Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

በዶ/ር መረራ ጉዲና “የኢትዮጽያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች” መጽሐፍ ላይ ያለኝ ዳሰሳ

$
0
0

የመጽሐፉ ርዕስ “የኢትዮጽያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች”
ጸሐፊ ዶ/ር መረራ ጉዲና
የገጽ ብዛት 264
የታተመበት ጊዜ ነሐሴ 2005
ዋጋ 80.90 ብር
ዳሰሳ በፍሬው አበበ (ጋዜጠኛ)

እንደ መግቢያ
merara gudinaበኢትዮጽያ ፓለቲካ ውስጥ መሳተፍ በተለይ ልሂቃንን የፍርሃት ቆፈን ውስጥ በከተተበት በዚህ ዘመን ራሳቸውን (ያውም በተቃውሞ ፖለቲካ) የፊተኛው ረድፍ ላይ ያሰለፉ እንደዶ/ር መረራ ዓይነት ሰዎች ካሳለፉት የሕይወት ውጣውረድ ልምዳቸውን ጨልፈው በመጽሐፍ መልክ ማቅረባቸው ለትውልድ ጭምር የሚተርፍ ውለታ ተደርጎ ሊታይ የሚችል ነው። ዶ/ር መረራ ጉዲና ከተማሪነታቸው ጀምሮ ያሳለፉትን የፖለቲካ ሕይወታቸውን የዳሰሱበት ይህ መጽሐፍ ዛሬ ላይ ሆነን ከ39 ዓመታት በፊት ስለነበረው የፍረጃና የጠላትነት ፖለቲካ፣ ስለነበረው መቻቻልና መግባባት የጠፋበት ውጥንቅጥ ትግል፣ በዚህም ትግል ውስጥ ነጥረው ስለወጡ መልካም ዕድሎችና ጉድለቶች እንድናስታውስ ዕድል የሚሰጥ ነው። በትላንት መነጽር ዛሬን እንድናይ፣ እንድንገመግም የሚያደርግ ነው። እናም ዶ/ር መረራ ብዙ ታሪክ ይዘው ቁጭ ላሉ ልሂቃን ጭምር ሥራቸው ጥሩ የማንቂያ ደውልም ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
የመጽሐፉ ጭብጥ
መጽሐፉ መደምደሚያውን ጨምሮ በ12 ምዕራፎች ተከፋፍሎ የቀረበ ነው። ጭብጡ በርዕሱ እንደተመለከተው የዶ/ር መረራን ሕይወትና የፖለቲካ ጉዞ የሚዳስስ ነው። በተለይ ከ1966 ቱ አብዮት ጋር ተያይዞ ስተፈጠሩት የፖለቲካ ቡድኖች፣ በአጋጣሚው ተጠቅሞ ሥልጣን ላይ ፊጥ ያለው ወታደራዊ አገዛዝ፤ እሳቸውም በመኢሶን አባልነታቸው ለሰባት ዓመታት የእስር መከራን ተቀብለው ያሳለፉትን የመከራ ሕይወት አሳይተውናል። እንደማንኛውም ኢትዮጽያዊ ጠንክሮ በመማር ድህነትን አሽቀንጥሮ ለመጣል ያደረጉትም የሕይወት ትንንቅ ለዚህ ትውልድ ጥሩ ትምህርት የሚሰጥ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
ወጣቱ መረራ ጎበዝ ተማሪ ነበረ፤ ያለችግርም ወደዩኒቨርሲቲ የማለፍ ዕድል አገኘ። ውጤቱ ቢያስደስተውም ከአምቦ ወደአዲስአበባ መጥቶ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ለልብስ እንኳን የሚሆን ሳንቲም እንዳልነበረው፣ በወቅቱ ይህን ለሟሟላት የቤተሰቦቹን በሬ ሸጦ በ1965 ዓ.ም አዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ እንደገባ ይተርካል። “ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ብዙ ዝግጅት ስላልነበረኝ በጊዜው የሱፍ ልብስ ጨምሮ የቅያሪ ልብሶች ያስፈልጋሉ ስለሚባል፣ ለዚህ ደግሞ ችግረኛ እናቴን ማስገደድ ስለከበደኝ አንድ ዓመት ሰርቼ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ለትራንስፖርት አንድ ትንሽ ወይፈን ሸጪ ወደአዲስአበባ መጣሁ…” (ገጽ40)
ዶ/ር መረራ ወደ ፖለቲካ ውስጥ የገቡት በገጠመኝ እንጂ አቅደው ወይም አስበውበት አልነበረም። በተለይ ደርግ ሰባት ዓመት አስሮአቸው ከተፈቱ በኋላ ሙሉ በሙሉ ትኩረታቸው ትምህርታቸው ላይ እንደነበር ግን በሳቸው አባባል የፖለቲካ ማኖ የነኩት ኢህአዴግ ከገባ በኃላ በተፈጠሩ ፕሬሶች አማካይነት እንደነበር ይተርኩልናል። “…ኢህአዴግ እንደገባ ማበብ የጀመሩ ጋዜጦች አስተያየት ሲጠይቁኝ አልፎ አልፎ ቃለምልልስ በመስጠት ማኖ መንካት ጀመርኩ። ከዚያም ቀጥሎ የአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ በስራ አጥነት ላይ ባዘጋጀው ውይይት ላይ መጀመሪያ የተጋበዘው ዶ/ር ሰለሞን ተርፋ የሚባለው የዲፓርትመንታችን ኃላፊ እዚህ ዩኒቨርሲቲ ቆይተሃል በእኔ ፈንታ ተሳተፍ አለኝ። እኔም የዲፓርትመንት ሊቀመንበር ትዕዛዝ ተቀብዬ ከዶ/ር በፈቃዱ ደግፌ ጋር በውይይቱ ተሳተፍኩ። ይህም ውይይት ከኢህአዴግ ጋር በቀጥታ የሚያጋጭ መስመር ውስጥ አስገባኝ…” (ገጽ 154)
ዶ/ር መረራ በፖለቲካ ትግል ውስጥ ቀንጣ ያለውንና ብዙም ጭንቀትና መስዋዕትነት የማያስከትለውን “የቢራ ላይ” የፖለቲካ ትግል አቀንቃኝ መሆናቸውን ሳይደብቁ ይነግሩናል። ይህ አስተሳሰባቸው ከዚህ ቀደምም ባንጸባረቁባቸው መድረኮች ክፉኛ ትችቶችን ያስተናገዱበት እንደሆነም ይታወቃል። እሳቸው ግን እንዲህ ይላሉ። “…አንዳንድ ጊዜ ስናደድ እኔ ቢራ እየጠጣሁ የሚደረገውን ትግል ነው የምታገለው። ከዚያ በላይ ከቻላችሁ በቦሌም ይሁን በባሌ መጥታችሁ ትግሉን ምሩት የምልባቸው ጊዜያቶች ነበሩ። በተለይ እናንተ በአሜሪካና በአውሮፓ የውሃ ልክ የምትችሉትን ሥሩ፣ እኛ ደግሞ ኢትዮጽያ ውስጥ ባለው የውሃ ልክ የምንችለውን እንሥራ የምለው ምክሬ በጣም የሚያበሳጫቸው አሉ። እንዲህ ዓይነቶቹ አስተሳሰቦች በአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓም ጎልቶ ይታያል…” (ገጽ227)
ዶ/ር መረራ በዚሁ መጽሐፋቸው ስለኢትዮጽያ የተቃውሞ ፖለቲካ፣ ስለዲያስፖራው ፍላጎትና ድጋፍ፣ ስለፌዴራሊዝም ትግበራና ውጤት፣ ስለምርጫ ስርዓት መበላሸትና በመሳሰሉት ጉዳዮች ሰፋ ያሉ ትንታኔዎችን አቅርበዋል።
በተለይ የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ጋር ያደረጉዋቸው ውይይቶችና የሳቸውን አቋም ያሳዩበት መንገድ ትንሽ ዘና የሚያደርግ ዓይነት ነው። አቶ መለስ ከተቃዋሚዎች ጋር በሚያደርጉዋቸው ውይይቶች ዲፕሎማሲውንና ጉልበትን ቀላቅለው ይጠቀሙ እንደነበር ይተርኩልናል። “…ሌላ ጊዜ ደግሞ ደግሞ ከጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ጋር ስንገናኝ እስቲ መጀመሪያ እንገማገም፣ እናንተም ስለእኛ የምታስቡትን ንገሩን እኛም ስለእናንተ ያለንን እንነግራቹሃለን አለን። ራሱ ከዶ/ር በየነ ጀመረ። አንተ አንዳንድ ጊዜ ከሰይጣኖች ጋር ታድራለህ እንጂ አብሮ የሚያሠራ ሁኔታ አለህ አለው። አቦ ቡልቻን ደግሞ እርሶ ቅን ኖዎት በዚህ ዕድሜዎ የሚለፉት ለሀገር ብለው እንጂ ለሥልጣን አይደለም፣ ነገር ግን ድርጅትዎ፣ ቢሮዎ ምን እንደሚሰሩ የሚያውቁ አይመስልኝም አላቸው። ወደእኔ ዞረና መረራ አንዳንድ ጊዜ ከሰይጣኖች ጋር ያድራል እንላለን፣ አንዳንድ ጊዜ ራሱም ሰይጣን ነው እንላለን፣ እስካሁን አልለየንም አለኝ። ዋናው ዓላማው እኛን ለመለያየት ይመስለኛል፤ ብዙ ያተረፈ ግን አይመሰለኝም። የእኔ ተራ ሲደርስ ብዙ ዝርዝር ውስጥ ሳልገባ …በእኔ ዕይታ ኢህአዴግ የብዙሃን ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሃገራችን እንዲፈጠር ምንም ዓይነት የፖለቲካ ፍላጎት የሌለው መሆኑ ነው አልኩት….(ገጽ219)”
ዶ/ር መረራ አሁንም አቶ መለስ በምን መልኩ ያስፈራሩዋቸው እንደነበር መተረክ ይቀጥላሉ። “አንድ ቀን ደግሞ የእነ ዶ/ር መረራ ድርጅት ውስጥ አስር የፓርላማ አባላት ኦነጎች ናቸው፤ ልናስራቸው ስለሆነ እንዳትቃወሙን አለኝ። እኔ ደግሞ ዝርዝራቸውን ስጠኝና በራሳችን መንገድ እናጣራለን፤ ሳናጣራ ብታስሩ ግን ጩኸታችንን አንተውም አልኩት፤ እሰጥሃለሁ አለኝ። በሌላ ጊዜም ስንገናኝ ይህንኑ ስም ዝርዝር ደግሜ ጠየኩት። ደህንነቶቼ ከልክለውኛል አለኝ። ፍንጭ እንኳን ካለው ብዬ በፓርላማ የመንግስት ተወካይ የነበረውን ሽፈራው ጃርሶን ዝርዝሩን እንዲሰጠን ጠየኩት። ባለቤቱ የከለከለህን እኔ ከየት አመጣለሃለሁ አለኝ። በዚህም የኦፒዲዮ ባለስልጣናት ታምነው ኦሮሞን የሚመለከት ምስጢር እንደማይደርሳቸው አወኩኝ።…” (ገጽ219)
ዶ/ር መረራ በጠ/ሚኒስትር መለስ ሞት የተሰማቸውን ሐዘን አስመልክቶ ድርጅታቸው መድረክ የሀዘን መግለጫ ማውጣቱን አስታውሰው በሐዘኑ ወቅት የታየው የሕዝብ ለቅሶ በሶስት ከፍለው አስቀምጠውታል። “…በፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ሙያዬ ለመገመት እንደቻልኩት ከዳር እስከዳር ሕዝቡ እንዲሳተፍ በተደረገው ለቅሶ አንዳንድ ነገሮች ግልጽ ነበሩ። ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍቅር የሚያለቅሱ ነበሩ፤ ለሆዳቸው የሚያለቅሱ ነበሩ፤ አባቶቻቸው ሲሞቱባቸው እንደዚያ ማልቀሳቸው የሚያጠራጥር አንዳንድ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ጩኸታቸው እንዳለ ሆኖ ቀረብ ብሎ ቲቪ ላይ ላያቸው ዓይናቸው ላይ እንባ አልነበረም…”(ገጽ 261) ካሉ በኋላ የታንዛኒያው ደራሲ አባባል ከኢህአዴግ መሪዎች ጋር እንደሚመሳሰል ይጠቅሳሉ። “የአፍሪካ መሪዎች ሕዝብ በፍቅር ሳይሆን በፍርሃት ሲያጨበጭብላቸው፤ በፍቅር ያጨበጨበላቸው እየመሰላቸው ልባቸው በደስታ ይፈነድቃል።”
ዶ/ር መረራ ጉዲና በመጽሐፋቸው ኢህአዴግ የሚከተለውን ፌዴራሊዝም አጥብቀው ይኮንናሉ። “…የአንድ ሐቀኛ ፌዴራሊዝም ተልዕኮ፣ በማዕከል የጋራ አስተዳደር ማስፈን፣ በአካባቢዎች የራስ አስተዳደር መፍጠር ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ ዴሞክራሲ በጣም አስፈላጊ ነው። የኢህአዴጉ ፌዴራሊዝም ግን ዴሞክራሲ አልባ ነው። ዴሞክራሲ አልባ በመሆኑ የሥልጣን ክፍፍል የለውም። በመንግስትና ፓርቲ መካከል ልዩነት የለም። የመንግስት ተቋማት የሚባሉት የሁሉም ችግሮች እናት በሆነው አብዮታዊ ዴምክራሲ አስተሳሰብ ተተብትበው ስለተያዙ የአካባቢ አስተዳደሮች ሲያንስ የሞግዚት አስተዳደደሮች፣ ሲበዛ የከፋፍለህ ግዛ ሴራ መሣሪያዎች ናቸው…” (ገጽ 260)
ዶ/ር መረራ የሀገሪቱን አጠቃላይ የፖለቲካ ችግር በመጽሐፋቸው ገምግመዋል። በግምገማቸውም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከአዙሪት ውስጥ እንዳይወጣ ያደረጉ ሶስት መሠረታዊ ችግሮች አሉ ይሉናል። “…የሃገራችን ፖለቲካ በቀላሉ በማይወጣበት አዙሪት ውስጥ የከተቱና ከአዙሪቱ በቀላሉ እንዳይወጣ ያደረጉ ሶስት መሠረታዊ ችግሮች እንዳሉ ነው። እነዚህን የታሪክ ፈተናዎችን በሚሆን መንገድ ካላለፍን የኢትዮጽያ ፖለቲካ ካለህበት እርገጥ የሚወጣ አይመስለኝም። አንደኛው የታሪክ ፈተና ሁለቱ የሀገራችን የፖለቲካ ጫፎች (አንዱ ጫፍ ኢትዮጵያዊነት ሠርተፊኬት ሰጪና ከልካይ እኛ ነን ብለው የሰየሙ ወገኖች ናቸው። ሌላው ጫፍ ደግሞ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ስም በጆሮአችን አንሰማም የሚሉ ናቸው) እነዚህ ኃይሎች የሀገሪቱን ፖለቲካ ከልክ በላይ ስለወጠሩት መሃል አካባቢ ተገናኝተው አብሮ ሊሰሩ የሚችሉ ኃይሎች በቀላሉ ሊወጡ አልቻሉም።
ሁለተኛው የታሪክ ፈተና …የተቃዋሚ ፓርቲ መሪነት ስልጣን እንደ ስልጣን በመቁጠር በህልም ዓለም የሚኖሩ በየጊዜው የሚፈጥሩት ችግር ነው።”
በሰሜን አሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሚሰበሰበው ግብር የግጭት ምንጭም መሆኑ ነው። ያለምንም ማጋነን አራት ኪሎ ከሚገኘው የሚኒልክ ቤተመንግስት ቀጥሎ አሜሪካ/ዋሸንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ማዕከል ሆናለች….” (ሰረዝ የተጨመረ፤ ገጽ177) በሚል ሁለገቡን የፖለቲካ አዙሪት አስቀምጠውታል።

በመጽሐፉ የታዩ መጠነኛ ግድፈቶች
ዶ/ር መረራ ተማሪ በነበሩበት ወቅት አማርኛ ይቸግራቸው እንደነበር የጠቀሱት ጉዳይ በመጽሐፋቸውም አልፎ አልፎ ተንጸባርቋል። የአማርኛ ቃላት አጠቃቀምና የፊደል ግድፈት መብዛት መጸሐፉ በቂ አርትኦት እንዳልተሠራበት ያሳብቃል። እንደአብነት ገጽ 39 ላይ “የትንንሽ ሰዎች” ሥራ ….. የሚል አባባል ይገኛል። ሰዎችን በአቋማቸው ወይንም በአስተሳሰባቸው ወይም በትምህርት ደረጃቸው መለያየታቸው ባያከራክርም የሰውን ልጅ ትልቅና ትንሽ ብሎ ማስቀመጥ ግን ተገቢ አይሆንም። ሌላ ቦታ ደግሞ የጥበቃ ሠራተኛ ለማለት “ዘበኛ” የሚል ቃል ተጠቅመዋል፤እንዲህ ዓይነት ትንንሽ የሚመስሉ ግድፈቶች ለትውልድ ጭምር በሚተላለፍ መጽሐፍ ላይ ታትመው ሲወጡ ጸሐፊውን ትዝብት ላይ የሚጥሉ ይሆናሉ።
ሌላው ከመጽሐፉ ታሪክ ጋር እምብዛም ተዛምዶ የሌለውና ምናልባትም ዶ/ር መረራ በተማሪነት ዘመናቸው ጉብዝናቸውን (የትምህርት ውጤታቸውን) ሊጎዳ የሚችል ድርጊት ፈፅሞብኛል ባሉት የቀድሞ መምህራቸው ላይ በጣም ወርደው ሰውየው ሰልጣን ለማግኘት ለአጼውና ለደርግ ስርዓት የቱን ያህል ያደገድግ እንደነበር እኛ አንባቢያንን ለማሳመን የሄዱበት ርቀት ዘግናኝ ነው። ዶ/ር መረራ ተማሪ እያለሁ መጥፎ ውጤት ሰጥቶኛል ያሉትን መምህር ክብር በሚያጎድፍና ቂም ባዘለ መልኩ ግለሰቡ ስልጣን ናፋቂ፣ አቋም የሌለው ሰው እንደነበር ማቅረባቸው በተለይ ዶ/ር መረራን ከሚያህል ብዙ የሕይወት ውጣውረድ ካየ ሙሁር የሚጠበቅ አይደለም። በነገራችን ላይ ተወቃሹ ሰውዬ በአሁነ ወቅት በሕይወት ይኑሩ፣ አይኑሩ ባላውቅም በስም ማጥፋት ዶ/ር መረራን ቢከሱ ዶ/ር መረራ ለፍ/ቤቱ የሰውየውን አጎብዳኝነትና ስልጣን ናፋቂነት ምን ብለው በተጨባጭ እንደሚያስረዱ ሳስበው ድፍረታቸው በጣም አስገርሞኛል። (ውድ አንባቢ ሆይ! ስለዚህ ጉዳይ በመጽሀፉ ገጽ ከ139-142 የሰፈረውን ማየት ይችላሉ)
(ምንጭ፡- ሰንደቅጋዜጣ 9ኛ ዓመት ቁጥር 416 ረቡዕ ነሐሴ 22/2005)


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>