Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ህዝበ-ሙስሊሙን ያለአግባብ በስጋት መፈረጅ፤ ማዋከብና መግደል በአፋጣኝ ይቁም!!

$
0
0

የነፃነት ጐህ

muslim1የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት አንቀጽ 11 ቁጥር 3 ”መንግስት በሀይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤ ሀይማኖትም በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ” ይላል፡፡በሀገራችን ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ በወታደራዊው ደርግ እንዲሁም አሁን ስልጣን ላይ ባለው ወያኔን ጨምሮ ሁሉም ሀይማኖቶች ከመንግስት ጣልቃገብነት ነፃ ሆነው አያውቁም። ፍትህ፣ ነጻነት፣ እኩልነት እና አንድነት ለብዙ ሀይማኖቶች መሰረታዊ እሴቶች ናቸው፡፡ እነዚህ እሴቶች ላለፉት 22 ዓመታት በዘረኛው የወያኔ መንግስት እየተሸረሸሩ እና እየተመናመኑ ዛሬ ከነአካቴውም ለመጥፋት ተቃርበዋል፡፡ ስለመሰረታዊ የሰው ልጅ መብት እና ነጻነት እንዳይወራ የወያኔ የጥይት አፈሙዞች በእያንዳንዱ ሰው እና የህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ተደቅኗል፡፡የእምነት ቦታዎችንም ሳይቀር በመድፈር ህዝበ-ምዕመኑ የኔ የራሴ የሚለው የአምልኮ ቦታ እና የአምልኮ ስርዓት እንዳይኖረው እያደረገ ነው።

ወያኔ አምባገነናዊ ስርአቱን ለማስቀጠል ሲል የዕምነት ተቋማትንና መሪዎቹን በቁጥጥሩ ስር ሲያደረግ ኖሯል፡፡ ይህ አንባገነናዊ ድርጊት በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይም ተግባራዊ በመደረጉ ምዕመናኑ የመንግስትን ድርጊት በመቃወም ላለፉት ሁለት ዓመታት ጠንካራ ሰላማዊ ትግል አድርገዋል፤ እያደረጉም ይገኛሉ፡፡ መንግስት አለመግባባቱን ለመፍታት የቀረቡለትን ሶስት ጥያቄዎች ከመፍታት ይልቅ በማን አለብኝነት የትግሉን ግንባር ቀደም መሪዎች ከማሰር ባለፈ በምዕመናኑ ላይ ኢሰብአዊ ጥቃቶችን ማድረሱ የአደባባይ ሃቅ ነው፡፡  ለወያኔ ህገመንግስትን የመጣስ ድርጊት አዲስ ባህሪው ባይሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ እያደረሰ ያለው የመብት ረገጣውን ማጠናከሩ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል፡፡ ይህ የመንግስት ሀይሎች ድርጊት ችግሩን ከማባባስ ባለፈ የሚያመጣው መፍትሄት አይኖርም፡፡

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ላነሷቸው ግልፅ የመብት ጥያቄዎች ብልሀት የተሞላበት ምላሽ መስጠት ያቃተው ወያኔ እየወሰዳቸው ያሉት ኢህገመንግስታዊ እርምጃዎች፤ በሙስሊሙ ሕብረተሰባ ላይ እየደረሰ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ከመንግስት ሌላ ተጠያቂ የሚደረግ አካል አይኖርም፡፡ ስለሆነም ይህ አይነቱ ህገወጥና ሀላፊነት የጎደለው ድርጊት እንዳይቀጥል ማድረግ ከተጠያቂነት ያድናል፡፡ መንግስት የተበደሉ ዜጎችን ቅሬታ በማጣራትም በህገወጥ ድርጊት በፈፀሙ ሃይሎቹ ላይ በአፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለበት፡፡

 

ሃይማኖታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ችግሮች ሲከሰቱ ሃይማኖታዊ ወይም መንፈሳዊ የሆኑ መፍትሔ ማፈላለግ ብቸኛው አማራጭ ነው፡፡ በእምነት ተቋማት ውስጥ ለሚነሱ ጥያቄዎች ፖለቲካዊ መልስ መፈለግ ችግሩን ከማስፋፋትና ወደ አላስፈላጊ ውዝግቦች ከመክተት ውጪ የሚፈጥረው በጎ ለውጥ አይኖርም፡ ፡ የቤተ-ክርስቲያን አለመግባባቶችን ቤተ-መንግስት ለማስታረቅ ሲሞክር ምን ይፈጠር እንደነበር ታሪክ ደጋግሞ አሳይቶናል። በቅርቡ እንኳ በዋልዳባ ገዳምና በምእመናኑ ላይ የተቃጣው ሰይጣናዊ፤ በትዕቢትና በማናለብኝነት የእምነትን ቀይ መስመርን በመጣስ የተወሰደ ጥቃት ሁለቱንም የወያኔ ቁንጮዎች መለስ ዜናዊንና አባ ፓውሎስን ግብአተ መሬት ማፋጠኑ ይታወሳል። መንግስታዊ ጣልቃ ገብነቶች ከእለት ወደ እለት እየገዘፉና እየጠነከሩ ሲመጡ የችግሮች ስር መስደድም የዚያኑ ያህል እየከፋ ይመጣሉ፡፡ ስለዚህ በእስልምና እምነት ላይ እየተደረገ ያለው መንግስታዊ ጣልቃ ገብነት በሀገሪቱ ህገ-መንግስት ላይ የተገለፀውን መንግስትና ሀይማኖት መለያየታቸውን የሚጥስ በመሆኑ አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃ ይወሰድ ዘንድ ግድ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በክርስትና እምነት እንደተደረገው ሁሉ፤ የህዝበ ሙስሊሙ ፀሎትና ልመና ጣልቃ ገብተው እየበጠበጡ ያሉ አምባገነኖች ላይ መቅሰፍት እንደሚያወርድ ጥርጥር የለውም።

በአወሊያ መጅሊሱ እንዲወርድ ሲባል የተጀመረው ሰላማዊ አቀራረብ አሁን ከአዲስ አበባም አልፎ ወደሌሎች ክፍለ ሀገራት  ደርሶ መሳሪያ አማዟል፡ ፡ ለዚህም ማሳያ በቅርቡ በመዲናችን አዲስ አበባ፤ ደሴና ኮፈሌ ላይ የመንግስት ሃይሎች በንፁሃን የሙስሊም ወገኖች ላይ ያደረሱት መጠነ ሰፊ ጥቃትና ግድያ መጥቀስ ይቻላል። በዚህም ሊያበቃ እንደማይችልም ሁኔታዎችን ተመልክቶ መገመት ይቻላል፡፡ ፖለቲካዊ ማንነት ባላቸው ግለሰቦችና ካድሬዎች ቤተ-እምነቶችን መምራት የኋላ ኋላ ይዞ የሚመጣው መዘዝ ሀገራዊ ቀውስ ነው፡፡ ለተቃውሞ የወጣውን ህዝበ ሙስሊም ሰለፊያ በሚል ቅፅል መጠሪያ ስም በመስጠት ዓላማቸውንም ከሽብር ጋር በማያያዝ መፈረጅ ሁኔታውን ከማባባስ ውጪ ዘላቂ መፍትሄ ሊያመጣ አይችልም፡፡

ሕጋዊ መብትን በግልም ሆነ በኅብረት መጠየቅ ሽብርተኛ አያደርግም፤ ሽብርተኛ የሚያደርገው መብታቸውን የሚጠይቁትን መግደል፣ መደብደብና ማሰር ነው፤ ዓለማዊውን ሥርዓት የማይነካውን፣ ከአምላኬ ጋር ግንኙነት ለመፍጠር የመረጥሁትን መንገድ አክብሩልኝ፤ በሌላ መንገድ ወደአምላኬ እንድሄድ አታስገድዱኝ ማለት ሽብርተኛነት አይደለም፤ ሽብርተኛነት የሚሆነው በሰዎች ላይ ባዕድ የሚሉትን እምነት መጫን ነው፤ ሽብርተኛነት የሚሆነው አትጫኑብኝ እያለ በሰላማዊ መንገድ የሚጮኸውን ሰው መደብደብ፣ ማሰርና መግደል ነው፤ ሽብርተኛነት የሚሆነው የሰዎችን ቅዱስ ቦታ በጥይትና በደም ማርከስ ነው፤ ሽብርተኛነት የሚገለጠው ሰላሜን ጠብቁልኝ እያለ በሚጮኸው ሰው ሳይሆን በጉልበቱ ብቻ ተማምኖ ሰላምን በሚያደፈርሰው ነው፤ ሕዝብ ሰላምን ሲያገኝ ይሠራል፤ ያመርታል፤ ኑሮውን ያሻሽላል፤ ይዝናናል፤ ይህ ሁሉ ጥጋብን ያመጣል፤ ሲጠግብ የሚያስቸግረውን እንዳይጠግብ መበጥበጥ የሚፈልጉ አይጠፉም፡፡ ጮሌነት ዕድሜ አለው፤ የጮሌነት ዕድሜ በጣም አጭር ነው፤ ነገር ግን ጠንቁ ከነኮተቱ በልጅ ላይ ያርፋል፤ የጮሌው ኃጢአት ልጁን አዋርዶ ያቃጥላል፤ ማንም ለማንም የሚመኘው መንገድ አይደለም፡፡

 

ስለዚህ ሙስሊም ወገኖቻችን ጥያቄያቸውን ህገ-መንግስቱ በፈቀደላቸው በሰላማዊ እና ህጋዊ መንገድ እስካቀረቡ ድረስ መንግስት አግባብነት ያለውን መፍትሄ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ የሃይማኖቶች ነፃነትን በዚህ አካሄድ እየጨፈለቁ መሄድ ትርፉ ስርዓታዊ ኪሳራ ብቻ ነው፡፡ የሃይማኖቱ ተከታዮች ይወክሉናል ብለው የመረጧቸውን የአመራር አባላትንም ሆነ ምዕመኑን ማሰር፤ ማንገላታትና መግደል በሀገሪቱ ውስጥ ህገ- መንግስታዊነት እና የህግ የበላይነት ያለመኖሩ ማሳያ ነውና ይኼ አምባገነናዊ እርምጃ በአስቸኳይ መቆም አለበት።

 

ድል ለጭቁኑ ህዝበ ሙስሊም!!

 

ፀሃፊውን በኢሜል yentsanetgohe@gmail.com ያገኙታል።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>