ኢትዮጵያ የሚለው ስም የወጣላት ከ4000 አመት በፊት እንደሆነ ይነገራል። የስም አወጣጡም ከኢትኤል እንደተሰየመ የታሪክ ተመራማሪው ዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ ግለጽ በሆነ መልኩ አስቀምጠውታል። ከዛሬ ጀምሮ አንተ አብራም ሳይሆን አብርሃም ትባላለህ። አብርሃም ማለት፡- የብዙሃን አባት ማለት ነው ብሎ እግዚአብሔር ስሙን እንዳወጣለት ሁሉ… አንተ ከዛሬ ጀምሮ ከፋ ሳይሆን ጴጥሮስ ትባላለህ። ጴጥሮስ ማለት፡- አለት ማለት ነው። በአንተ አለትነት ቤተክርስቲያን እመሰርታለው ብሎ እግዚአብሔር ለጴትሮስ ስምን እንዳወጣለት ሁሉ… የኢትኤልን ከዛሬ ጀምሮ ኢትኤል ሳይሆን ኢትዮጵ ትባላለህ። ኢትዮጵ ማለት የቃሉ ፊቺ ኢቲ ማለት ቢጫ ወርቅ… ዮጲ ማለት ደሞ ስጦታ ማለት ሲሆን …የኢትዮጵ ትርጉሙ ቢጫ የወርቅ ስጦታ ማለት ነው። ከኢትዮጵ ኢትዮጵያ የሚለው ስያሜ ተገኝቷል። ኢትዮጲ የመልከ ጸዲቅ ልጅ እንደሆነ እና ኢትዮጲያ የሚለውን ስም እግዚአብሔር እንዳወጣለት የታሪክ ሙሁሩ ዘርዝረው አስረድተውናል። የዚህን ዝርዝር ሁኔታ በተብራራ መልኩ ለማወቅ የምትፈልጉ ዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ገለጻ የሰጡበትን እና በኢትዮጵያ ታሪክ ዙሪያ የጻፉትን መጽሐፍ ብታነቡ ሰፋ ያለና የተብራራ ነገር እንደምታገኙ ለመጠቆም እወዳለው።
ኢትዮጵያ በመጻሀፍ ቅዱስ ላይ ከ 44 ግዜ በላይ የተጠቀሰች በእግዚአብሔር ስራ ውስጥ በተደጋጋሚ የምትገለጽ በህገ ልቦና ግዜ ህግ ለሙሴ ሳይሰጠው በፊት እግዛአብሔር የምትመልክ አገር ነበረች። ህገ ኦሪት ለሙሴ ሲሰጠው ህገ ኦሪትን በመቀበል በህገ ኦሪት የኖረች አገር ነች። በህገ ወንጌል ግዜም ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህች ምድር መቶ የወንጌልን ህገ አዲስ ኪዳንን ሲሰጥ ኢትዮጵያን ከእስራኤል ቀጥላ ህገ ወንጌልን የተቀበለች ተቀበላም ጠብቃ ያቆየች አገር እንደሆነች ታሪክ ይነግረናል።
እስልምና ነብዩ መሐመድ በተነሳ ወቅት ከአገሩ ሰወች ከቆሬሾች ታላቅ ተቃውሞ በተነሳበት ግዜ ሂዱ ወደ ኢትዮጰያ ህዝብ የማይበድልባት መንግስት ያለባት አገር ነች ብሎ የራሱ ዜጎች ሊገሏቸው እንደሚችል አውቆ ያቺ አገር ግን ሰው እንኳን አይበደልበትም ብሎ የርሱ ወገኖች የሆኑትን ሰወች በመላክ እንዲጠለሉ አድርጓል። ነብዩ መሐመድ ቆሬሽችን አሸንፎ ከመካ መዲና የእስልምናን እምነት በይፋ ሲያውጅ የመጀመርያን አዛን ያለው ቢላል የተባለው ኢትዮጵያዊ መሆኑ በእስልምና ታሪክ ተጽፎ እናገኘዋለን በዚህም ከሳውዲ አረቢያ ቀጥላ እስልምናን የተቀበለች አገር ኢትዮጵያ መሆና ታሪኮች ይነግሩናል።ሁለት ታላላቅ እምነቶችን ቀድማ በመቀበል ከአለማችን ልዩ ያደርጋታል።
ቅዱስ ያሬድ ድጓ፣ ጾመዱጓ፣ ምዕራፍ፣ ዝማሬ፣ መዋለት፣ የተሰኙ ድንቅና መለኮታዊ ጥበብን የተላበሱ መጽሐፍን በመጻፍ አለምን ያስደመመ ነው። እንደ ቅዱስ ያሬድ ታላቅ ሊቅና ጥበበኛን ያበቀለች አገር ናት። በዚህም የመላእክትን ዜማ የምታዜም የመላእክትን ሽብሻቦ የምታሸበሽብ ጥልቅ ምስጢር የሚነገርባት፣ የሚታይባት፣ እና ጥልቅ ምስጢር ያላት አገር ናት።
አክሱምን ያነጹ፣ ቤተ ጊዮርጊስን እና በዙርያው ያሉትን ቤተ ክርስቲያንን ከወጥ ድንጋይ ፈልፍለው ጥበብን የገለጹ፣ የሶፍ ዑመር ዋሻ ብዙ ምርምርን የሚጠይቅ ድንቅ ዋሻ የሚገኝባት፣ የሃረር ግንብ በጥንታዊ ጥበብ የታነጸ፣ የጢያ ተክል ድንጋይ ተመራማሪወችን ብዙ ያስባለ፣ ድንቃ ድንቅ የፈጠራን ጥበቦች ለአለም ያበረከተች፣ አለም የተደመመባት፣ የቅርስ መሃደር፣ ከአስራ አራት በላይ በአለም ቅርስነት ያስመዘገበች የድንቅ ሚስጥር ባለቤት ይቺው አገር ናት።
ሉሲ (ድንቅነሽ) እና ሌሎችም የሰው ቅሪት አጽም በተለያዩ አለማት ከተገኙ ቅሪቶች በብዙ ዘመን ቀዳሚነት ያለው የተገኙት ይህቺው ሚስጢራዊ አገር ውስጥ ነው። የአለም ሳይንትስቶች የሰው መገኛ ኢትዮጵያ እንደሆነችና ከኢትዮጵያ ተነስተው ወደተለያየ የአለማችን ክፍል በመሄድ አሁን ላለው የሰው አሰፋፈር መሰረቷ ይችው አገራችን መሆናን አፋቸውን ሞልተው እየተናገሩ ነው።
በቅኝ ያልተገዝች፣ ለመላው አፍሪካ የነጻነት በር ከፋች የሆነች፣ ለጠላት አለሸነፍ ባይነትን፣ ለውጪ ወራሪ አልገዛ ባይነትን፣ ያሳየችው፣ የሰው ክብር የማትፈልገ የራሳንም ክብር አሳልፋ የማትሰጥ፣ ቅኝ ገዢወችን ለመጀመርያ ግዜ ያንበረከከች ይችው ሚስጢራዊ አገር ነች።
የውጭ ጠላት የክፋት ድንጋይ ቢፈነቅሉ የማትሸነፍ፣ የጥፋት ቦንብ ቢያወርዱ የማትንበረከክ፣ አገር ስትሆን ሁል ጊዜም ከፈተኛ ጉዳት የሚደርስባት በአገር ጠላት ብቻ ነው። እነዚህ አገር በቀል አንባ ገነኖች ሕዝባችንን ይበድላሉ፣ ያሰቃያሉ፣ የሚሰቃየውም ዜጋው የሚያሰቃየውም ዜጋው በመሆኑ ጉዳቱን አሳዛኝ ያደርገዋል። ለአገር አሳቢ በመምሰል ስህተታቸውን እንደትክክለኝነት ይነግሩናል። ወንድሙን እየገደለ እንደ ጀግና ይፎክርብናል። ጥቂቶች ስልጣናቸውን ለማቆየት ባስታጠቋቸው ጢቂት ወታደሮች ሚሊዮኖችን እረግጠው ጀግና ነን እያሉ ሊኖሩ ይፈልጋሉ። እንግዲህ የገባው ይግባው ይህቺን አገር ሊያጠፋት የሚችል ማንም የለም። ትግሉ ከህዝቡ ጋር ብቻ ሳይሆን ከእግዚአብሔርም ጋር ስለሆነ ሊታሰብበት ይገባል። ካለበለዛ ግን ከሰውነት ክፍል አንዷ በካንሰር ከተጎዳት ቆርቶ ማስወጣትና ከዛ በኋላ ጤነኛ ሆኖ መኖር ስለሚያስፈልግ ከላይ ተቀምጠው ህዝባችን ላይ ካንሰር የሆኑትን ቆርጠም ማስወገድ ግድ ይለናል።
የንጽሃኑን ሕዝብ መብት እረግጠው የማስተዳደር ፍላጎት ማሳየት እና ለርካሽ ፖለቲካ ጥቅማቸው ይችን ሚስጥራዊ የሆነች አገርን ለማፍረስ ህዝቦቻንም ለማጥፋት ይጥራሉ። ነገር ግን ሊያጠፋት የተመኙ ሁሉ ሲጠፉ እንጂ ስትጠፋ አላየንም። ሰፊውን ህዝባችንን ሲበድሉ እና ሲያሰቃዩ የሚኖሩ ገዢዎች የዚች አገር ጠባቂ የእጃቸውን ቅጣት ሲስጣቸው እና ሲያጠፋቸው የምናይበትን እውነተኛ የሆኑትን ታሪኮችን እያየን ያለፍንበት ግዜ ብዙ ናቸው። ዛሬም የህዝብ ጠላት የሆነ ስለርካሽ ፖለቲካቸው ብቻ በማሰብ ይችን አገርን ሲበድሉ እና ሲጨቁኑ አመታቶችን አስቆጥረዋል። ይህቺ አገር ለማጥፋት ማሰብ ለመጥፋት የቀረቡ የጥፋት ልጆች እንደሆኑ ለመናገር እወዳለው። ሚስጥርን የሚያውቅ እግዛአብሔር ብቻ ነው ሚስጢርን የሚፈታ እግዛአብሕር እና እርሱ የመረጣቸው ቅዱሳኑ እንደሆኑ እናውቃለን። ይቺን አገር ጠላቶች ማንበብ ወይም ማወቅ አይችሉም። ስትታይ አቅም የሌላት የምትመስል… ጠላት ሲመጣ እሳት ሆና የምትፋጅ ናት። ብዙ ተመራማሪወች አዳዲስ ግኝቶች እያገኙ አዲስ ነገር የሚናገሩላት ድንቅ አገር በእግዚአብሔር የምትጠበቅ ይህቺ አገር ምስጢር ናት።
ይቆየን
ከ-ከተማ ዋቅጅራ
13.04.2015
Email- waqjirak@yahoo.com
The post ይህቺ አገር ምስጢር ናት!!! – ከ-ከተማ ዋቅጅራ appeared first on Zehabesha Amharic.