ሴይሙር ሀርሽ በምርመራ ጋዜጠኝነት (Investigative Journalism) አንጋፋና ስመ ጥር ከሆኑ የሙያው ሰዎች አንዱ ነው፡፡ ወደዚህ ስራ እንደተሰማራ ‹‹My Lai massacre›› በሚል ርዕስ የተዋጣለት ምርመራዊ ዘገባ አቅርቦ ነበር፡፡ ይህም እ.ኤ.አ በ1968 ዓ.ም የአሜሪካ ወታደሮች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችን እንደጨፈጨፉ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ዘገባ ነበር፡፡
ሀርሽ ከዚያን ጊዜ ወዲህ በርካታ የተደበቁ ምስጢሮችን እየፈለፈለ በማጋለጥ ይታወቃል፡፡ በተለይ ከ9/11 የአሜሪካ ጥቃት ወዲህ ኢራቅ ውስጥ በሚገኘው አቡ ጋሪብ እስር ቤት ባሉ እስረኞች ላይ የአሜሪካ ወታደሮች የሚፈፅሙትን ግፍ ይፋ አድርጓል፡፡ ‹‹60 Minutes›› የሚል ርዕስ ባለው የቴሌቭዥን ፕሮግራሙና በዘኒውዮርከር መፅሔት ላይ በምርመራ ጋዜጠኝነት ያገኛቸውን መረጃዎች ሲዘረግፍ ቆይቷል፡፡ በዚህ ሳምንት ደግሞ ሀርሽ አዲስ ሚስጢር ይዞ ለአለም ብቅ ብሏል፡፡
‹‹The White House’s Story (about the 2011 U.S Navy SEAL raid in Pakistan that killed Osama bin laden Might have been written by Lewis Carroll›› በሚል ርዕስ ነው ሚስጥሩን ይዞ ከች ያለው፡፡
ይሁን እንጂ ይህ የሀርሽ ፅሑፍ ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ ሲሰራበት በቆየው ዘኒውዮርከር መፅሔት ላይ ሊወጣለት አልቻለም፡፡ ፅሑፉን ያስተናገደለት ‹‹ለንደን ሪቪው ኦፍ ቡክስ›› ነው፡፡ እሁድ ዕለት ለንደን ሪቪው ኦፍ ቡክስ ላይ የቀረበው ይህ ፅሑፍ የበርካቶችን ቀልብ ስቦ በሰፊው ከመነበቡም በላይ በአለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ ሊሆን በቅቷል፡፡ የሚገርመው በዚሁ እለት ማንነታቸው ባልታወቁ ሀይሎች የለንደን ሪቪው ኦፍ ቡክስ ድረ ገፅ አደጋ ገጥሞት ከስራ ውጪ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
ሀርሽ ምን ይዞ መጣ?
ዋናውና አዲስ ነገር ሆኖ በሀርሽ ጽሁፍ የተጠቀሰው ቢን ላደንን ለመያዝ ስለተደረገው ዘመቻ የፕሬዝዳንት ኦባማ አስተዳደር ያስቀመጠው ስዕል ሙሉ በሙሉ ሀሰት መሆኑ ነው፡፡
ቢን ላደን የት እንደተደበቀ፣ ምን እየሰራ እንደነበርና ያለበት የጤንነት ሁኔታ ጭምር በአሜሪካና በፓኪስታን ባለስልጣናት እንደሚታወቅ ፅሁፉ ያስረዳል፡፡ በፓኪስታን ሰሜናዊቷ ከተማ አቦታድ የተከናወነው ‹‹ዘመቻ ቢን ላደን›› ግን እነዚህን እውነታዎች ወደ ጎን በመሸሸግ እንደነበር ይገልፃል፡፡
ከአንድ በጡረታ የተገለለ የአሜሪካ የስለላ ቢሮ ከፍተኛ የስራ ሃላፊ የተገኘውና በሀርሽ ጽሑፍ በዝርዝር ከቀረበው መረጃ ውስጥ የሚከተሉትን ነጥቦች ላካፍላችሁ፡፡
1. በ2011 የአሜሪካ ባህር ሃይል ልዩ ኮማንዶ (Navy SEAL) ቢን ላደን ተደብቆበታል በተባለው ሰሜን ፓኪስታን የአቦታባድ መኖሪያ ግቢ ውስጥ ያከናወነው ዘመቻ ድንገተኛ አይደለም፡፡ ኮማንዶቹ እንደተገለፀው በአደገኛና ምንነቱ ባልታወቀ ሁኔታ ውስጥ ልዩ ግዳጅ የተወጡም አይደሉም፡፡ ቢን ላደን በዚህ በአቦታባድ መኖሪያ ቤት ለአምስት ዓመት ያህል የፓኪስታን ጦር ሃይል እስረኛ ሆኖ ቆይቶ ነበር፡፡ ዘመቻው በዚያ ምሽት የተቀነባበረውም ሆነ ተብሎ በሂሊኮፕተር ወደ መኖሪያ ቤቱ እንዲያመሩ የተደረገውም በድብቅ ሳይሆን በስምምነት ነበር፡፡ በመሆኑም ኮማንዶቹ የገቡት የፓኪስታን እስር ቤት እንጂ የቢን ላደን መኖሪያ ቤት አይደለም፡፡
2. የፓኪስታን ጦር ሃይል ከፍተኛ የደህንነት አባላት ከአሜሪካ ኮማንዶዎች ጋር በመሆን በዘመቻው ወቅት ተሰማርተው ነበር፡፡ አቦታባዱን ‹‹መኖሪያ ቤት›› መግቢያና መውጫ የሚያውቁት እነዚህ የደህንነት አባላት ኮማንዶዎቹን እየመሩ ቢን ላደን ‹‹የታሰረበት›› ቦታ አድርሰዋቸው ነበር፡፡ በዚያ ምሽት የተተኮሰው አንድ ጥይት ብቻ ሲሆን፤ እሷም በአሜሪካ ኮማንዶዎች የተተኮሰችና ቢን ላደን ለሕልፈት የዳረገች ጥይት ነበረች፡፡
3. ከዘመቻው በኋላ በርካታ የአሜሪካ ባለስልጣናት የሚነገረው መግለጫ የአቦታባዱን ‹‹መኖሪያ ቤት›› የአሜሪካ ስለላ ተቋም (ሲአይኤ) አባላት እንደደረሰበት ነው፡፡ አንድ ለቢን ላደን የሚላላክ ሰውን ሲአይኤ ጠርጥሮት ባደረገው ክትትል መኖሪያ ቤቱን ለማወቅ እንደቻለ በሰፊው ሲዘገብ ነበር፡፡ ይህ ግን ሙሉ በሙሉ ውሸት ነው፡፡ ኢዝላማባድ ውስጥ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ የአቦታባዱ ‹‹መኖሪያ ቤት›› (እስር ቤት) ጉዳይ የተነገረው በሲአይኤ ሳይሆን ቢሮው ጠረጴዛ ላይ በተቀመጠለት መረጃ ነው፡፡
4. ቢን ላደን በአቦታባድ ‹‹መኖሪያ ቤት›› ውስጥ ታስሮ በቆየበት ጊዜ ሙሉ ወጪው የተሸፈነው በሳውዲ አረቢያ መንግስት ነበር፡፡
5. የፓኪስታን ጦር ሃይል ዶክተር ከቢን ላደን ዲኤንኤ (DNA) ወስደው በትክክል ራሱ መሆኑን ማረጋገጫ ጉዳዩ ለሚመለከተው መንግስት እንዲደርስ አድርገው ነበር፡፡ በመሆኑም ከዘመቻው በኋላ የኦባማ ባለስልጣናት በዚያ መኖሪያ ቤት ቢን ላደን ስለመኖሩ በእርግጠኝነት አናውቅም ነበር ያሉት ውሸት ነው፡፡
6. የፓኪስታን ከፍተኛ የጦር ሃይሉ ባለስልጣናት ማለትም የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጀነራል አሽፋቅ ፓርቪዝ ካያኒ እና የደህንነት ሃላፊው ጀነራል አህመድ ሹጃ ፓሻ ቢን ላደንን ለመያዝ (ለመግደል) ስለተደረገው ዘመቻ አያውቁም ነበር የተባለው ውሸት ነው፡፡
በአጠቃላይ ከላይ ከተቀመጡት ስድስት ነጥቦች በመነሳት ሀርሽ በፅሑፉ ያስቀመጠው ፕሬዝዳንት ኦባማና ከፍተኛ ባለስልጣናት የተናገሩት ሁሉ ሀሰት እንደነበር ነው፡፡ ቢን ላደንም በታሰረበት ቦታ እንደተገደለና እሱን ለመያዝ ምንም ጥረትና ስለላ እንዳልተደረገም ጭምር ነው፡፡
The post የኡሳማ ቢንላደን ግድያና የኦባማ ውሸት appeared first on Zehabesha Amharic.