Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ከፍትፍቱ አጉሩሱኝ ከመረቁ ፃመኛ ነኝ –ቢንያም ግዛው (ከኖርዌይ ኦስሎ)

$
0
0

Biniamየብዙሀኑ  የጣት ሽታ  እንደገደፈ ያሳብቃል። በጥቂትም ሆነ በብዙ ያልተነካካ ቢፈለግ በግራም ሆነ በቀኝ ቢነፍስ ፃሙን ያላፈረሰ ማግኘት አልተቻለም።ከፍትፍቱ አጉሩሡኝ ከመረቁ ፃመኛ ነኝ ብሎ እንክት አድርጎ ከሰለቀጠ ወዲያ ምንም  እንዳልገደፈ አፉን ጠረግ ጠረግ አድርጎ ባላየ ባልሰማ የሚጓዘው ተበራክቷል።  በዕንዶድም የማይነፃ ጣት! ከምን አይነት መረቅ ውስጥ ቢዘፈቅ ይሆን ? . . . ጠቢቡ ሠሎሞን በምሳሌው . . .  ስጦታ በስውር ቍጣን ታጠፋለች፥ የብብትም ውስጥ ጉቦ ጽኑ ቍጣን ታበርዳለች ያለው ትዝ አለኝ በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያን የባለስልጣን ቢሮዎችን ሳስባቸው ምን ቢያምራቸው እንኳን  ምራቃቸውን ገርገጭ አርገው ውጥው ስርዓቱ እና ህጉን በማክበር ቢፃሙ ምን አለ?  ሁሉም ቢሮ ስጋ ስጋ ደም ደም ነው የሚሸተው። በፃሙ!

 

ትምህርት ሚኒስቴር፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፣ ፍትህ ሚኒስቴር፣ ፌዴራል ፖሊስ ፣ ወህኒ ቤት፣ ሆስፒታል፣ ባንክ ቤቶች፣ ወ ዘ ተ . . . መጥቀስ እስኪታክት ድረስ ሁሉም በዋና ዋና  የሀጢያት አበጋዞች ተዘፍቀዋል። በተለይም በወያኔ ዘመን ያለቅጥ ተንሰራፍቶ የሚገኘው  ብዙ በደለኞችን ፃድቅ አድርጎ ፍርድን እና ፍትህን በማጣመም አይን የሚያስውረው በሽታ   ምድሪቷን ጠፍንጎ ከመግቢያው የግሙሩክ መስሪያቤት ጀምሮ እስከመውጫው ኢሚግሬሽን ድረስ በጉቦኝነት ጠፍንጓታል። በኢትዮጵያ ውስጥ ወያኔ እስካለ ድረስ ሀቀኛ ነኝ አልነካካም  ብትል እንኳን ብዙም ሳትሔድ በቀላሉ በጥንቃቄ እያሽከረከርክ በምትነዳበት መንገድህ ላይ የሸሚዙ ቁልፍ እስኪፈናጠር በላይ በላይ የሚበላው ትራፊክ ፖሊሱ እቁብ ስለደረሰበት ብቻ ፊሽካውን ነፍቶ ሲያስቆምህ ከመንጃ ፈቃድህ ይልቅ የመቶ ብር ኖቶችን ማዘጋጀቱ ብቻ ነው መገላገያ መንገዱ።በቃ ፃምህን ያስገድፉሐል።  በዚህ ውስጥ ያልተነከረ እና ያልተዘፈቀ  እጁን ያሳይ? . . . የተነከረበት ከሩቅ የሚሰነፍጠው መረቁ ምስክር ነው ። በጉቦ መረቅና  በሙስና የተዋዛ ጣት !

 

እጅ የሚስቆረጥም የፍትፍት ጉርሻ ፅኑ ቁጣን እንደምታበርድ ፥ የንፁሐንን ቃል እና ፍርድ በጉቦ ተጣሞ  ለማይገባቸው ሲፈረድላቸው ማየት አዲስ ነገር አይደለም። በተለይም ድንገት አዲስ እንደተወለደ ህፃን ከዚህ በፊት ሳይታዩ ከባዶ ካፒታል ላይ ተንደርድረው ከናጠጠ ሀብት ጋር ብቅ የሚሉት ቱጃሮች የሀብታቸው ምንጭ ከየት እንደፈለቀ ለማወቅ ግልፅ ሆኖ ሳለ ከባለስልጣናቱ ጋር በመሞሳመስ የሚያደራጁያቸው የተለያዩ የንግድ ሂደቶችም በፌደራሉ ስነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምንም አይነት ክትትል  ሊደረግባቸው የማይችልበት  ዋናው ምክንያት ባለስልጣናቱ ከላይ እስከታች እያንዳንዱን ተጠያቂ ስለሚያደርጋቸው እና ክትትል አድራጊውም ሆነ ድርጊቱን ፈፃሚው ከአንድ ወንዝ የተቀዱ ስለሆኑ ነው። ቢሆንም የኢትዮጵያ ህዝብ የስልጣኑ ባለቤት ሆኖ ይህ አገዛዝ ለፍርድ እስከሚቀርብበት ጊዜ  ድረስ  አንድነትን በመጠበቅ በፅናት እና  በትዕግስት ለሐገሪቷ ነፃነት እየታገሉ መቆየት የእያንዳዳችን ድርሻ ሊሆን የተገባ ግዳጃችም ነው።

 

እያልኩ ያለሁት ለምን ሰው ባለጠጋ ሆነ አይደለም። ይልቁንም የፖለቲካን የበላይነት እና ባለስልጣን መሆንን ተገን አድርጎ የሚደረግ  የሀገርን  ሀብት የመዝረፍ ወንጀል ከአውራነቱ የተነሳ  በምድሩም ሆነ በሰማይ  በሚሰየመው ችሎት እንደሚያስጠይቅም ለማሳሰብ ጭምር እንጂ። በተጨማሪም በኢትዮጵያ ከተከሰቱት ታላላቅ መፍትሔያቸው የራቁ የኑሮ ቀውሶች መካከል ለሰው ልጅ መኖር መሰረታዊ  የሆኑትን ብቻ    ለመገብየት ከዋጋው ግሽበት የተነሳ የሀገሪቱ የገንዘብ ጉልበት  እጅግ ደቃቃ  ሆኖ አቅም የለሽ በሆነበት፣ ስራ አጥነት ተበራክቶ ብዙሀን የወጣቱ ክፍል ህይወቱን ያጣበት የበረሀ ጉዞ እና በባህር ሰጥሞ አስከመቅረት  ዋጋ የሚይስከፍሉ የስደት አይነቶች ህዝብ እንዲጋለጥ፣ ወላጅ እየተጦረ እፎይ ብሎ በሚያርፍበት የሽምግልና ዘመኑ ለልመና ሰው ፊት የቆመበት እንዲሁም በብዙ ምሬት ውስጥ በመሆን ለተጎነበሰበት እና በምድሪቷ ላይ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሙስና ባህል እስኪመስል ድረስ በእጅጉ ተንሰራፍቶ ጥላውን እንዲያጠላ እና እንዲባባስ ገዢው ብድን ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። እየተጫወተም ይገኛል። አምባገነናዊነት፤ እብሪት፤

ግትረኛነትና ትምክህተኛነት በከባድ የተጠናወተው ቡድንተኛ መሪ የሃገሪቱንም ሆነ የህብረተሰቡን አንጋፋ ችግሮች በጋራ ተመካክሮ፤ የፖለቲካ ስልጣንን በመካፈል ፤ የሕዝቡን ድምጽ አክብሮ፤ በተለይ ሀገር ተረካቢውን ወጣቱን ትውልድ ፍላጎት ለማሟላት በሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫ  በእኩልነት ለመስራት የተዘጋጀ አይደለም። አቅሙም ልቡም የለውም። ይልቁንም የአብዛኛው ህብረተሰብ የኑሮ ሁኔታ ወደ ማጡ አባብሶታል። ይህ የአንድ ብሔር ብቻ ወገንተኛ  የፖለቲካ ብድን ፤ የኢትዮጵያን ህብረተሰብ እና የተለያዩ ብሔሮችን ግልፅ በሆነ አሰራር ሳያካትት የሀገሪቷን አንድነት  ባልጠበቀ ዘመቻው በአደገኛ ሁኔታ በሙስና እና በተለያዩ ጤናማ ባልሆኑ አካሄዶቹ የህዝቡን ኑሮ ከስሩ አናግቶታል። የጉቦኛነት ተስቦ ሳያንሰው ከሁሉም በላይ አዲሱ ትውልድ በኢትዮጵያዊነት ሳይሆን በጠባብ ጎሰኛነት  እንዲያምን በሚያደርገው ርብርብ ኢትዮጵያዊነት ከቶውንም ተሽሮ ብሔርተኝነት እንዲያብብ  የማያቋርጥ ተጋድሎ እያደረገም ጭምር ነው።

 

የሙስናው እንቅስቃሴ እና  ተግዳሮት  ለሀገርና ለህዝብ ጠንቅ መሆኑ አለም ሁሉ የሚስማማበት ስለሆነም በተለይም ደግሞ ሰላም በሰፈነባቸው  ሀገሮች ይህ ድርጊት እንደ ትልቅ ውርደት የሚታይ እና በአንዳንዶች ዘንድ ፈፅሞ የማይታወቅ ተልካሻ ስርዓት ነው። ዛሬ የስቃይ ኑሮ ገፈት ቀማሽ ያደረገን ወያኔ ከፅንሰቱ ጀምሮ እጁ ከሙስና ሳይፆም የረከሰ በመሆኑ ምክንያት አባላቱን እንኳን ሲመለምል ቀድሞውንም ስለ ኢትዮጵያ በመቆም ለትግሉ በእውነተኛነት አሳምኖ ሳይሆን በፍቅረ ንዋይ የተቃጠሉትን በማማለል ከድል ማግስት የሚገኘውን ሀብት በማለም ብቻ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ በሀገራችን የተማረው  ክፍል በሙያቸው፣ በዲግሪያቸውም ሆነ በልምድ እውቀታቸው ሰርተው ሀገር የሚያለሙበት  መንገዱ ሁሉ ቢዘጋጋባቸው ለመኖር ሲሉ የግዳቸውን ከባለስልጣናቱ ጋር የተለያየ አይነት የሙስና መንገዶችን ለማጠቀም የሚገደዱት።

 

በኢትዮጵያ ከኖርክ በብዙም ሆነ በጥቂቱ ለመኖር ስትል ጉቦ ትሰጣለ ወይም ታበላለህ። በዕጅ ማለት ብርቅ አይደለም። ከዘበኛው ጀምረህ ባለስልጣኑን እስክታገኘው ድረስ ሁሉን እያጉረስክ ማለፍ የግድ ነው። ለምሳሌ የገንዘብ ተመን ከወጣላቸው ጉቦኝነት መሀከል የመኪና መንጃ ፈቃድ ለማውጣት የሚከፈለው ክፍያ ነው። ካልሰጠህ መንጃፍቃድ የምይታሰብ ጉዳይ ነው ፥ ሊያውም ዳጎስ ያለ እንደሆነ ደግሞ ያሉበት ድረስ ይመጣልዎታል። ይህም ሂደት ሀገሪቷን ለከፍተኛ የመኪና አደጋ አጋልጦ ሰጥቷታል። በመሬት ንግዱ ዙሪያ እና የፃድቁን ውሳኔ ለማጣመም በፍርድ ቤቶች   የሚከፈሉት የዳጎሱ ጉርሻዎች ሐገር ሁሉ የሚያውቀው ራቁትነት ነው። የተማረው፥ፊደል የቆጠረው በደጅ ሆና ተስፋ ቆርጦ ሲማረር እና ፀሀይ ሲበላው ሌላው ዘሩን ጠርቶ የግንባሩን ምልክት አሳይቶ ለምሁሩ የተዘጋበትን በር አስከፍቶ ዘው ይልበታል። ለዚህ ሁሉ ውድቀት ዋናው  ምክንያቱ  ባለቤት እና እውነተኛ መሪ በሌላት ሀገር ላይ  የመንግስት ተቋማት ከፍትፍቱ አጉሩሱኝ ከመረቁ ፃመኛ ነኝ በማለት ሳይነክሱ መኖር አቅቷቸው ለሙስና በመዘፈቃቸው ብቻ ነው፡፡

 

ጉቦኝነት ሁሉን ዳሶታል ። ፈተናውን ሁሉ ለመለፍ ወይ ገንዘብ አሊያም እንደ ባለስልጣናቱ  ጥያቄ መሰረት ፍላጎታቸውን ማርካት የተለመደ ቢሆንም ይህን ሀገርን ወደኋላ የሚጎትት አሰራር ከስሩ ለማድረቅ ኢትዮጵያውያን የሆንን ሁሉ ለሀገራችን ነፃ መውጣት የምንከፍለው ሌላ ክፍያ አለ። በሁሉ አቅጣጫ አንድነታችንን በማጉልበት ለወያኔ አገዛዝ በእንቢተኛነት መጋፈጥ! ብሔር ከሀገር አይበልጥምና  የጎሰኝነትን እና የብሔርተኝነትን የመለያየት መርዝ አርክሰን በአንድነት መቆም!

 

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር።

ቢንያም ግዛው (ከኖርዌይ ኦስሎ)

 

 

 

 

The post ከፍትፍቱ አጉሩሱኝ ከመረቁ ፃመኛ ነኝ – ቢንያም ግዛው (ከኖርዌይ ኦስሎ) appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>