ዘረኛውና ፀረ-ሕዝቡ የህወሃት አመራርና የመከላከያ ሠራዊት መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በኃይል አንበርክኮ በባርነት እንዲገዛ ለማድረግ ቀደም ሲል በጫካና ከዚያ ደግሞ ይህ አስተሳሰበ ስንኩልና ጠባብ ጎጠኛ ኃይል የመንግሥት ሥልጣን ከያዘ በኋላ በመቶ ሽህ የሚቆጠሩ ተገድለዋል፤በመቶ ሽህ የሚቆጠሩ በተደራጀ ሴራ እንዲሰደዱ ተደርጓል፤በመቶ ሽህ የሚቆጠሩ በአሸባሪነትና አገር ክህደት ወንጀል ተፈርጀው ወህኒ ቤት ተጥለዋል፤በመቶ ሽህ የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች ተወልደው ካደጉበት ቀያቸው (መንደራቸው) በልማት ስም እንዲፈናቀሉ ተደርጓል፤ሆነ ተብሎ ዘራቸው እንዲጠፋ የሚያመክን መድኃኒት በመርፌና በክኒን መልክ እንዲወስዱ በማስገደድ ዘር እንዳይተኩ ተደርጓል ፤ የሀገር ሀብትና የህዝብ ንብረት ተዘርፎ በባለሥልጣናት የግል ሀብትነት ወደ ውጭ አገር እንዲሸሽ ተደርጓል።ኧረ ምኑ ተቆጥሮ በርእሰ መዲናዋ ከተማ አዲስ አበባ በሽዎች የሚቆጠሩ ታዳጊ ወጣቶች በርሃብ ጠኔ ከትምህርት ገበታ ውጭ ሲሆኑና በሞት አፋፍ ላይ እንዳሉ እየታወቀ ገዥዎቻችን ጀሮ ዳባ ልበስ ብለዋል፤የሌለ የውሸት እድገት እየሰበኩ ሀገሪቱን በብድር ከማትወጣው አዘቅት ውስጥ ከተዋታል።ህወሃት ለተተኪው ትውልድ የሰነቀለት ውርስ።
የገዥው ቡድን አባላት ከላይ እስከ ታች በዝርፊያ ሀብት አካብተው ከበርቴዎች ሲሆኑ ሌላው ኢትዮጵያዊ በቀን አንድ ማእድ እንኳን ለማግኘት እድለኛ መሆንን እየጠየቀ ነው።በአጠቃላይ ከመረን በላይ ጥጋባቸው ልኩን ያለፈ ሲሆን ግልምጫውና ፍጥጫው ከንቱ ድንፋታቸው ቀፎነታቸውን አመላካች ነው።በመናገር የተሸበረ በጹሑፍ የተሸበረ፤የራሱን ሠራዊት በእስረኛነት የያዘ ቡድን አንድ ጠንከር ያለ በትር ቢያርፍበት በአንድ ጀንበር እርስ በርሱ ተባልቶ ነገር አበላሽቶ ቦታውን እንደሚለቅ ብዙ ምልክቶች እየታዩ ነው።እዚህ ላይ ግን አንድ መጠቀስ ያለበት ነገር 1. ህወሃትና የህወሃት እንባ ጠባቂዎች በመጨረሻዋ ሰአት የሚያደርጉትን የአገር ማጥፋት ሴራ እንዴት መመከት ይቻላል? 2.ነፍጥ ያነገበው ኃይል በለስ ቀንቶት የህወሃትን ኃይል ቢያስወግድ ኢትዮጵያን በሰላም በአንድነትና በእኩልነት የሚያስተዳደር መርህ ያለው ይሆናል ወይ? 3. ሁሉም ኃይሎች በአማራው ነገድ ላይ የጥላቻ አመለካከት ያላቸውና ጣታቸውን የቀሰሩ ናቸው።ስለዚህ የዘር ማጥፋቱን ዘመቻ ነዳጅ ይጨምሩበታል ወይንስ ያስቆሙታል የሚለው በታሳቢነት እንዲቆይ መጠቆም ወይም ጠቅሸው ማለፍ እወዳለሁ።
ለህወሃት የመከላከያ ሠራዊት ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ማሳሰቢያዎችን በጹሑፍ መግለጼ ይታወቃል ይህን ሳደርግ ከሜዳ ላይ ተነስቼ አይደለም።የመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ ያለውን የጌታና የአሽከርነት ኑሮ እንዲሁም ስለላውና ውስጥ ያለውን ወከባ ስለማውቀው ነው።ቤተሰቡን የማይጠይቅ፤ከወዳጅ ዘመድ ደስታም ሆነ ሀዘን የተገለለ፤የጫማና ዩኒፎርም ወጭ ከዚያች የማትረባ ደመወዙ እየተቀነሰበት ኑሮ አልገፋህ ያለው መሆኑን ስለምገነዘብ ነው።እስካሁን ባሳለፋቸው ጊዚያቶች ምን እንዳደረገ መከላከያ ሠራዊቱ ራሱን ሊፈትሽ ይገባዋል።ዘመዶቹን ወላጆቹን እህትና ወንድሞቹን እየገደለ፤እያሰረና እያሰቃየ የመጣ መሆኑን ሊረሳው አይገባም።ምናልባት የኢትዮጵያ ሶማሌውን የሚያሰቃይ አንድ ኦሮሞ የመከላከያ ኃይል ሌሎች የክፍሉ ባልደረባዎች ደግሞ በተመሳሳይ ሁኔታ የሱን ቤተሰቦች ኦሮሞውን እያሰቃዩ እንደሚገኙ ሊረሳው አይገባም።በዚህ ላይ ደግሞ በትግራይ(ህወሃት)የመከላከያ ሠራዊት የበላይነት ተቀፍድዶ ተይዞ በዘረኝነት ሰንሰለት ውስጡ ነፍሮ በብሶት እየተንገበገበ እያለ መሣርያውን በህወሃት ጌቶቹ ላይ ሊያነጣጥር ይገባል እንጅ በቤተሰቦቹ ላይ መሆን አልነበረበትም። አሁንም በሕዝብ ላይ ያነጣጠረውን አፈሙዝ ማንሳት አለበት።እርግጠኛ ባልሆንም የተቃዋሚ ኃይሎች የኤርትራን በርሃ ለቀው ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ እንደሆነ ይነገራል ስለዚህ እጅ መስጠትና ወደዚያው መኮብለል የሚቻልበት ሁኔታ እንዳለ ማወቅና ከሕዝብ በመወገን ታሪክ ሠርቶ ማለፍ ከማንኛውም የግል ጥቅምና የህወሃትን ፍርፋሪ አንጋጦ ከመመልከት የበለጠ ነው።ከተራው ጀምሮ እስከ ላይኛው መዋቅር ድረስ ያለው ኃላፊነት የተያዘው ከአንድ ጎሣ(ከትግሬ) መሆኑ ሲታወቅ ቤት ትዳር የያዙ ሀብት ንብረት ያላቸው መሆኑን በግልጽ እየታወቀ ሞትን ከሌላው አካባቢ የተሰባሰበው ነገድ ተወላጅ የሆነው እንዲክፍል ተፈርዶበታል።ሩዋንዳ የሄደው ማን ነው?ወደ ሶማሌ ሄዶ የሞተውና እየሞተ ያለውስ ማን ነው?ወደ ደቡብ ሱዳን የሄደውስ ማን ነው?የሞቱት የሠራዊት አባላት ቤተሰብ ልጆቹ ማለቃቸውን ያውቃል ወይ?በመሠረቱ የመከላከያ ሠራዊቱ ከፖለቲካ ነፃ መሆን አልነበረበትም ወይ?የካድሬውንም ሆነ የአስተዳደር ሥራ ውስጥ ገብቷል ለምን?የደርግ የሠራዊት አባላት ጎዳና ላይ ተጥለው እያየ ይህ ሥርዓት ነገ ትብያ ሲለብስ የሱ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል አያውቅም ወይ?የደርግ ሠራዊት እኮ ለሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት ሲል ጥርሱን ነክሶ የወገቡን ትጥቅ ጠበቅ አድርጎ ታጥቆ ታግሎ ነበር የዓሳ ግማቱ ካናቱ ሆነና አገራችን ከጠልቶቿ እጅ ወደቀች።
ግፉና መከራው ጽዋውን ሞልቶ አልቻልህ ያለው ሕዝብ አሁንስ በቃ! ብሎ የተነሳበት ወቅት አሁን ነው ይሁን እንጅ ማን እንደሚመራውና የት ሊያደርሰው እንደሚችል የሚታወቅ ነገር የለም።የሰላማዊ ትግሉ በር እስከ መጨረሻው ተዘግቷል።በኤርትራ የሚገኙት የተቃዋሚ ኃይሎች አንድ ጣምራ ክንድ እንዲፈጥሩና ሕብረ-ብሄራዊ ድርጅት ሆነው እንዲቀጥሉ ጩኸታችን አሰማን ከበስተጀርባቸው ያለው ሁኔታ ማለትም የሻእብያ እጅ ስለአለበት ወደ አንድነት ሊመጡ አልቻሉም።ከኤርትራ ምድር ለቆ የሽምቅ ውጊያ ጀምሬያለሁ የሚለው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ኃይልም ሌሎች አጋሮቹን አልጨመረም የተናጠል ትግል ደግሞ በሰው ኃይል ማነስ፤በገንዘብና በቁሳቁስ እጥረት ተገቢውን ውጤት ላያመጣ ይችላል።በተለይ የዚህ አይነቱ እንቅስቃሴ ሰፊ የሕዝብ ሥራ መስራትን ስለሚጠይቅ በዚህ ዙርያ ብዙ ድካም ይኖራል።ያለ ሕዝብ ደጀን የሚደረግ እንቅስቃሴ ተንሳፎ ነው የሚቀረው።
አሁን እንቅስቃሴ የሚደረግበት አካባቢ የተመረጠበት ምክንያት ግልጽ ቢሆንም ከዚህ ቀደም ኢዲዩ፤ኢህአፓ፤ህወሃት/ኢህዲን፤አገር ወዳድ የሚባሉ ድርጅቶች ከደርግ ጋር ለ17ዓመታት የዘለቀውን ጦርነት ያካሂዱ የነበረው በዚሁ አካባቢ ነበር።ፍሽስቱ የህወሃት ቡድን በለስ ቀንቶት ሥልጣን ሲይዝ ሌሎች ከስረው ወጥተዋል።ሕዝቡ ግን ሞት እሥራት፤ እናት አባት ጧሪ ልጆቻቸውን፤ሚስት ባሏን፤ልጅ አባቱን አጥቶ መሬቱ በጥይትና በቦንብ ታርሶ ለሙ መሬት ደግሞ ለሱዳን በስጦታ ተለግሶ በድህነት እንዲኖር የተፈረደበት ሕዝብ ነው።ይህ ሁሉ ሲሆን ከሕብረተሰቡ ውስጥ እሾማለሁ እሸለማለሁ ያሉና የግል ሙገሳና ዝና ለማግኘት አባሪና ተባባሪ የሆኑ ፤በአዲስ ከመጣው ጋር ሁሉ የተሰለፉ ታሪክ የማይረሳው ጠባሳ ጥለው አልፈዋል።አሁንም የዚህ አካባቢ ሊጠነቀቅና ከዚህ ቀደም ከተፈፀሙ ስህተቶች ተምሮ ሊታቀብ ይገባዋል።
ይህ ሲባል የህወሃትን ሥርዓት አትታገሉ ማለት አይደለም የታመመን ማስታመም፤የቆሰለን እስኪያገግም መተባበር፤ስንቅ ሲያልቅ ስንቅ ማቀበል፤መደናገር ሲፈጠር መንገድ መምራትና አቋራጮቹን ማሳየት፤ታጋይ ሲሞት መቅበር፤የታጋዩ ክንድ ሲዝል በግል ብረቱ በራሱ የጎበዝ አለቃ እየተመራ ሽፋን መስጠትና ጠላትን (የህወሃትን ኃይል) ማንበርከክ ተገቢ ይሆናል። ህወሃት ምህረት ሊደረግለት የማይገባ በዓለማችን ከነበሩት ፋሽስቶች የከፋ በራሱ በኢትዮጵያዊ ዜጎች ላይ የፈፀመ አረመኔ በመሆኑ አይቀጡ ቅጣት ያስፈልገዋል ።