ከፊታችን ባለው እሁድ በኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ ይካሄዳል። በዚህ ቀን በሕገ መንግሥቱ መሠረት ዐምስት መቶ ዐምሳ[i]
[1] ሹማምንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለፈደረሽኑ ሸንጎ ቤት ደግሞ አንድ መቶ ዐሥራ ሰባት አባላት ከሃያ ሁለቱ አነሳ ብሔረ-ስቦች በነፍስ ወከፍ አንዳንድ፣ የቀሩት በሌሎች አንኳል ክልሎች በሚሰጠው ድምፅ ይመረጣሉ። ተመራጮቹ ዐምስት ዓመት ካገለገሉ በኋላ የአላፍነታቸው ጊዜ ያበቃና ወይ እንደገና በዕጩነት ላዲስ ምርጫ ይወዳደራሉ፤ ካልፈለጉ ደግሞ ባሰኛቸው የሥራ ዘርፍ ይሰማራሉ። የእሁዱ ምርጫ ገዢው መንግሥት ደምብ ሠርቶ ሥነ-ሥርዐቱን አደላድሎ ከጀመረበት ወቅት አምስተኛ መሆኑ ነው። የመጀመርያው በ፲፱፻፹፯ ዓ.ም. ነበር። ከዚያ በኋላ ዐምስት ዐምስት ዓመቱን እየቈጠረ በ፲፱፻፺፪፣ ቀጥሎም በ፲፱፻፺፯ና በ፳፻፪ ዓ.ም. ተካሂዷል።
ዐምስተኛነቱን ይቊጠር እንጂ የመጀመርያው የ፲፱፻፹፯ ዓ.ም. ምርጫ ላይ ሜዳውም ፈረሱም የተያዘው በኢሕዴግ ብቻ ስለነበር እንዲያው ለስሙ እንጂ ትርጒም ስለሌለው፣ ለታሪክና ለይስሙላ ካልሆነ በስተቀር ምርጫውን ምርጫ ብሎ መጥራቱ ያዳግታል።። ለመምረጥ ቢያንስ ቢያንስ ሁለት ከተቻለ የማይመሳሰሉ ተመራጭ ቡድኖች መገኘት ይኖርባቸዋል። አለበለዚያ የቃላት ጨዋታ ነው ማለት ይቻላል። ከዚያም አልፎ ደግሞ በዚያ ምርጫ የተሳተፈው የሕዝቡ ቊጥር እምብዛም አጥጋቢ አልነበረም ማለት ይቻላል።
ሕዝብ በመጠኑ መሳተፍ የጀመረውና አማራጭ አሳብና የፓሊቲካ መርሐ-ግብር የያዘ ተቃዋሚ ፓርቲ ብቅ ያለው በ፲፱፻፺፪ ዓ.ም. ምርጫ ላይ ስለነበር፣ ለትርጒም የሚበቃ ምርጫ የተጀመረው በዚያ ዓመት ነው ማለት ይቀላል። ከዚያ በፊት ባለው ምርጫ ተቃዋሚዎች ነን ባዮቹ ፓርቲዎች በዝግጅታቸውም ሆነ በቁመበት ዓላማ ደካማ ነበሩ ብቻ ሳይሆን ጊዜያቸውን ያሳልፉ የነበሩት እርስ በርስ በመቦጫጨቅ፣ እሕዴግን በመተቸትና በምርጫው አንሳተፍም በሚል አድማ ነበር። በዚያ ዓመት በወጣቶች የሚመራ ኢዴፓ የተባለ ፓርቲ ትኩስ አሳብ ይዞ ብቅ ሲል በኢሕዴግ ብቻ ሳይሆን በነባሮቹ የተቃዋሚዎች የፓለቲካ መስክ ሥጋት አሳደረ። ኢዴፓ አዲስ መጤ ድርጅት ቢሆንም፣ በተሰጠው የውይይት መድረክ ባሳየው የክርክር ብስለትም ሆነ በቀየሰው አዲስ የፓለቲካ ስልትና አቀራረብ በብዙ ሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነትን አፈራ። የቆመበት ዓላማና ጥንሰ አሳብ የገዢው ፓርቲ ተፃራሪ እንደመሆኑ የሚያበረግገው ነበር። ኢዴፓ በጐጠኝነት ቦታ ኅብረ-ብሔርነትን፣ በጥላቻ ስፍራ መከባበርን፣ በቂምና በቀል ፈንታ መቻቻልን፣ መንግሥትን መተቸት ብቻ ሳይሆን የሠመረና የሰከነ ሥራ የሠራ መስሎ ከታየ አምኖ መቀበልንም ጭምር የአቋሙ መሠረታዊ እምነት አድርጎ ስለተነሣ፣ በገዢው አምባገነን ፓርቲ ጓሮ ያልታሰበና ያልተጠበቀ ረብሻ ፈጠረ።
ከዚህም የተነሣ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሰላማዊ መንገድ በመቃወም ለውጥ ማምጣት የሚቻል መሆኑን በማመን በ፲፱፻፺፪ ዓ.ም. ምርጫ በሰፊው ተሳተፈ። ኢዴፓ ገዢውን ፓርቲ ከማደናበር አልፎ፣ ርስበርስ በመጋጨትና በሥልጣን ላይ ባለው በማደም ብርቅ ጊዜያቸውን ያጠፉ የነበሩትን የተቃዋሚዎችን ድርጅቶች ዐይናቸውን በሚለያያቸው ጉዳይና በሌላው አቾቻቸው ጒድፍ ላይ መጣል ትተው፣ በሚያስተባብራቸውና የዘለቄታ ለውጥ በሚያመጣው እንዲያተኩሩና ተግተው እንዲሠሩ በማድረግ ሦስቱን ያኽል ወደጥምረትና ኅብረት ሊያመጧቸው ችሏል።
ከተመሠረተ አንድ ዓመት እንኳ ያልሞላው ኢዴፓ፣ በዚያው በ፲፱፻፺፪ ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ ሁለት ወንበሮች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ዐሥራ አራት ወንበሮች ደግሞ በክልሎቹ ለመቀዳጀት በቃ። በዚህ አስመስጋኝ ሥራ የድርጅቱ መሪና ከቈርቋሪዎቹ አንዱ የነበረው ወጣቱ አቶ ልደቱ አያሌው ከፍተኛ ሚና ተጫዉቷል፤ አድኖቆትንና ገናናነትንም አትርፏል። ርግጠኛ ነኝ አሁን አሉባልታና መሠረተ-ቢስ የመንደር ወሬ ዉጤት ነው ብዬ በማምነው ስሙ ጠፍቷል። አንዱን ከመሬት አንሥቶ እስከ ሰማይ ከካቡት በኋላ ድምጥማጡ እስኪጠፋ እመሬት ላይ መልሶ ወርውሮ መጣሉ በኢትዮጵያ ምድራችን የተለመደ ሁኗል። የአቶ ልደቱም ዕጣ ይኸው መራራ ጽዋ ሁኖ የቀረ ይመስላል። ሁሉንም ጊዜው ይበቀለዋልና፣ አገሩ መስመር ሲይዝ ግን፣ አቶ ልደቱ ገና በዚህ በለጋ ዕድሜው በሠራው ጥሩ ሥራው ታሪክ እያስታወሰውና እየወደሰው እንደሚኖር ጥርጥር የለኝም።
ኢዴፓ የከፈተውን በር ለመዝጋት ሲል መንግሥት የተለያየ ዘዴና ተንኰል በየጊዜው በመቀየድ፣ ድርጅቱን እስከማሳደድ፣ መሪዎቹን በግፍ እስር ቤት አጒሮ እስከማማቀቅ ድረስ ቢጠቀምም ወላፈኑን ሊያጠፋ ግን አልቻለም። አለመቻሉንም የ፲፱፻፺፯ ዓ.ም. ምርጫ ቊልጭ አድርጎ ያሳያል። በዚህ ምርጫ ድምፅ ሊሰጥ ከተመዘገበው ሕዝብ ዘጠና ከመቶው ሲሳተፍ፣ ሁለት ወንበር ብቻ ይዘው የነበሩ ተቃዋሚ ኀይሎች ከዐምስት መቶ አርባ ሰባት ወንበሮች መቶ ሰባውን ከኢዴፓ መንጋጋ ሲነጥቁ፣ በፖለቲካ ንቃቷ የመነጠቀችውን መናገሻ ከተማዋን አዲስ አበባ ከጫፍ እስከጫፍ ጠቅልለው በእጃቸው አደረጓት።
የተቃዋሚ ኀይሎች ይኸንን ያልተጠበቀ ድል ከተቀዳጁ በኋላ፣ እፍሬ ላይ ለማዋልና ለመረጣቸው ሕዝብ ውለታውን ለመመለስ ችሎታም ብቃትም ያላቸው ሁነው አልተገኙም። ከፊተኛው ምርጫ በኋላ እንዳደረጉ፣ አሁንም የግንባታ ሥራቸውን ሳይታክቱ እንደመቀጠል፣ የገዢው ፓርቲ ባዘጋጀላቸው ውስብስብ ወጥመድ ውስጥ ወደቁ እንጂ ምንም ጠቃሚ ሥራ ሊሠሩ አልቻሉም። ገዢው ክፍል ዱብዕዳ በሆነበት ድል ተረብሾ፣ አእምሮውን ስቶ ባንገደገደበት ወቅት፣ ተቃዋሚዎቹ ኀይሎች መተንፈሻ በማሳጣት፣ የመጡላቸውን ጥሩ አጋጣሚዎች ተጠቅመው ጠልፈውት በመጣል ፈንታ፣ አከታትለው የተሳሳተ እርምጃ በመዉሰዳቸው፣ የመጨረሻ ውጤቱ ሕዝቡን ለጭፍጨፋ፣ መሪዎቹን ራሳቸውን ለእስር መዳረግ ሁኖ ቀረ። እስር ቤትም ገብተው ብዙ ጊዜ ከማቀቁ በኋላ የግፍ ፍርድ ሲፈረድባቸው፣ የፈጸሙትን ትግል ሁሉ ኀጢአት እንደሠሩ አድርገው በመቊጠርና፣ ገዢው መንግሥት በፈለገው መልክ ባሰናዳው ሰነድ ላይ ስሕተታቸውን በጣታቸው ፊርማ ተናዘውና አምነው ይቅርታ በመጠየቅ ነፃ ተለቀው ወጡ።
በዚሁ እጅግ አሳዛኝና አሰቃቂ ሥራቸው በቋፍ ላይ የነበረውን መንግሥት ነፍስ ዘርቶ፣ አዲስ ሕይወት አግኝቶ እንደገና እንዲንሰራራ አደረጉት። የርስበርሳቸውም ፍርክስክሳቸው ወጣ። ከዚያ በኋላ የሆነው ታሪክ ያደባባይ ምሥጢር ነውና ሁሉም ስለሚያውቀው እዚህ ላይ መድገሙ አስፈላጊ ሁኖ አይታየኝም። ሥራቸው ብዙዎቹን እንደዚህ ዐይነቶቹ እንኳንስ ሥልጣን አልያዙም እስከሚሉ አድርሷቸዋል። የሚያሳዝነው ድምፁን ብቻ ሳይሆን፣ ገንዘቡንና ነፍሱን የዘመድ አዝማዶችንም ነፍስ በሞት የሠዋላቸውን የኢትዮጵያን ሕዝብ መሥዋዕት ምንም ሁኖ አልታያቸውም። ባክኖና መክኖ ቀረ። ፖለቲካ የትርፍ ጊዜ ጨዋታ እንዳልሆነ የተገነዘቡም አይመስልም። እንደዚያማ ቢሆን ኖሮ እነኔልሶን ማንደላና ጓደኞቻቸው እነግራምሽ የመሰሉትና ሌሎችም አብዛኛውን ወርቃማ ሕይወታቸውን በጨለማ እስር ቤት ባልማቀቁም ነበር። ላገርና ለሕዝብ፣ ለእውነትና ላመኑበት ዓላማ አለመቆም መዘዙ ብዙ ነው።
ሕዝብ በቅንጅት ሰበብ በደረሰበት ፍጅትና ግፍ ተማሮ በሰላማዊ ትግል ብቻ ሳይሆን በተቃዋሚዎችም ላይ እምነቱን እስከማጣት መድረሱን የምናየው በ፳፻፪ ዓ.ም. ምርጫ ነው። ተቃዋሚ ኀይሎች ማሸነፍ የቻሉት አንድ ወንበር ብቻ ስለሆነ አገሩም ሕዝቡም ተመልሰው ባንድ አምባጋነን መንግሥት ጡንቻ ሥር ወደቁ። መንግሥት ውጤቱ ሕዝብ ምን ይኽል በሠራው ሥራ ስኬት መደሰቱን ያሳያል ብሎ ቢደነፋም፣ እውነቱን በጊዜው ታዛቢዎች የነበሩትም ሆኑ ሌሎች በሰፊው መዝገበውታልና መመራመሩ አስፈላጊ አይደለም።
እኔ ማትኰር የምፈልገው ተቃዋሚ ፓርቲዎች በገዢው መንግሥት ላይ ያላቸው ደካማና የተዛባ አመለካከት ነው። ነገሩን ባንድ እውን ነገር ልጀምር። ከ፲፱፻፺፯ ዓ.ም. ምርጫ በፊት ሊቀ ሊቃውንት መሐንዲስ አድማሱ አሜሪቃ አገር ይጐበኙ ነበርና አትላንታም ከነዚያ አንዷ ነበረች። ያነ አላፍላጎቴ ጐትተውኝ አስገብተውኝ የቅንጅት ድጋፍ ኮሚቴ አባላት አሰባሳቢ አድርገውኝ ነበርና፣ ዕድሉን በመጠቀም ሊቀ ሊቃውንቱን ጋብዘናቸው አንዳንድ ጥያቄ መጠየቅ ጀመርን። ከሁሉም የከነከነኝና ሁሌዬም የሚገርመኝ፣ ተቃዋሚ ኀይሎች ቢያሸንፉና እሕዴግ ሥልጣኑን ሊለቅ ባይፈልግ የተዘጋጀ ዕቅድ ካለ፣ ሀ. ለ. ሐ. መ. ብለው ይግለጡልን አልኩኝ። የመጀመርያውን ከብዙ በውጭ አገር ከተከናወኑት ሁናቴዎች ጋር በማያያዝና እንደአብነት በመጠቀም ገለጡልን፡ ግን አጥጋቢ ባለመሆኑ የሚቀጥለውን ብንጠይቅ፣ ሊናገሩት ዝግጁ አለመሆናቸውን ቢያስታወቁንም አቋማቸው የምዕራባውያን ግፊት ስለሚኖር ኢሕዴግ ከተሸነፈ በኋላ ደፍሮ ሥልጣን አልለቅም አይልም የሚል ነበር። መልሳቸው በጣም ገረመኝ። እነዚህ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ምን ያህል የገዢውን ፓርቲ መንፈስ እንደማያዉቁ ተገለጠልኝ።
ብዙዋቻችን እንደሚናውቀው ኢሕዴግ በመንግሥቱ ኀይለማርያም አገዛዝ ሥር ኢትዮጵያን ያናውጥ የነበረው በማርክስና ሌኒን ትምህርት ሰክራ በነበረችበት ጊዜ፣ የተመሠረተው የኅብረተ-ሰብአዊነት ርዝራዥ መሆኑ መረሳት የለበትም። በዚያን ዘመን ጠቅላላው ሕዝብ ይቅርና ሣሩም ቅጠሉም ከብቱም ጭምር ኅብረተ-ሰብአዊ ሁኖ ነበር ማለት ይቻላል። ሁሉም ይግባው አይግባው፣ ወደደም ጠላም ኅብረተ-ሰብአዊነትን ያራምድ ነበር። ከላይ ያለው መሪው ሲወድቅ ኅብረተ-ሰብአዊነት አብሮ ተፈረካከሰና ድራሹ ጠፋ።
በሥልጣን ላይ ተተኪዎቹ ግን ሌላ አምላክ ይዘው ብቅ አሉ። ኅብረተ-ሰብአዊነትና ዐለምአቀፍነት በጐሣነትና በጐጥነት ተመነዘሩ። ቡርዧዜ በአማራ፣ ላብ-አደር ደግሞ እንደሁናቴውና እንደቦታው በጭቁን ብሔር ብሔረ-ሰቦች፣ የመደብ ትግልም በነፍጠኛ ተተኩ። ስሙን መጻፍ እንኳን ከማይችል መሀይምን መጠቅሁ-ተራቀቅሁ እስከሚል ሊቅ ኅብረተ-ሰብአዊነትን እርግፍ አድርጎ ትቶ አዲሱን የጐሣና የጐጥ ካባ ለብሶ ተነሣ። ልክ መንግሥቱ እንዳደረገ፣ ኢሕዴግም የአዲሱን ወንጌል ሐዋርያቶች በየፊናው መላክ ጀመረ። የሚገርመው ብዙውን ጊዜ የአዲሱ መንግሥት ወንጌል ስባኪዎች እነኚያው የቀድሞው የኅብረተ-ሰብአዊነት ጀሌዎች ነበሩ ማለት ይቻላል። ልዩነቱ እነዚህ ሰባኪዎች ባለም ከፍተኛ የተራቀቀ ፍልስፍና ነው ሲባል የሚታወቀዉን የማርክስንና የሌኒን ትምህርት በመሪዎቻቸው በተሞሉት መሠረት ያንበለብሉት እንደነበረ ሁሉ፣ አሁን ደግሞ በተቃራኒው የዚያ ዝቃጭ ነው የሚባለውን የጐሣንና የጐጥን ተረት በዚያው ልክ አለምንም ይሉኝታ መተርተራቸው ነው።
እንግዴህ የመንግሥቱ ኀይለማርያም አእምሮ በኅብረተ-ሰብአዊነት እንደተሞላ ሁሉ፣ የኢሕዴግም ጭንቅላት ጢም ብሎ የተሞላው በጐሣነት ነው። የተሞላ ነገር (ለምሳሌ ሰዓት ወይንም ኮምፒቴር) የራሱ አሳብ የለውም፤ ፍንክች ሳይል በተመላው መሠረት ብቻ ነው የሚሠራው። ኢሕዴግም እንደዚያው ነው ማለት ይቻላል። ከኢሕዴግ መስማማት አቅቷቸው ከድርጅቱ የተወገዱትና አሁን በስሕተታቸው ንስሓ ገብተው ተጸጽተው ወይንም በመጸጸት ላይ ያሉት በሥልጣን ላይ የነበሩ መሪዎች ስሕተታቸውን አምነው ቢቀበሉም እንኳ፣ ዙረው ዙረው የጐሣና የጐጥ ካባቸውን ለቅልቀው መጣል አልቻሉም። ከተገነጠሉ በኋላ የመሠረቱት ፓርቲም ሆነ የጻፉት መጻሕፍት የሚያንጸባርቁት ይኸንኑ ነው። የመንግሥቱን ኅብረተ-ሰብአዊነትን የሚያንቀሳቅሰው የመደብ ጥላቻ እንደነበረ ሁሉ፣ የኢሕዴግን የጐሣ ሕይወት የሚያላውሰው ደግሞ የአማራ ፍራቻ ነው።
ትንተናዬ ኢሕዴግ ከተሞላበት አሳብ ሌላ የተለየ ያለው ስለማይመስለው፣ አንጋሮቹ ያልሆኑትን ተቃዋሚዎች የሚያያቸውና የሚፈርጃቸው በጥላቻና በጠላትነት ብቻ ነው ለማለት ነው። ከዚህም የተነሣ፣ ኢሕዴግ ምንም እንኳን ቢሸነፍ፣ የጦር ኀይሉ እስከደገፈው ድረስ፣ ሌላውን ያጠፋል እንጂ ሥልጣኑን ግን የሚለቅበት ሁናቴ በፍጹም አይታየኝምም፤ ሊታመንም አይቻልም። ሊቀ ሊቃውንት መሐንዲስ አድማሱ የገረሙኝ በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ በኢሕዴግ ጐን እየኖሩ ይኸንን ሳይገነዘቡ መቅረታቸው ነበር። በምዕራብ ዓለም ግፊት ይለቃል ብሎ ማመን ደግሞ የመጨረሻ ቅሌት ይመስለኛል። መጀመርያዉኑ እዚያ ያስቀመጣቸው ምዕራቡ ይልቁንም አሜሪቃኖቹ ራሳቸው መሆናቸውን ወይንም ረስተውታል፣ ካልሆነም ልብ አላሉም። ካላወቁ ደግሞ ያነ የአሜሪቃ አስተሳሰብና ዓላማ ምን እንደነበረ እንዲታወቅና፣ ሌሎችም እንዲገነዘቡት ማንበቡ እንዳይታክት ስል ከዚሁ ታች ከግርጌ ላይ አስቀምጨዋለሁ[2]። የአሜሪቃ መንግሥትም ሆነ ሌሎች ምዕራባውያን የሚፈልጉት ነገር ቢኖር ጥቅማቸውን እንዳንነካባቸው ነው። ስለዚህም ሲሉ ልዩነታችንን በማጉላት፣ የኛውኑ ቤት ልጆች በጐናችን አሰልፈው በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ በመግባት ለብዙ ዘመን የነሱ አሻንጉሊት ሁነን እንድንቀር ነው የሚፈልጉት።
ኢሕዴግ ጦሩ እስከደገፈው ድረስ ለውጭ አገር መንግሥታት ጫጫታ ደንታ የለውም፤ ምንም ቢሆኑ ከሱ የበለጠና የተሻለ ተላላኪ እንደማያገኙና ከጩኸት ውጭ ምንም እንደማያደርጉ በደምብ ተረድቶታል። ተቃዋሚዎች መተማመን የሚገባቸው በውጭ አገር እርዳታ ሳይሆን “ያገሩን ሰርዶ ባገሩ በሬ እንደሚሉ” በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ነው፤ የኢትዮጵያንም ችግር መፍትሔ መፈለግ ከአገሩ በመነሣት ነው። ችግሩም በመተባበር መፈታት ይኖርበታል። ለዚህም እንደመቀራረብና መቻቻል ያለ ነገር የለም። በኅብረ-ብሔር ሆነ ሳይወዱ በኢሕዴግ ተገደው ካልሆነም ራሳቸው ፈልገው በጐሣ ደረጃ የተዋቀሩትን ሁሉ መቅረብና ማክበር ተገቢ ይመስላል። ማወቅ የሚገባን የሚጠላው ኀጢአተኛው ሳይሆን ኀጢአቱ፣ሰዎቹ ሳይሆኑ ሥራቸው ነው። ይኸም የኢሕዴግን ሰዎች ሁሉ ጨምሮ መሆን አለበት ባይ ነኝ።
ተቃዋሚዎች መገንዘብ ያለባቸው የመንግሥቱ ኀይለማርያም ኅብረተ-ሰብአዊነት የኢትዮጵያን ሕዝብና ታሪክ ሳያገናዝብ በጉልበት በጫንቃው ላይ የተጫነ ርእየተ ዓለም እንደነበረ ሁሉ፣ የጐሣ መርሐ-ግብርም ልክ እንደዚያው በባዶ ኀዋኅዉና በሌጣ ጭንቅላት ተጠንስሶ በውድ ሳይሆን በግድ፣ ሕዝቡ ብቻ ሳይሆን ሣር ቅጠሉ ሳይቀር አሜን ብሎ እንዲቀበል ተደርጓል። ኢሕዴግ ሲወድቅ እሱም አብሮት እጅ ለእጅ ተያይዞ እንደሚጠፋ አይጠረጠርም።
ኢሕዴግ ሥራውና የፖለቲካ እምነቱ እንደሚመሰክረው ፈያታዊ መንግሥት እንጂ ሕዝባዊ መንግሥት አለመሆኑን ነው። ይኸ ዋናው ማትኰር ያለበት ነጥብ ነው። መነሻችንን መንግሥት ምንድር ነው ብለን ብንጀምር አግባብ ያለው ይመስለኛል። ስለመንግሥት የራሴን ሐተታ ከምተነትን ወይንም አሳቤን ከማኽል ይልቅ የምዕራብ ዓለም የፖለቲካ ሥርዐቱ መዋቅር መሠረት አድርጎ የተጠቀማቸውን የእንግልዞቹን የጆን ሎክንና የአዳም እስሚዝን ስለመንግሥት የጻፉትን ነጥቦች ባጭሩ ባሰፍር ይሻላል። ለአሜሪቃ ሕገ መንግሥት መሠረት ሁኖ ያገለገለው የጆን ሎክ ጽሑፍ ነፍስወከፍ ግለሰብ ከእግዚአብሔር በአደራ የተቀበላቸው በምንም መልክና ምክንያት መነካትና መደፈር የማይገባቸው ሦስት መብቶች አሉት፤ እነዚህም ሕይወት፣ ነፃነትና ጥሪት ናቸው። ግን ነፍሰወከፍ ሰው ጉልበተኛ፣ ቀማኛና ወራሪ ቢነሣበትና እነዚህን መሠራታዊ መብቶች ቢነጥቅበት፣ በግሉ ሊከላከል ዐቅም ስለሚያንሰውና ስለማይችል ከሌሎቹ ጋር በመሰባሰብ መንግሥት ሊያቋቊም ተገደደ። ሎክ የመንግሥት ሥራ እንግዴህ እነዚህ መሠረታዊ መብቶች በሱም ሆነ በሌሎች እንዳይጣሱ መጠባበቅ ነው ይላል። መንግሥት ራሱ ከጣሰ ደግሞ ሕዝቡ ተሰባስቦ አስፈላጊውን ኀይል በመጠቀም፣ በመሸፈት፣ በግድ ከሥልጣኑ አንሥቶት በሌላ መተካት አለበት ሲል ሎክ አሳቡን ያጠቃልላል። በዚሁ ላይ በመቀጠል የምጣኔ-ሀብት ተመራማሪዎች ቅዱስ መጽሐፍ የሚባል ስያሜ የተሰጠውን ጽሑፍ የደረሰው አዳም እስሚዝ በበኩሉ በላይ ጆን ሎክ የዘረዘራቸውን መሠረታዊ መብቶች ለመጠበቅና ለማበልጸግ መንግሥት ማድረግ የሚገባቸው ሦስት መሠረታዊ የሥራ መስኮች አሉ ይላል። እነዚህም አንደኛ፣ ሕዝብን ከወረራ መከላከል፤ ሁለተኛ፣ ነፍስወከፍ ግለስብን ከግፍና ከጭቈና መጠበቅ፤ ሦስተኛ፣ ግለ-ሰቦች ለብቻቸው መሥራት የማይችሉትን ለሕዝብ አገልግሎትና ጥቅም አስፈላጊ የሆኑትን ሥራዎችን (ለምሳሌ ያህል፣ ግድብ መገደብ፣ መንገድ መሥራት) መተግበር ናቸው ሲል ያጠቃልላል።
በነዚህ ሁለት መሠረታዊ የመንግሥት የሥራ ግዴታዎች ላይ የፈረንሳይን አብዮት ያካሄዱት የለውጥ ዘማቾችና መሪዎች ሌላ ሁለት ነገር ይጨምራሉ። አንደኛው፡ ሕዝቡ እንጀራውን የሚያገኝበት የተለያየ የሥራ ዘርፍ መፍጠር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ለሚፈለገው ሥራ ተገቢውን ሥልጠና ሰጥቶ ነፍስወከፍ ግለሰቡን ለሥራው ማሰናዳትና ማሰማራት ነው።
ሁላችንም እንደምናውቀው ኢትዮጵያውያን ባገራቸው በሥልጣን ያለው መንግሥት ሥራ ሊፈጥርላቸውም ሆነ፣ ያለውንም ሥራ ለይቶ ለጀሌዎቹና ለደጋፊዎቹ ካልሆነ በስተቀር ለሌላው ስለማይሰጥ በየፊናው ካገር ውስጥ ለሥራ ፍለጋ እየፈለሱ ናቸው። ብዙዎች በሃይማኖታቸው ምክንያት ወይንም በባይተዋርነታቸው፤ ካልሆነም ወዳቀዱበት ሳይደርሱ በጒዞ ላይ እንዳሉ በመንገድ ተገድለው፣ በባሕር ሰጥመው አሰቃቂ ሞት ሙተዋል፤ እየሞቱም ናቸው። እንግዴህ ተቃዋሚዎቹም ሆኑ ቀልብና ኅሊና ያለው መራጭ ማትኰር ያለበት በነዚህ ነጥቦች መሆን ይኖርበታል።
ይሁንና በዚህም ሆነ በሚቀጥለው ምርጫ ኢሕዴግ ይሸነፋል ብሎ ማሰቡ የሕልም እንጀራ ነው። በሌላው በኩል ደግሞ መታወቅ ያለበት፣ ኢሕዴግ ኢትዮጵያዊነትን ለመግደልና ከሰው ጭንቅላት መንቅሮ ለማዉጣት ያልሞከረው ወጥመድ፣ ይልተጠቀመው መሣርያ፣ ያልፈጸመው ድርጊት፣ ያልደነገገው ሕግ፣ ያልፈጠረው ምክንያት፣ ያልፈለገው ዘዴ ባይኖርም፣ ኢትዮጵያዊነትንና የኢትዮጵያን አንድነት ሊያጠፋና ሊደመስስ ግን አልቻለም ያሰኛል። ይልቅስ ለዚሁ ዓላማ ጠንክሮ በሠራ ቊጥር ሰሜቱ እየተጠናከረ ሄደ እንጂ የዛለ መስሎ አይታይም። ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዓላማቸው ማሸነፍ ቢሆንም ባያሸንፉ ደግሞ ወደቀቢፀ-ተስፋነት መድረስ የለባቸውም ብዬ አምናለሁ። እውድድር ሜዳ የገባ ሁሉ እኩል ዕድል ቢኖረውም ያሸንፋል ተብሎ አይታሰብም። ከምርጫ ቦርዱ እስከውጤት ነጋሪው፣ ካስመራጩ እስከታዛቢው፣ ከመገናኛ ብዙኃኑ እስከተቈጣጣሪው፣ ኢሕዴግ ወይንም አጎብጋቢዎቹ በሰፈኑበት ሜዳ ተቃዋሚው ወገን ገብቶ ያሸንፋል ብቻ ሳይሆን መጠነኛ ድምፅ ያገኛል ተብሎ አይታሰብም፤ አይታለምም። ምርጫው ግን ለተቃዋሚዎች ብዙ ዕድል ያበረክታል። አጋጣሚውን በመጠቀም፣ የገዢውን መንግሥት ገመና ሊያጋልጡ፣ ራሳቸውንና የራሳቸውን ሥራና ዕቅድ ሊያስታዉቁ፣ አንድነታቸውን ሊያጠናክሩና በሕዝቡም ዘንድ ጥንካሬአቸውን ሊያስመስክሩ ይችላሉ። ኢሕዴግ ግን እንደማንኛውም ሰብኣዊ ድርጅት ጊዜውን ጠብቆ መፍረሱና መጥፋቱ አይቀርም። ለማፈጣጠኑ የተቃዋሚዎች ፓርትዎች ትልቅ አላፊነት ቢኖርባቸውም፣ ዋናው ጠላቱ ግን ድርጅቱ ራሱና ሥርዐቱ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ድርጅቱ መንግሥት ሁኖ በሥልጣን በቈየ ቊጥር ችግሩ እየፈደፈደ፣ መፍትሔው እየጠበበ፣ የመጋፈጥ ኀይሉ እየተዳከመ፣ ሥራው ለብዙኃኑ እየሰለቸ፣ በዚያው መጠን ድግሞ የሕዝብ ጥላቻ እየበዛና እየተጠናከረ፣ የጦሩም ሆነ የፀጥታ ጠባቂው ኀይል ራሱ የሕዝብ ጥላቻ ሲያይልበት የመግደሉ ወኔና ኀይሉ እየቀዘቀዘና እየቀነሰ ይሄዳል። በሌላው በኩል ደግሞ መገንዘብ ያለብን ከሃያ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ልጆችና ወጣቶች በትምህርት መስክ ተሰማርተዋል፤ የከበርቴም ክፍል ቀስበቀስ እየተበራከተ ነው ያለው። የተማረው አዲሱ ትውልድና በመንግሥት ርዳታ ሳይሆን በገዛ ሀብቱ የሚታመን የከበርቴ ክፍል የኢሕዴግን አምባገነን አገዛዝ ሊቀበል ፈቃደኛ እንደማይሆን አያጠራጥርም። በመጨረሻም እነዚህ ሁሉ ኀይሎች ለመከራቸው አማራጭ የሆነ ሰላማዊ መተንፈሻ ሲያጡ በገፍ መነሣታቸው አይቀሬ ነው ማለት ይቻላል።
ያነ ለዘመናት ሕዝቡን አፍኖ የያዘው ድርጅትና መሪዎቹ፣ ከነጀሌዎቻቸው አብረው ከሕዝቡ በመቀማት በግፍ የደለቡትን ሀብት ብቻ ሳይሆን፣ የገዛ ራሳቸውንም ሆነ የቤተሰቦቻቸውን ሕይወት ያጡ ይሆናል። ታሪክ ደጋግሞ የሚነግረን ነገር ቢኖር፣ የዛሬውን እንጂ የነገውን ለማያስቡ፣ “እኔ ከሞትሁ ሰርዶ አይብቀል” ለሚሉ አምባገነኖች፣ የሚቈያቸው ዕጣ ይኸው መሆኑን ነው። ሰርዶስ መብቀሉን አያቋርጥም፤ እነሱንና ሥራቸውን ግን ከትውልድ ትውልድ ታሪክ እየወቀሰና እያረከሰ፤ እየወገዘና እያፌዘ ይኖራል። የኢሕዴግም መጨረሻው ይኸው ሳይሆን የማይቀር ይመስላል።
ስለዚህ ከንጉሥ ኀይሌ ሥላሴ በኋላ ኢትዮጵያን የሚመራ መንግሥት ሰላም እንዳያገኝና፣ አገሪቷም እንደዐረብ አገሮች ተከፋፍላና ተነጣጥላ ካልተበታተነች በስተቀር፣ ለወደፊቱ በቀይ ባሕር ላይ አሜሪቃ የሚትጫወተው ሚና እንዳይመነምን እንዳያድጉ ማደናቀፍ ከሚገባቸው በቀይ ባሕር አዋሳኝ ታዳጊ አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ መሆን አለባት።
የቀይ ባሕር ወተት የሆነውን የዐረብን ነዳጅ በነፃ አለቀረጥ ማለብ የምንችለው፣ መንግሥታችን ኢትዮጵያን ከጎረቤቷ ከሱማሌ ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ክፍለ ሀገሮቿን ራሳቸውን በሰሜንና በደቡብ ከፋፍሎ፣ የደከመውን ወገን በመርዳት፣ ያላመፀውን ጐሣ በማነሣሣት፣ ከዳር ድንበሯ ዘላለም ሁከትና ጦርነት እንዳይለያት በማድረግ፣ ፀረ-መንግሥት ተዋጊዎችን በሲአይኤ በማደራጀት በአገሪቷ ሰላም በመንሣት ብቻ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠንካራና ብርቱ ቢሆንም ቅሉ፣ በሥልጣን ፍላጎቱ ደካማ ጐን አለው። አንዱ በሌላው ላይ መንገሥ ዋና ምኞቱ ነው። በታሪካቸው ደሞክራሲያዊ መንግሥት መሥርተው አያውቁም። ከጥንት ጀምሮም ቢሆን አንዱ ንጉሥ ሌላውን በመግደል ሥልጣን መቀማትና ማመፅ ባህላቸው፣ ልማዳቸውና ታሪካቸዉም ነውና፣ እኛ ያሳደግነው ውሻም ቢሆን ሊነክሰን ቢሞክር በማስገልበጥ፣ ላንዲት ዘመን እንኳ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ሰላም ሳይኖር፣ ሰሜናዊና ደቡባዊ፣ እንዲሁም ኤርትራ፣ ትግሬ፣ አማራ፣ ኦሮሞ እየተባባሉ እርስ በርሳቸው ሳይስማሙ ለረጅም ጊዜ ከኖሩ፣ ቀይ ባሕር ለአሜሪቃ መንግሥት ጠቃሚ በር ሁኖ ይኖራል። ሱማሌና ኢትዮጵያ ሰላም ሁነው አንድ ቀን ከተባበሩ፣ የአሜሪቃ ታላቅነትና ብልፅግና በቀይ ባሕርና በዓለም ላይ አይኖርም።
ኢትዮጵያና ሱማሌ እማዶ ካሉት የዐረብ አገሮች ጋር በቀይ ባሕር ጥቅም ላይ ተስማምተው ቢዋዋሉ፣ የአሜሪቃና የአውሮጳ ሕዝብ “ቡፋሎ” ፍለጋ ወደጫካ መሄድ ካልሆነ በስተቀር፣ ጥበባችንን እንኳን ሽጠንና ለውጠን ለመኖር እንችልም። ሊቃውንቶቻችን ወደአፍሪቃ ሲፈልሱ ከሩቁ ማየትና መገንዘብ የኛ ተራ እንደሚሆን አንርሳ።”
(ይኸ አሳብ በዶክተር ክሲንጀር “የቀይ ባሕር ለጦር ሰልት ያለው ጥቅም” በማለት ለመንግሥታቸው ያቀረቡት ጥናት ሲሆን የአሜሪቃ መንግሥት የፓለቲካ መርህ መሆኑን በየጊዜው የወሰዳቸው ርምጃ ይደግፈዋል።)
[1] . ሕገ-መንግሥቱ ዐምስትመቶ ዐምሳ ቢልም በተግባር የታየው ግን አምስት መቶ ዐርባ ሰባት አባላት ናቸው እየተመረጡ ያሉት።
[2] . “ኢትዮጵያ ሰላም ካገኘች፣ ሕዝቧ ሠራተኛና ታትሪ ሰለሆነ፣ በዓለም ብድር ዕዳም እንደሌሎቹ የሦስተኛ ዓለም አገሮች ተዘፍቃ የማታውቅና የኰራች አገር በመሆኗ አንድ ቀን አድጋ ራሷን የቻለች አገር ትሆናለች። ዕድል አግኝታ በዘመናዊ ሥልጣኔ ቢትገፋ፣ የሚትቻል አገር አይደለችም።
The post በእሑዱ ምርጫ አንዳንድ ነጣጥቦች appeared first on Zehabesha Amharic.