ግብጽ የሃያ አንድ ክርስቲያን ዜጎችዋን በአይሲስ መታረድ ዜና እንደሰማች ዝም ብላ አልተቀመጠችም ነበር። ብሄራዊ የሃዘን ቀንም አላወጀችም። እንዲህ ነበር የሆነው። ከመቅጽበት ተዋጊ አውሮፕላኖችዋን አስነስታ ወደ ሊቢያ ላከቻቸው። የአይሲስ አራጆች የተከማቹበትን ደርና የተሰኘ ስፍራ እያከታተለች በቦምብ ቀጠቀጠችው። ብዙ አራጆች በድብደባው አለቁ። እንደ ግብጽ አጀማመር ቢሆን የሊብያው አይሲስ ክንፍ ድሮ-ድሮ ከምድረ-ገጽ ይጠፋ ነበር። ግና አልሆነም። አሜሪካ ጣልቃ ገባች። ግብጽ የአሜሪካን “ጸረ-ሽብር” ዘመቻ በማገዝዋ ምስጋና ማግኘት ሲገባት በተቃራኒው ተወገዘች። ከጥቂት ድብደባ በኋላ ፔንታጎን ግብጽን አስጠነቀቀ[0]። የኦባማ አተዳደርም ደብደባው በአፋጣኝ እንዲቆም ቀጭን መልእክት ላከ። ይህ ድርጊት ከዚህ ቀደም ስለ አይሲስ አፈጣጠር ኤድዋርድ ስኖደን[1] የለቀቀው ምስጢራዊ መረጃ ጋር ተዳምሮ በአሜሪካ ላይ የነበረውን ጥርጣሬው አጠናከረው።
ነገሩን ለማመን ያዳግት ይሆናል። በግልጽ የሚታዩ መረጃ እና ማስረጃዎች ግን ተአማኒነታቸው ጥርጥር ውስጥ የሚገባ አይደለም። “በአይሲስ እየታረዱ ያሉት ዜጎች የፊልም ቅንበር እንጂ እውነት አይደለም![2]” የሚሉ ባለሞያዎችም የትንተናቸው መነሻ ከዚህ ጉዳይ ጋር ይያያዛል።
ይህ አሸባሪ ድርጅት ስራውን ከጀመረ አንድ አመት ባልሞላ ግዜ ውስጥ ከመቶ ሺ በላይ ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ እንደገደለ ይናገራል። ቦምብ እንደዝናብ የሚወርድባቸው ሃገሮች፤ ሶማልያ፣ የመን፣ ኢራቅ፣ ሶርያ፣ አፍጋኒስታን፣ፓኪስታን… ተደምረው አይሲስ ከሚነግረን ግድያ ሩብ ያህሉንም አላደረጉም። የሃያላን ሃገሮች ምላሽ ግን በአፍ ከማውገዝ ያለፈ አለመሆኑ በአይሲስ አሰራር ላይ ተጨማሪ ጥርጣሬ ይፈጥራል።
አይሲስ የእስራኤል፣ የኢንግሊዝ እና አሜሪካ የጋራ ፕሮጀክት መሆንን ያጋለጠውን፤ የኤድዋርድ ስኖደን መረጃ እንደገና እንድንመረምረው ይገፋናል። በአይሲስ ዙርያ የሚተነትኑ አንዳንድ ጸሃፊዎች እጃቸውን በአሜሪካ ላይ መቀሰር ከጀመሩ ሰነበትበት ብለዋል። አሸባሪ ሃይልን መፍጠር ለአሜሪካ የመጀመርያ አይደለም። አላማው ይለያይ እንጂ ኦሳማ ቢን ላደንም የአሜሪካ ስሪት መሆኑ በይፋ ተገልጿል። የአሜሪካ ቁጥር አንድ ጠላት የነበረው ኦሳማ ቢን ላደን በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት በአሜሪካው የስለላ ተቋም፤ በሲ.አይ.ኤ እንደተፈጠረ በግልጽ ተቀምጧል። እ.ኤ.አ. በ1979 ሶቭየት ህብረት አፍጋኒስታንን በወረረች ግዜ ኦሳማ ቢን ላደን አማጺውን የሙጃህዲን ሃይል በመቀላቀል ወደ አፍጋኒስታን አመራ። በወቅቱ አሜሪካ ሙጃህዲንን ለማሰልጠን እና ለማስታጠቅ ሶስት ቢሊየን ዶላር እንዳፈሰሰች የብሪታንያው ዜና አገልግሎት ቢ.ቢ.ሲ. ዘግቧል። እንደ ቢ.ቢ.ሲ. ዘገባ ሲ.አይ.ኤ. ለኦሳማ ቢን ላደን በግል ደረጃውን የጠበቀ የኢንተልጀንስ ስልጠናም አድርጎለታል። ቀዝቃዛው ጦርነት ሲያበቃ እና ሶቭየት ህብረት አፍጋኒስታንን ለቅቃ ስትወጣ ነው ቢን ላደን አሜሪካ ላይ የዞረው።
የዘመናችን ዘግናኝ የሽብር ድርጅት የሆነው አይሲስንም የፈጠረችው አሜሪካ ናት የሚሉ ጸሃፍት ጥቂት አይደሉም። የእነዚህ ተንታኞች መረጃ በከፊል የሚንተራሰው ከአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት ኤጀንሲ ሰነድ የጠለፈው ኤድዋርድ ስኖደንን ነው። የአሜሪካ ስለላ ድርጅት NSA ውስጥ ይሰራ የነበረው ይህ ሰው የአሜሪካን ብሄራዊ ምስጢሮች ካጋለጠ በኋላ ሩስያ ውስጥ ተደብቋል። እርግጥ ነው። ኤድዋርድ ስኖደን የለቀቀው ሰነድ የአይሲስን አፈጣጠር ምስጢር በጥቁርና – ነጭ አስቀምጦታል። ሾልኮ የወጣው ይህ ሰነድ የአይሲሱ መሪ አቡባክር አል ባግዳዲ የአሜሪካ ደህንነት ግብአት እንደሆነ ይገልጻል። እንደ ምስጢራዊው የኬብል መረጃ ከሆነ ለአይሲስ መመስረት ሃላፊነቱን የሚወስዱት እስራኤል፣ ታላቋ ብሪታንያ እና አሜሪካ ናቸው። “ምክንያቱም” ይላሉ ዶክመንቱን የሚተነትኑ አምደኞች፣”ምክንያቱም እስላማዊ ጦረኞች የሚሏቸው ሃይሎች ሁሉ ከአለም ዙርያ እየሄዱ ሶርያ ላይ እንዲሰባሰቡ ነው።” ይህ ስትራቴጂ እውን ሲሆን፤ በአንድ በኩል በእነሱ የሚመራ ህይል ለማስቀመጥ እና በሌላ በኩል ደግሞ እስራኤል በቅርብ አደጋ ላይ መውደቋን ለማስመሰል የተወጠነ ታክቲክ ነው። መካከለኛው ምስራቅ ሽብር ያለ ማስመሰሉ አካባቢውን ዘልቆ ለመቆጣጠር ይረዳቸዋል። ይህን ለማድረግ አይሲስን እንደ ምክንያት ይጠቀሙበታል።”
የኤድዋርድ ስኖደን ምስጢራዊ መረጃ በጥሬው ተቀብለን፣ ስነዱን እንደማስረጃ ወስደን ለድምዳሜ መቸኮል የለብንም። ጉዳዩ ትንሽ ከበድ ያለ ነውና ሌሎች ተጓዳኝ ነገሮችን መመርመርም ተገቢ ይሆናል።
የእስላማዊ ዲሞክራቲክ ጂሃድ ፓርቲ መስራች እና ቀደም ሲል ከፍተኛ የአልቃይዳ ኮማንደር የነበረው ናቢል ናኢም ለሜዲያ የተናገረው መረጃ የኤድዋርድ ስኖደንን ማስረጃ ያጠናክረዋል። ናቢል ናኢም ለቤይርቱ ፓን አረብ ቴሌቭዥን በሰጠው ቃል፤ “አይሲስን ጨምሮ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያላቸው ደርጅቶች ሁሉ፤ በአሁን ሰዓት እየሰሩ ያሉት ለአሜሪካው የስለላ ተቋም ለሲ.አይ.ኤ. ነው።” ሲል በዚህ ወር መግቢያ ላይ ተናግሯል[3]።
ናቢል ናኢም በቴሌቭዥን የሰጠው አስደንጋጭ ምስጢር በዚህ አላበቃም፤ ሌላም ለማመን የሚከብድ ነገር አክሎበታል። አይሲስ በደንብ የሰለጠነ እና በደንብ የታጠቀ የሽብር ድርጅት ነው። መጠነ ስፊ የሆኑ የኢራቅን እና የሶርያን ክልሎች ተቆጣጥሯል።
የባህሬኑ “ዘ ገልፍ ዴይሊ ኒውስ” ጋዜጣም ባለፈው አመት አጋማሽ ላይ በዋና ገጹ የአይ.ሲስ መሪ አቡ ባክር አል ባግዳዲን የእስራኤሉ የስለላ ድርጅት ሞሳድ በጦር፣ በመንፈሳዊ ትምህርት እና በንግግር ክህሎት እንዳሰለጠነው ጽፏል[4]።
የዮርዳኖስ ባለስልጣናትን ጠቅሶ “ወርልድ ኔት ዴይሊ” የተሰኘው ጋዜጣ የአሜሪካ ወታደሮች በዮርዳኖስ ግዛት ውስጥ የአይሲስ አባላትን እንዳሰለጠኑ ዘግቧል[5]።
እነዚህን መረጃዎች በአንድ ወገን እንያዛቸው እና ወደ ሌሎች ምልከታዎች ደግሞ እንሂድ። ታላላቅ የአሜሪካ ጋዜጠኞችም የአይሲስ መጠናከር እና የአለም ዝምታ እንቆቅልሽ ነው የሆነባቸው። የፎክስ ኒውስ አምደኛ የሆነችው ግሬታ ቫን ሱስተረን እንግዳ የሆነባትን አስደንጋጭ የአይሲስ ግድያ እና የምእራባውያን ዝምታ እጅግ በመደነቅ ታነሳለች። አይሲስ በሺዎች የሚጠጉ ክርስቲያኖችን እያረደ፤ የተባበሩት መንግስታት፣ አሜሪካም ሆነ የአውሮፓ ህብረት ጉዳዩን ከምንም አልቆጠረውም ብላለች። ጋዜጠኛ ግሬታ ንግግርዋን ቀጠለች። “ያለነው በሂትለር ዘመን አይደለም። ዘመኑ የመረጃ ነው። እልቂቱን የሚያሳዩ መረጃዎች በግልጽ ይታያሉ። አሰቃቂ መረጃዎችን እየተመለከተ አለም ግን ዝም ነው ያለው። ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሊጋባን በማይችል ምክንያት ጉዳዩን ችላ ብሎታል። …” ትላለች።
ሌላው ሉ ዶብስ የተባለ በአሜሪካ ታዋቂ የቴሌቭዥን አቅራቢና ጸሃፊ፤ ህዝብ እየታረደ አለም ግን በአይሲስ ላይ ችላ ማለቱ እንዳስገረመው ይናገራል። ጋዜጠኛ ሉ ዶብስ ሜሪካዊውን ደራሲ ጆኒ ሞር በጉዳዩ ማብራርያ እንዲሰጥም አድሮታል። ጆኒ ሞር “Defying ISIS” “ውጉዝ መአሪዮስ አይሲስ” የሚል መጽሃፉ አይሲስን ከናዚዎች ጋር እያመሳሰለ ነው ያስቀመጠው። ጆኒ ሞር በፎክስ ኒውስ ላይ ቀርቦ የተናገረው ያስደምማል። “የ አይሲስ አራጆችን የጫኑ አርባ መኪናዎች በአንዲት የሶሪያ መንደር በነጻነት እየተዘዋወሩ 3000 ክርስቲያኖችን አፍሰው ወሰዱ። … ቦስንያ ላይ በቀን 140 ቦምብ ሲጥሉ የነበሩ የኔቶ ተዋጊ አውሮፕላኖች፣ በኢራቅ እና ሶርያ ላይ በቀን ከ 7 – 12 ቦምብ ሲጣል አይሲስ ግን ችላ ነው የተባለው።”
ጆን ዊልገር የተሰኘ የፖለቲካ ተንታኝ ደግሞ በአንድ ጥናታዊ ጽሁፉ፤ “አይሲስ የአሜሪካ ፍጡር ነው” ከማለት አልፎ፣ አይሲስን ከካምቦዲያው ካመሩዥ ጋር ያመሳስለዋል። በ 1969 እ.ኤ.አ. ፕሬዝዳንት ኒክሰን ካምቦዲያን በቦንብ አስደብድበው ሲያበቁ አንባገነኑ ፖል ፖትን አበቀሉ። የፖልፖት ካመሩዥ ከአይሲስ ጋር የሚያመሳስላቸው ነገር አለ። “ሁለቱም የአሜሪካ ውጤቶች፣ ሁለቱም የጨለማው ዘመን ጨካኞች ናቸው” ሲል ጽፏል።
ይህን ክስተት ስከታተል “ሲ. አይ. ኤ – ዘ ከልት ኦፍ ኢንተሊጀንስ” የተሰኘው መጽሃፍ ታወሰኝ። ቪክቶር ማርቼቲ የተባለ የቀድሞ ሲ.አይ.ኤ አባል የጻፈው “ዘ ከልት ኦፍ ኢንተሊጀንስ” መጽሃፍ አሚሪካኖች ብሄራዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር የማያደርጉት ነገር እንደሌለ ይነግረናል። ሲ. አይ.ኤ. የአሜሪካን ብሄራዊ ጥቅም ሲያስከብር ለሞራል እሴቶች፣ ለሰዎች ስብዕና እና ለፍትህ ቦታ እንደማይሰጥ ደራሲው ቪክቶር ማርቼቲ ይነግረናል። መጽሃፉ በከፊል በአሜሪካ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሳንሱር ተደርጎ የወጣ ነው። እንደዚህም ሆኖ ሲ.አይ.ኤ. ከረቀቀ ቴክኖሎጂ እስከ ረቀቀ ወንጀል እንደሚሰራ ይተነትናል። አሜሪካኖች ጉዳያቸውን ለማስፈጸም ዝናብ ማዘነብ ካለባቸው እንኳን፤ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ያንን ሊያደርጉ እንደሚችሉ መጽሃፉ ያሳየናል።
የአይሲስ አራጆች የሚናገሩት እንግሊዝኛ በአሜሪካ ቅላጼ (አክሰንት) ነው። አሜሪካ ተወልደው ያደጉ ሽብርተኞች ሊሆኑ ይችላሉ ብለን እንውሰድ። አይሲስ የሚለቅቃቸውን የቪድዮ ምስሎች የሚጠራጠሩ ባለሙያዎች፤ ጉዳዩን ከፖለቲካ ብቻ ሳይሆን ከሙያ አንጻርም ይመለከቱታል። የጃፓን ዜጎች ሲታረዱ የሚያሳየውን ቪድዮ ፍሬም፣ በፍሬም እያሳዩ የአይሲስ ግድያ ውሸት መሆኑን ለመግለጽ የሚሞክሩ የፊልም ባለሞያዎች የሚናገሩት ሙሉ በሙሉ ባያሳምንም ተመልካቹን ማደናገሩ አልቀረም[6]። እየወጡ ያሉት የግድያ ፊልሞች በአረንጓዴ ጨርቅ green screen በስቱዲዮ ውስጥ የሚሰሩ የትራይካስተር ቴክኒኮች ናቸው ብለው ነው እርግጠኝነት የሚናገሩት። ግሎባል ሪሰርች የተባለ አንድ የካናዳ የምርምር ተቋም፤ ISIS Video ‘Execution’ of Ethiopians in Libya Appears Fake [2] ሲል በሊቢያ የተሰዉት የኢትዮጵያ ሰማእታት ጉዳይ፤ የቪድዮ ቅንብር እንጂ እውነት አይደለም ሲል የምስሉን ፍሬም እየከፋፈለ በስሎው ሞሽን አቅርቦታል። ትንተናው አሳማኝ ላይሆን ይችላል። አይቶ መፍረዱ ግን ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም። ምኞታቸውም ከሆነ ይህ እውነት ይሆን ዘንድ ጸሎታችን ነው።
ያልተፈታ እንቆቅልሽ!
ለመሆኑ እስራኤል፣ የኢንግሊዝ እና አሜሪካ በጋራ ሆነው የአይሲስን ፕሮጀክት ለምን ፈጠሩ? የሚለው ጥያቄ ምላሽ ካገነ እንቆቅልሹን ይፈታው ይሆናል። ተንታኞች እና ተቺዎች ለዚህ በርካታ ምክንያቶችን ይደረድራሉ። አንደኛው ምክንያት እስራኤል በመሃከለኛው ምስራቅ ውስጥ ሁከት በመፍጠር የሁከቱ ተጠቃሚ ለመሆን እንድትችል ነው ይላሉ። ይህ ከሆነ እስራኤል በክልሉ ሃያልነቷን ሙሉ ለሙሉ ለማስከበር ይረዳታል ይላሉ። አይሁዶች ክርስትና እና እስልምና ጠላት ባይሆኑም በሁለቱም እምነቶች ላይ ችግር አለባቸው። ይሁንና አላማቸው የአይሁድን እምነት ለማስፋፋት ሳይሆን የእስራኤልን በሄራዊ ጥቅም ማስጠበቁ ላይ ነው። የእስራኤል አላማ የሁለቱ ሃይማኖት ተከታዮችን እርስ-በእርስ ማፋጀትና ማዳከም ነው ብለው የሚጽፉም አሉ። በእርግጥ አረቦች በሙሉ ጸረ-አይሁድ ናቸው። አረቦች በሙሉ ደግሞ ሙስሊሞች አይደሉም። እንደፍልስጤም፣ ኢራቅ፣ ዮርዳኖስ፤ ሊባኖስ እና ሶርያ ባሉ አረብ አገሮች ክርስቲያኖችም አሉ።
አሜሪካ እና እንግሊዝም ከዚህ ሽብር ጀርባ የሃገራቸውን ብሄራዊ ጥቅም ያስከብራሉ። አለምን በአሜሪካ አምሳል መፍጠር ከሚለው የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲን በሌላው ከመጫን ባሻገር ከመካከለኛው ምስራቅ በኢኮኖሚ ዘርፍ የሚያገኙት ጥቅምም ቀላል የሚባል አይደለም። አንደኛው “ሽብርን መዋጋት” በሚል ምክንያት የጦር መሳሪያ ሽያጭ ነው። ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በመሳርያ ሽያች በአመት ከአራት ትሪልዮን ዶላር በላይ ገቢ ያገኙበታል። መካከለኛው ምስራቅ ሃገር ያሉ ዋና ዋና የነዳጅ ክምችቶችን ለመቆጣጠርም የእነሱ የሆነን ሃይል በሽብር ሰበብ በስፍራው ማስቀመጥ ግድ ነው።
አሜሪካ ለሃገሯ ብሄራዊ ጥቅም ስትል በሌሎች ላይ ቁማር መጫወት አይገዳትም። በዚያን በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት አሜሪካኖች ከምስራቁ ጎራ ጋር የቃላት ጦርነት ነበር ያካሂዱ የነበረው። ያ ወቅት ለእኛ ግን ቀዝቃዛ አልነበረም። ለሁለቱ ሃያላን ሃገሮች የጦር ቀጠና ነበርን። አይሲስ የአሜሪካ ፍጡር ይሁንም አይሁን ገፈቱን የምንቀምሰው እኛው ሆነናል። በሰማዕታቱ እልቂት ምክንያት ከገባንበት ብሄራዊ ሃዘን ገና አልተላቀቅንም። ሁኔታው ሰቅጣጭ፣ ድርጊቱ ቅስም ሰባሪ ነውና የሃዘኑ ሸክም በቀላሉ የሚወርድ አይመስልም። ከዚህ ሁሉ ሃዘን በኋላም በአልጃዚራ ቴሌቭዥን ላይ የቀረቡ ወጣቶች ከአገር ቤቱ ኑሮ ወደውጭ መውጣቱን እንደሚመርጡ ተናግረዋል። አሁን ያለውን መረጃ ብቻ ይዞ አይሲስን የፈጠረችው አሜሪካ ናት ብሎ መደምደም ባይቻልም፤ ጥቅሟን ካስጠበቀላት ይህንን ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማትል ያለፉ ተመክሮዎች ይጠቁሙናል። የሌላው ማለቅ፣ መረበሽና መተራመስ ለአሜሪካ ደንታ አይሰጣትም።
[0]http://www.americanthinker.com/blog/2015/02/obama_administration_egypt_bad_iran_good_israel.html
[1]http://www.hangthebankers.com/?s=snowden
[3]http://www.infowars.com/former-al-qaeda-commander-isis-works-for-the-cia
[4]http://www.gulf-daily-news.com/NewsDetails.aspx?storyid=381153
[5]http://www.infowars.com/blowback-u-s-trained-isis-at-secret-jordan-base/
[6]https://www.youtube.com/watch?v=QrdDavSw_Fg
The post አሜሪካ አይሲስን ለምን ፈጠረችው? – ክንፉ አሰፋ appeared first on Zehabesha Amharic.