( ክፍል አንድ)
ምርጫ 2007 አስመልክቶ ገዥው መደብ “ምን አስቦ ምን ይፈጵማል ” የሚለውን መነጋገር ከጀመርን ግማሽ አመት አለፈው። ባለፋት ወራት በርካታ የተጠበቁም ያልተጠበቁም ድርጊቶች ተፈጵመዋል። ከእነዚህ ድርጊቶች ወሳኝ የሚባሉትን ነቅሶ በማውጣት መመልከት ያስፈልጋል። በመሆኑም ባለፋት ጊዜያቶች ይፈፀማሉ ብለን የገመትናቸውን ግምገማ እና በቀጣይ ወራት ሊፈፀሙ የሚችሉ እቅዶችን ትንበያ አስተሳስሮ ማየት ተገቢ ይሆናል። ባለፋትም ሆነ በቀጣይ ጊዜያት የሚኖሩ ተግባራት በመለየት መከራከር፣ መወያየትና በመሰረታዊ ጉዳዬች ላይ የጋራ መግባባት ፈጥሮ መንቀሳቀስ ወሳኝ ይሆናል።
እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል በአጀንዳው ዙሪያ መነጋገር መቻሉ የተለያዩ ጠቀሜታዎች ይኖሩታል። በአንድ በኩል በኢትዬጲያ የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ትግል የደረሰበትን ደረጃ ለመመልከት ያስችላል። በሌላ በኩል እንደ ግለሰብ ” የእኔ አስተዋጵኦ ምን ነበር? ፣ ከዚህ በኃላስ ከእኔ ምን ይጠበቃል?” የሚለውን ወደ ራሱ ውስጥ እንዲመለከት እድል ይከፍትለታል። በመሆኑም እነዚህን ከላይ የተጠቀሱ ጠቀሜታዎች ታሳቢ በመውሰድ እንደ አንድ ኢትዬጲያ ውስጥ የዲሞክራሲ ስርአት እንዲመጣ የሚመኝ ግለሰብ ያለፋትን ለመገምገምና ቀጣዩን ለመተንበይ የሚከተሉትን የመነሻ ሀሳቦች ለማንሳት ወደድኩ። እነዚህ አስተያየቶች የየትኛውንም የፓለቲካ ፓርቲ ሆነ የሚዲያ ተቋም ( “የእኔ የሆነውን ” ኢሳት ጨምሮ) አቋም የሚመለከት አይደለም። ከዚህ በተጨማሪም ግምገማውም ሆነ ትንቢቱ እንደመነሻ ለውይይት የቀረበ በመሆኑ ያገባኛል ባዬች በተሻለ ሁኔታ እንደሚያዳብሩት ታሳቢ ተወስዷል።
በዚህ ክፍል አንድና በቀጣዩ ክፍል ሁለት ” ምን ታቅዶ ምን ተፈፀመ?” የሚለው ላይ ብቻ ለማተኮር እሞክራለሁ። በሶስተኛው ክፍል “በቀጣይ ገዥው መደብ ምን ያስባል፣ የቀጣይ የትግል አቅጣጫው ምን ይሁን?” የሚለው ላይ የመነሻ ሀሳብ ይቀርባል። ” ምን ታቅዶ ምን ተፈፀመ?” በሚለው ክፍል ገዥው መደብ የምርጫው ሂደት ትኩረት እንዲነፈገው ያደረገበት ምክንያት፣ ህብረተሰቡን የሚያነቁ አካላት ላይ የተወሰደ እርምጃ፣ ምርጫ ቦርድን የኢህአዴግ ክንፍ ለማድረግ የተወሰዱ እርምጃዎችን፣ የፓርቲ በአላትን እንደ ቅስቀሳ ስልት የመጠቀም ስትራቴጂን፣ የሀይማኖት ተቋማት እና አመራሮች ላይ ገዥው መደብ አቅዶ የፈፀማቸውን እንመለከታለን።
ሀ• ምን ታቅዶ ምን ተፈፀመ?
1• ለምርጫው ሂደት ትኩረት የመንፈግ ስትራቴጂ
በኢትዬጲያ አዲሱ አመት መጀመሪያ ወር ላይ ከሲሳይ አጌና ጋር በነበረን ቆይታ ቅድሚያ ትኩረት ሰጥተን የተነጋገርነው ህውሀት/ ኢህአዴግ ቀጣዩ ምርጫ በሀገሬው ህዝብና የአለም አቀፍ ተቋማት እንዳይነገር ትኩረት መንፈግ ስትራቴጂ እንደሚከተል ነበር። የዚህ ስትራቴጂ መነሻ በምርጫ ዘጠና ሰባት ኢህአዴግ ለምን ተሸነፍን የሚለውን ሲገመግም የተቀመጠ አቅጣጫ እንደሆነ ለማመላከት ተሞክሯል። በ1997 አ• ም• የምርጫው ሂደት በመስከረም ላይ በይፋ ተጀምሮ ነበር። ካልተሳሳትኩ በትምህርት ፓሊሲው ላይ በፓለቲካ ፓርቲዎች መካከል ክርክር የተደረገው በመስከረም ወር ላይ ነበር። በተከታታይ ወራትም የተጋጋለ የምርጫ ክርክር በመካሄዱ ህዝቡ የፓለቲካ ፓርቲዎችን አላማ መገንዘብ ቻለ። እንደ እኔም ሆነ ኢህአዴግ እምነት የምርጫ 97 የፓለቲካ ድባብ ከግራ ወደ ቀኝ የገለበጠው በወቅቱ የተካሄዱት የምርጫ ክርክሮች ናቸው። ይህን አስመልክቶ የመለስ ትሩፋት ገጵ 301 ላይ የሚከተለውን ድምዳሜ ኢህአዴግ ማስቀመጡን ታመለክታለች፣
” … በምርጫ ክርክር ወቅት ኢህአዴግ ባልተዘጋጀበት ሁኔታ በሩን መበርገድ አልነበረበትም። ግንቦት ለሚካሄድ ምርጫ መስከረም ጀምሮ የሚዲያ ክርክር መካሄዱ ጥፋት ነበር።”
በመሆኑም የምርጫውን ሂደት ትኩረት መንፈግ የማይታለፍ ሆነ። አሁንም ሆነ ህውሀት በስልጣን ላይ እስከቆየ ድረስ ይህ ስትራቴጂ ተጠናክሮ ይቀጥላል። በምርጫ 2007 እያየነው ያለነው ይህንኑ ነው። እስከ ታህሳስ መጨረሻ ድረስ ስለምርጫ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ የሚወራ ነገር በመንግስት ሚዲያም ሆነ በገዥው መደብ ካድሬዎች አልነበረም። የምርጫ ክርክሩ የተጀመረው በዚህ ሳምንት ምርጫው ሊካሄድ ከሁለት ዲጅት በታች ቀናት ሲቀረው ነው። ይህም ቢሆን በሰአት ድልድሉ ገዥው መደብና ተላላኪዎቹ የአንበሳውን ድርሻ ወስደው ” አይኔን ግንባር ያድረገው” ቅስቀሳና ማስፈራሪያ ያደረጉበት ነበር። እንደዛም ሆኖ ከእነእጥረቱም ቢሆን የተቃዋሚ አመራሮች የተሻለ ነጥብ አስመዝግበው የወጡበት ነበር። ለዚህ እማኝ የሚሆነው በማህበራዊ ድረገጶች የተፈጠረውን መነቃቃት መመልከት በቂ ይሆናል። ከማህበራዊ ድረገጶች ወጥቶ በህብረተሰብ ደረጃ መነሳሳት ፈጥሯል ወይ? የሚለው ላይ የተሟላ መረጃ ስለሌለኝ ብዙ ማለት የሚቻል አይደለም። ይሁን እንጂ በምርጫ ለውጥ አይመጣም፣ መድብለ ፓርቲ ወደ መቃብር ከወረደ ቆይቷል ፣ ምርጫ ቦርድ የኢህአዴግ አንድ ክንፍ ነው፣… ወዘተ የሚለው አመለካከት በኢትዬጲያ ህዝብ ገዥ አመለካከት በሆነበት ሁኔታ የተለወጠ ነገር አለ ብሎ መገመት ማሞ ቂሎ ከመሆን የሚዘል አይደለም።
2• ህብረተሰቡን የሚያነቁ አካላትን ልክ የማስገባት ስትራቴጂ
ለዚህ ስትራቴጂ መነሻ የሆነውም የምርጫ 97 ውጤት ግምገማ ነው። በግምገማው የተደረሰበት ድምዳሜ የኢትዬጲያን ህዝብ ለመብቱና ነጳነቱ ለማታገል ወስነው የሚንቀሳቀሱ አካላትና ግለሰቦችን ” ዲሞክራሲያዊ ኢንስትሩመንት” በሚል አቅጣጫ “አብዬታዊና ዲሞክራሲያዊ እርምጃ ” መውሰድ የሚል ነበር። ይህ አብዬታዊ እርምጃ ባለፋት አመታት በሚያስደነግጥ ሁኔታ ተጠናክሮ ቀጥሏል። ይህ አይን ያወጣ የጭካኔ እርምጃ በኢትዬጲያ ህዝብ እየተለመደ ከመሄዱ የተነሳ ” ቀጣዩ ተረኛ እከሌ ፓርቲ፣ እከሌ ግለሰብ ነው!” የሚል ትንበያ የሚያሰጥበት አስፈሪ ደረጃ ደርሷል። እንደተባለውም ፓርቲዎችና ግለሰቦች እርምጃ ሲወሰድባቸው ” ምን አዲስ ነገር መጣ? ” የሚሉ አባባሎች ህብረተሰባችን ፀረ ዲሞክራሲን የመሸከም መጥፎ አዝማሚያ አሳይቷል። ይህ አስተሳሰብ ከገባንበት ፍጱም የድህነት አረንቋ ጋር መጃመሉ ስለማይቀር በሂደት እንደ ሀገር ብቻ ሳይሆን እንደ ሙሉ ሰው መቀጠላችንን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ወደ መሆን መሸጋገሩ አይቀርም።
ወደ ስትራቴጂው ስንመለስ ከአጭር ጊዜ አኳያ እንደ ቡድን የመጀመሪያ ሰለባ የሆኑት ራሳቸውን ” የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን” የሚል ስያሜ የሰጡት ወጣቶች ናቸው። እነዚህ ወጣቶች ላይ ገዥው መደብ ለምን ልዩ ትኩረት ሰጠ? የሚለውን መልሶ ማለፍ ተገቢ ይሆናል። የመጀመሪያው የቡድኑ አባላት ወጣት መሆናቸው ከሚፈጥርላቸው ጉልበት ባሻገር የተለያየ ፕሮፌሽን ባለቤቶች መሆናቸው ነው። የተለያየ ሙያ ባለቤት በመሆናቸው በሁሉም አቅጣጫ የገዥው መደብ ውሳኔዎች፣ እርምጃዎች፣ ፓሊሲዎችና ኩነቶችን ተከታትለው የመንቀፍ እድል ፈጥሮላቸዋል። በተለይ ራሱ ገዥው መደብ የሚፈጥራቸውን ኩነቶች ተገን አድርገው ( የህገመንግስት ቀን፣ የብሔረሰብ ቀን) የማስተማሪያ ስልት ቀይሰው መንቀሳቀሳቸው የሚያበሳጭ እንደሆነ ይጠበቃል። ይህም የኢትዬጲያ ህዝብ ( በተለይ ወጣቱ) ከድርጊቶቹ በስተጀርባ ያሉትን እውነታ እንዲገነዘብ እድል ፈጥረዋል።
ገዥው መደብ በሁለተኛ ደረጃ ልዩ ትኩረት ሊሰጥ ያስገደደበት ምክንያት ባልተጠበቀ ሁኔታ የምሁርነት ሚናን በመዘንጋትና በምናገባኝነት በመሸፈን ራሳቸውን ከሀገራቸው ጉዳይ ያገለሉ ምሁራንን የማነቃቃት ድርሻ በመጫወታቸው እንደሆነ ይገመታል። ይህ ደግሞ ለደቂቃ በትእግስት ሊታለፍ የሚችል አይደለም። የገዥው መደብ ፍላጐት ምሁራንና ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ባይተዋር እንዲሆኖ፣ አልፎ ተርፎም በተሰማሩበት ቦታ ወጣቱን ” ዲ -ፓለቲሳይዝ” እንዲሆን አድርገው እንዲያፈሩ ነው ( በቅርብ ጊዜ ፓለቲካ ምን ያደርግላችኃል የሚሉ የሀይማኖት ሰባኪያን በአደባባይ መውጣታቸውን ልብ ይሏል)። በመሆኑም ገዥው መደብ “ምሁራን በሁለቱም ወገን የተሳለ ቢላዋ” ብሎ የፈረጃቸው ከመሆኑ አንጳር ጦማሪያኑ በሚያነሱት አጀንዳ ተጐትተው ወደ አብዬቱ በመግባት ግንባራቸውን ለጥይት የሚሰጡበት ሁኔታ እንዳይፈጠር ማድረግ ጊዜ የሚሰጠው አይደለም።
ሶስተኛው ምክንያት እነዚህ ጦማሪያን በኢትዬጲያ ውስጥ ያልተጠበቀና አዲስ ሁኔታ መፍጠር መቻላቸው ነው። ይህም በአንድ በኩል ወጪ ቆጣቢና እያደር እየሰፋ የሚሄድ ስልት መከተላቸው ሲሆን፣ በሌላ በኩል ገዥው መደብ ባወጣቸው አፋኝ ህጐች ማእቀፍ ውጭ መንቀሳቀሳቸው ነው። ከዚህ አንጳር ጦማሪያኑ በግብር የመንግስታዊ ያልሆኑ ሲቪክ ድርጅቶችና የሚዲያ ሚና እየተጫወቱ በህግ ደግሞ በአዲሱ NGO LOW ሆነ በሚዲያ ህጉ መታቀፍ አለመቻላቸው ትልቅ ራስ ምታት ይሆናል። እስከማውቀው ድረስ በሁለቱም አዋጆች ጦማሪያኑን ለመመዝገብም ሆነ ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል ምእራፍም ሆነ የአንቀጵ ማእቀፍ የለም። በዚህም ምክንያት ይመስላል ገዥው መደብ በህልሙም አስቦት የማያውቀውን አዲስ የሚዲያ አዋጅ ወደ ማውጣት የተሸጋገረው።
በመሆኑም የገዥው መደብ የቅድሚያ እርምጃ እነዚህ የየትኛውም የፓለቲካ ፓርቲ አባላት ያልሆኑ ወጣቶችን የሽብርተኝነት ካባ በማልበስ ከጨዋታ ውጭ ማውጣት ነበር። ይህም ከሞላ ጐደል የተሳካ እርምጃ ቢሆንም በተቃራኒው የወጣቶቹን ፈለግ የሚከተሉ፣ የቀደምት ተግባራቸውን የሚዘክሩ፣ ከልደት በአላቸው አንስቶ በተለያዪ አጋጣሚዎች የወጣቶቹን ቀንዲልነት የሚዘክሩ አእላፍ ሀይሎች ከመፈጠር ሊያግዱት አልቻሉም።
ህብረተሰቡን እንዳያነቁ ልክ ከማስገባት አንጳር የገዥው መደብ ጡንቻ ቀጥሎ ያረፈው ተጵእኖ የሚያሳርፋ የፓለቲካ ፓርቲዎችና አመራሮች ላይ ነበር። ( ይቀጥላል)
The post ምን ታቅዶ ምን ተፈፀመ?፣ …የቀጣይ የትግል አቅጣጫ ምን ይሁን? (ኤርሚያስ ለገሰ) appeared first on Zehabesha Amharic.