ሥርጉተ – ሥላሴ 4.04.2015 /ዙሪክ ሲዊዘርላንድ/
„እንቅልፍ ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም“ – ከአቨው ብሂል
እንዴት ናችሁ የኔዎቹ ሐገር ሰላም ነውን? ዬዛሬ መነሻዬ “ኢትዮጵያዊቷ የISIS ሙሽራ እና “ጽንፈኛ” ሆነው የተገኙት አባቷ” ይህ እርእሱ ሲሆን በውስጡ ብንሄድበትም እርገቱ እንዲህ ይላል “ድምጻችን ይሰማ በዚህ ውዥንብር „ሳይደናገር” ላለፉት 3 ዓመታት ያሳየንን ሰላማዊ እና ስልጡን ተቃውሞ እንደሚቀጥል ቅንጣት ታህል ጥርጥር የለኝም።” ዬፁሑፉን ምንጭ ፌስ ቡክ ላይ ከካሳሁን ይልማ(የኢሳት ጋዜጠኛ) ሲል ዘሀበሻ ባጠናቀቅነው ሳምንት የመጀመሪያ ቀናት ጹሑፉን ለጥፎታል።http://www.zehabesha.com/amharic/archives/40100 እኔ የፌስ ቡክ ተሳታፊ ባለመሆኔ መልካም ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ለምን? ሚሊዮን አድናቂ አለና ብዙ ሰው አንብቦታል፤ በውስጡም አስቀምጦታል ብዬ ስለማስብ ብቻም ሳይሆን የዋህ ወገኖች ባልሆነ መልክ ሊተርጉሙትም ስለሚችሉ “ህልም እንደፈቺው” አይደል የሚባለው እንዲሁ ተንጠልጥሎ ከሚቀር ቅርጥምጣሚ ስጋቶች መሬት ላይ ወርደው በቅጡ መያዝ ስላለባቸው ልንሸራሸርበት እንዲህ አሰኜኝ። በቅድሚያ ግን ላመስግነው ዘሃበሻን – እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
እኔ የፌስ ቡክ ተሳታፊ ባለመሆኔ መልካም ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ለምን? ሚሊዮን አድናቂ አለና ብዙ ሰው አንብቦታል፤ በውስጡም አስቀምጦታል ብዬ ስለማስብ ብቻም ሳይሆን የዋህ ወገኖች ባልሆነ መልክ ሊተርጉሙትም ስለሚችሉ “ህልም እንደፈቺው” አይደል የሚባለው እንዲሁ ተንጠልጥሎ ከሚቀር ቅርጥምጣሚ ስጋቶች መሬት ላይ ወርደው በቅጡ መያዝ ስላለባቸው ልንሸራሸርበት እንዲህ አሰኜኝ። በቅድሚያ ግን ላመስግነው ዘሃበሻን – እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ጹሑፉ „ድምጻችን ይሰማን” አክብሯል። ለዚህም ለታናሼ ምስጋና ይድረሰው እላለሁ። ያልተመቸኝ ነገር ግን አለ። ለዚህም ነው ከእሜቴዋ ጋር ተመካክረን የምንለውን ልንል የተሰናዳን። እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች በተፈጠሩ ቁጥር ከሌሎች ነገሮች ጋር ዬምናያይዘው ነገር ፈጽሞ አይገባኝም። ባለቤቶች እኮ አሉ። በተጠያቂነት የሚቀርቡ። እኔ ሥርጉተ በእንደነዚህ ዓይነት ጉዳዮች ጋር አብሬ አልቆዝምም። ለወያኔ የፈጠራ ክስ አጨብጫቢነት የሰናፍጭ ታክል ክፍተት – ድንኳን ሰብርነትንም አልፈቅደውም። እኔ በግሌ ንቅናቄ፤ ድርጀት፣ ግንባር በአጠቃላይ ተልዕኮውና በውላዊ ሂደቱ ብቻ ነው የምለካው። “ሳይደናገር” ምን ያደናግረዋል? የተነሳበት ንፁህና ቀጥ ያለ ግልጽ የነፃነት ዓላማ አለው። ለማንኛውም ….
- ድምጻችን ይሰማ ለእንደዚህ መሰል ነገሮች በዬሰከንዱ ለሚፈጠር ግሎባል ግድፈት ጋራንቲ ዋስትና ሊሰጠን ፈጽሞ አይችልም። አይጠበቅበትም-ም። ስለምን የሚለውን እመጣበታለሁ።
- በፍጹም ሁኔታ እንዲህ አይነቶች ነጠላዊ ጉዳዩች ወይንም ቀንጣዊ ክስተቶችን ዬሚሊዮን ወላዊ ድምጽ ኃላፊነት ወስደው ከሚሸከሙ እንደ “ድምጻችን ይሰማ” ካለው ጋር ሆነ ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ማነካካት አይገባም ባይም ነኝ። ፈጽሞ በዚህ ዕይታ ውስጥ “ድምፃችን ይሰማ” መጠቀስ ሥሙ መነሳት አልበረበትም። ስለምን? የነጠረውን እውነት ፈላጊነታችነን ዳመናማ ያደርገዋልና። ለሰብዕዊ መብት ተሟጋችነታችነንም በአረም ያስውጠዋል። ወያኔ ሃርነት ትግራይ “አሸባሪ” ያላለው ምን አለና። ሳር ቅጠሉ ንፋሱ ሳይቀር ለወያኔ “አሸባሪ” ነው፤
- በሌላ በኩል የነፃነት ረሃብተኛነት ቋሚ ፍላጎትን ስንጥር ሊነቀንቅው አይገባም። ሶስት ዓመት እኮ ልጅ ተጸንሶ ተወልዶ በእግሩ የሚሄድበት ብቻም ሳይሆን አፍም የሚፈታበት ወቅት ነው። ንቅናቄው በዚህ ቆይታው ከመምህርነቱ በስተቀር የታዬበት ግድፈት የለም። ፈተናዎቹንም በስልትና በጥበብ በመያዝ ትብትቦቹን እዬረገጠ ወደ ፊት መገስገሱን ነው ያዬነው።
ወጀቡ ሊያል ይችላል። ጦሩም ሊመዘዝ። አውሎም ሊንጥ። እኔ እላለሁ ጋዜጠኝነት የማሰብ ጥበብ ልቅና የሚታይበት የህማማት ሙያ ነው። ጋዜጠኝነት የምቾት፣ የድሎት ወይንም የዕውቅና ፍለጋ፣ ወይንም የቅልጣን ሙያ አይደለም። ይልቁንም ሁሉንም መከራ ተቀብሎ ለዕውነት ጥንግና ድርብ በመሆን ሚዛን ጠብቆ ዘብ መቆም ነው። ስለሆነም ፈተናውን ሁሉ በመቀበል ሂደት ውስጥ አጋዢ ወይንም ጥግ ወይንም አይዞህ /ሽ/ የሚል ላይኖር ይችላል። ግን ዕውነት በጠባቂነት ስለሚሰለፍ፤ የእውነት አቅም ኃይልን እያመረተ ወደ ውስጥ የማዬትን ጸጋ ያፈልቀዋል – መጎናጸፊያውም ትጋትን አበረታቶ ፊት ለፊት ወጥቶ በማገዶነት መጓዝን ይመርቅለታል። ስለዚህ ለጋዜጠኛ ለእኔስ ሰው መሆኔ ብቻ ይበቃኛል – ይመራዋል። የሙያው ሥነ – ምግባር ሃይማኖቱም ይሄው ነው። ፈጣሪ አምላክ በአምሳሉ ለፈጠረው „ሰው“ ልዩ የአክብሮት አቅምና ጉልበት በውስጡ የመገንባት ጥበብ – ጋዜጠኝነት። ደንበር የለሽ ሙያ – ጋዜጠኝነት። ከተከፉ ጋር የሚሰለፍ መከራን የደፈረ ሙያ – ጋዜጠኝነት።
አብሶ ነፃነት ተጋድሞ እንደ ግንድ በአንባገነኖች በሚፈለጥበት ወቅት „ነፃነትን“ ነፃ ሊያወጡ የሚተጉ ከሌላ ሙያ ያሉ ወገኖች ሳይቀር ወደ ሙያው አዘንብለው የእውነት፣ የሰብዕዊ መብት ጥሰት፣ የህግ ረገጣን በመቃወም ፊት ለፊት ወጥተው አንባገነኖችን ሆነ አንባገነኖችን የሚደግፉትን ዲታ ሀገሮች ሳይቀር ይሟገታሉ። ለዚህ ሩቅ ሳንሄድ መምህርና ጋዜጠኛ ርዕዮትን አለሙን፤ መምህርና ጋዜጠኛ አብርሃም ደስታን እንደ ናሙና መውሰድ እንችላለን። በሌላም በኩል የዞን ዘጠኝ በመባል የሚታወቁትን ወጣት ትንታግ የብሎግ አርበኞች ዕጣ ፈንታ በማስተዋል መመርመር እንችላለን። የጠራቸው፤ ያሰባሰባቸው፣ ያነሳሳቸው አንድ ነገር ብቻ ነው። ማህበራቸውም አንድ ነው። የሰብዕዊ መብት ጥበቃ በአረም መዋጥ። ነፃነትነትን ከነደራጎን መንጋጋ ለማውጣት ከህዝብ ጎን ቆሞ „ሰብዕነትን“ ሁሉን መከራ መቀበል ነፃ ማውጣት። ይህ ነው የጋዜጠኝነት ተልዕኮ። በአጋጣሚ በእሳት ላይ ሁነው በዞን ዘጠኝ ጋዜጠኞች የቀጠሮ ቀን ሳይታክቱ፤ በራስ በመተማመን ፍጹማዊ መንፈስ በፍርድ ሂደቱ ቦታ በመገኘት እራሳቸውን ለመስጠት የተዘጋጁትን ወገኖቼን በማድነቅ – አመሰግናቸዋለሁ። በወራሪ ወታደር ታጅበው ይህን ያህል ጥንካሬ ማሳዬት፤ በመከራ ቀን ለዕንባ ዘብ መቆም የኢትዮጵያን ተስፋ ያሰፋዋል – ኑሩልን። እናንተ እራሳችሁ የጀግንነት ድሪ ናችሁና።
አሁን ወደ ነጥቤ። ሙያውን ከነፍሳቸው ጋር አዋህደው ወደውትም የጀመሩትም ቢሆን፤ መፍቅድ የቻሉት አንድ ነገርን ብቻ ነው። ዝናን አይደለም። ስለ እውነት ጧፍ መሆንን ብቻ ነው። ለዚህም አባ ትርጉም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን፤ አብነቱን በጥልቀት በመስተዋል መመርምር ይቻላል። ታታሪዎችን ጋዜጠኛ ውበሸት ታዬ እና ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝምም ፈለጉን አጠንከረው ራሳቸውን የሰጡበት ሚስጢር የህሊናቸው የማስብ ደረጃ ልቅናው ከፍ ያለ በመሆኑ፤ እነኝህ የዘመን አባ እና እማ ወራዎች ማገዶነቱን በመምረጥ በመከራው ዘመን ቀንዲል መሆን ችለዋል። በርካቶችም ሳይወዱ ተገደው ተሰደዋል። ይህ እንግዲህ በእኛዋ እናት ሀገር ኢትዮጵያ ያዬነው ጭብጥ ንጡር የሙያው ባላቤቶች ተግባር ነው። በውጪውም ቢሆን ከሞቀውና ቅልጥ ካለው ስልጡኑ ሀገራቸው ወጥተው ለሙያው ክብርና ሥነ – ምግባር ሲሉ ባልተወለዱበት ሀገር በጦርነት ውስጥ ያለፉ፤ የሃቅ ፈርጦች፤ ዬእውነት ኮከቦች የሙያው ዘውዶች ዓለማችን በዬዘመኑ በእጅጉ አስተናግዳለች።
በዘመነ አዶልፍ ሂትለር ያን ያክል እሳት ውስጥ ገብቶ የተርመጠመጠው አርበኛ ፍራንስ ለሆዱ አላደረም ነበር። ባለቤቱ ወ/ሮ ሶፊ በሚደርስባት ተጽዕኖ ተጨንቃ „ትዳራችን እይ ስትለው „እጃችን ተመልከችው የእኔና የአንቺ አንድ አይደለም አስተሳሰባችንም“ በማለት ነፍሱን ለናዚ በለሃሰብ ወታደሮች ሰጥቷል፤ አጋሩ ወ/ሮ ሶፊም ከልቧ በገባው ዕውነት ተማርካ እስከ መጨረሻው አብራው እንድትሆን አድርጓታል። አዶልፍ ሂትለር ጀርመንን ከሌላው የለዩበት ዶክተሪንና ያን ያህል ነፍስ ያጠፋበት፤ ያቃጠሉበት ኢ-ሰብዕዊነት ድርጊትና የሄሮድስ መለስ ዜናዊ „እንኳንም ከእናንተ ተፈጥርኩ፤“ ጠፍ መንገድ ሚሊዮኖች እንዲከፉ፤ አንዲገለሉ እንዲሞቱ እንዲሰደዱ ያደረገው ሁለቱም አንድ መንገድ ነው የተከተሉት። አዶልፍ ጀርመናዊነት ዝርያን ማንጠራራታቸው፤ ሄሮድስ ደግሞ ትግራዊነት ዝርያን ማንጠራራታቸው ወጥ የናዚዝም ጸረ ሰብዕ ፍላጎት በዬዘመኑ እንድናይ አድርጎናል። ለዚህም አውራንባ ታይምስን ከሁለት በከፈለው ግድግዳ የሰውን ልጅ ተፈጥሮ በቅጡ የመተርጎም አቅም ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ነጥሮ ወጣበት፤ በሌላም በኩል የኢትዮጵያ ቴሊቪዥንና ራዲዮ አገልጋዮችና የኛው ውድ ጋዜጠኛ አብርሃም ደስታ ደምቆ የወጣበት ሃቅ ማገርና ግድግዳው ሆነ ባላና ወጋግረው „ሰብዕዊነትን“ በእኩልነት ከማዬት፤ የተፈጥሮን ሚስጢሩን ከማግኘት ያደገ አስተሳሰብ መንጭቶ ነው። ዛሬም እሳት ከሚተፋው ቦንብ ሥር መስዋዕትነቱን እዬከፈሉ የሚገኙ አሉ።
ጋዜጠኝነት — እውነትን የመግለጽ ብቻ ሳይሆን እውነትን የማመን፤ እውነትን የማመን ብቻ ሳይሆን እውነትን የመቀበል፤ እውነትን የመቀብል ብቻ ሳይሆን ስለ እውነት ውስጥን ገዝቶ የእውነት ብራ መሆን የክቡሩ ጋዜጠኛ ምግባሩም ህይወቱም ነው። ጋዜጠኛ ውስጡ የሚቃጠለው እውነት ተዘቅዝቃ ስትንጠለጠል ነው። ጋዜጠኛ መንፈሱ የሚርመጠመጠው „ሰው“ የሚለው አባወራ / እማወራ ፍጡር ክብሩ ትቢያ ሲለብስ ነው። ተፈጥሮ ሲደፈር ማዬት ለጋዜጠኛ ህመሙ ነው።
በዬትኛውም መስፈርት ቢሆን አንድ ጋዜጠኛ በቋሚ የዕውነት ማገሩ ላይ ጽኑ የሆነ አቋም ሊኖረው ይገባል። ኢትዮጵያ የዓለም አካል ናት። ስለሆነችም ነው እኛ መኖራችን የዓለም አቅምና ጉልበት መሆናችን አትዘንጉ። ስለዚህም በሀገራችን ባለው የመብት ረጋጣና የመብት ድፍጠጣ አንባገነናዊ ጎጣዊ አፓርታይድ ሥርዓት ለማስወገድ በምናደርገው የነፃነት ትግላዊ ሂደት ከጎናችን ልትቆሙ ይገባል፤ በማለት በመላ ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵውያን ሲችሉ በጋራ፤ ሳይችሉ ደግሞ በግል የሚችሉትን ሁሉ በማደረግ ላይ የሚገኙት።
በአንፃሩም እንደ ዓለም አካልነታችን ከዬትኛውም ሃይማኖት ወይንም ማህበራዊ ተቋም በዓለም በሚከሰቱ አሉታዊ ሁነቶችም ሆነ መሰል ጥፋቶች ሊሳተፉ የወደዱና የፈቀዱ መኖራቸው ደግሞ ግድ ነው። ዓለም በሽታን የሚያውቅ መሳሪያ አላት። ነገር ግን የሰውን ልጅ አሉታዊና አዎንታዊ ረቂቅ አስተሳሰቡን የምታይበት ወይንም የምታነብበት ወይንም የምትመዘግብበት መስታውት ዘመን አመጣሽ ዲጂታል መሳሪያ እስካሁን አልፈለሰፈችም። ቢሆንማ ዕድሜ፣ ፆታ፣ ሃይማኖት ሳይለይ ይህ በዬሰከንዱ የሚታዬው እጅግ ዘግናኝ፣ አሰቃቂና አስፈሪ አደጋን መቆጣጠር በቻለች ነበር። ዛሬ በእያንዳንዱ ፍጥረት ዙሪያ ስጋት ገዝፎ አለ። ሰው ወጥቶ ስለመመለሱ ስለማያውቅ የስንብት ደብዳቤ ጽፎ መውጣት እዬተለመደ መጥቷል። እርግጥ አንድ የሚያድን ነገር ነበር። ይህን የሚያድን ነገር እሰከ አሁን ዓለም እራሷ አልተጠቀመችበትም። ሚስጢሩንም የደረሰችበት አይመስለኝም። ብትደረስበትም በአንድ ጀንበር ውጤት የሚታይበት አይደለም። የረጅም ጊዜ የጥረት ውጤት ነውና።
የሆነ ሆኖ ዓለም ያልቻለችውን ኢትዮጵያዊው „ድምጻችን ይሰማ“ ከዬትና በምን አቅሙ ያመጣዋል። ሚሊዮኖች የታደሙበት እንቅስቃሴ ውስጥ በምን ስሌትና በምን ሁኔታ፤ በምንስ አቅሙ ዬእንክርዳድ ከስንዴ የውስጥን ስሜትና አቅጣጫ መመርመር ያስችለዋል? ዳኝነት ለራስ ነው። ፁሑፉ ተጠያቂ እንዳለደረገው አውቃለሁ። ነገር ግን የዝንባሌው መንፈስና ጠረን „ድምፃችን ይሰማ“ አቅጣጫውን እንዳይቀር የሚነካኩ ኩነቶች አሉበት። እንደገናም ከውስጡ አረም ቢበቅል የሚል ቅርጥምጣሚ ስጋትም ሸቶኛል። በማህበራዊ ኑሯችንም ስንለካው „በሬ ካራጁ ጋር“ የሆኑ ገጠመኞች እንዳሉንም መዘንጋት የለብንም። ገጹን ታያላችሁ ይመቻችኋል። አብራችሁ መልካሙንም መልካም ያልሆነውን ትጋራላችሁ። ቀጥሎ ደግሞ አጋጣሚ ቀን የሰጣችሁ ቀን የምታውቁት ያ ሩህሩህ – አስተዋይ – ደግ – አለኝ ብላችሁ ያስጠጋችሁት እምነት የሰጣችሁት፤ በውስጣችሁ ያነገሳችሁት ገፅ ሌላ የማታውቁት ገፅ ሆኖ ያፋጣችኋል። እንደዚህ መሰሉ ረቂቅ ውስጣዊ መንፈስን የማንበብ ሆነ ቀድሞ የመተንበይ ብልሃት „ድምጻችን ይሰማ“ ከአቅሙ በላይ ስለሆነ ተጠያቂ ሊያደርገው ፈጽሞ አይችልም። የሆነ ሆኖ ….
ደግሞስ ምንስ አዲስ ነገር አለው። ከዬትም ቦታ ከዬትኛውም ሀገር እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸው ጋድሞች፣ ሲዖሎች፣ ጸረ ተፈጥሮዎች ይፈጠራሉ። በዬቀኑ አውሮፓ ላይ በግል አባል ሆነው የሚገኙ የሚታሰሩ፤ ሄደው የሚቀላቀሉ እንደ አሉ ዜናዎች ያመልክታሉ። ነገም ከነገም ወዲያ ኢትዮጵያ የዓለም አካል እንደመሆኗ ኢትዮጵያዊ የሆነ ወይንም የሆነች ይህን ጸረ ሰብዕ፤ ጸረ እድገት፤ ጸረ ነፃነት የሆነውን አጥፊ ድርጅት ሊቀላቀሉ የሚችሉ የጥፋት አቀንቃኝ ብቻ ሳይሆን መሪ ሆነው ሊገኙም የሚችሉ ይኖራሉ። ይህን መጠበቅ ይገባል። ለዚህ „ድምጻችን ይሰማ“ ጋራንቲ ወይንም ጥብቅ የዋስትና ኪዳን እንዲሰጥ አይጠበቅበትም – በፍጹም። ክፍል ከፍተው እኮ በይፋ „ጀሃዲስትነትን“ በአደባባይ ሲያውጁ ነበር። ይህን በዛ „ጆኖሳይድ“ በሚባል ክፍል ውስጥ የበቁት ዬኢንተርኔት ባለሙያ ኢትዮጵውያን ወገኖቼ አድራሻቸውን እንደሚይዙት ተስፋ አደርጋለሁ። ያው ኢትዮጵያዊነት ዬይሉኝታ ማርዳ በመሆኑ አሳልፈው ሳይሰጧቸው በመረጃነት አስቀምጠውት ይሆናል ብዬም አስባለሁ።
„ድምፃችን ይሰማ“ እንቅስቃሴ ነው። እንቅስቃሴው አንድ የነፃነት ትግል ፕሮጀክት አለው። ፕሮጀክቱ የዕምነቱን ነፃነት በነበረው አቮዊና ትውፊታዊ መልክ ማስመለስ ነው። ይህ ከተመለሰለት ዬፕሮጀክቱ ተልዕኮው ያበቃል ማለት ነው። በቃ! ግልጽ ጥያቄ ነው። „መሪዎቻችነን በመስጊዳችን እንመርጥ። ምርጫው የሃይማኖታችን ሥርዓት በሚፈቅደው መሰረት ስለመሆኑ ለእኛ ተውልን። መንግሥት በሃይማኖታችን ጣልቃ አይግባብን፤ ካለአግባብ የታሰሩ መሪዎቻችን ይፈቱልን፤ ከታሰሩበት ቦታ ኢ – ሞራላዊ ጭካኔ አይፈጸምባቸው፤ መሪዎቻችን የሃይማኖት መሪ እንጂ አሸባሪዎች አይደሉም፤ በሃይማኖታችን በምታደርሱት በደል ከፍቶናልና ድምፃችን ስሙ“ ይሄ ነው። ከተሳሳትኩኝ ልታረም ዝግጁ ነኝ። ይህን ቀላል ጥያቄ የወያኔ ሃርነት ትግራይ መመለስ አልቻለም። ለምን?
እስትንፋሱ የሚቆዬው በዚህ ዙሪያ በሚሰራቸው የጣልቃ ገብነት ተግባር ስለሆነ ሽፋን አይገኝም – ከዲታ ሀገሮች። በኢትዮጵያም „አሸባሪዎቸ አሉ እነሱን እዬገላገልኩላችሁ ነው። ሰብስቤ አስሬላችሁአለሁ፤ ማለት እንዲችል „ፈጥሮ የአሸባሪ ሥም ለጥፎላቸዋል“ ይህም ብቻ አይደለም። ይህን በማደረጉ „የድምጻችን ይሰማ“ በእልህና በቁጭት ተነሳስቶ ወደ ጥፋት ተግባር እንዲሰማራ፤ የሌሎችን የሃማኖት ተቋማትን በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትን ክብር በግብታዊነት እንዲያወድም – እንዲያዋርድ፤ ዬእርስ በእርስ ሃይማኖታዊ ግጭት ጠብ እንዲጭር፤ እሳት እንዲነድ ለማድረግ ብዙ ጥሯል። ግን አልተሳካለትም። „ድምፃችን ይሰማ“ የብልህነት ጥንካሬው ከብረት ቁርጥራጭ የተሰራ ነውና።
„ድምፃችን ይሰማን ፍላጎትና ተልዕኮ“ የቁጣ፣ የእልህ እርምጃ አድርገውት ቢሆን ኖሮ፤ ለወያኔ ሰፊ የሆነ የቅጠፈቱ ቋት ይሆን በነበር። ዓለምም „ትክክል ነህ ወያኔ ሃርነት ትግራይ በማለት ጎሽ! ደግ አደረከህ ብሎ ይሸልመው በነበር።“ ሌላው ወያኔ የማይተኛበት ነገር በመሃላቸው አስርጎ የማስገባቱ ጉዳይ ነው። ይህም ግምት ውስጥ ሊገባ ይገባዋል። አንድነት ለኢትዮጵያን የመሰለ ብሄራዊና መጠነ ሰፊ ትልም የነበረውን የተስፋ ፓርቲን ያፈረሰው በዚህ በሰለጠነበት የሸር ሙያው ነው። የሆኖ ሆኖ ወያኔ ሃርነት ትግራይ እንዳሰበው አልተሳካለትም የከሸፈ ባዶ ቀላሃ ነው የሆነው።
እንቅስቃሴው ትእግስቱን ዋጥ አድርጎ፤ መከራውን ችሎ በስልትና በጥበብ እርምጃዎችን ሳይመራ ለወያኔ ሴራ ቀለብ ቢሆን ኖሮ፤ እኛም ብዕራችን ሰብሰብ አድርገን፤ መንፈሳችን ቁጥብ አድርገን እንቀመጥ ነበር። ስለምን? ወጥቶ መቅረትን የሚመኝ አንድም ዜጋ ሊኖር አይችልምና። ሰቀቀን የሚደግፍና የሚበረታታ ነፍስ አይኖርምና። ጭካኔን የሚያባብል አንድም መንፈስ አይኖርምና። ከሁሉ በላይ የሃይማኖት ነፃነቱን ለመቀማት ማንም ሊተባበር አይችልምና። ነገር ግን በሁሉንም መሥፈርት የቀደመ፣ ብልህና ሥልጡን አመራሩ ተልዕኮውን በአረም አላስዋጠውም። ይልቁንም በጠራ መስመር መራው እንጂ ….። ከዚህ ጋር ተያይዞ መታዬት ያለበት ቁም ነገር በሰላማዊ ትግል ውስጥ ምላሽ ያለማግኘት ጉዳይ ዕድሜ ጠገብ ሲሆን፤ ከፍ እያሉና እያደጉ የሚሄዱ ማዕቀቦች መኖራቸውን መዘንጋት የለብንም። መብቱን የተቀማ ግን ህግን የጠበቀ፤ ብስጩነትን የተቆጣጠረ ግን ሙት መሬት ላይ ሆኖ ድልን ያለመ ብርቱ ሰላማዊ ተጋድሎ ከዚህ ጠንከር ብሎ ሊሄድ እንደሚችል ልብ ሊባልም ይገባዋል። እኔ በዕድሜዬ እንዲህ ያለ ምራቁን የወጣ ብርቱ፤ ተከታታይነት ያለው፤ ትጉህ፤ ንቁ፤ የመሪና የተመሪ ግንኙነት የሰመረበት ጤናማ ሂደት አይቼ አላወቅም። ከድንቅ በላይ ነው። ለታሪክ ሥጦታ ነው! በራስ የመተማማን ብቃቱ ከተነሳበት የእውነት ማህደር ይቀዳል። ስለዚህም – አይወዛወዝም።
ዬወያኔ ሃርነት ትግራይ የእስልምና እምነት ተከታዮችን ለቃቅሞ መሪዎችን ከማሰሩ በፊት ጉዝጓዝ ሰርቶለት ነበር። የክርስትና እምነትን ለማስነሳት። ይህን በድንገት የመሠረተው ጉዳይ አልነበረም። የረጅም ጊዜ ዕቅዱ ነበር። ባዶ ቦታ ላይ፤ ምንም ሰው በሌለበት ቦታ ላይ፤ መስጊድ ሲያሰራ ሲያበረታታ የነበረው – ለስውር ፍላጎት ማመሳከሪያነት ነበር። ስለምን? እሱ ለፈጠረው – ለፈበረከው ክስ ቅድሚያ ቬሎ ያስፈልገው ስለነበር። ይሄው ቀድሞውንም ኢትዮጵያን የእስልምና እምነት ተከታይ ሀገር ለማደረግ የታሰበ እርምጃ ሲወሰድ ነበር ለማለት። ግን ወያኔ የሠራው የድቡሽት ትዕይንት ሁሉ አሞራው በረረ ቅሉም ተሰበረ ነው የሆነበት።
ሥነ ጥበብ የመንፈስ ሃብትነቱ እያዋዛ ወደሚፈልገው በጎ አቅጣጫ የመግራት ረቂቅ ልዩ ክህሎቱ ነው። እኔ የማዬው „የድምጻችን ይሰማ“ የሶስት ዓመት ታሪካዊ መምህር አንቅስቃሴም የዚህን ያህል ለእኔ ከልቤ የገባ መሆኑን በድፍረት እናገረዋለሁ። እኔን ኮትኩቶ ከጎኑ ያሰለፈ፤ የአቅም ጥሪትን በአግባቡ የመምራትና የማስተዳደር ልቅና ያለው ሆኖ ነው ያገኘሁት። አንድ እንቅስቃሴ እኮ በተግባሩ ነው የሌላውን ቀልብ መግዛት የሚችለው። የሚወደደውም በተግባሩ ነው። እንዲህ ዓይነት በጨዋነት – የሰከነ፤ ዘመኑን – ያዳመጠ፤ የአብሮነት ሥነ ምግባርን – ያልጣሰ፤ የኢትዮጵያዊነት ረቂቅ ብልጹግ ቀለማም መንፈስን ያልተፃረረ፤ ልዑቅ – በተግባር የከበረ፤ በእድገት የጎለመሰ ረጅም ቆይታ ያለው ሰላማዊ እንቅስቃሴ በታሪኳ ኢትዮጵያ ኖሯት አያውቅም። የታደለ!
ስለሆነም መለኪያችን ሆነ መመተሪያችን እንዳአለ የአካሉን አጠቃላይ እንቅስቃሴና ወላዊ ትልም ተግባራዊነት ላይ ሊሆን ይገባዋል የግድፈት መለኪያችንም እንጂ በእስልምና ዕምንት ዙሪያ በዬሰከንዱ አንድ ሁለት ከዚህም የበረከቱ ቀንጣና ተናጠላዊ የግለሰቦች ከመስመር የወጣ ግድፈት በተፈጸመ ቁጥር፤ ዜናዎችን ባደመጥን ቁጥር ያን እዬመዘዙ ከዚህ ግዙፍ የነፃነት እንቅስቃሴ ጋር ስጋትን መቋጨት ወይንም ጥቂትም ቢሆን ማነካካት የተገባ አይደለም። ዛሬ እናቴ እንኳን ይህን መሰል መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ያለው አካል የአንድ ማህጸን ልጆችንም አወቀዋለሁ ለማለት ገደብ አለው። ስለዚህ ከሚጠበቀው በላይ የሠራና ያለዬነውን ደመ ግቡ ሥነ ምግባር ያሳዬን ውድ ብሩኽ የነፃነት ተጋድሎ እንቅስቃሴ አካላችን ስለሆነ ክብሩን ልንጠብቅለት፤ ለመንፈሱ ልንጠነቀቅለት ይገባል ባይ ነኝ። ዕሴቱ ከፍ ያለ ነውና። በሚመለከተው ጉዳይ ብቻ እንጥቀሰው … በሚያይዘው ኩሁነት ብቻ እንጥራው …
ፍላጎታችና ድጋፋችን መሰረት ይኑረው! ተጎድተዋል ወይ!? ጥያቄያቸው ትክክለኛ ነው ወይ? ይህን የነፃነት ትግሉ አካል ነኝ የሚል ወገን መመለስ ይኖርበታል። መልሱ አዎን ተጉድተዋል ነው። እንዲያውም የወያኔ ሃርነት ትግራይ በስውር በሚሰራው ሴራ ሀገርና ህዝብ የመበደሉ ገመና እንዳይጋለጥበት ካሳ ነው ያደረጋቸው። ይህን ልብ ልንለው ይገባል። ዬብዙ ሀገር ዲክታተሮች እዬተጠቀሙበት ያለውም በዚህ ስበብ ነው። ሁሉም እጣቱን የሚጠነቁለው ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ ነው። የበለጸጉ ሀገሮች የሰብዕዊ መብት ረገጣ ለዛውም በ21ኛው ምዕተ ዓመት እዬተመለኩቱ ዓይናቸውን በዓይነ እርግብ ሸፍነው ዲክታተሮችን ከጎናቸው ቁጭ አድርገው የሚያበረታቷቸውም በዚህ ምክንያት ነው። በተለይም ጋዜጠኞች የነፃነት ፍለጋ ጉዞና ሌላውን ደባል አጥፊ ፍላጎት መቀላቀል አይገባቸውም። ስለምን? ጋዜጠኝነት የማሰብ ጥበብ ልቅና ነውና። ማለት የሰው ልጅ የማሰብ ልቅናው መለኪያ አፍቅሮተ ሰው ነውና። አፍቅሮተ ሰው ደግሞ የሰውን ልጅ ተፈጥሮ ከማክበር ይነሳል።
ፍላጎታች ሥር አለው። ሥሩ አንድ ግንድን ፈጥሯል። ነፃነት የመፈለግ ጉዞና ራዕይ። ነፃነት የመፈልግ ጉዞ ዬሥሩ ሴል የሴቶች እኩልነትን፤ የህፃናት ጥበቃና ፍትህን፤ የሙያ ክብራዊ ዕውቅና፤ የአዛውንታት ክብርና ሞገስነት፤ የወጣቶች የተተኪነት መብት፤ የዘመኑ ሥልጣኔ እኩል ነፃነታዊ ማህበራዊ ተጠቃሚነት፤ የቤተሰብ አክብሮትና ጥበቃ፤ ሙያን የመምረጥና በፈለጉት ሙያ የመሰማራት ያልተሸራረፈ ነፃነት፤ በፈለጉት አካባቢ ሰርቶ የመኖር ነፃነት፤ ሃብት የማፍራትና የማስተዳደር እንዲሁም ባፈሩት ሃብት የመጠቀም ነፃነት፤ የመንፈስ ሃብት የማስፋፋት፤ የማሰራጨትና የማሳደግ ነፃነት፤ የዕምነት እኩልነት ነፃነት፤ ዕምነትን በዕምነቱ ዶግማና ቀኖና የማስተዳደር ነፃነት፤ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ ብቻ ሳይሆን በሃሳቡ ዙሪያ የመወያዬት፣ የመምከር የመተቸት ነፃነት፤ በሀገር ጉዳይ ላይ የመወስን ነፃነት፤ የመደራጀት – የመሰብሰብ – መሪዎችን የመመረጥና እራስም የመመረጥ የማስተዳደር ነፃነት፤ ድጋፍና ተቃውሞ የማቅረብ ነፃነት፤ ብሄራዊ ሰንድቅዓላማን የፈለጉትን ያህል ያልተገደበ የመውደድ ነፃነት፤ የሀገርና የክ/ሀገራት የወሰን ድንበር ውርሳዊና ተፈጥሯዊነት የመጠበቅ ነፃነት፤ በሀገር ንብረትና ሀብት እኩል ተጠቃሚ የመሆን ነፃነት፤ ትክክለኛ መረጃ የማግኘት ነፃነት፤ የሃብት ድልድና ሥርጭት የእኩልነት ነፃነት፤ የባህል ነፃነት፤ የፍልስፍና የሳይንስና የምርምር ነፃነት፤ የህግ የበላይነት ነጻነት ወዘተ ወዘተ …. ወዘተ …
ስለዚህ አንዱን ሥር ስንነካው ሌላው ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ብቻ ሳይሆን፤ ያሰምመዋል፤ ያቆስለዋል፤ ያጠወልገዋል። በተዘዋዋሪ አይደለም በቀጥታ – በእያንዳንዱ የፍላጎታችን ሥር ሴል ላይ ጥቃት ይፈጽማል።
ህም! „ለሚያራግቡት ደህና አጋጣሚ አገኙ“ ለሚባለው ከእውነት ያልተነሳ ቀልብ ሳቢያ ፍለጋ እንደማሰነ ነው ኑሮው የሚጠናቀቀው። ሳቢያ ደግሞ መንገዱ አጭር ነው። ወርዱም – ጥብቆ። በራሱ ጊዜ ይከሽፋል። በራሱ ጊዜ አጀንዳው ይሟሟል። ሳቢያ ቆይታው ለቅጽበት ነው። ለማደግ – ድፍረት የለውም። በዬትኛው አደባባይ ነው የሚታዩት?! አንገታቸውን ደፍተው ውስጥ – ለውስጥ አዩኝ – አላዩኝ ብለው ተሽሎክሉከው ነው እንደ እባብ መሬት ለመሬት ሲሄዱ የሚታዩት። ስለምን? የሚያቀርቡት አንዲት ሽራፊ የሃቅ ብናኝ የላቸውም። 30 ሺህ ፍትህ ጋዜጣ ሲቃጠልና ቁርሾው አገርሽቶ ለእስር የበቃባት ተሜ አፈር በሆኑት ሄሮድሳቸው ነው። ይህ እውነት አይደለም ለእነሱ። እሬሳ ታቅፈው ዜናውን ኢሳት ሲያቀርብ የተሳሰተ ማሰረጃ ሰጠ ብለው ሲከሱ ነበር። ከዚህ የበለጠ የተገለበ ጉዳይ ምን አለና?! በአደባባይ „ከአዲስ ዓመት በፊት ሥራ ይጀምራል መሪያችን“ አይደለም ያሉት? ግን ሆነ? አፈር ነው የጋጠው ቅጥፈታቸው። እነሱ በአስተሳሰብ ድህነት የተሸፈኑ ናቸው – ሠረገላቸውም ድንብስ። በጎጠኞች የህሊና ሰሌዳ ላይ ያለው ባዶ ቀለሃ … በቻ —–
ነገር ግን ምክንያታዊ የሆኑ አምክንዮች ጭብጣቸው ሆነ ዘላለማዊነታቸው ታሪክን በማብቀል – ነገን አሳምሮ በመስመቸት የበለጸገና የዳበረ ተመክሮን አዝምረው እውነትን በዓምድነት ያበራሉ። እውነት ቀጥ ያለ ደፋር ጧፍ ነው። ስለዚህ የአንድ ሰሞን አታሞ ዘላቂ ፍላጎትን ሊነቀንቀው አይገባም። እንዲያውም እንደ አሮጌ ቆርቆሮ ሲጮሑ ገዢ መሬት ላይ ያለው አሸናፊው ሥነ ልቦና ይደላደላል። ማንነት አለውና! ኢትዮጵያዊነት!
ለማንኛውም „የድምጻችን ይሰማ“ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት አንድ የነፃነት ማሰከበሪያ ፕሮጀክት ነው። ወያኔ ሃርነት ትግራይ አቅም ኑሮት ለጥያቄው መልስ ቢሰጥ፤ ከጀርባ ሆኖ የሚጎትተው አንዳችም ስውር ፍላጎት ስሌለው ታሪክን በተግባር አቅልሞ በምስራች ይሰናበታል። ይህ ማለት ግን ነፃነት በመከነባት ሀገር የሚኖሩ ዜጎች ለነፃነታቸው በፖለቲካ አስተሳሰባቸው ከሚፈልጉት የፖለቲካ ድርጅት ጋር ሆነው ትግላቸውን አያደርጉም ማለት አይደለም። የራህቡ – የመገለሉ – የመታረዙ – የሞቱ ሲሳይነታቸው እንደ ዜጋ የእስልምና እምነት ተከታዮችንም ታዳሚ የደርጋቸዋልና። ከዚህም ባለፈ የእስልምና እምነት አባላት የሆኑ ሴቶች – በፆታቸው፤ ወጣቶች – በዕድሚያቸው፤ የሙያ ሰዎች – በሙያቸው፤ የሥነ- ጥበብ ሰዎች – በጸጋቸው፤ የከተማ ነዋሪዎች በከተማ – የገጠር ነዋሪዎች በገጠር ነዋሪዎች ተደራጅተው እንደ ማንኛውም ዜጋ የቡኩላቸውን ድርሻ ይወጣሉ። ይህ ቀጣይ ነው። ከዚህም ባለፈ በተለምዶ በሚታወቁት በወበራ በሥራ ህብረት ወይንም በደቦ፤ በእድር፤ በቁቤ መሰሉን ተግባር በማህበራዊ ኑሯቸው ይከውናሉ። ነገም ቢሆን በማናቸውም የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊ የተሳትፎ ጎራዎች ሁሉ እኩል የመሳተፍ መብትም ግዴታም ይኖርባቸዋል። ይህን ኃላፊነት በብቃት የመወጣት አቅማቸው ሆነ ሥልጡኑ ሥነ ምግባራቸው በአደባባይ ታይቷል -ምስክር ነው። ያደርጉታል። ያኮራሉና።
መጠነ ሰፊውን የነፃነት ጥያቄ የእኔነት አቅም እንስጠው። በቅንነት ወደ ውስጥ እንዬው። በስጋት ቅንጥብጣቢ ጉዳዮች ፍሬያማ ተልዕኮው እንዳይጎዳ እንጠንቀቅለት። ወያኔ ሃርነት ትግራይ መጫሪያ መለማማጃ ማድረጉ ላይበቃ፤ እኛም ጥግ ከነሳናቸው ሁለት ያጣ የሁለት ሀገር ስደተኛ ይሆናሉ። በወያኔ ሃርነት ትግራይ ጥቃት የሚፈጸምበት ተቋም ወገን ትንፋሻችን ሊሆን ይገባል። እናስጠጋው! ጠረኑ እኛን – እኛን ስለሚል። አቅምም ነው በቅጡ መያዝም ማስተዳደርም ከቻልን።
ኢትዮጵውያን እጅግ ታላቅ ግዙፍ የወል ኪዳናዊ አምክንዮ አለን። „ሰው የመሆን፣ ኢትዮጵያዊነታችን ከጎጣዊ የበታችነት ወረራ የማስመለስ ፣ ነፃነትን – የመናፈቅ፣ ባለሀገር የመሆን፣ ዬወጥ ሰንድቅዓላማችን ብሄራዊ ክብር የማስመለስ፤ የጋራ የሆነ የሚያስማማ ብሄራዊ መዝመሩ ባለቤት የመሆን፤ በህዝብ በጸደቀ ህገ መንግሥት ድምጽ የሚመራት የእኩልነት የተስፋ ሀገር የማግኘት፤ ተናፋቂዋን ሀገራችን የርትህ ባዕት የማደረግ፣ የተጣሱ ደንበሮችን ተፈጣሯዊነት የማስጠበቅ፤ ፍቅር ወተታችን ምህረት ማራችን፣ አብሮነት ተክሊላችን የማደረግ ራዕይ የወልዮሽ አቅጣጫችን ነው። ግን እንዲህ ዓይነትን ችግሮች ሲያፋጥጡን በጋራ የመቀበል አቅም፤ መራራውን ዘመን አብሮ የመሆን ውስጣዊ ፈቃድ ከኖረን ብቻ። የማይናወጽ ዘላቂ ፍላጎት ከኖርን ብቻ። በመሰረታዊ የችግሩ ምንጭ መስማማት ከቻልን – ብቻ። ለተጎዳ – ለተገለለ ውስጣችን መገበር እስከፈቀድን ድረስ ብቻ።
እጅግ የማከብራችሁ ወገኖቼ ቆዳችን የውስጥ አካላችን መሸፈኛ ብቻ ነው። ጸጉራችንም የአንጎላችን መሸፈኛ። የውስጡ ልባችን፣ ኩላሊታችን፣ ደማችን፣ ሳንባችን፣ ትንፋሻችን ጠረኑ ሰውኛና ወጥ ነው። ሰውኛነት ደግሞ ሰብዕነትን ያዳምጣል። „የድምጻችን ይሰማ“ መሪዎች ኢ – ሞራላዊ ግፍ ከውስጣችን እናስገባው። የውስጣችን ማተብ እናድርገው። ከሂደቱ፤ ከተግባሩ፤ ከስልቱ፤ ከሥልጣኔው፤ ከብልህነቱ፤ ከስተዋይነቱም ለመማርም እንፍቀድ። ግምገማችን፣ እድምታችን ሆነ ዕይታችን በወላዊ ፍላጎቱና ግብዕቱ ላይ እንጂ በተነጠላዊ ግለሰባዊ ቅንጣቶች አይሁን እላለሁ – እኔ። …. በምንም ሁኔታ የትም ሀገር ቀርቶ ኢትዮጵያው ውስጥም በግልሰብ ደረጃ ይህ ነገር ቢከሰት ከጽኑው አቋማችን ፈቅ አንበል።
ናይጀሪያ ላይ እኮ የቦኮ ሃራም ቡድን የተወሰነው ክፍል ተቆጣጥሮ እዬጨፈረ ነው ያለው። ነገር ግን የናይጀሪያ ተወላጆች የእስልማና እምነት ተከታዮች የሆኑት በዚህ አልተፈረጁም። የሚደግፉት ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት ቢቻልም ማንኛውም ናይጀሪያዊ የእምነቱ ተከታይን ግን በጎሪጥ አይታይም። …. እንኳንስ አንዲት ጋት መሬት ኢትዮጵያ ውስጥ የሌለው። እንዲያውም ጋት መሬት እንዲኖረው ይህ አሸባሪ ቡድን ወያኔ ይፈልጋል። ለወያኔ ሃርነት ትግራይ የሚቀርበው እኮ የህዝብ ኃላፊነት አይደለም እእ! ቅዠቱን ማስፈጽም ነው “ የታላቋ ትግራይ ህልመኛነት“ አሽዋ ሞልቶ እህል ያለ፤ ዬሃውዚን ህፃናትን – ነፍሱጥር – እናቶችን፤ አዛውንታትን አስደብድቦ ድጋፍ ያፈሰ አረመኔ እኮ ነው ወያኔ ማለት። ወያኔና አሸባሪነት፤ ወያኔና ስጋትን መፈብርክ መቼ ተፋተው ሲውቁ ነውና። ኢትዮጵያዊ እስልምና እምነት ተከታዮችን ሰላም የነሳቸውና ሰላማቸውን ያሳጣቸው እሱ እራሱ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ነው። የወያኔ ሃርነት ትግራይ አንድ የአልሸባብ ጉድብ ቢደረምስ „የድምጻችን ይሰማ“ አካላዊ ቅስም አይሰበረም። ስለምን? ግንኙነት – ስሌለው። ይልቁንም እንደ ሰው ዬዓለምን ሰላም የነሳው፣ መኖርን በስጋት ያስዋጠው፤ ሃይማኖታቸውን ተገን አድርጎ ዬትውልድን ተስፋ ጥቁር ለማልበስ በሚተጋው፤ የሃይማኖታቸውን ክብር በማጥቆር በጥርጣሬ በጠቀለለው „የአሸባሪ ቡድን“ ክንፉ ሲሰበር፤ ሲደመሰስ ደስታውና የምሥራቹ ከእኛ ጋራ ነው የሚሆነው። እምነት ተወዶና ተፈቅዶ የሚቀበሉት የመልካም ነገሮች ሁሉ የነፃነት ፍሬ ነው። ሃይማኖት ሰብዕዊነት የፈጠረ ነው፤ ተፈጥሯዊነትን ያረቀቀ – ያጸደቀ ነው ነው እንጂ፤ የሰው እርድ ናፋቂ አይደለምና።
ክወና „ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም“ ይላሉ አቨው ቀደምቶች። ገና ዓለምን በሽብርተኛ ተግባሩ እዬናጠው ያለው ISIS ዬእስልማና እምነት ጽንፈኝትን የዓለም የስጋት ምንጭ ነው ተብሎ፤ የእምነት ነፃነታቸውን በግፍና በማንአለብኝነት የተቀሙት የነፃነት ራህብተኛ ወገኖቻችን የጠራ ጥያቄያ ቀጣይ እንቅስቃሴ ላይ እኛ እራሳችን ስጋት ማከል አይገባንም። እነሱም ከዚህ ጋር ሊያያዝ ይችላል ብለው፤ ወይንም የዚህ ድርጅት ኢትዮጵያዊ አባላት ተገኙ ወደፊትም ሊኖሩ ይችላሉ ብለው “ድምጻችን ይሰማ” አንድ ጋት ወደ ኋላ ከተልዕኮው ሊያፈግፍግ አይገባውም ባይ ነኝ። አይደለም ይሄ የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና ዛሬ “ድምፃችን ይሰማ” ከሚመሩት መሃከል የዚህ ድርጅት አባል አለ ብሎ ዓለም ዓቀፍ የስለላ ድርጅት ቢያረጋግጥ እንኳን “የድምጻችን ይሰማ” የሚልዮኖች ድምጽ ለእምነት ነፃነት ትግል ሊቋረጥ አይገባም። በዬደቂቃው እስር ሳይሆን ያን መራራ ስቃይ የተቀበሉ፤ የተደፈሩም መሪዎችን ማሰብ በአጽህኖት ይገባዋል። ንቅናቄው በህይወቱ እኮ የተከሰቱ በርካታ ፈታኝ ነገሮች አሉ። ጽንፈኛ መንፈሶች ነበሩ “ድምጻችን ይሰማ” ግን ክብር ነስቶ ጥሏቸው ነው የተጓዘው። ለደቂቃም ቀልቡን አልሰጣቸውም። ዞር ብሎም አላያቸውም። ቂጡ እንደ ወለቀ እንሰራ አውልቆ ሲያስቀራቸው ተመልክተናል። ትቢያ ነው ያለበሳቸው። ይህ ጥንካሬው በቀጣዩ ተስፋ ላይ ማዕቀብ እንዳይኖር ያደርገዋል።
እኔ በግሌ ሁልጊዜም ከድምጻችን ይሰማ መንፈስ ጋር መንፈሴ ውል አስሯል። ጥያቄያቸው በአግባቡ መልስ ሊያገኝ ይገባዋል ባይ ነኝ። ስጋትም የለብኝም። ነገም ከነገ ወዲያም ዘለግ አድርጌ በግለሰብ ደረጃ የሚፈጠሩ ግድፈቶች እንደሚኖሩ አስባለሁ፤ ነገር ግን ከ„ድምፃችን ይሰማ“ ተልዕኮ ጋር ግን አይደባለቅብኝም። ግልጽ ጥያቄ ነው ጥያቄው። ለዛውም በአንድ ስብሰባ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባ የነበረ፤ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ግን ያሾለከው ብርቅዬ ዕድል። „ድምጻችን ይሰማ“ ድምጹ ሊደመጥ የሚገባው ብቁና የነፃነት ትግሉ በኸረ ጉልበታችን ነው! የዕምነት ነፃነት የራበው ማስታገሻው ጥያቄው መልስ ሲያገኝ ብቻ ሲሆን „ድምፃችን ይሰማ“ ትግሉን አጠንክሮ በሚያደርገው ጉዞ እኛም በአጋርነት መሰለፍ ይገባናል። በተለይም ጋዜጠኞች፣ የጥበብ ሰዎች፣ የሰብዕዊ መብት ረገጣ የሚጎረበጥው ዜጋ ከጎናቸው ሊቆም ይገባል። ኢትዮጵያዊነትን የሚጠይቀው በኽረ ጥያቄ የመመለስ አቅም „ሰው“ መሆንን ብቻ ነው። ቅመሙ የተሠራው ከእኔም ከእርሰዎ ነውና – ኢትዮጵያዊነት!
ለነበረን ውብ ጊዜ አመስግኜ መሸቢያ ህልም ተመኝቼ ልሰናበት። ደህና ሁኑልኝ – የኔዎቹ።
ዓራት ዓይናማው መንገዳችን ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
The post ጋዜጠኝነት የማሰብ ጥበብ ልቅና ነው! – ሥርጉተ – ሥላሴ appeared first on Zehabesha Amharic.