Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የደብረ ሊባኖሱ እልቂት –ከዲ/ን ዳንኤል ክብረት

$
0
0

dr. asfea wossen asserate

daniel-kibret-300x207ኢያን ካምፕቤል ፋሽስት ኢጣልያ ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ላይ ስለ ፈጸመቺው አሰቃቂ እልቂት የሚተርክ The Massacre of Debre Libanos, Ethiopia 1937› የተሰኘ መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ ይኼ ብዙ ጊዜ የማይነገርለት ነገር ግን እርሳቸው ‹ፋሽዝም ከፈጸማቸው ጆሮ ጭው የሚያደርጉ የጭካኔ ሥራዎች አንዱ ነው› ብለው የገለጡት ዘግናኝ የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ሰብአዊ አረመኔነት በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በጥናት ተመሥርቶ በዝርዝር ቀርቧል፡፡

 

ጣልያኖች የኢትዮጵያውያንን የጀግንነት መንፈስ ለመስበር ከመጀመሪያው ተዘጋጅተው ነበር የመጡት፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደ አንድ ርምጃ የወሰዱት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ማንበርከክ ነው፡፡ ምንም እንኳን የተወሰኑ ጳጳሳት ከእነርሱ ጋር ለመሥራት ባያንገራግሩም እንደ አቡነ ጴጥሮስ ያለ ቆራጥ አባት መፈጠሩ፤ ብዙዎች ገዳማትና አድባራት አርበኞችን መርዳታቸው፤ ካህናቱም

ወግጅልኝ ድጓ ወግጅልኝ ቅኔ

ወንዶች ከዋሉበት እውላለሁ እኔ

እያሉ ሀገራቸውን ለመከላከል በረሐ መውረዳቸው ጣልያኖችን ዕረፍት ነሥቷቸው ነበር፡፡ በተለይም ደግሞ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓም በግራዝያኒ ላይ በተቃጣው የመግደል ሙከራ ዋነኞቹ ተሳታፊዎች አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ጋር ግንኙነት አላቸው መባሉ፡፡ አርበኛው ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ የፍቼ ተወላጅ በመሆናቸው ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሎ በመታሰቡ፡፡ ታዋቂው አርበኛ  ኃይለ ማርያም ማሞ  ከገዳሙ መነኮሳት ጋር ይገናኛል መባሉ ጣልያኖች በደብረ ሊባኖስ ላይ የዘንዶ ዓይናቸውን እንዲጥሉ አደረጋቸው፡፡

ይበልጥም ደብረ ሊባኖስ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያለው ቦታ የጣልያኖችን የጥፋት ትኩረት ስቦታል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱን፣ በእርሷም በኩል የጀግንነቱን መንፈስ አከርካሪውን ለመስበር ያሰቡት ፋሽስቶች የታላቁ ጻድቅ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ምዕራፍ፣ የእጨጌው መቀመጫና ለአያሌ ገዳማት መመሥረት ምክንያት የሆነውን ገዳም ለማጥፋት፣ ሲያጠፉትም ሌላውን ሊያስደነግጥ በሚችል መልኩ በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲሆን ወሰኑ፡፡

በዚህም መሠረት ግራዝያኒ ያቀናበረውና ጄኔራል ማለቲ የመራው ጦር ግንቦት 10 ቀን 1929 ዓም ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ወረደ፡፡ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ፍልሰተ ዐጽም የተከናወነበትን በዓል ለማክበር የተሰበሰቡትን ምእመናንንና መነኮሳትን መጨፍጨፍም ጀመረ፡፡ በጫጋል፣ በውሻ ገደል፣ በሥጋ ወደሙ ሸለቆና በደብረ ብርሃን አጠገብ በእንግጫ በተከናወነው ጭፍጨፋ ገና ነፍስ ያላወቁ ሕጻናት የቆሎ ተማሪዎችን ጨምሮ ከ1801 እስከ 2201 የሚደርሱ ምእመናንና መነኮሳት በግፍ ተረሸኑ፡፡ አውሬ እንዲበላቸውም የትም ተወረወሩ፡፡

በዚህም አላበቃም፡፡ በገዳሙ የነበሩ መጻሕፍት፣ የከበሩ ዕቃዎች፣ ንዋያተ ቅድሳት፣ ገንዘብና ሌሎች ንረቶች ተዘረፉ፡፡ ገዳሙም ነጻነት እስኪመለስ ድረስ በመከራ ውስጥ ኖረ፡፡

አስገራሚው ነገር ከ500 ዓመታት በፊት ግራኝ አሕመድ ገዳሙን ሲያቃጥል የሞቱት መነኮሳት ቁጥር 450 ነበር፡፡ ፋሽስት ኢጣልያ የጨፈጨፈቺው ከእርሱ አምስት ጊዜ እጥፍ የሚበልጥ መሆኑን ስናስበው የጭካኔውን መጠን ያመለክተናል፡፡

መጽሐፉን ስታነቡት ኀዘን፣ ቁጭትና ግርምት ይፈራረቁባችኋል፡፡ ሕጻናት፣ ወጣቶች፣ ጎልማሶችና አረጋውያን በሃይማኖታቸውና በኢትዮጵያዊነታቸው ምክንያት ብቻ የደረሰባቸውን ግፍ ስናስበው ልባችን በኀዘን ፍላጻ ይወጋል፡፡ ማንበብ እስኪያቅተን ድረስ በሰቆቃወ ደብረ ሊባኖስ እንዋጣለን፡፡ ለደረሰባቸው ግፍ ተመጣጣኝ ካሣ አለማግኘታቸውን፣ ኢጣልያ የፈረመቺውን ውል እንኳን ሳታከብረው 74 ዓመታት ማለፋቸው ስትመለከቱ፡፡ ግራዝያኒ ወስዷቸው ዛሬ እንደ አቤል ደም እየተካሰሱ በሮም የሚገኙትን የገዳሙን ንብረቶች ስታስታውሱ አባቶቻችን ልጅ አለመውለዳውን ዐውቃችሁ ይቆጫችኋል፡፡

ልጅ የለንም እንጂ ልጅማ ቢኖር

ተሟግቶም ተዋግቶም ያስመልስ ነበር፤

ብለው ያንጎራጎሩ ሲመስላችሁ ትቆጫላችሁ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይኼ እኛ ዛሬ የምንቀልድበት ነጻነት ምን ያህል ዋጋ እንደተከፈለበት ስታስቡ፣ ዋጋ ከፋዮቹንም በዓይነ ኅናችሁ ስትቃኙ ትገረማላችሁ፡፡ ግርምታችሁ በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ በዚያ የመከራ ዘመን የሰማዕታቱን ዐጽም ለመሰብሰብ፣ ቦታቸውም ለማወቅ በመንፈሳዊና ሀገራዊ ወኔ ታጥቀው የከወኑትም፤ ለታሪክም አስረጅ ሆነው የቆሙትን የክፉ ቀን ጀግኖች ስታስቡም ትደነቃላችሁ፡፡ እግረ መንገዳችሁን እንዲህ ያሉት የዓይን ምስክር ጀግኖች በዐረፍተ ሞት ከመገታታቸው በፊት ሌላውም ታሪካችን እንዲጻፍ ትማጸናላችሁ፡፡ አብዛኛው ሕዝብ አንብቦ እንዲጠቀምበትም በአማርኛ ታሪኩ ቢቀርብ መልካም መሆኑንም ሐሳብ ትሠነዝራላችሁ፡፡

ከዚህም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሁለት ሥራዎች እንደቀሩትም ትገነዘባላችሁ፡፡ ለእነዚህ ለእምነታቸውና ለሀገራቸው ሲሉ ለተሠዉ ሰማዕታት ተገቢውን ቦታ መስጠት፣ ታሪካቸውንም በስንክሳር ውስጥ በተገቢው ሁኔታ እንዲሠፍር ማድረግ፤ አያይዞም ደግሞ በዓላቸው በኦርዶክሳዊ ሥነ ሥርዓት እንዲከበርና ትውልድ ሀገራዊም መንፈሳዊም በረከት እንዲያገኝባቸው ማድረግ ይገባዋል፡፡ ለዚህም ደራሲው ኢያን ካምፕቤል አጥልቀው አጥንተው፣ ተንትነው ጽፈውታልና ምስጋና እየቸርን መጽሐፉን እናንብበው፡፡

መልካም ንባብ፡፡

The post የደብረ ሊባኖሱ እልቂት – ከዲ/ን ዳንኤል ክብረት appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>