“ሰማይ ሲደማምን ይወረዛል ገደል ወተት ይሸፍታል እንኳን ሰው ሲበደል፣” የሀገሬ ሰው ብሶቱን በቀረርቶ የሚገልጽበት ስንኝ ነው፡፡
አርበኞች ግንቦት 7 ፊሽካው ተነፍቷል ጦርነቱ ተጀምሯል ብሎ ባወጀ ማግሥት በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ድምጻቸው የተሰማው የግንባሩ ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ ጦርነት ያወጁት ኃይሎች ወደውና ፈቅደው ሳይሆን በወያኔ እብሪትና እምቢተኝት የገቡበት ጦርነት መሆኑን ገልጹ፡፡ከሁለቱም ወገን የሚጠፋው የወንድማማቾች ህይወት በመሆኑ ወደዚህ መንገድ በመግባታችን እናዝናለን፤ ገደልን ብለን የምንፎክርበት ሳይሆን በሚከተለው ጥፋት የምናዝንበት ነው ጦርነት ነው አሉ፡፡ አክለውም ወደማንፈልገው ጦርነት የገፋን ወያኔ ከእብሪቱ ወጥቶ ፈቃደኛ ከሆነ ጦርነቱን የጀመሩት ወገኖች አሁንም ቢሆን ኢትጵያን ለዴሞክራሲዊ ሥርዓት ለሚያበቃ ውይይትና ድርድር ዝግጁ መሆናቸውን ተናገሩ፡፡ ጦርነት መጀመሩን ካወጀ ግንባር መሪ አንዲህ አይነት ቅዱስ የሆነ አነጋገር መስማት ያስደስታል፡ የወያኔ ተቀዋሚ የሆን ሁሉ እንደህ ብናስብ መልካም ይመስለኛል፡፡ አባረህ በለው እያሉ መፎከሩም ሆነ ኮረኔል ማራኪ እያሉ ስክስታ መውረዱ ሲበጅ አላየንም፡፡
በወያኔ በኩል የተደመጠው ግን ጥቂት ሻዕቢያ የላካቸው በሚል ንቀት ደምስሰናቸዋል የሚል ጉልበተኝነት ነው፡፡ ከህሊና የሚመነጭ ሳይሆን ከጡንጫ የሚወጣ ባሩድ ባሩድ የሚሸት አስተውሎት የጎደለው ከትናንት አለመማርን የሚያሳብቅ ቃል ነው የሰማነው፡፡
ደርግ ወያኔዎችን ተራ የመንደር ሽፍቶች እያለ ማናናቁም ሆነ ሳይቃጠል በቅጠል ብሎ ለማጥፋት የመረጠው ወታደራዊ ዘመቻ ውጤት እንዳላስገኘ፣ መድፍ መትረየሱም ሆነታንክ አውሮፕላኑ በስልጣን እንዳላዘለቀው አይተናል፡፡እፍኝ የማይሞሉ ከሚል ማጥላላትና አወደምናቸው ደመሰስናቸው ከሚል ፕሮፓጋንዳ ወጥቶ፡ ጥያቄያቸው ምንድን ነው? ጠመንጃ አንስቶ ዱር ቤቴ ለማለት ያበቃቸው ብሶት ምንድን ነው? ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠቅመው መንገድ የቱ ነው ወዘተ ለማለት ፈቃደኝነትም አስተውሎትም ያልነበራቸው ሰዎች በመጨረሻ ሰአት ጉልበት ሲከዳቸው ለድርድር እጃቸውን ቢሰጡም የሚፈይድ አልሆነምና በእብሪታቸው ራሳቸውን ለስደት ለእስራትና ለሞት ሀገሪቱን ለውድቀት ዳረጓት፡፡
ጠመንጃ አንግበው ዱር ቤቴ ያሉ ወገኖቸን አላማ በወታደራዊ ኃይል ማጥፋት እንደማይቻል ወያኔዎች ከራሳቸው በተማሩ ነበር፡፡ ነገር ግን በሥልጣን ጥማት ታውረው እንኳን ከትናንት ከዛሬም የማይማሩ በመሆናቸው ዱር ቤት ከማለት አልፈው ፊሽካው ተነፍቷል ጦርነቱ ተጀምሯል ላሉ ወጎኖች የተለያየ ስም መስጠትና ጥቂቶች ናቸው ብሎ ማናንቅ፤ ደመስሰናቸዋል እያሉ መፎከር ገጠር ከተማ ሳይሉ ወጣቶችን የተለያየ ስም እየሰጡ ማሰርን ነው የተያያዙት፡፡
አሜሪካዊው ኤድመንድ በርክ የተናገሩት ተብሎ አንደሚጠቀሰሰው «መላው የሰው ልጅ ጥቅምና ደስታ ሁሉም መልካም ተግባር የተመሰረተው በፖለቲካ መቻቻልና አቅምን በማሸጋሸግ ድርጊት ነው»፡፡ስለሆነም ዜጎችን ዱር ቤት ለማለት የሚያበቁ ምክንያቶችን በፖለቲካ መቻቻልና በብሄራዊ መግባባት ለማስቀረት መጣር ለራስም ለሀገርና ለህዝብም የሚጠቅም ውጤት ያስገኛል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ እኛም ዱር ውሎ ማደሩን፣ዝናር መታጠቅ ጠብ መንጃ ማንገብና ቃታ መሳቡን እናውቅበታለን የሚል ደረጃ ከተደረሰ ደግሞ እያናናቁ፣ የተለያየ ስም እየሰጡና እየወነጀሉ ፕሮፓጋንዳ መስራት፣ወይም እንጨፍልቃቸዋልን እያሉ ጦር ማዝመት በሥልጣን ሊያሰነብት አለመቻሉን ወያኔ ራሱ ከመጣበት ሂደት መረዳት በቻለ ነበር፡፡ ነገር ግን ሲረገጡና ሲረግጡ አእምሮ እኩል ስለማያስብ ወያኔ ከደረግ ሽንፈት መማር አልቻለም፡፡
ወያኔን በፋኖነቱም ሆነ በመንግስትነቱ እንዳወቅነው ለሥልጣኑ ሲል ሀገር ቢፈርስ ሕዝብ ቢጨራረስ ደንታ የሌለው መሆኑ እንጂ ለሀገርና ለሕዝብ የሚያሰብ ቢሆን ጦርነቱ ከመባባሱ በፊት የሰላም በሮችን በመክፈት ነገሮች ሁሉ በውይይት በፖለቲካ መቻቻልና አቋምን በማሸጋሸግ ዴሞክራሲያዊ አግባብ መስመር እንዲይዙ ቢያደርግ ለራሱም ይበጀው ነበር፡፡
ጦርነት ከተባባሰና የሰው እልቂትና የሀገር ሀብት ውድመት ከነገሰ በኋላ ለማደራደርም ሆነ እጅ ለመጠምዘዝ ላይ ታች የሚሉ መንግሥታትና ተቋማትም የተጀመረው ጦርነት የሁለቱንም ወገን አቅም ወደሚፈትሽበት ደረጃ ከመደረሱ በፊት ዛሬ አሁን ቢያስቡበት ነው የተሻለ የሚሆነው፡፡ ነገሮች በገፉና በተካረሩ ቁጥር ዱር ቤቴ ያለው ወገን አቅሙን እየፈተሸ ጉልበቱን እያጠነከረ በራስ መተማመኑን እያዳበረ ስለሚመጣ በአንጻሩ ስልጣን ላይ ያለው ሀይል የሚወስዳው የጥፋት ርምጃዎች ይቅር ወደማይባል ደረጃ ስለሚደርስ ለድርድር መቀመጥ ቢቻል አንኳን ተዋጊው ኃይል የሚያቀርባቸው ቅድመ ሁኔታዎችና የሚያነሳቸው ጥያቄዎች የደደሩ ይሆናሉ፡፡
ጦርነት ሰው አይመርጥም የፖለተካ አሰላለፍ የብሄረሰብ ማንነት የሀይማኖት ምንነት ሳይለይ ሁሉንም ነው ተጠቂ የሚያደርገው፡፡ ጦርነቱ በሚካሄድበት አካባቢ እየኖሩ የኢህአዴግ አባልና ደጋፊ በመሆን መዳን ተቀዋሚ በመሆን ማመለጥ የዳር ተመልካች በመሆን መትረፍ አይኖርም፡ስለሆነም በተለይ የጦርነቱ መቀጠል ወይንም መቆም መፍትሄ በእጁ የሆነው ወያኔ አባላት የደርግና ወያኔን ጦርነት አጀማመርና እድገት ሂደትና ውጤት ቆም ብላችሁ አስቡና ለራሳችሁ ስትሉ መሪዎቻችሁ ከእብሪት መንገድ ወጥተው ወደ ሰላም መንገድ እንዲያመሩ ጠይቁ፡፡
እዚህ በሀገር ቤት በሞቀ ጎጆአችሁ እየኖራችሁ ሌሎችም አውሮፓና አሜሪካ እየተንደላቀቃችሁ፤እስረው ግደለው ደምስሰው ወዘተ የምትሉ የወያኔ ደጋፊ ነን ባዮችም ለሀገርና ለሕዝብ ደንታ ባይኖራችሁም አድራጎታችሁ እንደግፈዋለን ለምትሉት ወያኔ እንደማይጠቅም በግዜ ብትገነዘቡ መልካም ነው፡፡
ዛሬ ትናንት አይደለም፤ በሕዝብ ላይ እልቂት በሀገር ላይ ውድመት አድርሶ ተደብቆ መኖር ከህግ አምልጦ ማደር አይቻልም፡፡ ነገር ግን ወያኔ እስከ ዛሬ ያደረሰው ጥፋት ከበቂ በላይ ቢሆንም፤ጥፋቱ እያባነነው የሕዝብ ደም እያቃዠው ዛሬም በጥፋት ላይ ጥፋት እየጨመረ ነው፡፡ አስተሳሰባቸው እንደ ጋሪ ፈረስ የተቀየደ ደጋፊዎቹም ሆታና ጫጫታ የቁልቁለቱን መንገድ እያፈጠነለት ነው፡፡ በዚህ ከቀጠለ ጠፍቶ እንዳያጠፋን ያሰጋል፡፡
ኢትዮጵያ በመላው አለም ተበትነው ለየሚኖሩበት ሀገር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ያሉ እውቀትም ልምድም እድሜም የጠገቡ በረካታ አንቱ የተባሉ ልጆች አሏት፤እነዚህም ወገኖች በዚህ ወቅት የዳር ተመልካች ሊሆኑ አይገባም፡፡ ውድ ህይወታቸውን መስዋእት ለማድረግ በጦር ግንባር የተሰለፉ ልጆቿ ከሚያደርጉት የነጻነት ትል ጎን ለጎን ጥፋቱ ሳይበረታ ወያኔ ለድርድር አንዲንበረከክ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በያለበት በግል፤ በጋራና በተደራጀ ሁኔታ የሚችለውን ቢያደርግ ነው መልካም የሚሆነው፡፡ ዛሬ ምንም አንዳልያዩና እንዳልሰሙ ሆነው አድፍጠው የሚያዩትንና ኋላ እልቂት ሲባባስ ተደራደሩ ማእቀብ እንጥላለን፤አለም አቀፍ ፍርድ ቤት እናቀርባለን ወዘተ ለማለት የማይመለሱትን መንግሥታትና አለም አቀፍ ድርጅቶችም ማንቃት ማሳስብ ያስፈልጋል፡፡የወያኔ አባላትና ደጋፊዎችም ከጭፍን ሆይ ሆያታ ወጥታችሁ የድርጅታችሁ መሪዎች ለድርድር ፈቃደኛ እንዲሆኑ ማሳሰብ መጠየቅ ብሎም ማስገደድ ብትችሉ ለድርጅታችሁም ለመሪዎቻችሁም ለእናንተም ይጠቅማል፡፡ ለሰላም የሚደረግ ጥረት ውጤት የሚያስገኘው አቅም ከመፈተሹ በፊት ሲሆን ነው፡፡ለማይቀር ውድቀት አወዳደቅን ማሳመር ብልሀትም እውቀትም ነው፡፡