====================================
* በታላቁ የሮመዳን ወር እነሱና እኛ..
* የመረጃ እጥረት ይኖር ይሆን ?
* በጎ አድራጊዋ ጉብልና የአቡ ፈይሰል ቤተሰቦች…
* ” ዱአ .. ዱአ ላይ … ነ …ኝ “
የሮመዳን የመጀመሪያ ሳምነት …
=====================
የዘንድሮው ሮመዳን በሳውዲ በቀለጠ ሙቀት የታጀበ እንደሚሆን ማስጠንቀቂያዎች ጭምር ሲነገሩ ሰነባብተዋል ። እንደ መረጃው ከሆነማ በተወሰኑ ቀናት ሙቀቱ እስከ ሀምሳ ዲግሪ ይደርሳል ተብሎ ይታሰባል ። ይህ በተባለ ማግስት ሮመዳንን ከተቀበልን ሳምንት ሊጠጋ ቢሆንም ላያስችል የማይሰጠው ፈጣሪ ይመስገን የሚያስፈራ የሚያስበረግግ ሙቀት እስካሁን አልተስተዋለም !
ጾሙ የሳውዲን ትላልቅ ከተሞች የሞቀ የደመቀ እንቅስቃሴ ጾሙ እስኪፈታ ያለውን ጊዜ አቀዝቅዞት ይስተዋላል ። ያም ሆኖ የቀኑ ጾሙ ሊያከትም ሁለትና ሶስት ሰአታት እስኪቀሩት ከማለዳው እስከ ተሲያት ጸጥ ረጭ ብሎ የዋለው ከተማና በከተማው የከተመው ነዋሪ በውክቢያና ግርግሩ ይጨናነቃል ! ብቻ ሁሉም ተከባብሮ ያልፋል ፣ ለፈጥሩ ሰአት ገስግሶ ይደርሰናም አፍጥሮ ከጥድፊያው ላፍታ ይሰክናል … !
እነሱ በሮመዳን …
============
በሮመዳን የታደሉት የአረብ ወዛዝርትና ኮረዶችን ጨምሮ በሳውዲ ሰማይ ስር የከተመው ሙስሊማን በጾም ጸሎት የዋለውን ቤተሰቦቻቸው ጾም ለማስፈታት ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን የሚያደርጉበት ልዩ ወር ነው ። በሮመዳን ቤት ያፈራው ተጠራርጎ የሚዘጋጅ የሚሰናዳበት ፣ ለተራራቀ ቤተሰብ እስከ ወዳጅ ዘመድና ጎረቤት ኩርፊያ ጥላቻን በይቅርታ አጽድቶ አብሮ ለመብላትና ለመጠጣት የሚገባበዝበት ድንቅ ወር ነው! በሮመዳን ለነፍሳቸው ያደሩ ባለጸጎችና እንዳቅማቸው የሞላላቸው ከቤት ቤተሰቦች አልፈው በአውራ መንገድ የሚተላለፈውን መንገደኛ ፣ በየስራ ቦታና በየመስጊዱ የተሰባሰቡትን ጾመኞች ድረስ ሔደው ጾማቸውን እንዲፈቱ ያለምንም ከፍያ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ደግሰው ያበላሉ ያጠጣሉ ። አንዳንዴማ አንቱ የተባሉ ዲታ ባለጸጎች ከመንገድ ከጽዳተኛ አሽከራቸው እኩል ማዕድ የሚቆርሱበት ፣ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው የሚያዩባት ወር የሮመዳንን የፍቅር ተግዳሮት መታዘብ ለመንፈስ የሚሰጠው እርካታ የትየ ለሌ ሆኖ እናገኘዋለን ! ባለጸጎችም ዝቅ የሚሉበት ወር ነው ለማለት እንጅ በሮመዳን ባለጸጎችም ብቻ ሳይሆኑ እንዳቅማቸው የሚያድሩት ጭምር በሮመዳን ብቻቸውን አይበሉም ፣ አይጠጡም ! በሮመዳን የሰፈር ድሃዎች ለይተው በቻሉት መጠን የሚበላ የሚጠጣ በማቅረብ ይደግፏቸዋል ። ከምግብ መጠጡ አልፎ የገንዘብ እርዳታና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በምክርና የተለያየ ድጋፍ የሚሰጥበት የደግነት መገለጫ ወር መሆኑን እየተዛብኩ ኑሬታለሁና እውነቱን እነግረችኋለሁ ! አብዛኛው የኖርኩበት ሀገር ታዳሚዎች በሮመዳን እንዲህ ናቸው ።
እኛ በሮመዳን …
============
በሳውዲ ሰማይ ስር ያለውን ሀበሾች ውሎ አዳር ስንቃኘው ደግሞ የምናስተውለው ሌላ መልክ አለው ። በሮመዳን በአብዛኛው ሀበሾች ሌላው ቀርቶ በየሆስፒታሉ ያለ ጠያቂ የወደቁ ወገኖቻችን ህብረት ፈጥረን በመጠየቁ ፣ በመርዳትና በመደገፉ ረገድ ነፍሳችን አልፈቀደም አልያም አላስተዋለ እንደሁ እንጃ አይንና ጆሯችን ትኩረት አልሰጠም ። ጅዳ ውስጥ ከኮንትራት ስራ ተባረው በመጠለያ ያሉትን ፣ የአልጋ ቁራኛ የሆኑ ሆነው ቀን የጨለባቸውን እየረዳን ያለነው እኛ ሳንሆን አረቦች መሆናቸውን ሳስበው በሮመዳን መልካም በመስራት የመጣውን በረከት የነጠቁን ያህል ይሰማኛል በመንፈሳዊ ቅናት ድብን ያልኩባቸው ቀናቶች ብዙ ናቸው !
በሳውዲ የጠረፍ ከተማና በትላልቅ ከተሞች ብዙ ወገኖቻችን የእኛን ሰብአዊ ድጋፍ ይፈልጋሉ ፣ ግን አያገኙም ! በጅዛን ሆስፒታል ለአመታት ከአልጋ ያለወረደው ካልድ በአዘቦትም ሆነ በሮመዳን ጎብኝ ወገን የለውም ። በመዲና ቤተሰቦቿ ከአመታት በፊት ሀኪም ቤት ወርውረዋት ሄዱ የተባለች ስሟ በውል የማትታወቅ እህት ከሰመመን አልነቃችም ፣ ይህች እህት ጎብኝ የላትም ፣ ቤተሰቧን ከማፈላለግ ጀምሮ ወደ ፈጣሪ በጸሎት አንለምንላትም ! በጅዳ ከአራት አመት በላይ በደረሰባት አደጋ በሰመመን ያለችው እህት ጉዳይ ተመሳሳይ ነው ቤተሰቧ አይታወቅም ፣ እኛም እንዲታወቅ አላደረግንም !
በመኪና ግጭት አካላቸው የተሰናከለው በየሀኪም ቤቱ ሞልተዋል ። ይህን ሰሞን እንዲረዳ ከምናነሳው ወንድም መሀመድ ሁሴን ካለበት ቁንፊዳ ሌላ በመኪና አደጋ አካሉ ብቻ ሳይሆን ጀሮው ማስማት የተሳነው በከፋ አደጋ የተሰናከለ ወንድም አለ ! ችግረኛ መኖሩ ሲታወቅ የሀገር ገጽታ ፣ የመንግስትን ስም ያበላሻል ብለው ለምን እንደሚሸፋፍኑት ባይገገባኝም የያዙትን ጉዳይ ከዳር ለማድረስ የገደዳቸውን ኃላፊዎች ተጽዕኖ እየፈጠርን ሰብአዊ ስራን መስራቱ ገዶናል ! ከሁሉም የሚያስገርመውጉዳዩን የያዙት መረጃው እንዲወጣ አለመፈለጋቸው ሲሆን ለመፍትሔ ፍለጋ የተጉ አለመሆናቸው ይባሱኑ ያማል !
ዝቅ ሲል አረቦች በሮመዳን ለጽድቅ እየነፈነፉ መሰራት የሚፈልጓቸው የበጎ አድራጎት ሰራዎች ከአጠገባችን ሞልተው ተርፈዋል ። እነሱ በሮመዳን ማህበራዊ መገናኛ መድረኮችን ሲጠቀሙባቸው “የተቸገረን እርዳ !” የሚለውን የፈጣሪ ትዕዛዝ እያስተላለፉ በተግባር እያደረጉትም ነው ፣ እኛ በየፊስቡክ ገጻችን መድረክ “የተቸገረን እርዳ !” ሌላም ሌላ መልካም ምግባርን ተገቢ ነው የሚለውን አሽቆጥቁጠን እንለጥፋለን ፣ በተግባር ግን ብዙዎች የለንበትም !
እኛ እነሱን እያየን አናያቸውም ! ስደቱ ከፍቶ ፣ ጊዜ ጠሞ የለከፋቸውን ውስጠ ፌደዌ በሽታ ለማስታገስ መድሃኒት እንኳ ለመግዛት ኑሮ አልሞላ ብሎ የከበዳቸው አሉ ፣ የአልጋ ቁራኛ የሆኑትን ጨምሮ ውስጣቸው ባዶ ሆኖ በውጫቸው የተዋቡ የወገኖቻችን ድረስ ባለው ሰፊ ምህዳር በሮመዳን የእኛን ድጋፍ ፣ የእኛን ጸሎት ፣ የእኛን አለኝታና ድጋፍ የሚሹ በርከት ያሉ ማህበራዊ ችግሮች በውስጣችን ቢኖሩንም እኛ ለዚያ ግድ የለንም አልያም ያላስተዋልነው ነገር አለ …
የመረጃ እጥረት ይኖር ይሆን ?
====================
ከላይ የጠቀስኩትን ወደ መንፈሳዊ መነቃቃት ያመጣን ዘንድ የሰነዘርኩት ወቀሳ ቢጤ ዋና አላማ ያለፈው ትምህርት ከሆነን በሚል ነው ። ከሁሉ አስቀድሞ በሮመዳኑ በሚጠበቅብን ቦታ ስላለመገኘታችን የመረጃ እጥረት ይኖር ይሆን ? ብለን ለምንጠይቅ ለአብዛኞቻችን ቅንነት ስላጎደለብን እውነታ ብዙ ጥቂት ማሳያዎችን ለመጠቃቀስ ልሞክር ። ይህን ለማድረግ ደግሞ ወደ ቆዩ ማሳያዎችን አልሄድም ፣ በቅርብ እየተከወኑ ያሉ ሰሞነኛ ጉዳዮች መካከል አንድ ሁለት ልበል …
“ለመርዳት ለመደጋገፍ የተጎዳ እርዳታችን የሚሹ ወገኖችብ ለመርዳት መረጃ እጥረት የለንም!” እንዳይባል መረጃው አለ ። ቀዳሚው ማሳያየ የ9 ዓመቱ የአልጋ ቁራኛ የመሀመድን ፣ ብርቱ እናቱንና ቤተሰቡን ታሪክ ያልሰማ አለ አልልም ። ዳሩ ግን እኒህን የ9 አመት ግፉአን ወደ ሆስፒታል ጎራ ብለን ለማየት የቻልን ብዙዎች አይደለንም ! የእናቱን የፍትህ ፍለጋ ጩኸት እየተቀባበልን ብናሰራጨው ከፈጣሪ በታች ግፍ ፈጻሚዎችን ወደ ህግ ፊት የማቅረቡን ጉልበት ምስለኔ ሳይሻን እኛው ማፋጠን እንችላለን! …ይህ በሚጠበቅ ደረጃ እየተካሔደ አይደለም ! ቢያንስ ሳውዲ ያለ ሀበሻ የፊስ ቡክ ተጠቃሚ የብላቴናውን መሀመድ አብድልአዚዝ ፎቶናባ ቪዲዮ መረጃ ከፊት ገጹ ከማሰራጨት መቆጠብ የለበትም የሚል ጽኑ እምነት አለኝ … ብዙዎች ሰፊውን ዝርዝር መረጃ ቀርቶ የመሀመድን ፍትህ ጥያቄ ለማስተጋባት ከፊስ ቡክ ገጻችን ፎቶውን አንድ ሰሞን መለያ የማድረጉን ሞራል ከድቶናል፣ እኛ ግን ብዙዎች የሚጠበቅብንን አላደረግንም ! የሰው ልጅ ሰጥቶ አያጠግብም ፣ በሞራል ፣ ለመሀመድ ቤተሰቦች በጸሎትና በመሳሰሉት ከጎናቸው መቆም በራሱ ከገንዘብ በላይ ነው ! …ይህ መረጃ አለን የሚጠበቅብንን እያደረግን ግን አይደለም!
ቀጣዩ ምሳሌ የክፉው ስደት አካሉን ያሰናከለውና በኩንፊዳ ከተማ ሆስፒታል የሚገኘውን የወጣት አባወራ የወንድም መሀመድ ሁሴን ጉዳይ ነው ። ምናልባት አሳዛኙን መሀመድን ለመጠየቅና ለመደገፍ ከጅዳ 300 ኪሎ ሜትር መሄድ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል ። እንደኔ አስፈላጊም አይደለም ! መሀመድን የተሰበረ አንገት ለማቅናት አንድም ከአንድ ቀኗ ፈጡር ( ቁርስ) አለያም የአንድ ምሳዋን ግማሽ ዋጋ ለመሀመድ መስዋዕት ማድረግ ሰው ዳተኛ ሆኗል ለማለት ጊዜው አይደለም ። ዳሩ ግና በቅርብ የማውቃቸው ለመሀመድ እርዳታ ቀናኢ ሆነው ስልክ ደውለው ” አስር ብር ለመሀመድ አዘጋጅቻለሁ! ” የሚሉኝ ቀን ናፍቆኛል ። በርካቶች በመሀመድ ታሪክ ቢያዝኑም በእስካሁኑ እርዳታ ከ10 ሽዎች የጅዳ ፊስ ቡክ ተጠቃሚ መካከል በተግባር እየደገፉ ያሉት ወደ 20 የሚጠጉ እህቶችና ሶስት አራት ወንድሞች ናቸው። ያም ሆኖ በቀጣይ ቀናት በርካታዎች እጅግ ጥቂት የእርዳታ ተሳትፎ በማድረግ የአባወራውን ወጣት ቤተሰብ ሊደግፍ የሚችል እርዳታ ይሰባሰባል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ ! ከዚህ በተረፈ ያሌለው ያድርግ ብየ አልገፋም ፣ ወጭ ማድረጉ ከከበደን መሀመድ በስልክ ደውሎ ማጽናናት ማበረታታትና በጸሎት እንደሚያስቡት ማነጋገር ከገንዘብ በላይ የሚያክመው ሞራል ሊታሰብ የሚገባ ነው ባይ ነኝ ፣ ለመልካም ነገር መትጋት ዋጋው ከፍ ያለ ነውና !
በጎ አድራጊዋ ጉብልና የአቡ ፈይሰል ቤተሰቦች…
==============================
ትናንት ማምሻውን አንድ ባስደመመኝ ጉዳይ ወጌን ላክትም … የመሀመድ ገንዘብ እርዳታ እንድወስድ አንድ እህት መልዕክት አስቀምጣ ነበርና ስልክ ተደዋውየ ለመቀበል ከቤት የወጣሁት የአሱር ጸሎት እንዳከተመ ነበር ። ቀን ጸጥ ረጭ ብሎ የሚውለው ከተማ በሰውና መኪና የሚሞላ የሚተራመስበት ሰአት ነው ። በቀጠሮው ቦታ ደረስኩ ፣ ሀበሻዋ እህት ቦታዋን ካመላከተችኝ ከአሰሪዋ ጋር ወረደች ፣ እርዳታ የምታቀብለኝ እህት አጠር ያለች ፊቷ ክብ የሆነች ልጅ እግር ጉብል… የለመንኩትን እየሰጠች የተገላቢጦሽ አመስግናኝ ገንዘቡን ሰጠችኝ ! አሰሪዋም እጅጉን አመሰገኑኝ ፣ ይህ ሁሉ የሚሆነው ከግቢየቸው በር ላይ ነው “እቤት ግባ አፍጥር! ” ተብየ አሻፈረኝ በማለቴ ነው ግቢ በር እኔ በመኪናየ መስኮት እነሱ ለመኪናው አጠገብ ቆመው ተቀባበልን !
በልጅ እግሯ እህት ልጅነት ቀልቤ ተስቦ ተሰነባብተን ልንለያይ ልንቀሳቀስ ስል የቤቱ አባወራ ቴምር ውሃና ወተት ይዘውልኝ ሲንደረደሩ ወደ እኔ መጡ …
” ሰለም አሊኩ ፣ አቡ ፈይሰል መአክ ” አሉኝ በመልካም ምግባራቸው ተገርሜ ከመኪናየ ወርጀ ስሜን ማንቴስ ብየ አመስግኘ ያዘጋጁልኝን ለፍጡር የሚሆን ምግብ ተቀበልኳቸው ! ለካስ የእኛዋ ጉብል ሰራተኛቸው የመሀመድን ጉዳይ ነግራቸው ነበርና እርሳቸውም ” ጀዛከላህ !” ፈጣሪ ይስጥህ ብለው አመስግነውኝ የሰራተኛቸውን ደግነትና እንደልጅ እንደሚያዯት በቁሜ አጫወቱኝ ። ቀጥለው አጥር አስርገው ያወሩኝ ስለ ሀበሻው ቢላልና ነጃሽ ታሪክ በጥልቀት እንደሚያውቁና ሀበሻን እንደሚዎዱ ፈገግ እያሉ ጫወታውን አረዘሙት ፣ እኔም ተመስጨ መስማት ያዝኩ ” አየህ ወንድሜ ይህች የምታያትን ልጅ የመጣችው አሁን አደጋ ደረሰበት እንዳላችሁት ወንድም በመጣበት የየመን መንገድ ፣ በአሸጋጋሪዎች ነው። ገና የ 13 ዓመት ልጀ ነበረች ፣ የዛሬ 6 ዓመት ሮመዳን ስራተኛ ፈልገን ሰራተኛ ከሚያቀርብልን ሀበሻ ወደ ኪሎ 8 ሄድን ፣ ብዙ ሰራተኞች ደርድሮ ቢያሳየንም አንዲት እድሜዋ ወደ 20 የሚጠጋ ሰራተኛ መረጥን። ይህችን ልጅ ካስመረጡን ሰራተኞች ውስጥ ትንሿ ነበረች ። መስራት ባትችል ልጃችን ትጠብቃለች ብለንና ለነፍሳችንም ትሆናለች ብለን አመጣናት ። … ከመጣች በኋላ ግን እንኳን ልጅ ልትጠብቅ የእኛ ልጆች እሷን ጠባቂ ሆኖ ፣ ጥሩነቱ የቤተሰብ ናፍቆቱን ስትረሳው ከልጆቻችን እኩል እየቦረቀች ስትጫዎትና ፍቅር ስትሰጣቸው አድጋለች ፣ አላሀምዱሊላህ ዛሬ ያች ህጻን አድጋ ፣ መኖሪያ ፈቃድ አውጥተንላት ፣ ቤተሰቦቿን እየረዳች አብራን ስትኖር ሰራተኛ ሳትሆን ልጃችን ሆና ነው! ከእኛው ጋር በማደጓና መልኳም እንዳየሃት ቀይ በመሆኗ አረብ ነው የምትመስለው ፣ አረብኛም ቡልቡል ናት … ” ብለው የድሃ አደጓን ቤተሰብ ለማግኘት ያገጠማቸውን ክልትም አጫወቱኝ ፣ አቡ ፈይሰል ጫዎታቸው አይጠገብም …
” ዱአ .. ዱአ ላይ … ነ …ኝ ”
==================
ከአቡ ፈይሰል ጋር በነበረኝ ቆይታና ባየሁ በሰማሁት ተደስቻለሁ ፣ በድስታ መኪናየን አስነስቸ ወደ ሌላ ቀጠሮ እያመራሁ ያጋጠመኝን ደስ የሚል ታሪክ ላጫውተው ወደ ኩንፊዳው መሀመድ ስልክ ደወልኩ ። ስልኩ ደጋግሞ ቢጠራም አልተነሳም ፣ ደግሜ ደጋግሜ ደወልኩና ወደ መጨረሻው መሀመድ ስልኩን አነሳ ” ይቅርታ ወንድም ነብዩ ዱአ ላይ ነበርኩ !” አለኝ ። ረብሸው ከሆነ ይቅርታ ብጠይቀውም ጸሎቱን ጨርሶ ስልኬን ማንሳቱን አሳወቀኝ ! የስልኩ አለመነሳት ላጫውተው የነበረውን የእርዳታው ማሰባሰብ ያገናኘኝን የአቡ ፈይሰል ቤተሰብ ጉዳይ አስረስቶኝ የጅዳ ቆንስል ጉዳዩን እየተከታተልኩ እንደሆነ ተጫወትን ። ከዚያ ቀጥየ ስለ እርዳታው ሂደት ስጀመር የአቡ ፈይሰል ቤተሰብና የእኛ ጉብል ለስኬት የበቃ ታሪክ አጫወትኩት … ! …መሀመድ እጅግ በጣም ደስ አለው ፣ ሲቀጥልም እንዲህ አለኝ ” ዛሬ የገንዘቡ ነገር አላስጨነቀኝም ፣ ታሪኬን ከጻፍከው በኋላ ሰው ከአሜሪካ ፣ ከአውሮፖ ከሊባኖስና ከሳውዲ ይደውልልኛል ፣ አይዞህ ብለው እያበረታቱኝ ነውና የቀደቀው ሞራሌ እያንሰራራ ፣ ተስፋ የቆረጠው መንፈሴ በአላህ እትዳታና በሰው አይዞህ ባይነት እየታደሰ ነው ! በእኔ ላይ ለሆነው አላህ ምክንያት አለው ነቢዩ … እዚህ ሆስፒታል መድሀኒት ስለምንወስድ ለሁሉም ታማሚ ቁርስ ፣ ምሳ ፣ እራት በሰአቱ ይቀርባል ፣ እኔ ዘንድሮ ስለሆነልኝ ለማመስገንና ስለምህረቱ ልለምን መድኃኒቴ ዱአ ነውና በፍቃዴ እየጾምኩ ነው !… ለእናንተ ከጎኔ ለቆማችሁ ላልቆማችሁትም ፍቅር ስል ዱአ ላይ ነኝ ፣ እውነት እልሀለሁ ፣ ከልቤ አልቅሸ ፈጣሪየን አመሰግነዋሁ ፣ ዱአ .. ዱአ ላይ … ነ …ኝ !” የተቆራረጠ የሳግ ድምጽ ስሰማ የምሆነውን አጣሁ …በታደሰው የአባ ወራው መንፈስ ፣ በተገነባው የወንድማችህ ህይዎት ምክንያቱ ገንዘብ አለመሆኑን አሰብኩት … ” የሀበሻ ዘር ወገኔ ከሌለበት ቦታ ነው ያለሁ ፣ ሰው ይናፍቀኛል ፣ ወደ ሀገሬ ልግባ! ” ብሎ በምሬት የድሱልኝ ጥሪ ያሰማው የ9 ወር የአልጋ ቁራኛውን ወንድም ሳምንት ባልሞላ ቀን ተስፋውን ስለሞላለት ፋታሪ አምላክ ፣ ከአምላክ በታች የወንድማችን ጥሪ አሳዝኗችሁ በእርዳታና በሞራል ድጋፉ ለተሳተፋችሁ ምስጋናየ ከፍ ያለ ነው!
አሁንም ጊዜው ገና ነው ፣ አባወራውን መሀመድን የአቅማችን ያህል እንርዳው !
ስለሆነው ሁሉ ፈጣሪ የተመሰገነ ይሁን!
ነቢዩ ሲራክ
ሰኔ 19 ቀን 2007 ዓም
The post የማለዳ ወግ… ” ዱአ .. ዱአ ላይ … ነ …ኝ ” ጸሎት ላይ … – ነቢዩ ሲራክ appeared first on Zehabesha Amharic.