Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የነፃነት መውጫው መንገድ፣ ታጋዩ፣ ሕዝቡን ጠንካራ ምሽጉ ማድረግ ሲችል ነው

$
0
0

ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት            

እሑድ ሰኔ ፳፩ ቀን ፪ሺህ፯  ዓ.ም.              

ቅፅ ፫ ፣ ቁጥር ፲፯

moreshየአንድ ለነፃነት የሚታገል ኃይል የመጀመሪያ ተግባሩ፣ ጠንካራ ምሽግ መገንባት ነው። ምሽግ ሲባልም መሬትን ጎርዶ ራስን መቅበር፣ ወይም ደግሞ በኮንክሪት መከታ እና ጠለላ ገንብቶ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚወነጨፉ አውዳሚ የጦር መሣሪያ አረሮችን መከላከል አይደለም። ጠንካራ ምሽግ ሲባል፣ ታጋዩ ኃይል ነፃ አወጣዋለሁ የሚለውን ሕዝብ፣ ዓላማውን አሳውቆ፣ አሳምኖ እና አደራጅቶ የታጋዩ ኃይል የቀለብ፣ የመረጃ እና የሰው ኃይል ምንጭ ማድረግ መቻል ነው። በአጭሩ ሕዝቡን ባሕር፣ ታጋዩን ዓሣ ማድረግ መቻል «ለነፃነት እታገላለሁ» የሚል ኃይል የአደረጃጀት ስልት ሊሆን ይገባል። ይህን ያላደረገ ታጋይ ሌሎችን ነፃ ሊያወጣ ቀርቶ፣ ራሱም ነፃ አይሆንም። ራሱን ነፃ ያላወጣ ደግሞ፣ ብዙኃኑን ወደ ነፃነት ጎዳና ሊመራ አይቻለውም።

ለነፃነት የሚታገሉ ኃይሎች ደረጃ በደረጃ ሊያሟሏቸው የሚገቧቸው ሁኔታዎች አሉ። የዚህም የመጀመሪያው ማሳያው «ታጋዩን ኃይል እንመራለን፣» የሚሉ ቡድኖች እና ግለሰቦች ራሳቸውን ከማናቸውም ተጽዕኖ ነፃ አድርገው፣ የራሳቸው የመንቀሳቀሻ ቦታ በሕዝቡ መሀል ሠርተው መገኘት መቻል አለባቸው። አፋኝ ለሆነው ኃይል የሥጋት ምንጭ መሆናቸውን ወዳጅ ብቻ ሳይሆን፣ ራሱ ጠላትም እንዲያምን ሊያደርጉ ይገባል። ሕዝቡም እውነተኛ ምሽጋቸው የሚሆነው፣ ከአፋኙ እና ከጨቋኙ ኃይል የሚሰነዘርበትን ማናቸውንም ጥቃት የሚመክት እና ጥቃት ከመፈጸሙ በፊትም የሚከላከል መሆኑን በተግባር ሲያይ ነው። ይህ በተግባር በማይታይበት ሁኔታ፣ ሕዝብ፣ «የነፃነት ታጋዮች ነን» ባዮች ምሽግ ሊሆን አይችልም። በአንፃሩ፣ ሕዝብ የአፋኙ ኃይል ጥቃት እንዳይደርስበት ራሱን ለማዳን ሲል ወደ ያልተፈለገ አቅጣጫ ሊያዘነብል ይችላል። ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ ባለፉት ፳፬(ሃያ አራት) ዓመታት በጉልህ ታይቷል። በተለይ ከ፲፱፻፺፯ ዓ.ም. የምርጫ ድራማ በኋላ፣ ሕዝብ «ለነፃነት እንታገላለን» በሚሉትም ሆነ «በሕጋዊ እና ሰላማዊ መንገድ ለውጥ እናመጣለን» ባይ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ ጀርባውን መስጠቱ የአደባባይ ምስጢር ነው።

ሕዝብ «ለነፃነት ታጋዮች» ዕውነተኛ ምሽግ የሚሆነው፦ መልካም ዓላማ ስላለን፣ ወይም ደግሞ «ለአንተ ነፃነት ነው የምንታገለው» ስላልነው ብቻ አይደለም። ይልቁንም ሕዝብን ጨቁኖ የሚገዛውን ኃይል ማንበርከክ እንደሚቻል የገዥውን ኃይል የአፈና እና የስለላ፣ እንዲሁም የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ መዋቅሮች ለመበጣጠስ ያልተቆጠበ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል። የአፋኙ ገዥ መዋቅር እንደፈለገ መንቀሳቀስ፣ እንደለመደው ማዘዝ እና ማናዘዝ የማይችል መሆኑን በተጨባጭ ድርጊት በማሳየት፣ ሕዝቡን የነፃነት ታጋዩ ጠንካራ ምሽግ ማድረግ ይቻላል። ታጋዩ ለነፃነት መንገድ መሪ፣ ሕዝቡ የነፃነቱ መንገድ ሠሪ የመሆን የአብሮነት እና የአንድነት ስሜት በዓላማ እና በተግባር ሲገለጽ፣ ያን ጊዜ ያለጥርጥር ጠንካው ምሽግ ተገንብቷል ማለት ነው። ከሕዝብ ርቆ እና ወጥቶ፣ ሕዝባዊ ምሽግ መሥራት አይቻልም። የ«አየር በአየር ፖለቲካ» በማራመድ ሕዝብ እና ታጋዩ ሊገናኙ፣ ሊተዋወቁ፣ ሊነጋገሩ፣ እናም አብረው ሊሠሩ አይችሉም። አብረው ካልሠሩ ደግሞ  ምሽጉ በፍፁም አይሠራም። ይህ ምሽግ በሌለበት ሁኔታ ደግሞ «የነፃነት ትግሉ ታጋይ ነን» ለሚሉ ወገኖች መኖሪያ ቀለብ ከመስፈር ያለፈ ፋይዳ ያለው ትግል በሕዝቡ መሀል ይደረጋል ብሎ ማመን «በቅሎ ትወልዳለች፣ ሸንበቆ ያፈራል፣ ዝንብ ማር ትጋግራለች» ብሎ ማመን ይሆናል።

የነፃነት ታጋዩ ዓላማ የሠመረ፣ ተልዕኮውም የተቃና መሆን የሚችለው ምንጊዜም ትግሉን በሕዝቡ መሀል ሆኖ ሲመራ ነው። ትግሉ በዚህ አቅጣጫ ከተመራ፣ ሕዝቡ የታጋዩ ሁለንተናዊ ምሽግ በመሆን ለታጋዩ ጋሻ እና ጦር፣ አገልግል እና እንጀራ፣ እንሥራ እና ውኃ፣ ወፍ እና ደንጋይ ወዘተርፈ ሆኖ የነፃነት ትግሉን ከዳር ያደርሰዋል። ከሕዝብ መሀል ተነጥሎ የወጣ ታጋይ፣ ከባሕር የወጣ ዓሣ፣  ከመንጋው የተለየ ዝንጀሮ፣ አውራውን ያጣ ንብ ከመሆን አይልፍም። ሕዝባዊ ምሽግ የገነባ ታጋይ ኃይል ግን፣ የመረጃ እጥረት፣ የሥንቅ አቅርቦትም ሆነ የሰው ኃይል ችግር ለሕልውናው ፈታኝ መሰናክሎች አሆኑበትም። ምክንያቱም የሁሉም ነገር ምንጩ ሕዝቡ ስለሚሆን ችግሮቹን በትብብር ይፈታቸዋል። በአንፃሩ የታጋዩ እንቅስቃሴ ለጠላት እንዳይጋለጥ፣ ዓይን እና ጆሮ ሆኖ ያገለግለዋል። የዓለማችንን የነፃነት ታጋዮች ለድል ያበቃቸውይህ ዓይነቱ ቁርኝት ነው። የአፍሪቃ የነፃነት ታጋዮች ምሽጎቻቸው ሕዝባቸው፣ የአገራቸው ተራሮች እና ሸንተረሮች፣ ጫካዎች እና ወንዞች እንጂ፣ የጎረቤት አገሮች ሕዝቦች እና ተራሮች አልነበሩም። በአገራችንም በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ወቅት የአምስት ዓመቱ የአርበኝነት ተጋድሎ ያረጋገጠልን ሃቅ ይኸንኑ ነው። የራስ አበበ አረጋይ ጦር ምሽጎች የሰሜን ሸዋ ሕዝብ፣ እንዲሁም የአካባቢው ተረተርና ወንዞች ነበሩ። የደጃዝማች በላይ ዘለቀ ምሽጎች ከጎጃም እስከ አማራ ሣይንት እና መርሐቤቴ ያለው ሕዝብ፣ እንዲሁም ተራሮቹ እና ደኖቹ ነበሩ። የእነ ቢትወደድ አዳነ እና ራስ አሞራው ውብነህ ምሽጎቻቸው የቤጌምድርና ሰሜን ሕዝብ፣ እንዲሁም ሸለቆዎች እና ተራሮች ነበሩ። በአሁኑ ዘመን «ለነፃነት እንታገላለን» ከሚሉ ኃይሎች «ምን ያህሉ ይህንን ነባራዊ ሁኔታ አገናዝበው በተግባር ይተረጉማሉ?» ብሎ መጠየቅ አግባብነት አለው።

ከጠላትም ትምህርት ይቀሰማልና፣ የትግሬ-ወያኔ ቡድን ምሽግ የትግራይ ሕዝብ እና የትግራይ ተራሮች ነበሩ። ዛሬም ናቸው። ወያኔ በ፲፱፻፷፯ ዓ.ም. በሽሬ አውራጃ፣ የደደቢት በረሃ ጠቅላይ ሠፈሩን ሲመሠርት፣ ምሽግ ያደረገው የሽሬ አውራጃን ሕዝብ ነበር። ማንም እንደሚያውቀው ወያኔ ለ፲፯(አሥራ ሰባት) ዓመታት ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር ሲዋጋ፣ ደደቢትን ለቅቆ አያውቅም። በአንፃሩ ደደቢትን መሠረቱ አድርጎ የተፅዕኖ ክልሉን እያሠፋ፣ መላ ኢትዮጵያን የተቆጣጠረው ሕዝቡን ምሽግ በማድረግ መሆኑ ይታወቃል። የወያኔ መምህር የሆነው ሻዕቢያም ለ፴(ሰላሣ) ዓመታት ከአንድነት ኃይሉ ጋር ባደረገው ትግል ምሽግ ያደረገው የኤርትራን ሕዝብ እና የናቅፋን ተራራ መሆኑ ይታወቃል። ሻቢያ «ነፃ ኤርትራን መሠረትን» የሚለን፣ ከናቅፋ እየተወረወረ እና የኤርትራን በረሃዎች ምሽጎቹ እያደረገ ነበር። የሻዕቢያ ታጋዮች እና መሪዎቹ ከሕዝቡ መሀል ሆነው ተዋግተው እና አዋግተው ዛሬ «ጨበጥነው» ለሚሉት ድል በቅተዋል። ይህ ለነፃነት ትግል የሚያደርግ ማንኛውም ኃይል በተግባር ላይ ሊያውለው የሚገባው ነባራዊ ዕውነታ ነው።

ማንም እንደሚያውቀው ሻዕቢያ ገና ከምሥረታው ጀምሮ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ለማፍረስ በፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች የተገዛ እና የተመራ ፀረ-ኢትዮጵያ ቡድን መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም ሻዕቢያ እና መሪው ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ዛሬ ኢትዮጵያ ለገጠማት ሁለተናዊ ችግሮች ፈጣሪዎቹ መሆናቸውን ማንም ንፁሕ ኅሊና እና አስተዋይ ልቦና ያለው ሰው ይስተዋል አይባልም። በተፈጥሮ ሣይንስም ሆነ በማኅበራዊ ሣይንስ፣ የችግሩ ፈጣሪ የሆነ ነገር፣ የመፍትሔው አካል ሊሆን ከቶ አይችልም። ይህን የሚያደርጉ ኃይሎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ፣ ወይም ሆን ተብሎ የትግሉን አቅጣጫ ለማሳት፣ የውሉን ደብዛ በማጥፋት ሕዝቡ ተሰላችቶ የወያኔ አገዛዝ ጊዜ ገዝቶ ሥር እንዲሠድ እና እንዲደላደል ምክንያት ሆነዋል። ትግሉንም ከአገር ቤት አውጥተው ጎረቤት አገር፣ ያውም የችግሩ  ፈጣሪ ከሆነው  ከሻዕቢያ ጉያ ከትተው፣ «ለድል እናበቃሃለን» የሚሉ ወገኖች፣ በወያኔ  አገዛዝ ሕይዎቱ መላቅጡ የጠፋበትን ወጣት የእሣት እራት እያደረጉት እንደሆነ እያየን እና እየሰማን ነው።

«ሻዕቢያ ወያኔን ለማስወገድ እና ኢትዮጵያን ነፃ በማውጣቱ ትግል አጋራችን ይሆናል፤» ብለው ያመኑ አያሌ በትጥቅ ትግል የሚፋለሙ ድርጅቶች በኤርትራ ከመሸጉ ከራርመዋል። ሆኖም እስካሁን አንዲት ጋት እንኳን ፈቀቅ አላሉም። ለአብነት ያህል በተከታታይ ለአሥር ዓመታት ኤርትራ የኖሩት ፕሮፌሰር ሙሤ ተገኝ የሚነግሩን፣ ይህንኑ በሻዕቢያ በኩል የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነት ሊገኝ ቀርቶ ሊታሰብ አለመቻሉን ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር (ኢሕአግ) ሊቀመንበር የነበሩት ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ በሻዕቢያ ታፍነው የደረሱበት አለመታወቅ ሌላው የሕዝብ ጥያቄ ነው። ከኦነግ አንጃዎች የአንዱ መሪ የሆኑት ጀኔራል ከማል ገልቹ በሻዕቢያ የቁም እሥር መሆን አዘውትሮ የሚነሳ ጥያቄ ነው። አቶ መልኬ መንግሥቴም ለረጅም ጊዜ የአርበኞች ግንባርን እንቅስቃሴ ለመምራት አሥመራ ድረስ ደጋግመው ተጉዘው በዐይን አይተው፣ ዙሪያ ገባውን መዝነው ያለውን ችግር በዝርዝር ነግረውናል። ወደ ኤርትራ በረሃዎች ተጉዘው ሕይዎታቸውን በተዓምር አትርፈው የተመለሱ በደቡብ አፍሪቃ፣ በዩጋንዳ፤ እና በሌሎች አገሮች የሚኖሩ አያሌ ወጣቶች የሚነግሩን፣ ሻዕቢያ የኢትዮጵያ ሕዝብ አጋር እና ምሽግ ሊሆን ቀርቶ፣ ሊታሰብም የማይገባው መሆኑን ነው። ስለሆነም ደጋግሞ ሙከራ በተደረገበት እና ውጤት ባልተገኘበት ዘዴ ተመላልሶ ያነኑ ዘዴ መጠቀም፣ ችግሩ ከዘዴው ሳይሆን፣ ዘዴውን ከሚገለገልበት ሰው ወይም ቡድን ላይ ያለ መሆኑን ልገነዘብ ይገባል።

ከዚህ አንፃር፣ ለትግል የቆረጠ የዐማራው ወጣት ምሽጉ ያደገበት ወንዝ፣ ተራራ፣ ሸንተረር፣ ሜዳ እና ጫካ ብሎም ሕዝብ እንጂ፣ የማያውቀው ብቻ ሳይሆን፣ «የዘር ጠላቴ ነው፤» ብሎ የሚያምነው ሻዕቢያ እና የኤርትራ በረሃ ሊመረጥ ቀርቶ መታሰቡ የሚገርምና የሚደንቅ ነው። በአባት ጠላትነት ፈርጆ በዐማራው ላይ እልቂት የፈጸመበት ሻዕቢያ «የዐማራው ወጣት የነፃነት ምሽግ ይሆናል» ተብሎ በምንም ተዓምር አይታሰብም። እስካሁንም ድረስ በዐማራው ላይ በወያኔ  ለፈጸመበት እና ለሚፈጽምበት ሁለንተናዊ ግፍ እና በደል ምንጭ የሆነው ሻዕቢያ እና የኤርትራ ሕዝብ መሆኑን የዐማራው ወጣት ለአፍታም ቢሆን ሊዘነጋው አይገባም።  ነገር ግን «ሻቢያ ለዐማራው የነፃነት ትግል ምሽግ ይሆናል» ብሎ ማሰብ፣ «ዐማራው ወዳጅ እና ጠላቱን ለይቶ የማያውቅ፣ የሚሠራው ሥራ ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት አስቀድሞ መገንዘብ የማይችል እንሰሳ ነው፤» እንደማለት ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ በእርግጥም ሻዕቢያ እና ወያኔ እንደሚሉት ዐማራው «ሓድጊ» ነው ማለት ነው።

ሻዕቢያ እና ኤርትራ የዐማራው ወጣት ለናፈቀው ነፃነት በር ይከፍታሉ ብለው የሚያስቡ ካሉ፣ ሊሆን የሚችለው ኤርትራ የመሠቃያ እና ፋይዳ ያለው ነገር ሳይሠሩ ወዶ የመሞቻ መሬት መሆኑን ነው። ምንጊዜም ሻዕቢያ የዐማራ ሕዝብ ቋሚ የደም ጠላታችን መሆኑን የዐማራው ልጅ ለአፍታ እንኳን ሊዘነጋው አይገባም። ወንድሞቻችንን ከ፵(አርባ) ዓመታት በላይ አሥሮ እያሰቃየ ላለ ቡድን፣ ያሠራቸውን ሳይፈታ፣ እንዴት ከሻዕቢያ ጋር መልካም ግንኙነት ይታሰባል? «ዐማራው ግፍ ፈጽሞብኛል» ብሎ በሐሰት ላይ በተመሠረተ ውንጀላ በእነ እንድርያስ እሸቴ እና መሐሪ ዮሐንስ ተላላኪነት ዐማራው ይቅርታ እንዲጠይቅ ያስደረገው ኢሣያስ አፈወርቂ እንዴት ወዳጃችን ሊሆን ይችላል? ስለሆነም ሻዕቢያ እስከዛሬ ለፈፀመው ግፍ «ስሕተት ፈጽሜአለሁ» ብሎ በአደባባይ ዐማራውን ይቅርታ ሳይጠቅ፣ የዐማራው ልጅ የኢሳያስን ዐይን ለማየት፣ ከእርሱ ምጽዋት ለመቀበል፣ የኤርትራን መሬት ለመርገጥ መንቀሳቀስ፤ በአባት እና በወንድም አስከሬን ላይ ተረማምዶ ለገዳዮቹ «አበጃችሁ» ማለት ስለሚሆን ቆም ብለን ልናስብ ይገባል። የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያዊነት ቋሚ ጠላት፣ እንዲሁም ዐማራውን በነጭ ውሸት «ቅኝ ገዛን» ብሎ ለ፴(ሰላሣ) ዓመታት አያሌዎችን ገድሎ እና አስገድሎ፣ ዐማራን በዘር ጠላትነት ፈርጆ፣ ከራሱ ጥላቻ በላይ፣ ሌሎች ነገዶችን አደራጅቶ በዐማራው ላይ የግፍ ዶፍ እንዲወርድበት ያደረገውን  ሻዕቢያን፣ ለዐማራው ነገድ መድኅን ይሆናል ማለት «እባብ የእርግብ እንቁላል ይጥላል» ብሎ እንደማመን ይቆጠራል። ዛሬ ወደ ኤርትራ የሚያቀኑ ዐማሮች፣ ሻዕቢያ ወንድሞቻችንን ያረደበት ሳንጃ ደሙ ሳይደርቅ፣ የመታረዳቸውን ተገቢነት አምኖ መቀበል በመሆኑ፣ ይህ ድርጊት ይዋል ይደር እንጂ፣ ኋላ መዘዝ  ሊያስከትል እንደሚችል መናገር ነቢይ መሆንን አይጠይቅም።

ስለሆነም የዘረኛውን የትግሬ-ወያኔን አገዛዝ ለመታገል የቆጠረ የዐማራ ልጅ፣ ምሽጉን ወገኑን እና ያደገበትን ቀየ ማድረግ አለበት። የተፈጥሮ ምሽጉን ለቆ ከጠላት ወረዳ መግባት ወዶ ራስን ለጥቃት ማጋለጥ መሆኑን ወጣቱ ሊገነዘብ ይገባል። ከሁሉም በላይ የዐማራው ወጣት ሊሞትለት የተዘጋጀበትን ዓላማ አጥርቶ ማወቅ ይጠበቅበታል። «ለምን ዓላማ ነው የምሞተው? ለምን ራዕይ መስዋዕትነት መክፈል አለብኝ? ትግሉን የሚመሩት ሰዎች ከጎኔ አሉ ወይ? እነርሱስ እነማን ናቸው? ለዐማራው ነገድ ቀና አመለካከት አላቸው ወይ? ያለፈ ታሪካቸው እና ተመክሮአቸው ምንድን ነው? ለምን ኤርትራን መረጡ? ወዘተርፈ» ብሎ በመጠየቅ ለራሱ ተገቢ እና አሳማኝ መልሶችን ማግኘት አለበት። ለዚህም ካለፉት ትግሎች ተሞክሮ መማር ብልህነት ነው።

በሻዕቢያ በኩል ለኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በተለይም ለዐማራው ነገድ የሚጠቅም ጉዳይ ሊሠራ እንደማይችል ባለፉት  የ፳፬(ሃያ አራት) ዓመታት ወደ ኤርትራ ያቀኑት አርበኞች ጉዞ እና በመሪዎቹ ላይ ሻዕቢያ የወሰደው የአፈና እና የግድያ እርምጃ ከበቂ በላይ አሳይቷል። በመሆኑም ሻዕቢያ በተግባር ደጋግሞ ባሳየን እና ስለነፃነት ተጋድሎ ትግል ከታሪክ ከቀሰምነው ዕውቀት ስንነሳ፣ ኤርትራም ሆነች ሻዕቢያ የኢትዮጵያ ነፃነት ታጋዮች ምሽግ ሊሆኑ አይችሉም። «ይሆናሉ» ያሉ ወገኖች ምርጫቸው የራሳቸው ነው። በእኛ በሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት አመለካከት እና እምነት ግን፣ የዐማራው ልጅ፣ እርሱ በማይወስንበት፤ የሌሎች አጀንዳ አስፈፃሚ ለመሆን ጠመንጃ አንግቶ ኤርትራ በረሃ እገባለሁ ለሚል ወጣት አቋማችን «ይቅርባችሁ፣ አያዋጣም» ነው። በኋላ ላይ «መረጃ አጥቼ፣ መካሪ ስላላገኘሁ፣ በወጣትነት ስሜት ተገፋፍቼ» ብሎ ራሱን እንዳይወቅስ፣ ብሎም ራሱን ከፀፀት ለማዳን፣ ዕውነተኛውን መረጃ መስጠት ስላለብን ይህን መግለጫ ለማውጣት የተቋቋምንበት ዓላማ አስገድዶናል። ዓላማችን የዐማራውን ሕይዎት መታደግ ነውና!

 

ዐማራውን ከፈፅሞ ጥፋት እንታደግ!

ፈለገ-አሥራት የትውልዳችን ቃልኪዳን ነው!

The post የነፃነት መውጫው መንገድ፣ ታጋዩ፣ ሕዝቡን ጠንካራ ምሽጉ ማድረግ ሲችል ነው appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>