Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

በምርጫው ውጤት ሊተላለፉ የተፈለገው መልእክት ምንድን ነው?። (ዳዊት ዳባ)

$
0
0

Friday, June 26, 2015

ዳዊት ዳባ

electionምርጫው ወያኔ በሚፈልገው እንደውም ባቀደው መንገድ አጠናቋል።  “እረጭ ያለ ምርጫ”። እስከቅርብ ጊዜ እንዲደርሰን የተደረገው መረጃ ምርጫውን በመቶ ፐርሰንት ማሸነፋቸውን ነበር። አሁን ለይቶለታል። በመቶ ፐርሰንት ማሸነፋቸውን ብቻ ሳይሆን በተወሰኑት ምርጫ ጣቢያዎች ላይ አገኘንም የሚሉት ድምጽም በተመሳሳይ መቶ ፐርሰንት እንደሆነም ነው። ሌብነቱ እንዳለ ሆኖ ምርጫውን ከዚህ በተሻለና በሚመስል መንገድ ከውኖ በመንግስትነት ለመቀጠል መሞከሩን  የሚያውቁት ነበር።  አልፈለጉትም እንጂ መቶ ከመቶ ከሚለው በተጓዳኝ አሁንም እንደ አንድ አማራጭ  አይተውት ነበር ብሎ በእርግጠኛነት መናገር ይቻላል። የሩቆቹ ነጮቹ አለቆቻችንም  የተሻለ ብለው የመከሩት ይህንኑ እንደነበረም እየሰማን ነው። ታዲያ ለምን? መቶ በመቶውን ምርጫቸው አደረጉት።

 

አንደኛው ምክንያት ነገሮችን ከተለመደው በጣም ባፈነገጠ መንገድ ማድረጉን ደጋግመው ተጠቅመውበት ፍቱን የሆነ መላ ሆኖ ስላገኙት ነው። አሁንም ይህው መላ ህዝብን ተስፋ በማስቆረጥ ተገዥነቱን ለማስቀጠል የጠቅማል ብለው ስላሰቡ ነው። ሁለት በአገር ውስጥ የሚደረገውን በይበልጥም ሰላማዊ የሆነውን ትግል ማከርከርያ ለመምታት ነው።

 

መታወቅ ያለበት ተገዥነትም ሆነ ገዥነት የጭንቅላት ጨዋታ አለበት። ትክክል ናቸው አይደሉም የሚለውን እናቆየውና  ለሀይሉ እራሱን ፍፁም በሆነ ሁናቴ ያስገዛው አገሬው ነው ብለው ሰዎቻችን ያምናሉ።  ይሄን ምርጫ ያከናወኑበት ጠቅላላ ሁናቴ ይህ እምነታቸው ምን ያህል ስር የሰደደና  ለውሳኔያቸውና ለድርጊቶቻቸው ሁሉ መሰረት  መሆኑን ነው የሚያሳየን። በዚህ 24 አመት ውስጥ ተመሳሳይነት ያላቸውን ድፍረትና ንቀት ያለባቸውን ተግባራቶች  ብንዘረዝር  ከአንድ ሚሊዬን ምክንያቶች ውስጥ የዚህ ምርጫ ውጤት አንዱ ብቻ ሆኖ  ነው የምናገኘው።  ስልሳ ጀነራሎች ካንድ ዘር ሶሙ ስንል ሌላ ስልሳ ጀነራሎች አሁንም ከራሳቸው ዘር ሾመዋል። ተገዥ አድረገንዋል የሚለው እሳቦት ለውሳኔ ዋንኛ መሰረት እስከሆነ  ተገዥ እንደሆንን እንድንቀጥል ጉልበታቸውን አግዝፈው ማሳየት ደግሞ  አለባቸው። መቼም ልናሸንፋቸው የማይቻለን እንደሆነም ደጋግመው ሊያስታውሱን ግድ ይላል። በተጓዳኝ ደግሞ የትኛውንም አይነት የኛመገዳደር ኮስሶ እንዲታይ  ማድረግ ደግሞ አለባቸው። አይቀጡ ቅጣት የሚያስቀጣም ተደርጎ እንዲወስድም ይፈለጋል። ለማንኛውም ይህ ሁሉ አዲስ አይደለም ሗላ ቀር ተብሎ የተተው ነው እንጂ ድሮ በባርያ ስረአት ዘመን ባርያ ለማሳደር ሲጠቀሙበት የነበረ ነው።

 

መቶ በመቶ አይነት እርምጃ በዋናነት ተገዝቶልናል ብለው ከሚያስቡት ህዝብ በላይም ማማ የሆናቸው ክፍል እንደተሸከመ እንዲቀጥል በእጅጉ አስፈላጊ ስለሆነም ነው። ጦሩ፤ካድሬው፤ የፓርላማ ምናምንቴው፤ አንድ ለአምስት የተደራጀው፤  አጋር በሚል በየዘሩ ያሰባሰቡት…። ፈቅደው ተጠቃሚ አደረጉት እንጂ  ያው ተገዥቸው አድርገው ነው የሚያዩት።

 

ይህ ሰው ያንድ አውራጃ አስተዳዳሪ ነው። ባለቤቱን ቀድሞ ውጪ ልኳል። አሁን ላይ እፎይታ ሊሰማው አልቻለም። በዚህ ምርጫ ሰበብ ስራ በዝቶበት ጭንቅም ላይ ነው የሰነበተው።  ከነልጆቹ ከቤቱ ለቆ በመሳርያ የሚጠበቅ ቦታ ከቶ ነበር። ልጆቹን በመሳራያ እያስጠበቀ ትምህርት ቤት ማመላለስ ድረስ ፈርቷል። በደወለ ቁጥር እነዚህን ልጆች ከዚህ በቶሎ ማውጣት እንዴት አቃተሽ። የዚህ አገር ሁኔታ አይታመንም። አስፈሪ ነው። አንድ እራሴን ሁኔታዎች ሲብሱ ወደጎረቤት አገር በቶሎ መሻገር እችል ነበር። እነዚህ ልጆች ግን ምን አድረጌ። ሲያለቃቅስ ነው የከረመው።

 

ስርአቱ ውስጥ የዚህ ግለሰብ አይነት እጅግ በዙ ናቸው። የዚህ አይነቶቹ በእርግጥም መቶ ከመቶ ካልሆነ ባነሰ ውጤት በጭራሽ አይፀኑም።  ዋናው ነገር ቁንጮዎቹ እዚህ ድረስ ያሳስባቸዋል። ያስባሉም። ልብ ልንለው የሚገባ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ትንሽ ለቀቅ አድርገው ቢሆን  ዘንድሮ እኛም የተዘረፍነው ድምፅ  ጨምረንም  ነፃነታችንን መጠየቃችን አይቀርም ነበር። በመቶ በርሰንት

 

እንዳሸነፉን ሲነግሩን ደነገጥን። መቶ በመቶው በዚህ አኳያም እንደሚጠቅም አስበውበታል ማለት ይቻላል። በተጨማሪም  በሰላማዊው ትግል ውስጥ ድርሻ እያደረጉ ካሉ ዜጎች ውስጥ የተገኘውን ያህል ተስፋ ቆርጠው አብዛኞቻችንን የሚመስሉ ከተገኙም የሚለው  አለበት።

 

Graham Peebles አሳምሮ ገልፆታል።

 

The recent election was an insult to the people of Ethiopia, who are being intimidated, abused and suppressed by a brutal, arrogant regime that talks the democratic talk, but acts in violation of all democratic ideals.

 

“ፈላጭ ቆራጭ አንባገነን ሆናችሁ ያለምህረት ስትቀጠቅጡ የኖራችሁትን ህዝብ ምርጫ ተደርጎ እኛን መረጠን ማለት ስድብ ነው። እናውቃችሗለን  ስለዲሞክራሲ ትቀደዳላችሁ ነግር ግን አንዳቸውን  የዲሞክራሲ እሴቶች እንኳ ማክበር የተሳናችሁ ደናቁርቶች ናችሁ።”

 

{ይሄ አሸነፍን ለዛውም በመቶ ፐርሰንት የሚለው ለይልቃል ወይ ለሰማያዊ፤ ለመድረክ ወይ ለመራራ ነው ካልን በትልቁ እራሳችንን እየሸነገልን ነው። ትግሉም ካኛ ጋር ነው። መልክቱም ለኛ ለዜጎች ነው።}

 

ሁለተኛው በአገር ውስጥ የሚደረገውን ሰላማዊውን ትግል ለማድቀቅ ከተቻለም እስከመጨረሻው ለማጥፋት ነው። ስርአቱ ድርጅቶችን እስከነብሳቸው እየበላ ነው። ብዙ ሺ ሰላማዊ ታጋዬች እስር ቤት ነው ያሉት።። በስቅላት መግደል ሁሉ ጀምረዋል። ባአጠቃላይ ሰላማዊ ትግሉን ብቻ ሳይሆን እውነተኛ ታጋዬችን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥፋት ቆርጠው የተነሱ ነው የሚመስለው። ለነገሩ በቅጥቀጣ የሚጠፋ ቢሆን ኖር ድሮ ይጠፋ ነበር። ስለዚህም በተጓዳኝ አይሰራም ብለን እንድናምን ማድረግ አለባቸው። ይህንን ነው ያደረጉት።  የሚቀጥለውን የምርጫ ድራማ ካሁኑ የመስራትም ጉዳይ አለበት። ሰይብል ነው ያሉት ሰርተውታል ማለት ይቻላል።

 

ሰላማዊውን ትግል በተመለከተ ደግሞ ግማሹን ስራ በርትተን  ለረጅም አመታት እኛም ስንሰራበት ነው የከረምነው። ስለዚህም በቀላሉ ተፈጻሚ ሊሆን የሚችል ሆኖ ታይቷቸዋል። የድርሻችንን ማድረጉን ዛሬም ቀጥለናል። አጉልተን አገር ውስጥ የሚደረገው ሰላማዊ ትግል አይሰራም፤ አያስፈልግም ማለት የጀመርነው  ከምርጫ 97 ማግስት ነው። ይህው ላለፈው አስራ አንድ አመት አካባቢ እየተለዋወጥን ሰርተንበታል። አንዱ ቡድን ሲደክመው ወይ መሳሳቱን አውቆ ሲተወው ሌላው እየተቀበለ እስካሁን ቀጥሏል። ዛሬ የጉጀሌው የኛም ጥረት ተደምሮ ሰላማዊ ትግል አያስፈልግም የሚለው የብዙዎች እምነት ነው። እንደውም ሰላማዊ ትግል አይሰራም የሚለው ይዘቱን ቀይሮ መታገል አያስፈልግም ወደሚለው አድጓል። እግዚአብሔር እንዳመጣቸው እሱ አንድ ነገር ያድርግ ብቻ አይደለም በተፈጥሮ በሂደት ታመውና አርጅተው ይሞታሉ የሚባሉ አነጋገሮች መስማት የተለመደ ሆኗል።

 

የተዘራው ነው የሚታጨደው።

 

 

 

ደቡብ ኦሞ ደራሼ ውስጥ በጊዶሌ አውራጃ መምረጥ የሚችለው የህዝብ ቁጥር 11773 ለለምመረጥ የተመዘገበው 646 ነው። ንብን የመረጠ 431፤ ጃንጥላን 171፤ ሌላ ሰምቼው የማላውቅ ድርጅትን 44 ህዝብ ነው የመረጠው። በሌሎች ምርጫ ጣብያዎች ውጤት ቢገለጽ ከጊዶሌው ብዙም ልዩነት የሚታይበት አይመስለኝም። ምን አልባት በኦሮሚያ ክልል በተወሰነ ደረጃ ልዩነት ሊኖረው ይችላል።የምርጫው እለት በቀጥታ ስርጭት በፌስ ቡክ፤ በሳይቶች በመወያያ መድርኮች ስለምርጫው አፈፃፀም  ይተላለፉ የነበሩ የቀጥታ ምስክርነቶችን ስሰበስብ ነበር። ባብዛኛው ምርጫ ጣቢያ የምርጫ ካርድ የወሰዱና ሊመርጡ የወጡት  አንድ ላምስት የተደራጁ ደጋፊዎች መሆናቸውን የሚያሳይ መረጃ ነበር በብዛት የሚመጣው።

 

ይህ ስኬት ከተባለ መቼስ ማል ጎደኒ ብቻ ነው ማለት የሚቻለው።  ይሄ ቁጥር ግን የሚያስፈራ ነው። መጀመርያም ቢሆን የሀይሉ አማራጭ ውጤታማ የሚሆነው በሰላማዊው ትግል መቃብር ላይ ነው የሚለው በጥንቆላ ይሆናል እንጂ እስራተጃዊ ሆነ ፖለቲካዊ ፋይዳው ተሰልቶ የተደረሰበት አይደለም። ይህ ተስፋ መቁረጥን እንጂ ተሳትፎ በመንፈግ የማሳጣት ትግልም አይደለም። ሲጀመር ካገዛዙ ባህሪ አኳያ የማሳጣቱ ትግል በዋናነት ፋይዳው እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ በሁሉም ወገን ስምምነቱ አለ። ከባድ ያደረገው ይህንን አይነት አቋም እንድንወስድ ያደረጉን ገፊ ምክንይቶች የተሳሳቱ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ዘርፈ  ብዙ የሆኑ ተጓዳኝ ጉዳዬችን አካቶ የተያዘ አቋም ባለመሆኑ ነው። መስሎን ነው እንጂ የጎዳነው ባጠቃላይ ትግሉን ነው።  በዋናነት በሀይል የሚደረገውን ትግል። ንቁ ድርሻ ምርጫውላይና ሰላማዊው ትግሉ ላይ ከነበራቸው ዜጎች ነው የመሳርያውን ትግል እየተቀላቀሉ ያሉት። ሰላማዊ ትግሉን ዜጎች በሚሊዬኖች ጉዳዬ ብለው ይዘውትና ተሳትፈውበት ቢሆን ኖር ትግሉ ወደ ህዘባዊ እንቢተኛነት የማደግም የተሻለ እድል ነበረው። እረጭ ያለ ምርጫ ሲያቅዱ እረጭ ማድረግ ነው መዳኒቱ ትግል አይደለም።

 

ስለተጠያቂነት ከሆነ ምርጫ ያልነው ተጠያቂነትን በዋናነት መውሰድ ግድ ይልብናል።  ምርጫውን እንደ መብቱም እንደ አንድ ትግልም መወስድና ተሳትፎ ማድረግ ይገባቸው የነበሩ   ዜጎች በዚህ ደረጃ በማነሳቸው።  የነበሩ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ አስገብቶም  ቢታይ ልንሰራቸው ይገቡ የነበሩ ነገር ግን ያልሰራናቸው ስራዎች ብዙ መሆናቸውን አጋላጭ ነው። ተጠያቂነቱ በተዋረድ ይቀጥላል። ህዘብም ቢሆን በማኩረፍ ሆነ ተስፋ በመቁረጥ ጠብ የሚል መብት የለም። ቀላል የሆነው የዚህ አይነት ትግል ላይ እንኳ ድርሻ ለማድረግ አቅማችን የተሟጠጠ ዜጎች እዩት የሰራነውን።

 

“If there is no struggle, there is no progress. Those who profess to favor freedom, and yet depreciate agitation, are men who want crops without plowing up the ground. They want rain without thunder and lightning. They want the ocean without the awful roar of its many waters. This struggle may be a moral one; or it may be a physical one; or it may be both moral and physical; but it must be a struggle. Power concedes nothing without a demand.It never did and it never will.”
Frederick Douglass

 

“ትግል ከሌለ የሚሻሽልና የሚለወጥ ነግር የለም። ነጻነትን አብዝተው እያሹ ምንም አይነት አስተዋፆ ለማድረግ ተነሳሽነት የሌላቸው ሰዎች ሳያርሱ አዘመራን ማጨድ የሚጎመጁ አይነት ናቸው። ነጎድጓድና መብረቅ የሌለበትን ዝናብ ያልማሉ። ማእበል የሌለበትንም ውቂያኖስ እንዲሁ። ተገደው ካልሆነ ገዥዎች ፈቅደው የሚሰጡት ጠብታ ነፃነት የለም። አይኖርምም። መገደዱ አለባቸው። ማስገደዱ በሀይል ይሆናል ወይም ተሽሎ በመገኘት። ወይም በሁለቱም። የግድ ግን መታገል አለብን።”

 

ለነጻነት ለሚደረገው ትግል ወገንተኛ የሆኑ የበዙት መገናኛዎች ምርጫውን በሚመለከት ለጥፋቱ ድርሻቸው ከፍ ያለ ነው።  ሀላፊነት አለመወጣት ብቻ ሳይሆን አፍራሽ ሚናቸው የጎላ ነበር ባይ ነኝ። ይህንን ለማሳየት አስቤው የነበረው በትንሹ ከምርጫው ሶስት ወር በፈት ጀምሮ በጣም ካነሰም አንድ ወር ውስጥ ሽፋን የተሰጣቸውንና የተሰራባቸውን ቁምነገሮችን ሁሉ በዝርዝር በሰንጠረዥ ማስቀመጥ ነበር።  አንገብጋቢነቱ፤ አንድምታው፤ ህዘብ እንዲወስደው የተፈለገው የጠራው መልእክት። ቃላት ምርጫው። ሆን ብሎ ማንኳሰስ ነበር አልነበረም?። ተስፋ አስቆራጭ ነበር አበረታች?። ምርጫው ውስን በሆነ የጊዜ ሰሌዳ የሚካሄድ ነው። አጥኖትና ቀዳሚነት አግኝቷል አላገኘም?። በምርጫ ቅስቀሳው የነበረ ድርሻ ካለ። የመሳሰሉት ወሳኝ ጥያቄዎች  በማንስት መገናኛው የነበረውን  አስተዋፆ ማሳየት ነበር። በዚህ እሳቦት ሳዳምጠው ሳገላብጠው ስቦረብረው ስለነበር ተልቅ የሆነ የጥፋት ድርሻ እንደነበራቸው ግልጽ ብሎ ማየት ችያለው። ክሴን ከዚህ በላይ ላመረው እችል ነበር። ቢቸግር ነው እንጂ ይህም በራሱ ዱላ ማቀበል ነው። ልተወው።

 

አገር ውስጥ የሚደረገውን ትግል እንደግፋለን የሚሉ ድርጅቶችና ድጋፍ ማህበራትም ሀላፊነታቸውን ባግባቡ አልተወጡም። መሽኮርመም ይታይባቸው ነበር። ለታሪክ መዝገብ ቤት የሚቀመጥ አቋም መግለጫ ከመጻፍ የዘለለ አልነበረም አስተዋፆቸው። ይህን ያህል የሰው ድርቀት አለ ወይ ነው የሚያሰኘው። የተያዘውን አቋም እንኳ በካሜራ ፊት መናገር ታቡ ነበር። የፖለቲካ ትግል  መናገርን አብዝቶ ይፈልጋል።

 

እንደዚሁ ተጠያቂነቱ ይቀጥላል አብያተ እምነቶች ህዝብን ወደአምላክ መመለሱ አንድ ነገር ነው። የግድ የተራበና ነጻነት የሌለው  ባርያ መሆን ግን የለበትም። ይህ ክፉ ስራ ነው። አምላክም አይደሰትበትም።  ስርአቱን አያገለገላችሁ ያላችሁ ዜጎች በይበልጥም ቀለም የቀመሳችሁ ሁሉ  መቶ ፐርሰንት  ህዘብ አሸነፍኩህ እንዲባል አድርጋችሗል። ይህ ንቀት ነው። ይህ በህዝብ ላይ ማላገጥ ነው። ለዚህ ድርሻችሁ የጎላ ነውና የደረስንበትን ደረጃ እስቲ ቆም ብላችሁ እዩት።

 

ወያኔ እንዳቀደው ምርጫው እረጭ ያለ እንዲሆን እገዛ ያደረጉ ሌሎች አስተሳሰቦች።

  • ትግል መሆኑ ቀርቶ ምርጫ ስለተባለ ብቻ ፍታዊ ምርጫ ይደረግና ድምጽ ተሰጥቶ፤ ጠብ ሳይል ድምጽ ተቆጥሮ አብላጫ ድምጽ ያገኛ ስልጣን መያዝ አለበት። ይህ ካልሆነ ምን ያደርጋል። የሚገርመው ይህንን የምንጠብቀው ዛሬም ከወያኔ ነው።

 

  • የሚገለውም የገደለውም ምርጫ ጫወታ ውስጥ ስለምትገቡ ነው። ይህ ሲታገሉ የሞቱትንና የታሰሩትን ተጎጂ አድርጎ ማየትና ነገ የሚገደሉትን አስገዳይ አሳሳሪ አድርጎ መፈረጅ ድረስ ይሄዳል። ይሄ ፍርደ ገምድል መሆን ብቻ አይደለም ጭካኔም ነው።

 

  • በምርጫው የታሰተፉ እውነተኛ ተቃዋሚዎች የመጨረሻ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል እንዴትም እንደሚመጣ ምንም ብዥታ በጭራሽ አልነበራቸውም። አይደለም ለራሳቸው ለህዘብ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ አስረግጠው ሲናገሩት በጥረታቸውም ሲገልፁት የነበረ ነው። ይህ በሆነበት እያወቁ ለምን ተሳተፉ የሚለውን ጥያቄ ቆም ብሎ ለሰከንድ እንኳ ለማሰብ አለመፈልግ። በቃ  ለስልጣን ነው ብሎ መደምደም።

 

  • ትግል የሚያካሂዱበትን ነባረዊ ሁኔታ በጭራሽ ግምት ውስጥ አለማስገባት። ፍቃድ ጠይቀው የሚሰለፉት ፈሪዎች ስለሆኑ ነው።  ትግሉን ከሰላማዊ ወደ ህዝባዊ እንቢታ ያላሳደጉት እየተቻለ ስለሚፈሩ ነው። በመንግስት ታውቀው በግላጭ እየሰሩ መሆኑ እየታወቀ በሚስጥር የማይደራጁት እየቻሉ ነግር ግን ጥቅሙ ስላልታያቸው ነው።  አቅምና ጉልበታቸውን ግምት ውስጥ ሳያስገቡ በዛ ላይ ድርሻም እገዛም በሌለበት ውጤትና ተግባር አብዝቶ መጠየቅ። ሲጀመር ታጋዬች ለህዘብ ወይስ ህዘብ ለታጋዬች ነው ጉልበት መሆን የሚገባቸው። በሁለቱም አቅጣጫ ያስኬዳል ብንል እንኳ እስከ ድክመቶቻቸው እነሱ  መራራ መሰዋትነት  እየከፈሉ ትግሉን ቀጥለዋል። እኛስ?።

 

 

አገር ቤት ያሉ ሰላማዊ ታጋዬች ምርኩዝ የያዘ የተቀዳደደ ድሮቶ የለበሰ ባዶ እግሩን የሚሄድ ሽማግሌ ቢሆን እንኳ በርታትና ጉልበት ሆነነው፤ አፅድተን ሱፍ አልብሰነው አሸናፊ ማድረግ  መናቃችን ግድ ይለዋል። ፍቱንም ነው።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

The post በምርጫው ውጤት ሊተላለፉ የተፈለገው መልእክት ምንድን ነው?። (ዳዊት ዳባ) appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>