Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የሰላም ትግሉ በኢትዮጵያ (ክፍል ፬) –አንዱዓለም ተፈራ

$
0
0

አንዱዓለም ተፈራ/ የእስከመቼ አዘጋጅ

አርብ፤ ሐምሌ ፲ ቀን፤ ፳ ፻ ፯ ዓመተ ምህረት ( 7/17/2015 )

አሁን ካለንበት ወደፊት ለመሄድ ከየት እንጀምር? ( የመጀመሪያው ጉዳይ )

አሁን ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለችበት የፖለቲካ ሀቅና የታጋዩ ክፍል በቆመበት መሬት፤ በር የሚያንኳኳና ደረስኩ የሚል ጥሪ መጥቷል። ትግሉን አብረን ማድረግ አለብን! እያለ። በያለንበት እንተባበር! እያለ። መቼም ይሄን የማይል ሕይወት የለም። ሁላችን እንፈልገዋለን። ሁላችን ትክክለኛና መሆን ያለበት ግዴታ ነው እንላለን። ሌላ አማራጭ እንደሌለ እናምናለን። ታዲያ ከየት እንጀምር? በክፍል አንድ፤ በአሁኑ ሰዓት የሰላማዊ ትግሉ በኢትዮጵያ ምን እንደሆነ ገልጫለሁ። በክፍል ሁለት ደግሞ፤ ስለሰላማዊ ትግሉ ያለንን ግንዛቤ አሳይቻለሁ። በክፍል ሶስት፤ ከዚህ ቀደም የሰላማዊ ትግል ካካሄያዱ ሌሎች ሀገሮች የምንማረውን ዘርዝሬያለሁ። በዚህ በአራተኛው ክፍል፤ ሶስት ጉዳዮች ያሉት ዘገባ አለኝ። የመጀመሪያው ጉዳይ፣ አሁን ካለንበት ወደፊት ለመሄድ ከየት እንጀምር? የሚለውን ራሱን በመመርመር፤ አጠቃላይ ሂደቱን እነድፋለሁ። ተከታትለው በሚወጡት የሁለተኛውና የሶስተኛው ጉዳዮች፤ በተጨባጭ በዝርዝር ማድረግ ያለብንን እዘረዝራለሁ።

ወደፊት ለመሄድ፤ መጀመሪያ ያለንበትን የፖለቲካ ሀቅ በትክክል ማወቅ፤ ግድ ይላል። ያለንበትን በትክክል ማወቁ፤ ለምናደርገው ጉዞ ትክል ማጠንጠኛው ነው። ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ከባርነት ለመውጣት የሚያደርገው የነፃነት ትግል ነው። ታጋዩም መሪውም ሕዝቡ ነው። ለዚህ የምንስማማባቸውን አስፍረን፣ ማድረግ ያለብንን ለይተን አቅርበን፣ የነገዋን ኢትዮጵያ ሕያውነት ገሀድ የማድረጉ ኃላፊነት የኛ ነው።

ለሁሉም እስኪ በመጀመሪያ የምንስማማባቸውን መሠረታዊ የሆኑ ዋና ሀገራዊ ሀቆች ላስፍር፤

፩ኛ.      በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ገዢ፤ እንደ ኢትዮጵያዊ ሳይሆን፤ እንደ ጠላት ወራሪ የሚገዛ ቡድን ነው፤ እናም ይህ መንግሥት መወገድ አለበት። ይህ መንግሥት ሕገወጥ ነው። ይህ መንግሥት አድሎዓዊ ነው። ይህ መንግሥት አምባገነን ነው። ሀገራችንን ወደ አደገኛ አዘቅት እየወሰዳት ነው። አስተዳደሩ በሙስናና በዘረኝነት የተወጠረ ነው። ረሃብና ድህነት እንደ ጥላ አብረውን የሚጓዙ ወዳጆቻችን በሆኑበት ሀቅ፣ ስደትና ከሀገር የነፍስ አውጭኝ ሩጫ በነገሡበት ሀቅ፣ ጥቂቶች ከምርጥ ዘር የመጡ ሁሉን በሚቆጣጠሩበት ሀቅ፣ ወጣቱ በሱሰኛ እጽዋት በተመረዘበትና ሥራ ባጣበት ሀቅ፣ ኢትዮጵያዊ መንግሥት አለ ብሎ መናገር፤ የሀገርን ትርጉም አላዋቂነትን ያሳያል። እናም ይሄን ለምናውቅ፤ ይህ መንግሥት መወገድ አለበት።

፪ኛ.      ይህ መንግሥት መወገድ ያለበት፤ በጠቅላላ በሕዝቡ ተሳታፊነት በተካሄደ ትግል ብቻ ነው። ሕዝቡ የድሉ ባለቤት የሚሆነው፤ ሕዝቡ በሙሉ “የኔ” ብሎ በአንድነት፣ ሀገራዊ ነፃነትን ባነገበ አንድ ድርጅት ሥር ታግሎ፤ ነፃ ሲሆን ብቻ ነው። ሀገራዊ ነፃነት፤ በሕዝቡ አንድነት ብቻ እንጂ፤ በድርጅቶች ጋጋት አይካሄድም። እናም በምንችለው ሁሉ ጥረታችን መሆን ያለበት፤ ይሄን የሕዝቡን በአንድነት የትግል መነሳሳት እውን ማድረግ ነው። በጭፍን ይሄን መንግሥት እንጣል ብቻ ማለት፤ የአንድነት ሀገራዊ ትግልን ባህሪይ አለመረዳትን ያሳያል። እናም ሕዝባዊ ትግሉ በአንድ ድርጅት ሥር መካሄዱ የግድ ነው። ሕዝቡን ተክቶ የሚታገል ፓርቲ የለም። በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከመጠቀው የተማረው ወጣት አንስቶ፤ በቁጥር በብዙ ሚሊዮን እጥፍ ከሚበልጡትና የቴክኖሎጂን ጭላንጭል ሊያዩ ቀርቶ፤ የዕለት ምግባቸውን ከየት እንደሚያገኙ እስከ ጣጠራቸው የገጠር ዘመዶቻችን ድረስ፤ የዚህ ትግል ባለጉዳዮች ነን። ይሄን በተስተካከለ መንገድ እንዲሄድ ማድረግ እንችላለን። ዕውቀቱ፣ ልምዱና ችሎታው አለን። እያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊ ነን የምንል ሁሉ፤ የዚህ ትግል ባለጉዳዮች ነን። ጥረት ማድረግ አለብን። በሌሎች ጫንቃ ላይ ልንንጠላጠል፣ ወይንም ሌሎችን አዝለን የድሉን ፍሬ ልንበላ አንችልም።

፫ኛ.      የሚቀጥለው መንግሥት ሲመሠረት፤ ሁሉን አቀፍና ጊዜያዊ መሆን አለበት። ላንዴም ለመጨረሻ ጊዜም ከጦርነት እሽክርክሪት ወጥተን፣ ኢትዮጵያዊ የሆነ መንግሥት እንዲኖረን፤ ከድል በኋላ መቋቋም ያለበት፤ የሽግግር መንግሥት ነው። ይህ የሽግግር መንግሥት፤ በትግሉ ላይ ከተሰማሩት የተውጣጣ ሆኖ፤ የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት፤ ሁሉን አቀፍ በሆነ መንገድ፤ ከሕዝቡ በትክክል በመሰብሰብ፤ ያዘጋጅና ያቀርባል። በዚህ ወቅት ብዙ ሌሎች ጉዳዮች ይከናወናሉ። በተወሰነ ጊዜ የሚካሄድ የዴሞክራሲያዊ ምርጫ ያዘጋጃል። ትክክለኛ ምርጫ ያካሂዳል። ለተመረጠው ክፍል ሥልጣኑን ያስረክባል።

እንግዲህ ይህ አሁን ላለንበት የትግል ሁኔታ፤ በሀራችን ላይ ያለና መሠረታዊ የሆነ፤ ሁላችን የምንስማማበት፤ የፖለቲካ ግንዛቤ ነው። እዚህ ላይ ልዩነት ካለ፤ ወደፊት መቀጠል አይቻልም። የትግሉ ባለቤት ከሆነው፤ ከሕዝቡ ጋር፤ እየታገለ ካለውና ለወደፊት ከሚቀላቀለው ጋር አብሮ ተደራጅቶ ለትግል መሰለፍ፤ ግዴታ ነው። ለየግላችን ድርጅት ፈጥረን፣ በራሳችን ድርጅት ሥር ብቻ በመሰባሰብና፣ ከሌሎች በየራሳቸው ድርጅቶች ከተሰባሰቡት ጋር በመተባበር ለመታገል መሞከር፤ መሠረታዊ የሆነውን የሀገር ጉዳይ፤ ከድርጅት በታች አድርጎ ማስቀመጥ ነው። በርግጥ በሁሉም ጉዳዮች ላይ፤ በግለስብም ሆነ በቡድን፤ አንድ አቋም ሊኖረንና ልንስማማ አንችልም። በዚህ ምንም ዓይነት ብዥታ ሊኖረን አይገባም። ሀገራችንን ከወገንተኛው አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ነፃ ለማውጣት፤ መታገያችን በሆኑ መሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ግን፤ የግድ መስማማት አለብን። መሠረታዊ የሆኑት መታገያ ሀገራዊ ጉዳዮቻችን ምንድን ናቸው? መሠረታዊ የሆኑት መታገያ ሀገራዊ ጉዳዮቻችን፤ ከላይ በቁጥር ፩፣ ፪ትና ፫ ከሰፈሩትና ከምንስማማባቸው የፖለቲካ ሀቆች ይመነጫሉ።

፩ኛ.      በኢትዮጵያ ሀገራችን፤ ኢትዮጵያዊነታችንን አምነን የምንገኝ ኢትዮጵያዊያን፤ በዚሁ በኢትዮጵያዊነታችን፤ አንድነታችንን እናንጠብቃለን። ኢትዮጵያዊያን አንድ ነን። በማንኛውም መንገድ ኢትዮጵያዊ ሆነን ስንገኝ፤ ያ ኢትዮጵያዊነታችን አንድና አንድ ብቻ መሆኑን እናስከብራለን። የተለየ ቦታ ያለው ኢትዮጵያዊነት አይኖርም።

፪ኛ.      የሀገራችን የኢትዮጵያን ዳር ድንበር አስከብረን፤ በግዛቷ ስፋት ውስጥ፤ ሁሉም መሬቷ ለኢትዮጵያዊያን እንዲውል አድርገን፣ አንድነቷን እንጠብቃለን።

፫ኛ.      እያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን፤ በሀገራችን የፖለቲካ ጉዳይ ስንሳተፍ፤ በግል ኢትዮጵያዊነታችን ላይ ከመነጨ መብት ነው። የያንዳንዳችን የግለሰብ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲያዊ መብትን፤ ያለማዛነፍ እናከብራለን።

፬ኛ.      በሀገራችን በኢትዮጵያ፤ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን እናደርጋለን። በሕግ ፊት የበላይና የበታች አይኖርም። ሁሉም ኢትዮጵያዊ፤ በሕግ ፊት እኩል እንዲሆን እናደርጋለን።

፭ኛ.      የኢትዮጵያ ሕዝብ ሉዓላዊነትን እናስከብራለን። ምን ጊዜም ቢሆን፤ በኢትዮጵያ ውስጥ፤ ሕዝቡ የመንግሥቱ ባለቤት እንጂ፤ መንግሥቱ የሕዝቡ ባለቤት የሚሆንበት ክስተት ያቆማል። የሕዝቡን የበላይነት እናከብራለን።

ከላይ የተዘረዘሩት አምስቱ መታገያ ሀገራዊ ዕሴቶቻችን ናቸው። እኒህ ግድግዳና ማገር ሆነው፤ ቤቱን የሚሸከሙ ናቸው። ጣራው ከላይ ይደረባል። ምርጉና ልሰናው ይከተላል። በነዚህ ዕሴቶቻችን ላይ መጨመር ይቻላል። ተጨማሪዎቹ ግን፤ ጊዜን ጠብቀው፤ ለነዚህ አምስት ዋና መታገያ ዕሴቶቻችን ተገዝተው ሲቀርቡ ነው ተቀባይነት የሚኖራቸው።

እንግዲህ እንደዚህ የተበታተነ ትግል በያዝንበት ወቅት፤ ለስምምነቱም ሆነ ለመለያየቱ መድረካችን አደባባዩ ሆኗል። በሚስጥርና በጓዳ የሚደረግ ስምምነትም ሆነ ልዩነት፤ አድሮ የራሱ አዛባ እየጠፈጠፈ፤ ብትንትናችንን ያወጣዋል። እናም ባደባባይ ይሁን መስማማታችን። ለሕዝብ የሚደረግ የሕዝብ ጉዳይ፤ ግልጽነት ግዴታው ነው። ከማን ይደበቃል። በማን ጀርባ ይንሾካሾካሉ? አይቻልም።

ትግሉ ተደራጅተው ለሚታገሉት ብቻ የተሠጠ፤ የግል ኃላፊነታቸው አይደለም። ይህ ሀገራዊ ትግላችን፤ “እኔ ስላልተደራጀሁ አያገባኝም!” ወይንም “ተጠያቂ አልሆንበትም!” ብዬ ላመልጠው አልችልም። ኢትዮጵያዊነቴን ካልካድኩ በስተቀር! እናም፤ ግለሰብ እና በድርጅት ያሉ የድርጅት አባላት እኩል ተጠያቂነት አለብን። ስለዚህ ጥረቱ ከሁላችን መሆን አለበት። ራስን ነፃ ለማውጣት፤ “ድርጅቶች እኮ አይረቡም!” “እነሱ መድረኩን አጣበው ይዘውታል!” እና ሌሎች ይኼን የመሳሰሉ ማምለጫ አባባሎች ተበልተዋል። አይሠሩም። መታገል ያለባት መሆኗን የተረዳች እህት፤ በግለሰብ ያለባትን ኃላፊነት ለመወጣት፤ ማድረግ ያለባትን የምትወስነው ራሷ እንጂ፤ ያሉ ወይንም የሌሉ ድርጅቶች አይደሉም። የድርጅቶች መኖር ወይንም አለመኖር፤ የአንድን ግለሰብ የትግል ፍላጎት፤ አያስሩም። ካልወደዳቸው፤ ሌላ መንገድ እንዲፈልግ ያስገድዱታል።

በተጨማሪም፤ ሌሎቹ አይረቡም በማለት የሚቀርበው ያለመስማማት መንገድ የትም አያደርስም። የኢትዮጵያን ሕዝብ ባንድ አቆራኝቶ ለማታገል የተነሳ ድርጅት ሆነ ግለሰብ፤ “ይሄ አንዲያ ነው!” ወይንም “ያቺ አንዲህ ነች!” “ያ ድርጅት እንዲያ ነው!” ወይንም “እነሱኮ . . .!”  በማለት ላለመተባበር ማምለጫ ማበጀት፤ ኃላፊነት የጎደለው አካሄያድ ነው። ደግሞስ ለምን በሁሉ ነገር ከሚስማሙን ጋር ብቻ እንሠራለን ብለን እንነሳለን? ይሄ እኮ የሀገር ጉዳይ ነው!  እንኳንስ በትግሉ የተሰማሩት ቀርቶ፤ ገና የገዠው ክፍል አባላት፤ ትግሉ ሲግልና መፈርጠጥ ሲጀምሩ፤ አቅፈን ከጉያችን እናሰልፋቸዋለን። የያዝነው ሀገራዊ ትግል ነው! ቁርሾ መወጫ ጨዋታ አይደለም።

ሰሞኑን በግብታዊነት ድርጅቶችን ለማስተባበር ጀምሬ ነበር። በርግጥ ትልቁ ስህተት ከኔ ነበር። ወደፊት እንዳሰብኩት አልሄደም። ከዚህ ጠቃሚ ተመክሮ ወስጃለሁ። በሂደቱ ብዙ ታጋዮች ድጋፍ አድርገውልኝ፤ እንዴት ሊተባበሩኝ እንደሚችሉ ሃሳብ ሠጥተውኛል። አብረውኝ ቆመዋል። አብረን ወደፊት እንሄዳለን። በጣም አመሰግናቸዋለሁ። የጊዜውን አጣዳፊነት፣ የአደጋዉን አስጊነትና የሁኔታውን አመቺነት ብቻ አንግቤ፤ ከእውነታው ይልቅ ፍላጎቴን አስቀድሜ ያደረግሁት ሩጫ፤ ፍሬ ሳይይዝ ቀረ። አምናለሁ፤ ይህ በአንድነት ተሳባስበን የመታገሉ ግዴታ፤ አብሮን አለ። የትል አልሄደም፤ አይሄድምም። ከኔ በፊት ሌሎች ጥረውበታል። አሁንም ሌሎች በሚችሉት እየጣሩ ነው። ጊዜ ይወስዳል። በትግሉ ብዙ የቆዩ አሉ። በትግሉ ብዙ የተማሩ አሉ። በትግሉ በተለያየ መንገድ፤ የተለያየ ግብ ይዘው የቀረቡ አሉ። እናም እኒህን ሁሉ በአንድ ማሰባሰቡ ቀላል አይደለም። ከተጨባጩ የሀገራችን የፖለቲካ ሀቅ በላይ፤ አስቸጋሪና ተጎታች የሚሆነው፤ በትግሉ ዙሪያ ያሉትን ወደ አንድ እንዲመጡ መለማመጡ፣ ማባበሉ፣ ማንቆለጳጰሱ፣ ማስጎምጀቱ፣ ማጓጓቱና መጎተቱ ነው። ከዚህ በተሻለ መንገድ አሁንም ሳላርፍ እቀጥላለሁ።

በተለያዩ ታጋይ ድርጅቶች ሥር ያሉት አባላት መረዳት ያለባቸው፤ በድርጅታቸው ሥር ያከናወኑት ሁሉ፤ እያንዳንዱ ድርጅት የፈጸመው በጎ ተግባር፣ ያከናወናቸው ትክክለኛ ጀብዱዎች፣ ጉድለት የታየባቸው ተመክሮዎችና በትግሉ የተሰዉ ጓዶቻቸው፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነት ያደረጉት ስለሆነ፤ የየግል ድርጅቶች ታሪክ ሳይሆን የመላ ኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል አካል በመሆኑ፤ የየድርጅቶቻቸው ስም ቢቀየር፣ ድርጅቶቹ ቢፈርሱ፤ ይህ ታሪክ ቋሚ ሆኖ ይኖራል። እናም በአንድ እንሰለፍ ስንል፤ ይሄን ታሪክ ወደ አንድ አጠቃለን እናመጣዋለን እንጂ፤ ማንም ሊሠርዘው አይችልም። ትግሉ አንድ ነው። የኢትዮጵያዊያን የነፃነት ትግል ነው። አሁን የያዝነው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግልና ታሪክ እንጂ፤ የድርጅቶች ትግል ወይም የድርጅቶች ታሪክ አይደለም። ከወራሪው የፋሽስቱ ጣልያን ጋር ተጋፍጠው የተሰለፉትን አርበኞቻችን፤ በአብቹ ተሰለፉ በበላይ ዘለቀ፤ አርበኞቻችን ብለን እናነሳቸዋለን እንጂ፤ የአብቹ አርበኞች ወይንም የበላይ ዘለቀ አርበኞች አንላቸውም። አሁን ያሉት ድርጅቶች መሠረታቸው፤ የአባሎቻቸው ቁጥር ብዛት፣ ያላቸው ታሪክ፣ ያካበቱት ንብረት ወይንም የመሪዎቻቸው ማንነት ሳይሆን፤ መርኀ-ግብራቸውና ርዕዩተዓለማቸው ነው። ያ ደግሞ ትርጉም የሚኖረው፤ ሕዝቡ የመምረጥ መብት ኖሮት፤ ከዚህኛው ያኛው ይሻላል ብሎ የሚያማርጥበት ወቅት ሲመጣ ነው።

ሁለተኛውን ጉዳይ በሚቀጥለው ጽሑፌ አቀርባለሁ።

ከታላቅ ምስጋና ጋር

eskemecheeske.meche@yahoo.com  http://nigatu.wordpress.com


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>