Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

(በዚህ ሳምንት የተማርናቸው ሦስት ነገሮች) 1ኛ) “ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ለምን ኬክ አይበሉም?”… 2ኛ) የኢትዮጵያ መንግሥት ሲያፍን እንደ አንበሳ ሲጠብቅ እንደ ሬሳ ኾነ… 3ኛ) ፕሮፌሰር መስፍን ምሁራዊ አይበገሬ ናቸው

$
0
0

(የቡና ቁርስ)

በዚህ ሳምንት የተማርናቸው ሦስት ነገሮች
habesha in libya

1ኛ) “ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ለምን ኬክ አይበሉም?”

ታዋቂው ገጣሚ እና ጸሐፊ በዕውቀቱ ሥዩም ከሦስት ዓመታት በፊት የለንደን ኦሎምፒክን በማስመልከት በተዘጋጀ የሥነ ጽሑፍ ፌስቲቫል ላይ ተሳታፊ ነበር። በጊዜው ካቀረባቸው ግጥሞች መካካል ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘለት “ኀሠሣ ሥጋ” የተባለው ነበር።

“እልፍ ከሲታዎች ቀጥነው የሞገጉ ፥
በየሸንተረሩ በየጥጋጥጉ፥
“ስጋችን የት ሄደ?” ብለው ሲፈልጉ ፥
አስሰው አስሰው በምድር በሰማይ፥
አገኙት ቦርጭ ኾኖ ባንድ ሰው ገላ ላይ። ”

ግጥሙ በዩናይትድ ኪንግደም እና በሌሎች ያደጉ አገራት ወስጥ ኢ-እኩልነትን በሚመለከት የሚደረገው ክርክር እና የነበረው ጭንቀት በተጧጧፈበት ጊዜ የቀረበ ስለነበር የጊዜውን መንፈስ መያዝ ችሏል። በዚያን ወቅት ኦኩፓይ ዎል ስትሪት ንቅናቄ ናኝቶ ነበር። ከንቅናቄው ዋነኛ ዓላማዎች መካከል አንዱ የኢኮኖሚ ልዩነቱን ከነመዘዙ ለሕዝብ በግልጽ ማሳየት ነበር። አንዳንድ ጊዜ ፊት ለፊታችን ያለ ችግርን በጥሞና መመልከት ያዳግተናል። የበዕውቀቱ ሥዩም ግጥም ይህን ችግር በጣፋጭ እና አጭር ቋንቋ ያስቀምጣል።

የውስጥና የውጭ መሬት ነጣቂዎች እና ጥቂት ከበርቴዎች በተንሰራፉባት ኢትዮጵያ የኢ-እኩልነት እና የኢኮኖሚ መደብን ጉዳይ ማንሳት እና የፖለቲካ ኢኮኖሚ ፍጭት ዋነኛ አካል ማድረግ አግባብነት ያለው ቢኾንም እስካሁን በተገቢው መጠን አልተዳደሰሰም፤ ሙግት አልተደረገበትም። በ1995 ዓ. ም የጀመረው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ሁሉንም የጠቀመ አይደለም። በርካታ የኢኮኖሚክስ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በእድገቱ የመጀመርያዎቹ ዘጠኝ ዓመታት የታየው አስደንጋጭ የዋጋ ግሽበት የድኻ ሠራተኞችን ኹነኛ ገቢ (real income) ክፉኛ ያዳቀቀ ነበር። በተጨማሪም እድገቱ ከኢንደስትሪያላይዜሽን እና በርካታ ሠራተኞችን ለመቅጠር ከሚችሉ የአገልግሎት ዘርፍ አካላት ጋር የተፋታ በመኾኑ በከተሞች የተንሰራፋውን ሥራ አጥነት ትርጉም ባለው ደረጃ ለመቀነስ እንዳይችል አድርጎታል። እነዚህ እና ሌሎች ምክንያቶች ተደራርበው በተለይ የከተማ ድኾች (urban poor) የእድገቱ ጦስ (development cost) ተሸካሚዎች ኾነዋል “አሁን ተሰውተን ለመጪው ትውልድ ሀብታም አገር ማውረስ” የሚለውን መፈክር ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ኹኔታ አንጻር ስንመረምረው መስዋዕትነቱን እንዲፈጽሙ የሚጠበቅባቸወቅም ኾኑ የተገደዱት የከተማ ድኾች ኾነው እናገኛቸዋለን። በተቃራኒው ይኼን መፈክር ጮኽ ብለው የሚያሰሙት ደግሞ በዋጋ ግሽበት በሰከረ እና በሥራ አጦች በተሞላ ዕድገት ተጠቃሚ የኾኑት ናቸው።

ይህ ግልጽ የኾነ የኢኮኖሚ እውነታ ቢኾንም ለብዙዎች ተሰውሮባቸው ቆይቷል። ነገር ግን ባለፈው ሳምንት በደቡብ አፍሪካ፣ በሊቢያ እና በሜድትራንያን-በኢትዮጵያ ስደተኞች ላይ የደረሰው ሞት እና እንግልት የቀሰቀሰው ብሔራዊ ሐዘን ሳይበርድ መዘራት የጀመረ አንድ አመለካከት አፍንጫችን ሥር ከነበረው የኢ-እኩልነት መዘዝ ጋር እንድንፋጠጥ ያደረገ ነው። የፌስ ቡክ እና ትዊተር ያላሰለሰ ተሳታፊ የኾኑትን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴዎድሮስ አድሃኖምን ጨምሮ በርካታ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የአገዛዙ ደጋፊዎች እንዲሁም የመንግሥት የፕሮፖጋንዳ ጣቢያዎች በተደጋጋሚ ካስተጋቧቸው አመለካከቶች አንዱ “ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አገር ውስጥ ሠርተው መኖር ሲችሉ ከ40 እስከ 90 ሺሕ ብር እየከፈሉ አደጋ ላይ የሚጥላቸውን የስደት ሕይወት መርጠዋል “የሚል ነው። ነገር ግን ይህ አመለካከት የአገዛዙ ብቻ ነው ብሎ መደምደም ከእውነት የራቀ ነው። በተለይ በተለምዶ የመካካለኛ መደብ አባላት ተብለው የሚጠሩ ገቢያቸው የተደላደለ ኑሮ እንዲኖሩ የሚፈቅድላቸው አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ሐሳቡን እንደሚጋሩት በተለያዩ መድረኮች በሚሰጧቸው አስተያየቶች ተስተውሏል።

የዚህ ሐሳብ ዋነኛ ችግር ጥያቄውን መጠየቁ ሳይኾን ‘ ርግጠኝነት የተሞላበት መልስ በቅጽበት ለመስጠት መሞከሩ ነው። ማኅበራዊ ሳይንቲስቶች ኢ-እኩልነት ሲጨምር ሁለት ነገሮች እየተሸረሸሩ እንደሚመጡ ይጠቁማሉ። አንደኛው ማኅበራዊ ንቃት (social consciousness) ነው። ይህ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ኾነን በምናደርገው የኢኮኖሚ መስተጋብር ምክንያት የሚፈጠር የጋራ ንቃት ነው። ይህ ንቃት ባልንጀሬነትን እና ወገንተኝነትን የሚያጸና ነው። የኢኮኖሚ መደብ ልዩነት እየሰፋ ሲመጣ እነዚህ ውጤቶች እየኮሰመኑ ይሄዳሉ። ኢ-እኩልነትን የሚሸረሽረው ሁለተኛው እሴት ደግሞ ማኅበራዊ ኅሊና (social conscience) ነው። ይህ ለፍትህ መጨነቅን፣ ራስን ሌላ ሰው ጫማ ውስጥ በማስገባት በበጎ ልቡና ለመረዳት መፈለግን (empathy) ወዘተ ይመለከታል። በዚህ ሳምንት ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ላይ የተነሱ ችኩል ጥያቄያዊ ትችቶች የእነዚህ እሴቶች ቀስ በቀስ መሸርሸር ነጸብራቅ ነው። በብድር፣ በመዋጮ እና ጥሪት አሟጠው አገር ለቀው የሚሰደዱ ሰዎች እና ቤተሰቦቻቸውን በጥንቃቄ በመጠየቅ እና በማነጋገር ለመረዳት ከመጣር፣ ሕይወታቸውን ለመመርመር ከመሞከር እና የኑሯቸውን የትርፍ እና የኪሳራ ስሌት መዋቅር (risk and reward structure) በጥሞና ከማጥናት ይልቅ “ኢንፎርሜሽን የላቸውም፣ ተሸውደዋል፣ ያላቸውን ዕድል መጠቀም አልሞከሩም” ወዘተ የሚሉ መረጃ ላይ ያልተመሠረቱ-ከወንድማማችነት፣ ከወገንተኝነት እና ከባልጀሬ መንፈሶች ጋራ የተጻረሩ የሩጫ ፍርዶችን አስተውለናል። ከመደብ ልዩነት ከመነጩ ከእነዚህ ፍርዶች-በ13 ዓመት የእድገት ሂደት ውስጥ እንዲህ ያለውን ክፍፍል ካየን ጥቂት ቆይተን “ለምን ኬክ አይበሉም?” የሚል አሳፋሪ ትችትን ልንሰማ እንችላለን።
yilikal

2ኛ) የኢትዮጵያ መንግሥት ሲያፍን እንደ አንበሳ ሲጠብቅ እንደ ሬሳ ኾነ

የኢትዮጵያን የመንግሥት ሥርዐት ለመረዳት የሚፈልግ ሰው በዚህ ሳምንት የተፈጠሩ ሁለት ነገሮችን እና የእነርሱን ግንኙነት እንደ ምሳሌያዊ ማስተማርያ ሊወስድ ይችላል። የመጀመርያው፦ መንግሥት ሐዘንተኞች ከቁጥጥር ውጪ ወደኾነ ዐመጽ እንዳይገቡ የወሰደው ፈጣን እና ቁርጠኛ ርምጃ ነው። ሁለተኛው፦ የሐዘኑ ምንጭ ለኾነው የኢትዮጵያውን ስደተኞች ጥቃት ዘገምተኛ፣ አሻሚ እና የተዘበራረቀ መልስ መስጠቱ ነው። የመጀመርያውን የተመለከተ የኢትዮጵያን መንግሥት ብቃት (competence) ያስተውላል። ሁለተኛው ደግሞ የአስተዳደሩን ችግሮች አጉልቶ የሚያሳይ ነው። እነዚህ ልዩነቶች ከምን መነጩ? አምባገነን መንግሥታትን የሚያጠኑ የፖለቲካ ሳይንቲስቶች ከሚሰጧቸው መልሶች መካከል አንዱን እነኾ፦

የአምባገነን መንግሥታት ዋነኛ ዓላማ ዕድሜን ማራዘም (survival) ነው። ሌሎች ዓላማዎች ቢኖሯቸውም ሁሌም ከዕድሜ ማራዘም ያነሰ ቦታ ያላቸው ናቸው። ዕድሜ ለማራዘም ደግሞ ዋነኛ ስልታቸው አምባገነናዊ ቁጥጥር (authoritarian control) ነው። የአምባገነናዊ ቁጥጥር ሁለት መሣርያዎች አፈና (repression) እና ደልሎ መማረክ (co-optation) ናቸው። እነዚህ መንግሥታት ሁለቱን መሣርያዎች በጥንቃቄ እና በጥናት አቀናጅተው ይጠቀሙባቸዋል። የሁለቱ ቅንጅት ሚዛን ከጨቋኝ ጨቋኝ ይለያያል። አንዳንድ አምባገነኖች ከአፈናው ቀነስ፣ ከማባበያው ጨመር ያደርጋሉ። ሌሎቹ ደግሞ ወደ አፈና ያዘምማሉ። ለምሳሌ በሶቭየት ሕብረት አምባገነናዊ ቁጥጥር ላይ ጥናት ያደረጉት ዲሚትሪ ገርሸንሰን የቅንጅቱን ሚዛን በተመለከተ በስታሊን እና በብሬዥኔቭ መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት ያትታሉ። የአምባገነኖች ዓላማ ዕድሜን ማቆየት በመኾኑ አገዛዞቻቸው ከሁሉም በላይ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጧቸው እና የሚያፋፏዋቸው እነዚህን ሁለት የቁጥጥር መሣርያዎች በተግባር የሚያውሉትን ተቋማት ነው። እነዚህ ተቋማት የተሻለ የሰው ኃይል እና ሌሎች እምቅ ሀብቶች (resource) ያገኛሉ፤ ተወርዋሪ እና አዳዲስ ነገሮችን መፍጠር የሚችሉ ይኾናሉ። በረዥም ጊዜ ዕውቀት እና ብልኃት ያከማቻሉ። ቀልጣፋም ይኾናሉ። ይህ ልዩነት ያለው በተቋማት መካከል (inter-institutional) ብቻ ሳይኾን በተቋማት ውስጥም (intra-institutional) ነው። አንዳንድ ተቋማት አምባገነናዊ ቁጥጥርን ከሌሎች ተግባራት ጋር ቀላቅለው ይሠራሉ። እንዲያ ሲኾን ይህን ሥራ የሚሠሩ ዲፓርትመንቶች እና ዴስኮች ከሌሎቹ ይልቅ ልዩ ትኩረት እና ክብካቤ ይደረግላቸዋል።

በዚህ ምክንያት ብዙ አምባገነን መንግሥታት አምባገነናዊ ቁጥጥርን የማይመለከቱ ድንገተኛ ቀውሶች እና ችግሮች ሲገጥሟቸው በዝግጁነት እና በአቅርቦት ችግር ምክንያት ፈጣንና ቁርጠኛ መልስ ለመስጠት ይቸገራሉ። በሜክሲኮ፣ በኒከራጓ፣ በበርማ፣ በግብጽ እና በሶቭየት ሕብረት የተሠሩ ጥናቶች እንደዚህ ዐይነቱን የተቋማት አለመመጣጠን እና የሚያስከትሉትን ችግር ይዳስሳሉ። ሙሉ ለሙሉ አምባገነንነት ውስጥ የተዘፈቀው የኢትዮጵያ መንግሥትም ከአምባገነን ቁጥጥር ውጪ ያልታሰቡ የቤት ሥራዎች ሲደነቀሩበት ቢንገዳገድና ቢውተረተር ሊያስገርመን አይገባም። ያልተዘራ አይታጨድም።

mesfin
3ኛ) ፕሮፌሰር መስፍን ምሁራዊ አይበገሬ ናቸው

የ82 ዓመቱ ማርክሲስት ፈላስፋ ሮበርት ፖል ዉልፍ በሳምንት ሁለት ጊዜ በታዋቂው ብሎጋቸው (The Philosophers Stone) የዘመኑን ፖለቲካዊ ጥያቄዎች እያነሱ የሰላ አስተያየቶች ይሰነዝራሉ። አልፎ አልፎ አወዛጋቢ ሐሳቦችን እያነሱ ተከታዮቻቸውን ያሟግታሉ። በተጨማሪም ግሩም መጻሕፍት ያሳትማሉ። አንዳንድ ጊዜ በየዩኒቨርሲቲው እየዞሩ ሌክቸር ይሰጣሉ። ከሁለት ዓመታት በፊት ሰማንያኛ የልደት በዐላቸውን ሲያከብሩ በአዛውንትነታቸው እንዲህ ያለ ሕይወት (vitality) ያለው የሐሳብ እና የኮሚዩኒኬሽን ኑሮ የሚኖሩበትን ምክንያቶች አቅርበው ነበር። አንደኛ፦ በእርሳቸው ትውልድ ካሉ ጓደኞቻቸው ይልቅ ከወጣቶች ጋር መዋል፤ ሁለተኛ፦ ከዩኒቨርሲቲዎች እና ከሐሳብ መድረኮች አለመራቅ፤ ሦስተኛ፦ ውዝግብን እና ሙግትን አለመፍራት፤ አራተኛ፦ በሶሻል ሚዲያ እና ሌሎች ሚዲያዎች ላይ በንቃት መሳተፍ።

በዚህ ሳምንት ድፍን ሰማንያ አምስት ዓመት የኾናቸው ፕሮፌሰር መስፍን ከሁለተኛው በስተቀር ሌሎቹን የሮበርት ዉልፍ መመርያዎች በሃይማኖታዊ ወኔ የሚከተሉ ናቸው። ሁለተኛውን መመርያም የገደፉት ተገደው እንጂ ፈቅደው አይደለም። 60 ዓመታት ከቆየ የአደባባይ ምሁራዊ ኑሮ በኋላም እንኳ ፕሮፌሰር መስፍን በሐሳብ እና በፖለቲካ ሕይወት ያለመታከት መሳተፋቸውን አላቆሙም። አሁንም ልክ እንደ ቀድሟቸው ይጎነትላሉ፣ ይነቁራሉ፣ ያወዛግባሉ፣ ያበሳጫሉ፣ ያስጨበጭባሉ። ሐሳቦቻቸውንም ይኹን የፖለቲካ አቋሞቻቸውን የሚቃወሙ በርካታ ናቸው። የፖለቲካ ተሳትፏቸው የውጤት ምስክር ወረቀት (scorecard) ቢመረመር በቀይ እስኪሪብቶ የተጻፉ ብዙ ውጤቶች ይገኛሉ። አሜሪካዊው ታላቅ ዳኛ ጀስቲስ ኦሊቨር ዌንደል ሆልምስ እንደሚሉት የምሁር ሕይወት “በማያቋርጥ የጥይት እሩምታ መካከል ውስጥ ኾኖ ማሰብ ነው” ፤ አንዳንዴ ጥይቱ ያቆስላል። ሕይወት ያለው ምሁር ቁስሉን ሲያክ እና ሲደባብስ አይቆይም። በፍጥነት ተነስቶ ወደ ፍልሚያው ይመለሳል። ዕድሜ ሲገፋ እንዲህ ዐይነቱ ጽናት እና ጉልበት እየቀነሰ ይመጣል። ለምሁራዊ ኑሮ መልካም ዋጋ የሚሰጡ ማኅበረሰቦች የአዛውንት ምሁራንን ጉልበት ለመደገፍ እና ጽናታቸውን ለማደስ ብዙ ነገሮች ያደርጋሉ። በዩኒቨርሲቲዎች፣ በጥናት ተቋማት እና በሚዲያዎች ተቀማጫ ፌሎው (resident fellow) እየተደረጉ ከወጣት ምሁራን እና ከተማሪዎች ጋራ ንቁ መስተጋብር እንዲያደርጉ ዕድል ይመቻችላቸዋል። በኮንፈረንስ እና በየሌክቸሮች ይጋበዛሉ። የምርምር ረዳቶች ተመድበውላቸው መጽሐፍ ይጽፋሉ። ፖለቲከኞች እና ፖሊሲ አውጪዎችን ያማክራሉ። ፕሮፌሰር መስፍን ይኼን ማጣታቸው ብቻ ሳይኾን በሐሳባቸውን እና በፖለቲካ ተሳትፏቸው ምክንያት በአዛውንትነታቸው ዘብጥያ ከመውረድ አንስቶ ብዙ እንግልት አስተናግደዋል። ከእነዚህ ገደቦች እና ጫናዎች ጋር ተገዳድረው በጋዜጣ፣ በመጽሔት፣ በመጻሕፍት፣ እና በማኅበራዊ ሚዲያዎች መሳተፋቸውን ቀጥለዋል። ይህን ጽናታቸውን ለማድነቅ የአይዲዮሎጂያቸው ወይም የሐሳቦቻቸው ደጋፊ መኾን አያስፈልገንም። ሕይወት ላለው ምሁራዊ ኑሮ ጽዋችንን እናነሳለን፤ ለፕሮፌሰር መስፍን ደግሞ መልካም ልደት!!

Source: 7-killo Magazine

The post (በዚህ ሳምንት የተማርናቸው ሦስት ነገሮች) 1ኛ) “ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ለምን ኬክ አይበሉም?” … 2ኛ) የኢትዮጵያ መንግሥት ሲያፍን እንደ አንበሳ ሲጠብቅ እንደ ሬሳ ኾነ… 3ኛ) ፕሮፌሰር መስፍን ምሁራዊ አይበገሬ ናቸው appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>