Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

እኔ ማን ነኝ? –ከሥርጉተ ሥላሴ

$
0
0

28.03.2014 /ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ/

„ቤት በጥበብ ይሠራል። በማስተዋል ይጸናል“ መጸሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ 24 ቁጥር 3“

ከሥርጉተ ሥላሴ 02.023.2014 (ሲዊዘርላንድ - ዙሪክ)

ከሥርጉተ ሥላሴ 02.023.2014 (ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ)

እንዴት ናችሁ ክብረቶቼ አንዲት በትርጉም የምትቃና ነገርን አንስቼ ወደ ጉዳዬ አመራለሁኝ። “ያልመከተ ተፈነከተ፤ ያልተደራጀ ተፈጀ። – በተከበሩ ፀሐፊ ጌታቸው ኃይሌ በ25.03.2015 ከተፃፈው ልትቃና የሚጋብትን ብቻ ላንሳ  … “ አማራ ነን” የሚሉ ሰዎች አሉ። “አማራ አይደላችሁም” ብንላቸው ግራ ይጋቡና፥ “ታዲያ ምን ልታደርጉን ነው፤ ዶርዜ፥ ወይስ እስላም?” ብለው ሊጠይቁ ይችላሉ። ዬክቡር ጸሐፊ ጌታቸው ኃይሌ አገላለፃቸው እኔን እንደገባኝ የአማራ ብሄረሰብ አባላት የት ልትመድቡን ነው? ከዬትኛው ብሄረሰብ ወይንም ነገድ ልታዳብሉን ነው? ለማለት እንጂ ከዬትኛውም ብሄረሰብ እስልምና ሃይማኖት እምነት ተከታይ ወገን የለንም ለማለት አይመስለኝም። የጸሑፉ ጭብጥ ያለፈውና የአሁን ስታያይዙት መንፈሱ በዚህ ፍሰት የሚሄድ ቅንነት – ጠገብ ዝንባሌ ነው፤ እንጂ እስልምና ተከታይ አማራ ወገን የለንም ለማለትም ወይንም ሃይማኖቱንም እንደ አንድ ብሄረሰብ መለያ አድርጎ ለማግለል ወይንም ነውር ሆኖ አይደለም። በዬትኛውም ብሄረሰብ እስልምና የሚከተል ኢትዮጵያዊ ወገን አለን። ስለዚህም የኔዎቹ የእስልምና እምነት ተከታዮች ደሞቼ እንዳይከፋችሁ በዚህ የተቃና ትርጉም ውሰዱት። ኢትዮጵያዊነትን የፈካ ውህድና ውብ የሚያደርገውም ይህን መሰሉ ጌጣማ ፍልቅ ዓምዳዊ ጭብጥ በወጥነት መግለጹ ነው። እንደሚታወቀው ፍጥጥ ያሉ ጭብጦች እያሉ አማራ በነገዱ መጠራቱ ብቻ ሳይሆን ጭራሽም ባለቤትም አድራሻም የሌለው ተደርጎ የመታዬት ዝንባሌ እጅግ ጎልቶ ይታያል። ውለታውንም ገደል። ይህ የታሪክም ራስን የመጋጥም ዝበት ነው። ለዛውም በግራ ቀኝ የቁርሾ ማወራረጃ ሆኖ እዬተፈጨ።

“አማራ” ለማለትም የሚጨንቃቸው ወገኖቼ እንዳሉ በግሌ ተገንዝቤያለሁ። ስለሆነም ነው የመፍትሄ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን እውቅና የማስገኘት ተጨማሪ ሃሳብ ይዘው የቀረቡት። ኢትዮጵያዊነት ሁሉንም ቀለማም መለያዎች ያቀፈና የተዋበ ስለሆነ ለእኔ በግሌ የሚቀለኝ ብቻ ሳይሆን፤ ክብርና ሞገስ የሚሰማኝ ኢትዮጵያዊ ነኝ ስል ብቻ ነው – ለሥርጉተ፤ እንጂ የሚመክት ጉልበታም አቅም ያለው አመክንዮ በማቅረብ ኩሰት ዝንባሌዎችን ሁሉ መግራት መሞረድና መልጋት እንዲሁም ቀጥ አድርጎ ማቆም ይቻላል። መኖር ብቻ ሳይሆን ቀለማም ሁለንታናዊነቱ በሁሉም መስክ አንቱ ነውና። ወያኔ በጥብቆ ውስጥ ተገብቶ መቀርቀር ካለ ታላቁ ዓርማ ኢትዮጵያዊነት ይደብዝዛል፤ ስለሆነም ይህን አብዝቶ ይህን ይሻዋል። ተከታዮችም “ለምን ወጥተው እኛ አማረ ነን አይሉም” ሲሉ ተዘውትረው ይደመጣሉ። መልሱ የበታችነት ስለማይስማው ብቻ ነው። ምን አጥቶ ብድር ይሂድ?! ሌላው በሌላ ክንፍ ያለው ወገን ደግሞ አማራ ምን እንዳለው፤ ምን እንደሚችልና ምን እንደሚፈለግ ዘመን ጠገብ አቅሙን ስለሚያውቁ – ይፈሩታል። ስለዚህም እንዳልተፈጠረ አድርገውም ተረት ይናገራሉ። ወይም ጸጉራቸው ሲቆም ይታያል። ልባቸው ግን ያውቀዋል። ማገርነቱን ባላና ወጋግራነቱን – ረቂቃዊ ጥልቅ መንፈሱን። ነፍሱ ከኢትዮጵያዊነት ጋር የተዋህደ ሰለሆነ ብቻ ሳይሆን ሥልጡኑ ሰብዕናው ጎጥ ላይ ኋላቀርነትን ፍለጋ አይማስንም። የጠራ መስመሩ ኢትዮጵያዊነት ነው።

አሁን ወደ ጉዳዬ „እኔነትን“ የሚገልጸው ሰብዕና ወይንስ ሥም? እንደ ሥርጉተ —- እኔነትን የሚናገረው ውስጥን የማዬት አቅምና ክህሎትን ነው። አቅምና ክህሎት ሊመሳሰሉ ሊወራረሱ ይችላሉም ባይ ነኝ። ክህሎት የአቅም ክምችት ሂደት ሲሆን አቅም ደግሞ ክህሎትን ለመፍጠር፤ ወይንም ክህሎትን ለመወለድ የብቃት የውይይት እርገት ማሳረጊያ ይሆናል።

„እኔ ማን ነኝ?“ ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት መቻል በራሱ ትልቅ እርምጃ ነው ብዬ አምናለሁ። „እኔ ማን ነኝ?“ ለሚለው መላሹ „ሥም“ ሊሆን ከቶ ይችላልን? „ሥም“ ተለይቶ መጠሪያ እንጂ የውስጥ ጌጣማ፣ ውበታዊ ሰብዕና አብሳሪ ሊሆን አይችልም እላለሁ። በዛ ሥም ብዙ ሰዎች ይጠራሉና።

ስለሆነም አመልካች ወይንም አቅጣጫ ጠቋሚ ፍሬ ዘር መልክና ቁመና፤ አካላዊ ማንነት ከሚገልጸው ትርጉም አንጻር ሳይሆን ከመንፈስ ፈሎች የእርባታ አጸዳዊ ችሎታ፤ ከሥራ ፍቅር አስተሳሰብ ትንፋሻዊ ጠባይና ውስጣዊ ሰብዕናን ከሚጠይቀው ሥነ ምግባር ጥልቅ – ሰብዕዊነት ማህጸን ይነሳል። በሥራ – በፍቅር – በትዳር እንዲሁም በውስጣዊ ህይወት የውስጠት ሃዲዶች የከተሙ ከዬአቅጣጫው የሚነሱ አምክኖያዊ ጭብጦች „እኔን“ ይተርጉማሉ – ያብራራሉ።

„እኔ ማን ነኝ?“ ለሚለው በኽረ ጥያቄ እራስን ሳያታልሉ ይህን „እኔ ማን ነኝ?“ የመመለስ አቅም – ቁርጠኝነት – መወሰን የመቻል ብቃት ነው። ስለምን? ምላሹ በቀጥታ የፈተናን ድብቅነት ተጋፍቶ ወይንም ረግጦ „እኔን“ ይገልፃልና። ይህን መሰል ወደ ውሰጥ የማዬት እና ውስጣዊ ህይወትን በትኖ ዘርዝሮ በመንፈስ ሰሌዳ ደፍሮ የመገምገም አንጡራ ተግባር መንገዱ የሰላ ነውና፤ የመተርጎም ማዕከል ነው። እዬተዘወተር መንጠር ይኖርበታል። እንደ አጉልቶ የሚሳይ መነጸር ወይንም የሩቁን አቅርቦ እንደ የሚሳይ መሳሪያ ነውና። መፍትሄም!

ስለሆነም ከሚገበዬው እውቀትና ልምድ አኳያ እራስን ፈተና ውስጥ አስቀምጦ መለካት ንጹህ አዬር ሊሆንም ይገባል። ስበቱ ውጪያዊ አዬሩን ሆነ ውስጣዊ ትንፋሹን በማመዛዘን መልክ አስይዞ ሚዛኑን ይጠበቅለታል። ማህበራዊ እውነታዎች የሚፈቅዱትን በባህላዊ ውስጠዊ ሰብዕናን ደረጃ – በደረጃ በመቅረጽ፤ በማሻሻልና የተረጋጋ ውስጣዊ ህይወትን በሰላም ገነት ላይ ባለጉልት ያደርጋል ።

የኑሮው ዘዴ መነሻ ትልሙ ይሁን መድረሻ ግቡ „እኔ ማን ነኝ“ የሚለው ይሆናል። „እኔ“ ማን መሆኑን ካወቀ ከሌላው „እኔ“ ጋር በሰመረ ሰረገላ አብሮ ፍቅር የሚጠይቀውን ተፈጥሯዊ አዎንታዊ ሥነ ምግባር በቀናነት ለመፈጸም ንቁ ወታደር ይሆናል። ለመቅዘፍም „አልጋ ባልጋ ነው መንገዱ አንተን አምነው ሲሄዱ“  ይሆናል። የምር። በእኔ ላይ ሽወዳ እውር ስለመሆኑ ይህ እርምጃ „እኛ“  የሚለውን ቀይሮ „የእኔ“ „በእኔ“ ውስጥ ሁሉንም ሳይቆጠብ የሚለገሰው ገደብ የለሽ ባለመብቱ ዐፄ ፍቅር ይሆናል ማለት ነው። „እኔ ማን ነኝ ?“ እራስን አምጦ የወለደ „የእኔ“ እርካባዊ ሂደት ነው። የውበት አካል የውስጥ አብነት የእኔ ነው። ድርሻውን አስጠግቶ ቤተኛ ማድረግ።

ማለት „እኔን“ „እኔ“ ይወልደዋል። ሂደቱ በስበትና በግጭት ማህል፤ ቢያስፈልግም በጥሰት ውስጥን አውጥቶ ካለይሉኝታ ለተፈቀደለት „እኔ“ በግልጽነት መገበር ይሆናል። እርግጥ ስቃይ አለው – ፈታኝ ነው። ውጤቱ ግን ሰውኛ ጠረን ያለው ስለሚሆን የፍቅርን የአዬር ቧንቧ ከፍቶ ፍሰቱ በተስተካከለ ዝውውር እርካታን ማፍታትን ይተውናል።

መቸቱ ሆነ ገቢሩ ጊዜ የማይገደብለት፤ ደንበር አልበሾ በመሆን ነፃነቱ ሊታወጅለት ይገባል። ነፃነቱን የተቀማ ፍቅር ባይፈጠር ይሻለዋል። ከሁሉም ነገር በላይ ፍቅር በአንክሮ የሚጠይቀው ነገር ልቅ የሆነ የተፈጥሮ ውበቱን የማይጋፋት ንጹህ ነፃነትን ነው። ይህን ብቻ ፍቅር „ከእኔ“ ይፈልጋል። የዚህ ድርጊት ባለሟል ምላሹ „እኔ ማን ነኝ?“ ለሚለው የደፈረ ባለወኔ ብቻ አቅም ይኖረዋል።

ፍቅር ማለት ለሥርጉተ አንድ የላቀ የሙያ ዘርፍ ነው። የተፈጥሮ ባለጸጋ ዲታ የሆነ አለቃ ሩህሩህና ደግ ሙያ ነው። ፍቅር መንፈስ ነው – ቅዱስ።  በሰው እጅ ተንቦልቡሎ ያልተሰራ በደም የቀለመ፤ ፈልቆ የሚያፈልቅ የቀን ተሌት ብርሃን ነው። ዳመና፤ ጉም፤ ጨለማን የሚጥስ ጀግና! ተወዶ የሚያስወድድ፤ ተከብሮ የሚያስከብር – ዐፄ ነው። የፍቅር ባለ ሙያ ማለት መስዋዕትነት ፈቅዶ ሴሉን የገበረ ወይንም የሰጠ፤ እራሱን ያልሸጠ ወይንም ማንነቱን ያልተዋሰ፤ ተፈቅዶና ተወዶ ከውስጥነት በሐሤት የሚቀበሉት የመንፈስ አራሽ – የጸጋዎች ሁሉ እናት ነው – ዓፄ ፍቅር።

እርግጥ ነው ትናንት የአንድ ህብረተሰብ ሞራላዊ ጭብጥ አለ። ይህ ጭብጥ ግን ባለበት ቆሞ አይጠብቅም። ትናንት ያልነበሩ እውነታዎች ዘመን ይፈጥራቸዋል። ወይንም ተከድነው የኖሩትን ዘመን ይገልጣቸዋል – ክንብንባቸውን ያነሳል። አዳዲስ ሥነ ምግባራዊ ጭብጦች „እኔን“ በዬፌርማታው ያፋጥጣል። ስለዚህ የሰው ልጅ ሁልጊዜ ቦታውን ሞልቶ ሳይሆን አዳዲሶችን አዎንታዊ ቀንበጥ ዕሳቤዎችን፤ ዝንባሌዎችንና ዘዴዎችን ሊያዋህድ የሚችል የእንግዳ መቀበያ ክፍል በህሊናው በቋሚነት ሊኖረው ይገባል። (reserved class) ዓለምም ማድረግ ያለባት ይህኑኑ ነው። እርግጥ ልማዳዊ ደንብ በተለይ በረጅም ጊዜ የሚፈጠርና የሚዳብር እንደመሆኑ፤ ይህን በቆይታ ቤቱን የገነባ ደንብ ከአዲሱ ቁሳዊና መንፈሳዊ ባህል ጋር ጎልብቶ በህብርተሰቡ ዘንድ ሥር እስኪሰድ ድረስ ጊዜን ሆነ ትእግስትን ይሻል። በተለይ በማለቅ ላይ ባሉ አሮጌ ልማዶች በሚወገዙበትና በአንጻሩም ደግሞ አዲሱ ሞራሊቲ ገና ለጋ እድገት ዘገባ ላይ እያለ ድብልቅ ቅይጥ ስሜቶች ፈልተው እስኪሰክኑ ድረስ ማስተዋልን ትእግስትን በአጽህኖት ይጠይቃል።

የሽግግር ወቅቱ እንዳለ የሚቀጥሉትና አዲሶችን የሚዋህዱበት አዲስ ምዕራፍ ለመቀበል የሚያንቁ ገመዶች ሁሉ በስክነት መልክ መያዝ አለባቸው። ልዕልት ኢትዮጵያ ሀገራችን በተፃፈ ህግ እንደሚተዳደሩት ሀገሮች በተጻፈ ህግ፤ እንዲሁም ባልተፃፈ ህግ እንደሚተዳደሩት ሀገሮች ባልተፃፈ ህግ በጣምራ ህግ ትተዳደራለች። ይህ የእኔ  ዕይታ ነው። ጭብጦችንም የማቅረብ አቅም አለኝ። እርግጥ ዬህግ ባለሙያዎች ላይስማሙበት ይችላሉ:። እኔ እንደማስበው ግን ከተጸፈው ህግ ይልቅ ያልተጻፈው ህጋችን የበለጠ ተከባሪ፤ አጓጕ፤ ተወዳጅ፣ ስኬታማ፣ ተፈጻሚነት ሆነ ጉልበትም አለው ባይም ነኝ። ስለምን? ቀመሩ በፈቃደ ህዝብ ስለ ሰከነ።

ስለሆነም ሂደቱ በኃይል ሳይሆን መንፈስን አለስልሶና አዋዝቶ መሆን አለበት። የሆነ ሆኖ በሽግግር ወቅት በብዙ ሰዎች ውስጣዊ ሰብዕና መሰረታዊ ማህበራዊ ልማዶች ጊዚያቸውን ጠብቅው እዬተዳከሙ ሲሄዱ፤ የቀደመውን አንለቅም በሚሉ ደግሞ አዲሶቹን የሚቀጭጭ ውስጣዊ ግፊት ሊያነግሡ ይችላሉ። አጠቃላይ ሰብዕና ለመሆን በመፈለግና -በመሆን፤ በማለትና – በማደረግ፤ በማቀድና – በመገኘት መካከል ትልቅ የልዩነት ግንብ አለ። ውስጣዊ ሰብዕናን ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት ፍሪያማ የሚሆነው ከውስጣዊ አካላዊ እና ውጪያዊ እውነታዊ ዛቢያ አኳያ የተመጣጠነ የግንዛቤ ለውጥ ማምጣት ሲቻል ብቻ ነው። ስለዚህ እኔ ዛሬ የጀመርኩት ያልተለመደ ደፋር እርምጃ እንደ መነሻነት ተወስዶ በመሆን ሰቅ ተማክሎ ማዳበር ይቻላል። እርግጥ በዚህ ሃሳብ ዙሪያ የሚጠብቁኝ ጠብሰቅ ያሉ ጉልበታም ትችቶችና ፈለጣ እንደሚኖሩ አስባለሁ። ለመሸከም ስለተሰናዳሁ እቅሜ ሙሉዑ ነው።

ወደድንም ጠላንም ይህ ዬግሎባላይዜሽን አዲስ ዓለም በማህበራዊ ሚዲያ ያመጣው መጠነ ሰፊ ፈጣን የዛሬ ለውጥ ብቻ ሳይሆን ከዛሬው ባደገና በጎለመሰ መልኩ አዲስ ግኝቶች ዳብረው ተሻሽለው ነገ ይፈልቃሉ። ፍቅርንም ሰብዕዊነትንም፤ እንደ ሰው የመሆን ሚስጢርም ከዘመኑ ጋር ይመነደጋሉ። ስለዚህ ለዘመኑ መመቸት ግድ ይላል። ፍቅር የተጠረገ ልብን አብዝቶ ይሻል። ቅይጥ ፍላጎት፤ ታችና ላይ የሚዘል ተራጋጭ ስሜት፤ የዘበጠ ፍላጎት ቁርሾ ተከል ዝንባሌዎች ወንዝ አያሻግርም። ከመብቀሉ በፊት ይፈልሳል – ክው!

ይህን ማዳን የትውልዱ ዕጣ ነው። በቆዬው ባህል ጸንቶ መቆም መልካም ቢሆንም፤ ከዘመን ጋር ግጭት መፍጠር ደግሞ አዳጋው ሰፊ ነው። የተቆጣጠረ ክር ካልተፍታታ ጥቅም አይሰጥም። ጤነኛ የውስጥነት ዓይን ዘመኑን በአጽህኖት ይጠይቃል። ልደግመው አሁንም ሰብዕዊነት፤ እንደ ሰው ማሰብ፤ የሰው ልጅ ለተፈጥሮ የሚሰጠው አክብሮት በፍቅር ፍልስፍና ማደግ አለበት። እድሜ ሲጨምር አዕምሮም ከጣሪያም ከግድግዳውም ማደግና መዳበር ብቻ ሳይሆን  ለም ሆኖ ለስልሶ መጠበቅ ይኖርበታል (fertility)። ሁልጊዜም የሰው ልጅ ለፍቅር ተሸናፊ መሆን አለበት። ለሚወደው ነገር፤ ሥነ ምግባር የማይገዛ በሰው ደረጃ ለማዬት ዳገት ነው። ፍቅር የነጠረ የመኖር ሚስጥር ነውö እርግጥ አለም በቅቡ ነው የሚነጉደው። ግን ጸጋውን አውጥቶ ተጠቃሚ ለመሆን ድምጹን አጉልቶ ማውጣት ያስፈልጋል። ስለ ፍቅር ለሰው ልጅ ከተሰጠው ዕምቅ ሃብት፤ ምንም እንኳን ጥናታዊ መረጃ ማደረግ የሚስችል ሁኔታ ላይ ባልሆንም አንድ አስረኛውን እንኳን አልተጠቀምንበትም። ለዚህ ነው ዓለምና ተስፋዋ እንዲህ እንዳመጠ ተንበርክኮ – የሚታዬው። በአብዛኛው የሚታዬው ፍቅር በተቃራኒ ፆታ ቅንጣት ጉዳይ ወይንም በትናንሽ ግንኙነቶች ዙሪያ ብቻ ነው። ነገር ግን የተፈጥሮ ጭንቅላት ፍቅር ነው።

ስቃዩ ሙቀትን፤ ጭንቀቱ ምህረትን እንዲያድል፤ የፈላ ሰዋዊ ስዋሰዋዊ ትንፋሽ ጠገብ ፍላሎትን እንደ አሻው ማስመቸት ያስፈልጋል። የነፍስን ጨዋታ የምላሻ ጨዋታውን አጉልቶ መግለጥ ይጠይቃል። ፈጣሪ አምላክ የሰጠው የማይገሰስ የውሰጥ ሰላም ተጠቃሚ መሆን ያለመቻላችንም መሰረታዊ ምክንያትም ይህን የመተግበር ክህሎታችን ጠባብ በመሆኑ ይመስለኛል።

የፍቅር ረቂቅነት ልቡን እስከሚያገኙት ድርስ ነው። ምቱን እስኪለኩት ድረስ ነው። በቁጥጥር ሥር እስኪያውሉት ድረስ ነው እንጂ እንደ ፍቅር ለማዳ ቤተኛ እንሰሳ የለም! አዳኝም የምህረት ሐዋርያም። ግን ደፋር ካገኘ ነው፤፡

… ከዚህ በኋላ ቀያሹ እሱ እራሱ ይሆናል። ዋናው የውስጥ ወጥነትን ከጥቃት ለማዳን ለፍቅር ውስጥን በሚገባ መዘርዘር አስፈላጊና መሰረታዊ  ከመሆኑ ላይ ነው። ሁልጊዜም መድገም መሰለስ መመላለስ፣ መለማማድ – መለማመድ ቅንብሩን መከተል ቃናውን ማዋሃድ በአጽህኖት ያስፈልጋል። ጥገና ለሚያስፈልጋቸው የቃና መሳሪያዎቹም ጥንቃቄ፣ ፍጥነትና አድማጭነት ቀልቡ ናቸው። መዘግዬት ግን ዳጥ ነው።

ይህን ለማድረግ ከማንምና ከምንም ስደት ያልጠዬቀውን ንጹሁን „እኔን“ ሳይታክቱ ፈልጎ ማግኘት የመፍትሄው ቁልፍ ነው። ስለዚህም ዘመኑ እራሱ እዬዳጠው ዬሚሄደው ትብትብ አፍታቶ፤ በተፍታታ አቀራረብ — በተብራራ ገለጻ፤ ደረጃውን በጠበቀ የአዬር ሁኔታ ተፈጥሮውን ማድነቅ፤ ማክበር ፋኑስ መሆን ያስፈልጋል። አጉል አቅጣጫ ይዞ አጉል ቦታ ከሚቀረቀር ሰባራ ጎማ፤ ፍቅርን አድኖ ዘመናዊነትን ማስታጠቅ በእጅጉ ያስፈልጋል። እያዋዙ ባህልን – ወግን – ልማድን የዕምነት ዶግማዎችን ሳይጋፉ ጭንቅላቱን ፍቅርን በጠረጴዛ ዙሪያ ማወያዬቱ እጅግ ሥልጡነነት ነው። እንዲያውም ዘግይተናል።

„እኔ“ „እኔን“ ስሰጥለት ቁምነገሩ ለማደግደግ ለመገዛት መሆን አለበት። በልግስና በድርጊት መንቆጥቆጥ አለበት – ፍቅር። ሁለቱ „እኔዎች“ በመንፈስ በድርጊት አኃቲነትን የሚፈጥሩት ሰው – ሰው የሚሸተውን ሰውኛ ጠረን ውስጣቸው ሲያደርጉ ብቻ ነው። ተስፋ ካለተዕቅቦ ሲዋኝ። ዋና የፈለገ ፍቅርን ይዞ ወንዝ ይውረድ ፍቅር ጥሩ የዋና መምህር ነው። ፍቅር ቀለሙ አዲስ ነው። አዲስ ቀለም ይናፍቀን …. ፈቃድ …..

ትልም ምርት – ምርት ግብዕት፤ እርገት – ስክነት፤ – ስክነት ውበት -፤ ውበት ሁነት፤- ሁነት ትፍስት ይሆን ዘንድ የሰማነውን በልቦናችን ያሳድር፤ የኔዎቹ ብርቅ የሐገሬ ልጆች ውድ – አንባቢያን በአብሮነት ቆዬን ሳትሳሱ ፍቅርን በፍቅር አትኩሮት ጠልፋችሁ ሁሉን ሰጣችሁኝ።  ልግስናችሁ እንሆ ቁሞ አስተማረኝ። ስለሆነም እኔ ሎሌያችሁ – ውስጤን በንጽህና ሰጠኋችሁ። ውለታ ሳላጓድል ወይንም ሰላንጋልል በቅንነት – አከበርኳችሁ። የመንፈሴ ጌጥ አድርጌም በመንፈሴ ማህጸን  እንሆ አተምኳችሁ! ኑሩልኝ!  ዘሃበሻ ጌጦቼ – ኑሩልኝ። እግዚአብሄር ይስጥልኝ። በድጋሚ በፍቅር ለጥ ብዬ ሰግጄ – ተሰናበትኩ። መልካም የማስተዋል – የመደማመጥ ክብራዊ ጊዜም ተመኘሁ።

  • ዕይታ በትህትና – የዚህ ጹሑፍ መንፈስ ትንሽ ጠጠር ስለሚል፤ ከቻሉ ደጋግመው ሲያነቡት መልዕክቴን ሊያገኙት ይችላሉ። ግጥም መሰል አመክንዮን ያስተናገደ – ስለሆነ። አመሰግናለሁ – በአክብሮት

ስለ ፍቅር መዋረድ የነፃነት ፍለጋ ጽድቃዊ ጉዞ ነው፤

ፍቅር ለተስፋ አድሮ የሚገኝ ብቸኛ ማተበኛም – ትውልድ።

እኛን ስለሰጠን አምላካችን እናመስግን!

 

The post እኔ ማን ነኝ? – ከሥርጉተ ሥላሴ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>