Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ዛሬም አይመረንም

$
0
0

ይገረም አለሙ ( ግንቦት 2005)

ምርጫ 2007 ከተጠናቀቀ በኋላ የተለያዩ ነገሮች እየሰማን ነው፡፡ምርጫ ማለት በእለቱ ጠዋት 12 ሰአት ተጀምሮ ምሽት 12 ሰአት የሚጠናቀቀው ሂደት አይደለም በሚል በተለያዩ ምሁራን የተሰጠው አስተያየት እውነትም ትክክልም ነው፡፡ ከወያኔ በስተቀር የሌሎቹን ተወዳዳሪዎች ዝግጅትና ሂደት እንደታዘብነው ሙሉ ትኩረታቸው የድምጽ መሽጫ እለቱ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ይህም በመሆኑና በቂ ቅድመ ዝግጅት ባለማድረጋቸው ወያኔ በቀላሉ ታዛቢዎቻቸውን ከጨዋታ ውጪ በማድረግ በየምርጫ ጣቢያው የተቀዋሚዎቹን ውጤት ዜረ0 ማድረግ ቻለ፡፡
clash
አራት አመት ሙሉ ምንም ሳይሰራ ወይንም ለምርጫ ተወዳዳሪነት የሚያበቃ ቅድመ ምርጫ ሥራ ሳይሰራ( በወያኔ ጫናም በራስ አቅም ማጣትም) የኢትዮጵያ ሕዝብ ወያኔን ስለሚጠላ ይመርጠናል በሚል ብቻ ወያኔ የራሱንም የምርጫ ቦርድንም ስራ አጠናቆ በቦርዱ ስም የምርጫ የግዜ ሰሌዳ ሲያወጣ የምርጫ ሥራ የሚጀምሩ ፓርቲዎች እንዲህ አሳፋሪ ለሆነ ውጤት ይዳረጋሉ፡፡ የምርጫ አንዱ ዝግጅት ማጭበርበርን ማስቀረት የማይቻል ቢሆንም መግታት የሚያስችል መሆን አለበት፡ለዚህ የሚያበቃ ዝግጅት ከሌለ ወይንም የወያኔ የማጭበርበር ዝግጅትና ድፍረት የማይቻል መሆኑ ከታወቀ ወደ ምርጫ አይገባም፤ ቢገባም ጫናው ሲበረታ ይወጣል፡፡ የምርጫው ውጤት አስቀድሞ የታወቀ ነው እያሉ አጃቢ ሆኖ መዝለቅ ግን ምን ይሉት ስትራቴጂ እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ ሌላ ቀርቶ ይህ ካልሆነ እንዲህ መደረጉ ካልተገታ ከምርጫው እንወጣለን (ለአፋቸው እንኳን) ያሉ የሉም፡፡

በምርጫ ተወዳድሮ ስልጣን መያዝ ወይንም መጋራት ሲታሰብ፤
በአራት ዓመታት ውስጥ
1-ድርጅታዊ አቅምን ማጎልበት; ማለትም በፕሮፓጋንዳ ሳይሆን በተግባር መሬት መርገጥ፡
2-ለምርጫ ተወዳዳሪነት የሚያበቁ ተግባራትን ማከናወን፤ማለትም
ሀ-ዓላማቸውን በአጭሩና በግልጽ የሚያስረዱ ሰነዶችን ማዘጋጀት፤ማሰራጨት፡
ለ-እምነት ጽናትና ብቃት ያላቸውን ዕጩ ተወዳዳሪዎች ማዘጋጀት፤
ሐ-ታዛቢዎችን በብዛትና በጥራት ማዘጋጀት፤
3-የፖለቲካ ምህዳሩ ሁሉን በእኩል ደረጃ ማወዳደር የሚችል እንዲሆን ጉድለቱን፤አድሎአዊነቱን ወዘተ በበቂ ማስረጃ እያሳዩ አማራጭ ሀሳብ እያቀረቡ በሁሉም መንገድ መታገል፤ ሕዝቡን የዚህ ትግል ኣካል በማድረግ ማንቀሳቀስ፡፡
4-ነጻ ፍትሀዊና ተአማኒ ምርጫ ለማካሄድ የሚያበቁ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ አማራጭ ሀሳቦችን በማቅረብ ሁለንተናዊ ትግል ማካሄድ፡፡ (ምርጫ ቦርድ ነጻ ተቋም እንዲሆን ማስቻልን ዋና ስራ ያደረገ)

5-በጠመንጃ የያዘውን ሥልጣን በጠመንጃ አስጠብቆ የሚኖረው ወያኔ ለነጻ ምርጫ ፈቃደኝነቱም ዝግጁነቱም እንዳማይኖረው ስለሚታወቅ ምርጫ ሊያጨበረብርባቸው የሚችሉ ቀዳዳዎችን ሁሉ ለመድፈን ካልሆነም አስቀድሞ በተአማኒ ማስረጃ ለማጋላጥ መስራት፡፡

እነዚህና ተመሳሳይ ተግባራት በአራት ዓመታት ውስጥ ተከናውነው የመጨረሻው ምርጫ የሚካሄድበት ዓመት ላይ የተሰሩ ስራዎች ተገምግመው በሚገኘው ውጤት መሰረት በምርጫ መወዳደር ወይንም አለመወዳደር ይወሰናል፡፡ ውሳኔው መወዳደር ሆኖ ወደ ምርጫ ፉክክር ከተገባ ደግሞ የእለት ተእለቱ እንቀስቃሴ በቅጡ እየተፈተሸ የመወዳደሩ ፋይዳ እየተገመገመ ወያኔ ሥልጣን ወይም ሞት በሚለው መርሁ እስከምን ድረስ የከፋ ተግባር ሊፈጽም እንደሚችል እየተጤነ እስከ መጨረሻው መዝለቅ አለያም በማናቸውም ግዜ ከምርጫው የመውጣት ውሳኔ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡

የምርጫ 2007ን ሂደት ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው፡፡ ተቀዋሚዎች በምርጫው ማግስት የሚሉትን ማለትም ድምጽ ተዘረፈ፤ታዛቢ ታሰረ ታፈነ፤ተወዳዳሪ ተከለከለ፤ነጻነት በሌለበት ነጻ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም ወዘተ ከምርጫው በፊት አያውቁትም ነበር ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ከምርጫ 2002 እስከ ምርጫ 2007 በነበሩት አመታት እነዚህ ነጻ ምርጫ ለማካሄድ የማያበቁ ያሉዋቸው ጉዳዮች እንዲለወጡ ወይንም እንዲሻሻሉ ምን ሰሩ ብለን መለስ ብለን ብንቃኝ የምናገኘው ብዙም ነገር የለም፡፡ በወቅታዊ ትኩሳቶች ላይ የተሳካም ያልተሳካም ሰላማዊ ሰልፍ ሲያዘጋጁ አንድም ቀን “ለነጻ ምርጫ ነጻ ምርጫ አስፈጻሚ” ብለው አያውቁም፡፡ እንደውም ወያኔ ሌላ ሌላው የሰራው አልበቃ ብሎት ምርጫ 97ን እያሰበ በቅዠት መንፈስ የሰላማዊ ሰልፍ ቦታ በየጽ/ቤቶቻቸው ጓሮ መርጦላቸው የሚሄዱበትንም መንገድ ሲወስንላቸው በጸጋ ተቀብለው ሰልፍ እየወጡ ትልቅ የፖለቲካ ስራ እንደሰሩ ያናገሩ ነበር፡፡ እሱ ይህንን ያደረገው ምርጫን እያሰበ ሲሆን እነርሱ ከጊዜያዊ ፕሮፓጋንዳ በዘለለ ስለምርጫ አስበውና የዝግጅታቸው አንድ አካል አድረገው ነበር ብሎ ደፍር መናገር የሚቻል አይመስለኝም፡፡

በምርጫ 2002 ተቀዋሚው አንድ ወንበር ባገኘበት፤ ወያኔ ያንን ውጤት ለማስጠበቅ አይደለም አንድም ተቀዋሚ በፓርላማ ላለማየት የራሱን አውራ ፓርቲነት አውጆ መኖር ያለባቸው ታማኝ ተቀዋሚዎች ብቻ ናቸው ብሎ በይፋ ነግሮ ሌሎች እንዳይንቀሳቀሱ መንገዱን ሁሉ ዘግቶ ባለበት ምን ሰርተው ምን ጥንካሬ ፈጥረው ምን ተማምነው ወደ ምረጫ ገቡ ብለን ብንጠይቅ ቀናና ተገቢ ምላሽ የሚኖራቸው አይመስለኝም፡፡የማስተዋል ችግር ካልሆነ በስተቀር አንድነትን ባፈረሱበት ወቅት ፕ/ር መርጊያ “ለሚታዘዙንና ከእኛ ጋር ተስማምተው ለሚሰሩ ሰጥተናል” በማለት አስበውትም ይሁነን አምልጦአቸው የተናገሩት ለምርጫ 2007 ውጤት ግልጽ አመላካች ነበር፡፡

ምርጫ ከገቡ በኋላም ምርጫ ቦርድና ወያኔ አንድም ሁለትም ሆነው ለምርጫ ቅስቀሳ ቃላትን ሳይቀር ሲመርጡላቸው፤እጩዎቻቸውን አለመዘግብ ሲሏቸው፤ ተወዳዳሪ ፓርቲዎችን አሸባሪ የውጪ ተላላኪ ወዘተ እያሉ ፕሮፓጋንዳ ሲሰሩባቸውና አባሎቻቸውን ሲያስሩ ወዘተ የሚሆነውን እየተቀበሉ አድርጉ የተባሉትን እያደረጉ(ለምሳሌ እንዲህ ብላችሁ
እንዳትቀሰቅሱ፤በክርክር መድረክ ላይ እንዲህ አይነት ቃላትን አንዳትጠቀሙ ወዘተ) እስከ መጨረሻ የመቀጠላቸው ዓላማ ግልጽ አይደለም፡፡

በምርጫው እስከ መጨረሻው በመቆየታችን ወያኔን አጋልጠናል የሚል ቃል ከተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች እየሰማን ነው፡፡ በጣም የሚገርም ነው፡፡ ለመሆኑ ወያኔ ከምርጫ 97 ያለፈና ከምርጫ 2002 የቀረ ምን የተደበቀ ማንነት ነበረው፡፡በምርጫ 2007 አስቀድሞ የማይታወቅ ከዚህ በፊትም ያልሰራው ምን አዲስ ነገር አደረገ ፣ ምን አዲስ ባሕርይ አሳየ፡፡ ፖለቲከኞቻችን ራሳቸውን አጋልጠው ካልሆነ በስተቀር ወያኔን ያጋለጡበት አንድም ነገር የለም፡፡

ባለፉት 24 ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ ያላወቀው አንድም የወያኔ ማንነትና ምንንት የለም፡፡ በምርጫ ተወዳድረው ያሸነፉትን የሚያስር፤ስለ ሰላም የሚዘምሩትን ጦረኛ የሚል፤ስለ ሀገር አንድነት ነጻነትና ሉዐላዊነት የሚታገሉትን በሀገር ክህደት የሚከስ፤ስለ ሰው ልጅ እኩልነት፣ ስለ አንድ ሀገር ልጅነት ስለ አብሮነት የሚያስተምሩትን በዘር ማጥፋት ወንጀል የሚከስ እጃቸው ከብእርና ከኪቦርድ ውጪ ነክቶ የማያውቅ አዳዲስ ሀሳብ አፍላቂዎችን አሸባሪ ብሎ የሚከስ ወዘተ ወያኔ ምን የተደበቀ ማንነት ኖሮት ነው በምርጫው እስከ መጨረሻው በመዝለቃችን አጋለጥነው የሚባለው፡፡

እንዲህ አይነቱን ራስን ለማጽናኛና ወቅታዊውን መነጋገሪያ ጉዳይ ለማድበስበሻ የሚቀርቡ ረብ የለሽ ነገሮችን ተወት አድርገን እውነቱን ለመናገርም፡ የሚነገሩና የሚጻፉ እውነቶችን ለማዳመጥም ወኔ፣ድፍረት ቅንነት ይኑረን፡፡ትግላችንን ውጤት አልባ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ በእውነት ስለ እውነት ለመነጋገር መድፈር አለመቻላችን ነው፡፡ ስራችን የታይታ፣ጽሁፍ ንግግራችን የፕሮፓጋንዳ፤አስተሳሰባችን ከራስ በላይ ነፋስ ጉዞአችን በጥላቻ የተተበተበ ፖለቲካችን የሴራ ሆኖ በድል አልባ ትግል ለወያኔ አገዛዝ በየአምስት አመቱ ህጋዊነትን እያላበስን እንኖራለን፡፡ እስቲ አሁን አንኩዋን ይቆጨን፤ከመማረር አልፈን ለማምረር እንሞክር፡፡ እናም ሰበብ መደርደሩ ምክንያት ማብዛቱ ይቆየንና 24 ዓመት ሙሉ በተደረገው ትግል ለውጥ ማምጣት ያልተቻለው ለምንድን ነው ብለን መነጋገር እንጀምር፡፡ የነገ ጉዞ እቅድ ዝግጅታችን ከዚህ ውጤት ይመንጭ፡፡

The post ዛሬም አይመረንም appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles