Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

(በዚህ ሳምንት የተማርናቸው ሦስት ነገሮች) 1ኛ) የአይሲስ ፍላጎት ተቃርኖን ማጦዝ ነው 2ኛ) ፓን አፍሪካኒዝም እንጀራ አይጋግርም 3ኛ) የዌንዲ ሸርማን ምላስ ከስቴት ዲፓርትመንት ራስ የተጣላ ነው

$
0
0

የቡና ቁርስ

1ኛ) የአይሲስ ፍላጎት ተቃርኖን ማጦዝ ነው

ይህ ሳምንት ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች እጅግ ክፉ ጊዜ ነበር። በደቡብ አፍሪካ በተቀሰቀሰው የስደት ጠሎች ኹከት በርካቶች የአካል እና የንብረት ጉዳት ደርሶባቸዋል። በሜዲትራኒያን ባህር ላይ ስደተኞችን ይዛ ወደ አውሮፓ የምትጓዝ ጀልባ ሰጥማ ከ700 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል፤ ቁጥሩ ባይረጋገጥም ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውያን የአደጋው ሰለባ እንደኾኑ ዜናዎች ይጠቁማሉ። ትላንት ደግሞ አይሲስ በሊቢያ 30 ክርስቲያን ኢትዮጵያውያንን በአሰቃቂ ኹኔታ መግደሉን የሚያሳይ፣ ሰውነትን የሚያራዥ እና አጥወልዋይ ፊልም ሶሻል ሚዲያ ላይ አሰራጨ። አይሲስ እንዲህ ዐይነት አፍ የሚቆልፍ ዘግናኝ የጅምላ ግድያ ሲፈጽም የመጀመርያው አይደለም። የግብጽ፣ የአውሮፓ፣ የአሜሪካ፣ የዮርዳኖስ፣ የኢራቅ እና የሶርያ ዜጎች የተመሳሳይ ጥቃት ሰለባዎች ኾነዋል። ቡድኑ እንዲህ ዐይነት አረመኔያዊ ተግባር ንጹሃን ሰዎች ላይ ለምን ይፈጽማል?
ethiopian killed by isil 3
ለዚህ ጥያቄ አይሲስን የሚከታተሉ ተንታኞች የተለያዩ መልሶችን ይሰጣሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ተቃርኖን ማጦዝ (accelerating contradictions) ነው። የጽንፈኛ እና ነውጠኛ ድርጅቶችን መጣጥፍት የሚያነብ ይህን ሐሳብ በሚገባ ያውቀዋል። በርካታ ጽንፈኛ ድርጅቶች የሚጋሩት አንድ መላምታዊ ሐሳብ አለ፤ እነርሱ የሚቃወሟቸው የተረጋጉ የሚመስሉት ሥርዐቶች በውስጣቸው የተደበቁ የማይፈቱ ቅራኔዎች አሏቸው የሚል። ሥርዐቶቹ ተቃርኗቸውን ይዘው ለረዥም ጊዜ ሳይበጠበጡ እና ሳይተራመሱ መቆየት ይችላሉ። የጽንፈኛ ታጋዮች ዋነኛ ስትራቴጂካዊ ሥራ እነዚህ ተቃርኖዎች ከተደበቁበት እንዲወጡ ማድረግ ነው። ይኼም ሁለት ግቦች አሉት። አንደኛ፦ የተቃርኖዎች መጦዝ ሥርዐቶቹ ያናውጣል፤ ሁለተኛ፦ ተቃርኖው እየገፋ ሲመጣ የጽንፈኛ ቡድኖች የድጋፍ መሠረት ይጨምራል። ይህን በታሪክ ስትራቴጂ ፋሺስቶች፣ ስታሊኒስቶች፣ ናዚዎች፣ ሌኒኒስቶች እና ሌሎችም ቡድኖች ተጠቅመውበታል። ዃን ኮል የተባሉ መካከለኛ ምሥራቅን የሚያጠኑ የታሪክ ተመራማሪ የአይሲስን ድርጊት ከዚህ ስትራቴጂካዊ ግብ ጋራ ያገናኙታል።

ቡድኑ የሚቃወመው የተለያዩ ሃይማኖቶች በአንድ ላይ የሚኖሩበትን ትዕግስት እና መቻቻል የሰፈነበትን ማኅበራዊ ሥርዐት ነው። አይሲስ ይህ ሥርዐት እንዲገረሰስ ይፈልጋል። ይህን ለማድረግ ክርስቲያኖችን እያደኑ በአሰቃቂ ኹኔታ መግደል ብቻ በቂ አይደለም። በክርስቲያኖች እና በሙስሊሞች መካከል ከረር ያለ ተቃርኖ እንዲፈጠር ማድረግ ዓላማው ነው። ስለዚህ የሚፈጽማቸውን አሰቃቂ ግድያዎች በፊልም ቀርጾ ፊት ለፊታችን ያመጣል። የግድያ ዜና በመስማት እና የግድያውን ሂደት በማየት መካከል ያለውን ስሜት የመቀስቀስ የአቅም ልዩነት በሚገባ ያውቀዋል። ፊልሙን የሚያሳየን ክርስቲያኖች ዘግናኝ ድርጊቱን ተመልክተው ከቁጥጥር ውጭ የወጣ የቁጣ እና የእልህ ስሜት ውስጥ እንዲገቡ ለማድረግ ነው። ስሌቱም እንዲህ ዐይነት ቁጣ ሲነሳ መቻቻል ይቀንሳል የሚል ነው። አንዳንድ ሰዎች መስመር ተላልፈው በቃላት እና በድርጊት ሙስሊም ወገኖቻቸውን መግፋት እና ማንገላታት ይጀምራሉ፤ በግጭት እና በመጠላላት የሚጠቀሙ ጠባብ ሐይሎች “ግርግር ለሌባ ያመቻል” እንደሚባለው በቀዳዳው ገብተው ልዩነትን ለማስፋት ይሞክራሉ። ብዙኃን ሙስሊሞች እንደ ብዙኃን ክርስቲያኖች- እንደ ብዙኃን ሰብአዊ ፍጡራን ሁሉ- ለጽንፈኛ ቡድኖች ግድ የላቸውም። በተለምዶ ቀን ተቀን የሚኖሩት ሕይወት ሰላማዊ እና በመቻቻል ላይ የተመሠረተ ነው። ይኹንና የቁጣ ስሜት እና የመጠቃት መንፈስ ድባብ ሲፈጠር እንዲህ ያለው በተለምዶ ተቻችሎ የመኖር ሂደት ይናጋል። በዚህ ምክንያት የሚጦዘው ተቃርኖ ማኅበራዊ ሥርዐቱ ላይ አደጋ ይጋርጣል። በተጨማሪም ለአይሲስ ዐይነት ቡድኖች አባላት የመመልመያ ማኅበራዊ መሠረት (social base) ይሰጣል።

ይህ የአይሲስ ተቃርኖን የማጦዝ ስትራቴጂ የሚከሸፈው የድርጊቱን ዓላማ በሚገባ በመረዳት እና እርስ በርስ ከመጠነቋቆል እና ከመጠቋቆም ይልቅ አትኩሮታችን አይሲስ ላይ ሲኾን ብቻ ነው። ዋስትናችን መቻቻል ነው።

2ኛ) ፓን አፍሪካኒዝም እንጀራ አይጋግርም

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በአንደበተ ርቱዕነት እና በስምሙ መልሶቻቸው አይታወቁም። ይኹንና የደቡብ አፍሪካውን ቀውስ በተመለከተ የሰጡት ምላሽ ከብዙ አፍሪካዊ ፖለቲከኞች እና ምሁራን ሐሳብ ጋራ ተመሳሳይ ነበር፤ አፍሪካውያን በፈቀዱት የአፍሪካ አገሮች ሄደው የመኖር መብት እንዳላቸው የሚያሳስብ። ይህ የአፍሪካውያን የመንቀሳቀስ ነጻነት (freedom of movement) የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ አንዱ መሠረታዊ መርኾ እና ያልሰመረ ሃልዮት (unfulfilled ideal) ነው። ሲናገሩት እና ሲፈክሩት ይጥማል። ነገር ግን አሁን ለደረሰው ቀውስ አግባብነት ያለው እና ተግባራዊ መልስ አይደለም።

ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር ተጉዞ የመሥራት እና የመኖር መብት እጅግ አወዛጋቢ የፖለቲካ ጽንሰ ሐሳብ ነው። ከሮማን ኢምፓየር ጀምሮ በርካታ ፈላስፎች እና የሰው መብት ተሟጋቾች የተለያዩ ሃልዮታዊ እና ተግባራዊ ምክንያቶችን እየሰጡ ደግፈውታል። አንዳንድ ጊዜ ተሳክቶላቸው የሕግ እና የመንግሥት ፖሊሲ አካል እንዲኾን አድርገውታል። የአፍሪካ የነጻነት አባቶች እና የፓን አፍሪካኒዝም ደጋፊዎች ከዚህ ጎራ ይመደባሉ። ይህ መብት “ብሔራዊ አንድነትን ይሸረሽራል፣ ወንድማማችንነት እና መረዳዳትን ይጋፋል፣ ድኾችን ይጎዳል፣ ግጭትን ይጨምራል ወዘተ” የሚሉ ሙግቶችን በማቅረብ በጥብቅ የሚቃወሙትም አሉ። በየአገሩ እና በየአህጉሩ ክርክሩ እንደጦፈ ነው። በደቡብ አፍሪካ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ አጋማሽ ለዚህ መብት ፖለቲከኞች እና ሌሎች ልሂቃን የነበራቸው ቀናዒነት ከፍ ያለ ነበር። በውስጥ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ምክንያቶች ይህ ቀናዒነት እየተሸረሸረ መጥቶ አሁን ብዙ ልሂቃን መብቱን በጥርጣሬ መመልከት ጀምረዋል፤ ስደተኞች ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ ለማድረግ የሚወጡ ጥብቅ የቪዛ እና የድንበር ቁጥጥር ደንቦች እንዲሁም የኢኮኖሚ ዋስትና ሕጎች ድጋፍም ጨምሯል። በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በስደተኞች ጉዳይ ቀኝ ዘመምተኝትን አሳይቷል። እንዲህ ዐይነት የፖለቲካ ኹኔታ ላይ ያለን አገር ስለ አፍሪካውያን እንቅስቃሴ መብት ለማስተማር መሞከር ለተፈጠረው ችግር ግልጽ የኾነ መፍትሄ አያመጣም።

ይልቁንስ ተግባራዊ መፍትሄዎች መሻት የተሻለ አማራጭ ነው። በአገሪቱ ስደተኛ ጠሎች የሚያስነሷቸው ኹከቶች ቀጣይ መኾናቸው ግልጽ ነው። አሁን ያለው ጥቃት የመጀመርያው ሳይኾን እ.ኤ.አ ከ2000ዎቹ መጀመርያ ጀምሮ ቀስ በቀስ እየተበራከተ የመጣው ኹከት አካል ነው። በደቡብ አፍሪካ ስር የሰደዱ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እስኪፈቱ ስደተኞችን የችግሮቹ ተጠያቂ ማድረጉ እና ጥላችን ማነሳሳቱ ይቀጥላል። የአሁኑ ኹከት ቢበርድ እንኳን በኢትዮጵያውያን እና ሌሎች ስደተኞች ላይ ቀጣይ አደጋዎች ተጋርጠዋል። እነዚህ ስደተኞች ለመጡባቸው አገራት መንግሥታት ዋነኛ ጉዳይ መኾን ያለበትም ሊመጡ የሚችሉትን ቀጣይ አደጋዎች መቀነስ ነው። ለምሳሌ፦ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ከናይጄሪያ፣ ሞዛምቢክ፣ ዚምባቡዌ፣ ማላዊ፣ ኬንያ፣ እና ሌሎች የአፍሪካ መንግሥታት ጋራ በመኾን የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በአገሪቱ በሚኖሩ ስደተኞች ላይ ችግር እንዳይደርስ ጥበቃ እንዲያደርግ፣ ግጭት ቀስቃሾች ላይ ርምጃ እንዲወስድ፣ ለፖሊስ እና ለታውንሺፕ ፖለቲከኞች ትምህርት እና መመርያ እንዲሰጥ እንዲሁም ግጭት ሲከሰት በፍጥነት ጣልቃ እንዲገባ ግፊት ማድረግ ይችላል። ባለፉት ዐራት ዓመታት ደቡብ አፍሪካ አህጉሪቱን በኢኮኖሚ ብቻ ሳይኾን በፖለቲካም ለመምራት ያላትን ፍላጎት በግልጽ አሳይታለች። ይህ እያደገ የመጣ የመሪነት ምኞት (ambition) ለእነ ኢትዮጵያ የተጽዕኖ አቅም (leverage) ይሰጣቸዋል። ደቡብ አፍሪካ በአህጉሪቱ ተሰሚነትና ክብር ስለምትፈልግ የዲፕሎማሲ እና የፖለቲካ ጫናውን ወደ ጎን ለማለት ይከብዳታል። እንዲህ ዐይነቱ ጫና “ሁላችንም አንድ ነን” ከሚለውን መፈክር ይልቅ የአካል እና የንብረት መብትን ለማስጠበቅ ይረዳል።

3ኛ) የዌንዲ ሸርማን ምላስ ከስቴት ዲፓርትመንት ራስ የተጣላ ነው

የአሜሪካ ባለ ሥልጣናት ስለ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ሲጠየቁ የሚሰጡት መልስ የተለመደ እና ተመሳሳይ ነው፤ “ዴሞክራሲ ሂደት ነው፤ ኢትዮጵያ ቀስ በቀስ ከተሞክሮ እየተማረች ወደ ዴሞክራሲ እንድምትሸጋገር ተስፋ አለን” የሚል። ይህ መልስ ለሽግግር “ሁለት ዐሥርት ዓመታት አይበቃትምን?” የሚል ተከታይ ጥያቄ ያስነሳባቸዋል። ይህን ጥያቄ ለመመለስ አስቸጋሪ የሚያደርገው ሁሉም አገሮች ያሉበትን የዴሞክራሲ ደረጃ የሚያሳዩ ኢንዴክሶች ባለፉት ዐሥር ዓመታት በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ እድገት ወደ ኋላ እንጂ ወደ ፊት እንዳልኾነ በግልጽ ማስቀመጣቸው ነው። ለምሳሌ፦ በፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪዎች ዘንድ እጅግ በጣም ክብር የሚሰጠው Polity IV Score የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሽግግር ተቀልብሶ ወደ ሙሉ አምባገነናዊ ሥርዐት እየተጓዘች እንደኾነ ያሳየናል። እነዚህ ኢንዴክሶች እና አጠቃላይ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዞ ለአሜሪካ ባለ ሥልጣናት የተሰወሩ አይደሉም። ስለዚህ ብዙ ጊዜ መልስ ሲሰጡ ለመተርጎም የሚከብዱ አሻሚ ቃላቶችን ይመርጣሉ። ነገር ግን ባለፈው ሳምንት በዚህ ጉዳይ ላይ የተናገሩት በውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የሥልጣን ርከን አራተኛ ደረጃ ላይ የኾኑት የፖለቲካ ጉዳዮች ምክትል ሴክሬታሪ ዌንዲ ሼርማን “ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አገር ነች” ሲሉ የማያጨቃጭቅ እና የማያሻማ መግለጫ ሰጥተዋል። ይህ የሚገርም እወጃ ነው።

ዌንዲ ሸርማን የሚሠሩበት የውጪ ጉዳይ መሥርያ ቤት በየዓመቱ የሰብአዊ እና የፖለቲካ መብቶችን በተመለከተ ሪፖርት ያወጣል። ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ያወጣቸው ሪፖርቶች አንዱም ሳይቀር የኢትዮጵያን የፖለቲካ መብቶች ጥበቃ ክፉኛ የሚተቹ ናቸው። ዌንዲ ሸርማን የፖለቲካ ነጻነት የሌለበት ዴሞክራሲ ሊኖር ይችላል ብለው ያምናሉ ወይም የራሳቸው መሥሪያ ቤት የሚያወጣውን ሪፖርት አያነቡም። በተጨማሪም ባለፉት ስድስት ዓመታት በኢትዮጵያ ጉዳይ እያደገ ያለውን የተለምዶ አስተሳስብ (conventional wisdom) አገሪቱ በዴሞክራሲ እየቀጨጨች፣ በኢኮኖሚ እየፋፋች እንደኾነ የሚያወሳ ነው። ይህ አስተሳሰብ አጠያያቂ ቢኾንም በየኮንፈረንሱ፣ በየስብሰባው እና በየሴሚናሩ በአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኤክስፐርቶች ጭምር ተደጋግሞ የሚነገር ነው። ዌንዲ ሸርማን የራሳቸው ኤክስፐርቶች ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ የሚናገሩትን ልብ ያሉ አይመስሉም። ጆሮ ደፍኖ ምላስን ማውለብለብ እንዲሉ።

• በዚህ ሳምንት ለተጎዱ፣ ለተንገላቱ እና ውድ ሕይወታቸውን ላጡ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ጥልቅ የኾነ ሐዘናችንን እንገልጻለን!!

 

Source: 7 killo Magazine

The post (በዚህ ሳምንት የተማርናቸው ሦስት ነገሮች) 1ኛ) የአይሲስ ፍላጎት ተቃርኖን ማጦዝ ነው 2ኛ) ፓን አፍሪካኒዝም እንጀራ አይጋግርም 3ኛ) የዌንዲ ሸርማን ምላስ ከስቴት ዲፓርትመንት ራስ የተጣላ ነው appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>