በቅርቡ ሜርሰን ሄልዝ ኤንድ ሳኒቴሽን (Mercen Health and Sanitation Index) የተባለ ተቋም 25 የአለማችንን ከተሞች ቆሻሻ ሲል ፈርጇቸዋል፡፡ ተቋሙ እንደሚለው እነዚህ ከተሞች ንጽህና የሌላቸውና አየራቸው የተበከለ እንዲሁም በውስጣቸው የሚያልፉ ወንዞች በቆሻሻ የተሞሉ ናቸው፡፡ ተቋሙ በቆሻሻነት የፈረጃቸውን የአለማችን ከተሞች በቅደም ተከተል ሲያስቀምጥ የአዲስ አበባ መገኛ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ሆኗል፡፡ አስሩ ቆሻሻ ከተሞች በቅደም ተከተል እነዚህ ናቸው፡፡
1.ባኩ (አዘርባጃን)
የነዳጅ ሃብት እንዳላት የሚነገርላት አዘርባጃን በዋና ከተማዋ በኩል የቆሻሻነት ስሟን ተከናንባለች፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የአዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ በከፍተኛ የአየር ብክለት ውስጥ የምትገኝ ሲሆን በዚህም ሳቢያ ለህይወት አደገኛ ተብላ ተፈርጃለች፡፡ በካስፒያን ባህር የተከበበችው አዘርባጃን በነዳጅ ማውጣት ሂደትና በመርከቦች እንቅስቃሴ ወቅት በሚወጣ ጭስ የታፈነች መሆኗን የከተሞቹን ደረጃ ያወጣው ተቋም ገልጾዋል፡፡
2.ዳካ (ባንግላዲሽ)
ወንዞቿ ተበክለዋል፡፡ አየሯ ቆሽሾዋል፡፡ በየጎዳናዎቿ ላይ የወዳደቁ ቆሻሻ ነገሮችን መመልከት ብርቅ አይደለም፡፡ ይህቺ ከተማ ዳካ ትባላለች፡፡ የባንግላዲሽ ርዕሰ መዲና፡፡
በዚህች ከተማ በርካታ ሰዎች በጣም በተጠጋጋ ሁኔታ የሚኖሩ ሲሆን በዚህም ሳቢያ ለበሽታና ለሞት የመጋለጥ እድላቸው ሠፊ ነው፡፡
3. አንታናናሪቮ
(ማዳጋስካር)
የህዝብ ቁጥሯ በፍጥነት እየጨመረ ይገኛል፡፡ በዚህም ምክንያት ከጊዜ ወደጊዜ ለአየር ብክለትና ለንጽህና ጉድለት እየተጋለጠች ነው፡፡ 8ኛዋ አህጉር በሚል
ቅጽል ስም የምትጠራውና በህንድ ውቅያኖስ ላይ የሠፈረችው ማዳጋስካር ዋና ከተማዋ በቆሻሻነት 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
4.ፖርቶ
ፕሪንስ (ሄይቲ)
ከአመታት በፊት ከባድ ርዕደ መሬት ያስተናገደችውና በርካታ ዜጎቿን ያጣችው ብሎም የመሠረተ ልማቷ የወደመባት ሄይቲ ዋና ከተማ ፖርቶ ፕሪንስ ቆሻሻ ናት፡፡ አየሯና ውሃዋ ተበክሏል፡፡ የአየር ብክለትን ለመከላከል የሚደረገው እንቅስቃሴ ደካማ መሆን
ለከተማዋ መቆሸሽ ምክንያት ነው፡፡ በሙስና የሚታሙት የሄይቲ ባለስልጣናት ለህብረተሰቡ ጤና ግድ ያላቸው አይመስሉም፡፡
5.ሜክሲኮ ሲቲ
(ሜክሲኮ)
ደቡብ አሜሪካ ውስጥ ካሉት ዋና ከተሞች ሁሉ የሜክሲኮ ሲቲን ያህል በአየር ብክለት የተጎዳ የለም፡፡ ለዚያም ነው ከተማዋ ሁሌም በጭስ ተሸፍና የምትታየው፡፡
6.አዲስ አበባ (ኢትዮጵያ)
የኛዋ ከተማ አዲስ አበባ አፍንጫችን ይዘን
የምናልፍባቸው አካባቢዎችና ለማየት የሚቀፉ ወንዞችን የያዘች ከተማ ናት፡፡ ከፍተኛ የንጽህና ጉድለት ያለባትና ከክልል ከተሞች እንኳ በእጅጉ ባነሰ ደረጃ ላይ የምትገኘው አዲስ አበባ ከአለማችን ቆሻሻ ከተሞች ጎራ ተመድባለች፡፡ ሜርሰር ሄልዝ እንደሚለው በአዲስ አበባ ለውሃ ወለድ በሽታ የመጋለጥ እድል ከፍተኛ ነው፡፡ ልጆች ያለ እድሜያቸው የሚሞቱትም ለዚህ ነው ብሏል፡፡
7.ሙምባይ (ህንድ)
የህንድ መንግስት የሙምባይ ከተማን የንጽህና ችግር ለመቅረፍና የአየር ብክለትን ለመከላከል 1 ቢሊዮን ዶላር መድቦ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የአለማችን ቆሻሻ ከተሞች ጎራ ከመሰለፍ አላዳናትም፡፡
8.ባግዳድ (ኢራቅ)
የኢራቅ ህዝቦች ችግራቸው ጦርነት ብቻ አይደለም፡፡ በየዕለቱ ድንገት በሚፈነዱ ቦንቦች ብቻ ሳይሆን በውሃ ወለድ በሽታ ጭምር ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡ በተለያየ ጊዜ የኮሌራ በሽታ ተከስቶ በርካታ የባግዳድ ነዋሪዎችን ገድሏል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ፕሮግራም እንደሚለው በሚቃጠል ነዳጅና ከጦር መሳሪያዎች በሚወጣ ጭስ ሳቢያ ባግዳድ በአየር ብክለትም የተጎዳች ከተማ ናት፡፡
9.አልማቲ (ካዛኪስታን)
ነዋሪዎቿ ግዴለሽ ናቸው፡፡ የቤታቸውን ቆሻሻ ሁሉ እያወጡ በየመንገዱ ሲወረውሩ እፍረት አይሰማቸውም፡፡ መርዛማ የሆኑ ገዳይ ኬሚካሎችን ሳይቀር በግዴለሽነት በየቦታው ይጥላሉ፡፡ በዚህ ምክንያትም የካዛኪስታንዋ
ከተማ አልማቲ ለኑሮ የማትመች ሆናለች፡፡
10.ብራዛቪል
(ኮንጎ)
የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ያለባት ብራዛቪል ለጤና የማይመቹ ከሚባሉ ከተሞች አንዷ ናት፡፡ የንጽህና ጉድለትና የአየር መበከልም ሌሎች የከተማዋ ራስ ምታቶች ናቸው፡፡
ምንጭ – ቁምነገር መጽሔት
The post አስሩ የዓለማችን ቆሻሻ ከተሞች appeared first on Zehabesha Amharic.