አሜሪካ ዳላስ የሚኖር አንድ ወዳጄ ለትምህርት ከሠላሳ ዓመታት በፊት ፈረንሳይ እያለ የገጠመውን እንዲህ ነግሮኝ ነበር፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ጓደኞቹ ጋር ምግብ ለመብላት ይወጣሉ፡፡ የገቡበት ምግብ ቤት ደረጃው ከፍ ያለ ነበር፡፡ የምግቡን ዝርዝር ያዩና ስሙ ደስ ያላቸውን ያዛሉ፡፡ ምን ዓይነት ነው? እንዴት ነው የሚሠራው? ምን ምን ያካትታል? የሚለውን የምግብ ማውጫ ዝርዝር ለማየት ዕድል የሰጠ ወይም አስተናጋጇን የጠየቀ ከመካከላቸው የለም፡፡ ሁሉም ያንኑ አዘዙ፡፡ አስተናጋጇም ጠረጲዛውን ካስተካከለቺ በኋላ በሰሐን ሙዳ ሙዳ ሥጋ በአራት መዓዝን ቆርጣ አመጣችና በየፊታቸው ከቢላዋና ከሹካ ጋር አስቀመጠች፡፡
ፊታቸው ፈካ፣ ሀገራቸው የተውት ጥሬ ሥጋ ፈረንሳይ ድረስ ተከትሎ በመምጣቱ ተገረሙ፡፡ ምናልባት አበሻነታችንን ዐውቃ ይሆን ጥሬ ሥጋ ያመጣችልን? ብለውም አሰቡ፡፡ አዋዜ ባለመኖሩ ቢያዝኑም በቢላዋ እየቆረጡ ጠረጲዛው ላይ በነበረው ቁንዶ በርበሬ እየጠቀሱ ያጣጥሙት ጀመር፡፡ ናፍቆት አሳስቷቸው ባንዴ ሰሐኑን ባዶ አደረጉት፡፡ የጥሬ ሥጋውን ነገር እያነሡ ሲደሳሰቱ አስተናጋጇ እሳቱ የፋመበት አራት መጥበሻ ይዛ መጣች፡፡ ፈገግ ብላ መጥበሻዎቹ ያሉበትን ትሪ መሰል ነገር ጠረጲዛው ላይ ስታስቀምጠው ግን ክው ብላ ነው የቀረቺው፡፡ ብርንዶ በመሰለው ፊቷ አፍጥጣ እያየቻቸው ‹‹ሥጋው የታለ›› ብላ በፈረንሳይኛ ጠየቀቻቸው፡፡ እነርሱ ሲፋጠጡ ሴትዮዋ በድንጋጤ እንደሄደች አልተመለሰቺም፡፡
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዋሽንግተን ዲሲ ወደ አዲስ አበባ እየተጓዝኩ ነው ይህን ታሪክ ያሰብኩት፡፡ የተቀመጥኩት የአደጋ ጊዜ መውጫው በር ያለበት ጋ ነበር፡፡ ፊት ለፊት በስተ ቀኝ በኩል የመጸዳጃ ክፍሉ አለ፡፡ እስካሁን ድረስ ወደ ሠላሳ የሚጠጉ ሰዎች ለመጠቀም መጥተዋል፡፡ ሰዎቹን እንድቆጥር ያደረገኝ የማየው ነገር ስላስገረመኝ ነው፡፡ የመጸዳጃው በር አንድ ሰው እንዲያስገባ ሆኖ የተሠራ፣ አካፋዩ ጋ የሚታጠፍ፣ መሐል ወገቡ ላይ ደግሞ ክፍሉ መያዝ አለመያዙን የሚያመለክት የሚበራ ምልክት ያለበት፣ ከምልክቱ ወረድ ብሎ የተንጠለጠለ የሲጋራ መተርኮሻ የተቀመጠበት፣ በሁለተኛው ተካፋይ ላይ በአማርኛ‹ ይጫኑ› በእንግሊዝኛ ደግሞ PUSH የሚል ቃል የተጻፈበት ነው፡፡
ወደ መጸዳጃ ክፍሉ ወጣቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋውያንና ጎልማሶች መጥተዋል፡፡ በአብዛኛው የመጡት ወጣቶችና ጎልማሶች ናቸው፡፡ ወደ መጸዳጃ ቤቱ ከመጡት ሠላሳ ሰዎች መካከል አሥራ ሰባቱ የሲጋራ መተርኮሻውን የበሩ መክፈቻ መስሏቸው ሲስቡት ነቅለውታል፡፡ አጠገቤ የነበረው ሰው የተነቀለውን መልሶ መትከል ሥራው ሆኖ ነበር፡፡ ከመጡት መካከል አምስቱ መጸዳጃ ቤቱ መያዝ አለመያዙን በሚያሳየው ምልክት በኩል ለመክፈት ይታገሉ ነበር፡፡ ከእነዚህ ሃያ ሁለት ሰዎች ስድስቱ ብቻ አረጋውያን ናቸው፡፡ የቀሩት ደግሞ ወጣቶችና ጎልማሶች፡፡ ከጎኔ የነበረው ሰው ቢያንስ ለዘጠኝ ጊዜ ለመጸዳጃ ቤቱ ውኃ ለመልቀቅ ሄዷል፡፡ ከእነዚህ መካከል ግን አረጋውያኑ ሁለቱ ብቻ ናቸው፡፡
የምመለሰው ከአሜሪካ ነውና ተጓዦቹ ቢያንስ የተወሰኑ ቀናት ቢበዛ ደግሞ ዓመታትን በአሜሪካ ቆይተዋል ብዬ ገመትኩ፡፡ ያም ባይሆን እንኳን ወደ አሜሪካ የመጡት በአውሮፕላን ነው፡፡ በርግጥ በላቲን አሜሪካ በኩል አድርገው ወደ አሜሪካ የሚገቡ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ እነርሱም ቢሆኑ ግን ወደ ላቲን አሜሪካ ሀገሮች በአውሮፕላን ገብተው ከዚያ በመኪናና በባቡር ወደ ሜክሲኮ የሚደርሱ ናቸው፡፡
እነዚህ ወገኖቻችን የአውሮፕላኑ በር እንዴት እንደሚከፈት ለምን ጠፋቸው? ብዬ ጠየቅኩ፡፡ የመጀመሪያው በሁላችን ኅሊና ሊመጣ የሚችለው ምክንያት ‹የልምድ ማጣት ነው› የሚል ሳይሆን አይቀርም፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች በአውሮፕላን ተጉዘው ወደ አሜሪካ የመጡ ናቸውና ቢያንስ አንድ ጊዜ በዚህ በር መጠቀማቸው አይቀርም፡፡ በረራው ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ቢደረግ ወይም ከአንዳንድ የአውሮፓ ሀገሮች ወደ ኢትዮጵያ ቢሆን ኖሮ ይኼ ምናልባት አንድ ምክንያት ሊሆን ይችል ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚወጣ አንዳንድ ሰው የአውሮፕላን ጉዞ ልምድ ሊያጥረው ይችላል የሚለውን እንይዝለታለን፡፡ በባሕር በኩል ወደ አውሮፓ የሚገቡ አንዳንድ ወገኖችም አውሮፕላን ላይ የሚሣፈሩት የመኖሪያ ፈቃድ አግኝተው ወደ ሀገር ሲመለሱ ነው፡፡ ይህም ሊያዝ የሚችል ነው፡፡ ግን አሁን እየተጓዝን ያለነው ከአሜሪካ ወደ አዲስ አበባ ነው፡፡
እኔ ግን የማናውቀውን ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ ስናውቅ በትምህርት መልክ ለማወቅ ያለመጣር ክፉ ልማድ አንዱ ምክንያት ይመስለኛል፡፡ አበው ‹ሞኝ ሺ ጊዜ ብልጥ አንድ ጊዜ ይሳሳታል› ይላሉ፡፡ ብልህ ሰው መጀመሪያ ባለማወቁ ቢሳሳትም አለማወቁን ወደ ዕውቀት ይቀይረዋል፡፡ አዲሱን ገጠመኝ በሚገባ አስተውሎ ዕውቀት ያደርገዋል፡፡ ሞኝ ግን ያኔውኑ ከችግር መውጣቱን ወይም ነገሩን መከወኑን እንጂ በድጋሚ በተስተካከለ መንገድ ነገሩን ለመፈጸም የሚያስችል ዕውቀትን አይሸምትበትም፡፡ ምናልባትም እንደ አጋጣሚ ሆኖ ትክክለኛውን ነገር ቢሠራው እንኳን፣ ዳግመኛ ለመሥራት የሚያስችል ልምድ ግን አይቀስምበትም፡፡ ገጠመኙን ወደ ዕውቀት አልቀየረውማ፡፡
በሩን መክፈት አቅቷቸው የሲጋራ መተርኮሻውን ካወለቁት ሰዎች መካከል ሦስቱ እንደገና ተመልሰው ያንኑ መተርኮሻ አውልቀውታል፡፡ እንዲያውም ሁለቱ ሰዎች አስተናጋጆቹ ጋሪ ይዘው እስከሚያልፉ ድረስ ከፊቴ ቆመው ነበርና የት ሀገር እንደሚኖሩ ለመጠየቅ ዕድል አግኝቼ ነበር፡፡ ሁለቱም አሜሪካ ነው የሚኖሩት፤ አንዱ ሰባት አንደኛው ደግሞ አምስት ዓመታቸው ነው፡፡
ብልህ ሰው አንድን ከዚህ በፊት አድርጎት የማያውቀውን ነገር ከማድረጉ በፊት ወይ ያነባል፣ ወይ ያጠይቃል፣ አለበለዚያ ደግሞ ሌሎችን አይቶ ይማራል፡፡ በሩ ላይ ‹ይጫኑ፣ PUSH› የሚል ምልክት አለው፡፡ ያንን አንብቦ የበሩን አከፋፈት መገመት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያውያን እናቶችና አባቶች ነገሩን ላያነቡት ይችላሉ፡፡ ወጣቶቹና ጎልማሶቹ ግን ለምን አላነበቡትም? በመመሪያ የመሥራት ልማድ አለመኖር ይመስለኛል፡፡ ስንቶቻችን ዕቃ ስንገዛ ከመጠቀማችን በፊት ማኑዋሉን እናየዋለን? ስንቶቻችንስ በካርቱኑ ላይ ለተጻፉት ነገሮች ትኩረት እንሰጣለን? ስንቶቻችንስ በዕቃዎች ላይ የሚጻፉ መግለጫዎች ጠቃሚዎች ናቸው ብለን እናምናለን? በሲጋራ መተርኮሻው ላይ የተለኮሰ ሲጋራ ሥዕል ይታያል፡፡ እርሱን የሚያይ ሰው ምን ይሆን? ብሎ ለማሰብ እንዴት ሰከንዶች ማጥፋት አቃተው? ወይም ከመንቀሉ በፊት ሥዕሉን ለምን አላየውም? ለዕውቀት ስሱ አለመሆን አይመስላችሁም፡፡
አንባቢ ሰው በአራት ይከፈላል፡፡ የመጀመሪያው ለጉዳዩ ሲል የሚያነብ ነው፡፡ የትምህርት ቤት መጻሕፍትን፣ የጥናት ደብተሩን፣ የምግብ መሥሪያ መመሪያውን የሚያነበው ዓይነት፤ እንዲህ ያለው ሰው ጉዳዩ ሲያልቅ አንባቢነቱም ያቆማል፡፡ አንዳንዶቻችን ከዩኒቨርሲቲ በኋላ ከመጽሐፍ ጋር የተቆራረጥነው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ለኑሮ የሚያነብ፡፡ ያለ ንባብ መኖር የማይችል፡፡ ምግበ ኅሊና የሚፈልግ፡፡ ካላነበበ የሚርበው ዓይነት፡፡ ሦስተኛው ዓይነት አንባቢ የሚባለው ደግሞ ከማንኛውም ነገር በፊት ስለዚያ ነገር የሚገልጠውን የሚያነብ ነው፡፡ ያለ ዕውቀት የማይመራ፡፡ መንገድ ሲሄድ፣ ዕቃ ሲጠቀም፣ መድኃኒት ሲወስድ፣ አዲስ ምግብ ሲመገብ፣ ወደማያውቀው ሀገር ሲሄድ፣ አዲስ ሞያ ውስጥ ሲገባ ስለዚያ ነገር የተጻፈውን አንብቦ ካልሆነ በቀር የማይወስን ዓይነት፡፡ አራተኛው ሰው ተገድዶ ብቻ የሚያነብ ነው፡፡ አንድን መግለጫ፣ ጽሑፍ ወይም ማስታወቂያ ለማንበብ ሁኔታዎች ሲያስገድዱት ብቻ የሚያነብ፡፡
ሦስተኛው የንባብ ልምድ አለመኖር ሌሎቹን ዓይነት አንባቢዎችም ይጎዳል፡፡ ልብሶቻችን ላይ የተለጠፉትን መመሪያዎች አለማንበብ፣ የገዛነውን መድኃኒት መግለጫ አለማየት፣ የገዛነውን ዕቃ ማኑዋል አለማስተዋል የገንዘብም የጤናም ኪሣራ ያስከትላሉ፡፡ በእኛ ላይ ብቻም ሳይሆን በሌሎች ላይ ችግር ፈጣሪ ያደርገናል፡፡
አንድን ነገር ስንሠራ መጀመሪያ ስለዚያ የተጻፈ ነገር የመፈለግ ልምድ ቢኖር ኖሮ በመጸዳጃ ቤቱ ላይ ‹ይጫኑ› የሚለውን ማንበብ ይቻል ነበር፡፡ ልምዱ ስለሌለ ግን ጽሑፉን የሚያየውም ሰው ደመ ነፍሱ የሚመራውን እንጂ ልቡናው የሚመራውን ለማድረግ ሲከጅል አላይም ነበር፡፡
ሌላው ችግር ደግሞ ‹መጠየቅ ያደርጋል ሊቅ› የሚለው አባባል መዘንጋቱ ያስከተለው ይመስላል፡፡ ስለ በሩ አከፋፈት እዚያው የቆሙትን ወይም ፊት ለፊት የተቀመጡትን ሰዎች መጠየቅ ቀላል ነበር፡፡ ካልሆነም የበረራ አስተናጋጆቹን ጠርቶ ማማከር፡፡ መጠየቅ ነውር፣ ክብረ ነክ፣ አላዋቂነትን መግለጥ ይመስለናል መሰል የተለመደው እንዲሁ በመሰለኝ መሥራት ነው፡፡ አንደኛዋን ወጣት እንዲያውም ከጎኔ የነበረው ሰው ‹‹ብትጠይቂንኮ እንነግርሽ ነበር› ሲላት ‹‹በዚህ የሚከፈት መስሎኝ ነው›› ነበር ያለቺው፣ የነቀለቺውን የሲጋራ መተርኮሻ እያሳየቺው፡፡ እንዲህ ያለው መሰለኝ የሚመራው አስተሳሰብ በር ላይ ተከስቶ በሰላም ታለፈ እንጂ የሚፈነዱ ወይም የሚቃጠሉ ነገሮች ላይ ቢሆን ኖሮ ውጤቱ ይከፋ ነበር፡፡
‹አራዳ በፎቶ ኮፒ ይሠለጥናል› የሚል አባባል በፌስ ቡክ አይቻለሁ፡፡ ‹አድርገኸው የማታውቀውን ነገር ከማድረግህ በፊት የሚያውቀው ሰው ሲያደርግ አይተህ ተከተል› የሚል ነው የመዝገበ ቃላት ትርጉሙ፡፡ ወደ አውሮፓ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሻገሩ የሀገራችን ሰዎች የጻፏቸውን የጉዞ ማስተዋሻዎች ብንመለከት የአውሮፓውያንን አመጋገብ የለመዱት በዚህ ዘዴ መሆኑን ይነግሩናል፡፡ ሹካ ሲያነሡ ማንሣት፣ ፓስታ ሲጠቀልሉ መጠቅለል፣ ሲጎርሱ መጉረስ፡፡
ይህንን ጽፌ ስጨርስ አንዲት ወጣት ልጅ መጣች፡፡ ‹ይጫኑ› የሚለው ምልክት ጋ የሚሳብ መክፈቻ ትፈልጋለች፡፡ ገርሞኝ ሳያት ከጎኔ የነበረው ተሳፋሪ ‹እሱ ምን ይላል?› አላት፡፡ ጠጋ ብላ አየቺውና ‹ኦ ሶሪ› ብላ ገፋ አደረገቺው፡፡ መጽሐፈ መነኮሳት ‹ከሰይጣን ይልቅ ልማድን ፍራ› ያለው ይኼን ነው አልኩ በልቤ፡፡
ከአሜሪካ ወደ አዲስ አበባ
The post ከመጸዳጃ ቤቱ ፊት ለፊት – ዳንኤል ክብረት (ዲ/ን) appeared first on Zehabesha Amharic.