Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

አምባገነኖች ለምን ምርጫ ያካሂዳሉ? –ከአብይ ተክለማርያም

$
0
0

ከአብይ ተክለማርያም (የቀድሞው የአዲስ ነገር ጋዜጠኛ)

በመጪው ግንቦት ወር በኢትዮጵያ ምርጫ ይካሄዳል። በአምባገነን ሥርዐት ውስጥ የሚደረግ ምርጫ ለገዢም ኾነ ለተገዢ ምጥ ነው። “አምባገነኖች ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል እምነት የሚጣልባቸው እንዳልኾኑ እየታወቀ ምርጫ ላይ ለምን ይሟዘዛሉ?” የሚለው እንቆቅልሽ ለብዙዎች ያልተፈታ ጥያቄ ነው። ዐቢይ ተክለማርያም አምባገነኖች ለምን ምርጫ ያካሂዳሉ የሚለውን እንቆቅልሽ ለመፍታት ስምንት መላምቶችን ይዞ ብቅ ብሏል። በመጀመርያው ክፍል እውን እንደሚባለው አምባገነኖች ምርጫ የሚያደርጉት ሌጂትሜሲ ፈልገው ነውን? ሲል ይጠይቃል።
******

abiye

አምባገነኖች ከሚያካሂዱት ምርጫ ጋራ የሚስተካከል ‘የነፍስ ውጪ-ነፍስ ግቢ’ ፖለቲካ ያለ አይመስልም። ዋንጫውን በልቶ “የርግብ አሞራ” ብሎ የሚጨፍረው ቡድን ማንነት ጫዎታው ሳይጀመር የተረጋገጠ ቢኾንም “ለግጥሚያው ሽር ጉዱ” የሚጀመረው ከአንድ ዓመት በፊት ነው። አምባገነኖች ደግሞ ለሥራ ሲነሱ በጠዋቱ አፋቸውን የሚያብሱት ተቺዎቻቸው ላይ በሚያሳርፉት ዱላ ነው። የዞን ዘጠኞችን ዕጣ ፈንታ ልብ ይሏል።

በምርጫ ሰሞን ተቀናቃኞች መደበቅ እንኳን አይቻላቸውም። ከሁለት እና ሦስት ዓመታት በፊት አፉን ወለም ያለው ሳይቀር በጥርጣሬ ይታያል፣ በዐይነ ቁራኛ ይጠበቃል፣ ከዚያ አልፈው ደፈርፈር ያሉት ደግሞ ለልማት ተብለው ከተቆፈሩ የውኃ ጉድጓዶች ፊት ለፊት በተገነቡ የፖለቲካ እስር ቤቶች ውስጥ ይዶላሉ። ሚዲያው የሥርዐቱን ታላቅነት፣ ልማታዊነት፣ አብዮታዊነት፣ ብሔርተኝት እና ከዓለም አንደኛነት በመለፈፍ ሕዝቡን ሁሉ በዲስኩር ስካር ናላው እስኪዞር ድረስ ይግተዋል። ተቃናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰበብ እየተፈለገ ይዘጋሉ፤ ያልተዘጉት ድርጅቶች አባላት “ምነው የእኛም በተዘጋ” እስኪሉ አካልና ነፍሳቸው የስንግ ይያዛል። ይኼን ሁሉ አንቀጥቃጭ ምት ተቋቁመው የአምባገነኑን መንግሥት ሹማምንት ባገኟት ጥቂት አጋጣሚ በድፍረት የሚሞግቱ ደግሞ “ጉድ ነው – ፖሊሲ የላቸውም” እየተባለ ማፌዣ ይኾናሉ- ዓለማቀፍ ኮንሰልታንቶችን ቀጥሮ ፖሊሲ ማስጻፍ ልዩ ሞያ ይመስል፤ ከዚያ በላይ የሠላማዊ ሰልፉ፣ የይውደም መፈክሩ፣ የልብ አፍስስ ቀበሌ ስብሰባው ጋጋታ። ከዚያ በሁዋላ ምርጫው ይደረግና በአብዛኛው በተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች እስር የሚጠናቀቅ አወዛጋቢ ቆጠራ ይቀጥላል። አምባገነኑ ምርጫውን ከ-እስከ (Landslide) አሸነፈ ተብሎ ይለፈፋል፤ “ታላቅ የሕዝብ ሠላማዊ ሰልፍ” ተደርጎ፤ የሚዛትባቸው ተዝቶባቸው በመጪው ምርጫ በድል እንገናኝ ተባብሎ ቅዠቱ ይጠናቀቃል። እፎይ!!

በአምባገነን ሥርዐት ውስጥ የሚኖሩ በርካታ ሰዎች ይህ ለገዢውም ለተገዢውም ሰላም የሚነፍግ ድራማ ለምን እንደሚካሄድ እንቆቅልሽ ይኾንባቸዋል። ምርጫ ሲቃረብ “እባካችሁ ተውን አርፈን እንኑርበት፤ በተበላ ዕቁብ በሰንበት ባትበጠብጡን . . .” የሚሉ አስተያየቶችን መስማት የተለመደ ነው:: ከአሳዛኙ ድራማ በላይ እንቆቅልሽ የሚኾነው የሐሰት ምርጫ የሚያደርጉ አምባገነን ሥርዐቶች ዕድሜያቸው እንደ ማቱሳላ የተንዘላዘለ መኾኑ። ከግርጌ የተቀመጠውን ቻርት በጥሞና ይመልከቱ።

የፓርቲ አምባገነኖች (party dictatorships) ከሌሎች አምባገነኖች የላቀ ዕድሜ አላቸው። ብዙዎቹ ከኻያ ዓመት በላይ የመቆየት ዕድላቸው ከ50 ፐርሰንት በላይ ነው (ይህን ቻርት ስንመለከት ኢሕአዴግ ለ24 ዓመት በሥልጣን ላይ መቆየቱ ሊያስገርመን አይገባም።) የፓርቲ አምባገነንነትን ሥርዐት ከሚከተሉ አገሮች መካከል የምርጫ ድራማን የሚያካሂዱ በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። በርግጥ እነዚህ አምባገነኖች ዕድሜ ጠገብ የመኾናቸው መንስዔ ምርጫ ብቻ አይደለም። ይኹንና የአምባገነን ሥርዐትን የሚመለከቱ ምሁራዊ መጣጥፎች ብናገላብጥ ምርጫ ለዕድሜ ማስረዘሚያ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ እንማራለን። ለምን? የአምባገነንነትን ሥርዐት የሚያጠኑ የፖለቲካ ምሁራን ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ሰንጠረዦችን ቧጠዋል፤ ብዙ ምርምር አድርገዋል፤ የሂሳብ ቀመሮችን ፈጥረዋል። በሰባት ኪሎ መጽሔት የመጀርያው ጽሑፌ ውኃ ያነሳሉ ያልኳቸውን ስምንት መላ ምቶች በርብሬ ለማሳየት እሞክራለሁ። የእነዚህን መላምቶች ጨመቅ እንካችሁ።

1) በአምባገነን ሥርዐት ውስጥ የሚደረጉ ምርጫዎች በቀረቡ ቁጥር ማኅበራዊ ሳይንቲስቶች “ዘ ኤል ዎርድ” የሚሉትን ቃል መስማት የተለመደ ነው። ይህ “ዘ ኤል ዎርድ” የሚወክለው ሌጂትሜሲ የሚለውን ቃል ነው። ቃሉን በሙሉ ስሙ የማይጠሩት እንደ ብዙ የፖለቲካ ጽንሰ ሐሳቦች ግልጽና እቅጩን የኾነ ትንተና ሊሰጠው የሚያስቸግር ቃል በመኾኑ “በሩቁ” እንደሚሉት ለመግለጽ ነው። የሌጂትሜሲ ፍልስፍናዊ ትርጉም እጅግ አወዛጋቢ ቢኾንም ከአምባገነኖች ምርጫ ጋራ በተገናኘ ጥቅም ላይ ሲውል ተግባራዊ ትርጉም ይዞ ነው። በፖለቲካ ምሁራን ዘንድ “የሕዝብ ኀልዮት” ተብሎ የሚጠራ አምባገነኖች የሚያደርጉትን ምርጫና ሌጂትሜሲ በሁለት ዐይነት መንገድ የሚያገናኝ ኀልዮት አለ።
abye tekelemariam

፩) የውስጥ ሌጂትሜሲ፦ ብዙ አምባገነኖች ሥርዐታቸው በጥቂቶች የሚሽከረከር ሳይኾን መደበኛ የአካሄድ ሥነ ሥርዐት የሚከተል እና ሉዓላዊ ተቋማት ያሉት እንደኾነ ማሳየት ይፈልጋሉ። “በሕዝብ በተመረጠ” ፓርላማ ሕጎችንና ደንቦችን ተከትሎ አዋጅ ማውጣታቸው ከዚህ ፍላጎት የመነጨ ነው። ምርጫን ማሸነፍ የሕዝብ ድጋፍና የብቃት ማረጋገጫ ማሳያ እንዲኾንላቸው ይመኛሉ። ይህ ዐይነቱ የውስጥ ሌጂትሜሲ ፍጹማዊ ሌጂትሜሲ ተብሎ ይጠራል። ከዚህ የተለየው ሌላኛው የውስጥ ሌጂትሜሲ ሐሳብ ንጽጽራዊ ሌጂትሜሲ ይባላል። የአፈና እና የጭቆና ተጠቂ የኾኑ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ወቅት በቆርኪ-ተሰፍሮ፣ በስንዝር-ተለክቶ በተሰጣቸው የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ መላወስ ይሳናቸዋል። አምባገነኖች ወደ እነዚህ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጣታቸውን እየቀሰሩ “እርባና ቢስነታቸውን ተመልከቱ” በማለት የተቃዋሚዎችን ሌጂትሜሲ በመዳመጥ በንጽጽር የራሳቸውን ሊያጎሉ ይሞክራሉ።

፪) ውጫዊ ሌጂትሜሲ፦ አምባገነን መንግሥታት የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አካል ለመኾን ከፈለጉ ቢያንስ የይስሙላ ጨዋነት ሊያሳዩ ይገባል። በተለይ እ.ኤ.አ ከ1990ዎቹ መጀመርያ አንስቶ የፖለቲካ ሥርዐቶች ጨዋነት ከሚለካባቸው መስፈርቶች መካከል አንዱ ጊዜውን የጠበቀ ምርጫ ማካሄድ ነው። ለምሳሌ እ.ኤ.አ በ1993 ኢሕአዴግ ባወጣው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዶክመንት (አብዮታዊ ዲሞክራሲ 1 ) የምዕራብ አገሮችን ድጋፍና ርዳታ ለማግኘት ምርጫ ማድረግ ግዴታ እንደኾነ ያስቀምጣል።

ይህ ኀልዮት ምን ያህል ጠንካራ ነው? በማስረጃዎች የተደገፈ ነውን?

አንዲት አሜሪካዊት የፖለቲካ ምሁር ላስታውሳችሁ። ባርባራ ጌዴስ ይባላሉ። በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ ሎስ አንጀለስ የፖለቲካ ሳይንቲስት ናቸው። ከዕድሜያቸው አብዛኛውን ያሳለፉት አምባገነን መንግሥታትን በማጥናት ነው። የሥራዎቻቸው ፋይዳ በፖለቲካ ሳይንቲስቶች ዘንድ ከፍተኛ እውቅናን አስገኝቶላቸዋል። በባርባራ ጌዴስ ጥናትና ምርምር ላይ ተመርኩዘው የተጻፉ ምሁራዊ መጣጥፎች በርካታ ናቸው። ከፕሮፌሰር ጌዴስ አስተዋጽዖዎች መካከል አንዱ ከላይ የጠቀስኩትን ሌጂትሜሲንና የአምባገነን ምርጫን የሚያገናኝ ሕዝባዊ መላምት በማስረጃዎች ላይ ተመርኩዙ አንኮታኩቶ መጣል ነው። ለምሳሌ፦ አምባገነኖች ያላቸውን የሕዝብ ተቀባይነት በጥንቃቄ የሚመረምሩ ጥናቶች፤ ምርጫ ከሚደረግበት ወቅት ይልቅ ምርጫ በሌለበት ጊዜ የበለጠ ተቀባይነት እንዳላቸው ያሳያሉ። የሥርዐቱ ተገዢዎች በምርጫ ሰሞን በሚጦዘው አፈናና ጭቆና እንዲሁም ከምርጫ ጋራ ተያይዞ በሚመጡ ውዝግቦች ምክንያት በሚፈጠረው አለመረጋጋት ምሬት አሰቃይቷቸው ለአምባገነኑ ያላቸው አስተያየት ቢቀንስ የሚያስገርም አይደለም። ይህን ባርባራ ጌዴስ የሌጂትሜሲ ዕዳ (legitimacy cost) ብለው ይጠሩታል። ይህ ሐሳብ ወደ ውጫዊ ሌጂትሜሲም ይሻገራል። በምርጫ ወቅት አምባገነን መንግሥታት ከዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የሚያገኙት ሽፋን ከአዎንታዊነቱ ይልቅ አሉታዊነቱ ያመዝናል። የሰብአዊ መብት ድርጅቶችና ሌሎች ዓለም አቀፍ ሲቪክ ማኅበራትም ምርጫን ተገን አድርገው አምባገነን ሥርዐቶች የሚፈጽሟቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና አፈናዎች የሚያጋልጡ ዳጎስ ያሉ ሪፖርቶች ያወጣሉ። ይህን የሚያሳዩ በይዘት ብጠራ (content analysis) ላይ ያተኮሩ ጥናቶች አሉ። የአምባገነኖች ወዳጅ መንግሥታት ሳይቀሩ በምርጫ ጊዜ የሚከሰቱ አፈናዎችንና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ፈራ ተባ እያሉ ሲያወግዙ ይታያል። በርግጥ እንደ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹና በ2000ዎቹ መጀመርያ ሊበራል ዲሞክራሲ የዓለም ልዑል አይዲዮሎጂ በነበረበት ወቅት እንዲህ ዐይነቱን አሉታዊ ሪፖርቶችና ውግዘቶችን የሚያስከትል ምርጫ አለማካሄድ ይመረጥ ነበር። ይኹንና ከዚያ በኋላና ከዚያ በፊት አምባገነኖች ምርጫ ባለማካሄዳቸው ከሚመጣባቸው ትችት የበለጠ ምርጫ አካሂደው ከምርጫው ጋር ተገናኝቶ በሚነሱ ጉዳዮች የሚከሰትባቸው ውግዘት የበለጠ አሉታዊ ነው። ሌጂትሜሲን የሚሰባብር እንጂ የሚጨምር አይደለም። ታዲያ አምባገነኖች ምርጫ ሲያደርጉ ሌጂትሜሲያቸው የሚቀንስ ከኾነ ለምን አይተውትም?

በጽሑፌ ክፍል ሌሎቹን መላምቶች ይዤ እመለሳለሁ።

ምንጭ 7 ኪሎ ሚድያ

The post አምባገነኖች ለምን ምርጫ ያካሂዳሉ? – ከአብይ ተክለማርያም appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>