ላስ ቬጋስ ኒባዳ
ትላንትና ምሽት ላይ ሁሌ እንደማደርገው ፤ የኢንተርኔት መረጃ መረቦችን ዜና መፈተሽ ጀመርኩ ። ያው እንደሚታወቀው በዋሽንግተን ዲሲ 32ኛው የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌደሬሽን ዝግጅት በየፈርጁ እየተከናወነ ስለሆነ ፤ ያሉትን ዜናዎች ለመመልከት እየተጣደፍኩ ነበር ወደ ቤቴ የገባሁት ። የፖለቲካ ፤ የሙያ ፤ የወጣቶች ፤ የሴቶች ማህበራቱና ሌሎቹም ጭምር በየፊናቸው ማንነታቸውን ለማስተዋወቅ ሽር ጉድ የሚሉበት ሳምንት ቢኖር ይህ የወርሃ ጁን የመጀመሪያ ሳምንት ነው ። እኔም ዋሽንግቶን ዲሲ በአካል ባልገኝም ፤ ለረጅም ጊዜ የኖርኩበት አካባቢም ስለሆነ ብዙ ትዝታዎች አሉኝና ፤ አሁን ካለሁበት ስቴት በሃሳብ ዲሲን ቃኝቻለሁ ።
በሰአታት ውስጥ የተለያዩ አይነት ዜናዎች ይጎርፋሉ ። አንዱን ሳልጨርስ ሌላው ይከተላል ።እናም ቦታው ላይ ባልገኝም ካለሁበት ቦታ ሆኜ በሃሳብ ደረጃ የደገፍኩት የፕሬዚደንት ኦባማን የኢትዮጵያ ጉዞ የሚቃወመውን ሰልፍ ነበር ። ድምፁ ከተዘረፈበት ፤ የሰላማዊ ታጋዮቹ ታንቀውና በዱላ ተደብድበው ከሞቱበት ፤ በነጻነት ሃሳባቸውን በመግለፃቸው አሸባሪ ተብለው ብሎገሮቹ ከታሰሩበት ህዝብ ጎን ይቆሙ ዘንድ የሚጠይቀው ይህ ሰላማዊ ሰልፍ በነጩ ቤተመንግስት መግቢያ ላይ እየተደረገ ነበር እንደደረሰኝ መረጃ ።
የሰልፉን ውጤት አያለሁ ብየ እንደጓጓሁ ዜናውን ከመረቡ ላይ ተጭኜ ስከፍተው የሰልፉ ዜና ቀርቶ ርእሱ የአሜሪካው ድምፅ ራዲዮ ጋዜጠኛ ሄኖክ ሰማእግዜር ሆኖ አገኘሁት ። የሰልፉ አቢይ አላማ እዚህ ላይ ከሃዲዱ እንደዋጣ ባቡር እውር ድንብሩን በደም ፍላትና በባዶ ጭኽትና ጫጫታ ታጅቦ እንክትክት ብሎ ተሰባበረ ።
አሜሪካኖች የማያዩ መስለው የሚያዩ ትላልቅ አይኖች አላቸው ። የማይሰሙ መስለው በደንብ የሚያዳምጡ ጆሮዎችም አላቸው ። ከፋም ለማም እነዚህ አይኖችና ጆሮዎች ፤እንኳን ነጩ ቤተ መንግስት ፊት ለፊት አይደለም በመላ ሃገሪቱ ብሎም በመላው አለም የሚደረገውን ክንዋኔ ሁሉ መዝግበው ያስቀምጣሉ ። ስለኛም ውሳኔዎች ሲሰጡ እንደመረጃ የሚያቀርቡት እነዚህኑ አይነት ተግባራቶቻችንን ነው ። እንደ ሲፒጄ የመሳሰሉ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅቶችም ነገ በኛ ላይ ውግዘት ያቀርባሉ ። ይህ ደግሞ ለወያኔ መደብደቢያ ዱላችንን ማቀበል ይሆናል ።
ሄኖክ ሰማእግዜር የሚያቀርባቸው ዝግጅቶቹ ወያኔ ዘመምነት ይስተዋልባቸዋል ብለን ብናምን እንኳ ፤ የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ የሚመራባቸው መርሆዎች ሄኖክን እድንደልቡ ሊፈነጭበት እንዳይችል ሊገድቡት እንደሚችሉ ሙሉ በሙሉ እተማመናለሁ ። በዚህ ላይ ሄኖክ ሰማእግዜር የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ወክሎት የመጣ ግለሰብ ነው ። የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ህዝባችን ያለበትን የመረጃ እጥረት በተወሰነም ደረጃ ቢሆን እየቀረፈ ያለ የመረጃ አውታር ነው ። ሄኖክን እንደግለሰብ ብንጠላው እንኳ በአሜሪካ ድምፅ ተወካይነቱ ብቻ በህገ ልቡና አክብሮት የመስጠቱ ጨዋነት እንዴት ይጠፋናል ?
በቦታው ተገኝተው ሲጮሁና ሄኖክን ሲያዋክቡ የነበሩት ወገኖች ደግሞ ለብሰውት የነበረው ቲ-ሸርት ኢሳት የኔ ነው የሚል ነው ። ኢሳት ወያኔ ሃሳቤን በነጻነት ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዳላስተላልፍ ከለከለኝ ብሎ የሚከስ ሚዲያ ነው ። የኢሳት ዜናዎች ሁሉ ብሎገሮች ታፈኑ ፤ ጋዜጠኞች አሳባቸውን በመግለፃቸው ተሳደዱ ታሰሩ ፤ የሚል ነው ። ሃሳብን በነጻነት የመግለፅ ምልክት በሆነችው ዋሽንግቶን ዲሲ ፤ የዚህ መብት አስከባሪ ፕሬዚደንት በሚኖሩበት ነጩ ቤተመንግስት መግቢያ ላይ የኢሳት አባላት በምን የሞራል የበላይነት ነው ጋዜጠኛውን ሄኖክ ሰማእግዜርን ያን ያህል ወከባ ሊያደርሱበት የቻሉት ?
ሔኖክ እንደ ማንኛውም ዜጋ በዚች ሃገር ወስጥ ሙሉ መብት አለው ። መብት ስል ደግሞ ፤እንደጋዜጠኝነቴ ፤ በትውልድ ሃገሬም ሆነ በሌሎች ህይወቴ ይዛኝ በነጎደችበቱ አገራት ሁሉ ኖሮኝ የማላውቀውን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እዚህ አሜሪካ በሚገባ ተጠቅሜበት ስላረጋገጥኩ የሌሎችን መብትም አከብራለሁ ፤ እንዲከበርላቸውም እጥራለሁ ። እንደኔ ፈቃድ አሰቡም አላሰቡ ፤ ብወዳቸውም ብጠላቸውም ፤ መብታቸው እንዲከበር አብሪያቸው እቆማለሁ ። ስለዚህም ዛሬ በሄኖክ ሰማ እግዜር ላይ የተደረገውን ወከባ አወግዛለሁ ። የዚህች የነፃዋ አሜሪካ አገር ህግ ለሄኖክ ባጎናፀፈው መበቱ ላይ የሚገዳደር ካለም ከጎኑ እቆማለሁ ። ይህ የጋዜጠኝነት ብቻ ሳይሆን የዜግነትም ግዴታየ ነው ።
በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ሕገ-መንግስት አንደኛው አመንድመንት (First Amendment) ለማንኛውም ሰው ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ይሰጠዋል ። ይህ መብት ታዲያ ተናጋሪውን ብቻ ሳይሆን የመረጃ ተቀባዩንም መብት የሚጠብቅ ነው ። መረጃ ተቀባዩ የማንበብ ፤ የማድመጥ ፤ የማይጣጣሙ አስተያየቶችን የመመልከትና የመመርመር መብትን እንዲሁ ፤ አንደኛው አሜንድመንት (First Amendment) ይጠብቅለታል ።
የተባበሩት መንግስታት አለም አቀፉ የሰባዊ መብት ኮንቬንሽን አንቀጽ 19 እንዲህ ይላል ። “ማንም ሰው በነጻነት የማሰብና ያሰበውን የመግለፅ መብት አለው ፤ ይህ መብት አንድ ሰው ሃሳብን ያለ ምንም (ማንም) ጣልቃ ገብነት የመግለፅ የመጠየቅና የመመርመር ብሎም መረጃን የማግኘትና በማንኛውም ሜዲያ ሃሳቡን የማስተላለፍ ያልተገደብ መብት ያጎናጽፈዋል ።” http://www.un.org/en/documents/udhr/inde…
ታዲያ እንደማንኛውም ባለ መብት ጋዜጠኛም ሃሳቡን ያለ ምንም (ማንም) ጣልቃ ገብነት የመግለፅ የመጠየቅና የመመርመር ብሎም መረጃን የማግኘትና በማንኛውም ሜዲያ ሃሳቡን የማስተላለፍ ያልተገደብ መብት ተጎናፅፏል ።
ሄኖክ ሰማእግዜር ተገቢ መረጃ አላቀረበም በተባለበት ወቅት እንኳ ባለሙያው ጋዜጠኛ አበበ ገላው የinvestigative journalist ስራውን ሰርቶ የሄኖክ ሰማእግዜርን ዘገባ በአገሪቱ ህግ መሰረት በሚገባ ተሟግቶታል ። የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮም እስከመብታችን ጣራ ድረስ በመሄድ በቦርድ ደረጃ ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔ መስጠቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው ።
መቼም ነገርን ነገር ያነሳዋል አይደለም የሚባለው ! በቅርቡ በጋዜጠኛ አበበ በለው ላይ በአትላንታ የደረሰውና በፓልቶክ የግንቦቶች ደጋፊዎች ነኝ በሚለው የመግረፊያና የመዝለፊያ አፌርስ ሩም ውስጥ ይከናወን የነበረው አሳፋሪ ተግባር እጅግ የሚዘገንን ነው ።
አበበ በለው እኔ ወደኤርትራ በተመላለስኩባቸው ጊዜያት ከመጀመሪያው ጉዞየ አንስቶ ፤ በኤርትራ በኩል ኢትዮጵያ ነፃ ትወጣለች ብየ አላስብም እያለ ይሞግተኝ የነበረ ሰው ነው ። ታዲያ ሁል ጊዜ እኔም የሱን ሃሳብ አክብሬ እሱም የኔን አሳብ አክብሮ ነው የምንለያየው ። ከወራት በፊት እነ ልኡል ቀስቅስንና እነጋዜጠኛ ክንፉ አስፋን በራዲዮው አቅርቦ ቃለ መጠይቅ አድርጎ ነበር ኤርትራን በተመለከተ ። ያ ሁሉ ውርጂብኝ አበበ በለው ላይ የደረሰበት በግንቦቶች ሙዚቃ መደነስ ባለመፈለጉ ነው ። አርበኞች የሚለውን ስም ያልጨመርኩት እዚህ እነሱን የሚወክላቸው ወይም ጥሩንባውን የሚነፋላቸው አንድም ወገን አለመኖሩን ስለማውቅ ነው ።
አበበ በለው ራሱ ባይልክልኝም ጉዳዩን አስመልክቶ ለነአምን ዘለቀና ለብርሃኑ ነጋ የጻፈው ደብዳቤ ደርሶኛል በጎንዮሽ ። ነአምን ዘለቀ ጉዳዩን ቀለል አድርጎ ልያልፈው ቢሞክርም ለአበበ በለው ደብዳቤ በፅሁፍ መልስ ሰጥቷል እንደኢሳት ተውካይነቱ ። ብርሃኑ ነጋ ግን እስካሁን ድረስ በፅሁፍ መልስ እንዳልሰጠው እርግጠኛ ነኝ ። በስልክ አነጋግሮት ሊሆን ይችላል ብየ እገምታለሁ ። ግን ጨዋ መሪ የእድርም ይሁን የእቁብ በፅሁፍ ለተላከ ደብዳቤ በፅሁፍ መልስ መስጠት ተገቢነው ። ያ ካልሆነ ግን ስልጡኑን የአለም ስርአት እንዴት ልንቀላቀልና ህዝባችንን ይዘን ልንራመድ እንችላለን ?
በአጠቃላይ የሰዎችን የማይሻርና የማይገሰስ መብት የማክበር ልምድ ይኑረን ። ስለሰብአዊ መብት እንከራከራለን እያልን እኛው የምንጨፈልቀው ከሆነ ፤ የመናገርና ሃሳብን በነጻነት የመግለፅ መብትን በተግባር ሳይሆን ለፕሮፓጋንዳ ብቻ የምንጠቀምበት ከሆነ ፤ የሰዎችን የመሰብሰብ ነፃነት መብት የማንቀበል ከሆነና የሰዎችን የእምነት ነጻነት የምንጋፋ ከሆነ ፤ እኔ በበኩሌ ጨቆኞችን አንስቼ ሌላ ጨቋኞች ትከሻየ ላይ የምጭንበት ምክንያት ስለሌለ ትግሉ ባፍንጫየ ይውጣ ።
ጁላይ 4 ቀን 2015 እ.አ.አ
The post ጋዜጠኛ ሔኖክ ሰማእግዜር ላይ የተደረገውን ወከባ አወግዛለሁ ! – ከጋዜጠኛ ደምስ በለጠ appeared first on Zehabesha Amharic.