከአራተኛው ክፍለ ዘመን እስከ 1950 ዎቹ  ድረስ ለ1500 ዓመታት ገደማ ከግብጽ በሚላኩ ጳጳሳት ትተዳደር የነበረችዋን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ይመሩ የነበሩ የግብጽ ክርስትያኖችን ግን ኢትዮጵያዊነትን እንዳስ ተማሩ አድርገው ተርከዋል።   ይህ አድሏዊ እና ሚዛናዊነት የጎደለው አቀራረባቸዉ በምያሳዝን መልኩ እውነታን ከማየት ይልቅ ስሜታቸዉን የተከተለ ጽሁፍ እንዲያቀርቡ አድርጔቸዋል ።

በተመሳሳይ የተዛባ እይታቸው የክርስትና እምነት ተከታይ የነበሩት በርካት የአገራችን ነገስታት ሙስልሞች ክርስትናን በግድ እንዲቀበሉ ለማድረግ ለረዥም ዘመናት የፈጸሙትን ጭፍጨፋ ሲያስተባብሉ በኢማም አህመድ የግዛት ዘመን የተደረገዉን የተለየ በደል አስመስለው አቅርበዋል።   እንደ ሌሎች ነጥቦቻቸው ሁሉ ይህ የዜጎችን እኩልነት ያለመቀበል ስሜት የፈጠረባቸው የአድሏዊነት መንፈስ መሆኑን በ 21 ኛ ክፍለ ዘመን መገንዘብ ያለመቻላቸውን አሳዛኝ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።

 

በአጭሩ የጥንቶቹን ሙስልሞች ታሪካዊ ጠላት ከሚሏቸው የሙስሊም ሃገሮች ማለትም ከቱርክ ፣ ከግብጽ ፣ ከሱዳን ፣ የመንና ሰኡዲ አረቢያ ጋር በተለያዩ የታሪክ ዘመናት አብረው አገር ያደሙ ፣ እስልምናን በግድ ሰዎች ላይ ይጭኑ የነበሩ እያሉ ሲያወግዙ በዘመኑ ያሉትን ደግሞ ታሪካዊ ጠላት ከሚሏቸው ጋር በማበር አገር ሊያጠፉ የተነሳሱ አክራሪዎች በማለት  በምሬት ከሰዋል ።  የዚህ ሁሉ የታሪክ ብረዛ አላማ  ህዝበ ሙስልሙን  በቀደምት አባቶቹ ታሪክ እና በዛሬው ንቃቱ ሊያሸማቅቁት የሚያስችሉ የስነ- ልቦና ጫናዎች በማድረግ በሃገሩ ከጀመረው የእኩል ባለቤትነት የመብት ጥየቃው እንዲታቀብ ለማድረግ መሆኑንን መገመት አያዳግትም።

የሚያስተዛዝበው ጉዳይ ፣ ዲያቆን ዳንኤል የጥንቶቹን ሙስልሞች ከጠላት ጋር አብረው አገር ያደሙ ፣ ወገኖቻችንን በሃይል ወደ እስልምና እንዲገቡ ያደረጉ የነበሩ  አስመስለው ሲወነጅሉ ከቆዩ በኌላ የዛሬዎቹን ሙስሊሞች  ደግሞ ለማሸማቀቅ እንዲመቻቸው የጥንቶቹን ሲያወግዙ መቆየታቸዉን የዘነጉ ይመስል የጥንቶቹ በጋራ መኗኗርን ገንብተው የነበሩ  ለአገር በጎ አሳቢዎች እንደ ነበሩ ለማስመሰል ጥረት ማድረጋቸው ቀደም ሲል ካቀረቡት የውንጀላ ሃሳቦቻቸው ጋር የተጣረዙ ሃሳቦችን አቅርበዋል።  እንደ ሃይማኖት አባት ሰዎች እውነትን እንዲመሰክሩ የሚያበረታቱ  መሆን ሲገባቸው እርሳቸው ግን በሃሰት የሌላ እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸውን ከክርስትና እምነት ተከታይ  ወገኖቻቸው ጋር የሚያጋጭን ጽሁፍ በማቅረብ  በሃገራችን ላይ ከፍተኛ የደም መፋሰስን ሊያስከትል የምችሉ የሃይማኖት ግጭቶችን መለኮስ የሚችሉ ቅስቀሳ ማድረጋቸው ያለባቸዉን የሃይማኖት አባት ሃላፊነት የዘነጉ መሆናቸዉን አጋልጧል።

በአክራሪ ሙስልሞች የተፈጸሙ ወንጀሎች ብለው ዲ/ን ዳንኤል  የዘረዘሯቸውን አስከፊ የጥፋት ድርጊቶች ስንሰማ በቅድሚያ የምናስበው በሃገራችን ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ የሆነ ወደ ከፍተኛ የደም መፋሰስ እያመራ ያለ ውጥረት በክርስትና እና በእስልምና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን መካከል እንደተፈጠረ ነው።  በአንድ ሃገር ይህን መሰል ወንጀል ሊፈጸም የሚችለው  ሃገርን የሚመራው መንግስት ይህን መሰል ወንጀል ለመቆጣጠር በቂ የጸጥታ አስከባሪ ሃይል የሌለው ከሆነ አልያም መንግስት ድብቅ አላማዉን ለማሳካት ሆን ብሎ በወኪሎቹ ሲያስፈጽም ብቻ ነው ።

የጸጥታ ሃይልን ጥንካሬ በተመለከተ በይፋ የሚታወቀው ጉዳይ መንግስት ያደራጀው የጸጥታ አስከባሪ ሃይል ከአገራችን ተርፎ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የተ/መ ድርጅት የሰላም አስከባሪነት አገልግሎት የሚሰጥ ፣ በሶማሊያ በውጊያ የተሰማራ እና በአፍሪካን ቀንድ በጠንካራነቱ የሚታወቅ ነዉ ።  ስለዚህ ሃገራችን እርሳቸው የዘረዘሯቸውን ወንጀሎች ሁሉ  ሊያስቆም የሚችል ብቃት ያለው የጸጥታ አስከባሪ ሃይል ያለው  መሆኑ የተረጋገጠ እስከሆነ ድረስ መሰል ብቃት ያለው መንግስት ባለበት ሃገር ውስጥ የወንጀሎቹን መፈጠር ያለማስቀረቱ ጉዳይ አንድም መንግስት የውንጀሎቹን ፈጻሚዎች እያዬ የሚያልፍ መሆኑን አልያም ደግሞ በጀሌዎቹ ማስፈጸሙን የሚያመላክቱ  ናቸው ።  ሌላው የዚህን እይታ አሳማኝነት የሚያጠናከረው ነጥብ ህወሃት በቀዳሚነት የኦርተዶክስ ቤ/ክርስቲያንን ለማዳከም በትጋት መስራቱን ያለመሸሸጉ እና  እቅዱንም ስለ ማሳካቱ በማን አለብኝነት ስሜት የቤ/ክርስቲያንቷን አከርካሪ መሰበሩን ማሳወቁ ነው (አቦይ ስብሃት የቀድሞ የህውሃት መሪ እንደተናገሩት “አማራን እና ኦርቶዶክስን አከርካሪያቸውን ሰብረናል” ማለታቸው ነው) ።  ታድያ ይህን ግልጽ የሆነ ጉዳይ ዲ/ን ዳንኤል  እንዴት ሳይጠረጥሩ ቀሩ ?  ለዚህ ያለኝ ምላሽ  በእርግጥ እርሳቸው መጠርጠር የለባቸዉም ነው። ምነው ቢባል እርሳቸው የህወሃትን አላማ በእርግጠኝነት ያውቃሉና።

የሙስልም አክራሪዎች በሚሏቸው እንደተፈጸሙ ከጠቀሷቸው ወንጀሎች አንዱ በጅማ ከተማ አቅራቢያ በክርስትና እምነት ተከታይ ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ወንጀል ነው።  ይህ ወንጀል እንደ ተፈጸመ የክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን የወንጀሉ ሰለባ የነበሩትን ክርስቲያን ወገኖቻችንን ቃለ-መጠይቅ አድርገው የቀረጹትን ቪዲዮ አዘጋጅተው  ለቀው ነበር ።  በቃለ ምልልሱ የተሳተፉት የወንጀሉ ሰለባ የነበሩት ክርስቲያን ወገኖቻችንን በዘመዶቻቸዉ እና  በእነርሱ ላይ የተፈጸመውን ግፍ በተመለከተ ወንጀሉን የፈጸሙትን ቡድኖች ቆመው ሲከላከሉላቸው የነበሩት የመንግስት ታጣቂዎች ናቸዉ የሚል ምስክርነት በወቅቱ ሰጥተዋል።    የቪዲዮው አዘጋጆች በወቅቱ ተጠያቂ አድርገው የከሰሱት ህወሃትን ነበር  በዚህም ምክንያት በቪዲዮው መጀመርያ ላይ የቀረበው የሟቹ ጠ/ሚንስትር ምስል ነበር።   በአሳዛኝ መልኩ ከተወሰነ ግዝያት በኌላ ዲ/ን ዳንኤል  ይህንኑ ህወሃት ተወንጅሎበት የነበረዉን የወንጀል ድርጊት ዛሬ በህዝበ ሙስልሙ ላይ መለተጠፍ ለምን አስፈለጋቸው?

ዲ/ን ዳንኤል  በእርሶ አስተሳሰብ በአንድ ወንጀል ስንት አካሎች ይጠየቃሉ ብለው ያምናሉ? ዲ ዳንኤል ወንጀሉን በሙስሊሙ ላይ ያላከኩበት ምክንያት

1ኛ/ የህወሃት አለቆቹን ከፈጸሙት ወንጀል ነጻ ለማድረግ

2ኛ/ ህወሃት የእስልምና እና የክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ለማጋጨት የሚሸርበዉን ሴራ እንዲያሳኩ የተሰጣቸውን ተልእኮ ከግብ ለማድረስ ።

ለዚህም ነው የሃይማኖት አባት ካባቸዉን ተጠቅመው  ለህወሃት የሚሰሩ  የውስጥ አርበኛ ናቸዉ የምለው። ይህን ነጥብ በተመለከተ የተጠቀሰኩትን የቪዲዮ መረጃዎች ከዚህ በታች ይመልከቱ

Ethiopian Government incited killing in Jimma, Ethiopia : https://youtu.be/SwSYIHlQ5ZI

ሌላው እሳቸው እና መሰሎቻቸው በተደጋጋሚ ሙስሊሙን የሚወነጅሉበት ክስ በበደኖ ህወሃት ከአማራ ብሄር ተወላጅ በሆኑ ክርስቲያን ወገኖቻችን ላይ የፈጸመው  ወንጀል ነው።  የወንጀሉ ሰለባ ከነበሩት የክርስትና እምነት ተከታይ የአካባቢው ነዋሪ ሙስልም ወገኖቻቸው እንዴት ከሞት እንዳዳኗቸው መረጃ ያቀረቡበትንና የቃለ-ምልልስ ሙሉ ዘገባ ከዚህ በታች ይመልከቱ።

ዲያቆን ዳንኤል ጽሁፋቸዉን ካቀረቡ ከጥቂት ግዝያት በኌላ  በ2011 አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በውቅቱ በሃገራችን ስለ ነበረው የሃይማኖት መቻቻል እና በዚያም ረገድ የአሜሪካ ፖሊሲ ምን መምሰል አለበት በሚል ጉዳይ ላይ ዘጠኝ ወራት የፈጀ ጥናት አካሄዶ ነበር ። የጥናቱም ውጤት በዊኪሊክዊ ይፋ ሾልኮ ወጥቷል።  ይህም የዊኪሊክ መረጃ ጥናቱ በየክልሎች ያሉ በርካታ የክርስትና እና የእስልምና እምነት አባቶችን አስተያየት ፣ የመጅሊስ እና ሲኖዶስ አባላትን ግምገማ ያካተተ መሆኑን አሳዉቋል።   ተሳታፊዎቹ ስለ ሁለቱ እምነት ተከታዮች አብሮ መኗኗርም ሲገልጹ በጥቅሉ በሃገራችን ያለው የሃይማኖት ግንኙነት ሁኔታ ሁልግዜ ፍቅር በፍቅር ነው ባይባልም የሁለቱ እምነት ተከታዮች  በጋብቻ የተሳሰሩ መሆንና በአንድ ቤተሰብ ዉስጥ የሁለቱ እምነት ተከታዮች መኖር tolerate የምደረግ መሆኑ በዘር የመቆራኘትን  ስላስከተለ ይህን ግንኙነት ለመጠበቅ ማህበረሰባችን ችግሮችን የሚፈታበትን ለየት ያለ ዘዴ mechanism እንዲያበጅ አስችሎታል የሚል አስተያየት ሰጥቷል።  አጥኚዉ ቡድን ይህኑኑ ሃሳብ ለቀድሞ ፓትርያርክ አቅርቦ  እርሳቸውም በጥናቱ ውጤት የተስማሙ መሆናቸዉን በመግለጽ አንድ ተዘነጋ ያሉትን ነጥብ አክለዋል ። ይህም በዋናይቷ ከተማ የሚደረገው የሃይማኖት እሽቅድምድም ሲሆን በእርሳቸው አመለካከት ጥቂት የሁለቱም እምነት ተከታዮች አክራሪነት ታይቶባቸዋል የሚል እንደ ነበር ጥናቱ ያስረዳል።

ከዚህ በተጨማሪ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ ስለ አክራሪነት ስጋት በጥናት ቡድኑ ተጠይቀው ስመልሱ የአክራሪነት ስጋት እንደሌለ የገልጹ ቢሆንም ጥቂት  የሚያሰጋቸው ጉዳይ ቢኖር የሶማልያ ክልል በድርቅ በተጠቃበት ወቅት ከፈደራል መንግስት አፋጣኝ እርዳታ እንዲደርስ ባለመደረጉ  በወቅቱ  አል-ኢታሃድ በመባል የሚጠራው አክራሪ ድርጅት ለተጎጂዎች እርዳታ እያደረገ ስለነበር የአካባቢው ህዝብ ወደ አል-ኢታሃድ እና  ወደ ኦጋዴን ነጻ አውጪ ሊሳብ የመቻል አደጋ ነበር ።  ከዚህ ባሻገር ፓርቲያቸው የሚተገብረው ፖሊሲ  የሙስሊሙን ህብረተሰብ መብት ቀደም ሲል ከነበሩት ስርአቶች በተሻለ መልክ እንዲከበር ስላስቻለ የሙስሊሙ ህብረተሰብ የፓርቲያቸው ደጋፊ በመሆኑ ለአክራሪ አስተሳሰቦች ጆሮ አይሰጥም በማለት የሽብር ስጋት በአገሪቱ እንደሌለ ገልጸው ነበር።

ታዲያ እውነታው ይህ ሆኖ እያለ ዲ /ዳኒኤል ህዝባችንን ሊተላለቅ የተቃረበ የሚያስመስል ጽሁፍ ያቀረቡት ለምን ይሆን ? ይህን የህዝባችንን የመኗኗር ብቃት የሚሸረሽር እና ለአመታት ልቆይ  የሚችል የማይበርድ የደም መፋሰስ ሊያስከትል   መርዛም የሃሰት ዘገባ ማቅረባቸው ለምን ይሆን ? ለዚህ ዋነኛው ምክኒያት ጽሁፋቸው ክፉ ስሜታቸዉን የተከተለ እንጂ መሬት ላይ ያለዉን ሁኔታ ያላገናዘበ መሆኑን እና  ልቦናቸው በእስልምና እምነት ላይ ባለቸው ጭፍን ጥላቻ ተደፍኖ ለህዝባችንና ለሃገራችን ደህንነት ደንታ ቢስ እንዲሆኑ ማድረጉን ነው ። ለነገሩ እንደ ሃይማኖት አባት ይጠበቅባቸው የነበረው የተጣላን በማስታረቅ በህዝባችን መካከል ሰላም ማስፈን ነበር። ያለመታደል ሆኖ እሳቸው ግን በትጋት እየሰሩ ያሉት ህዝባችንን ለማፋጀት ነው። ለህሊናቸው አቤቱታ ማቅረብ እወድ ነበር  ፣  ዳሩ ግን ….. ለክፍል ሶስትላቆየው መሰለኝ

ከአብዱላህ

 

 

The post የዲያቆን ዳንኤል ስሜታዊ ትንተናና መሬት ላይ ያለው እዉነታ ! ክፍል 2 – ከአብዱላህ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>