ላንተ፣ ላንቺ ለርስዎስ
ትርጉም አለው?
ንክክ አለን ወይ – ቅርርብ?
ዝምድና አለን ወይ – ትስስር?
ይጎንጠኛል – ወይስ – ያቅፈኛል?
ይጠራኛል – ወይ – ያርቀኛል?
እውነት አድዋ – ለኔ ምኔ ነው?
እ ከ ከ ከ ከ ከ ከ ከ ከ!!!
አድዋማ!
አድዋ እኮ!
ሩቅ አይደለም
በቀን በወር አይለካም፤
ያጥንት የሥጋዬ ፍላጭ ሆኖ
በደም ሥሬ የሚፈስ ደም
ስብሳቢ ቆዳዬ ከውኖ
የምንነቴ አምድ ነው
አድዋማ እኔኮ ነው።
አድዋ እኮ!
ሰማዩ ከላይ ሆኖ
ደመናው ጉልበት ዘግኖ
ከዋክብትና ጨረቃ
አየሩም ከኛ ወግኖ
ያሤሩበት
ያደሙት፣
ጥላቸውን የጣሉበት
ብርሃን የሠጡበት
እኮ ነው።
አድዋ እኮ!
ሜዳ ሸንተረሩ
ወንዝና አፈሩ ሳይቀሩ
ቋጥኝ ደንጋዩ ሲደረደር
ሸለቆው ከኛ ሲያብር
ተራራውም ሲውተረተር
ማንነቱን ያሳየበት
ተናግሮ ያሰማበት
ያጌጠ ያማረበት
እኮ ነው።
አድዋ እኮ!
እምዬ ሚኒሊክ
እቴጌ ጠሐይቱ
የቤተ መንግሥቱ
የቤተ ክህነቱ
የቤት እንሰሳቱ
የጓሮ አታክልቱ
የኔነው ነፃነት
አልሻም ባርነት
ብለው የቆሙበት
ባንድ የተነሱበት
ባንድ የዘመቱበት
እኮ ነው! አድዋ!
አድዋ እኮ!
ሽማግሌ አባቱን
አዛውንት እናቱን
ውድ ባለቤቱን
የታዘለ ጨቅላ ልጁን
የሞቀ ጎጆውን ጥሎ
ሞፈር ቅንበሩን ስቅሎ
የተዘራ ስብሉን
የውሎ ስንቁን ጠቅልሎ
የዘመተው ወገኔ
የሱን ኑሮ ለኔ
የሠጠበት ዘመቻ እኮ ነው!
እንዴ አድዋ ባይኖር እኮ!
ያገር የወገኔ ጀግንነት ባያበራ
ኢትዮጵያ እንደገና ተጠናክራ
ባልገዛም ባይነቷ ተከብራ
የነፃነት እድሜዋን ቆጥራ
ኢትዮጵያዊ ሆኜ እንድፈጠር
እኔ እንድኖር አይሆንም ነበር።
አድዋ እኮ!
ቆራጥነት ተንቦግቡጎ
የወንድ የሴት ጀግንነት
ሞት አይፈሬነት ፈጎ
ያያት ቅድመ አያት ሸንጎ
ምክር ዘዴ ተፈልጎ
የታየበት
የፋፋበት
ያበበበት – ያፈራበት
የታሪክ አምድ እኮ ነው።
አድዋ እኮ!
አይቀጡ ቅጣት ተሰንዝሮ
የጠላት ቅስሞ ተሰብሮ
ቋንጃ ቁመናው ተመትሮ፣
ጠላት አንገቱን ደፍቶ
የተቀጣበት
ያፈረበት
ያለቀሰበት
የሞተበት
ታሪካችን ያበራበት
እኮ ነው!
አድዋ እኮ!
ኢትዮጵያዊነታችን አብርቶ
የወገናችን አንድነት ፀንቶ
ነፃነታችን ጎልቶ
የሞቀበት
የደራበት
ያጌጠበት
ያማራበት
እኮ ነው!
አድዋ እኮ!
በታሪካችን አዲስ ምዕራፍ
ለኢትዮጵያዊነት ቋሚ ድጋፍ
ተራራውና ሸንተረሩ
ወግነው ከጋሻው ከጦሩ
ሸለቆውና አፈሩ
ከወገን ጋር ሲኮሩ
ወንዙ ውሃው ፈሳሹ
ሲሞላ ቀድሞ ደራሹ፣
ኢትዮጵያ እያለ ደንፍቶ
በመደፈሩ ተቆጥቶ
የተጫነው አህያ
በቅሎይቱና ፈረሱ
ወደፊት ቆርጠው ሲገሰግሱ!
ኢትዮጵያ!
ኢትዮጵያ!
ኢትዮጵያ! እያለ
የገደሉ ማሚቶ
ሲጮህ መልሱን አጉልቶ!
የምረግጣትን መሬት
የተቀለሰችልኝን ጎጆ ስሪት
ያረጋገጡልኝ
የሠጡኝ
ያበጁልኝ እኮ ባድዋ ነው!
ታዲያ ከዚህ የበለጠ ምን አለው?
አድዋ እኮ!
እኔ ተፈጥሬ እንድኖር
ቅድመ አያቶቼ ገብተው አፈር
በተቀበሩበት ምድር
በረገፈ አጥንታቸው
መሬቱን ባቀለመው ደማቸው
ኢትዮጵያዊነቴን አንጸው
አበልጽገው
ያ እኮ ነው
አድዋ ጽዋው!
እምዬ በሉ!
ጣይቱ በሉ!
ኢትዮጵያ በሉ!
አድዋ በሉ!
ማንነታችሁን ተቀበሉ!
አንዱ ዓለም ተፈራ
እስከመቼ፤ ረቡዕ፤ የካቲት ፲፰ ቀን ፳፻፯ ዓመተ ምህረት
ሳኒቬል፤ ካሊፎርኒያ ( Wednesday, 2/25/2015 )
The post አድዋ ለኔ! – አንዱ ዓለም ተፈራ appeared first on Zehabesha Amharic.