በሀገረ አሜሪካ መስፍን በዙ የሚባል ትንሽ ሰው አለ። ይህ ሰው ” ቲጂ ቴሌቪዥን” የሚባል በህውሀት የሚደገፍ ተንቀሳቃሽ መንኩራኩርና እሷን የሚሸከምበት ኮልኮላታ አለችው። የሁለቱም ቴክኒሻን፣ ፓይለት፣ ኮፓይለት፣ አስተናጋጅ፣ ተስተናጋጅ እሱ ብቻ ነው። ማንንም ስለማያምን አያሳፍርም። ለነገሩ የሀገሬ ልጆች እንደሰው ሰለማይቆጥሩት አይጠጉትም። በደንብ የሚያውቁት ደግሞ ” ከራሱ የተጣላ፣ግማሽ ሰው” ይሉታል። ቀትረ ቀላል!
እናም ህውሀት የሸለመውና ግርማ ብሩ ወጪውን የሚሸፍንለት መንኩራኩርና ኮልኮላታ አለው። ታዲያ! መንኩራኩሯን ሲሾፍራት በጣም ስለሚፈራና ድንጉጥ ስለሆነ የቀድሞ ክልል አንድን የሚያክል ባይነኩላር በሁለት አይኖቹ ላይ ይገጥማል። ባይነኩላሩ ካሜራ ስለተገጠመለት የድፍረቱ ምንጭ ሆኖ ያገለግለዋል። በጥርጣሬ ለተመለከተውና መንኩራኩሯን ለተጠጋ ሁሉ ” እስቲ ወንድ ከሆንክ ጫፌን ንካ! ” እያለ በተደጋጋሚ ይማፀናል። ጫፋን ሲነኩት እንደ ጐማ ተጠቅልሎ ለመተኛት እየተዘጋጀ። በነገራችን ላይ ወገቡም ላይ ሻጥ ያደረጋት ዲሞፍተር አለችው። ርግጥ ዲሞፍተሯ ቀጥረው እንደሚያሰሩት ጌቶቹ የክርኑን እርዝመትና ክብደት ማሳየት አልቻለችም። አይቻላትም። ምድሪቷ የጌቶቹ ( የድሮ ጓደኞቼ) አይደለችምና! …ይህ አሜሪካ ነው!!
መቼም የድሮ ጓደኞቼ እንደዚህ አይነት ከራሳቸው የተጣሉ ትናንሽ ሰዎችን ለፕሮፐጋንዳ መጠቀም የመጨረሻ አማራጫቸው እየሆነ መሄዱን ስመለከት ያሳዝነኛል። ርግጥ ምንጩን ስለማውቀው ሀዘኔታዬ ገደብ አለው። ደጋግሜ እንደምናገረው ምንጩ የበታችነት ስሜት ( inferiority complex) ነው። ይሁን እንጂ ይህ ስሜት የሚፈጥረው የፍርሀት ጐርፍ ራሳቸውን ተሸክሞ እንደሚሄድ ስለማውቅ እምብዛም አይገርመኝም። በሌላ በኩል የበታችነት ስሜቱ ዘረኝነት የፈጠረውና ከዘመኑ ጋር መለወጥ እንደማይችል ሳስብ ደግሞ ሀገራዊ አደጋው እየታየኝ እደነግጣለሁ። በየጊዜው የሚፈለፈለው የበቀል እርግዝና ማቆሚያው የት ነው?… ጠመንጃና ጉልበት እስከ መቼ መፍትሔ ይሆናል?… በየቦታው ” ጥቁር ባንዲራ” ይዘው በሚቆሙ ጃርቶች መከበብ ምን ይፈይዳል?……
የቀድሞ ጓደኞቼን ባህሪ ትተን ወደ መስፍን በዙ እንመለስ። መነሻችን እሱ በመሆኑ። የሌላችሁን ባላውቅም ባጋጣሚ የተመለከትኳቸው ” ቲጂ ቴሌቪዥን” ፕሮግራሞቹ ” የሞኝ ዘፈን ሁልጊዜ አበባዬ!” የሚለውን ያስታውሰኛል። የመስፍን “አበባዬ” ክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ ነው። አልፋና ኦሜጋው። በጥላሁን ስም ካልነገደ የራሱን ቀፎነት መደበቅ አይችልም። እስኪሰለቸን ጥላሁን ገሰሰ አሜሪካን ሀገር ቱር ሲያደርግ የሚያዞረው እሱ እንደሆነ ይነግረናል። የማሞ ቂሎ ነገር ጌቶቹን እንዳስቀየመ እንኳን ሳያውቅ ጥላሁን አሁን አምባሻ ያለበትን በንዲራ እንደሚጠላና እንደ ኢትዬጲያ ባንዲራ እንደማይቆጥር ሀይለማርያም ደሳለኝን ፊት ለፊቱ አስቀምጦ ይነግረዋል። ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ጋሽ ሀይሌ መልስ የመስጠት አቅሙ እንዳሁኑ አልጐለበተም እንጂ ቢጐለብትማ ኖሮ፣
” አምባሻዋን ጠፍጥፈው የፈጠሯት የሰሜን ሰዎች ናቸው። በአንባሻዋ ላይ በሌላው አካባቢ ያለው ህዝብ ምንአይነት ስሜት እንዳለው አያውቁም ነበር” የሚል የግመሏን ምላሽ የሚያስታውስ ታሪካዊ መልስ ይሰጥ ነበር።
መስፍን በዙ ሰሞኑን ለፈፀመው ቂላቂል ስራ እንደሱ ወረድ ብዬ መልስ መስጠት ሳስብ አንድ ነገር አገኘሁ።በአንድ ወቅት ንዋይ ደበበ በድምጳዊ ሰለሞን ተካልኝ ላይ የሰጠው አስተያየት። የሚገርም ምላሽ ነው! ብራቮ ንዋይ!! እንደ እውነቱ ከሆነ መቀነስም መጨመርም አላስፈለገኝም። የመጨረሻዎቹ መስመሮች ” የፓለቲካ ጨዋታ እንዴት በጣም ለትናንሽ፣… ላልበሰሉ… ከሁሉም በላይ ሆዳም ሰዎች” በማለት የገለፀውን ለመስፍን በዙ ምላሽ ይሁንልኝ። አንቀጱ በሙሉ አርቲስት ንዋይ ለተናገረለት ሰው ቋሚ ንብረት ሆኖ ይቀመጥ። ስያሜውንም ” የሰለሞን ዴዜዴራታ” ይበለው።
እነሆ! ንዋይ ” የሰለሞን ዴዜዴራታን” እንዲህ ነበር ያስቀመጠው፣
” … አሁን ላይ ሆኞ ስገመግመው ሙያተኛ ነው?… ወይንስ ፓለቲከኛ ነው?… ወይንስ የትግሉን አምባ ዝም ብሎ እዛም፣ እዛም እየገባና እየሄደ የሚበጠብጥ ያበደ ሰው ነው?… ግራ ይገባኛል። ሰውየውን በቀጥታ ለመተርጐም ግራ ያጋባል። ምክንያቱም እጅግ ከማናችንም በፊት ቀድሞ የከረረ ትግል ለማድረግ የወሰነ የሚመስል ሰው ነበር። እንደውም አሁን በስልጣን ላይ ያለውን መሪ ( አቶ መለስ መሆኑ ነው) የጡት ማስያዣና ፓንት አልብሶ በሲዲው ላይ አድርጐ እየዞረ የመሸጥም ጠንካራ የትግል ስሜት ነበረው። ኧረ! እንደውም እጁን በሰንሰለት አስሮ ፣በብረት ውስጥ ቁጭ ብሎ የእነማንዴላን የትግል አርአያነት ሊላበስ የሞከረ ነው። እኛን ሁሉ መንፈሳችንን የሚያበረታታ ፣ አሳምኖ አብረነው እንድንቆም ካደረገ በኃላ ባልታሰበ ጊዜ ውስጥ ዛሬ እንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ገባ። እንደዚህ አይነት ፍጡር አለወይ የሚያሰኝ ይመስላል። ለምን? …ከማንም በላይ በአትኩሮት ሲከታተሉትና ማንነቱን ሲመረምሩ የነበሩት እነሱ ናቸው። ታሪኩ በሙሉ እጃቸው ላይ አለ።… የፓለቲካ ጨዋታ እንዴት በጣም ለትናንሽ ሰዎች እንደሚጠቅም!… እንዴት ላልበሰሉ ሰዎች እንደሚጠቅም!… ከሁሉም በላይ እንዴት ለሆዳም ሰዎች ምቹ እንደሆነ ነው።…ታሪክና የኢትዬጲያ ህዝብ ጊዜውን ጠብቀው ፍርድ እስኪሰጥ ድረስ መጠበቅ ነው!!…”
The post “የሰለሞን ዴዜዴራታ!!” – ከኤርሚያስ ለገሰ (የመለስ ትሩፋቶች መጽሐፍ ደራሲ) appeared first on Zehabesha Amharic.