Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

(የሊቢያው እልቂት ጉዳይ) እኛ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ነን!!

$
0
0

አፈንዲ ሙተቂ

ISIL የሚባለው ሰይጣናዊ ቡድን በምድረ ሊቢያ በዜጎቻችን ላይ የፈጸመው አረመኔያዊ ድርጊት ያስቆጣኝ በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ የመጀመሪያው ምክንያቴ በጥይት የተረሸነውና በስለት የታረደው ኢትዮጵያዊ ወንድሜ መሆኑ ነው፡፡ አዎን!! “ዘወትር በድህነት ከምንገላታ ወደ ውጪ ሄጄ ዕድሌን ብሞክር ይሻላል” በሚል የሃሳብ ምጥ ተነሳስቶ በምድረ ሊቢያ በኩል ወደ አውሮጳ ለመሻገር ሲሞክር በአረመኔው ቡድን የተያዘው ወገኔ ደም በረሃ አሸዋ ላይ እንደ ጎርፍ መፍሰሱ በእጅጉ ያንገበግበኛል!! ያስቆጣኛል!! ያስቆጨኛል!! ከአስከፊው የሰሃራ በረሃ የውሃ ጥም እና የሞት መልዕክተኛ ከሆነው የሜዲትራኒያን ባህር ጉዞ ተርፎ ወደ ማልታና ኢጣሊያ መድረሱ እንኳ እያሳሰበኝ ሳለ ከሁለቱ ሰይጣኖች በሺህ እጥፍ የሚብሰው ISIL የተባለ ሶስተኛ ሰይጣን በሊቢያ ምድር ላይ ወገኔን ጠልፎ እንደ በግ አጋድሞት ሲያርደው ማየቱ ይቅርና መስማቱ ራሱ ሲቃው የማይቻል ህመም ነው የሆነብኝ፡፡ የፈሰሰው ክቡር የሆነው የወገኔ ደም ነውና ስለርሱ ሞት እኔ ታምሜአለሁ (ብታምኑም ባታምኑም ባለፈው አንድ ሳምንት ውስጥ የምርምር ስራዬን አቁሜአለሁ፤ እንኳንም የቢሮ ሰራተኛ አልሆንኩ)!!

(ፎቶ ፋይል)

(ፎቶ ፋይል)


ሁለተኛው ምክንያቴ ይህ ISIL የተሰኘ “ከላባ” የሰይጣኖች ቡድን ዘወትር እንደለመደው በወገኖቼ ላይ የፈጸመውንም አረመኔያዊ አድራጎት እኔ በምከተለው የእስልምና እምነት ላይ ማላከኩን መቀጠሉ ነው፡፡ በዚህም ሳያበቃ “ይህንን የፈጸምኩት ለናንተ ብዬ ነው፤ በየትኛውም የዓለም ክፍል የምትኖሩ ሙስሊሞች አዳኛችሁ እኔ ብቻ እንደሆንኩ አውቃችሁ ልትቀበሉኝ ይገባል” እያለ ማላገጡም ቁጭቴን ከፍተኛ ደረጃ ላይ አድርሶታል፡፡ እንደዚያ ዓይነት ድርጊቶችን የሚፈጽምበት ዓላማም የእስልምና እምነትን ጥላሸት መቀባት እና በሙስሊሙ እና በሌሎች ወገኖች መካከል ግጭት እንዲቀሰቀስ ማድረግ እንደሆነም በደንብ ስለምረዳ “አንተ አረመኔ! በእስልምና ስም የምትነግድ የሰይጣን ማህበርተኞች ስብስብ” ብዬ እናገረው ዘንድ የተገባም ነበር (በአማርኛ የጻፍኩትን እርሱ ባይረዳውም እንኳ)፡፡

እንግዲህ ባለፈው አንድ ሳምንት ውስጥ ሰይጣናዊው ISIL በወገኖቻችን ላይ ያደረሰውን አደጋ ተከትሎ አንዳንድ ጽሑፎችን ስንጽፍ የነበረው በነዚህ ሁለት መነሾዎች ነው፡፡ ወደፊትም በተጠቂ ወገኖቻችን ቤተሰቦች ላይ የደረሰውን መሪር ሐዘን ለማሻር በሚደረገው ርብርቦሽ ውስጥ የተቻለንን ሁሉ ማድረጋችንን እንቀጥላለን፡፡ ታዲያ የተወሰኑ ሰዎች ይህንን መጠነኛ እንቅስቃሴአችንን ፍርሃት የወለደው ራስን የመደበቅ መፍጨርጨር አድርገውት ሲመለከቱት ለመታዘብ በቅተናል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ “ይህ ጉዳይ እናንተን ስለማይመለከት አርፋችሁ ተቀመጡ” ዓይነት ጽሑፎችን ሲበትኑ ተስተውሏል፡፡ አንዳንዶች ጭራሽ ISIL በኛ እጅ የተፈጠረ እንደሚመስላቸው ለማየት ችለናል፡፡ ጥቂቶች ደግሞ ከእስልምና እምነት ጋር ተያያዥነት የሌላቸው ትረካዎችንና ሀሳብ-ወለድ አመክንዮዎችን እያነሱ ነገሩን በእምነታችን ላይ ለማላከክ ሞክረዋል፡፡

በእውነቱ እነዚህ ወገኖች በሦስት ነገሮች አስገርመውናል፡፡ አንደኛ በጉዳዩ ዙሪያ በአማርኛ ቋንቋ ስንጽፍ የነበርነው ሙስሊሞች ኢትዮጵያዊያን መሆናችንን መርሳታቸው ነው፡፡ አዎን!! ኢትዮጵያዊ መሆናችን ብቻ ለወገኖቻችን እንድንናገር ያስገድደናል፡፡ “ኢስላም” እምነታችን እንጂ ዜግነታችን አይደለም፡፡ እምነቱ ጥንት ከዐረቢያ ወደ ኢትዮጵያ የገባ ቢሆንም ዜግነታችን ወደ ሳዑዲያ አልተቀየረም፡፡ የብሄር መለያችንም ወደ ዐረብ አልተለወጠም፡፡ የጥቁር አፍሪቃዊነት መታወቂያችንም ተፍቆ ወደ ነጭነት አልተለወጠም፡፡ ከሌሎች እምነቶች መካከልም የሚበዙት ከውጪ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ቢሆንም የየእምነቶቹ ተከታዮች በዜግነታቸው ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ “ኢትዮጵያዊያን በእምነት ብንለያይም ተፋቅረን ነው የኖርነው” እያልን ስንጽፍና ስንናገር የነበረው ከድሮም ጀምሮ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለፕሮፓጋንዳ ብለን የምንጽፈው ሳይሆን በተግባር የኖርነው ህይወታችን ነው፡፡ ዛሬ ለወገኖቻችን መቆርቆራችንም በደማችን ውስጥ ሲዘዋወር የነበረው ህብርነታችን የቀሰቀሰው ብሄራዊ ወኔ ነው፡፡ ይህ በሌላ ዓለም የማይታየው ጥብቅ የወንድማዊነት ቃል-ኪዳናችን የዜግነት ግዴታችንን እንድንወጣ ቢያንቀሳቅሰን በአንዳንዶች ዘንድ “ፍርሃት ወለድ ነው” ተብሎ መታሰቡ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡

ሶስተኛው ነጥብ ደግሞ እነዚህ ወገኖች እስከዛሬ ድረስ ISIL ስለሚባለው ቡድን ተገቢ ግንዛቤ አለመውሰዳቸው ነው፡፡ ቡድኑ “ከእስልምና የወጣ አፈንጋጭ የእስልምና ጠላት ነው፤ የሰይጣን ወኪል ቢሆን እንጂ በጭራሽ የእስልምና ወኪል ሊሆን አይችልም” ተብሎ በዓለም ሙስሊሞች የተወገዘው ገና ከመነሻው ነው፡፡ ሌላው ይቅርና ጽንፈኛ እና አሸባሪ ተብለው በምዕራባዊያን የተፈረጁት አል-ቃኢዳ እና “ጣሊባን” እንኳ ISIL ከእስልምና ውጪ ነው ማለታቸው በዓለም ሚዲያዎች በተደጋጋሚ ጊዜያት ተዘግቧል፡፡ ይህንን ሰይጣናዊ ቡድን የእስልምና ወኪል አድርጎ ማሰብ በጣም ያሳምማል፡፡

እንደምታስታውሱት ስለዚህ ጨፍጫፊና ሰይጣናዊ ቡድን በየጊዜው ስንጽፍ ነበረ፡፡ እኔም ሆንኩ ሌሎች ሙስሊም ወንድሞቼ የአንጃው ድርጊቶች ከእስልምና ጋር ሆድና ጀርባ መሆናቸውን ማሳወቅ ከጀመርን አንድ ዓመት ሊሞላን ነው፡፡ እርግጥ ያኔ ስለቡድኑ አረመኔነት ስንጽፍ የነበረበት ዋነኛ ምክንያት በርካታ ወገኖች (ኢትዮጵያዊያን አይደሉም) የአንጃውን አድራጎት ከእስልምና ጋር ማያያዛቸው ስላበሳጨን ነው፡፡ ዛሬ ሳይታሰብ 30 ዜጎቻችን የአረመኔያዊው ቡድን ሰለባ ሲሆኑብን ደግሞ ቁጭታችን እጥፍ ድርብ ሆኗል፡፡ በመሆኑም ለወገኖቻችን በጋራ መጮኻችን የዜግነትነት ግዴታችንን ከመወጣት እና አንጃው የእምነታችንን ስም ከመጥፎ ድርጊቶች ጋር እያገናኘ ሲያደርስብን የነበረው የስነ-ልቦና ጉዳት ምን ያህል ግዙፍ እንደሆነ ከማስረዳት ውጪ ከሌላ ትርፍ ጋር የሚያያዝበት ምክንያት ሊኖር አይገባም፡፡

*****
ከላይ የገለጽኳቸው አንዳንድ የተዛነፉ አመለካከቶች የታዩት በጥቂቶች ዘንድ ነው፡፡ አብዛኛው ህዝባችን እንዲህ ዓይነት ነገር ሲያልፍም አይነካው፡፡ እነዚህንም ጥቂቶች አይቶ እንዳላየ ሆኖ ማለፍ ይቻል ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህ ጥቂቶች ነገሩን እየመላለሱት የዋሃን ዜጎቻችንን ሊበክሉት ይችላሉ በማለት ለዛሬ ብቻ በጉዳዩ ላይ ይህቺን ማስታወሻ ጽፌአለሁ፡፡ ስለዚህ እህት ወንድሞቼ አንዳንዶች በሚያሳዩት ያልተገባ ጸባይ ሳትለወጡ በጋራ የጀመርነውን ወገንን የመርዳት ጥረት ከግብ እንድናደርሰው በትህትና እጠይቃችኋለሁ፡፡

*****
ማስታወሻዬን ከማሳረጌ በፊት ጥቂት ነጥቦች ለማውሳት እፈልጋለሁ፡፡

• ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ISIL ስለተባለው ቡድን ስጽፍ የነበረው ከናንተ የተለየ እውቀት ኖሮኝ አይደለም፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት ቡድኑ ለሚፈጽማቸው የጭራቅ ድርጊቶች እስልምናን መጥቀሱ በጣም ስለሚያናድደኝ ነው በዚህ ግድግዳ ላይ የተሰማኝን ስጽፍ የነበረው፡፡ ቡድኑ በልዩ ልዩ ሀገራት ውስጥ የሽብር ድርጊቶችን እየፈጸመ እነዚህን ድርጊቶች ተከትለው ሊፈጠሩ በሚችሉ ቅራኔዎች በኩል ማህበራዊ መሰረቱን ለማስፋት የሚጥር መሆኑ ደግሞ የአደባባይ ሚስጢር ነው፡፡ ይህንን ከይሲ ምኞቱን ለማምከን ያለን ዋነኛ መሳሪያ ከጥንት እስከ ዛሬ ያለንን ፍቅርና ህብርነት የበለጠ ማጠናከር ነው፡፡

• አንዳንዶቻችሁ ስለጂሃድ የጻፍኩትን ጽሑፍ ካነበባችሁ በኋላ ልዩ ልዩ የቁርኣን አንቀጾችን እየጠቀሳችሁ “አንጃው የሚፈጽመው ድርጊት በቁርኣንም የተነገረ ነው” የሚል አዝማሚያ ያለው የመከራከሪያ ሃሳብ አምጥታችኋል፡፡ አንዳንዶቻችሁም በዚህ ዙሪያ አንድ ነገር ጻፍልን ብላችሁኛል፡፡ በእውነቱ ሃሳቡ መነሳቱ ተገቢ ነው፡፡ ይሁንና ሀገር በተጨነቀችበት በዚህ ቀውጢ ጊዜ ውስጥ በእንዲህ ዓይነት አጀንዳ ዙሪያ መነጋገሩ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ISIL የሚባለው አንጃ አንዱ ፍላጎትም ይህንን በመሳሰሉ ጥያቄዎች ዙሪያ ሰዎችን ማወዛገብና ማበጣበጥ ነው፡፡ ስለዚህ “ለጊዜው ጥያቄው ይለፈኝ” እላችኋለሁ፡፡ ለወደፊቱ ግን በዚህ ርዕስ ዙሪያ አንድ መጣጥፍ አዘጋጅቼ ላስነብባችሁ ቃል እገባለሁ፡፡ ለዝግጅት የሚረዷችሁ ጥቂት ነጥቦችን ግን ወርወር ላድርግላችሁ፡፡
1. ቅዱስ ቁርኣን በመጽሐፍነቱ በሁሉም ሙስሊሞች ሊነበብ ይችላል፤ “አል-ፉስሓ” የሚባለውን ጥንታዊ ዐረብኛ የሚናገር ሰው ደግሞ የቁርኣንን አንቀጾችን ቃል በቃል ሊተረጉም ይችላል፡፡ ነገር ግን ቁርአንን ማንበብ የሚችል ሰውም ሆነ እና የዐረብኛ ቋንቋ በቂ እውቀት ያለው ሰው የቁርኣንን ትክክለኛ መልዕክት እና ፍካሬያዊ ይዘት (inner meaning) ለመተንተን አይችልም፡፡ የቁርኣን አናቅጽ ያላቸውን ፍካሬና የሚያስተላልፉትን ትክክለኛ መልዕክት የመተንተን ስልጣን ያለው ለዚህ የሚያገለግለውን የእውቀት ዘርፍ በስፋት ያጠና ምሁር (ዓሊም) ነው፡፡ ይህ ኢስላማዊ የትምህርት ዘርፍ “ተፍሲር” ይባላል፡፡ በእንግሊዝኛ Qur’amic Exegesis ይሉታል፡፡ አንድ ሰው እዚህ ደረጃ ላይ የሚደርሰው ብዙ ሂደቶችን ካለፈ በኋላ ነው፡፡

2. ቁርኣን 6236 አንቀጾች (አያት) አሉት (6666 አንቀጾች ነው ያሉት የሚለው መረጃ ስህተት ነው)፡፡ ከነዚህ አንቀጾች መካከል የሸሪዓ ህግ ምንጭ ሆነው የሚያገለግሉት ግን 500 ብቻ ናቸው፡፡ እነዚህ አናቅጽ የሰላት አፈጻጸም፣ ዘካት፣ ሐጅ፣ የረመዳን ጾም፣ ውል መዋዋል፣ ንግድ፣ ጋብቻ፣ ከሌሎች ህዝቦች ጋር ግንኙነት መመስረት፣ ጂሃድ እና ሌሎችንም የህይወትና የአምልኮ ዘርፎችን ይመለከታሉ፡፡

3. እነዚህ 500 አንቀጾች በየዘርፉ ቢከፋፈሉ ጂሃድን የሚመለከቱት ስንት ይሆናሉ?…. ቁጥራቸው ትንሽ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡ ስለጂሃድ የሚያወሱት ጠቅላላ የቁርኣንን አንቀጾችስ ስንት ይሆናሉ…?. ቁጥራቸው ብዙ ነው፡፡ ከዚህ ልዩነት እንደምትገነዘቡት ስለጂሃድም ሆነ ስለሌሎች የህይወት ዘርፎች የሚያወሱት በርካታ የቁርኣን አንቀጾች የመጽሐፉ አካል ቢሆኑም ሁላቸውም የህግ ምንጭ ሆነው አያገለግሉም፡፡ ይህ ለምን ሆነ…?. ሰፊ መነሻ አለው፡፡ ሁሉንም ወደፊት እናወጋለን!! ኢንሻ አላህ!!

4. ሌላኛው መሰረታዊ ነጥብ ደግሞ ይኸውላችሁ!! ከቁርኣን አንቀጾች መካከል መልእክታቸውም ሆነ ይዘታቸው በግልጽ ትርጉም እና ትንታኔ የማይደረስባቸው አሉ፡፡ እነዚህን አናቅጽ ለመፍታት የሚችለው ስልጣን የተሰጠው “ሙፍቲ” ብቻ ነው፡፡
እንግዲህ እስልምናን የሚያሳብቡ ጽንፈኛ ቡድኖች ከስህተት ላይ እየወደቁ ዓለምን ሲያተራምሱ የነበሩት ከላይ ባነሳናቸውና በሌሎችም መሰረታዊ ነጥቦች ከጥራዝ ነጠቅ ያልዘለለ እውቀት ይዘው ስለሚነሱ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ጭራሽ እነዚህ ነጥቦች በሃይማኖቱ ውስጥ መኖራቸውን ይክዳሉ፡፡ ሆኖም ከላይ የጠቀስኳቸው ነጥቦች ሁሉ ከነቢዩ ሙሐመድ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው አስተምህሮ ውስጥ በጥብቅ የተከበሩ ናቸው፡፡ ብዙሃኑ የዓለም ሙስሊምም በዚሁ ያምናል፡፡እነዚህን ነጥቦች እምቢ ብሎ ከህዝበ ሙስሊሙ ያፈነገጠ ግለሰብም ሆነ ቡድን በነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) አንደበት “አፈንጋጭ” ተብሎ ተወግዟል፡፡ ነቢዩ ከዚህ የአፈንጋጭነት ባህሪ እንድንታቀብ ሲያስጠነቅቁን እንዲህ ብለዋል፡፡

“ከጀመዓው ያፈነገጠ (የተነጠለ) ወደ ጀሃነም ብቻውን ተገነጠለ”
አላህ ከዚህ የአፈንጋጭነት ባህሪ ይጠብቀን፤ ለአፈንጋጮችም አደብ ይስጣቸው፣ እምቢ ካሉም አላህ ያጥፋቸው፡፡ ISIL ግን ከመነሻው ሰይጣናዊ በመሆኑ አላህ ድምጥማጡን ያጥፋው፡፡ ሀገራችንንና ወገናችንን ከክፉ ነገር ይጠብቅልን፡፡ አሚን!!
——-
አፈንዲ ሙተቂ
ሚያዚያ 18/2007

The post (የሊቢያው እልቂት ጉዳይ) እኛ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ነን!! appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>