ከአንደኛው የዓለም ጦርነት መባቻ ጀምሮ ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት የማቋቋም ጥረት አንዳንዴ ተፋፍሞ ሲግም በሌላ ጊዜ ደግሞ ሲሟሽሽ ቆይቶ ከሰባ ዓመት ያልተቋረጠ ጥረት በኋላ እ.አ.አ በ1998 ዓ.ም ጀሮም ስምምነት በፈረሙ አራት ሀገራት እ.አ.አ በ2ዐዐዐ ዓ.ም በሄግ ከተማ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍ/ቤት ተመሰረተ::
የዚህ ፍርድ ቤት መቋቋም የሰው ልጅ የህግ የበላይነት ለማስፈን ከወሰዳቸው እርምጃዎች እንደዋነኛ ስኬት ተቆጥሮአል:: ይህ ፍርድ ቤት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ተንሰራፍቶ ያለው ባለስልጣናት ለሰሩት ወንጀል ተጠያቂ ያለ መሆን ባህል (Culture of impunity) ይሰብራል በሚል እምነት በህግ ምሁራን፤ ለፍትሕ ከበሬታ ባላቸው ህብረተሰብና መንግስታት ዘንድ በትልቅ ደስታ ተቀባይነት አገኝቶአል:: በአንጻሩ ደግሞ ለሰው ልጅ ሕይወትና መብቶች ደንታ የሌላቸው መንግስታት ይህንን ፍርድ ቤት በመደበኛ ጠላትነት ፈርጀውት ለውድቀቱ ሌት ተቀን ይኳትናሉ:: ለዚህ ፍርድ ቤት ምስጋና ይግባውና የአንድ አገር መሪ እንደቀድሞው በማን አለብኝነት ሰውን እንዳሰኘው ጨፍጭፎ የአንድ ዘመን ወጣት ጭዳ አድርጎ ዙምባቡዌ ጐዳና ላይ መንሸርሸር ቀርቶአል:: ዛሬ እንደ መንግስቱ ኃይለማርያም ያሉ ጨፍጫፊዎችና ሌሎችም ይህንን ሰይጣናዊ ድርጊታቸው ከመፈጸማቸው በፊት ከጀርባቸው ይህ ፍርድ ቤት መኖሩና ለወንጀል ድርጊታቸው አንድ ቀን ተጎትተው በዚሁ ፍርድ ቤት ፊት ቀርበው ከፍትህ ጋር እንደሚፋጠጡ ስለሚያውቁ ከእርኩስ ድርጊታቸው ይታቀባሉ::
አምባገነን መሪዎች ይህንን ፍርድ ቤት ምን ያህል እንደሚፈሩት በአንድ ወቀት በሱዳኑ መሪ በአልበሽር የደረሰው ጥሩ አመላካች ነው:: በዓለም አቀፍ ወንጀል ፍርድ ቤት ክስ ቀርቦበት መጥሪያ የሚያሳድደው አልበሽር ኢትዮጵያን ጎብኝቶ ወደ አገሩ ሲመለስ እግረ መንገዱን መቀሌ አውሮፕላን ማረፊያ ያርፋል:: የተሳፈረበት አይሮፕላን መጠነኛ ችግር ስለገጠመው ጥገና እስኪደረግለት ትንሽ ይዘገያል:: አልበሽር አይሮፕላኑ ውስጥ እየጠበቀ ሳለ አንድ የአሜሪካን አይሮፕላን ቀስ ብሎ የአልበሽርን አይሮፕላን ይጠጋል:: አልበሽር ይህንን የአሜሪካን አይሮፕላን ባየ ጊዜ እኔን ለመያዝ የመጣ ነው በሚል በፍርሃት ይርድ እንደነበር ሁኔታውን የታዘቡ ሰዎች ገልጸዋል:: የአንድ አገር መንግስት የዚህ ፍርድ ቤት ሥልጣን መቀበልና አለመቀበል በአገሪቱ የዴሞክራሲ ስርዓት መኖር አለመኖር ልኬት ነው:: ስለሆነም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚከተሉ አገራት አፍሪቃንም ጨምሮ የዚህ ፍርድ ቤት አባል ሲሆኑ በአምባገነኖች ደግሞ የፍርድ ቤቱ አባላት ካለመሆናቸው በላይ ፍርድ ቤቱን በማውገዝ ግምባር ቀዳሚዎች ናቸው:: ይህንን ፍርድ ቤት የሚያወግዙ መሪዎች እንዲህ የሚሆኑት በፈጸሙት በወንጀል አንድ ቀን እዚሁ ፍርድ ቤት እንቀርብ ይሆናል ከሚል ፍርሃታቸው የመነጨ መሆን አለበት እንጂ ይህንን ለሰው ልጆች መብት ዘብ የቆመ ፍርድ ቤት የማያወግዙበት ሌላ ምን ምክንያት ሊኖር ይችላል?
ይህንን ፍርድ ቤት ከማንኛቸውም መሪዎች በላይ የሚያወግዙት የብቸኛዋ የተባበሩት መንግስታት መመስረቻ ቻርተር የፈረመችው አፍሪቃዊት አገር፣ የዓለም አቀፍ ህግጋት በመቀበል በቀዳሚነት ትታወቅ የነበረችዋ ኢትዮጵያ፣ የዛሬዎቹ መሪዎች ናቸው:: እነዚሁ የኢትዮጵያ መሪዎች ከማንም በላይ ይህንን ፍርድ ቤት ለመዝለፍ በተለያዩ መድረኮች ያዙኝ ልቀቁኝ ሲሉ ምን ፈርተው ነው ከሚለው ጥያቄ መሸሽ አይቻልም:: የኢትዮጵያ መሪዎች ከማንም በላይ ይህንን ፍ/ቤት በማብጠልጠል በፍርድ ቤቱ የጥላቻ ዘመቻ ለመክፈታቸው ማስረጃዎቹ እነሆ:-
1.በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በኒውዮርክ በተባበሩት መነግስታት ጉባዔ ተገኝተው ኢትዮጵያውያንን ባሸማቀቀ መልኩ ይህንን ፍርድ ቤት ሲዘልፉ፣ ሱያንኳስሱ ሰሚ ሁሉ እኚህ ሰውዬ ምንን ፈርተው ነው ይህንን ፍርድ ቤት እንዲህ የሚያብጠለጥሉት ብሎ መየጠቁ አይቀርም:: ፍርድ ቤቶች በነጻነት የፍትህ ስርዓቱን የሚያስተናግዱበት ዴሞክራሲ ሰፍኖ ሕዝብ የስልጣን ባለቤት የሆነበት አገር መሪ አቶ ኃይለማሪያም በፍርድ ቤቱ ላይ ያዘኑበት ዓይነት ነቀፌታ ቢሰነዘር ምናልባት ሰሚ ያገኝ ይሆናል:: እንደ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የውሃ ሽታ የሆነበት አገር በፍርድ ቤቱ ላይ የሚሰነዝረው ነቀፌታና እሮሮ የቁራ ጩኸት ከመሆን አይዘልም::
2.የኢትዮጵያ መሪዎች በፍርድ ቤቱ ላይ የቋጠሩት ቂም በዚህ ብቻ አላበቃም:: አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ከኒው ዮርክ ጠቅላላ ጉባዔ መልስ በአዲስ አበባ በተደረገው የአፍሪቃ የመሪዎች ስብሰባ ላይ ይህንን ፍርድ ቤት ሲያወግዙ በሃፍረት እየተሸማቀቅን አድምጠናል:: ቂሙና ጥላቻው የከረረ በመሆኑ እነዚህ ውርጅብኞችም በቂ ሆነው አልተገኙም::
3.በጥር 25 ቀን 2ዐዐ7 ዓ.ም አዲስ አበባ በተደረገው የአፍሪቃ የመሪዎች ጉባዔ በፍርድ ቤቱ ክስ ቀርቦባቸው በቂ መረጃዎች እያሉ እነዚህ ማስረጃዎች ባለመገኘታቸው ክሱ ከተነሣላቸው ከኬኒያው ፕሬዚዳንትና የፍርድ ቤት መጥሪያ ከሚያሳድዳቸው ከሱዳን መሪ አልበሺር ቀድመው የኢትየጵያ ተወካዮች ፍርድ ቤቱን ለማውገዝ አጀንዳ አስያዙ:: ኢትዮጵያ የፍርድ ቤቱን ስልጣን ካልተቀበሉ ጥቂት የአፍሪቃ አገራት አንድዋ መሆንዋ አንሶ የኢትዮጵያ ተወካዮች በምንም መልኩ ሳይነኩ በማያገባቸው ገብተው ሲፈተፍቱ ማየት ከማስገረሙም በላይ ያሳፍራል:: ለፍትህ ከበሬታው በላቸው የአፍሪቃ መሪዎችም ትዝብት ላይ መውደቃቸውም አያጠራጥርም:: ሌላም አስገራሚና የውድቀት ምልክት መሆኑ የሚያረጋግጠው የኢትዮጵያን ውግዘብ ደግፎ በተራው ፍርድ ቤቱ ያብጠለጠለው ማን መሆኑ ታውቃላችሁ? ሙጋቤ:: ባልተለመደ መልኩ በወቅቱ ሙጋቤ እንደልማዱ አላሸለበም ነበር:: የኢትዮጵያ መሪዎች የሙጋቤ ድጋፍና አቋም የአይጥ ምስክር ድምቢጥ አይነት ነው:: ፈረንጆች ወዳጅህ ማን እንደሆነ ብትነግረኝ አንተን ማን እንደሆን እነግርሃለሁ (tell me who your friends are and will tell you who you are) የሚለው ብሂል የኢትዮጵያና የዚምባቡዌ መዎች ማንነት ይገልጻል::
በጉባዔው ላይ ኢትዮጵያ መሪዎች ያቀረቡዋቸው ሃሣቦች ፣ጉባዔው በፍርድ ቤቱ ላይ የፀና አቋም እንዲወስድ፣ ፍርድ ቤቱ በተለይ በአፍሪቃ መሪዎች ላይ ማተኮሩ የዓለም ሕብረተሰብ እንዲያወግግ፣ ወንጀለኛ መሪዎችን የሚዳኝ አፍሪቃዊ ፍርድ ቤት ይቋቋም የሚሉ ነበሩ:: ከእነዚህ ጥያቄዎች አንዱም ውሃ የሚቋጥር አይደለም:: በመጀመሪያ የትኛው የአውሮፓ መሪ ነው መሣሪያ ሳይዙ ለሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ዜጐች ላይ ጥይት የሚያርከፈክፈው? አሜሪካን ውስጥ ነው ወይስ ኢትዮጵያ አንተ የዚህ ዘር አባል አይደለህም ከዚህ ጥፋ፣ አንተ የዚህ ሃይማኖት ተከታይ ስለሆንክ የሃይማኖት ነጻነት የለህም የሚባለው?
በፍርድ ቤት የተከሰሱት እኮ በነጻ ምርጫ ለስልጣን የበቁት የታንዛኒያ ወይም የደቡብ አፍሪቃ ወይንም የጋና ፕሬዝዳንቶች ሳይሆኑ ሕፃናት ለጦርነት አሳልፎ ያስፈጀው ቻርለስ ቴለር፣ በዳርፉር ጭፍጨፋ ተጠርጥረው ሕይወታቸው የቆጥ ላይ እንቅልፍ የሆነባቸው የሱዳኑ አልበሽር፣ በኃይማኖት ስም ህዝብን ያፈናቀለውና የጨፈጨፈው ዩጋንዳዊው ኮኒ ሲሆኑ እንዲሁም ሌሎች ተመሳሳይ ወንጀል የፈጸሙ ወንበዴዎች ናቸው:: ፍርድ ቤት ከቀረቡት ከአስር በላይ አፍሪቃውያን ፕሬዝዳንት አልበሽር ብቻ ክስ እንዲቀርብባቸው ጉዳያቸው ዐቃቤ ህጉ እንዲያጣራ ጥያቄ ያቀረበው የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ሲሆን፣ ሌሎች በሙሉ ምርመራው እንዲካሄድባቸውና ክስ እንዲቀርብባቸው ጠያቂዎቹ ኃያላን መንግስታት ሳይሆኑ የየአገራቸው መንግስታት ናቸው:: እንዲያውም ፍርድ ቤቱ በአፍሪቃውያን ወንጀለኞች ላይ ብቻ ቢያነጣጥር እንኳን ለአፍሪቃውያን ፍትሕ እስከቆመ ድረስ ይህ በራሱ ለአፍሪቃውያን ትልቅ ቁም ነገር አይደለም ወይ? ካምቦድያ ውስጥ ወንጀለኞች ስላልተከሰሱ የአፍሪቃ ወንጀለኞች በነጻ ይሂዱ ማለት በዓለም አቀፍ ሕግ ቀርቶ በየአገራቱ ሕግ የተፈቀደ አይደለም:: በነገራችን ላይ በአሁኑ ወቅት የዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቱ ዐቃቢ ህግ አፍሪቃዊ ያለልሆኑ ጉዳዮች ይከሰሱ አይከሰሱ የሚለውን ለመወሰን ከአስር መዝገቦች በላይ በመመርመር ላይ ይገኛል::
ፍርድ ቤቱን የመሰረተው የሮማ ህግ በሚዘጋጅበት ጊዜ የአፍሪቃውያን ተሳትፎ ከየትኛውም አህጉር የበለጠ ነበር:: ከየትኛውም አህጉር በላይ አፍሪቃ አገራት የፍርድ ቤቱ አባል ሆነዋል:: ነገር የተበላሸውና መሪዎቿ ከአቋማቸው ሽብርክ ያሉት አንዳንድ የአፍሪቃ መሪዎች ከዚህ በፊት ልማዳዊ ህግ ሆኖ የቆየውና በሰፊው ሲሰመራበት የነበረው የአንድ አገር መሪ በስልጣን እስካለ ድረስ አይከሰስም የሚለው ሕግ ተለውጦ አሁን ግን በህጉ በተጠቀሱት ወንጀሎች የተጠረጠረ መሪ ከተጠያቁነት አይድንም የሚለው በወንጀል ህጉ ላይ ከሰፈረ ወዲህ ነው::
ሌላው በፍርድ ቤቱ ላይ የሚሰነዘረው ስሞታ ፍርድ ቤቱ የኃያላን መሳሪያ ሆኖአል የሚል ሲሆን ሀቁ ግን ይህንን አያረጋግጥም:: የፍርድ ቤቱ ዋና አቃቢ ህግ የጋምቢያ ተወላጅ ሴት ወይዘሮ ሲሆኑ በፍርድ ቤቱ መዋቅር ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የያዙ አፍሪቃውያን በብዛት ይገኛሉ:: የኢትዮጵያ መሪዎች ፍርድ ቤቱን ከመዝለፋቸውም በላይ እግረ መንገዳቸው ለአፍሪቃ የወንጀል ፍርድ ቤት በአፍሪቃውያን ይቋቋም ያሉት የምራቸው እንዳልሆነ ማንም ይገነዘበዋል:: በእውነት አሁን የአፍሪቃ መሪዎች ከጥቂቶቹ በስተቀር የዚህ የሚቋቋመው ፍርድ ቤት መጥሪያ አክብረው ፍርድ ቤት ቀርበው ለቀረበባቸው ክስ መልስ ይሰጣሉ? የተባበሩት መነግስታት የጸጥታው ምክር ቤትና መላው የሰለጠነው ዓለም ከጀርባው ያሳለፈው ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንኳን የመያዝ ትዕዛዝ የወጣበትን አልበሺር በአፍሪቃ በኩራት እንደልቡ ሲንሸራሸር የፍርድ ቤቱ አባል የሆኑ አገራት ይዘው ማስረከብ ሲገባቸው አንዳቸውም ለመያዝ አልሞከሩም::
ይህ አለም አቀፍ ፍርድ ቤት አባል ለሆኑ አገራት ህዝቦች ከጨቋኝ መሪዎቻቸው የሚጠብቃቸው ከለላ ሲሆን የኢትዮጵያ መሪዎች በኢትየጵያውያን ላይ ለሚፈጽሙ ወንጀሎች ግን ለዓለም አቀፍ ሰላም ጠንቅ እስካልሆኑ ድረስ ኢትዮጵያውያን ምንም አይነት ከለላ የላቸውም:: በህግ ያለተገደበ ስልጣን አደገኛነቱ የተረጋገጠ ነው:: አንድ አምባገነን መሪ ከኋላዬ ህግ አለ እጠየቅበቃለሁ ካላለ ማንን ፈርቶ ከድርጊቱ ይታቀባል? ስለሆነም እንደ ማንኛውም የዓለም ህዝብ ኢትዮጵያውያን የህግ ከለላ ያስፈልገናል:: የዚህ ፍርድ ቤት አባል መሆን ይገባናል:: የጠበቆች ማህበር፣ የህግ ምሁራን፣ የሴቶች ማህበርና የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኢትዮጵያ የዚህ ፍርድ ቤት አባል እንድትሆን በመንሥስት ላይ የሚችሉትን ያህል ግፊት ማድረግ ይኖርባቸዋል::
The post ኢሕአዴግ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቱን ለምን ይፈራዋል? appeared first on Zehabesha Amharic.