Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

አንቀፅ 39: የራስን ዕድል በራስ መወሰን ሲባል –አስራት አብርሃም

$
0
0

 

Asrat Abrha

አስራት አብርሃም

ውብሸት ሙላት በተባለ የህግ ምሁር ሰሙኑ ገበያ ላይ የዋለው “አንቀፅ 39 የራስን ዕድል በራስ መወሰን” የተሰኘ መፅሐፍ መግቢያ (ፀሐፊው የቃላት ክልሼነት ለማስወገድ ነው መሰል ማስረጊያ የሚል ርዕስ ሰጥቶታል) “የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት አዲስ አይደለም፤ አሮጌ ነው። ብዙ ተፅፎበታል።” በማለት ነው የሚጀምረው፤ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ በተቃውሞም፣ በድጋፍም ጭምር በልዩ ልዩ ሚዲያዎችና መንገዶች ሲፃፍበት እንደነበር ይገልፅና ይህን መፅሐፍ ማዘጋጀት ያስፈለገበት ምክንያት ሲገልፅ ደግሞ “ለአብዛኛው ሰው በሚሆን መልኩ ጠቅለል ብሎና ራሱን ችሎ በመፅሐፍ መልኩ ስለሌለ ይህንን ክፍተት ለመሙላት በማሰብ” መሆኑን ይገልፃል።

ይህ መፅሐፍ በኢፌዲሪ ህገመንግስት አንቀፅ 39 ዘጠኝ ላይ ያለው የራስ ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል የሚለውን ሀሳብ ከታሪክ፣ ከፍልስፍና፣ ከህግና ከፖለቲካ አንጻር እያነሳ በጥልቀት የሚተነትን ነው፤ እኔም ሌሎች የሀገራችን ምሁራን በስፋትና በጥልቀት እስኪተነትኑትና እስኪፈትሹት ድረስ እንደመጥምቁ ዮሃንስ መንገድ ልጠርግ በማሰብ ነው በዚህ መፅሐፍ ዙሪያ አንድ ሁለት ለማለት የወደድኩት።

የመፅሐፉ የመጀመሪያው ምዕራፍ ንዑስ ርዕስ “የብሄር ጥያቄ” የሚል ሲሆን ፀሐፊው በኢትዮጵያ ጨቋኝ ከሚባለው ብሄር የተገኘው ነው ያለውን ዋልሊኝ መኮንን “ኢትዮጵያ የአንድ ብሄር ሀገር ሳትሆን የብዙ ብሄረሰቦች ሀገር ናት” ገፅ (3-4) በማለት ድፍሮ ለመጀመሪያ ጊዜ መፃፉን ይነግረናል። የአንድ የሶፊስቶች ተረት በማምጣት፤ የብሄር ጥያቄ የብሄር ጭቆና ውልድ መሆኑን ይገልፅና የጭቆናው ዓይነትና ደረጃው ግን ያን ያህል እንደሚባለው የተጋነነ እንዳልሆነ ነው የሚያትተው፤ ተረቱ የሚለው እንደዚህ ነው፤ አንድ ሰው በደል ይደርስበትና ክስ ለማቅረብ ወደ ፍርድ ቤት ይሄድና ለፍርድ ቤቱ የሚያስገባውን ማመልከቻ ለአንድ ራቦር ፀሐፊ እየነገረ አፃፈ አሉ፤ ፅፎ እንደጨረሰ ለባለጉዳዩ ያነብለታል፤ ሲነበብለት ባለጉዳዩ  ስቅስቅ ብሎ ማልቀስ ይጀምራል፤ የፃፈለት ሰውዬ “ምነው ጌታዬ ማልቀስዎ?” ብሎ ቢጠይቀው “ለካስ ይህን ያክል ተበድዬ ኑሯል? አለ ይባላል” (ገፅ 5) ይልና ፀሐፊው ሲቀጥል በእርግጥ “ሰውዬው ተበድሏል፤ ትንሽ የበደል ጫፍ ያገኘው ራቦር ፀሐፊ እጅግ አጋንኖና አጣፍጦ እንደፃፈው ሁሉ የኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተውን ከራቦር ፀሀፊው አድራጎት ጋር ሲያመሳስሉት ይሰማል” ይለናል። ዋልሊኝ ሲል ሰምተው “ለካ ይህን ያህል ተበድለን ኖረናል” ብለው የብሄር ጥያቄ እንዳጎኑት ዓይነት አድርጎ ነው የሳለው የሚመስለኝ፤ ለማንኛውም ዋልሊኝ መኮንን ደፍሮ ፃፈው እንጂ በያኔዋ ኢትዮጵያ የብሄር ጥያቄና ጭቆናው ጣሪያ የነካ ጉዳይ የነበረ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ጥያቄው ራሱ አሁን ያፈራው ውጤት በማየትም መረዳት የሚቻል ነገር ነው።

በዚህ የብሄር ጥያቄ ላይ በህግ መንግስቱ የሚታየው ጉድለት አንድ ብሄር ወይም ብሄሮች ስለሚለያዩበት እንጂ አንድ ለመሆን ወይም ለመጠቃለል ቢፈልጉ ስለዚህ ጉዳይ ምንም ያለማለቱን ልብ ብሎታል፤ ስለዚህ ጉዳይ ሲገልፅ “የእኛ ህገ መንግስት ፈፅሞ የብሄሮችን መዋሃድ ወይንም ወደ አንድ ብሄር የመጠቃለል አዝማሚያን በቃልም በተግባርም አላማው አላደረገም፤ ተቃራኒው የበለጠ እውነት ይመስላል” (ገፅ 9-10) ይላል፤ ይሄ ተገቢ የሆነ ምልከታ ነው። ህገ መንግስቱ ከኢትዮጵያ መገንጠል እንደፈቀደ ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ መጠቃለል የሚፈልጉ ህዝቦች ወይም አንድ ብሄር ከሌላ ብሄር ጋር መዋሃድና መጠቃለል ቢፈልግ ስለሚቻልበት ሁኔታ አለማስቀመጡ የህገ መንግስቱ መሰረታዊ ዓላማ ምን እንደሆነ ግርታን ነው የሚፈጥረው፤ ህገ መንግስቱ ሲረቀቅ እንደዚያ ቢደረግ ኖሮ  አንቀፁ ፍትሃዊነት የሚንፀባረቅበት በሆነ ነበር።

ፀሀፊው በስልሳዎቹ ነበረው ዓለም አቀፍና ሃገራዊ የብሄርተኝነት ትግል እንቅስቀሴ ከዳሰሰ በኋላ በእኛ ሀገርም በዚያ ዘመን የነበሩ ልሂቃን ጥያቄው በማራገብና በማጦዝ እንዚህ ደረጃ ላይ እንዳደረሱት ነው የሚያትተው፤ “የዚያን ዘመን ልሂቃን የብሄርን ጉዳይ በየአገኙት አጋጣሚ እና መድረክ ሰብከዋል። የብሄር ብሄረሰብም ስልጣን ትምጣ ብለው ተመኝተዋል። ከዚያም እነዚህ ልሂቃን ህዝቡ ከማለት ፈንታ ሕዝቤ በማለት ሲጠሩ ተስተውለዋል ከዚያም ያን ህዝብ (የብሀረሰብ አባል) ያኔ የሚለውን ልሂቅ እንደሚከተል ቀድመው ያውቁታልና!

እስቲ ላሙን ንዳው አቧራው ይነሳ

ይከተል የለም ወይ ኮርማው እያገሳ

እንደሚባለው መሆኑ ነው፤ ብሄርተኝነት ስትጎንና ስለብሄር ሲወራ የብሄሩ አባል እያገሳ መከተሉ አይቀሬ ነው” በማለት ነው የሚያስቀምጠው።

የዚህ የብሄር ጥያቄ ጉዳይ አላግባብ ሲለጠጥና ሲራገብ የሚኖረው አደገኝነት ሲብራራ ደግሞ አደጋው እንደ ዩጎዝላቪያና እንደ ሩዋንዳ ለጭፍጨፋና ለዘር ማጥፋት ወንጀል ምክንያት እንደሚሆን ነው የሚያትተው። ለዚህ አደገኛ አካሄድ በእኛ ሀገር አልፎ አልፎ የሚታየው ዘርን መሰረት ያደረገ የህዝቦች መፈናቀልና ግጭት እንደማሳያ መቅረብ የሚችል ነው።

በኢትዮጵያ በዘመነ ኢህአዴግ የብሄር ጥያቄ አፈታት በተመለከተ ፀሀፊው ሲያስረዳ ስልጤ፣ መንጃ እና ቅማንት የተባሉ ብሄረሰቦች ጉዳይ ያነሳና በእነዚህ ብሄሮች ጥያቄ ላይ የተጠሰው ምላሽ የሚታየው ተቃርኖና መፋለስ ያስቀምጣል። በሌላ በእኩል ደግሞ በፌደራሉ መንግስታዊ መዋቅር ውስጥ የሚታየው ፍፅም ያልተመጣጠነ ስልጣን በማንሳት በገዥው ፓርቲ የሚሰበከው የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት እውነትነት የሌለው ፕሮፖጋናንዳ መሆኑን በምሳሌ ነው ያስቀመጠው፤ ቁልፍ የሚባሉ መንግስታዊ የስልጣን እርከኖች በእነማን እንደተያዙ በማሳየት።እንደዚሁም በደሬዳዋ አስተዳደርና የሃረሪ ክልል አፈጣጠርን በማምጣት ኢህአዴግ መራሹ መንግስት የብሄር ጥያቄዎችን ለመፍታት የሄደበት መንገድ ከራሱ ከህገ መንግስቱ ሳይቀር ምን ያህል እንደሚቀረን ያሳየናል።

በምዕራፍ ሰባት ላይ ደግሞ የአማራ ጉዳይ ነው የሚያነሳው። አማራ የሚባል ብሄር አለ ወይስ የለም የሚለው የምሁራኑ ክርክር ያነሳና የለም የሚሉትን ትንሽ ጎሸም ያደረጋቸው ይመስለኛል። ይህ ምዕራፍ የሚጀምረው

… እና አማራ ነኝ … መከራ የመከረኝ

መስዋዕትነት ያጠነከረኝ … ፍቅር የተዘከረኝ…

ብፈራንኳ ፍቅርን ነው’ንጂ … በሌላ አልጠረጠርም

ማንም እንዳሻው ለክቶ … እንዳሻው ሊቆርጠኝ ቢያልም…

ከልክ አልፌ አላጥርም

ጉራም ቢሆን ልቀናጣ …

ስሞ ባያሳድገኝ … ነክሶ እሚያነቃኝ አላጣ …

በሚለው የሙሉጌታ ተስፋዬ ግጥም ነው የሚጀምረው። ከዚህ ግጥም ወረድ ብሎ እንዲህ ይለናል “ስለአማራ መፃፌ፣ አማራ ብሄር ስላልሆነ ወይንም የማንነት ጥያቄ ስላነሳ ሳይሆን አንዳንድ ምሁራን ስለአማራ ጉዳይ ሲፅፉ አማራ የሚባል ብሄር የለም በማለት የብሄርነት ህልውናውን ጭምር ከመጠራጠራቸው የተነሳ ነው። … እንደውም አማራነትን ከኢትዮጵያዊነት እና አልፎ አልፎም ከክርስቲያንነት ጋር አምሳያ በማድረግ ሲያትቱ ይስተዋላል።”

ውብሸት ይህን ዓይነት ዝንባሌ መኖሩን ካወሳ በኋላ ለማጠናከርያነት የፕሮፌሰር መስፍን መከራከሪያ ያነሳል፤ “እሳቸው (ፕሮፌሰር መስፍን) ሊቃውንት አማራ የሚለው ቃል ከስርወ ቃሉ በመነሳት ነፃ፣ የተመረጠ፣ መገዛትን የማይወድ ወዘተ ሕዝብ ነው በማለት የሰጡትን ትርጓሜ መነሻ ያደርጋሉ። አማራ ማለት ነፃ ሕዝብ ማለት ነው ከሚለው አንፃር ብዙም ፍንጭ የማይገኝ ቢሆንም ነፃነትን የሚወድ ለማለት ነው ከተባለም  ነፃነትን የሚጠላ ህዝብ ያለ ስለማይመስለኝ ይህ ዓይነቱ አተረጓጎም ብዙም ስለብሄሩ የሚገልፀው ነገር ያለ አይመስልም”  በማለት ነው የፕሮፌሰር መስፍን  ሀሳብ በምክንያት ውድቅ የሚያደርገው። ገፅ 73 ላይ ደግሞ “ፕሮፌሰር መስፍን ቀጥለውም የተለያዩ ሰዎች “አማራ ነኝ” ሲሉ ክርስቲያን ነኝ ማለታቸውንም እንደሆነ በመግለፅ ክርስቲያን ከሚለው ጋርም ያመሳስሉታል” በማለት አስቀምጦታል፤ በመጨረሻ ይህን ሀሳብ ሲያጠቃልለው “ሊቃውንት ከስርወ ቃሉ በመነሳት ትርጉም የሰጡት አማራ የሚባል ቢያንስ ህዝብ በመኖሩ ነው። የአለቃ ታዬም የአማራን ህዝብ ከየት መጣነት አስረዱ ከማለት ውጪ የለም አላሉም።” በማለት ነው መከራከሪያውን የሚዘጋው። እንግዲህ እኔ የለሁበትም፤ ፕሮፌሰር መስፍን  በህይወት ስላሉ መልስ ይስጡበት። አማራ የለም የሚለው መከራከሪያ የአንድ ህዝብ ህልውና መካድ ብቻ ሳይሆን እንግዲህ ይሄ ጨቋኝ የማሳጣት ሴራ ወይም ወንጀል ተብሎ ያለማስከሰሱም አንድ ነገር ነው።

ይልቅ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፤ መንጌ ብሶት የወለዳቸው የኢህአዴግ ልጆች ሱሉልታ በደረሱ ጊዜ ዕቃውን ሁሉ ወደ ዝምባዌ ከሸካከፈ በኋላ በቴሌብዥን ቀርቦ በቅጡ የማያውቀውን የኢትዮጵያ ታሪክ ሲደሰኩር የዋለ ዕለት “አማራ ማለት በተራራ ላይ የሚኖር ነፃ ህዝብ ነው፤ ትግሬውም በተራራ ላይ ይኖራል፤ ሌላውም እንደዚሁ በተራራ ላይ ይኖራል እንግዲህ ማነው አማራ?!” ብሎ ነበር ያለው፤ ለካ እንደ ሁለተኛ ክፍል ተማሪ ከፕሮፍ ሸምድዶ ኖሯል፤ በአግባቡ ለመሸምደድም እኮ ልምድና እርጋታ ይጠይቃል፤ ከሄደ በኋላ እንደተሳሳተ ገብቶት ነው መሰል ከቀይ ሽብሩ ለምን ተውኳቸው የሚል ዓይነት የፀፀት ምልክት አሳይተዋል ለገነት አየለ በሰጣት ቃለመጠይቅ ላይ!!

በዚህ መፅሐፍ ላይ ስፊ ትኩረት የተሰጠው ሌላው ጉዳይ የመገንጠል ጉዳይ ነው፤ ይህ አንቀፅ በህገ መንግስቱ እንዲካተት ሆኖ በፀደቀበት እለት የነበሩ ስሜቶች ለማሳየት በወቅቱ እዚያ የነበሩት እና አሁን ሁለቱም በህይወት የሌሉት ነገር ግን ፍፅም ተቃራኒ አቋም የነበራቸው ሻለቃ አድማሴ ዘለቀ እና ዶ/ር አብዱልመጅድ ሁሴን የተናገሩትን አስቀምጠዋል፤ ሻለቃ አድማሴ “በትናንትናው ዕለት (ህዳር 13/1987 ዓም) ጥቁር ክራቫት አድርጌ ነው የዋልኩት። 90% የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብም በትናንትናው ዕለት በማዘን ወደ እግዚአብሄር ፀልዮአል፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ከዚህ የከፋ ውሳኔ ተወስኖ፣ ከዚህ የከፋ ህገ መንግስት ወጥቶ አያቅም፤ ጥቁር ቀን ብሎ አውግዞታል” በማለት የአንቀፁን መፅደቅ ሲኮንኑት፤ በተቃራኒው ደግሞ ዶ/ር አብዱልመጅድ “99.9% የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የደስታ ቀን ነው። አንቀፅ 39 ትናንት ባይፀድቅ ኖሮ ግን ለብዙዎች ክፉ ቀን ይባል ነበር፤ ትናንት የፀሀይ ቀን ነው” በማለት ነበር ደስታቸውን የገለፁት።

ፀሀፊው የራስ ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል የሚኖረው ጥቅም እና ጉዳት ሚዛናዊ በሆነ መንገድ በምሁራዊ ትንተና አስደግፎ አቅርቦታል፤ ከአሁን በፊት ከነበረው የእርግማንና የውግዘት አቀራረብ በተለየ ሁኔታ በምሁራዊነት ተጠያቃዊ መንገድ ትርፍ እና ኪሰራው ጉዳትና ጥቅሙ ለማሳየት ጥረት ማድረጉ ነው አንዱ የዚህ መፅሐፍ ጥቅሙ! ይህን መፅሐፍ አንብበን ስንጨርስ በቂ የሆነ እውቀት ስለመገጠል እንደኖረን ያደርገናል፤ መገንጠል ለሚፈልጉ ኃይሎችም ሆነ መገንጠል ለሚቃወሙ ኃይሎች ለሁለቱም እኩል ጠቃሚ የሚሆን ነው፤ ሁለቱም ወገኖች ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚያደርግ ነው። በሌላ አቅጣጫ ካየነው ደግሞ ጥቅሙናን ጉዳቱን በትክክል ሳይገነዘቡ አንድን ነገር መቋወምም ሆነ መደገፍ ተገቢም አዋጭም ስለማይሆን ነው።

ሌላው በዚህ መፅሐፍ የምናገኘው አዲስ እውቀት የራስን እድል በራስ መወስን እስከመገንጠል መብት በህግ መንግስት ደረጃ ያስቀመጠች ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ ያለመሆኗ ነው። ከዚህ በፊት ሶቬየት ህብረት እና ዩጎዝላቢያ በህገ መንግስታቸው ላይ የራስን እድል በራስ መወስን እስከመገንጠል መብት አስቀምጠው እንደነበር ይታወቃል፤ ነገር ግን ሀገራቱ ከሶሻሊዝም መውደቅ ጋር ተያይዞ ሲፈራርሱ ይሄ አንቀፅ እንዲቀር ተደርጓል። በጣም አዲስ የሚሆነው እስካሁን ስሟን በቅቱ ሰምተናት የማናውቅ ሴንት ኪትስ እና ኔቪስ የምትባል የሁለት ደሴት ጥምር ሃገርም እንደዚሁ አንዷ ደሴት መገንጠል ከፈለገች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መገንጠል እንደምትችል በህግ መንግስቷ ላይ ማስቀመጧን አስፍሯል። የሚገርመው ደግሞ የአንዷ ደሴት ገዥው ፓርቲና ተቋሚው ፓርቲ ለሴቷን ለመገንጠል በደሴቷ ፓርላማ ላይ ተስማምተው የነበረ ቢሆንም ህዝቡ በተሰጠው ሪፈረንደም ግን በአንድነት ለመኖር ፍላጎት በማሳየቱ የመገንጠሉ ጉዳይ በዚያው ቀርቷል፤ በሌላ ሁኔታ ደግሞ በህገ መንግስታቸው ላይ የመገንጠልን መብት ማያሰፍሩም፤ አንድ ህዝብ ወይም አከባቢ የመገንጠል ሀሳብ ካነሳ እንደ አንድ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ተወስዶ ሪፈረንደም የሚሰጥበት ሁኔታ እንዳለ ከልምድ ወይም ከታሪክ የምናየው ነገር ነው። ኖርዋይ ከስዊዲን የተገነጠለችው በዚሁ ሁኔታ ነው፤ ሌሎችም አሉ። የካናዳዋ ኩቤክ ግዛትና የታላቋ ብሪቴን እስኮትላድ ሪፈረንደምም ማየት ይቻላል፤ በእነዚህ ሁለት ግዛቶች ህዝቡ እንዲገነጠል ወይም አብሮ እንዲኖር ሪፈረንደም ተስጥቶት በሁለቱም ቦታዎች ህዝቡ አብሮ መኖሩ መርጦ መገንለጠሉን ውድቅ አድርጎታል።

ነገር ግን ገለልተኛ የሆኑ መንግስታዊ ተቋማት በሌሉበት፤ ህዝቡም በነፃነት መወሰን በማይችልበት እንደኛው ዓይነት ሀገር ለአንድ ህዝብ ሪፈረንደም ቢሰጥ የፖለቲካ ልሂቃኑ የሚፈልጉት ነገር ይፈፀማል እንጂ የህዝቡን ይሁንታ በትክክል ለማወቅ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። ውብሸት ስለዚህ ጉዳይ ሲያትት “አምባገነኖች ፈላጭ ቆራጮችም ሕዝበ ውሳኔን እንዲከናወን ያደርጋሉ። ሕዝበ ውሳኔን አይፈሩትም፤ ይልቁንም ይደፍሩታል። ህዝብን መድፈር የተለማመደ ህዝብን እንዳሻው በማድረግ የሚገዛ መሪ የሕዝበ ውሳኔን ውጤት ምን ማድረግ እንዳለበትና ምን እንደሚሆን ቀድሞ ይወስንና ሕዝቡ ድምፅ እንዲሰጥ ያደርጋል። የህዝብ ድምፅ የፈጣሪ ድምፅ ነው የሚለውን አባባል ቀይረው የቄሳሩ ድምፅ የህዝቡ ድምፅ ነው ይሉታል። የፕሬዝደንቱ ወይንም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይንም የገዥው ፓርቲ ውሳኔ የህዝቡ ውሳኔ ይሆናል።”

የሆኖ ሆኖ ከዚሁ የመገንጠል ሀሳብ ጋር መኖራችን ካልቀረ ስለምንነቱ፣ ስለአተገባበሩና ስለአጠቃላይ ባህርይ በደንብ አውቆ መቆየቱ ጠቃሚ ነው የሚመስለኝ፤ ለመገንጠልም መገንጠል ለማስቀየትም ስለጉዳዩ በቂ እውቀት ይዞ መገኘት አስፈላጊ ነው።ለዚህ ደግሞ ይሄ የውብሸት መፅሐፍ ጠቃሚ ሆኖ አገኝቸዋለሁ።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>