Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የሳይንቲስቱ ልጅ ጥያቄ –ከዳንኤል ክብረት (ዲ/ን)

$
0
0

ባለፈው እሑድ፣ የትንሣኤ ዕለትማልዳ ነው ከዕንቅልፏ የተነሣቺው፡፡ እናቷ ቤተ ክርስቲያን አድራ፣ አባቷ ደግሞ ሌሊት ከውጭ ሀገር ገብቶ ደክሟቸው እንደተኙ አልተነሡም፡፡እርሷም በጠዋት የተነሣቺው ጓደኛዋ አደራ ስላለቻት ነው፡፡ ‹‹የቴሌቭዥን የትንሣኤ ፕሮግራም የተቀረጸው እኛ ቤት ነው›› ብላ አጓጉታታለቺ፡፡የተነሣቺው ጓደኛዋን በቴሌቭዥን ለማየት ስትል ነው፡፡ ደግሞ ‹ዘፈን ምናምን አቅርቤያለሁ› ብላታለቺ፡፡ የጓደኛዋ አባት ‹ፍቅርእዚህም እዚያም›፣ ‹ትሄጅብኛለሽ› እና ‹ፍቅር በኪችን ውስጥ› የተሰኙ ሦስት አስቂኝ የፍቅር ፊልሞች ላይ የሠራ ‹ታዋቂ አርቲስት›ነው፡፡ ጓደኛዋ እንደነገረቻት ከሆነ የበዓሉ ፕሮግራም እነርሱ ቤት ሲቀረጽ የቀረ አርቲስት የለም፡፡ በዓሉ ራሱ ሕዝቡን ሊያዝናናስለማይችል ‹ዘና እንዲያደርጉት› ተብሎ ቀልደኞቹ ሁሉ እነርሱ ቤት መጥተው ነበር፡፡
daniel
ከቀረፃው ማግሥት ጓደኛዋ ትምህርትቤት ስትመጣ የታዋቂ አርቲስቶችን ፊርማ በየደብተሯ ሰብስባ መጥታ ጓደኞቿን ሁሉ ስታስቀናቸው ነበር፡፡ በርግጥ ክፍል ውስጥ እርሷናጓደኞቿ ትምህርታቸውን ረስተው የአርቲስቶችን ፊርማ ሲያደንቁ ያዩዋቸው መምህራቸው እንደ መገሰጽ ቢያደርጉም፣ እንደመስማት ያላቸውተማሪ ግን አልነበረም፡፡ ምክንያቱም እርሳቸው ታዋቂ አይደሉማ፡፡ ደግሞ መምህር ከመቼ ወዲህ ነው ታዋቂ የሚሆነው፡፡ ይኼው ስንቱአርብቶ አደርና አርሶ አደር ሲሸለም መምህር መቼ ተሸልሞ ያውቃል፡፡ በተለይ ደግሞ ብዙዎችን ተማሪዎች ያናደዳቸው ‹‹የዘፈነም፣የተወነም፣ ፊልም የሠራም፣ ማስታወቂያ የሠራም አርቲስት አይባልም›› ያሉት ነገር ነው፡፡ ‹‹አርቲስት የሚለው ስም ለሰዓሊዎች የሚሰጥስም ነው፡፡ ያውም ስካልፕቸርና ፔይንቲንግ ለሚሠሩት ብቻ፡፡ እርሱምቢሆን እንደ ደጃዝማችና ግራ አዝማች ማዕረግ ሳይሆን የሞያ መጠሪያ ነው፡፡ እስኪ አሁን አርቲስት ማይክል ጃክሰን፣ አርቲስት ቢዮንሴሲባል ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? ሰው ማዕረግ የሚያበዛው ስሙ ብቻውን ለመቆም ዐቅም ስለሚያጣ ነው፡፡ እስኪ ተመልከቱ፡፡ ዳቪንቼ፣ ሼክስፒር፣ሞዛርት፣ ፒካሶ የሚለው ስምኮ ብቻውን የሚቆም ነው፡፡ ዕዝል ቅጽል አያስፈልገውም፡፡›› ያሉትን ነገር ተማሪዎቻቸው ‹‹እርሳቸውከቴሌቭዥን ሊበልጡ ነው እንዴ›› ብለው ሙድ ያዙባቸው፡፡

ለነገሩ እርሳቸውም አብዝተውታል፡፡‹አርሶ አደርና አርብቶ አደር፣ ሠልጣኝና የትራፊክ ፖሊስ፣ ታራሚና ፍርደኛ፣ ጋዜጠኛና ጎዳና ተዳዳሪ ማዕረግ ሆነው ከስም በፊትበሚቀጸሉባት ሀገር ‹አርቲስት› ማዕረግ አይደለም ብለው ተማሪን ማሸበር በአሸባሪነት የሚያስከስስ እንዳይሆን ያሰጋል፡፡ እንዲያውምኢቲቪ ቢሰማቸው ‹በአሸባሪነት ሊያስከስስ ይገባል ሲሉ አንዳንድ የሕግ ምሁራን አስገነዘቡ› ብሎ ለዜና ጥብስ ያውላቸው ነበር፡፡
እርሷ ሶፋ ወንበር ላይ ተቀምጣይኼንን ሁሉ ስታስብ ጓደኛዋ በቴሌ ቭዥን ዘገየች፡፡ እስኪጀመር ድረስ ያቺ የ12 ዓመት የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ማሰቧን ቀጠለች፡፡‹‹ቆይ ግን አባዬ ምንድን ነው? አንድም ቀንኮ በቴሌቭዥን ታይቶ አያውቅም፡፡ ይኼው ኤልዳና እንኳን ስንት ጊዜ በቲቪ ልትታዪ ነው፡፡አባዬ ግን ዶክተር ምናምን ከሚሆን አርቲስት ቢሆን ነበር ጥሩ፡፡ እርሱ ዶክተር ሆኖ ምንም አልጠቀመንም፡፡ አንዴ አሜሪካ አንዴጃፓን፣ አንዴ ጀርመን ለወርክ ሾፕ መሮጥ ብቻ ነው፡፡ በርግጥ የኤልዳናም አባት ውጭ ይኼዳል፡፡ ግን እርሱ ሲሄድም ሲመጣም በሚዲያይነገርለታል፡፡ ሊሄድ ነው፣ እየሄደ ነው፣ ሊደርስ ነው፣ ደረሰ ይባልለታል፡፡ የኔን አባት መሄድና መምጣት ግን እኛና የኢትዮጵያአየር መንገድ ብቻ ነን የምናውቀው፡፡

ደግሞ የኤልዳና አባት ውጭ ሲሄድሰው ይከበዋል፣ ጉርድ ቀሚስ ያደረጉ ሴቶች፣ ቁጥርጥር የተሠሩ ወንዶች፣ አጅበውት ፎቶ ይነሣሉ፡፡ የኔ አባት ግን ፎቶዎቹን ሁሉሳይ ወይ ከራሰ በራ ሰው ጋር ወይ ድክምክም ካሉ ሴቶች ጋር ነው የሚነሣው፡፡ ደግሞኮ የኤልዳና አባት ሁልጊዜ የአበባ ጉንጉን ሲቀበልነው የሚታየው፡፡ የኔ አባት ግን ሯጭ ይመስል ሜዳልያ ሲቀበል ነው የምናየው፡፡ ኤልዳና ቪዲዮውን በስልኳ ስታሳየን ሰው ሁሉ ኡኡእያለ አዳራሽ ውስጥ ለአባቷ ይጨፍርለታል፡፡ የኔ አባት ግን አንድ ጠረጴዛ ነገር አጠገብ ይቆማል፤ የሆነ ነገር በፓወር ፖይንትያሳያል፤ አንድ ጊዜ ይጨበጨብለታል፡፡ በቃ፡፡ አንድም የሚጨፍር ሰው አይታይም፡፡ አባዬ ግን ምንድን ነው?

ቆይ ግን እኛ ቤት ኢቲቪዎች የማይመጡትለምንድን ነው? አባቴ አርቲስት ስላልሆነ ነው አይደል፡፡ የኔ አባትኮ እንኳን ለፋሲካ ለአርሂቡ ቀርቦ አያውቅም፡፡ እውነታቸው ነው፡፡በአርሂቡኮ አርቲስቶች ሲቀርቡ ‹እንትናዬ አድናቂህ ነኝ፣ እወድሃለሁ፤ ቀጣዩ አልበምህ መቼ ነው የሚወጣው? ምን ፊልም ልትሠራልንነው?›› የሚል ሰው ይደውልላቸዋል፡፡ አሁን አባዬ አርሂቡ ላይ ቢቀርብ ምን ሊባል ነው? ምን ተብሎ ሊጠየቅ ነው? ደግሞ ማንምአድናቂ አያገኝም፡፡ አልበም የለው፤ ፊልም የለው፣ ሰዎች በምን ያውቁታል፡፡

አባዬ ግን አርቲስት መሆን ነበረበት፡፡ዶክተርነት ምን ያደርግለታል፡፡ አርቲስት ቢሆን ኖሮ በኋላ ሲያረጅ ‹የክብር ዶክትሬት› ተብሎ ይሰጠው ነበር፡፡ ‹የክብር አርቲስት›ብሎ ግን ማንም አሁን አይሰጠውም፡፡ ዶክተርነት ይደረስበታል፡፡ አርቲስትነት ግን አይደረስበትም፡፡ እንዲያውም እነርሱ ሲጠሩ ‹ክቡርዶክተር› ነው የሚባሉት የኔ አባት ግን ‹ዶክተር› ብቻ ነው፡፡

እርሷ ይህንን ስታወጣና ስታወርድየቴሌቭዥኑ ፕሮግራም ጀመረ፡፡ ጋዜጠኛውም ‹እያዝናናን እናስተምራለን› ብሎ የጓደኛዋን ቤት አሳየ፡፡ ምንም እንኳን የተቀረጸው በጾምጊዜ ቢሆን ዶሮው፣ በጉ፣ ክትፎው፣ ቅቤው፣ ዕንቁላሉ ይታያል፡፡ ለነገሩ እንደ ኢቲቪ አቆጣጠር ጾሙ አንድ ሳምንት ሲቀረው ያልቃል፡፡ከዚያ በኋላ ቀረጻ ይቻላል፡፡ ጓደኛዋን አየቻት፡፡ ቤታቸው እየታየ ነው፡፡
እየሮጠች አባቷን ቀሰቀሰቺው፡፡
‹‹ጓደኛዬ በቴሌቭዥን እየታየችነው›› ስትለው ድካሙ ባይለቀውም እርሷን ለማስደሰት ተነሥቶ ዓይኑን እያሸ ወደ ሳሎን መጣ፡፡ ‹እያት ኤልዳናን› አለቺው፡፡ ኤልዳናእየተጠየቀቺ ነው፡፡ ቃለ መጠይቁ ሲያልቅ ‹አባዬ አንተ መቼ ነው በቲቪ የምትቀርበው› አለቺው ልጁ፡፡

‹‹ሚዲያችን ከታዋቂ ይልቅ ለዐዋቂቦታ ሲኖረው›› አላት አባቷ፡፡
‹‹አንተ ግን ለምን ታዋቂ አልሆንክም››

‹‹ልጄ እኔኮ ታዋቂ ነኝ፡፡ የኢቲቪጋዜጠኞች ግን አያውቁኝም፡፡ የቢቢሲ፣ የሲኤንኤን፣ የአልጀዚራ ጋዜጠኞች ያውቁኛል፡፡ እኔ አንድ ነገር ስለ ግብርና ከተናገርኩ ወይምከጻፍኩ ያ ዜና ይሆናል፡፡ እዚህ አገር ግን ዕውቀት ዜና አይሆንም ልጄ፡፡ እዚህ ሀገር ዜና የሚሆነው ፖለቲካና ቀልድ ነው፡፡››
‹‹እሺ ለምን አርሂቡ ላይ አትቀርብም››
‹‹ያማ ጋዜጠኛውን ማሰቃየት ነውልጄ››
‹‹ለምን ይሰቃያል?››

‹‹ምን ይጠይቀኛል? ጥናታዊ ጽሑፎቼንማንበብ ሊኖርበት ነው፡፡ ምርምሮቼን መቃኘት ሊኖርበት ነው፡፡ ስለ እኔ የተሰጡ የሌሎች ሳይንቲስቶችን ምስክርነት ማገላበጥ ሊኖርበትነው፡፡ ይሰቃያል ልጄ፡፡ ቀልድ የለመደን ሰው ዕውቀት ያሰቃየዋል፡፡በቀለላሉ የመጀመሪያ አልበምህ መቼ አወጣኸው? የመጀመሪያው ፊልምህምን ነበር? ገጠመኝህ ምንድን ነው? እያለ ሰዓቱን መሙላት ሲችል ምን በወጣው ሳይንቲስ አቅርቦ ይሰቃያል፡፡ ጋዜጠኞቹ መዘጋጀትስለማይችሉም ስለማይፈልጉም አይደል እንዴ ‹እስኪ ራስሽን ለአድማጮች አስተዋውቂ› የሚሉሽ፡፡ ይኼኮ የጋዜጠኛው ሥራ ነበር፡፡ አንብቦ፣ ፕሮፋይል ሠርቶ ቢመጣ ኖሮእንዲህ አይልም፡፡ ደግሞም አለቆቹም ላይወዱለት ይችላሉ፡፡ ዕውቀት የመለወጥ ኃይል አለው፡፡ ሕዝቡ ደግሞ እንዲዝናና እንጂ እንዲለወጥ አይፈለግም፡፡››
‹‹ተዪው እኔን፡፡ አንድ ገበሬበዓል እንዴት ነው የሚያከብረው? ድንበር ላይ ባሉ ወታደሮች ዘንድ እንዴት ይከበራል? ተረኛ ሆነው ሆስፒታል ወይም እሳት አደጋመከላከያ ውስጥ ባሉ ባለሞያዎች ዘንድ ፋሲካ ምን ዓይነት በዓል ነው? በዕለቱ አየር ላይ በሚሆኑ የአውሮፕላን አብራሪዎችና አስተናጋጆች፣መርከብ ላይ በሚሠሩ ኢትዮጵያውያን፣ ሆስፒታል በተኙ ሕሙማን፣ በዓል እንዴት ይከበራል? የሚለውን እንኳን መች ያሳዩናል፡፡ ለምንይመስልሻል?

‹‹እነርሱ ታድያ አርቲስት ናቸውእንዴ?››

ልጄ የኑሮ አርቱማ ያለው እዚያውስጥ ነበር፡፡ የኛነታችንን ሌላ ገጽታ የምናየውማ እዚያ ውስጥ ነበር፡፡ ግን ይኼ ማሰብ ይጠይቃል፤ መመራመርን፣ ማንበብን፣ መዘጋጀትንይጠይቃል፡፡ ማሰብ፣ ማንበብና መዘጋጀት ደግሞ እዚያ ቤት የሚወደዱ አይመስሉኝም››
‹‹እሺ ታድያ መቼ ነው የኛ ቤትበቴሌቭዥን የሚቀርበው?››
‹‹ወይ እኔ መቀለድ፣ ወይ እነርሱማወቅ ሲጀምሩ››

The post የሳይንቲስቱ ልጅ ጥያቄ – ከዳንኤል ክብረት (ዲ/ን) appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>