Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ጊፍት ሪል እስቴት ወደፊት ወይስ ወደ ኋላ

$
0
0

nlmqi6fn76e6fjt0pj5uአንዳንዴ እንዳለመታደል ነው መሰል በሌሎች ሀገሮች ተብለው ተብለው ያለቀላቸው ነገሮች እኛ ሀገር ሲገቡ ልክ በዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ እንደምንሠራቸው መስለው ቁጭ ይላሉ፡፡ ሌላ ቦታ ተሠርተው፣ ችግሮቻቸው ታውቀው፣ ልምድ ተቀስሞባቸው፣ አዳዲስ አሠራሮችና ቴክኖሎጂዎች ተፈልስፈውላቸው፣ የኖሩ ጥበቦች እኛ ሀገር ሲገቡ የእናታቸው መቀነት ያደናቅፋቸዋል፡፡ እንዲህ እንድል ከሚያደርጉኝ ነገሮች አንዱ ሪል እስቴት ነው፡፡ ከምዕተ ዓመታት በላይ የዘለቀን የቤቶች ግንባታ ዘዴ እኛ ሀገር ገብቶ መከራውን ሲያይ መታዘቤ ነው እንዲህ ያሰኘኝ፡፡ በሰው መሬት ላይ መገንባት፣ ያልተገባ ውል ከቤት ገዥ ጋር መዋዋል፣ ለአካባቢ ጤናና ውበት አለመጨነቅ፣ በጊዜ ገንብቶ አለማስረከብ፣ ገንዘብን ይዞ ከሀገር መጥፋት፣ ቤት እሠራለሁ ብሎ የወሰዱትን መሬት መሸጥ፣ የፍሳሽ ማስወገጃና የውስጥ ለውስጥ መንገድ የሌለው መንደር መገንባት፣ ኧረ ስቱ ይነገራል፡፡

እኔ ጊፍት ሪል እስቴት ከሚባል ድርጅት የዛሬ ሰባት ዓመት ቤት ገዝቻለሁ፡፡ የቤቱን ዋጋ በመቶ በመቶ ከፍያለሁ፡፡ መቶ በመቶ ብትከፍሉ በፍጥነት ይደርስላችኋል ዋጋም ይቀነስላችኋል ተብሎ ስለነበር፡፡ ጽድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ አሉ፡፡ ነገር ግን ይሄው ሰባት ዓመት ሆነው፤ ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም ሆኗል፡፡ የቤቱ መሠረት ከመውጣት ያለፈ ነገር ጠብ ሊል አልቻለም፡፡ በተደጋጋሚ ከዋና ባለቤቱና ሥራ አስኪያጁ ጋር ተነጋግረናል፣ ከአራት ጊዜ በላይ ተጻጽፈናል፡፡ ውጤት ግን አላመጣም፡፡

ጊፍት ከደንበኞቹ ጋር ውል ሲፈርም በአሥራ ስምንት ወራት ገንብቶ ሊያስረክብ ነበር ግዴታ የገባው፡; እኔ እስከማውቀው ድረስ ግን ከሦስት ዓመት በፊት ገንብቶ ያስረከበው ቤት የለም፡፡ ገንብቶ ያስረከባቸው ቤቶች ቢሆኑም አምስት ችግሮች አሉባቸው፡፡ የመጀመሪያው የባለቤትነት ማረጋገጫ የላቸውም፡፡ ጊፍት ሪል እስቴት ስሙ እንዲነሣበት ከማይፈልጋቸው ነገሮች አንዱ የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ ነው፡፡  የአዲስ አበባ መስተዳድር እንኳን ሕገ ወጥ ይዞታዎችን ሕጋዊ ለማድረግና ካርታ ለመስጠት በተዘጋጀበት በዚህ ዘመን ጊፍት ግን ቤት ላስረከባቸው ሕጋዊ ገዥዎች እንኳን የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተሩን ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለም፡፡ ሲጠየቅም የየካ ክፍለ ከተማና የአዲስ አበባ መስተዳድር ካርታውን እንደያዙበትና ለማስለቀቅ እየታገለ መሆኑን ነው የሚናገረው፡፡ ምንጊዜም የሚያመካኘው በመስተዳድሩ ነው፡፡

ሁለተኛው ችግራቸው መንገድ ነው፡፡ ወደ ጊፍት ሪል እስቴት የሚወስደው መንገድ በሁለት ችግሮች ምክንያት አልተሠራም፡፡ አንደኛው ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በተፈጠረ ግጭት ሲሆን ሌላው በሪል እስቴቱ ድክመት፡፡ ድርጅቱ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር አይጥና ድመት ሆኖ  ነው የሚኖረው፡፡ ለዚህ አንደኛው ምክንያት ደግሞ ችግሮችን በሰላማዊ ውይይት ከመፍታት ይልቅ ማስፈራራትን ስለሚመርጥ ነው፡፡ የክፍለ ከተማው ባለሥልጣናት ባሉበት ችግሩን ለመፍታት የተጠራውን ስብሰባ የጊፍት ኃላፊዎች ባለመገኘታቸው ነው ውጤት አልባ የሆነው፡፡ የድርጅቱ መኪኖችም ሆኑ ነዋሪዎቹ ከዋናው አስፓልት ወደ ግቢው ለመግባት የሚጠቀሙበትና ‹መሪ ቁጥር አንድ› የሚባለው መንገድ ጊፍት ሪል እስቴት የሚደርስበትን መዋጮ ባለመክፈሉ ከሁሉም የአካባቢው መንገዶች ተለይቶ እስካሁን አልተሠራም፡፡ አስፓልት ይሆናል የተባለው መንገድ ኮብል ስቶን እንደናፈቀው ቀርቷል፡፡ የወረዳው መስተዳድር ችግሮቹን ለመፍታት ያደረገው ጥረትም በድርጅቱ እምቢ ባይነት ከሽፏል፡፡ ክፍለ ከተማውም ከዐቅሜ በላይ ነው ብሏል፡፡ ነዋሪዎቹ ግን ይሰቃያሉ፡፡

በሪል እስቴቱ ግቢ ውስጥ መንገድ የለም ማለት ይቻላል፡፡ በተፈጥሮው ሜዳ የሆነ ነገር እንጂ ሆነ ተብሎ የተሠራ መንገድ የለም፡፡ ከቤት ገዥዎቹ ጋር በገባው ውል መሠረት ግን የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ሠርቶ የማስረከብ ግዴታ ነበረበት፡፡ በግቢው ውስጥ ያሉ ኃላፊዎች ድርጅቱ ገንዘብ ስለሌለው ሊሠራው እንደማይችል ይነግሩናል፡፡ ዘወትር የሚሰጡት ምክንያት የነዳጅ ብር ስለጠፋ፣ መካኒኩ ደመወዝ ስላልተከፈለው፣ የሠራተኞች ደመወዝ ስላልደረሰ፣ መኪናው ተበላሽቶ የመለዋወጫ መግዣ ስለሌለ የሚል ነው፡፡ ያ ግን ሕጋዊ ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡ ወይ ባልዘፈንሽ እንደሚባለው አሁን መሐል መንገድ ላይ ዐቅም የለኝም ከማለት መዘጋጀት አስቀድሞ ነበር፡፡ ዝናብ ጣል ካደረገ ጊፍት ግቢ ውስጥ በቦቴ ጫማ እንኳን ለመግባት ከባድ ነው፡፡ መግባት የሚቻለው በሄሊኮፕተር ብቻ ነው፡፡ ለዚያውም ማረፊያ ከተገኘ፡፡

ሦስተኛው ችግር ውኃ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪ ወር ሙሉ ውኃ ጠፋብኝ ብሎ ያማርራል፡፡ ጊፍት ግቢ ውስጥ ግን ላለፉት ሰባት ዓመታት ውኃ የለም፡፡  ውኃ በአህያ እያሸከሙ ቤት የሚሠሩ የሪል እስቴት ባለቤቶች ያሉት ጊፍት ግቢ ነው፡፡ ውኃ የሌላቸው የአራት ሚሊዮን ብር ቤት ሠሪዎች ያሉት ጊፍት ግቢ ነው፡፡ አንዳንዶች ከአካባቢው በጀሪካል እየገዙ፣ ሌሎች በቦቴ እያስመጡ፣ ሌሎች ደግሞ በአህያ እያጓጓዙ ነው ኑሮን የሚገፉት፡፡ ውኃ የሌለው ብቸኛው የሀገራችን ሪል እስቴት ነው ጊፍት፡፡ በዚህ አያበቃም አራተኛ ችግርም አለ፡፡ ጊፍት ውስጥ መብራት የለም፡፡ ለነዋሪዎቹ የታደለቺው መብራት የፍሪጅ መብራት ናት፡፡ ቤቱ ውስጥ መብራት መኖሩን ከመናገር ያለፈ ሌላ ትርጉም የሌላት፡፡ ሰሞኑን የሚደረገውን የምርጫ ክርክር በቴሌቭዥን የማያዩ ነዋሪዎች ያሉት ጊፍት ግቢ ነው፡፡ የኤሌክትሪኩ ኃይል ቴሌ ቭዥን አያንቀሳቅስም፡፡ እንጀራ መጋገርና ስቶቭ መጠቀምማ ጎረቤት ላለው ሥላሴ ተሥለውም አያገኙት፡፡ እንደ ራሽን ጊፍት አንድ ቆጣሪ ለስድስትና ለሰባት አከፋፍሏቸዋል፡፡  አምስተኛው ችግር ደግሞ የፍሳሽ ማስወገጃው ነው፡፡ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በተፈጠረ ግጭት የግቢው የፍሳሽ ማስወገጃ አልተሠራም፡፡ ማጠራቀሚያ ተብሎ ግቢው ውስጥ የተሠራው ዋና ጉድጓድም ከመፋሰሻው ጋር አልተገናኘም፡፡ ለዚያውም የሰዎች ቤት በር ላይ የተሠራ አስገራሚ ዲዛይን ያለው የማጠራቀሚያ ጉድጓድ ነው፡፡

እነዚህን ችግሮች እንዲፈታ፣ መንደሩን ወደ መኖሪያነት እንዲቀይር ድርጅቱ በተደጋጋሚ በደንበኞቹ ተነግሮታል፡፡ የመፍትሔ አቅጣጫዎቹ ግን አስደናቂ ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሐሰት ቃል ይሰጣሉ፡፡ የዛሬ ወር፣ የዛሬ ሳምት፣ ከሦስት ወር በኋላ ያልቃል ይላሉ፡፡ ለእነርሱ ሳምንትም፣ ወርም፣ እኩል ናቸው፡፡ አንሠራም ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አብዛኞቹ ገዥዎች ውጭ ሀገር ስላሉ ለጊዜው ጩኸው ይሄዳሉ ብለው ያምናሉ፡፤ ስለዚህም ቢሯቸውን ዘግተው ይጠፋሉ፡፡ የሉም፣ ስብሰባ ላይ ናቸው፣ ውጭ ሀገር ሄደዋል የጸሐፊዎቹ መልሶች ናቸው፡፡ ከዚህ የባሰ ከመጣ ደግሞ በክፍለ ከተማውና በከተማው መስተዳድር ያመካኛሉ፡፡ ክፍለ ከተማው አስቸገረን፣ መስተዳድሩ የኛን ጥያቄ አይመልስም፣ ወዘተ የተለመዱ ማመካኛዎች ናቸው፡፡

እንዲህ እየሆነ ግን እስከ መቼ መጓዝ ይቻላል? ባፉት ሰባት ዓመታት ከሰባት በላይ የሥራ ኃላፊዎች ተቀያይረዋል፤መፍትሔ ግን አልመጣም፡፡ እንደ ከበደ ሚካኤል ግጥም የሰማው ሲሄድ ያልሰማው ይመጣል፡፡ ድርጅቱ ኮርፖሬት ኃላፊነቴን እየተወጣሁ ነው ብሎ ለቀይ መስቀል ቤት ሲሰጥ መስቀል አደባባይ ላይ ቢል ቦርድ ለጥፏል፡፡ የኛን ቤት ግን እስካሁን አላስረከበም፡፡ አሁንም በዓል በመጣ ቁጥር ቤት አስረክበናል፣ ሌሎቻችሁ ግዙ ይላል፡፡ በሚገባ ያስረከበው ቤት ግን የለም፡፡ ይኼ ሁኔታ የሚያዛልቅ አይመስለኝም፡፡

  1. ድርጅቱ ዐቅም ከሌለውና ቃሉን የማያሟላ ከሆነ የውሸት ቃል በየጊዜው ከሚገባ ቁርጡን ይንገረን
  2. የሚመካኝባቸው የመንግሥት አካላትም ጠርተው ይጠይቁት
  3. ቃሉን እንዳላሟላ እያወቁ አሁንም ሌሎች ደንበኞችን የሚሸነግሉ አስተዋዋቂ ድርጅቶችም የሞራል ኃላፊነታቸውን ይወጡ
  4. ቤት ገዥዎችም ከመንገብገብና ቢሮ እየሄዱ ከመጨቃጨቅ ይልቅ እንደ አክሰስና በርታ ቤት ገዥዎች ተደራጅተው የጋራ መፍትሔ ይስጡ

 

 

 

 

The post ጊፍት ሪል እስቴት ወደፊት ወይስ ወደ ኋላ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>