Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የሚሚ ስብሃቱ እና የባሏ ዘሪሁን ተሾመ (ዛሜ ኤፍ ኤም)ሬዲዮ ሊዘጋ ነው ያላችሁ ተሸውዳችኋል

$
0
0

ከብስራት ወልደሚካኤል

ዛሜ ኤፍ ኤም 90.7 ሬዲዮ (የሚሚ ስብሃቱ እና የባሏ ዘሪሁን ሬዲዮ )ሊዘጋ ነው በሚል የዜና መረጃውን ለሰጡን እናመሰግናለን፡፡ ነገር ግን ይሄንን አምናችሁ ለምትቀበሉ ግን ተሸውዳችኋል፡፡ ምክንያቱም ሚሚ ስብሃቱና ባሏ ቀደም ሲል ከኢህአዴግም ለህወሓት ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩት በብሐረ ትግራይ ትስስርነት የሚመስላቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ከዛ ይልቅ ከህወሓት ያስተሳሰራቸው ለጣቢያው ፈቃድ ከማግኘታቸው ጀምሮ በህወሓት ከከፍተኛ ገንዘብ እስከ ህግ ከለላ የሚደርስ ድጋፍ ይደረግላቸው ስለነበር ነው፡፡ ለዚህም ከየትኛው ካዝና እንደሆነ ባይታወቅም ለዛሚ ኤፍ ኤም ብቻ በሕወሓት ባለስልጣናት በዓመት እስከ 15 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር በጀት ይመደብላቸው እንደነበርስ ስንቶች ያውቁ ይሆን? ጣቢያውስ ለምን እንደተቋቋመስ ስንቶች ያውቁ ይሆን?
Mimi sebhatu
ጣቢያው (ዛሚ ፐብሊክ ኮኔክሽን/ዛሚ ኤፍ ኤም 90.7) በ1998 ዓ.ም. ሲቋቋም አዲስ አበባ በሙሉ የቅንጅት ደጋፊ ከመሆኑ በላይ ኢህአዴግን አምርሮ ይጠላልና ወጣቶችን በገንዘብና በልዩ ጥቅማጥቅም ከመደለል በተጨማሪ በአዲስ አበባ አካባቢ ያለውን መረጃ በአማራጭ ስም የህወሓትን የበላይነት ለማስጠበቅ እንደሚዛን ለመጠቀም የታለመ ነበር፡፡ ሚገርመው ከዛ በፊት በነ ዶ/ር ብርሃኑ እና ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም (ወደ ፖለቲካው ሳይገቡ በፊት) እና ጋዜጠኛ መለስካቸው እና ሌሎች ባለሙያዎች የተሳተፉበት በከፍተኛ በጀት የተመሰረተው አዲስ ብሮድካስቲንግ ካምፓኒ ትልቅ የሚዲያ ተቋም (ኤፍ ኤም ሬዲዮ፣ አጭርና መካከለኛ ሞገድ፣ ወደፊት ቴሌቪዥን ጣቢያ) ነፃ የብሮድካስ ሚዲያ ለማቋቋም ማመልከቻ አስገብተው ፈቃድ ተገኝቶ እጅግ ዘመናዊ የሬዲዮ ጣቢያ ማሽኖች ከገቡ በኋላ ተከልክለዋል፡፡ ከዛ በኋላ ዶ/ር ብርሃኑ እና ፕ/ር መስፍን በምርጫ 1997 ዓ.ም. የተደራጀ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ በመመስረት ቅንጅት እንዲመሰረት ዋነኛ ተዋንያን ነበሩ፡፡ በምርጫውም ቅንጅት አዲስ አበባን ከኢህአዴግ ጅቦች አፀዳ፤ከዛም የአዲስ አበባ ህዝብ የመስተዳደሩን መብት በቻርተር ስም ባንድ ለሌት ህግ ተቀማ፡፡ በዚህ ብቻ ሳያበቃ በቀለኛው ኢህአዴግም የአዲስ ብሮድካስቲንግ ካምፓኒ መሳሪያዎች በሙሉ ወረሰ፣ ሊቋቋም የነበረው ብሮድካስት ጣቢያ ዋና አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ መለስካቸው አምሃ (አሁን የቪ ኦ ኤ ጋዜጠኛ) ታስሮ ከፍተኛ በደል ከተፈፀመበት በኋላ ተለቋል፡፡

የአዲስ አበባን እና አካባቢውን ህዝብ የመረጃ ፍሰት በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን እና በሬዲዮ ፋና ብቻ ሚዛን ማስጠበቅ (በኢህአዴግ መረጃን ማዛባት) ስለማይቻል በከተማው የተወሰነ ኤፍ ኤም ሬዲዮ በግል ስም ማቋቋምና ድጋፍ ማድረግ ወደሚለው ተመራ፡፡ ያኔ ቀዳሚ የሆኑት ሚሚ ስብሃቱ እና ባለቤቷ ዘሪሁን ዕቅዱን ለመፈፀም ፈቃደኝነታቸውን ገለፁ፤ወደስራም ገቡ፡፡ ከዛ በፊት ሚሚ ስብሃቱ ከመሰናበቷ በፊት የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ጋዜጠኛ የነበረች ሲሆን፤ ባለቤቷ አቶ ዘሪሁን ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በአቶ መለስ ዜናዊ እና ስብሃት ነጋ ቀጭን ትዕዛዝ ከተባረሩ መምህራን አንዱ ነበር፡፡

mimi sibehatuበመጨረሻም ለዛሚ ኤፍ ኤም በዓመት 15 ሚሊዮን ብር ከህወሓት ተመድቦ ወደስራ ሲገባ፤ ሚሚ ስብሃቱ በአስገራሚ ሁኔታ ለአንድ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ከሚገመተው በ4 እጥፍ የሚልቅ ጋዜጠኞች ቀጠረች፡፡ እነ ሚሚ ስብሃቱም ለጣቢያው የተመደበውን ብር በቀጥታ ሙሉ በሙሉ ወደስራ ከማስገባት ይልቅ አብዛኛውን ወደኪሳቸው በመወርወር ለተቀጠሩት ጋዜጠኞች በወቅቱ ደመወዝ መክፈል ሳይችሉ ይቀራሉ፡፡ ያኔ በአንድ ጊዜ 20 ጋዜጠኛ ከጀማሪው ዛሚ ኤፍ ኤም ስራ ይለቃሉ፡፡ ከዛም አቶ መለስ ዜናዊ በባለቤታቸው አዜብ መስፍን አማካኝነት እና በነ ስብሃት ነጋ የተመደበው ብር ዓመት ሳይሞላው የት ሄዶ ነው ይህ የተፈፀመውና እና ሌሎችም ጥያቄዎች ከአስገዳጅ ሁኔታ ጋር ካቀረቡ በኋላ የቀሩት ጋዜጠኞችን (የቅርብ ቤተሰብ የነበሩትን) ጨምሮ ሌላ ጋዜጠኞች እንዲቀጠሩ፣ የጣቢያውም የአየር ሰዓት በመዝናኛ እና ቴክኖሎጂ ላይ የሚያተኩሩ ወጣቶች ተወዳድረው እንዲሰሩ ዕድሉ እንዲፈጠር የሚል ሐሳብ ቀረበና ተግባራዊ ተደረገ፡፡ የፖለቲካና ማኀበራዊ ጉዳይ በነሚሚ ቁጥጥርና ክትትል የሚመራ ዜና እና ውይይቶች እንዲቀርቡ ሲደረግ መዝናኛዎች ላይ ተወዳድረው የሚገቡ ወጣቶች የአየር ሰዓቱን በመጋራት እንዲሰሩ ይደረጋል፡፡

በጣቢያው መዝናኛ እና ቴክኖሊጂ ላይ የአየር ሰዓት ተጋርተው ይሰሩ ከነበሩት መካከል ጋዜጠኛ ስለሺ ሐጎስ (በእስር ላይ የምትገኘው የጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ እጮኛ) እና አሁን ከዞን 9 ብሎገሮች ጋር በእስር ላይ የሚገኘው የአዲስ ጉዳይ መፅሔት አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ አስማማው ኃ/ጊዮርጊስ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ሚገርመው እነ ሚሚ መዝናኛ ላይም ሳንሱር ይቃጣቸው ስለነበር እነዚህና ሌሎች ወጣቶች ባለመስማማት ስራቸውን በፈቃዳቸው አቁመው ወጥተዋል፡፡ ይህ ሁሉ ቢኖርም ከእንግሊዝ ከሚያገኙት ርዳታ በተጨማሪ በህወሓት ቀጥተኛ የፋይናንስ ድጋፍ ይደረግለት የነበረው የነ ሚሚ ዓመታዊ በጀት ግን እስከዛሬም አልቆመም፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ማንኛውም የግል ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ በወቅቱ ከነበሩት 5ቱም) የአየር ሞገድ ኪራይና ግብር ለብሮድካስ ባለስልጣን በየዓመቱ የሚከፍሉ ቢሆንም የነ ሚሚ ግን በዝምታና ይታለፍ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ለአንድ ጉዳይ ሁለት የህግ ትግበራ የተለመደም አይደል?እንደዛ ነው፡፡ ጣቢያው አድማጭ ባለመኖሩ የኢህአዴግ ድርጅቶች እንኳ በግድ ከበላይ በሚሰጥ ግዴታ ካልሆነ በዚህ ጣቢያ መ፣ስታወቂያ እንኳ አያስነግሩም፡፡ ስለዚህ ከህወሓት ከሚመደብለት በጀት በቀር ገቢ እንኳ አልነበረውም፡፡ የኢህአዴግ አባላትም ቢሆኑ ጣቢያውን የሚወዱት አይደለም፡፡ አቀራረቡና የመረጃዎቹ ይዘት ምን እንደሆነ ለማወቅ የግድ ባለሙያ አያስፈልገውና፡፡ ስለዚህ ጣቢያው የተቋቋመው የአዲስ አበባን መረጃ ለማዛባት እና ለማስተንፈስ በሚል ቢሆንም እስካሁን ስኬታማ ሊሆን አልቻለም፡፡
የሚሳዝነው በዚህ ጣቢያ ህወሓት ሊያስራቸው ያሰባቸውን ዕጩ እስረኞች ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ገፅ 3፣ አይጋ ፎረም፣ ትግራይ ኦን ላይን እና ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ቀጥሎ ይፋ የሚደረገው በዚሁ በነሚሚ ስብሃቱ (ዛሚ ኤፍ ኤም)ነው፡፡ ለዚህም አንድ ማስረጃ ብቻ ጠቅሼ ልለፍ፡፡ ረቡዕ መስከረም 3 ቀን 2004 ዓ.ም. በዚህ ዛሚ ኤፍ ኤም አንዱዓለም አራጌና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ አመፅ ሊቀሰቅሱ ነው፣ ህዝብ ሊያሸብሩ ነው፣ መንግሥት እንዴት ዝም ይላቸዋል በሚል ሚሚ ስብሃቱ ፣መሰረት አታላይ፣ ዘሪሁን ተሾመ(የሚሚ ባል)፣…በጣቢያው የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ ውይይት ላይ ሲያቀርቡ ነበር፡፡ ከዛም የጣቢያው ስርጭት እንዳለቀ በዕለቱ ከቀኑ 10፡00 ሰዓት አካባቢ የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዱዓለም አራጌ እና ታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ታሰሩ፣ በምሽት የቴሌቪዥን ዜናም እንደወንጀለኛ ተቆጥረው የዕለቱ አብይ ዜና ሆነው አመሹ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን መንግሥት የከሰሳቸውና ከአንባቢ ውጭ ያደረጋቸው ፍትህ እና ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ፣ አዲስ ጉዳይ፣ ፋክት፣…እና ሌሎችም የተዘጉ መፅሔቶች አመፅ ሊቀሰቅሱ ነውና ዝም ሊባሉ አይገባም በሚል ሚሚ ስብሃቱና በልደረቦቿ በዛሚ ኤፍ ኤም ሲሞግቱ ነበር፤ተግባራዊም ተደረገ፡፡ ይህ የሚያሳየው እነ ሚሚ ስብሃቱ የተቋቋሙለት ዓላማ ምን እንደሆነ ትንሽ ፍንጭ ለመስጠት ያህል እንጂ ዝርዝር ሁኔታ እንዳልሆነ ልብ ይሏል፡፡ እና ዛሬ የነሱ ሬዲዮ ዛሚ ኤፍ ኤም ሊዘጋ ነው…የሚለው ከጀርባው ሌላ አጀንዳ እንዳለ መርሳት የለብንም፡፡ ለዚህም የበዓሉ ግርማ ኦሮማይ መፅሐፍ ላይ ስዕላይ ባራኺን እነ ሻዕብይ ለስለላ ተልዕኮ አሰማርተውት …በሚዲያቸው ያስተጋቡት ግን ይሄ ከሃዲ ጥሎን ሄደ፣ ድሮም አይረባም…ምናምን ፕሮፖጋንዳን ያስታውሰናል፡፡
በነገራችን ላይ ነገ ሸገር ኤፍ ኤምም ሆነ ሌሎቹ (ከህወሓት ሰወች ውጭ ) ያሉት የግል ጣቢያዎች የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በህግም ሆነ በሌላ የጉልበት መንገድ መዘጋታቸው የማይቀር ነው፡፡ በዕቅድ መልክ የተያዘ አዲስ መመሪያ(የግል ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ፈርሰው ከመንግስት የአየር ሰዓት ተከራይተው እንዲሰሩ ሚያዝ) እየወጣ ነውና፡፡

በተለያ የብሮድካስት አየር ሞገድ ፈቃድ ሰጭው የኢትዮጵያ ብሮድካስ ባለስልጣን በነ ዘርዓይ አስገዶም (የኢቴቪ ስራ አስኪያጅ የነበረው) በነ ልዑል ገብሩ እየተመራ እነ ሚሚ ፈቃድ ተነጥቀው ጣቢያው ይዘጋል ማለት የዋህነት ነው፡፡ ምናልባት ሌሎችን ጣቢያዎች ለመዝጋት እንደምሳሌ ለመጠቀምና እን ሚሚን ወደ ሌላ ፋናም ሆነ ኢብኮ በማዛወር ተጨማሪ ተልዕኮ ለመስጠትና አቅጣጫ ለማስቀየር ታስቦ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ የነ ሚሚ ስብሃቱ (የህወሓት ሌለው የአዲስ አበባ ሚዲያ ክንፍ) በአገልግሎት ጥራትና ግብር ባለመክፈል በሚል የሚዘጋ የሚመስላቸውም ካሉ ተሳስተዋል፡፡ ምናልባት ሰሞኑን ሚሚ ስብሃቱ በየ አደባባዩ የፕሬስ ነፃነት ተዳፈነ ብላ ግር ግር እንድትፈጥር ሊደረግ ሁሉ እንደሚችል ጠብቁ፤ ግን እንዳትሸወዱ፡፡ ይህ የህወሓት ሉላው ስትራቴጂ መሆኑንም እንዳትዘነጉ፤ እንዳትሸወዱ፡፡ ጨወታው ሌላ ነውና አጀንዳ ባናደርገው ይመረጣል፡፡ ነገሩ አህያ ለአህያ ቢራገጥ ጥርስ አይሰበርም ነውና…

The post የሚሚ ስብሃቱ እና የባሏ ዘሪሁን ተሾመ (ዛሜ ኤፍ ኤም)ሬዲዮ ሊዘጋ ነው ያላችሁ ተሸውዳችኋል appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>