Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

[በዚህ ሳምንት የተማርናቸው ሦስት ነገሮች] 1ኛ) ቶርቸርን እስከ መቼ “ጆሮ ዳባ ልበስ” እንለዋለን? – 2ኛ) የጦስ ዶሮ ለእርድ እየቀረበ ስለ ላባው መሟገት – 3ኛ) ወጣትነትን የሚበላውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ በብርቱካን ልደት እናስብ

$
0
0

1ኛ) ቶርቸርን እስከ መቼ “ጆሮ ዳባ ልበስ” እንለዋለን?

እ.ኤ.አ. በ2008 ዓ.ም የጆርጅ ታውን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር የኾኑት ጀምስ ራይመንድ ቭሪላንድ በቶርቸር ጉዳይ የተለመደ አስተሳሰባችንን የሚፈታተን አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ አሳትመው ነበር። በርካቶች ለፖለቲካ ፓርቲዎች እና ለገልለተኛ ፕሬስ ምንም ቦታ የሌላቸው አምባገነኖች ለይስሙላም ቢኾን የፓርቲ ፉክክር እና ምርጫን ከሚፈቅዱ አምባገነኖች በተለየ የከፉ ቶርቸር ፈጻሚዎች ናቸው ብለው ያስባሉ። የፕሮፌሰሩ ጽሑፍ ይህን አስተሳሰብ የሚመታ ነው። በጽሑፋቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲኖሩ የሚፈቅዱ እና የይስሙላ ምርጫ የሚያካሂዱ አምባገነን መንግሥታት (electoral dictatorships) ከሌሎች አምባገነን መንግሥታት የበለጠ ቶርቸር እንደሚፈጽሙ በጠንካራ ዴታ ላይ ተመሥርተው ያሳያሉ። ሁሉም አምባገነኖች ቶርቸር ይፈጽማሉ፤ የምርጫ አምባገነኖች ግን የበለጠ ይፈጽማሉ። ይህ ለምን ይኾን?
edom Jpurnalist
ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባሉባቸው አምባገነኖች የኩብለላ አደጋ (threat of defection) ተቃዋሚ ከሌለባቸው አምባገነኖች የላቀ ነው። ይህን አደጋ ለመቀነስ የምርጫ አምባገነኖች የተለያዩ ስልቶችን እና መሣርያዎችን ይጠቀማሉ። ከስልቶቹ መካከል አንዱ የኩብለላን ዋጋ እጅግ ከፍተኛ ማድረግ ነው። ለዚህ ደግሞ ቶርቸር ከዋነኛ መሣርያዎች አንዱ ነው። ይኹንና የምርጫ አምባገነኖች ቶርቸርን የመደበቅ እና የማዳፈን አቅማቸው የፓርቲ ውድድር ከሌለባቸው አምባገነኖች የተሻለ ነው። ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። የምርጫ አምባገነኖች ዓለምአቀፍ ጸረ-ቶርቸር ሕጎችን ለመፈረም አያቅማሙም። በዚህ ምክንያት ብዙዎች እነዚህ አምባገነኖች ቶርቸር ላለማድረግ የቆረጡ መስለው ይታይዋቸዋል። እነዚህ አገሮች የሚፈጥሯቸው የይስሙላ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት የሚሰጧቸው የዴሞክራሲያዊነት ድባብ ለአምባገነኖቹ አዎንታዊ አመለካከት (positive perception) ያላብሷቸዋል። ይህ አመለካከት እንደ ቶርቸር ያለ ክፉኛ ጥቃት አይፈጽሙም ተብሎ እንዲታመን ያደርጋል። መንግሥታቱ ይህን መሰሉን የማሰቃየት ተግባር ፈጽመዋል ተብለው ሲከሰሱ የመጀመርያ መስመር መከላከያቸው የይስሙላ ተቋማት መኖራቸውን መጥቀስ ነው። ይህ የሙግቱን መድረክ ያጨቀየዋል። አንዳንድ ጊዜ ራሳቸው የቶርቸር አጣሪ ኮሚሽኖችን በመፍጠር ተጠያቂነት ያለባቸው ለማስመሰል ይሞክራሉ። “የተሻሉ አምባገነኖች” የሚለው ስማቸው ቶርቸር አልፈጸምንም ብለው ሲከራከሩ ሙግታቸው እንዲደመጥ ዕድል ይፈጥርላቸዋል። ከግብጽ አብዮት በኋላ እንደተመለከትነው በእነዚህ ዐይነት አገራት የሚፈጸመው የቶርቸር መጠን እና ስፋት በደንብ የሚታወቀው ሥርዐቶቹ ከፈራረሱ በኋላ በሚደረጉ ምርመራዎች እና ጥናቶች ነው።

ባለፈው ሳምንት የዞን ዘጠኝ ታሳሪዎች ላይ የደረሰው ቶርቸር በታሳሪዎቹ በራሳቸው ተጋልጧል። ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በታሳሪዎቹ ከገባው አቤቱታ መካከል በተለይ በሁለቱ ሴት ታሳሪዎች ላይ የደረሰው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እና ግፍ ሲያስቡት ያጥወለውላል። ማሕሌት እና ኤዶም ራቁታቸውን በመርማሪዎቻቸው ፊት እንዲቆሙ ተደርገዋል፤ ክብራቸው እና ሰብእናቸውም ተደፍሯል፤ እንደዚህ ዐይነት ቶርቸር እ.ኤ.አ በ1930ዎቹ በጀርመን “verschärfte vernehmung” በሚል ስም የተፈጠረ ነው። ዓላማው በሰውነት የአካል ክፍል ላይ ምንም ዐይነት ጠባሳ ሳይታይ እስረኛን ማሰቃየት ነው። እስረኞች ቶርቸር ተደርገናል ብለው ጠባሳቸውን እንደ ማስረጃ እንዳያሳዩ ያደርጋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ በፊት ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን፣ ርዕዮት ዓለሙን እና እስክንድር ነጋን ጨምሮ በበርካታ የፖለቲካ ተቀናቃኞቹ ላይ እንዲህ ዐይነት ዝምተኛ ቶርቸር ፈጽሟል። እነዚህ ሰለባዎች ከእስር ቤት የሰቆቃ ድምጻቸውን ሊያሰሙላቸው የሚችሉ ደጋፊዎች እና ወዳጆች ያሏቸው ባለ ከፍተኛ ስም (high profile) ታሳሪዎች ናቸው። ባለፉት ዐሥር ዓመታት በተለያዩ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የወጡ ዳጎስ ያሉ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት በሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን (በኦጋዴን፣ በኦሮምያ፣ በአማራ ክልል፣ በአዲስ አበባ ወረዳ ስምንት ቶርቸር ቻምበር) ጠባሳ ለመደበቅ ሙከራ ያልተደረገባቸው ስቃዮች ተፈጽሞባቸዋል። እነዚህ እንግዲህ በአጥኚዎች ምርመራ የታወቁ ናቸው፤ ያልታወቁትን ቤት ይቁጠራቸው።

ይህ ሁሉ ኾኖ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ልክ እንደ ሙባረክ መንግሥት ሁሉ የቶርቸር ዲፕሎማሲን ያሸነፈ ይመስላል። የመንግሥቱ ስም ከቶርቸር ጋር የሚነሳበት አጋጣሚ እጅግ ውሱን ነው። አገር ውስጥም ቢኾን የኢትዮጵያ መንግሥት ስለሚጨፈልቃቸው የተለያዩ ሕገ መንግሥታዊ መብቶች የፖለቲካ ውዝግብ ቢኖርም በአገሪቱ እየተደረገ ያለው መጠነ ሰፊ የማሰቃየት ተግባር ግን በሚገባው መጠን ሲወሳ እና የክርክር እና የሙግት ማዕከል ሲኾን አይታይም። የቶርቸር የፖለቲካ ጉልህነት (political salience) አለማግኘት ለኢትዮጵያ መንግሥት ጠቅሞታል፤ ምክንያቱም መንግሥት ጥሷቸዋል ተብለው በተደጋጋሚ ከሚጠቀሱት መብቶች በላይ ቶርቸር የፖለቲካ ጎራውን እና ጨዋን ኅብረተሰብ በሙሉ የሚያስቆጣ እና የሚያጥወለውል በመኾኑ ቅንጅት ያለበት ተቃውሞን የማፋፋም ዕድሉ ከፍ ያለ ነው። ከዞን ዘጠኝ፣ ከእነ እስክንድር ነጋ እና ከአጠቃላዩ የፖለቲካ እስረኛ የሚመጡትን የሰቆቃ ድምጾች ጆሯችንን ከፍተን እናድምጥ።
Yilikal
2ኛ) የጦስ ዶሮ ለእርድ እየቀረበ ስለ ላባው መሟገት

የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ይልቃል ጌትነት ኢንተርቪው ሲሰጡ እና ንግግር ሲያደርጉ ብዙ ጊዜ ሶሻል ሚዲያ ይታመሳል። በተለይ በተቺዎቻቸው ዘንድ ጥልቅ አሉታዊ ስሜትን ይቀሰቅሳሉ። “የአዲሲቲቱን ኢትዮጵያ ኹኔታ ያልተረዱ አክራሪ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛ፣ የአሮጌው ሥርዓት ናፋቂ፣ የፖለቲካ እና የፖሊሲ እውቀት የሌላቸው፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን አይዲዮሎጂ እና የፖለቲካ ስልት ወደ 1980ዎቹ የሚመልሱ” ወዘተ የሚባሉ ክሶች ይሰነዘሩባቸዋል። በዚህ ሳምንት ሊቀመንበሩ በአሜሪካ የኢትዮጵያውን ስብሰባ ላይ ያደረጉት ንግግር ከተሠራጨ በኋላ እርሳቸው እና ፓርቲው እነዚህን ትችቶች እንደ አዲስ አስተናግደዋል። በተመሳሳይ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት ፓርቲው ላይ ከፍተኛ ጥቃት ሊፈጽም እንደተዘጋጀ የሚጠቁም መጠነ ሰፊ ፕሮፖጋንዳ የመንግሥት ሚዲያን በመጠቀም እያፋፋመ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ፓርቲው ባለፈው ሳምንት በመስቀል አደባባይ በአይሲስ የተገደሉ ኢትዮጵያውያንን ለማሰብ በተጠራው የሕዝብ ስበሰባ ላይ “የተቃውሞ ጩኸት አቀነባብሯል፣ ኹከት ለመፍጠር ሞክሯል” ሲል ይወነጅለዋል። በቅርብ ጊዜ በርካታ የፓርቲው አባላት የመንግሥት ዱላ አርፎባቸዋል። የእነዚህ ሁለት ክስተቶች ግንኙነት መረዳት ስለ ሰማያዊ ፓርቲ ብቻ ሳይኾን በአምባገነን አገሮች ስለሚደረጉ በፓርቲ ዙርያ ስለተደራጁ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ጥሩ ግንዛቤ ይሰጠናል።

አምባገነን መንግሥታትን የሚያጠኑ የፖለቲካ ሳይንቲስቶች የተቃውሞ ፓርቲ ፖለቲካን በተመለከተ የሚያነሱት አንድ እንቆቅልሽ አለ፤ ምርጫን በሚያደርጉ አንዳንድ አምባገነን መንግሥታት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጫን የማሸነፍ መጠነኛ የኾነ ዕድል አላቸው። እነዚህ የፉክክር አምባገነናዊ ሥርዐቶች (competitive authoritarianism) ይባላሉ። ከእነዚህ ሥርዐቶች ውጪ ግን በሌሎች የምርጫ አምባገነን መንግሥታት ተቃዋሚዎች ምርጫን የማሸነፍ ዕድላቸው ወደ ዜሮ ይጠጋል። ይህን ፓርቲዎቹም ያውቁታል፤ ደጋፊዎቻቸውም ይገነዘቡታል፤ ሌላውም ሕዝብ ይረዳዋል። ነገር ግን እነዚህ ፓርቲዎች በየጊዜው ለምርጫ ይሳተፋሉ፤ ከዚያ ጋር ተያይዞ አባሎቻቸው ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ይቀበላሉ። እንቆቅልሹ ይህ ነው፡- የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካው መድረክ አመክኗዊ ተዋናይ (rational actor) ከኾኑ እንዲህ ዐይነት ኹኔታ ሲያጋጥማቸው እንደ ከሰረ ቢዝነስ ለምን ራሳቸውን አይዘጉም? ወይም መጀመርያውኑ ለምን ይፈጠራሉ?

ይህን ለመመለስ ብዙ ቲዎሪዎች ተነድፈዋል፤ ብዙ ኢምፔሪካል ምርመራዎች ተደርገዋል። ከእነዚህ ጥናቶች ውስጥ የወርቅ ደረጃ ካገኙት አንዱ ኬኔት ግሪን በላቲን አሜሪካ አምባገነን መንግሥታት ላይ ያደረጓቸው ጥናቶች ናቸው። እንደ ግሪን በእንደዚህ ዐይነት አምባገነን መንግሥታት የሚፈጠሩ ፓርቲዎች ዋነኛ ባሕርያቸው ሐሳብ ገላጭነት (expressive) ነው። ሐሳብ ገላጭ ፓርቲዎች በምርጫ የማሸነፍ ዕድል ባይኖራቸው እንኳ የፓርቲውን አባላት ጥልቅ ተቃውሞ በፖለቲካ መድረኮች ለማሳየት ይኖራሉ። ሐሳብ ገላጭ ፓርቲዎች በአምባገነን አገራት ብቻ ሳይኾን በዴሞክራሲያዊ አገራትም ይመሠረታሉ። ለምሳሌ በአሜሪካ ሊበሪቴርያን እና ግሪን ፓርቲዎች ምርጫን እንደማያሸንፉ ቢያውቁም ምርጫን ጨምሮ በተለያዩ የፖለቲካ መድረኮች ሲሳተፉ ረዥም ጊዜ አስቆጥረዋል። በአምባገነን መንግሥታት ወደ ተቃውሞ የፓርቲ ፖለቲካ መምጣት ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላል። ግሪን እንደሚሉን እና በሌሎች ጥናቶች እንደተረጋገጠው የአይዲዮሎጂ ጽናት እና ታማኝነት ያላቸው ሰዎች ከሌሎች በበለጠ ይህን ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ናቸው። ወደ ፖለቲካው መድረክ መጥተው የሚገነቧቸው ፓርቲዎች የአይዲዮሎጂ ፍጹማዊነት (ideological purism) ይታይባቸዋል። በተጨማሪም እንደዚህ ዐይነት የአይዲዮሎጂ ጽናት እና ፍጹምነት ከመንግሥት የሚመጣ ጥቃትን ለመከላከል ይጠቅማል። መሀል ሰፋሪዎች ጫናን አለመቋቋም ብቻ ሳይኾን ለመንግሥት ማባበያዎች የመንበርከክ ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው። ስለዚህ በአምባገነን ሥርዐት የምናገኛቸው ፓርቲዎች በአብዛኛው የአይዲዮሎጂ ፍጹማዊነት የሚታይባቸው ናቸው። ይህን አንዳንድ ጊዜ በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ስትራቴጂካዊ መተባበር እንዳይኖር ያደርጋል። ይኹንና ለእነዚህ ፓርቲዎች መኖር ከፍተኛ አስተዋጽዖ አለው። አቶ ይልቃልም ይኹኑ ፓርቲያቸው ለመሀል ሰፋሪ (median voter) የሚመች አይዲኦሎጂ እና ፖሊሲ ባያመጡ ሊገርመን አይገባም። የአምባገነንነት ተጨባጭ ኹኔታዎች ውጤት ነው። ግሪን እንደሚያሳዩን በተለያዩ ምክንያቶች አምባገነን መንግሥታት እየተዳከሙ መጥተው ወደተፎካካሪ አምባገነናዊነት ወይም ዴሞክራሲያዊ ሥርዐት ከተቀየሩ የእነዚህ ፓርቲዎች ባሕርይም ይለወጣል። አይዲዮሎጂያዊ ፍጹማዊነታቸውም ይቀንሳል። የፖለቲካ ተሳትፎ ዋጋ (cost of participation) ሲቀንስ ብዙ የመሀል ሰፋሪዎች እነዚህን ፓርቲዎች ስለሚቀላለቀሉ የፓርቲዎቹ አቋም ይለዝባል። በተጨማሪም ፓርቲዎቹ በምርጫ ለማሸነፍ ሲሉ ፍጹማዊ ፖሊሲዎቻቸውን እና አይዲዮሎጂያቸውን ያረግባሉ፤ ያለሰልሳሉ፤ ከሐሳብ ገላጭነት ወደ ምርጫ ፓርቲነት (electoral party) ይሸጋገራሉ።

ይህ ከኾነ ከእነ ሰማያዊ ፓርቲ ዐይነት ቡድኖች ጋር “ጽንፈኝትህን ቀንስ አትቀንስ፣ ፖሊሲህ አይረባም ይረባል” ብሎ መነታረክ ነጥብ ዐልባ እና ጉንጭ አልፋ ይኾናል። መጀመርያውኑ እንደ ፓርቲ እንዲፈጠሩ ያደረጋቸው፤ በኋላም የመቆየት ዕድላቸውን ያሰፋው እና ዕድሜያቸውን የሚያራዝመው የአይዲዮሎጂ ጽናታቸው ነው። በሥርዐቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንደ ሐሳብ ገላጭ ፓርቲ ከተመለከትናቸው የሚያስጨንቀን ለመሀል ሰፋሪ የሚማርክ ፖሊሲ እና አይዲዮሎጂ ይዘው መምጣታቸው ሳይኾን የሚደርስባቸው የመብት ጥሰት እና እንግልት ይኾናል። ከአቶ ይልቃል ጌትነት ንግግር ይልቅ አሳሳቢው የኢትዮጵያ መንግሥት ለእርሳቸው እና ለፓርቲ ባልደረቦቻቸው የሳለው ቢላዋ ነው።
birtukan-mideksa
3ኛ) ወጣትነትን የሚበላውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ በብርቱካን ልደት እናስብ

በኢትዮጵያ ተቃውሞ ፖለቲካ ኅየንተ ክብር ያገኙት ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በዚህ ሳምንት 41ኛ የልደት በዐላቸውን አክብረዋል። በብርቱካን የፖለቲካ ሕይወት መነጽር ኢትዮጵያ ለስለስ ካለ አምባገነንነት ወደ ሙሉ አምባገነንት ያደረገችውን ሽግግር ልንቃኘው እንችላልን። እርሳቸው በ26ዓመታቸው ለጸረ ሙስና አጀንዳ የፓርላማ ተወዳዳሪ ኾነው ወደ ፖለቲካ ብቅ ሲሉ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት እየተጠናቀቀ ነበር። በጦርነት ወቅት የታየው ትብብር ለወደፊቱ የዴሞክራሲያዊ እና የባልንጀሬነት መሠረት ይኾናል ብለው የገመቱ በርካቶች ነበሩ። በዚያ ምርጫ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) “አዲስ አበባን ነጻ እናውጣ!” በሚል መፈክር ስር ተንቀሳቅሶ ማሸነፍ ባይሳካለትም በየወረዳው ገዢውን ፓርቲ ተገዳድሮ ነበር። ከብዙዎቹ የሽንፈት ምክንያቶች መካከል ዋነኛው በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የተፈጠረው የድምጽ መከፋፈል ነበር።

ወይዘሪት ብርቱካን 27ኛ ዓመት የልደት በዐላቸውን ሲያከብሩ በኢሕአዴግ ውስጥ ክፍፍል ተነስቶ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አሸናፊነት ተጠናቀቀ። አቶ መለስ ተሸናፊን ቡድን ወደ ኋላ የሚያይ እና ራሳቸውን ደግሞ ወደፊት የሚመለከቱ፤ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲን እና ካፒታሊዝምን የሚያጸኑ አድርገው አቀረቡ። በክፍፍሉ ተሸንፈው ለእስር የተዳረጉት አቶ ስዬ አብርሃን በመፍታት ወይዘሪት ብርቱካን ብሔራዊ ትኩረት አገኙ። በተለይ በአዲስ አበባ በወቅቱ የተቀሰቀሰው ኹከት ለበርካታ ወጣቶች መታሰር እና መሞት ምክንያት ቢኾንም የአቶ መለስ ቃል ኪዳን ላይ ተመሥርተው መጪውን ጊዜ በተስፋ የሚጠብቁ ብዙ ነበሩ። በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት እየተሻሻሉ የመጡት የፕሬስ፣ የመደራጀት፣ የመሰብሰብ እና የመናገር ጥበቃ ይህን ተስፋ አጠናከረው። አቶ መለስ በምዕራብ አገር ከተሞች እየዞሩ “ዲሞክራሲን አሰፍናለሁ፣ ኢኮኖሚን አሳድጋለሁ፣ ሲቪል ሶሳይቲ እንዲሰራፋ አደርጋለሁ፤ የሚሰጠኝ ብድር እና ርዳታ እጥፍ ይደረግልኝ” እያሉ ሲወተዉቱ ነበር። በመሬት ላይ መሻሻሎች እየታዩ ስለነበረ ጥያቄ እና ጥርጣሬ አልተነሳባቸውም። ይህ አድቮኬሲ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት አጥተውት የነበረው ክብር መልሶ አስገኘላቸው፤ የብሌየር ኮሚሽን ዋነኛ አባል እንዲኾኑም አደረጋቸው። እነዚህ ለውጦች እያደጉ ሄደው ምርጫ 97ን ወለዱ።

ብርቱካን ሚደቅሳ በ32 ዓመታቸው የአገሪቱ ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ ተቀዳሚ ፕሬዝዳንት ሲኾኑ ከመጪዎቹ ዘጠኝ ዓመታት መካከል አራቱን በእስር ቤት፤ ሦስቱን ደግሞ በስደት ያሳልፋሉ ብሎ የጠበቀ አልነበረም። በምርጫው ምክንያት የተነሳው ውዝግብ ጦዞ ብርቱካን እና ሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ዘብጥያ የወረዱት፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር በፍጥነት እየጠበበ የመጣው እና ጥበቃቸው የተሻሻለ ይመስል የነበረው መብቶች የተቀለበሱት፣ እርሳቸው የልደት በዐላቸውን ባከበሩ በስድስተኛ ወሩ ነበር። በዚህ ሳምንት ወይዘሪት ብርቱካን ልደታቸውን ያከበሩት በስደት ነው፣ ከእስር ፋታ ሲያገኙ የፈጠሩት ፓርቲ ከመንግሥት በደረሰበት ጥቃት እና በውስጥ ችግር ምክንያት ተዳክሟል። እርሳቸው ወደ ፖለቲካ ሲመጡ የነበረው የዴሞክራሲ ተስፋ ጨልሟል።

በዲሞክራሲያዊ አገሮች እንደ ብርቱካን ያሉ በወጣትነታቸው ብዙ የተጓዙ እና ብሔራዊ ትኩረትን ያገኙ ፖለቲከኞች 41 ዓመት ሲኾናቸው ከተሞክሯቸው ተምረው፣ የአመራር ብቃታቸውን አሻሽለው፣ የአይዲዮሎጂ እና የፖሊሲ ግንዛቤያቸውን አዳብረው የሞያቸው ጫፍ ላይ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። አምባገነን ሥርዐት ግን በራሱ ቡድን ውስጥ ለሌሉ ወጣቶች እንዲህ ያለውን ዕድል አይሰጥም። ወይዘሪት ብርቱካን 41ኛ ዓመት የልደት በዐላቸውን ሲያከብሩ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ብዙ አስተዋጽዖ ማድረግ እየቻሉ በጡንቻ ከመድረኩ እንዲገለሉ የተደረጉ ወጣቶችን እናስባለን፤ ለወይዘሪት ብርቱካን ደግሞ ረዥም ዕድሜ እንመኛለን።

Source: 7-killo Magazine

The post [በዚህ ሳምንት የተማርናቸው ሦስት ነገሮች] 1ኛ) ቶርቸርን እስከ መቼ “ጆሮ ዳባ ልበስ” እንለዋለን? – 2ኛ) የጦስ ዶሮ ለእርድ እየቀረበ ስለ ላባው መሟገት – 3ኛ) ወጣትነትን የሚበላውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ በብርቱካን ልደት እናስብ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>